Monday, June 17, 2013

ተስፋ

እግዚአብሔር አምላክ የሰው ልጅ ተረጋግቶና በሰላም ይኖር ዘንድ ከሰጠው ስጦታ መካከል አንዱና ዋነኛው ተስፋ ነው። ከ22ቱ ፍጥረታት መካከል በተስፋ የሚኖር የሰው ልጅ ነው። ሰው በተስፋ የማይኖር ከሆነ ባዶ፣ ተቅበዝባዥና በጭንቀት የሚኖር ብሎም ራሱን ወደ መጥላትና ማጥፋት የሚጓዝ ግደለሽ ይሆናል።
ተስፋ ማለት በየዕለቱ ሊገጥሙን ለሚችሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች መፍትሔ፣ ለሃዘናችን መጽናኛ፣ ለደስታችን ፍሬ በጉጉት የምንጠብቅበት ብቻም ሳይሆን  አስቸጋሪ መስለው ለሚታዩን ነገሮች በጎ ነገርን የምናይበት ረቂቅ የአምላክ ስጦታ ነው። ለዚህም ነው ሰዎች በምክራቸው  "ተስፋችሁ ሕያው፣ ጠንካራ፣ ጽኑና የማይናወጥ መሆን አለበት" የሚሉት። ተስፋ ካለን ብዙ ንገሮች አሉን፤ የምንሄድበት አቅጣጫ፣ የምንንቀሳቀስበት ኃይል፣ ብዙ አማራጮች፣ ሺህ መንገዶችና ሊገመቱ የማይችሉ ህልሞች አሉን። ተስፋ ካለን መሄድ ወደ ምንፈልግበት ቦታ ግማሽ መንገድ ላይ ደርሰናል ማለት ሲሆን ተስፋ ከሌለን ወይም ተስፋ ከቆረጥን ግን ለዘለዓለሙ ጠፍተናል ማለት ነው።

ተስፋ
“ተስፋ” የሚለው ቃል መጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንዲህ ተብራርቷል፦

  • ተስፋ ምኞትና ናፍቆት ብቻ ሳይሆን አለኝታና መተማመን የሚገኝበት ነው (ሮም.15:13)
  • የክርስቲያን ተስፋ በክርስቶስ ትንሣኤ ላይ የተመሠረተ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው (1ጴጥ. 1:3-5)
  • ተስፋ በዚህ ዓለም አይወሰንም (1ቆሮ.15:19)
  • በሚመጣው ዓለም የእግዚአብሔር መንግሥት ተካፋዮች እንድንሆን ለእኛም ለሌሎችም ተስፋ አለን (ኤፌ.1:18፤ 1ተሰ.2:19)
  • ተስፋችን ምንም እንኳን አሁን ባይታይም የተረጋገጠና የማይጠፋ ነው (ዕብ.11:1፤ ሮም 5:5)
  • እግዚአብሔር ስለማይዋሽ ተስፋችን ከንቱ አይሆንም (1ጢሞ.1:1፤ ቲቶ 1:1-2)
  • ተስፋ ከእምነትና ከፍቅር ጋር የተያያዘ ነው (1ቆሮ.13:13)
  • ተስፋ በቅድስና እንድንኖር መከራን እንድንታገስ ያበረታታናል (1ዮሐ.3:3፤ ሮም 8:18)
  • እግዚአብሔር ለሰጠው ተስፋ ተካፋዮች መሆናችንን በመንፈስ ቅዱስ አረጋግጧል (ሮም 8:14-16፤ ኤፌ.1:13-14)
ሆኖም የእግዚአብሔር ተስፋ ፈቃዱን ለሚያደርጉ መሆኑን አውቀን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም መትጋት አለብን።

መንፈሳዊ ተስፋ፦
"አሁንስ ተስፋዬ ማን ነው? እግዚአብሔር አይደለምን? ትዕግሥቴም ከአንተ ዘንድ ነው።" (መዝ 38፥7) በእግዚአብሔር ለሚያምን  ሰው ተስፋው እግዚአብሔር ነው፤ ገነት መንግሥተ ሰማያት ነው። በኑሮውም አይጨነቅም፣ አይረበሽም። እግዚአብሔር መልካሙንና የሚያስፈልገውን ሁሉ በስዓቱና በጊዜው እንደሚሰጠው ያውቃል ይረዳል። ሁሉን ነገር ለአምላኩ ያስረክባል፣ በእግዚአብሔርም እንደሚከናወንለትም ያምናል። ቅዱስ ዳዊት "እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ በርታ፥ ልብህም ይጽና እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።" (መዝ 26፥14) ብሎ ማነን ተስፋ ማድረግ እንዳለብን ስላስተማረን እኛም ዛሬ በጉዟችን፣ በኑሯችንና በሕይወታችን ሁሉ እርሱን ተስፋ በማድረግ ምድራዊ ሰላምና ሰማያዊ ሕይወት ማግኘት እንድንችል መንፈሳዊ ተስፋ ሊኖረን ይገባል።

ሥጋዊ/አለማዊ ተስፋ፦
ይህ አይነቱ ተስፋ ለሥጋችን የሚያስፈልጉ ነገሮችን በብርቱ የምንመኝበት ነው። በዚህ የተስፋ ጉዞ ብዙ ነገሮች ተስፋ ቢስ ሊያደርጉን ይችላሉ። ነገር ግን ጽናትን፣ ብርታትንና ትዕግስትን ገንዘብ ካደረግን ተስፋችንን መመለስ እንችላለን። ምክንያቱም ሰው ካለ ተስፋ ለስዓታት መቆየት አይችልምና። የአደጉ አገሮች እራሳቸውን በማጥፋት የቀዳሚነቱን ቦታ ይዘዋል፤ ለዚህም አይነተኛውና ዋነኛው ምክንያት ተስፋ በመቁረጣቸው ነው፤ ለሰው ልጅ የሚያስፈልገው ሁሉ አላቸው ነገር ግን ተስፋ የሚያደርጉት ነገር የለም። ለእኛ ለታዳጊ አገሮች ግን ብዙ ነገሮች ተስፋ የምናደርጋቸው አሉን። ለምሳሌ፦ በፖለቲካው፣ በማህበራዊውና በኢኮኖሚው ዘርፍ ዘመናዊ ፖለቲካንና ዲሞክራሲን፣ የማህበረሰብ አንድነትንና ፍቅርን እንዲሁም አገራችን በሀብት አድጋ ከበለጸጉ አገሮች ጋር ተወዳድራ የማየት ተስፋ አለን። እነዚህና መሰል ነገሮች በተስፋ እንድንኖር ያደርገናል አድርጎናልም። ልክ ዛሬ እንደምናየው የእግር ኳስ ተስፋ፤ በኳስ በቅርብ ከአለም ጋር እንደምንቀላቀል ሙሉ ተስፋ አለን።
በአጠቃላይ መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ተስፋ ለሕይወታችን መሰረት ነው። ወደ ጥፋትና ኃጢአት ሊመራን የሚችል ተስፋም ስላለ ተስፋ ስለምናደርገው ነገር ቆም ብለን ልናጤነው ይገባል። እግዚአብሔር አምላክ ከኃጢአት በስተቀር ተስፋ የምናደርገውን ነገር በጸጋው ያድለን፡ አሜን!!!

Tuesday, June 11, 2013

የዘንድሮው ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ውሳኔ ተግባር ላይ ከዋለ ለቤተክርስቲያን አስትዋጾው የጎላ ነው


የቅዱሳን ጳጳሳት ተግባር "በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።"(ሐዋ 20:28)  ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተገለጸው የዘንድሮ ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖደስ ጉባኤ ከመነሻው እስከ ፍጻሜው ይኽን የማሳይና የሚያረጋግጥ ነበር።
ጉባኤው ሲጀመር ፓትርያሪኩ ያነሷቸውን ነጥቦች ስንመለከተ ለዚች ቅድስት ቤተክርስቲያን ችግር ለሚያሳስበው ለሚያንገበግበው እውነተኛ የቤተክርስቲያን ልጅ የዘወትር ጥያቄዎች ነበሩ። ዘመን አመጣሹን(ዘረኝነቱን)ና የተለያዩ ችግሮችን ወደኋላ በመተው ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅማትን የመወያያ አጀንዳ አድርገው ጉባኤውን በመጀመራቸው ቅዱስ ፓትርያሪኩን ልናመሰግናቸው ይገባል። እግዚአብሔር በእርሳቸው ላይ አድሮ ቤተ ክርስትያኗ ከአለችበት ከተለያዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሊታደጋት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።
ቅዱስ ፓትርያሪኩ በዋናነት ያነሷቸው ነጥቦች፦
  1.  መንፈሳዊነትን የለቀቁ/ ብልሹ አሠራርን ማረምና ማስወገድ
  2. አስተዳደሩን በአዲስ መልክ ማዋቀር
  3.  የፋይናንስ አያያዝን ማስተካከል
  4. የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን እንደገና ማዋቀር 
እነዚህ 4ቱም ነጥቦች የቤተ ክርስቲያን መሰረታዊና ቤተ ክርስቲያኗን ወደፊት እንዳትጓዝ ያደረጉ ችግሮች ናቸው። የቤተ ክርቲያኗ የበላይ ጠባቂ ጳጳሳት በእነዚህና ሌሎች ጉልህ ችግሮች ላይ መወያየታቸውና ለችግሮች  መፍትሔ የሚሆኑ ዝርዝር ተግባራትን ማስቀመጣቸው የቤተ ክርስትያንን የነገ ጉዞ ያመላክተናል። ምንም እንኳ የቤተ ክርስቲያን ጉዞ የመስቀል ጉዞ ቢሆንም ውስጣዊ ችግሯን ማስወገድ ግን የአባቶቻችን እና የእያንዳንዳችን ተሳትፎ ጉልህ አስትዋጾ አለው።
ጉባኤው ከብዙ ውይይትና ምክክር በኋላ ለቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ ናቸው ብሎ ያመነበትን ውሳኔዎች ወስኖ መግለጫ ስጥቷል። ከውሳኔዎችም መካከል፦
  • በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የሚታዩ ብልሹ የአስተዳደርና የአሰራር ችግሮችን  እንዲሻሻሉ ማድረግ፤ 
  • ጥራት የጎደለውን የፋይናንስ አያያዝን በተገቢው መልኩ ማስተካከል እንዳለበት፤ 
  • ሙስናንና ለብክነት የተጋለጡ/መንፈሳዊነትን የለቀቁ አሰራሮችን ለመቅረፍ ዓብይ ኮሚቴ ማዋቀርና ችግሮች እንዲቀረፉ ማድረግ
  • የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአንድ ሀገረ ስብከት፤ በአንድ የቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እንዲመራ መድረግ 
  • የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ ምርጫ
  • ከሀገር ውጪ ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር የተጀመረው የሰላም ውይይት ጥረት መቀጠል እንዳለበት 
  • በመካከለኛው ምሥራቅና በሌሎች የዓለም ክፍሎች ለሥራ ፍለጋ በሕገ ወጥ መንገድ በሚሄዱ ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰውን ዘግናኝ ድርጊት ለማስቆም በኹኔታው ጎጂነት ላይ ግንዛቤ የሚፈጥር ትምህርት በስፋት እንዲሰጥ ቅ/ሲኖዶስ ለመምህራን፣ ካህናትና ሰባክያን ሁሉ መመሪያ ሰጥቷል
ይህ ውሳኔ  ተግባራዊ ከሆነ ቤተ ክርስቲያናችን ከመቸውም በበለጠ ተጠቃሚ ትሆናለች። አገራችን ኢትዮጵያም በእድገት ወደፊት ትገሰግሳለች። ምክንያቱም 
  1. ዘመን አመጣሹንና የዘመኑ ፖለቲካ ያመጣውን የዘረኝነት መንፈስ አሶግዳ አገራዊ ስሜት ያለውና በህገ እግዚአብሔር የሚመራ ዜጋ መፍጠር ስለምትችል፤
  2. ከሙስና እና አለማዊነት የተላቀቀ የአሰራር መርህ መዘርጋት ስለምትችል፤
  3. ለ21 ዓመታት በአስተዳድር ጉዳይ የተለያዩት አባቶችና በቅዱስ ሲኖዶስ መዋቅር ስር የማይተዳደሩ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ወደ ቀደምት አንድነታቸው መምጣት ስለሚችሉ፤
  4. በተጠቀሱት ችግሮች  ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን የራቁ ምዕመናን ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መመለስና መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን መቀጠል ስለሚችሉ፤ 
  5. ህዝበ ክርስቲያኑ በሙሉ ከሥጋዊ አስተሳሰቦች ርቆ በመንፈሳዊ ሕይወት እየተጋ ለልማትና ለአገር እድገት መሥራት ስለሚችል ቤተ ክርስቲያናችንና አገራችን በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተጠቃሚ ይሆናሉ።

ቅዱስ ሲኖዶስ ቢያስብበት፦

ቅዱስ ሲኖዶስ በውጭ ሀገር በልዩነት ከሚገኙ አባቶች ጋር የሰላም ውይይት መቀጠል እንዳለበት መወሰኑ  ይበል የማሰኝ ነው።  አባት ልጅን ይፈልጋል፤ ኢየሱስ ክርስቶስ 99ኙን ነገደ መላእክት ትቶ አንድ ልጁን አዳምን ፍለጋ ከሰማየ ሰማያት እንደ ወረደ፤ ለሰሚና ለአጠራር በማይመች መልኩ ቤተ ክርስቲያንን ገለልተኛ ብለው ራሳቸውን ያገለሉ ወገኖቻችንን በቅዱስ ሲኖዶስ ስር እንዲተዳደሩ ያለመሰልቸት በተደጋጋሚ የአንድነት ጥሪ ቢያስተላልፍ መልካም ነው።  

በውጭ ለምትገኙ ብፅዕዋን አባቶች፡

ልዩነቱን ትታችሁ፣ ቅዱሳን አባቶቻችን እንዳስተማሩት በትህትና ራሳችሁን ዝቅ አድርጋችሁ፣ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ስትሉ ይህ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሁሉንም የሚያስማማ ስለሆነ ሰላምና አንድነት የምትፈጥሩበትን ሁኔታ አመቻቹልን። እናንተም ከታሪክ ተወቃሽነት ነጻ ትሆናላችሁ እኛም ልጆቻችሁ ከእናንተ ትህትናንና እርቅን በተግባር እንድንማር አድርጉ።

ገለልተኞች፦

ምንም እንኳ ገለልተኛ የሚለው ትርጉም ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጥና የሚመች ባይሆንም አትፍረዱ ይፈረድባችኋል የሚለውን ቃል በማስታውስ እኔም እንደናንተ ከትችት ራሴን አግልዬ፤ 
ለመገለላችሁ እንደ አንድ ምክንያት ስታቀርቡ የነበረው ብልሹ አስተዳደርን ነበር፤ ዛሬ ግን ቅዱስ ሲኖዶስ በዋናነት የአስተዳደር ችግሩን አጀንዳ አድርጎ  ስለተወያየበትና ውሳኔ ስለሰጠበት ተግባራዊ ይሆን ዘንድ የእናንተም አስትዋጾ በእጅጉ ያስፈልጋል። ስለሆነም ቅዱስ ጳውሎስ "ሁሉም በአግባብና  በስርዓት ይሁን" (1ኛ ቆሮ 14:40) ብሎ እንዳስተማረው እናተም መገለሉን ትታችሁ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ትመሩ ዘንድ የታናሽነት መልእክቴን በእግዚአብሔር ስም ማስተላለፍ እወዳለሁ። መገለል ከክፉ ሥራ፣ መገለል ከተንኮል፣ መገለል ከአለማዊነትና መገለል ከኃጢአት እንጂ ከቅዱስ ሲኖዶስ ሊሆን አይገባምና። 

ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስ በመግለጫው ለቤተ ክርስቲያን ክብርና ሉዓላዊነት መጠበቅ፣ ለህልውናዋ መቀጠልና ለዕድገትዋ መስፋፋት የሚቆረቆሩ የቤተ ክርስቲያናችን አገልጋዮችና ምእመናን በሙሉ ቅ/ሲኖዶስ የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎች ለመተግበር አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ በጠየቀው መሰረት ሁላችንም ውሳኔው ተግባር ላይ እንዲውል ርብርብ ልናደርግ ይገባል።

                                        ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

Monday, June 3, 2013

የሰማያዊ ህዝባዊ ሰልፍ ጠቀሜታ




ትናት ግንቦት 25፣2005 ዓም የሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ሰልፍ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የፓርቲው ደጋፊዎችና የገዝውን ፓርቲ አገዛዝ በመቃወም በዋናነት የተለያየ ምክንያት ተፈልጎላቸው በእስር ቤት የሚገኙ የፖለቲካም ሆኑ ሌሎች እስረኞች እንዲፈቱ፣ ዲሞክራሲ በአገራችን ይስፈን፣ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ አይግባ እና ሌሎችንም ችግሮች በማንሳት ድምጻቸውን ሲያሰሙ ውለዋል። ይህንንም የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን እና ድረ ገጾች በስፋት ዘግበውታል።

1, ETV
ኢቲቪ ዜናውን በመዘገቡ ሊመሰገን ይገባል። በዜናው ላይ ያስተላለፉት መልክት የራሱ የሆነ ሌላ ጥያቄ ቢያስነሳም።

2, የኢሳት/ESAT ዘገባ

3, የጀርመን ሬዲዮ ድምጽ እና ሌሎችም ድርህረ ገጾች በስፋት ገልጸውታል።

በአጭሩ የዚህ ህዝባዊ ሰልፍ ጠቀሜታው

1, ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ለመብቱ፣ ለነጻነቱና ለዲሞክራሲ መስፈን ፍራቻን አስወግዶ በአንድነት መጓዝ እንዳለበት አመላካች በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

2, ለገዥው ፓርቲ፦
  • በአዓለም መንግስታት እይታ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
  •  ህዝቡ ምን ያክል እንደተማረረና ጥላቻ እንዳለው እንዲረዳ ያደርገዋል።
  • ህብረተሰቡን የሚጠቅም ስልታዊ እቅድ እንዲነድፍ/ እንዲከተል አቅጣጫ ጠቋሚ በመሆኑ ሰልፉ ለሁሉም ህብረተሰብ ክፍል ጠቀሜታው የላቀ ነው።