Wednesday, July 9, 2014

አንድነት በአዲስ ስልት

በየመን ታሪክ በማይረሳ ህገወጥ ድጋፍና ትብብር የግንቦት 7 የፍትህ፣ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ጽሐፊ የሆኑትንና የብርታኒያ ዜግነት ያላቸውን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ለወያኔ ለሞትና ለስቃይ አሳልፎ መስጠት የሰሞኑ አነጋጋሪና ስሜት ቀስቃሽ ዜና ሁኗል።  ይህ ክስተት ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ለነጻነትና ለፍትህ የሚታገሉ ሁሉ ድርጊቱን በመተቸት ላይ ናቸው፤ በተለያየ መልኩ የድርጊቱን አስከፊነትና ለአቶ አንዳርጋቸው ያላቸውን ድጋፍ በመግለጽ ላይ ይገኛሉ። ብርታኒያም ዜጋዋን ከወያኔ እጅ ለማስለቀቅ የምትወስደው እርምጃ በጉጉት እየተጠበቀ ነው። በተለይ በንቅናቄው አባላት ከፍተኛ ቁጣን አስነስቷል። ይህ ቁጣም በድርጊት እንደሚገለጽ ንቅናቄው በመግለጫ አሳውቋል። መግለጫውን ከዚህ መመልከት ይቻላል!

ወያኔዎች/ሕወሓቶች የሥልጣን ጊዜን ለማራዘም የማይቆፍሩት ጉድጓድ፣ የማይፈነቅሉት ድንጋይ፣ የማይከተሉት ስልት፣ የማይወዳጀጁት ኃይል እንደማይኖር ለሁላችንም የማይሰወር ገሃዳዊ እውነታ ነው።  በተለይ ደግሞ ለሥልጣናቸው ስጋትና ጭንቀት የሚፈጥሩትን ድርጅቶች በአሸባሪነት እስከመክሰስ እና አባላሎቻቸውንም በስቃይና በመከራ ወደ እስር ቤት መወርወር የዘወትር ተግባራቸው ነው። ይህንንም ተግባራቸው ዛሬም በአቶ አንዳርጋቸው ላይ በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፤ ነግም ማነህ ባለ ባለሳምንት/ተራ ማለታቸው አይቀርም።
ስለዚህ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት እያንዳንዳችን ከዚህ አስከፊ ሥርዓት ለመላቀቅ እና ፍትህ፣ ነጻነትና ዲሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለማየት አዲስ ስልት በወኔና በቁርጠኝነት ለመከተል መንደፍ ይኖርብናል። ይህ ካልሆነ ግን ወያኔ 23 ዓመት ኢትዮጵያውያንን እንደፈለገ ከፋፍሏል፣ አሰቃይቷል፣ ድርጅቶችን ዘግቷል፣ ተቋማትን አዳክሟል እኛንም ግዝቶናል ነግም ይቀጥላል።
የግንቦት 7 ንቅናቄ ፦
  1. ምንም እንኳ ንቅናቄው ታላቅ መሪ ቢያጣም በመግለጫው ተግባራዊ የመጀመርያ እርከን የትግል ጥሪ በተግባር ላይ እንዲውል ከማስተባበር በተጨማሪ በመረጋጋትና በማስተዋል ዘላቂ ስልቶችን መንደፍ(የአጭርና የረጅም)፣ የትግል ስልትና የመዋቅር አደረጃጀትም በተወሰነ ደረጃ መቀየር፣ 
  2. አባላት በግልጽ ባይታወቁም ከአንዳርጋቸው መያዝ ጋር ተያይዞ  በሚያደርጉት የስሜት መለዋወጥ እንዳይጋለጡ በጥበብና በጥንቃቄ እንዲጓዙ ማሳሰብ(በተለይ ኢትዮጵያ ለሚገኙ አባላት)፣
  3. ብርታኒያ የድፕሎማሲውን ሥራ እና የአቶ አንዳርጋቸውን ደህንነት ሁኔታ እንዲከታተሉ በጥብቅ ከመረጃ ጋር(የወያኔን የእስር ቤት ድብደባ፣እንግልትና ስቃይ በጥልቀት እንዲገነዘቡት) ግፊት ማድረግ፣
  4. ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር በስፋትና በጥልቀት የጎረቤት አገሮችን ሁኔታ ማጤን እና ወዘተ...
ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች፦
  1. የቱንም ያክል የሀሳብ ልዩነት ቢኖርም በመርህ ደረጃ ኢትዮጵያን ነጻ ማውጣትና ህዝቧ ነጻነትና ፍትህ እንዲያገኝ እስከሆነ ድረስ ድርጅቶች ሁሉ በመጀመርያ ህብረት ፈጥሮ ወያኔን ማስወገድ የሚቻልበትን ተግባራዊ አንድነት መፍጠር፣
  2. የብሔር ፖለቲካ እኛም አለን ከማለት ውጭ እንደ ኢትዮጵያ ታላቅ ታሪክ ያላት አገር በቀላሉ ብሔርን ገንጥሎ መሔድና መታገል ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችሉ ማሰብና አገራዊ ስሜትን መላበስ፣ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” የሚለውን ብሂል በተግባር ማዋል በእጅጉ ውጤታማ ያደርጋል፣
  3. የድፕሎማሲው ስራ በተጨማሪ ከሁሉም የሚጠበቅ ነው፣
ከሁሉም ኢትዮጵያዊ፦
  1. የራስን መብት በራስ ማስከበር በሚል መርህ ቃል ሁላችንም መብታችንን ለማስከበር ቆርጦ መነሳት። ለመብታችን  እስራትን፣ እንግልትን፣ ድብደባን በጸጋ መቀበልና አገራዊ ስሜት ተላብሰን እንደ አባቶቻችን ድልን ለመቀናጀት የበኩላችንን ድርሻ መወጣት! በሌላ አነጋገር ሁላችንም አንዳርጋቸው ጽጌን፣ አንዷለም አራጌን፣ እስክንድር ነጋን፣ እርዮት ዓለሙንና ሌሎችን ሁነን መነሳት።
  2. አገራዊ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግና የሥራ ማቆም አድሚያ ማድረግ! ለመብት፣ ለነጻነት፣ለፍትህ ሲባል መደረግ የሚገባቸውን ነገሮች ሁሉ ማድረግና የኢትዮጵያን ታሪክ መመለስ። 
በአጠቃላይ ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ የተከሰተው ድርጊት የወያኔን ውርደትና ውድቀት የሚያፋጥን እና  የኢትዮጵያን ነጻነትና ፍትህ የሚያጎናጽፍ ሊሆን እንደሚችል አመላካች ነው የሚል እምነት በብዙዎች ላይ አሳድሯል። ስለዚህ ሁሉም ለኢትዮጵያ ነጻነት የቀመና ፍትህ ፈላጊ ሁሉ ይህን በአቶ አንዳርጋቸው ላይ የተከሰተውን ድርጊት እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ አንድነትና ህብረት በመመስረት ለለውጥ በአዲስ ስልት፣ በአዲስ መንፈስ፣ በአዲስ ትግል መጓዝና መራመድ ይኖርብናል። ይህ ከሆነ ከአለምንም ቅድመ ሁኔታ ነጻነትና ፍትህ እንጎናጸፋለን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!

ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች!

Saturday, July 5, 2014

መሪን በማሰርና በመግደል ትግልን ማስቆም አይቻልም

ነጻነትና ፍትህ የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊ አገር ለመገንባት የለውጥ መሪዎች ከለውጥ በፊት ብዙዎች በብዙ መከራና ስቃይ ያልፋሉ። ሕይወታቸውንም ሳይቀር በሰማዕትነት አሳልፈው ይሰጣሉ ሰጠዋልም። ደም ሳይፈስ ስርየት የለም እንዲል መጽሐፍ መሪዎች ሰማዕትነትን ሳይቀበሉ ነጻናትና ፍትህ መጎናጸፍ አይቻልም። የብዙ አገሮችን የዲሞክራሲ ግንባታን ስንመለከት የሰሞኑ ዜና የመጀመርያ እንዳልሆነ ያስገነዝበናል።
የየመን የጸጥታ ኃይሎች የግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ጽሀፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በህገ ወጥ በማገት ለኢትዮጵያ የወያኔ መንግሥት አሳልፋ መስጠቷ ሰበርና ታሪካዊ ዜና ኋኗል።  ንቅናቄው ባወጣው መግለጫ አቶ አንዳርጋቸው አንድ ግለሰብ ሳይሆኑ ለጽዕኑ ዓላማ የማይጨበጥ መንፈስ ናቸው ሲል ተናግሯል። እንዲሁም የንቅናቄው ዋና ጽሀፊው አንዳርጋቸው ለለውጥ እራሱን አሳልፎ የሰጠ የዘመኑ ጀግና መሪ እንደሆነ መግለጫው ያረጋግጣል። መግልጨዋም የመን አንዳርጋቸውን አሳልፋ መስጠቷን ፤ ጽኑ መንፈስ

እንደሚታወቀው እራስ ወዳድነት በነገሰበት ዓለም ሕይወትን አሳልፎ  እንደመስጠት ከባድ፣ አስፈሪና አስቸጋሪ ፈተና የለም። ሆኖም ግን አቶ አንዳርጋቸው ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ፍትህና ነጻነት ይሰፍን ዘንድ ሕይወታቸውን አሳልፈው መስጠትን ስመለከት የትግል ስልታቸው ምንም ይሁን ምን ለእኔ የተለየ ስሜት ፈጥሮልኛል። ግንቦት 7 መሪዎችም ሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ አገራዊ ለውጥ ፈላጊ ሁሉ በሰላማዊ መንገድ ኢትዮጵያን ከከፋፋይና ከዘረኛው ወያኔ/ሕወሓት ኃይል ነጻ ማውጣት የሚቻለው ሕይወትን አሳልፎ እስከመስጠት ድረስ በቆራጥነት መታገል ብቻ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ ገልጧል። ንቅናቄው  ራዕይና ተልኮውን ለህዝብ ግልጽ አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። የንቅናቄው ራዕይና ተልኮ እንደሚከተለው በድረ ገጽ ላይ ሰፍሯል።

ራዕይ
የግንቦት 7 ንቅናቄ፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቱ የተከበረበት፣ የኢኮኖሚ ብልፅግናና ማኅባራዊ ፍትህ የሚያገኙበት፣ የዜጎች ህይወት፣ ደህንነትና ጥቅም የተከበረበት ሃገር እንዲኖረው ማድረግ ነው።

ተልዕኮ
የግንቦት 7 ንቅናቄ፣ ቀዳሚ ተልዕኮ የመንግስትና የፖለቲካ ስልጣን በሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደት የሚያዝበትንና የሃገሪቱ ዜጎች ምርጫ በተግባር የሚገለፅበትን ብሄራዊ ሥርአት እንዲገነባ ማገዝ ነው።

መሰረታዊ ዕሴቶችና መርሆዎች
  • የግለሰቦችና የህዝብ መብቶች መከበር የአዲሱ ፖለቶቲካዊ ሥርአት የሚዕዘን ድንጋይ ነው፣
  • የአዲሱ ፖለቲካዊ ስርአት የጀርባ አጥንት በመሆን የአምባገነን መንግስታትንም ሆነ ፓርቲዎችን፣ እንዲሁም ፖለቲከኞችን መረን ያጣ ሥልጣን ለመቆጣጠር፣ ነፃ መንግስታዊ የሆኑና ያልሆኑ ተቋማት ምሥረታና መጠናከር አስፈላጊነቱን በማመን፣
  • ነፃ የፖሊስና የመከላከያ ሃይል፣ ነፃ የምርጫ ቦርድና ነፃ ፕሬስ እንዲመሰረቱና እንዲጠናከሩ መታገል፣
  • የሃይማኖት፣ የዘውግ፣ የባህልና የመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ልዩነቶች የሚያደምቁን ውበቶቻችን እንጂ፣ የርስ በርስ መጠቃቂያ መሳሪያዎች አለመሆናቸውን በማመን፣ ይህንን ውበት ያላበሱን ልዩነቶቻችንን የሚያከብር በሃገራዊ አርበኛነት ላይ የቆመ ጠንካራ ህብረተሰብ መገንባት፣
  • ዜጎች ከሚጋሩት ህይወት፣ ህልምና ተስፋ እንዲሁም በታሪክ ካዳበሩት የጋራ ትስስር ይልቅ፣ የዘውግ፣ የሃይማኖትና ባህላዊ ልዩነቶቻቸውን ለአጭር ጊዜ የፖለቲካ ጥቅም የሚቆምሩ ፖለቲካዊና ተውፊታዊ ጎታች ሃይሎችን መታገል፣
  • ዜጎች በዘውግ ጀርባቸው፣ በሃይማኖታቸው፣ በቋንቋቸው፣ በባህላቸው፣ በእድሜያቸው፣ በጾታቸው ወይም በመልክአ ምድራዊ ልዩነቶቻቸው ወይም በግላዊ አቅመ-ደካማነታቸው የተነሳ አድልኦ የማይፈጸምባቸውና የዜግነት የእኩልነት መብታቸው የሚከበርበት ፖለቲካዊ ሁኔታ ማመቻቸት፣
  • ሃገሪቱን ለማገልገል የቆረጡ፣ ታታሪ፣ ብሩህ፣ አርቆ አሳቢና ሆደ-ሰፊ፣ ለዜጎች አርአያ የሚሆኑ መሪዋች እንዲፈጠሩ ማገዝ፣
  • የመልካም አስተዳደር፣ የተጠያቂነትና የግልፅነት መርሆዎች፣ ህዝብን ማዕከል ካደረገ የውሳኔ አሰጣጥ ጋር ተሳስረው በተግባር የሚተረጎሙበትን ሥርአት መመሥረት፣
  • በጥረት የሚገኝ ውጤት የሚከበርበት፣ ሃገርን ማገልገል ድንቅ የሚባልበት፣ ችሎታና ታታሪነት ብቻ የሽልማት መስፈርቶች የሆኑበት፣ ዜጎች በፖለቲካ ትስስራቸውና በዘውግ ማንነታቸው ሳይሆን በአበርክቶአቸው የድካማቸውን ውጤት የሚያገኙበትና የሚወደሱበት ፖለቲካዊ ሥርአት መመሥረት፣
  • ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችና ህዝባዊ ግንባሮች ጋር ቅንብርና ትብብር በመፍጠር፣ በመሃላቸው ያለውን ውጥረት ማርገብ፣ ብሎም፣ ሁሉን በአካተተ፣ ሰፊ የፖለቲካዊ ስርአት አማካይነት ብሄራዊ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር፣
  • ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ፣ የህዝብ ግንባርና እንዲሁም መብትና ጥቅሜ አልተጠበቀም የሚል ቡድን፣ በፖለቲካ ዕምነቱም ሆነ ፕሮግራሙ የተነሳ የማይገለልበትን፣ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሥርአት ማቋቋም ነው።
ለአቶ አንዳርጋቸው ጽናትና ብርታት የሆነው ራዕዩና ተልኮው ነው። ይህን ለማሳካትም ግላዊ ሕይወቱን አለመመልከቱ እውነተኛና ቆራጥ ታጋይ እንደሆነ ምስክር ሁኖለታል።  የንቅናቄውን ራዕይ፣ ተልኮና በመርህ ደረጃ ያስቀመጣቸው ነጥቦች እውን ይሆኑ ዘንድ አንዳርጋቸው እራሱን አሳልፎ ሰጠ። የሀገር ፍቅር፣ የሀገር ስሜት፣ የባንዲራ ክብር፣ ለመብት መቆም፣ ለነጻነትና ለፍትህ መታገል እንዲህ በተግባር ሲገለጽ ለኢትዮጵያ የመጀመርያ ባይሆንም ለዘመኑ ትውልድ ግን የሀገር ስሜትና ፍቅር ምን እንደሆነ ይረዳ ዘንድ ትልቅ ተምሳሌት ሁኖልናል ብሎ በልበ ሙሉነት መናገር ይቻላል።
ወያኔ/ሕወሓት ዛሬ ላይ የተቀመጠባትን ወንበር ለመያዝ በአደረገው እልህ አስጨራሽ የበርሃ ትግል ምንም አይነት መሪና ታጋይ ሳይሞት፣ ሳይማረክና ሳይነጠቁ ከዚህ እንዳልደረሱ እንሱ ጠንቅቀው ያውቁታል። ማንን መቼና እንዴት በትግል ጊዜ እንደተለያቸው በሚገባ ያስታውሱታል። እራሳቸውም ቢሆን ሥልጣን ይጋፋል ብለው የሚያስብትን ታጋይ ማስወገዳቸውም የማይረሳ ገሀዳዊ እውነታ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ እያወቀ  እንዳላዋቂ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ፣ አይቶ እንዳላየ ዝም ሲላቸው  ሰማዕታት ዘካሪ ነን ሲሉም ይሰማሉ።
መሪን በመግደልም ሆነ በማሰቃየት ትግልን ማስቆም አይቻልም። እውነተኛ ትግል፣ የለውጥ ትግል፣ የነጻነት ትግል፣ የሰላም ትግል፣ የመብት ትግልና ትግሉ ዲሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን መገንባትና ማየት እስከሆነ  ድረስ ትግሉ ይበልጥ ይቀጥላል እንጂ በአንዳርጋቸው ምክንያት ትግሉ ይቆማል ብሎ ማሰብ ታሪክን እና የትግልን ጸባይ እንደአለማወቅ ይቆጠራል። ትግል እጅግ እልህ አስጨራሽ ጉዞ ነው፤ ያሰቃያል፣ ውጣውረዱ ከባድ ነው፤ መውጣት መውረዱ አድካሚና አሰልቺ ነው፤ ነገር ግን ተስፋ እስካልቆረጡ ድረስ ለዓላማ፣ ለራዕይና ለእውነተኛ ሀገራዊ ተልኮ እስከታገሉ  ድረስ ለውጥ ይመጣል። ይህም አንዱ የለውጥ ምልክት ነውና።
እኔ ግንቦት ሰባት ብሆን፦ በአንዳርጋቸው መያዝ፣ መታሰር፣ መገደልም ቢሆን ኩራት ይሰማኛል እንጂ ፍራትና ሀፍረት አይሰማኝም። ትግሌን ወደፊት አንድ እርምጃ አስኬዳለሁ እንጂ ከትግሌ ወደኋላ ለአፍታም ቢሆን አልገታም። ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ታጥቄ እነሳለሁ እንጂ ትጥቄን አላወልቅም፣ የሀገር ፍቅር፣ የሀገር ስሜት፣ ለፍትህና ለነጻነት የምሰጠው ቦታ ይበልጥ ታላቅና ጽዕኑ ይሆንልኛል። ኢትዮጵያዊ ማንነቴን እንድረዳ በር ይከፍትልኛል። አንዳርጋቸው ለምን እራሱን አሳልፎ ሰጠ ብዬ እንድጠይቅና መልሱም ዲሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚለው ለእኔ ብርታት፣ ጽናትና ጥንካሬ ይሆነኛል። አንዳርጋቸው ቢያልፍ ሺ አንዳርጋቸው መተካት ይችላሉ ተተክተዋልም፤ አንዷለም ቢታሰር ሺ አንዳለሞች አሉ፤ እስክንድር ቢታሰር ሺ እስክንድሮች ብዕራቸውን አንስተዋል፤ እርዮት ብትታሰር ሺ እርዮቶች የጋዜጠይነትን ሙያ ተቀላቅለዋልና።
 እኔ ግንቦት 7 ብሆን፦ ለንቅናቄው ዓላማ፣ ራዕይና ተልኮ እንድፋጠን ያደርገኛል እንጂ ምንም አይነት ድካም አይሰማኝም። የአንዳርጋቸው መያዝ የወያኔን ፍራትና ጭንቀት ተመልክቸበታለሁና።
እኔ ግንቦት 7 ብሆን፦ ውጤት ተኮር የሆነ ዘላቂ የትግል ስልት በመንደፍ ትግሌን ይበልጥ አጠንክሬ እንድጓዝና እንድከተል ያደርገኛል እንጂ ትግሌ አይቆምም። የወያኔ ባለ ራዕይ መሪ ተብዬው(መለስ) ሲያልፍ ፓርቲው እንዳላቆመ ሁሉ የግንቦት 7 ትግልም ይበልጥ ክብሪት ተለኩሳል። የትግል ስልቴም እንዴት፣ የት፣ መቼና በማን ..........................
እኔ ግንቦት 7 ብሆን፦ ስለየመን እና ስለ ወያኔ በማውራትና በመዛት ጊዜ አላጠፋም፤ ምክንያቱም ከሁለቱም የአገር መሪዎች መልካም ነገር አልጠብቅምና። እንዲሁም ስለ ብርታኒያ በማውራት ጊዜ አላጠፋም። ምዕራባውያን የኢትዮጵያን አንድነትና መረጋጋት አይፈልጉትምና። ነጻነቴን በእራሴ እንጂ ሌላ ሰው ሊያስከብርልኝ እንደማይችል ጠንቅቄ አውቃለሁና።
እኔ ግንቦት 7 ብሆን፦ እንደ ታላቁ የነጻነት መሪ ኔልሰን ማንዴላ ለይቅርታ፣ ለፍቅር፣ ለሰላም፣ ለነጻነትና ለፍትህ የፈጠንኩና የቆምኩ፤ ለበቀል የዘገየሁ በመሆን የአንዳርጋቸውን ራዕይና ዓላማ ከግብ ለማድረስ ሌት ከቀን እታገላለሁ እንጂ በቀልተኛ አልሆንም።
እኔ ግንቦት 7 ብሆን......................................

ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም እንደሚባለው ሞት ፈርቶ ትግል የለም!ነጻነት የለም! ፍትህ የለም! ዲሞክራሲ የለም!
መሪን በማሰርም ሆነ በመግደል ትግልን ማስቆም አይቻልም!!!