Friday, May 2, 2014

ቅድሚያ ለሰው ህይወት ወይስ ለከተማ መስፋፋት?


  •  digg


  • 651
     

    Share
አዲስ አበባን ለማስፋት የወጣው ማስተር ፕላን በአዲስ አበባ ዙርያ ያሉ የኦሮምያ ክልል ገጠር መሬቶች የአዲስ አበባ ከተማ አካል እንደሚያደርጋቸው የተረዳ  የኦሮሞ ህዝብ በተለይ በኦሮሞ ተማሪዎች በተለይ በአምቦ፣ በአዳማ፣ በድሬዳዋ ከባድ አመፅ አስነስቷል። የብዙ ተማሪዎችንም ህይወት ቀስፏል።
ማንም ሰው አገር ቢያድግ፣ ከተማ ቢሰፋ ቢያድግ ደስ ይለዋል እንጂ ለአመፅ አይነሳሳም ነበር። በተለይ በተማረው ህብረተሰብ ዘንድ ማስተር ፕላኑን መቃወም ትልቅ ችግር እንዳለ ያመላክታል። ይህ የተማረው ህብረተሰብና በመማር ላይ ያሉ ተማሪዎች ከተማ እንዴት እንደሚሰፋ ጠንቅቀው ያዉቃሉ። ከተማ ሲያድግ በዙርያው የሚገኙትን የገጠር ቦታዎች ማካተቱ አይቀሬ እንደሆነ ገሃዳዊ እውነታ ነው። ነገር ግን በጣም ትልቅ ችግር እና በሕወሓት አምባ ገነናዊ የአገዛዝ ዘመን እየተስተዋለ ያለው የከተሞች ማስፋፋት ስትራተጂ አፈፃፀም ኗሪዎችን በእጅጉ ጎድቷል፤ እየጎዳም ነው።
የገጠር መሬት ወደ ከተማ ክልል እንዲገባ ሲደረግ በቦታው ሃብት ንብረት አፍርተው የሚኖሩ አርሶአደሮች (ህብረተሰብ) ያለ ፍቃዳቸው ከቀያቸው ይፈናቀላሉ። ቤት፣ መሬት አልባ ይሆናሉ። በቂ ካሳ (ክፍያ) አይሰጣቸውም። በዚህ መሰረት አርሶአደሮቹ ተቃውሞ ያሰማሉ። ይህ ጉዳይ በኦሮምያ ብቻ አይደለም የተከሰተው። በሁሉም የአገሪቱ ከተሞች ተከስቷል። የብዙ ሰው ህይወት አልፏል። በህዝቡ ላይ በድህነት ላይ ድህነት፣ በርሃብ ላይ ርሃብ፣ በችግር ላይ ችግር፣ በርዛት ላይ እርዛት ተጨምሮበታል። ይህን ጉዳይ በተመለከተ  ሁሌ ተቃውሞ አለ። ይህን ጉዳይ የተለያዩ ሚዲያዎች በሚገባ ዘግበውታል። 
 ይህ ነገር ተቃውሞ መቀስቀሱ ታድያ አይገርምም። ምክንያቱም አርሶ አደሮችን ከቀያቸው የሚያፈናቅል መሆኑ ነው። ወደሌላ ቦታ እንዳሄዱ እንኳ በብሔሮች መካከል የዘራው የብሔር ፖለቲካ ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓቸዋል። በብዛትአማረኛ ተናጋሪዎች ለረጅም ጊዜ ከሚኖሩበት ቦታ ብሔርን ምክንያት በማድረግ እንዴት እንደተፈናቀሉ የማይረሳ ታሪካዊ ክስተት አለ። ይህ ባለበት በከተማ ማደግ ሽፋን ቤታቸው መሬታቸው ተነጥቆ ካለምንም ክፍያ ሜዳ ላይ ሲወድቁ ተቃውሞ ባያሰሙ ነበር የሚገርመው። ከርሃብ ጦር ይሻላል እንዲሉ ሰላማዊው ተቃውሞ ምላሹ ሞት እና እስራት ቢሆንም ዝም ብሎ በርሃብ ከመሞት ይልቅ ተቃውሞን እያሰሙ መሞትን ህዝብ የመረጠ ይመስላል። 
በጣም የሚገርመው እና የሚያዛዝነው ግን መንግስት ነኝ ባዩ  የሕወሓት አገዛዝ ተቃውሞ ለሚያሰሙ ሰዎች መፍትሔ ከመስጠት እና ሁኔታውን ለህዝብ በሚገባ ከማስረዳት ይልቅ የኃይል እርምጃ በመውሰድ ይደበድቧቸዋል፣ ይገድሏቸዋል፣ ያስሩዋቸዋል፣ ያሰቃያቸዋል። እርግጥ ነው ከገዢው መደብ መፍትሔ አንጠብቅም። ችግሩ እንዲፈጠር እና እንዲበባስ ያደረጉት ሆን ብለው ስለሆነ።  እውነተኛ ለህዝብ የቆመ መንግሥት ቢሆን ኑሮ ተቃውሞ  ከመነሳቱ በፊት የሚመለከታቸውን የህብረተሰብ ክፍል በሚገባ ደረጃ በደረጃ ጥልቅ ውይይት ማድረግ እና  የከተማ መስፋት በምን መልኩ እና እንዴት በሚለው ዙርያ ግንዛቤ ቢፈጥር ኑሮ  የሰው ህይወት ባልጠፋ ነበር። አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማም እንደሚባለው ሆን ብሎ የተደረገን ነገር ህዝብ በሰላማዊ ተቃዉሞ ሃሳቡን ቢገልጽም የህይወት ሰለባ ከመሆን ባለፈ ለሕወሓት_ቅንጣት ያክል ርህራሄ ሊሰማው አልቻለም፤ አይችልም።
ገዢው ፓርቲ የኃይል እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥቦ መፍትሔ ማፈላለግ ካልቻለ በስተቀር ይህ በቀላሉ የተነሳው እሳት ተቀጣጥሎ ወደ ቤተ መንግሥት ገብቶ የተቀመጡበትን ወንበር እንዳይበላው ቢያስብበት መልካም ነው። ነገር ግን  የሕወሓት ስልጣን አይደለም የሚያሳስበን ንጹሃን ዜጎች ሰባዊ ርህራሄ በሌላቸው ካድሪዎች ደማቸው መፍሰሱ እንጂ። ይኸው ዛሬም በርካቶች ደማቸው ፈሷል፤ አካላቸው ጎድሏል፤ የቀሩትም በእስር ቤት እየተሰቃዩ  ነው።  የፍትህ ያለሽ ቢሉም ፍትህ ፊቷን አዙራባቸዋለች። ግን እስከመቼ??? መልሱ እጅግ በጣም ቀላል ነው ..............
  1. ህዝብ የብሔር ልዩነቱን አንድነት አድርጎ ለነጻነት በህብረት መቆም ሲችል
  2. የእምነት/ሀይማኖት፣ ባህል እና ቋንቋ ልዩነቱን በልዩነት ይዞ ለአንዲት አገር ኢትዮጵያ በጋራ ማሰብ እና መንግሥት ነኝ ባዩን መንግሥት አይደለህም አልመረጥንህም፤ አንተ አትመራንም ማለት ስንችል።
  3. እያንዳንዳችን ለመብታችን መቆም ስንችል። የተፈጥሮ ጸጋወችን የመጠቀም ተፈጥሮአዊ መብታችን እንደሆነ በትክክል ተረድተን መብትን ለማያውቀው ሕወሓት ማሳወቅ ስንችል።
  4. በተለያየ ጥቅማጥቅም ተይዘው ህዝብን ለሚያሰቃዩና ለሚገድሉ ለሕወሓት ተላላኪዎችና ካድሪዎች ከምንም በላይ ህዝብ ሰላምን እና ሰላምን ብቻ እንደሚፈልግ ማስረዳት። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጠቅሶ እንደሚገኘው ቢሆኑም
     (የሰው ልጅ ሆይ፥ በዓመፀኛ ቤት መካከል ተቀምጠሃል ያዩ ዘንድ ዓይን አላቸው እነርሱም አያዩም፥ ይሰሙም ዘንድ ጆሮ አላቸው እነርሱም አይሰሙም እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና።) ሕዝ 12፥2
     
    ሕወሓት ሆይ፣
     
    (እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ፥ የምድርን በረከት ትበላላችሁ እምቢ ብትሉ ግን ብታምፁም፥ ሰይፍ ይበላችኋል የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና። ፍርድ ሞልቶባት የነበረው የታመነችይቱ ከተማ እንዴት ጋለሞታ ሆነች! ጽድቅ አድሮባት ነበር፥ አሁን ግን ገዳዮች አሉባት።) ኢሳ 1፥19_20 ብሎ የሁሉ ፈጣሪ እግዚአብሔር በነብዩ ኢሳያስ አማካኝነት እንደተናገረው እሺ ብትሉ፣
     
    • ህዝብን በስርዓት ማስተዳደር ብትችሉ

    • ለሰላምና መረጋጋት እንደመንግሥት የድርሻችሁን መወጣት ብትችሉ

    • መከፋፈሉን ትታችሁ አንድነትን ብትሰብኩ

    • ማፈናቀልን አቁማችሁ ማስፈርን ብትሰሩ

    • ንጹሃን ዜጎችን ከማሰር ይልቅ ፍትህን ብታውጁ

    • አገርን ከመሸጥ ይልቅ መጥፎ ድርጊታችሁን እና ጸባያችሁን ብትሸጡ

    • ህዝብን ከመግደል ይልቅ የመኖር መብትን ብታስከብሩ

    • ብሔርን ከማጋጨት ይልቅ ፍቅርን እና አንድነትን ማምጣት ብትችሉ
    • ከተማ ከማስፋት ይልቅ ለሰው ህይወት ቅድሚያ ብትሰጡ የምድር በረከት(የህሌና እረፍት፣ ተከብራችሁ ስልጣን ላይ መቆየትን) ትበላላችሁ ....እምቢ ብትሉ ደግሞ ...............አንድ ቀን ህዝብ ሰይፍ ሁኖ ይበላችኋል፤ ያጠፋችኋል፤ ይበቀላችኋል፤ የእጃችሁን ይከፍላችኋል!!!!!!!!!!