Friday, March 15, 2013

መንፈሳዊ ሕይወትና ስደት


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

መንፈሳዊ  ሕይወትና ስደት


የዚህ አጭር ጽሁፍ ዓላማ በተለያየ ምክንያት በስደት ለምንኖር የቦታ መቀየር ተፅዕኖ ሳያሳድርብን በሃይማኖታችን ጸንተን እስከመጨረሻው በመንፈሳዊ ሕይወት እንድንኖርና እግዚአብሔር አምላክ ሁልጊዜ ከስደተኞች ጋር መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ተገንዘበን  “እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል” መዝ 145፡9 የሚለውን ህያው ቃል በውስጣችን አስቀምጠን የሚመጣብንን ፈተና ሁሉ በእግዚአብሔር እንደምንወጣው ለማስረዳት ነው።
 ነብዬ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለው? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለው? ወደ ሰማይ ብወጣ አንተ በዚያ ነህ፤ ወደሲኦልም ብወርድ በዚያ አለህ። እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፣ እስከ ባሕህር መጨረሻም ብበር በዚያ እጅህ ትመራኛለች ቀኝህም ትይዘኛለች። በውኑ ጨለማ ትሸፍነኛለች ብል ሌሊት በዙርያ ብርሃን ትሆናለች” መዝ 138፡7-11  ብሎ  እንዳስተማረን የሁሉ ፈጣሪ እግዚአብሔር በማንኛውም ቦታ፣ ጊዜ፣ ስዓትና ሁኔታ በምህረቱ፣ በቸርነቱ፣ በይቅርታውና በርኅራኄው እየጎበኘ በመንፈሳዊ ሕይወት እንድንኖር በምንሄድበት ሁሉ ጠብቆቱ አይለየንም።
በተለያየ ምክንያት ከምንወዳት ከአደግንባት አገራችን ወጥተን በባዕድ አገር በስደት በእምነት፣ በባህል፣ በቋንቋ እንዲሁም በአመለካከት ከማይመስሉን ጋር በተለያየ  ፈተናና ውጣ ውረድ ኑሮን ለመግፋት በመታገል ላይ ለምንገኝ ሰዎች ሰላማችን፣ እረፍታችን፣ መፅናኛችን፣ መከታችን፣ ሞገሳችንና ኃይላችን እግዚአብሔር ነው። ያለእርሱ ምንም ነገር መስራትና ማድረግ የማንችል ባዶዎች መሆናችንን ተረድተን ወገን ዘመድ በሌለበት እርሱን ተስፋ አድርጎ የስደትን አስከፊነት ታግሶና ተቋቁሞ ሥርዓትና ሕጉን ጠብቆ እግዚአብሔርን ማምለክ መንፈሳዊነት ነው። የስደት አስከፊነት እጅግ ከባድ ቢሆንም የተወለዱበትን፣ ያደጉበትን አገርና ህብረተሰብ ጥሎ መሰደድ እንዲሁም ከማያውቁት ህብረተሰብና አካባቢ ጋር መላመድ በስጋዊ አስተሳሰብ ከአየነው ይህ በራሱ ከባድ ነው። ስደት እስኪለመድና መረጋጋት እስኪገኝ ድረስ በብዙ መከራ፣ፈተናና ውጣ ውረድ ሕይወት ባዶ መስላ እስክትታየን ድረስ እጅግ አስቸጋሪ ነገር ውስጥ የገባን ይመስለናል ከባድም ነው። ይህንን የስደት አስቸጋሪ ሁኔታ ልንቋቋመው የምንችለው በእምነት ውስጥ ስንኖርና እግዚአብሔር አምላክን በመንገዳችን ሁሉ ስናስቀድም ብቻ ነው። በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክትን ስለአንተ ያዝዛቸዋል፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሱኋል” መዝ 90፡11 እንዳለ ቅዱስ መጽሐፍ የቅዱሳን መላእክትን ተራዳይነትና አማላጅነት አምነን ሕይወታችንን በሙሉ ለእግዚአብሔር አስረክበን የምንሄድ ከሆነ ሥራችን የተሳካ ይሆናል። የወጣንበት ዓላማም ከግብ ማድረስ እንችላለን።
ስደትን ከመንፈሳዊ ሕይወት ጋር አያይዞ መሄድ እጅግ አስፈላጊ ነው። “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ነገር ግን አይዞችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለው” ዮሔ 16፡33 ብሎ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው በስደቱ ዓለም የሚያጋጥመንን የተለያየ  መከራና ችግር ልናሸንፋና ድል ልናደርገው የምንችለው እርሱ ስለኛ የሚጨነቅ አምላክ መሆኑን ተረድተን በሕጉና በስርዓቱ ስንመራ ብቻ ነው። “ከእኔ ተማሩ እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝ” ማቴ 11፡28 ያለ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌ ገና በህፃንነቱ ከእናቱ ከቅድስት ድንግልማርያም ጋር ወደ ግብጽ በርሃ በመሰደድ ስደትም እንዳለ አስተማረን ማቴ 2፡13-23  አዎ ለእኛ ሲል መሰደድ የማይገባው አምላክ ተሰደደ፤ መራብ፣ መጠማት፣ መሰቃየት የማይገባው አምላክ ተራበ፣ ተጠማ ተሰቃየ በቀራኒዮ አደባባይ በመስቀል ላይ ተሰቀለ። ስለዚህ በክርስቶስ ክርስትያን፤ በመንፈስ ቅዱስ መንፈሳውያን እንደተባልን ክርስቲያናዊ ሕይወት መንፈሳዊ ሕይወት ሊኖረን ያስፈልጋል። ለመንፈሳዊ ሕይወት ደግሞ መከራ፣ ችግር፣ ፈተና፣ እንግልት፣ ውጣ ውረድ በአጠቃላይ በስደት ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ነገሮች ሁሉ መሰናክል ሊሆኑብን አይገባም። “በጊዜውም አለጊዜውም ጽና” 2ጢሞ 4፡2 ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ በችግርም በመከራም፤ ሲመቸም ሳይመችም፤ በደስታም በሃዘንም ጊዜ፤ በቦታም ያለቦታም፤ በስደትም  በእምነት መጽናትና እግዚአብሔርን ማገልገል እንዳለብን ለመንፈስ ልጁ በጢሞቴዎስ አማካኝነት አስተምሮናል። በተጨማሪም ወደ ሮሜ ሰዎች በላከው መልእክቱ “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ወይስ ጭንቀት፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ራብ፣ ወይስ ራቁትነት፣ ወይስ ፍርሃት፣ ወይስ ሰይፍ ነውን? ሮሜ 8፡35  በማለት ምንም ነገር ቢመጣ ከምናመልከው አምላክ መለየት እንደሌለብን በሚገባ ገልጾልናል። ለመሆኑ እኛ የተደረገልንን ነገር ረስተን በዘገየብን ነገር እግዚአብሔርን እያማረርን ነው ወይስ እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን ከአንተ አንለይም ሁሉም ለበጎ ነው እያልን ምስጋና የባህሪው የሆነውን አምላክ ከልብ እያመሰገነው ነው? መልሱን ለእራሳችን።
ሁላችንም ለዚች ምድር መጻተኞች መሆናችንን ተረድተው ብዙ የእግዚአብሔር ሰዎች በስደት በነበሩበት ጊዜ ችግሩን ሁሉ ታግሰው በመንፈሳዊ ሕይወት ይኖሩ እንደነበር ዛሬም እንዳሉ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዱናል። ይልቁንም በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እጅግ ጠንክረውና ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቀው ከመኖርም አልፎ በሃይማኖታቸው ላይ የሚመጣባቸውን ፈተና በጸጋ ተቀብለው ሰማዕትነትን የተቀበሉ ብዙዎች ናቸው። እስኪ የዮሴፍን ታሪክና የሰለስቱ ደቂቅን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንመልከትና ከሕይወታቸው እንማር።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስደትን በመንፈሳዊ ሕይወት ከኖሩ ሰዎች መካከል ወጣቱ ዮሴፍ ታላቅ ምሳሌ ነው። ታሪኩን ከዘፍ 37፡1_ ጀምሮ እንደምናገኘው ዮሴፍን ወንድሞቹ በግፍ፣ በተንኮልና በምቀኝነት ወደ ግብፅ በባርነት አሳልፈው ሸጡት። ዮሴፍ የስደትን መከራና ውጣውረድ የሚቋቋምበት የእድሜ ክልል ውስጥ አልነበረም። ነገር ግን እግዚአብሔርን በፍፁም እምነት ያመልክ ስለነበር በስደት ዓለም የሚያመልከው  አምላክ እግዚአብሔር ሞገስና ኃይል ሆነው።  
ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ እግዚአብሔር ዓለቴ አምባዬመድኃኒቴአምላኬበእርሱም የምተማመንበት ረዳቴ፣ መታመኛዬና የደኅንነቴ ቀንድ መጠጊያዬም ነው” መዝ 17፡2  እንዳለ እግዚአብሔር ለዮሴፍ ኃይል፣ መጠጊያ፣ ረዳትና ጠባቂ ሆነው። እግዚአብሔርን በፍፁም እምነት ካመለክነው በምንሄድበት ሁሉ እንደ ዮሴፍ ጥላችን፣ ከለላችን፤ ጋሻችን ፣ መከታችን፤ ረዳታችንና ጠባቂያችን ነው።  ዮሴፍ የሁሉ ፈጣሪ እግዚአብሔርን አምኖ ስደትን በጸጋ ተቀብሎ፣ የገጠመውን ፈተና ሁሉ ድል እየነሳ በነበረበት በስደት ሕይወት ውስጥ እያለ ለሥራው ታማኝና ታታሪ ስለነበር ጲጥፋራ በሃብት በንብረቱ ላይ ኃላፊ አድርጎ ሾመው። በዚያ ኃላፊነት ተሰጦት በጲጥፋራ ቤት እያለ ታላቅ ፈተና መጣበት፡፡ አዎ ዓለማዊ ስልጣንና ኃላፊነት ካላወቅንበት ፈተናና መከራ ይዞ ነው የሚመጣው፤ ለዮሴፍም የገጠመው ይህ ነበር። ማለትም የጲጥፋራ ሚስት ማንም የሌለበትን ስዓት ጠብቃ ለዝሙት ጋበዘችው። ዮሴፍም እኛ ብቻችንን ሆነን ማንም ሰው ባያይም የማመልከው አምላክ እግዚአብሔር  ያያልና “በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአት እሰራለሁ?” ዘፍ 39፡9 በማለት በስደት ዓለም ሞገስና ኃይል ለሆነው ለእግዚአብሔርና በቤቱ ላይ ኃላፊ አድርጎ ለሾመው ለጲጥፋራ ታማኝነቱን አሳይቶ የዲያቢሎስን ክፉ ሥራ አከሸፈበት።
እኛም ዛሬ ለእግዚአብሔርና ለምናገኘው ማንኛውም ኃላፊነት ታማኝ ሆነን ከኃጢአት ርቀን በመንፈሳዊ ሕይወት ለመኖር ከተጋን በስደት ዓለም እንደ ዮሴፍ ፈተናውን ሁሉ በድል እንወጣለን። በመንፈሳዊ ሕይወት የሚኖር ሰው እግዚአብሔርን ያስቀድማል፤ ኃጢአትን ለመስራት ምክንያት አይፈጥርም ይልቁንም እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአትን እሰራለው ብሎ ለሥራው፣ ለተሰጠው ኃላፊነት፣ ለትዳሩና ለሁሉም ነገር ታማኝ ይሆናል። በዚህም ምክንያት በእግዚአብሔርም በሰው ዘንድም ሞገስን ያገኛል። ዮሴፍ በሥራው ሁሉ እግዚአብሔርን ያስቀድም ስለነበር በእስር ቤት በነበረበት ጊዜም እግዚአብሔር ሞገስ ሆኖት ለእስረኞች ኃላፊ እንዲሆን አደረገው። “አንተን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩም” መዝ 24፡3  በማለት ቅዱስ ዳዊት  እግዚአብሔርን ተስፋ ያደረገ ሰው በማንኛውም ቦታ ቢሄድ፤ በማንኛውም ችግር ውስጥ ቢገባ ከቶ አንዳች ነገር እንደማይሆን ይነግረናል። ለዚህም ነው ዮሴፍ በስደት በነበረበት ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ ሞገስን፣ አስትዋይነትንና ጥበብን አድሎት በስደት ለሚኖርባት ግብፅም እንዲሁም ለስደት የዳረጉትን ወንድሞቹን እንኳ ሳይቀር ለበረከት ምክንያት የሆናቸው። እኛም እንደ ቅዱስ ዮሴፍ በምንሄድበት ሁሉ እግዚአብሔርንና ትዕዛዙን አክብረን፣ በእምነታችን ጸንተን በመንፈሳዊ ሕይወት የምንኖር ከሆነ በስደት ለምንኖርበት አገርም፣ ለአገራችንና ለቤተሰቦቻችን የበረከት ምክንያት ልንሆን ስለምንችል መትጋት ያስፈልጋል።
 እኛም ዛሬ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያቆብ፣ የዮሴፍ፣ የዳንኤል የሰለስቱ ደቂቅን የእምነታቸውን ጽናት እየተመለከትን እነርሱ የሠሩትን ሥራ መስራት ይገባናል። በስደት ዓለም የምንኖር ሰዎች ዳንኤልንና ሰለስቱ ደቂቅን ማስታወስ ለእምነታችን ጽናት ከበቂ በላይ ነው። ዳንኤልና ሰለስቱ ደቂቅ/ አናንያ አዛርያ ሚሳኤል/ በምርኮ ከትውልድ ቦታቸው ወደ ባቢሎን ተጋዙ። ታሪኩን በዳን 1፡1_ ጀምረን እንደምናገኘው  እነርሱ ግን በምርኮ በነበሩበት ስዓትም እግዚአብሔርን ከማምለክ ወደ ኋላ አላሉም። ይልቁንም በጾምና በጸሎት ይተጉ ነበር እንጂ።  ዳንኤልና ሰለስቱ ደቂቅ እግዚአብሔርን በጾም በጸሎት ተግተው ይለምኑት ስለነበር ሞገስና ጥበብን፤ በተለያየ አውራጃ ላይ ሹመትንም አደላቸው። ሰይጣን ለምቀኝነት አያርፍምና በስደት እግዚአብሔርን ስላመለኩ ሰለስቱ ደቂቅን ወደ እሳት፣ ዳንኤልን ወደ አናብስት ጉርጓድ እንዲጣሉ አደረገ ተጣሉም። እውነት እውነት እላችኋለሁ  የሰናፍጭ  ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ  ይህን ተራራ ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም  ነገር የለም።” ማቴ 17፡20 ብሎ ለሐዋርያት እንደተናገረው ዳንኤልና ሰለስቱ ደቂቅ ፍጹዕም እምነት ስለነበራቸው እሳቱ ውኃ፤ አናብስቱ እንደ መልካም ጓደኛ ሆኑላቸው። እምነታቸው ቅዱስ ሚካኤልንና ቅዱስ ገብርኤልን ወደ አናብስት ጉርጓድና ወደ እሳቱ እንዲመጡ አደረገ። ሰለስቱ ደቂቅ ወደ እሳት ሊጣሉ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀራቸው እምነታቸውን የገለጹበት ቃል አስደናቂ ነው፤ “የምናመልከው አምላክ ከሚነደው እሳት እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፣ ባያድነንም እንኳ አንተ ላቆምከው ለወርቅ ምስል ለጣኦት አንሰግድም” ዳን 3፡17   እንዴት አይነት እምነት ቢኖራቸው ነው? ዛሬ ብዙዎቻችን ምድራዊ ኑራችን አልተሟላም ብለን እግዚአብሔርን ስናማርር እንገኛለን። እነርሱ ግን ከእሳት እቶን ባያድነንም፣ በዚህ ምድር በሥጋ እንድንቆይ ፍቃዱ ባይሆንም ለጣኦት አንሰግድም አሉ። ስለዚህ እኛም እንደ አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤል ወደ ስደት የመጣንበት ዓላማ ቢሳካም ባይሳካም፣ የተመኘነውን ማግኘት ብንችልም ባንችልም፣ የስደት ሕይወት ከባድ ቢሆንም ባይሆንም፣ ብዙ ችግሮች ቢገጥሙንም  እምነታችንን፣ ባህላችንንና ማንነታችንን አንለውጥም አንቀይርም አንተውም ማለት ያስፈልጋል። እንዲህ ብለን በእምነት ከጸናን ደግሞ አምላካችን ይረዳናል፤በቅዱሳን ምልጃና ጸሎት ከፈተና ሁሉ ያወጣናል።
በመንፈሳዊ  ሕይወት ለመኖር ከእኛ የሚጠበቁ በርካታ ነገሮች አሉ። ከብዙ ጥቂቶቹን ለማየት እንሞክራለን።
1.   ቃለ እግዚአብሔርን መማር፦  መንፈሳዊ ሕይወት ቀስ በቀስ የሚያድግ ስለሆነ በአንዴ ተነስቶ መንፈሳዊ ሰው መሆን አይቻልም። ያለንን መንፈሳዊ ጸጋም እስከመጨረሻው አጽንተን የምንጓዝ ምግበ ነፍስ የሆነውን ቃለ እግዚአብሔር  ስንሰማና ስንማር ነው።  ሰው መማሩን፣ መጠየቁን፣ የአባቶችን ምክር ካቆመ ለተለያዩ ፈተናዎች እየተጋለጠ መሄዱን ያሳያል። “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” ማቴ 4፡4  ተብሎ እንደተጻፈ መማር፣ ቅዱሳት መጽሐፍትን ማንበብ፣ አባቶችን መጠየቅ በእግዚአብሔር እንድንታመን፤ በቅዱሳን አማላጅነና ተራዳይነት አምነን እንድንጠቀም፤ የቤተክርስቲያናችንን ታሪክ፣ ሕግ፣ ስርዓት፣ ዶግማና ቅኖና እንድናውቅ ያደርጋል።
ቅዱስ ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሳጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” 2ጢሞ 3፡16  እንዳለ ቅዱሳት መጽሕፍት ለመንፈሳዊ ሕይወት እጅግ አስፈላጊዎች ናቸው። በእርግጥ ቅዱሳት መጽሕፍትን በቀላሉ ማግኘት ከባድ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ዛሬ የምንኖርት ዓለም በቴክኖሎጂ ሰውን ከሰው ማገናኘት፣ የምንፈልገውንም ነገር በፍጥነት  ለማገናኘት የምታስችልበት ደረጃ ላይ ደርሳለች። ስለዚህ ይህን የቴክኖሎጂ የመረጃ  መረብ ለመንፈሳዊ አገልግሎት በመጠቀም ለነፍሳችን የሚያስፈልጋትን ምግብ መመገብ እንችላለን። እዚህ ላይ ግን በጥንቃቄ ማወቅ የሚገባን ነገር ትክክለኛው የቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ የሚተላለፍበት ድረ ገጽ የቱ ነው የሚለው መሰመር አለበት። ብዙዎች በስሜ ይመጣሉ የሚለው የወንጌል ቃል ይፈጸም ዘንድ በርካቶች በቤተክርስቲያናችን ስም የጡመራ ድረ ገጽ ከፍተው ቅዱሳንን ሲሳደቡ፣ የብሉይና የሐዲስን ሕግ አሟልታና አስማምታ የያዘችውን ቤተክርስትያን ሲተቹ፣ ከዚህም አልፎ እመ አምላክ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያምን መግለጽ በሚከብድ መልኩ ሲጽፉና ሲናገሩ እናያለን እንሰማለን። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል ከእነዚህ ደግሞ  ራቅ” 2ጢሞ 4፡5  ብሎ ለመንፈስ ልጁ ለጢሞቴዎስ እንዳስጠነቀቀው እኛም ከእነዚህ ርቀን የራሳችን የሆኑትን ድረ ገጽ ለይተን በመጠቀም መንፈሳዊ ሕይወታችንን ማሳደግ ይኖርብናል።
2.  ትዕዛዛተ እግዚአብሔርን መጠበቅአባቶቻችን ሃይማኖት ካለስርዓት ዋጋ የለዉም፤ ካለምግባር መንግሥተ ሰማያት ሊያስገባን አይችልም በማለት የእግዚአብሔርን ትዕዛዝና ሕግ መፈፀምና መጠበቅ እንዳለብን በአጽንኦት ይነግሩናል። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ሕግና ትዕዛዝ ሁሉን አሟልቶ የያዘ ነውና። በትዕዛዛቱ ውስጥ ስለእግዚአብሔር ማንነትና ምንነት፣ መልካም ምግባር መፈፀም እንዳለብን እና የሃይማኖታችንን ስርዓትና ሕግ እንረዳበታለን። ስለዚህ በመንፈሳዊ ሕይወት ለመኖርና መንፈሳዊ ሰው ለመሆን ትዕዛዙን መፈፀምና መጠበቅ ያስፈልጋል።  
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “የሚወደኝ ቢኖር ትዕዛዜን ይጠብቅ” ዮሐ 14፡15 መቼም እግዚአብሔርን የማይወድ ማንም የለም እርሱን የምንወድ ከሆነ ደግሞ ትዕዛዙን መጠበቅ ነው። እግዚአብሔርም በእኔ የምታምኑ ከሆነ፣ ከወደዳችሁኝ፣ ከአከበራችሁኝ ሕግና ትዕዛዜን ጠብቁ ፈፅሙ በማለት ትዕዛዙን መጠበቅ እርሱን መውደዳችን የምንገልፅበት መንገድ መሆኑን ይነግረናል።“ትዕዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችሁ የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው” ዮሐ 14፡21 በማለት 6ቱ ቃላተ ወንጌልን ማቴ 5፡21 እና 10ቱ ትዕዛዛተ ኦሪት ዘፀ 20፡1 - 17 ከጾምና ከጸሎት ጋር መፈጸም እንዳለብን ያስረዳናል።
3.  ጾምና ጸሎት፦ ጸሎት ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር፤ እግዚአብሔርን ማመስገን፣ መለመን፣ መጠየቅ መማጸን ማለት ነው። እንዲሁም ሰው አሳቡን ለእግዚአብሔር የሚገልጥበት፣ እግዚአብሔር የሰውን ልመና ተቀብሎ ፍቃዱን የሚፈፅምበት ረቂቅ ምስጢር ነው። ጾምና ጸሎት ሁለቱ የማይለያዩ የእግዚአብሔር የበረከት ስጦታዎች ናቸው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌ በምድር በነበረበት ጊዜ ከፈፀማቸው አበይት ተግባራት መካከል ጾምና ጸሎት ይገኙበታል። እርሱ የዲያብሎስን ፈተና በጾምና በጸሎት ድል እንደምንነሳው በገዳመ ቆሮንቶስ ለ40 ቀንና ለ40 ሌሊት ጾሞና ጸልዮ አሳይቶናል። ማቴ 4፡1_ ስለጾም ኢትዮጵያዊ ቅዱስ ያሬድ “ንጹም ጾም ወናፈቅር ቢጸነ፣ ወንትፋቀር በበይናቲነ፣ ዓይን ይጹም እምርእየ ሕሱም፣ ዕዝን ይጹም እምሰሚዓ ሕሱም፣  ልሳንኒ ይጹም እምተናግሮ ሕሱም ትርጉም ጾምን እንጹም፣ ባልንጀራችንን እንውደድ እርስ በርሳችን እንዋደድ፣ ዓይን ክፉ ከማየት ጀሮ ክፉ ከመስማት፣ አንደበትም ክፉ ከመናገር ይጹም በማለት እንዴት መጾም እንዳለብን በሚገባ ገልጾልናል።
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና  ፀልዩ” ማቴ 26፡41  ፈተና እንዳይገጥማችሁ ተግታችሁ ፀልዩ ብሎ እንዳስተማራቸው እኛም ወደ ፈተና እንዳንገባ በጸሎት መትጋት ያስፈልጋል።  ጾምና ጸሎት ወደ ፈተና እንዳንገባ የምንጠበቅበትና ከፈተናም የምንወጣበት ታላቅ መሳሪያ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል። ይህ ዓይነት ግን ከጸሎትና ከጾም በቀር አይወጣም” ማቴ 17፡21ሰይጣንን ልታስወጡ የምትችሉት፣ በፈተና ውስጥ ብትሆኑ ከገባችሁበት ፈተናና ችግር ልትወጡ፣ ልትፈወሱ የምትችሉት በጸሎትና በጾም ብቻ ነው ሲል ጌታችን በሐዋርያት አማካኝነት ገልጾልናል። እኛም ካልጾምን ካልጸለይን ወደ ፈተና እንገባለን ከገባንም አንወጣም። ጾምና ጸሎት ከፈተና የምንወጣበትና የምንጠበቅበት ብቻም ሳይሆን የሚያስፈልገንን ሥጋዊ ነገርም እንድናገኝ አማላካችን በቸርነቱ እንዲጎበኘን ይረዳናል። “ለምኑ ይሰጣችኋል፤  ፈልጉ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያ አንኳኩ ይከፈትላችሁማል” ማቴ 7፡7 እያለ ቅዱስ ወንጌል የምንፈልገውን ነገር እግዚአብሔር አምላክን በጾምና በጸሎት ከለመንነው በሚስፈልገን ስዓትና ጊዜ እንደሚሰጠን ያስረዳናል። ስለዚህ እኛ ወደፈተና እንዳንገባ፣ ከገባንም ከፈተና እንድንወጣና የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ እንድናገኝ የስደትን ኑሮ፣ ባህልና የአየር ጠባይ ለውጥ ምክንያት ሳናደርግ እንደ አባቶቻችን እግዚአብሔርን በጸሎትና በጾም መለመን መማጸን አስፈላጊ ነው።
4.  ትዕግሥትሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው ትዕግሥት ከመንፈስ ፍሬዎች አንዱ ነው። ገላ 5፡22_23 የመንፈስ ፍሬ ብሎ የዘረዘራቸው ምግባረ ሰናያት እርስ በእርሳቸው ግንኙነት አላቸው። ዕምነት ያለው ሰው የውሃት፣ ቸርነት፣ በጎነት ሊኖረው ይገባል፤ ፍቅር ያለው ሰው ደስታ፣ ሰላም ከእነዚህም ጋር ትዕግሥትም አለው። ፍቅርና ዕምነት ያለው ሰው እራሱን መግዛት ይችላል። ፍቅር ይታገሳል እንዲል 1ቆሮ 13፡4። ትዕግሥት ቻይ፣ ልበ ሰፊ፣ ትሁትና መሀሪ የሆነ ሰው ጠባይ መለያ ነው። ትዕግሥት ዘርፈ ብዙ ነው። በአገልግሎት፣ በጸሎት፣ በማህበራዊ  ሕይወትና በፈተና ጊዜ ትዕግሥት አስፈላጊ ነው። ትዕግሥት የሌለው ሰው በቀላሉ ይጨነቃል፣ ይረበሻል፣ ይበሳጫል ምክንያቱም ለምን አሁን የምፈልገው ነገር አልሆነም ብሎ ስለማይረጋጋና ስለሚቸኩል ነው። በተለይ በስደት ዓለም ስንኖር የምናያቸው፣ የምንሰማቸው እና የምናገኛቸው ነገሮች በአብዛኛው ትዕግሥትን የሚፈታተኑ ስለሆኑ ትዕግሥት ከመቸውም በበለጠ ያስፈልጋል። 
ጠቢቡ ሰሎሞን “ለሁሉም ጊዜ አለው” መክ 3፡1  እንዳለ ጸሎታችን ልመናችን መልስ የሚያገኝበት፣ የሚያስፈልገን ሥጋዊ ነገር የምንናገኝበት፣ እጅግ አስቸጋሪ መስሎ የሚታየን የብቸኝነት የስደት ኑሮ የሚያበቃበት ጊዜ አለና ይህን በትዕግሥት መጠበቅ ይኖርብናል። “ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሰው እርሱ አይዘገይም” ዕን 2፡3  እግዚአብሔርን እናውቀውና እናከብረው ዘንድ ልመናችን ሊዘገይ ይችላል። ነገር ግን እግዚአብሔር የእኛን ልመና አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው በሚያስፈልገን ሰዓት እንደ አባታችን ኢዮብ ትዕግሥትን አለማምዶ ቢዘገይም ይሰጠናል። ትዕግሥት ባለማወቅም እንኳ ቢፈጽሙት ፍሬው እጅግ ታላቅና ጽድቅንም ያፈራል። “በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።  ለመቀጣት ታገሡ፤ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርችኋልና፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? ነገር ግን ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፥ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል።” ዕብ 12፡2_11  እንዲሁም አባታችን ኢዮብ “እነሆ ቢገድለኝ ስንኳ እርሱን በትዕግሥት እጠብቃለው ነገር ግን መንገዴን በፊቱ አጸናለው” ኢዮ 13፡15 በማለት ይህ የመጣብኝ ሥጋዊ ፈተና ለሞት ቢዳርገኝም እንኳ በትዕግሥት ሞቴን እጠብቃለው እንጂ እምነቴን በሥጋዊ ፈተና ምክንያት ከእምነቴ ወደ ኋላ አልልም እንዳለ እኛም እንደ  አባቶቻችን የመጣብንን ፈተና  ሁሉ ታግሰን፣ የጽድቅን ፍሬ እንበላ ዘንድ ትዕግሥትን ገንዘብ ማድረግ ያስፈልጋል።
5.  ከክፉ ባልንጀራ መራቅ/ጓደኛን መምረጥ/በዚህ በምንኖርበት በስደት ዓለም ከማን ጋር መዋል፣ መነጋገር፣ መወያየትና መመካከር እንዳለብን ካለወቅን ልንነሳ በማንችልበት አወዳደቅ ልንወድቅ እንችላለን። ብዙዎች በጓደኛ ምክንያት ከእምነታቸው፣ ከባህላቸው፣ ወጥተው ማንነታቸውን ለውጠው የክፉ ጓደኛቸውን ገጸ ባህሪ ተላብሰው እናገኛቸዋለን። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋልበጽድቅ ንቁ ኃጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና” 1ኛ ቆሮ 15፡33 እያለ ምን አይነት ጓደኛ መከተል እንዳለብን ይመክረናል።
ክፍ ባልንጀራ የጀመርነውን መንፈሳዊ ሕይወት እስከመጨረሻው እንዳንዘልቅ እንቅፋት ይሆንብናል። እስኪ ጓደኞቻችንን እናስታውስ ስንቶች ናቸው ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ብርታት ሊሆኑን የሚችሉ? ስንቶች ናቸው ሃይማኖታዊ ስርዓታችንን እንድንጠብቅ የሚመክሩን የሚያበረቱን? ስንቶች ናቸው ባህላችንን ማንነታችንን እንድጠብቅ የሚገፋፉን? በእርግጥ እጅግ መልካም ለመንፈሳዊ ሕይወታችን አስትዋጽኦ የሚያደርጉ ጓደኞች አሉ ይኖራሉም። አባቶቻችንና ቅዱሳን መጽሐፍት እንደ እነዚህ አይነት ሰዎችን እንድንከተል ነው የሚመክሩን። ክፉ ጓደኛ  በመጀመሪያ ሲቀርብ መልካም ቃላቶችን መርጦ እኛን ወደርሶ ሊያቀርብ በሚችልበት በደካማ ጎናችን ነው የሚቀርበን። እናታችን ሔዋንን ሰይጣን ሲቀርባት በውዳሴ ነበር የቀረባት ማንም አወድሷት የማያውቀውን የውዳሴ አይነት ነበር ያቀረበላት ፍጻሜው ግን መከራና ሞት ነው የጠበቃት። ስለዚህ እኛም የሚቀርቡንን ሰዎች ለምንና እንዴት ብለን እራሳችን መጠየቅ ያስፈልጋል አለበለዚያ ግን እንደ  ሶምሶን ጸጋችን ተገፎ መንፈሳዊነት ርቆን ከውኃ የወጣ አሳ እንሆናለን።
በአጠቃላይ ከላይ ለማየት እንደሞከርነው ከእኛ  የሚጠበቁ ነገሮችን እያደረግን፣ የቀረውን ነገር እግዚአብሔር በቸርነቱ እንዲጎበኘን በጸሎት እየለመን፣ በመንፈሳዊ ሕይወት እድንጓዝ እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮችን ማስወገድ ይኖርብናል። በትንቢተ ሕዝቅኤል ንስሐ ግቡ ኃጢአትም ዕንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኃጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ። የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም ለእናንተ አድርጉ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለ ምን ትሞታላችሁ? የምዋቹን ሞት አልፈቅድምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ።” ሕዝ 18፡30_32 ተብሎ እንደተጻፈ አንዱና ትልቁ እንቅፋት ኃጢአታችን ነውና እርሱን በንስሐ ታጥበን በሕይወት እንኖር ዘንድ የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን፤ የድንግል ማርያም፣ የቅዱሳን ምልጃና ጸሎት አይለየን አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!