Saturday, November 30, 2013

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ታቦተ ጽዮን

                                                    በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

እግዚአብሔር አምላክ ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ካወጣቸው በኋላ የአምልኮ ሥርዐታትን ይፈጽሙበት ዘንድ የምስክሩን ድንኳን፣ የቃል ኪዳኗ ታቦትንና ለአምልኮ ሥርዐቱ ማከናወኛ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳትን እንዲሠሩ በሙሴ በኩል ታዘው ነበር፡፡ ከቃል ኪዳኗ ታቦት ውስጥም በእግዚአብሔር ጣት ዐሥርቱ ትእዛዛት የተጻፉበት የሕጉ ጽላት፣ አርባ ዓመት ሙሉ እስራኤላውያን በሲና ምድረ በዳ የተመገቡትን መና የያዘች መሶበ-ወርቅ፣ አሮን ለክህነት አገልግሎት ስለመመረጡ ምስክር የሆነችው ለምልማና ፍሬ አፍርታ የተገኘችው የአሮን በትር ይገኙባታል፡፡(ዕብ.9፡4)
ታቦተ ጽዮን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትመሰላለች፡፡ ይህን ለመረዳት ግን ስለ ታቦተ ጽዮን አሠራርና መንፈሳዊ ትርጉም አስቀድመን ልንረዳ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ታቦተ ጽዮንን እንዲሠራ ብልሃትን፣ ጥበብን፣ ማስተዋልን፣ ዕውቀትን ይለይ ዘንድ መንፈሱን ያሳደረበትን ከይሁዳ ወገን የሆነውን ባስልኤልን መረጠ ፡፡(ዘፀ.25፡9) እርሱም እግዚአብሔር በሰጠው ማስተዋል ከማይነቅዝ እንጨት ርዝመቷ ሁለት ክንድ ተኩል፤ ወርዱዋም አንድ ክንድ ተኩል፣ ቁመቷም አንድ ክንድ ተኩል እንዲኖራት አድርጎ ታቦቷን ሠራት፡፡ በመቀጠል በውስጥም በውጪም በጥሩ ወርቅ ለበጣት፣ ከታቦቷም ዙሪያ የወርቅ አክሊልን አደረገላት፡፡ ካህናት ታቦተ ጽዮንን ለመሸከም እንዲረዳቸውም በአራቱም መዓዘናት በወርቅ የተሠሩ ቀለበቶችንና በእነርሱም ውስጥ የሚገቡ ሁለት መሎጊያዎችን ሠራ፡፡ ከጥሩ ወርቅም የስርየት መክደኛውን በቃል ኪዳን ታቦቷ ላይ በርዝመቷና በወርደዋ ልክ ሠራ፡፡ የስርየት መክደኛውን እንዲጋርዱት አድርጎም ጥሩ ከሆነ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ኪሩቤልን ሠራ፤ በስርየት መክደኛው ግራና ቀኝም አደረጋቸው፡፡ እነዚህ በጥሩ ወርቅ የተሠሩት ሁለቱ ኪሩቤል ፊታቸው ወደ ስርየት መክደኛው ሆኖ እርስ በእርሳቸው የሚተያዩ ተደርገው የተሠሩ ናቸው ፡፡ በዚህ በስርየት መክደኛው በሁለቱ ኪሩቤል መካከል እግዚአብሔር ለሙሴ በመገለጥ ሰው ከባልንጀራው እንደሚነጋገር ያነጋግረው ነበር፤ ለሕዝቡ በደመና አምድ ይታያቸው ነበር፡፡(ዘፀ.25፡22፤33፡8-11)
ወደ ትርጓሜው ስንመጣ ታቦተ ጽዮን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ስትሆን፣ በውስጡዋ የያዘችው የሕጉ ጽላት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ታቦቷ ከማይነቅዝ እንጨት መሠራቷ የጌታን እናት ንጽሕናን የሚያመለክት ሲሆን በውጪም በውስጧም በጥሩ ወርቅ መለበጡዋ የቅድስናዋና ድንግል በሕሊና ወድንግል በሥጋ መሆኗን የሚያስረዳን ነው፡፡ ታቦቷን አራት ሌዋውያን ካህናት ይሸከሟት ዘንድ በግራና በቀን በተዘጋጁ አራት ከወርቅ የተሠሩ ቀለበቶች ሲኖሩአት፤ በነዚያ የወርቅ ቀለበቶች ውስጥ ሁለት መሎጊያዎች ይገቡባቸዋል፡፡ ታቦተ ጽዮንን ለማንቀሳቀስ ሲፈለግ አራት ካህናት በመሎጊያዎቹ ይሸከሟታል፡፡ይህ ሥርዐት በሰማያትም የሚታይ እውነታ ነው፡፡ የጌታን መንበር ገጸ ንሥር፣ ገጸ ሰብእ፣ ገጸ ላህም፣ ገጸ አንበሳ ያላቸው አርባዕቱ እንስሳት ይሸከሙታል፡፡(ኢሳ.6፡1-5፤ ሕዝ.1፡1-16) እንዲሁም ለአማናዊቷ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያም “የምስራች የሚናገሩ፣ ሰላምንም የሚያወሩ፣ የመልካምንም ወሬ፣ መድኃኒትንም የሚያወሩ፣ ጽዮንንም አምላክሽ ነግሦአል የሚሉ እግሮቻቸው በተራሮች ላይ እጅግ ያማሩ ናቸው” የተባለላቸው የእርሱዋንና የጌታችን ስም ተሸክመው የሚሰብኩ ወንጌላውያን አሏት፡፡(ኢሳ.52፡7)የስርየት መክደኛው ታቹ መቀመጫው ንጹሐን አንስት ላዩ መክደኛው የንጹሐን አበው ግራና ቀኙ የወላጆቹዋ የሐናና የኢያቄም ምሳሌ ነው፡፡ እርሱን በክንፎቻቸው የጋረዱት ኪሩቤል የጠባቂ መልአክ ቅዱስ ሚካኤልና የአብሣሪው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ምሳሌዎች ናቸው፡፡

የስርየት መክደኛው ስርየቱ የሚፈጸምበት ስፍራ ነው፡፡ ነገር ግን እውነታውን ስንመለከት በዚህ ቦታ ምንም ዓይነት መሥዋዕት ሲቀርብ እንዳልነበር እንረዳለን፡፡ ይህም በጊዜው አማናዊው መሥዋዕት ገና እንዳልተሠዋ ያስገነዝበናል፡፡ ይህ ስፍራ እግዚአብሔር ለሙሴ የሚገለጥበት ቦታ ነው፤ ከእርሱ ውጪ ሌላ ነገር በእዚያ ላይ ማረፍ የለበትም፡፡ ይህ በራሱ የሚሰጠን አንድ ማስተዋል አለ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን ሊፈጽም ሰው በሆነ ጊዜ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብበት ልዩ ስፍራ እንዳለ ያመላክተናል፡፡ ስለዚህም ይህ ስፍራ ለዚህ እንደተጠበቀ ወይም በዚህ ምሳሌ አማናዊ መሥዋዕት የሚቀርብበት ሥፍራ እንደሚያስፈልግ የሚያሳስብ ነው፡፡ ይህ እንደሆነ ለማመልከት ሲባል ለኃጢአት የቀረበው መሥዋዕት ከታረደ በኋላ ካህኑ ደሙን በጣቱ በመንከር ሰባት ጊዜ በስርየት መክደኛው አንጻር በመገናኛ ድንኳን ውስጥ ይረጨው ነበር፡፡(ዘሌዋ.4፡6) ነገር ግን ይህ ደም ከዚያ ስርየት መክደኛው ላይ አያርፍም ነበር ምክንያቱም በዚህ ስፍራ መቅረብ ያለበት መሥዋዕት መለኮት የተዋሐደው ነፍስ ግን የተለየው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ሥጋውና ቅዱስ ደሙ ነውና፡፡

ይህ የስርየት መክደኛ ሌላም ለእኛ የሚያስተላለፈው መልእክት አለው፡፡ መልእክቱም አማናዊው መሥዋዕት መቅረቡ እንደማይቀርና፣ መሥዋዕቱ የሚቀርብበት ስፍራ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ሆኖ እግዚአብሔር በምህረት በሚገለጥበት በጸጋ ዙፋኑ በጽላቱ ላይ መሆን እንዳለበት ነው፡፡(ዕብ.4፡16) በዚህም እግዚአብሔር አምላክ በነቢዩ ሚልክያስ “ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና በየስፍራውም ስለስሜ ዕጣንን ያጥናሉ ንጹሕም ቁርባን ያቀርባሉ”(ሚል.1፡11) እንዳለው የስርየት መክደኛው በዓለም ዙሪያ ላለችው አንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን ምሥጢረ ቁርባንን ለምትፈጽምበት ጽላት ወይም ታቦት ምሳሌ መሆኑን ያሳየናል፡፡ በሐዲስ ኪዳን ጽላቱ(ታቦቱ) የሚያርፍበት ስፍራ መንበር ተብሎ ሲጠራ የእግዚአብሔር ስም የተጻፈበትና ቅዱስ ሥጋው ክቡር ደሙ የሚፈተትበት ደግሞ ጽላት ወይም ታቦት ወይም መሠዊያ ተብሎ ይጠራል፡፡

የስርየት መክደኛው በታቦቱ አናት ላይ መሆኑም ቅዱስ ኤፍሬም “ የእኛን ሥጋ ለነሣኸውና ፣ መልሰህ ለእኛ ለሰጠኸን ፣ ለአንተ ክብር ምስጋና ይሁን ፡፡ ከእኛ በሆነው ሥጋህ በኩል እጅግ የበዛውን የአንተን ስጦታ ተቀበልን፡፡” ብሎ እንዳመሰገነ፤ እግዚአብሔር ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረቡን ያሳየናል፡፡ የስርየት መክደኛውን የሚጋርዱት በጥሩ ወርቅ የተሠሩት የኪሩቤል ምስሎችም አማናዊው መሥዋዕት በሚሠዋበት ጊዜ በዙሪያው ረበው የሚገኙ የመላእክት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ይህን ለማስገንዘብ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በመንበረ ታቦቱ ላይ ምስለ ፍቁር ወልዳ እንዲቀመጥ ታዝዛለች፡፡ ምስለ ፍቁር ወልዳን ላስተዋለ ሰው በትክክል የታቦተ ጽዮንን መንፈሳዊ ትርጉምን ይረዳል፡፡

ይህን ድንቅ የሆነ መንፈሳዊ ትርጉምን ይበልጥ ለመረዳት አንድ ምሳሌ የሚሆነንን እውነታ እንመልከት፡፡ ንጉሥ ዳዊት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑ ታቦት ከአቢዳር ቤት ወደ ጽዮን ከተማ ባስመጣበት ጊዜ በታቦተ ጽዮን ፊት ለእግዚአብሔር በሙሉ ኃይሉ በደስታ እየዘለለ መንፈሳዊ መዝሙርን አቅርቦ ነበር ፡፡(2ሳሙ.6፡12-17) ይህን ዓይነት ተመሳሳይ ድርጊት በሐዲስ ኪዳንም ተፈጽሞል ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድስት ኤልሳቤጥን በተሳለመቻት ጊዜ የስድስት ወር ፅንስ የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የጌታችንን እናት የሰላምታ ድምፅ በሰማ ጊዜ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ከእናቱ ማኅፀን ውስጥ ሳለ በደስታ ዘሎአል(ሰግዶአል)፡፡ (ሉቃ.1፡44) ቅዱስ ዳዊት በታቦተ ጽዮን ፊት እንዲያ ደስ መሰኘቱና ለአምላኩ የምስጋና ቅኔን መቀኘቱ ለሰው ልጆች ሁሉ የመዳናቸው ምክንያት የሆነችውን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጁዋን ኢየሱስ ክርስቶስን በታቦተ ጽዮን በኩል በማየቱ ነበር፡፡

ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን አባቶችም ይህንን እውነታ ይጋሩታል ፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ኤፍሬም፡- “ከአዳም ጎን በተገኘችው አንዲት አጥንት ምክንያት ሰይጣን ከአዳም ማስተዋልን አራቀ፡፡ ነገር ግን ከእርሱ አብራክ በተገኘችው በቅድስት ድንግል ማርያም ምክንያት በእርሱ ላይ ሠልጥኖ የነበረው ሰይጣን እንደ ዳጎን ተሰባብሮ ወደቀ፡፡ ታቦተ ጽዮን በተባለችው በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ውስጥ ባደረው በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የድል አዋጅ ታወጀ ፡፡ በቃል ኪዳኑዋ ታቦት ሥር ዳጎን ተሰባብሮ እንደተገኘ እንዲሁ ክፉው ሰይጣን በታመኑበት ፊት ድል ተነሳ፡፡ እግዚአብሔር በቃል ኪዳኗ ታቦት ኃይሉን በመግለጥ ዳጎንን ሰባብሮ እንደጣለው እንዲሁ እግዚአብሔር ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ በመወለድ በኃጢአት ምክንያት በእኛ ላይ ሠልጥኖ የነበረውን ሰይጣንን ድል ነሳው፡፡” (1ሳሙ.5፤6) ሲል ቅዱስ ጀሮም ደግሞ “ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድስትና ንጽሕት ነበረች፡፡ በቃል ኪዳኗ ታቦት ውስጥ የሕጉ ጽላት ብቻ እንደነበር እንዲሁ እርሷም በሕሊናዋ ከእግዚአብሔር ሕግጋት ውጪ ሌላ ምንም ሃሳብ አልነበራትም፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም በውስጥም በውጪም ነውር የሌለባት ንጽሕት ናት፡፡ እንደ ቃል ኪዳኗ ታቦት በውጪም በውስጥም በቅድስና የተጌጠችና ሕጉንም ጠብቃ የተገኘች የክርስቶስ ሙሽራ ናት ፡፡ በቃል ኪዳን ታቦቱ ውስጥ ከሕጉ ፅላት ውጪ ሌላ ምንም ነገር እንደሌለ እንዲሁ አንቺም ቅድስት ሆይ በሕሊናሽ ምንም ነውር የሌለብሽ ቅድስት ነሽ፡፡” ብሎ ሲያመሰግናት፤ የእስክንድርያው ዲዮናስዮስ ደግሞ “ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካህን ይሆን ዘንድ በሰው እንዳልተመረጠ እንዲሁ ቅድስት ድንግል ማርያም የጌታ ማደሪያ ትሆን ዘንድ በእግዚአብሔር የተመረጠችና በመንፈስ ቅዱስ ለእርሱ ማደሪያነት የተዘጋጀች ናት፡፡ የመለኮት ማደሪያ ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር የከተመባት ከተማ ሆና ትኖር ዘንድ ለዘለዓለም በእግዚአብሔር ታትማለች” በማለት ስለእርሱዋ ይመሰክራል፡፡

አዳም ድኅነቱ ከሴት ወገን በሆነች በቅድስት ድንግል ማርያም በኩል እንደሆነ ተረድቶ ለሚስቱ “ሔዋን” ብሎ ስም እንደሰጣት እንዲሁ ንጉሥ ዳዊት በቅድስት ድንግል ማርያም በኩል እንደሚድን በመረዳቱ አምባዬና መጠጊያዬ ነሽ ሲላት “ጽዮን” ብሎ ለድንግል ስያሜን እንደሰጣት በመዝሙራቱ ማስተዋል እንችላለን፡፡ጽዮን የንጉሥ ዳዊት ተራራማዋ ከተማ ስትሆን፣ የስሟ ትርጓሜ አምባ፣ መጠጊያ ማለት ነው፡፡ ይህን ይዘው ብዙዎች ነቢያት ስለድንግል ሲናገሩ ጽዮን የሚለውን ስም ተጠቅመዋል፡፡

ነቢያት ስለቅድስት ድንግል ማርያም ሲናገሩ ጽዮን የሚለውን ስም እንደሚጠቀሙ ወደ ብሉይ ኪዳን ሳንገባ በሐዲስ ኪዳን ብቻ ስለ ጽዮን የተጻፉትን በማንሣት ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ኢሳይያስ ከአይሁድ ወገን የሆኑ የራሳቸውን ሥርዐትና ሕግ ለማቆም ሲሉ በክርስቶስ ከማመን ስለተመለሱት ሲጽፍ፡- “እነሆ በጽዮን የእንቅፋት ድንጋይና የማሰናከያ አለት አኖራለሁ”(ኢሳ28፡16፣8፡14) አለ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ስለክርስቶስ የተነገረ ነው በማለት በሮሜ 9፡33 ላይ ጠቅሶት እናገኛለን፡፡ስለዚህም ነቢዩ ኢሳይያስና ቅዱስ ጳውሎስ ጽዮን ያሏት ቅድስት ድንግል ማርያምን እንደሆነ በዚህ ኃይለ ቃል መረዳት እንችላለን፡፡ የማሰናከያ አለት የተባለው ክርስቶስ እንደሆነም “እነሆ የብዙዎች ልብ ሐሳብ ይገለጥ ዘንድ ይህ ለእስራኤል ላሉት ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፡፡”(ሉቃ.2፡34-35) ተብሎ ተጽፎአል፡፡ ስለዚህ የማሰናከያ አለት የተባለውን ክርስቶስን ፀንሳ የወለደችው ቅድስት ድንግል ማርያም ጽዮን መባሉዋን በእነዚህ ጥቅሶች ማረጋገጥ እንችላለን፡፡

ነቢዩ ዳዊትና ኢሳይያስ ጽዮን ከተሰኘች የሙሴ ፅላት ካህኑ በሚያቀርበው መሥዋዕት አማካኝነት አፋዊ ድኅነት እንደተደረገ፣ ከእመቤታችን ከተወለደው አማኑኤል አማናዊ ድኅነት እንዲፈጸምልን“መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል ከያዕቆብም ኃጢአተኝነትን ያስወግዳል”(መዝ.13፡10፤ኢሳ.59፡20) በማለት ስለክርስቶስ ትንቢትን ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ ለጌታችን ለመድኃኒታችን ሰጥቶ በሮሜ.11፡26 ላይ ተጠቅሞበታል፡፡ በዚህም ቦታ ጽዮን ያሏት ቅድስት ድንግል ማርያምን መሆኑን ማስተዋል እንችላለን፡፡ ምክንያቱም እርሱ ከእርሱዋ እንጂ ከሌላ አልተወለደምና፡፡ ነገር ግን “መድኃኒት” የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመሆኑ “መልአኩም እንዲህ አላቸው፡-እነሆ ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁ በዳዊት ከተማ መድኅኒት እርሱ ክርስቶስ ተወለደ” (ሉቃ.2፡10)በማለት ገልጾልናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢየሱስ ማለት “መድኃኒት ማለት ነው (ማቴ.1፡21) የኢየሱስም እናት ደግሞ ቅድስት ድንግል ማርያም መሆኑዋን ማንም የማይክደው ሐቅ ነው፡፡ ስለዚህም ነቢያቱ “መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል” ሲሉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽዮን ከተባለችው ከቅድስት ድንግል ማርያም ይወለዳል ማለታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡

ምንም እንኳ ቅዱስ ዳዊትና ሌሎች ነቢያት ስለቅድስት ድንግል ማርያም ለመናገር ሲሉ ጽዮን የሚለውን ስም አብዝተው ይጠቀሙ እንጂ አልፎ አልፎ ግን ጽዮን በማለት ስለ ከተማዋ ተናግረው እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ ሚክያስ “ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ጽዮን ትታረሳለች”(ሚክ.3፡12)ይላል፡፡ ይህ በቀጥታ ስለጽዮን ከተማ የተነገረ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለጌታችን መናገር ሲፈልግ ስለእርሱ የሚናገሩትን ብቻ መርጦ እንደተጠቀመ እንመለከታለን፡፡ እኛም እንዲሁ ለቅድስት ድንግል ማርያም የተነገሩትን አስተውለን ልንለያቸው ይጠበቅብናል፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ስለቅድስት ድንግል ማርያም ያልተጻፉ ነገር ግን ጽዮን የሚለውን ስም ይዘው የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት አሉና፡፡ ቢሆንም ስለታቦተ ጽዮን የተጻፉ ገቢረ ተአምራት ሁሉ እግዚአብሔር ቃል ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለዶ ለፈጸማቸው ታላላቅ የድኅነት ሥራዎች ምሳሌዎች ናቸው፡፡

በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በብሉይ ኪዳን በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙትን ገቢረ ተአምራት ለድንግል ማርያምና ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በመስጠት ተርጉማ ለልጆቹዋ ታስተምራለች፡፡ በኅዳር 21 ቀንም በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙት ታላላቅ ተአምራት የሚታሰቡበት ቀን ነው፡፡ በዚህ ቀን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙትን ታላላቅ ተአምራት እግዚአብሔር ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ በመወለድ ከፈጸማቸው ታላላቅ የድኅነት ሥራዎች ጋር በማነጻጸር በድኅነታችን ውስጥ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ድርሻ ምን እንደሆነ ትገልጻለች፡፡ ለምሳሌ ታቦተ ጽዮንን የተሸከሙ ካህናት እግራቸው የዮርዳኖስን ባሕር በመንካቱ ባሕሩ ለሁለት እንደተከፈለ እንዲሁ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ተወልዶ ጥምቀትን በራሱ ጥምቀት በመመሥረት ከሰይጣን ባርነት ወደ እግዚአብሔር ልጅነት እንዳሸጋገረን እናወሳበታለን(ኢያ.3፤ ማቴ.3፡13-17) ፡፡ ፍልስጥዬማውያን ከእስራኤላውያን ጋር ውጊያ በገጠሙ ወቅት ታቦተ ጽዮንን ማርከዋት ዳጎን በሚባለው ቤተ ጣዖታቸው ውስጥ አኑረዋት ነበር፡፡ ነገር ግን ታቦቷ ዳጎኑን በፊቷ ሰባብራ እንደጣለችው እንዲሁ ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደው በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ ሠልጥኖ የነበረው ሰይጣን ድል መነሳቱን እናወሳበታለን፡፡ ((1ሳሙ.5፤6)

በዚህ መልክ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መንጎቹዋን ስለቅድስት ድንግል ማርያምና ስለልጁዋ ስለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም በእርሱ ስለተሰጠን ሰማያዊ የአገልግሎት ሥርዐት፣ ስለታቦት ጥቅምና አገልግሎት፤ ታቦተ ጽዮንንና ቅድስት ድንግል ማርያምን በማነጻጸር በሰፊው እንደምታስተምር መረዳት እንችላለን ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤትና በረከት ያሳትፈን፡፡ የእግዚአብሔር አብ ጸጋ የእግዚአብሔር ወልድ ቸርነት የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት በእኛ ላይ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኑር አሜን!!



ምንጭ፦  ማኅበረ ቅዱሳን ድኅረ ገጽ




Monday, November 25, 2013

ቅኔአዊ ግጥም የሳዑዲን ግፍና በደል አስመልክቶ

          (በሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)saudi and ethiopians

እንዲህ እንዲያ ብለው አሙን ፤ ተጠይቀው ሲመልሱ
የወገኖቻችንን ደም ፤ በእብደት ግፍ ያፈሰሱ
የኢትዮጵያ ስደተኞች ፤ ባሕላችንን ተቃረኑ
ንጽሐችንን አረከሱ ፤ ነፍሳችንን አስኮነኑ
መጠጥ በማዘዋወር ፤ በስርቆት ወንጀል በምኑ
አንተ አረመኔ እንስሳ ፤ ምኑን ብየ ላውጣልህ ስም
መጠጥ ምንህ ነውና ፤ ስካርህ የአንተ በሰው ደም
አስገድዳ አልደፈረችህ ፤ ደፈርካት እንጅ በማደም
መድፈርህ ሳያንስ ሳይበቃ ፤ አርደህ በላሃት ርጉም
አንተ ውሉደ አጋንንት ፤ አረመኔ ዘረ ሰዶም ፡፡
    ሌቦች ነበረ ያልካቸው ? እሰይ እንኳንም ሰረቁ
    ፈልገውት እንዳይመስልህ ፤ ምንም ነገር አይደል ድንቁ
    እባክህ ለከት ይኑርህ ፤ በዚህ አይታማም ወገኔ
    ነቢይህ ያውራህ ታሪኩን ፤ ያበሻን ማንነት ብያኔ
    የፍትሕ ደግነት ባለቤት ፤ ሕዝብ እንደሆነ መናኔ
    ነገር ግን እንዲያ ማድረጉ ፤ ሲያደርግ ባላይም በዓይኔ
    የሚነግርህ ስለነበረ ፤ መንገሩ ነበር በቅኔ
    በቋንቋው ጸጋ በዘይቤ ፤ በሰምና ወርቅ ምጣኔ ፡፡
ሐበሻ እንደዚህ ማስኖ ፤ የመከራ ዓይነት ለመጋቱ
ሞት በመንገዱ እየበላው ፤ አሁንም ለስደት መትጋቱ
ውዲቷ ሀገሩን እንደጠላ ፤ እየጣለለት መውጣቱ
ቅድስቲቱን እናት ሀገር ፤ ያረገብንን ያሳር ጓዳ
ለዜጎች ሲዖል ገሃነም ፤ ምቾት የሞላት ለእንግዳ
ሀገር ወገንን አውድሞ ፤ ተግቶ የሚሠራ ለባዳ
ይሄንን ቅጥረኛ መንግሥት ፤ ለጠላት ያደረን ባንዳ
ወልዳቹህ በማሳደግም ፤ ለዚህ ያበቃቹህት ይሁዳ
እናንተው ስለሆናቹህ ፤ የታሪኩ ሀሁ ሠሌዳ
ምሰሶው ወራጅ ማገሩ ፤ መሠረቱና ግድግዳ
ለችግራችን ተጠያቂ ፤ የምስቅልቅሉ ባለዕዳ
እናንተው መሆናቹህን ፤ ሊጠቁምና ሊያስረዳ
ያለንበትን ስንክ አሳር ፤ አውጥቶ ሊያሳይ ከሜዳ
ለማድረግ ነበረ እንጅ ፤ ከቶም አልነበር ሊጎዳ
መናኛ ነገርን ወስዶ ፤ ሊጠቀም ሊሆነው ጋዳ
እናንት በምቾት በቅንጦት ፤ እየኖራቹህ በተድላ
በሠራቹህት ሸር ክፋት ፤ እሱ መዋጡን ባሜኬላ
የስሕተታቹህን ርቀት ፤ የክብደቱንም ልክ ጣራ
ትኩረታቹህን በማግኘት ፤ ሊያሳውቅ እንጅ ያን ዳራ
አነፃፅራቹህ እንድታዩት ፤ በግብረገባዊ ተዋስኦ
በእምነታቹህ ሚዛን ልክ ፤ እንድትለኩት ያለ አድልኦ
ለማድረግ ነበረ እንጅ ፤ ከቶም አይደለም የአመል
የእውነት ምስክር አለን ፤ ከፈላስፋ እስከ አምላክ ቃል ፡፡
    የልቅ ማሰብ ያለባቹህ ፤ ለዚህ ለዚያ ሁሉ ሴራ
    ሀገራችንን ለማፍረስ ፤ ላረጋቹህት ስርሠራ
    ብትከፍሉ የማትጨርሱት ፤ አለባቹህና ብዙ ዕዳ
    ከቶ እንዴት ትሆናላቹህ ፤ አስቡበት አለው ፍዳ
    ይብላኝ ለእናንተ እንጅ ፤ እኔስ አለኝ ሀገር የእርሻ
   ጊዜአዊ ነው የኔ ችግር ፤ ለነገ አለኝ መፈወሻ
   መግቢያ አላጣም እኔ እንዳንተ ፤ አልነቀል መጨረሻ ፡፡
አርቃቹህ ብታስቡ ፤ መኖሪያቹህ ምድረበዳ
እህል ዘርቶ የማያበቅል ፤ የማያቆም አገዳ
አሁን ነገ ላይ ተሟጦ ፤ በሚያልቀው ዘይት ታብዮ
እንዲህ በግፍ ላይ መጫወት ፤ ፍርጃህ ነው የልቅ በል ወዮ
ሐምሳ ዓመታት ለማይቆየው ፤ አቤት ስንቱ ተደረገ
ደጅህ ላይ አለ ጠብቀው ፤ ይነቅልሀል ስደት ነገ
ዘይትህን ሲጨርስ መሬቱ ፤ ሌላ የለው የተነፈገ
ወዴት ይሆን መሰደጃህ ፤ ጎረቤትህ ከመሸገ
ጠላት አርገህ ካቆየኸው ፤ ፊትህን ማየት ካልፈለገ ፡፡
ላለው ሆኖልህ ነገሩ ፤ ዛሬ ላንተ ያደገደገ
ነገ አጠገብህ አይኖርም ፤ በሩን ይዘጋል እያሸገ
ያው በተራህ ትቆጥራለህ ፤ በየዓይነቱ ግፍ ወፍዳ
የዘሩትን ማጨድ አይቀር ፤ አጥቶ መውጫ ቀዳዳ
ወገን ንቃ ይግባህ ሴራው ፤ እኛን ማጥፋት የፈለጉት
እርስ በርስህ እያፋጁ ፤ አስቀምጠው ባንዳ መንግሥት
ሀገርህን ለመውረስ ነው ፤ ሲነጥፍባቸው ሲሳይ ሀብት ፡፡
    ብዙ ነው ሴራው ትብትቡ ፤  ምኞታቸውን ለማስመር
    እግዜርን ይዘህ ታገለው ፤ ሳትከፋፈል በብሔር
    ወጥመዱ ይከሽፋል ሴራው ፤ ይወድቁበታል ለአሳር
    የአንተ ቀን ደግሞ ይመጣል ፤ ይኖርህማል አኩሪ ሀገር ፡፡

Wednesday, November 20, 2013

ቅዱስ ሚካኤል

                        (በመልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው)

 ፩፦ ድርሳን ዘቅዱስ ሚካኤል
 ቅዱስ ማለት ልዩ፥ ክቡር ማለት ነው፤ ሚካኤል ማለት ደግሞ «መኑ ከመ አምላክ፥ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማነው?» ማለት ነው። ሚካኤል የሚለው ስም ቃሉ የዕብራይስጥ ነው፤ ሚ - የሚለው «መኑ» ማለት ነው፥ ካ - የሚለው «ከመ» ማለት ሲሆን፥ ኤል - ማለት ደግሞ «አምላክ» ማለት ነው። ይህን ማለትም የቅዱስ ሚካኤልን ስም በጠራን ቊጥር የምንመሰክረው ስለ እግዚአብሔር ነው፤ በመሆኑም እግዚአብሔርን በባሕርይ የሚመስለው፥ በሥልጣንም የሚተካከለው፥ በምድርም በሰማይም እንደሌለ የሚናገር ልዩ፥ ክቡር ስም ነው። የነቢያት አለቃ ሙሴ ባሕረ ኤርትራን ለሁለት ከፍሎ ሕዝቡን ያሻገረለትንና ፈርዖንን ከነሠራዊቱ ያሰጠመለትን አምላክ እግዚአብሔርን በመዝሙር ሲያመሰግን፥ «አቤቱ በአማልክት መካከል (በስም አማልክት ከሚባሉ፥ በስመ አማልክት ከሚጠሩ፥ አንድም አማልክት ዘበጸጋ ከተባሉ ከነቢያት ከካህናት መካከል) አንተን የሚመስል ማነው? በቅዱሳንም ዘንድ እንደ አንተ የከበረ ማነው?» ብሏል። ዘጸ ፲፭፥፲፩። ቅዱስ ዳዊትም፦ «አቤቱ፥ ከአማልክት የሚመስልህ የለም፤» ብሏል። መዝ ፹፭፥፰።


፩፥፩፦ «ስሜ ድንቅ ነውና ለምን ትጠይቃለህ?» መሳ ፲፫፥፲፯
የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ በመሥራታቸው፥ እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን እጅ ለአርባ ዓመት አሳልፎ ሰጥቷቸው ነበር.። በዚህ ዘመን ከዳን ወገን ማኑሄ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፥ ሚስቱም መካን ስለነበረች ልጅ አልወለደችም ነበር። የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ እንደምትፀንስ፥ ወንድ ልጅም እንደምትወልድ፥ ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ እንደሚሆን ነገራት። የሚያሰክር መጠጥ እንዳትጠጣ፥ የረከሰም ነገር እንዳትበላ፥ በልጁም ራስ ላይ ምላጭ እንዳይደርስ (ፀጉሩን እንዳትላጨው) አስጠነቀቃት። እርሷም ተመልሳ የሆነውን ሁሉ ለባሏ ነገረችው፤ «የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኔ መጣ፥ መልኩም እንደ እግዚአብሔር መልአክ እጅግ የሚያስደነግጥ ነበረ፤ ከወዴትም እንደመጣ ጠየቅሁት፥ እርሱም ስሙን አልነገረኝም፤» አለችው።
ማኑሄም፥ «ጌታ ሆይ፥ ወደ እኛ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው እባክህ እንደገና ወደ እኛ ይምጣ፤ ለሚወለደውም ልጅ ምን እንደምናደርግ ያስገንዝበን፤» ብሎ ወደ እግዚአብሔር ለመነ። እግዚአብሔርም የማኑሄን ቃል ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ በእርሻ ውስጥ ሳለች እንደገና ወደ ሴቲቱ መጣ፥ እርሷም ፈጥና ባሏን ጠራችው፥ «እነሆ፥ አስቀድሞ ወደ እኔ የመጣው ያ ሰው ደግሞ ተገለጠልኝ፤» ብላ ነገረችው። እርሱም፦ «ከሚስቴ ጋር የተነጋገርህ አንተ ነህን?» ብሎ ቢጠይቀው «እኔ ነኝ፤» ሲል መለሰለት። ማኑሄም፦ «እነሆ ቃልህ በደረሰ ጊዜ የልጁ ነገር፥ ግብሩስ ምንድነው?» ብሎ ዳግመኛ ጠየቀ። መልአኩም ለሴቲቱ ነግሯት የነበረውን ሁሉ መልሶ ነገረው። ማኑሄ ለመልአኩ የፍየል ጠቦት ለማዘጋጀት ቢፈልግም፦ «አንተ የግድ ብትለኝ እህልህን አልበላም፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ብታደርግ ለእግዚአብሔር አቅርብ፤» አለው። ምክንያቱም ቅዱሳን መላእክት ቅድሚያ የሚሰጡት ለእግዚአብሔር ክብር ነው። እነርሱን ግን እግዚአብሔር ራሱ እንደሚያከብራቸው እንደሚያስከብራቸውም ያውቃሉ።
ማኑሄ የተገለጠላቸው የእግዚአብሔር መልአክ እንደሆነ አላወቀም፥ ሚስቱም አላወቀችም። በመሆኑም፦ «ነገርህ በደረሰ ጊዜ እንድናከብርህ ስምህ ማን ነው?» በማለት ጠየቀው። የእግዚአብሔርም መልአክ፥ «ስሜ ድንቅ ነው፥ ለምን ትጠይቃለህ?» ብሎታል። ማኑሄም የፍየሉን ጠቦትና የእህሉን ቊርባን በድንጋይ ላይ ለእግዚአብሔር አቀረበ። መልአኩም ተአምራት አደረገ፥ ማኑሄና ሚስቱም ይመለከቱ ነበር። ነበልባሉም ከመሠዊያው ላይ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በመሠዊያው ነበልባል ውስጥ ወደ ሰማይ ዐረገ፥ ማኑሄና ሚስቱም ተመለከቱ፥ በምድርም በግንባራቸው ወደቁ። (ሰገዱለት)። ይህ መልካም የምሥራችን የተናገረ፥ የተለያዩ ተአምራትን ያደረገ፥ መሥዋዕታቸውንም ወደ ሰማይ ያሳረገ፥ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ነው። ሚካኤል ማለት በሁለተኛ ትርጉሙ «የእግዚአብሔር ነገሩ ዕፁብ ድንቅ ነው፤» ማለት ነውና። መሳ ፲፫፥፩-፳። በዚህም የስሙ ትርጓሜ ነገረ እግዚአብሔር መሆኑን እንረዳለን።
፩፥፪፦ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ፤ ኢያ ፭፥፲፬
ከነቢያት አለቃ ከሙሴ በኋላ በእርሱ እግር ተተክቶ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የመራው ኢያሱ ነው። የመረጠውም ሰው ሳይሆን እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔርም፦ «በሕይወትህ ዘመን ሁሉ የሚቋቋምህ የለም፤ ከሙሴ ጋር እንደነበርሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ አልጥልህም፥ ቸልም አልልህም፤» ብሎታል። ኢያ ፩፥፭። ይህ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የሆነለት ታላቅ ሰው ኢያሱ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት አስፈልጐታል። ምክንያቱም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ለመሆኑ ምልክቱ ቅዱሳን መላእክት ናቸውና። እግዚአብሔር ባለበት ቅዱሳን መላእክት አሉ፥ ቅዱሳን መላእክትም ባሉበት እግዚአብሔር አለ። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደባት ሌሊት የምሥራቹን «እነሆ፥ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደሰታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ እነሆ፥ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት ተወልዶላችኋል፤ ይኸውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ ነው።» በማለት ለእረኞች የነገሯቸው ቅዱሳን መላእክት ናቸው። እረኞቹም፦ «እስከ ቤተልሔም እንሂድ፥ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን ነገር እንወቅ፥ አሉ።» ሉቃ ፪፥፮-፲፭። በዚህም ቅዱሳን መላእክት የገለጡላቸውን ምሥጢር እግዚአብሔር ገለጠልን ብለዋል።
ኢያሱ ወልደ ነዌ፥ ሕዝቡን እየመራ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ ዐይኑን አንሥቶ ቢመለከት እነሆም የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው በፊቱ ቆሞ አየ። ወደ እርሱም ቀርቦ «ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህን?» አለው። እርሱም «እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ነኝ፤ አሁንም ወደ አንተ መጥቻለሁ፤» ብሎታል። ኢያ ፭፥፲፫-፲፭። የእግዚአብሔር ሠራዊት የሚባሉት ቅዱሳን መላእክት ናቸው። «ያዕቆብም መንገዱን ሄደ፥ በዓይኖቹም የእግዚአብሔርን ሠራዊት ከትመው አየ፥ የእግዚአብሔር መላእክትም ተገናኙት። ያዕቆብም ባያቸው ጊዜ እነዚህ የእግዚአብሔር ሠራዊት ናቸው አለ፤» ይላል። ዘፍ ፴፪፥፩-፪። ቅዱስ ዳዊትም፦ «ሠራዊቱ ሁሉ፥ ፈቃዱን የሚያደርጉ አገልጋዮቹ፥ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤» ብሏል። መዝ ፩፻፪፥፳፩። የእነዚህም (የእግዚአብሔር ሠራዊት) አለቃቸው ቅዱስ ሚካኤል ነው። ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ይሁዳ «የመላእክት አለቃ ሚካኤል» በማለት መስክሮለታል። ይሁዳ ፩፥፲፪።
፩፥፫፦ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉት፤ ራእ ፲፪፥፯
ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በደሴተ ፍጥሞ በግዞት ሳለ በተመለከተው ራእይ ሃላፊያትና መጻእያት ተገልጠውለት ስለነበረ፥ «በሰማይም ሰልፍ (ጦርነት) ሆነ፤» ካለ በኋላ «ሚካኤልና መላእክቱም ዘንዶውን ተዋጉት፥ ዘንዶውም ከነሠራዊቱ ተዋጋቸው። አልቻላቸውምም፥ ከዚያም በኋላ በሰማይ ቦታ አልተገኘላቸውም። ዓለሙን ሁሉ የሚያስተው ዲያቢሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፥ ወደ ምድርም ተጣለ፥ መላእክቱም (የዘንዶው ሠራዊት) ከእርሱ ጋር ተጣሉ፤» ብሏል። ራእ ፲፪፥፯-፱።
ታሪክ፦ ሰይጣን በክህደቱ አጥቶት እንጂ ክብርም ፥ ኃይልም፥ ሥልጣንም ነበረው። በአሥሩ የመላእክት ከተሞች በተሾሙ አሥር የመላእክት አለቆች ላይ የአለቃ አለቃ ነበረ። የተፈጠረው የመላእክት አለቃ ሆኖ ነው። ይኽንንም ቀሌምንጦስ ተናግሮታል። እግዚአብሔር መላእክትን በነገድ መቶ ፥ በከተማ አሥር አድርጐ ፈጥሮ ተሰወራቸው። ይህም ካልፈለጉኝ አልገኝም ፥ ባሕርዬም አይመረመርም ሲላቸው ነው። ወዲያው፦ «እኛ ምንድር ነን? ከየት መጣን ? ማንስ ፈጠረን? በራስ በራሳችን ተፈጠርን ? ወይስ ከሌላ ነው?» አሉ። ሳጥናኤል ከበታቹ እንዲህ ሲሉ ሰማ። ከበላዩ ደግሞ «ፈጠርኳችሁ፤» የሚል አጣ። በቦታው ከሁሉ በላይ አድርጎ ፈጥሮት ነበርና «እኔ ፈጠርሁ፤» ብሎ አሰበ ፥ አስቦም አልቀረ «እኔ ፈጠርኋችሁ፤» አለ። ይኽን ሰምተው «ሰጊድ ይገባዋል፤» ያሉ አሉ። «እኛም እንደ እርሱ ነን፤» ያሉም አሉ። « አምላክ ነኝ ያለስ ከእርሱ በቀር ሌላ የለምና ፥ ይሆንን?» ብለው የተጠራጠሩ አሉ። ሀልዎተ እግዚአብሔርን ሳይመረምሩ የቀሩም አሉ። እኲሌቶቹ ግን ፦ «በምን ፈጠርኋችሁ ይለናል፥ በቦታ ከበላይ በመሆን ፈጠርኋችሁ እንዳይለን ፥ እኛ የበታቾቻችንን መቼ ፈጠርናቸውና ነው?። በዚያውስ ላይ ምቀኞቹ አይደለንም፤ በእውነት ፈጣሪ ከሆነ ፈጥሮ ያሳየን ።» ብለው፦ «ፈጥረህ አሳየን፤» አሉት። እርሱም እፈጥራለሁ ብሎ ፥ እጁን ወደ እሳት ቢጨምር ፈጀውና « ዋይ» አለ። በዚህን ጊዜ «በአፍአ ያለውን (የሚነገረውንና እና የሚሠራውን ብቻ የሚያውቅ) አምላክ ቢሆን ነው እንጂ ውሳጣዊውን (ልብ ያሰበውን የሚያውቅ) አምላክ ቢሆን ኖሮ ገና ሳስበው ለምን አሰብከው ፥ ባለኝ ነበር ፤» አለ። ወዲያው ልቡን ተሰማውና «ዋይ» አለ። እግዚአብሔር ግን ፈወሰው። ይህንንም ማድረጉ ንስሐ ቢገባ እንደሚምረው ሲነግረው ነበር።
ከዚህ በኋላ በመላእክት ሽብር ቢጸናባቸው፦ መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል፦ «ንቁም በበህላዌነ እስከ ንረክቦ ለአምላክነ ፤ አምላካችንን እስክናገኘው ድረስ በየህልውናችን ጸንተን እንቁም ፤» በማለት አጽንቷቸዋል። ይህም በጎ አርበኛ ጦር በተፈታ ጊዜ «አይዞህ ባለህበት ጽና፤» ብሎ እንደሚያጸናው ማለት ነው።« ወበእንተዝ ደለዎ ይፁር ዜናሃ ለማርያም ፤ በዚህ ምክንያት የድንግል ማርያምን ዜና ያደርስ ፥ ብሥራቷን ይናገር ዘንድ ተገባው ፤ » እንዲል ፥ ብሥራት ተሰጥቶታል። «በስድስተኛው ወር (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ፥ ስድስተኛው ሺህ ደግሞ ሲጀምር) መልአኩ ገብርኤል . . . ወደ አንዲት ድንግል ተላከ» ይላል። ሉቃ ፩፥፳፮።
እግዚአብሔርም ጨርሶ ሳያስታቸው ብሎ እርሱ (ሳጥናኤል) በሌለበት በኲል በምሥራቅ ባሕረ ብርሃንን አፍስሶላቸዋል። ከዚህም ጋር ስሙ የተጻፈበት መጽሔተ ብርሃን ቢሰጣቸው አንድነቱ ሦስትነቱ(ምሥጢረ ሥላሴ) ተገልጦላቸው « አሐዱ አብ ቅዱስ ፥ አሐዱ ወልድ ቅዱስ ፥ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፤» ብለው አመስግነውታል። እርሱን ግን ባደረው ጨለማ ጠቅልሎ በዕለተ እሑድ ከኢየሩሳሌም ሰማያዊት ወደ ኢዮር አውርዶታል። ከሰባቱ ሰማያት ሦስቱ ፦ ኢዮር ፥ራማ፥ ኤረር የመላእክት ናቸው። በውስጣቸውም አስር የመላእክት ከተሞች አሉ። በእነርሱም ላይ አስር አለቆች ተሹመዋል። እግዚአብሔር ሳጥናኤል በሌለበት በኲል ባሕረ ብርሃንን ያፈሰሰላቸው «እኔ ፈጠርኩ » እንዳይል ነው።
ሳጥናኤል በኢዮር ሆኖ በዕለተ ሠሉስ የተፈጠሩ ዕፅዋት፥ አዝርዕት ፥ አትክልት ፥ጽጌያትን አይቶ እንዳያደንቅ፦ «እንዲህ አድርጐ አከናውኖ የፈጠረለት ቢኖር ነው፥ » አለ። እግዚአብሐርም «ከወደድሃት በዚያ ላኑርህ ፤» ቢለው «ደገኛይቱን ማን ከልክሎኝ ፤» አለ። ከዚህ በኋላ ለሚካኤልና ለገብርኤል «እናንተ ኢየሩሳሌም ሰማያት ይሏችኋል ፥ ሰባቱ ሰማያት እንኳ አያህሏትም። እኛ ከጩኸት በቀር የተጠቀምነው የለም። ገዢ ነኝ የሚለውን ወግተን እጅ እናድርግ።» ብሎ ላከባቸው። እነርሱም የተላኩትን ከንጉሥ ከተማ እንደገባ ዕብድ ውሻ አድርገው ሰደዷቸው። ተመልሰውም አልተቀበሉንም ቢሉት ፦ «ቀለምጺጸ እሳት (የእሳት ፍንጣሪ) የሆኑ ሚካኤል ገብርኤል በእኔ ዘንድ ምን ቁም ነገር ናቸው። ይልቁንስ ኑ ተሸከሙኝና እንሂድ ፤» አላቸው። በዚህን ጊዜ በአርባዕቱ እንስሳ (በኪሩቤል) አምሳል አራት ሁነው ተሸክመውት ሽቅብ እወጣለሁ ቢል ኃይል ተነሥቶታል። ወደ ታች እንጂ ወደ ላይ መውጣት የማይቻለው በመሆኑም ፦ «ጐየ እግዚእ ምስለ አርያሙ፤ እግዚአብሔር ሰማዩን (ጽርሐ አርያምን) ጠቅልሎ ሸሸ፤» ብሎ ተመለሰ።
ቅዱሳን መላእክት ግን ፍጥረትን ሲፈጥር እያዩ ያመሰግኑ ነበር። በዕለተ ረቡዕ ፀሐይ ፥ ከዋክብት ፥ ጨረቃ ፥ ሲፈጠሩ አይተው አመስግነው አመስግን ቢሉት ፦ «አንሰ ዕድው (ውፁዕ) እምዝንቱ ኅሊና፤» እንዲል፦ «እኔ ከዚህ ውጪ ነኝ ፥ ባይሆን አራተኛ አድርጋችሁ ብታመሰግኑኝ እወዳለሁ፤» አላቸው። እነርሱም «ይህ ስሑት ፍጥረት እንዲህ እያለ እስከ መቼ ሲታበይ ይኖራል?» ብለው ሄደው ቢገጥሙት ድል አደረጋቸው። ሁለተኛም ቢገጥሙት ዳግመኛ ድል አደረጋቸው። በዚህን ጊዜ፦ «እኛስ ለአምላክነትህ ቀንተን ነበረ ፥ አንተ ግን ፈቃድህ ሳይሆን ቀረ፤» ብለው ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክቱ ፦ «ፈቃዳችሁ ፈቃዴ ነው ፥ ነገር ግን ድል የሚነሣበትን (የሚሸነፍበትን) ታውቁ ዘንድ ነው፤» ብሎ ስሙ የተጻፈበትን ትእምርተ መስቀል ሰጣቸው። ያን ይዘው በዕለተ ረቡዕ ወደዚህ ዓለም አውርደውታል። በዚህን ጊዜ የእርሱ ወገኖች ለሦስት ተከፍለዋል። ሀለዎተ እግዚአብሔርን ሳይመረምሩ የቀሩ በአየር ቀርተዋል። ይሆን ፥ አይሆን ብለው የተጠራጠሩ በዚህ ዓለም ቀርተዋል። « አምላክ ነው ፥ ሰጊድ ይገባዋል፤» ያሉ አብረው እንጦሮጦስ ወርደዋል።
፩፥፬፦ ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል፤ ዳን ፲፪፥፩
ቅዱስ ሚካኤል ለእግዚአብሔር መንጋ እረኛቸው ነው። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት፦ በመዝ ፴፫፥፯ ላይ «የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት (ፈሪሃ እግዚአብሔር ባላቸው) ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ (ይከትማል፥ የእሳት አጥር ይሆናል)፥ ያድናቸውማል፤» እንዳለ፥ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በተለይም በፍጻሜ ዘመን ከሚመጣው መከራ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ያድናል። ይህ ምሥጢር የተገለጠለት ነቢየ እግዚአብሔር ዳንኤል፦ «በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው (በአማላጅነት በተራዳኢነት የሚቆመው) ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል፥ ሕዝብም በምድር ከተፈጠረ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን ይሆናል፤» ብሏል። ዳን ፲፪፥፩። በዚህም፦ ገናና መልአክ፥ የመላእክት አለቃ፥ አማላጅና ተራዳኢ መሆኑን መስክሮለታል። ስለዚያች ቀን፥ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ «ያንጊዜ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከዛሬ ያልተደረገ፥ ከእንግዲህም ወዲያ የማይደረግ ታላቅ መከራ ይሆናል፤» ካለ በኋላ፥ «መላእክቱንም ከታላቅ የመለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥ የተመረጡትንም ከሰማይ ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ መዐዝን ይሰበስቧቸዋል።» ብሏል። ማቴ ፳፬፥፳፩-፴፩። ቅዱስ ዮሐንስም ስለ ሓሳዊ መሲሕ ዘመን ተገልጦለት፥ «ከዚህ በኋላ ሌላ አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፤ . . . ለአውሬውም (ለፊተኛው አውሬ) ምስል ያልሰገደውን ሁሉ እንዲገደሉ ያደርጋቸዋል፤» ብሏል። ራእ ፲፫፥፲፩፣ ፲፭። እንግዲህ የዚህን ክፉ ዘመን መከራ ሥጋ ለባሽ የሆነ ሁሉ ስለማይቋቋመው የመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤልና የሠራዊቱ ተራዳኢነት አስፈልጓል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «መላእክት ሁሉ መናፍስት አይደሉምን? የዘለዓለም ሕይወትን ይወርሱ ዘንድ ስለ አላቸው ሰዎችስ ይላኩ የለምን?»ያለው ለዚህ ነው። ዕብ ፩፥፲፬።
፩፥፭፦ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፤ ዳን ፲፥፲፫
ነቢዩ ዳንኤል፥ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በሦስተኛው ዓመተ መንግሥት በራእይ ምሥጢር ተገልጦለታል፥ ነገሩም ከእግዚአብሔር በመሆኑ ምሥጢር ነበረ፥ ታላቅ ኃይልና ማስተዋልም በራእዩ ውስጥ ተሰጥቶታል። ነቢዩ ዳንኤል ስለ ሕዝቡ ኃጢአትና ሊመጣ ስላለው መከራ ሶስት ሳምንት ሙሉ አዝኗል። (ጾም ጸሎት ይዟል)። ማለፊያ እንጀራ አልበላም፥ ሥጋና የወይን ጠጅም በአፉ አልገባም፥ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ራሱን ዘይት አልተቀባም። ከልጅነቱ ጀምሮ ጾም ጸሎትን አጥብቆ የያዘ ነቢይ ዳንኤል በራእይ የተገለጠለት ምሥጢረ ሥጋዌ ነው። «ዳንኤልም ከንጉሡ ማእድ እንዳይበላ፥ ከሚጠጣውም ጠጅ እንዳይጠጣ ልቡ ጨከነ፥ እንዳያበላውም የጃንደረቦቹን አለቃ ለመነው፥ እግዚአብሔርም በጃንደረቦቹ አለቃ ፊት ለዳንኤል ሞገስንና ምሕረትን ሰጠው። . . . ይህንም ነገራቸውን ሰምቶ ዐሥር ቀን ፈተናቸው። ከዐሥር ቀንም በኋላ ከንጉሡ ማዕድ ከበሉ ብላቴኖች ሁሉ ይልቅ ሰውነታቸው አምሮ ሥጋቸው ወፍሮ ታየ። አሚሳድም መብላቸውንና የሚጠጡትን ጠጅ አስቀርቶ ጥራጥሬውን ሰጣቸው፤» ይላል። ዳን ፩፥፰-፲፮።
በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ ዐሥር ቊጥር ፲፫ ላይ፦ «ዳንኤል ሆይ! አትፍራ፥ ልብህ ያስተውል ዘንድ፥ ሰውነትህም በአምላክህ ፊት ይዋረድ ዘንድ ከአደረግህበት ከመጀመሪያው ቀን (ኀዘን፥ ጾም፥ ጸሎት ከጀመርክበት ዕለት) ጀምሮ ቃልህ (ጸሎትህ፥ ምልጃህ) ተሰምቷል፥ እኔም ስለ ቃልህ መጥቻለሁ። የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሃያ አንድ ቀን በፊቴ ነበር። እነሆም ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፥ እኔም ከፋርስ ንጉሥ ጋር በዚያ ተውሁት።» የሚል እናገኛለን። ይኽንንም የተናገረው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ነው። ነቢዩ ዳንኤል ጾም ጸሎት በሚይዝበት ጊዜ ዘወትር ወደ እርሱ እንደሚመጣ «ገብርኤል ሆይ! ራእዩን ለዚህ ሰው ግለጥለት፤ . . . እኔም ገና ስናገርና ስጸልይ፥ በኃጢአቴና በሕዝቤም በእስራኤል ኃጢአት ስናዘዝ፥ በአምላኬም በእግዚአብሔር ፊት ስለ ተቀደሰው ስለ አምላኬ ተራራ ይቅርታን ስጠይቅ፥ ገናም በጸሎት ስናገር አስቀድሜ በራእይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል እነሆ አየበረረ መጣ፥ በማታም መሥዋዕት ጊዜ ዳሰሰኝ።» የሚል አብነት ይገኛል። ዳን ፰፥፲፮፣ ፱፥፳።
ቅዱሳን መላእክት ሁልጊዜ ከዲያቢሎስና ከሠራዊቱ ጋር ይዋጋሉ፥ ያሸንፉማል። ቅዱስ ገብርኤል ወደ ነቢዩ ዳንኤል ሳይመጣ ለሶስት ሳምንት የዘገየበትን ምክንያት ሲነግረው «የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሃያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ፤» ብሏል። ይህም በፋርስ ንጉሥና በሠራዊቱ ካደሩ አጋንንት ጋር ሲዋጋ መሰንበቱን ያመለክታል። ይኸውም ዕለቱን ማሸነፍ ተስኖት ሳይሆን ሰይጣን ኢዮብን በከሰሰበት መንገድ እስራኤልን እየከሰሰ ቀኑን አዘግይቶበታል። ታላቁ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ሰይጣን አዘገየኝ፤» ያለው ከዚህ ተመሳሳይ ነው። ቅዱስ ገብርኤል በሦስተኛው ሳምንት መጨረሻ ሊመጣ የቻለበትን ምክንያት ሲናገር ደግሞ «ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፥ እኔም ከፋርስ ንጉሥ ጋር በዚያው ተውሁት፤» ብሏል። በዚህም ቅዱሳን መላእክት እንኳ እርስ በርስ እንደሚረዳዱ እንማራለን። ይህም ድካም ተሰምቷቸው አንዳቸው የሌሎቹን እርዳታ ይፈልጋሉ ማለት ሳይሆን የአገልግሎት አንድነታቸውን የሚያጠይቅ ነው። ይህ እንዲህ ከሆነ እጅግ ደካማ የሆኑ የሰው ልጆች የኃያላን መላእክት ተራዳኢነት እንዴት አያስፈልገንም ይላሉ? በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ አብነት ለመሆን በጌቴሴማኔ አጸድ በጸለየበት ጊዜ «የሚያበረታታው የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ታየው፤» ይላል። ሉቃ ፳፪፥፵፫። እንግዲህ እርሱንስ ምን ሊሉት ነው?
፩፥፮፦ ከአለቃችሁ ከሚካኤል በቀር የሚረዳኝ ማንም የለም። ዳን ፲፥፳፩
ሰይጣን ሠራዊቱን አሰማርቶ በአሕዛብ ነገሥታት እያደረ የእግዚአብሔር ሕዝብ የተባሉ እስራኤልን ዘወትር በጦርነት ያስጨንቃቸው ነበር። በዚህም ምክንያት ሲወድቁ ሲነሡ፥ ሲነቀሉ ሲተከሉ፥ ሲፈርሱ ሲገነቡ፥ ሲበተኑ ሲሰበሰቡ፥ ሲሰበሩ ሲጠገኑ ኖረዋል። በዚያ ዘመን መጋቤ ብሉይ ተብሎ የሚታወቀው ቅዱስ ሚካኤል ነው። እርሱም ዘወትር ከቅዱስ ገብርኤል ጋር ሆኖ ሕዝቡን ይረዳቸው ነበር። ይኽንንም «ወደ አንተ የመጣሁት ለምን እንደሆነ ታውቃለህን? አሁንም የፋርስን አለቃ እዋጋው ዘንድ እመለሳለሁ፥ እኔም ስወጣ እነሆ የግሪኮች አለቃ ይመጣል። (ሰይጣን በግሪክ ንጉሥ አድሮ ሌላ ጦርነት ይጀምራል)። ነገር ግን በእውነት ጽሑፍ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፥ በዚህም ነገር ከአለቃችሁ (ከመላእክት አለቃ) ከሚካኤል በቀር የሚያጸናኝ የለም።» በማለት ቅዱስ ገብርኤል ለነቢዩ ለዳንኤል ነግሮታል። ቅዱስ ገብርኤል እንዲህ ካለ እኛስ ምን እንበል?
፩፥፯፦ በመላእክት አለቃ ድምጽ፥ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳል፤ ፩ኛ ተሰ ፬፥፲፮
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለጻድቃን ሊፈርድላቸው፥ በኃጥአን ሊፈርድባቸው ዳግም እንደሚመጣ ቅዱሳት መጻሕፍት በመተባበር ይመሰክራሉ። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት፦ «እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል። አምላካችንም ዝም አይልም፥ (ይፈርዳል)፥ እሳት በፊቱ ይነድዳል፥ በዙሪያውም ብዙ አውሎ አለ።» ብሏል። መዝ ፵፱፥፫። ነቢዩ ዘካርያስም በበኲሉ የሚመጣው ከቅዱሳን ሁሉ ጋር እንደሆነ ሲናገር፦ «አምላኬ እግዚአብሔር ከቅዱሳኑ ጋር ይመጣል፤» ብሏል። ዘካ ፲፬፥፮። በአዲስ ኪዳን ደግሞ ራሱ ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ እመሕያው) በጌትነቱ ቅዱሳን መላእክትን ሁሉ አስከትሎ በሚመጣበት ጊዜ፥ ያንጊዜ በጌትነቱ ዙፋን ይቀመጣል፤» ብሏል። ማቴ፳፭፥፴፩። በዕርገቱ ጊዜም ቅዱሳን መላእክት ለደቀመዛሙርቱ ተገልጠው፦ «እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እያያችሁ ለምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ ሲያርግ እንዳያችሁት እንዲሁ ዳግመኛ ይመጣል፤» ብለዋቸዋል። የሐዋ ፩፥፲፩። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ትንሣኤ ሙታን ባስተማረበት ትምህርቱ፦ «ወንድሞቻችን ሆይ፥ ስለ ሞቱ ሰዎች፥ ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች እንዳታዝኑ ልታውቁ እንወዳለን። ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ እንደተነሣ ካመንን፥ እንዲሁ እግዚአብሔር ሙታንን በኢየሱስ ያስነሣቸዋል። ይህንንም በእግዚአብሔር ቃል እንነግራችኋለን፥ ጌታችን በሚመጣ ጊዜ ሕያዋን ሆነን የምንቀር እኛ የሞቱትን አንቀድማቸውም።» ካለ በኋላ «ጌታችን ራሱ በትእዛዝ፥ በመላእክትም አለቃ ድምፅ፥ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፤» ብሏል። ፩ኛ ተሰ ፬፥፲፫-፲፮። ይህ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ነው። እንዲህ እስከመጨረሻው ከጌታ የማይለየውን መልአክ «ለምን ስሙ ተጠራ?» ማለት ራስን ከጌታ መለየት ነው።
፩፥፰፦ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ከሰይጣን ጋር ተከራከረ፤ ይሁ ፩፥፱
የያዕቆብ ወንድም ይሁዳ፥ ቅዱስ ሚካኤልና ሰይጣን የተከራከሩበትን ምክንያት ሲናገር፦ «የመላእክት አለቃ ሚካኤል እንኳን ስለ ሙሴ ሥጋ ከሰይጣን ጋር በተከራከረ ጊዜ የስድብን ቃል ሊናገር አልደፈረም፥ እግዚአብሔር ይገሥጽህ አለው እንጂ። እነዚህ ግን የማያውቁትን በመሳደብ ይበድላሉ፤» ብሏል። ይሁ ፩፥፱። ቅዱስ ይሁዳ፥ በዘመኑ ላሉትም ሆነ እስከ ዓለም ፍጻሜ ለሚነሡት ተሳዳቢዎች እንደተናገረው፥ የመናፍቃን ሥራቸው፥ እንደ ግብር አባታቸው እንደ ዲያቢሎስ ቅዱሳንን መርገም ነው።
የነቢያት አለቃ ሙሴ ከዚህ ዓለም በሞት የሚለይበት ጊዜ ሲደርስ፥ ከሞዓብ ሜዳ በኢያሪኮ ፊት ለፊት ወዳለው ወደ ናባው ተራራ ወደ ፈስጋ ራስ ወጣ፤ እግዚአብሔርም የከነዓንን ምድር ካሳየው በኋላ፦«ለዘርህ እሰጣታለሁ ብዬ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማልሁላቸው ምድር ይህች ናት፤ እነሆም፥ በዐይንህ እንድታያት አደረግሁህ፥ ነገር ግን ወደዚያች አትገባም፤» አለው። የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴም እንደ እግዚአብሔር ቃል በዚያ በሞዓብ ምድር ሞተ። በቤተ ፌጎርም አቅራቢያ በናባው ምድር ቀበሩት፥ እስከዛሬም ድረስ መቃብሩን ማንም የሚያውቅ የለም። ዘዳ ፴፬፥፩-፯። የሙሴ መቃብር እንዴት ሊታወቅ አልቻለም? የቀበረውስ ማነው?
ታሪክ፦ እግዚአብሔር የሙሴን መቃብር ከእስራኤል ሰውሮባቸዋል፥ የሰወረበትም ምክንያት ካላቸው ጽኑዕ ፍቅር የተነሣ መቃብሩን እንዳያመልኩ ነው። አንድም የተቀበረበትን ቦታ ካወቁ ጧት ማታ እየሄዱ ከመቃብሩ ላይ እያለቀሱ ኀዘን እንዳይጸናባቸው ብሎ ነው። የነቢያት አለቃ ሙሴ ወደ ተራራው ሲወጣ ሁለት መላእክት በአረጋውያን ተመስለው መቃብር ሲቆፍሩ አገኛቸው። መላእክት መሆናቸውን ግን አላወቀም። «አክብር ገጸ አረጋዊ» የሚለውን ሕግ ስለሚያውቅ «ላግዛችሁ፤» ብሎ መቃብሩን ቆፍሮ ጨረሰላቸው። እነርሱም፦ «ልክ ይዘን አልመጣንም፥ ስለዚህ ሟቹ በግምት አንተን ስለሚያክል ውስጡ ተኝተህ ለካልን፤» አሉት። እርሱም «እሺ፥በጀ፤» ብሎ ተኝቶ ሲለካ በዚያው ነፍሱ ከሥጋው ተለይታ አርፏል። ከዚህ በኋላ አፈር መልሰውበታል። የሙሴ መቃብር በሰው ዘንድ ያልታወቀው በዚህ ምክንያት ነው።
እስራኤል ዘሥጋ ከሞቱ ይልቅ የመቃብሩ መሰወር አሳዝኖአቸዋል። በዚህን ጊዜ የሰውን ችግር መግቢያ በር አድርጐ መግባት የሚያውቅበት ሰይጣን ወደ ሕዝቡ የሚቀርብበትን ምክንያት አገኘ። ቀርቦም «ኑ፥ ተከተሉኝና የሙሴን መቃብር ላሳያችሁ፤» አላቸው። እንዲህም ማለቱ ለእነርሱ አዝኖላቸው ሳይሆን፥ የሚሆንለት መስሎት፥ በሙሴ ሥጋ አድሮ ሊመለክ ፈልጐ ነው። ሕዝቡም እውነት መስሏቸው ተከተሉት። በዚህ ቅጽበት የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወርዶ ሰይጣንን ተቃወመው። «በቅዱሱ በሙሴ ሥጋ ማደር አትችልም፥ እርሱ የእግዚአብሔር ማደሪያ ነው፤» ብሎ ተከራከረው። በመጨረሻም ሦስት ጊዜ «እግዚአብሔር ይገሥጽህ፤» ቢለው ሰይጣን እንደ ትቢያ ተበትኖ ርቆላቸዋል። ይህ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ፍላጐታችንን ምክንያት አድርጐ ባልሆነ መንገድ እንዳይመራን ሰይጣንን ይቃወምልናል፥ ተከራክሮም ያሸንፍልናል ብለን እናምናለን። እንኳን በሕይወት እያለን ሞተንም በመቃብር ይጠብቀናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
፩፥፱፦ በእስራኤል ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ፤ ዘጸ ፲፬፥፲፱
ከባርነት ቤት ከግብፅ የወጡትን ሕዝብ፥ እግዚአብሔር፦ ቀኑን በደመና ዓምድ፥ ሌሊቱን ደግሞ በብርሃን ዓምድ መርቷቸዋል። የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን እስራኤልን «ሂዱ፤» ብሎ ከለቀቃቸው በኋላ መልሶ ስለጸጸተው ሠራዊቱን ይዞ ተከተላቸው። ፈርዖንም በቀረበ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ዓይናቸውን አንሥተው ግብፃውያን ሲከተሉአቸው አዩ፤ እጅግም ፈርተው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። ምክንያቱም ሸሽተው እንዳያመልጡ ከፊት ለፊታቸው ያለው ባሕር ነው። በዚህ ላይ ፈርዖን ከነሠራዊቱ የተከተላቸው በፈረስ በሰረገላ በመሆኑ ሸሽተውም ቢሆን ማምለጥ አይችሉም። መሸሻ ሜዳ፥ መሸሎኪያ ቀዳዳ፥ መመከቻ ጋሻ፥ መሸሸጊያ ዋሻ አልነበራቸውም። ሙሴንም፦ «በግብፅ መቃብር ስላልኖረ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ አወጣኸንን? ከግብፅ ታወጣን ዘንድ ይህ ያደረግህብን ምንድነው? በምድረ በዳ ከምንሞት ብንገዛላቸው ይሻለናልና፦ ተወን፥ ለግብፃውያን እንገዛ፥ ብለን በግብፅ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን?» አሉት። ሙሴም ለሕዝቡ «አትፍሩ፥ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘለዓለም አታዩአቸውምና ቁሙ፤ (በእምነት ጽኑ)፤ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ።» አላቸው። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ «ለምን ትጮኽብኛለህ? ከብቶቻቸውን እንዲነዱ ለእስራኤል ልጆች ንገር። አንተም በትርህን አንሣ፥ እጅህንም በባሕሩ ላይ ዘርጋ፥ ክፈለውም፥ የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ ውስጥ በየብስ ያልፋሉ። እነሆም እኔ የፈርዖንን እና የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፥ በስተኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሰረገሎቹ፥ በፈረሰኞቹም ላይ እከብራለሁ። (ኃይሌን ገልጬ እመሰገናለሁ)። ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ፥ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር ባገኘሁ (ኃይሌን ገልጬ በተመሰገንሁ) ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ (ኃያልና ገናና ፈጣሪ መሆኔን) ያውቃሉ፤» አለው። በእስራኤልም ሠራዊት ፊት ይሄድ (ይመራቸው፥ ይጠብቃቸው) የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ (ከፈርዖንና ከሠራዊቱ በክንፈ ረድኤቱ ጋረዳቸው)፤ የደመናውም ዐምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ፥ በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፥ በዚያም ጭጋግና ጨለማ ነበረ፤ ሌሊቱም አለፈ፥ ሌሊቱንም ሁሉ እርስ በርሳቸው አልተቃረቡም። ሲነጋም እግዚአብሔር አስቀድሞ እንደተናገረ በበትረ ሙሴ ላይ ኃይለ እግዚአብሔር ተገልጦ ባሕረ ኤርትራ ለሁለት ተከፈለ፥ ውኃው ግራና ቀኝ እንደ ግድግዳ ቆሞ፥ እስራኤል በደረቅ ተሻገሩ፥ ግብፃውያን ሰጥመው ቀሩ። ዘጸ ፲፬፥፩-፴፩።
እስራኤል ዘሥጋን በመንገዳቸው ሁሉ የጠበቃቸው፥ መና ከሰማይ ያወረደላቸው፥ ተአምራትን ያደረገላቸው፥ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ርስታቸው የመራቸው፥ በደመና መጋረጃ የጋረዳቸው፥ በክንፎቹም የሸፈናቸው መጋቤ ብሉይ የተባለ ቅዱስ ሚካኤል ነው። እኛንም ከዲያቢሎስና ከሠራዊቱ ይጠብቀናል፥ ከአሽክላው ይሰውረናል፥ ወደ ምድረ ርስት ገነት መንግሥተ ሰማያት ይመራናል፥ ብለን እናምናለን። ኅዳር አሥራ ሁለት ቀን በየዓመቱ በማኅሌት እና በቅዳሴ የምናከብረው ይኽንን ለእስራኤል ዘሥጋ የተደረገውን በማሰብ ነው። የበለጠው ደግሞ እስራኤል ዘነፍስ ለምንባል ክርስቲያኖች ይደረግልናል።
የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማላጅነት፥ የቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት አይለየን አሜን።

My Heart Cries

 Samrawit Tessema - English Poem on Ethiopians tortured in Saudi Arabia 2013.

Click here to listen  Samrawit poem 

Wednesday, November 13, 2013

ከዚህ መከራ እና ስቃይ እንዴት እንላቀቅ?

ዛሬ ላይ ስለ ስቃይ፣ መከራ፣ችግር እና እንግልት በቃላት መግለጽ አስፈላጊ አይመስለኝም። ምክንያቱም በእራሳችን ላይ ቀን በቀን በተግባር እየተፈጸመብን ነውና። ከተግባር በላይ አድን ነገር ሊገልጸው የሚችል ነገር የለም አይኖርምም። ምን አልባት አንዳንድ ሰዎች ችግሩ በቀጥታ ከእኔ አልደረሰም ልንል እንችል ይሆናል “አንተ በሰላም እንድተኛ ከፈለክ ጎረቤትህ ሰላም ይሁን” ይባል የለ በአገራችን ብሂል፤ ምናልባት ለጥቂት የዘመኑ እድለኞች ችግሩ በቀጥታ ባይደርሳቸውም ጎረቤት፣ ወገን ዘመድ ስቃይና እንግልት በዝቶበት ከሚችለው በላይ ሲሆን ሕይወትን በችግር ሲገፉ ማየት ለሰብአዊ ፍጡር እንቅልፍ የማያስተኛ ትልቅ በሽታ ነው። ይህን እያየ  አንድ ሰው ራስ ደና ካለ እሱ ከሰባዊ መደብ ወጥቷል ማለት ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ትናት እና ከትናት በስተያ የነበረን ልዩ  መለያ ጠባያችን መተሳሰብ፣ መረዳዳት፣ የጎረቤት ችግር  ችግሬ፣ ጭንቀቱ ጭንቀቴ፣ አገሬ ህይዎቴ እያልን የኖርን ህዝቦች ነበርን። በተለይ ደግሞ  የአገርና የዜግነት ክብር ምን እንደሆነ በተግባር ያየን፣ ለአለምም ያሳየን ህዝቦች ነበርን።
በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት አንድ አገር አገር ለመባል ሦስት መሰረታዊ ነገሮች ያስፈልጓታል። ከእነዚህ መሰረታዊ ነገሮች መካከል አንዱ ከተነካ ሉዐላዊት አገር የሚለው ይቀርና ሌላ ስም ይሰጣታል። እነዚህ ሦስቱም ተደጋግፈውና አንዱ የአንዱን ሉዐላዊነት መጠበቅ፣ ማስጠበቅ ይኖርበታል። አንዱ አንዱን ካጣ ምዕሉ ሊሆን አይችልምና። የአንድ አገር ሦስቱ መሰረታዊ ነገሮች የሚባሉት ግዛት፣ ህዝብና መንግስት ናቸው።
  1. ግዛት፦ የአንድ አገር ግዛት ማለት ወሰኗ፣ ድንበሯ፣ የቆዷ ስፋቷ፣ በውስጧ የየያዘዛቸው ወንዝ፣ ተራራ፣ሸለቆ፣ ባጠቃላይ ሙሉ ካርታዋ ማለት ነው። የኢትዮጵያ ግዛት ስንል በምስራቅ፣ በሰሜን፣ በደቡብና በምዕራብ ከሚያዋስኗት ግዛቶች የምትለይበት ቦታ፣ ድንበር ወይም ክልል ጀምሮ  በውስጧ የየያዘዛቸው ወንዝ፣ ተራራ፣ሸለቆ ወዘተ ሙሉ የቆዳ ስፋቷን ያዋስናል። ከዚህ የቆዷ ስፋቷ ትንሽ ከተነካ ግን የነበራት ሙሉ ግዛት አይኖራትም። ይህን ግዛቷን ለማስጠበቅ መንግሥት በማስተባበር ህዝብ በመተባበርና በመጠበቅ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት። ዛሬ ላይ የምናያቸው ነገሮች ግን ከዚህ የራቁ ናቸው። መንግሥት ለግዛቷ ሲጨነቅ አናይም፣ ህዝብም በተመሳሳይ። እንደ ጥሬ እቃ ግዛቷን ሲሸጥም፣ ሲደራደርባትም እናያለን። የጽሕፌ ዓላማ ይህን ማንሳት ስላልሆነ እዚህ ውስጥ መግባት አልፈልግም።
  2. ሕዝብ፦ ከሁሉም በላይ ክብርና ሥልጣን ሊሰጠው የሚገባ ነው። ሕዝብ ከሌለ የምንላቸው ነገሮች የሉም። ህዝብ ከሌለ ለግዛት ስም ጠርቶ፣ ወሰን ወስኖ ሊያስቀምጥ የሚችል አካል የለም። ስለዚህ ሕዝም ውድ ዋጋ ያለው ነው። በሌላም በኩል ፈጣሪ አክብሮና ባለ አዕይምሮ አድርጎ የፈጠረው መተኪያ የለለው ፍጡር ነው። ስለዚህ ግዛት በሕዝም ይከበራል፤ መንግሥት ደግሞ  በሕዝብ ይከብራል/ይነግሣል። ላከበረው፣ ላነገሠው ሕዝብ መንግሥት ዋጋ ሊከፍልለት ይገባል። ከዚያ ውጭ ግን(የዜግነት ክብር በኢትዮጵያችን ፀንቶ፣ ታየ ህዝባዊነት ዳር እስከዳር በርቶ)እያልን የአገር መለያ፣ የማንነታችን መገለጫ የሆነውን ባንዲራ እያውለበለብን የምንዘምረው የህዝብ መዝሙር ከንቱና ዋጋ አልባ ሆኗል ማለት ነው። ባንዲራ ደግሞ ጨርቅ አይደለም ልዩ መለያ ማንነታችን ነው። ይህን የማንነት ጉዳይ ሊያስከብረው የሚችል ደግሞ  ህዝብ ነው። ሕዝብ ማለት ደግሞ እያንዳንዳችን ስብስብ/ድምር ውጤት ነው።                                                                      ዛሬ ላይ እየተፈጸመ ያለው ችግር፣ ስቃይና እንግልት እንዲሁም ሞት የጥቂቶች ብቻ ሳይሆን የሕዝብን ክብርና የማንነታችንን መገለጫ ባዲራን ክብር የሚነካና ለዘላለም የማይጠፋ ጥቁር ጠባሳ ነው። ይህ ሲፈጸም ዝም ብሎ  ማየት ግን ከውርደትም በላይ ውርደት ከአረመኔነትም በላይ አረመኔነት ነው። የአረብ ሃገራት እኮ በሕዝባችን ላይ በደልና ግፍ የሚፈጽሙት አረመኔነት ቢሆንም ቅሉ አገራቸውንና የሕዝባቸውን የኑሮ ሁኔታ እንዳይነካባቸው ስለሚፈልጉ ጭምርም ነው።  ታዲያ እኛ ወገናችን የዜግነታችንን መገለጫ የሆነውን ባንዲራ ከራሱ ላይ ጠምጥሞ ሲሞት ስናይ እንዴት አስቻለን? አዎ እውነት ነው በስሜት ብዙዎቻችን በእጅጉ ተጎድተናል፣ ተረብሸናልም፣ ምግብ መመገብ አቅቶናል። ፊታችን በእንባ ታጥቧል። ግን መፍትሔ ሊሆን አልቻለም። ይህ አዲስ ክስተትም አይደለም፤ አስር፣ አስራ ዓመታትን አስቆጥሯል። ችግሩ፣ ስቃዩ  እየባሰ፣ እየጎላ መጣ እንጂ። በአገር ውስጥም በውጭም ችግሩ ያው ነው ልይነቱ የውጭው በመገናኛ ብዙኃን ጎልቶ  መታየቱ እንጂ ብዙዎች አገር ውስጥም እየተሰቃዩ፣ መከራ በዝቶባቸው የሚኖሩት በርካታ ናቸው። ወደ ሦስተኛው መሰረታዊ ነገር ልግባ መፍትሔውን በኋላ እንመለስበታለን።
  3. መንግሥት፦ መንግሥት ማለት በጥሬ ትርጉሙ በአንድ አገር  ውስጥ ሕጎችን ለማውጣትና ለማስፈጸም፣ ሕዝብን ለማስተባበርና ደኅንነቱን ለማስጠበቅ፣ አገርን ለማስከበር  ስልጣንና ኃላፊነት ያለው አካል ማለት ነው። እንዲሁም በምርጫም ይሁን በሌላ መንገድ በሕዝብ ድጋፍ ስልጣን ላይ የወጣ አካል ነው። ስለዚህ ይህ በሕዝብ ድጋፍ ሥልጣንን የያዘ አካል ከስሙና ከትክክለኛ ትርጉሙ አንፃር ለህዝብና ለአገሪቱ ግዛት ከማንም በላይ የሚጨነቅ፣ የሚያስብና የሚቆረቆር አካል ነው ማለት ነው። ምክንያቱም ሕዝብ ከሌለ መንግሥት የለም፤ ግዛትም ከሌለ እንዲሁ። ከምንም በላይ ለመንግሥት መኖር ሁለቱም ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው። የየትኛም አገር መንግሥት ይህን ተገንዝቦ ለሁለቱም የሚገባውን እንክብካቤና ክብር መስጠት ካልቻለ የመኖር ዋስትናው ጥያቄ ውስጥ ይገባል። አወዳደቁም በእጅጉ የከፋ ይሆናል። 
ከዚህ አንፃር የአገራችን መንግሥት የቱ ጋር ነው ያለው ብሎ መጠየቁ መሰረታዊና አስፈላጊ ጥያቄ ነው። ያለበትን ደረጃም በተገቢው መንገድ ማሳየት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል። ስንተቻች/ስንነታረክ ብዙ ዓመታትን አሳልፈናል። አሁን ጊዜው የተግባር ነው። ተግባራዊ ሥራ ለመስራት ወኔ ሰንቀን መነሳት ይኖርብናል። የጦርነት ወኔ አይደም የሰላም፣ የአገር ፍቅር፣ የዜግነት ክብር ወኔ፣ የማንነት ወኔ እንጂ። 
ሰሞኑን የዓለምን ዓይንና ጀሮ የሳበ ትልቁ ክስተት በሳዑዲ አረቢያ ለማየትም ሆነ ለመስማት ዘግናኝና አሰቃቂ በሰው ልጆች ላይ እየተፈጸመ ያለው ድርጊት ነው። በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያውያን እህት ወንድሞቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና መከራ ነው። የክብራችን መገለጫ ባንዲራችን ሳይቀር በደም ታጠበ። ወንድሞቻችንም ሰማዕትነትን ተቀበሉ፤ ባንዲራችንም ተጨምራ በድንጋይ ተወገረች። አሁን ችግሩን ማዉራት መደጋገም መፍትሔ አይሆንም። ስለመከራው፣ ስቃዩ፣ እንግልቱና ችግሩ የመገናኛ ብዙኃኖች አወሩልን፣ እኛም ብዙ አወራን፣እያወራንም ነው። 
የሁላችንም ውሳጣዊ ጥያቄ ከዚህ አስከፊ መከራና ስቃይ እንዴት እንላቀቅ?እንዴት ነጻነታችንን እንጎናፀፍ?እንዴት ወደነበርንበት ክብር እንመለስ?የሚለው ስለሆነ በዚህ ዙርያ ለመደርደርያ ያክል ጥቂት ነጥቦችን ላንሳ።
  •  አንድነት መፍጠር፦ ችግር ለመፍታትም ሆነ መፍትሔ ለመፈለግ እኛ አንድ መሆን ይኖርብናል። መግባባት፣ መነጋገር፣ መወያየት በምንችልባቸው ነገሮች ላይ አንድ መሆን አለብን። እኛ በሃሳብ በአመለካከት ከተለያየን እንዴት ችግር ልንፈታ  እንችላለን። ከላይ ባነሳናቸው መሰረታዊ ነገሮች ላይ የጋራ መግባባት ሊኖረን ይገባል። ለአንድ አገር ግዛት፣ ሕዝብና መንግሥት እንደማስፈልግ መግባባት አለብን። በአንድ አገር ውስጥ የተለያየ ቋንቋ፣ ባህል፣እምነት ያለው ህዝብ በአገሪቱ ግዛት አንድ መሆን መቻል አለብን። ይህንን ሊያስተባብርና ሊመራ እንዲሁም አንድ ሊያደርገን የሚችል መንግሥት ሊኖረን ይገባል። ከዚያ ውጭ በቋንቋ፣ በባህል፣ በእምነት እንደተለያየን ሁሉ አንድ ሊያደርገን የሚችል የጋራ የሆነ ነገር ከለሌን ችግሩን በህብረት መቅረፍም ሆነ መቀነስ አንችልም። ስለዚህ መንግሥትም ይህን ተረድቶ ለመለያየት ምክንያት የሆኑ ነገሮችን፣ አንድነታችንን ሊያከስም የሚችሉ ነገሮችን ሊያስወግድልን ይገባል። ብሔር፣ ጎሳ፣ ቋንቋ፣ እምነት እያለ ሊከፋፍለን፣ ሊለያየን አይገባም። ይህን ድርጊት የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ የግል/ሰባዊ መብት ድርጅቶችና ሕዝብ ሁላችንም አግባብ ባለው መልኩ ማውገዝና ማስቆም ይኖርብናል። አንድነት፣ ህብረት ከሌለ ምንም ማድረግ የማንችል ባዶዎች ነንና። የቀደሙት አባቶቻችን በአንድነታቸው ያስመዘገቧቸውን ድል መመልከት እኛ ዛሬ አንድነት እንድንፈጥር ትልቅ ትምህርት ይሆኑናልና። ስለዚህ ዛሬ ላይ እየደረሰ ያለውን አሰቃቂ ድርጊት ለማስቆም  አንድነት ፈጥረን መወያየት፣ መነጋገርና መፍትሔ መፈለግ ትልቁ ሥራችን ሊሆን ይገባል። 
  • አገራዊ ስሜት መፍጠር፦ ሁላችንም በእየአለንበት አንድነት መፍጠር ስላልቻልን አገራዊ ስሜታችንም በእጅጉ ወርዶብናል ማለት ይቻላል። ወጣቱ ስለአካባቢው እንጂ እንደ አገር ማውራት አቁመናል። ስለ ኢትዮጵያ ሲወራ እንደ ሁለተኛ ሦስተኛ ዜጋ ሁነን ቁመን የምንሰማ በርካቶች ሁነናል። ኢትዮጵያዊነት ምን ማለት እንደሆነ ትርጉሙም ስሜቱም ጠፍቶብናል። ወጣቱም ብሔርን፣ ቋንቋን ይሰብካል። የፖለቲካ ድርጅቶችም ይህንኑ ያስተጋባሉ። ለአገር ሳይሆን ለብሔር ብቻ የቆሙ ናቸው። መንግሥትም ለስልጣን ማራዘሚያ ሲል አገራዊ ስሜት እንዲጠፋ ምክንያት ሁኗል። ይህን ከባድ ችግር አሶግደን አገራዊ ስሜት ሰንቀን ኢትዮጵያዊነት ምን ማለት እንደሆነ ከተረዳን አሁን በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን ችግር ማስቆም እንችላለን። አገር ወዳዶች ከሆን በቀላሉ ከአገር አንወጣም። አገራዊ ስሜት በውስጣችን ከነገሰ ለአገር፣ ለወገንና ለክብራችን ዘብ እንሆናለን።  በዚህ መልኩ ችግሩን ከአምላክ ጋር ማስዎገድ ይቻላል።
  • ዜጎች ሕጋዊና አግባብ ባለው መንገድ እንዲወጡ ማድረግ፦ እኛ ሁላችንም ማለት ይቻላል አገራዊ ስሜት ስለሌለንና ዜጋ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ስለማይገባን ከመንግሥት ጀምሮ ሰዎችን ወደ ውጭ ማስወጣት እንደ አንድ የገቢ ማስገኛ መንገድ አድርገነዋል። ዜጎች ሕጋዊ ሁነው እንዲወጡ ሳይሆን ገንዘብ ከፍለው በተሳሳተ መንገድ ሲሄዱ ይመለከተኛል የሚል አካል ባለመኖሩ ችግሩ እንዲባባስ አድርጎቷል። ኤጄንሲ ነን ባዮች ለሚያገኟት ሽርፍራፊ ሳንቲም እንጂ የዜጎች መከራና ስቃይ አይገዳቸውም። ይህን ችግር ለመቅረፍ ማንኛውም ሰው ከአገር ሲወጣ በሕጋዊ መንገድ እንዲወጣ ቢደረግ አማራጭ መፍትሄ ነው። ይሁን እንጂ በሕጋዊም ሆነ በሌላ መንገድ ከአገር የወጣን ሰው እንደ ዜጋ ሰባዊ መብቱ ሊከበርለት የሚችልበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርብናል። ኤጄንሲዎችም ገንዘብ ላይ ብቻ ሳይሆን ለሚልኳቸው ሰዎች ደኅንነትና ክብር እንዲያስቡ ማድረግ። ይህን ጉዳይ የሚመለከተው ሁሉ በኃላፊነት ይዞ ቢቀሳቀስ ችግሩን በመጠኑም ቢሆን መቀነስ ይቻላል።
  • ኤምባሲዎች/ቁንስላዎች የዜጎችን መብት እንዲያስከብሩ ማድረግ፦ መቼም በየአገራቱ የተሰየሙት ኤምባሲዎች/ቁንሰላዎች ፓስፖርትና መታወቂ ለማደስና መሰል ጉዳዮችን ለማስተናገድ ብቻ አይመስለኝም። ይልቁንም በቅርበት ሁነው የዜጎችን መብት ማስከበር እንደ አንድ ትልቅ ኃላፊነት ይወስዱም ዘንድ እንጂ። ስለዚህ እነዚህ አካላት በዋናነት በሕጋዊም ሆነ በሌላ መንገድ የገቡትን ዜጎች መብት ከሚኖሩበት ሕግ አንጻር ማስከበር ተቀዳሚ ተግባር ማድረግ አለባቸው። የአሰሪና ሰራተኛ የስምምነት ውሉንም በሚገባ ማየትና ማስፈጸም ይኖርባቸዋል። ከክፍያ መጠን ጀምሮ ማየትና ከመግሥት ጋር ወጥ የሆነ የውል ስምምነት እንዲኖር መወያየት አለበት። አንድም ሰው ቢሆን ዜጋ ነውና መብቱ ሊከበርለት ይገባል። ይህን ማድረግ የሚችሉ የኢምባሲ/ቁንስላና ዲፕሎማት ሰራተኞ ያስፈልጋሉ። ይህን ማድረግ ከተቻለ ችግሩን በቀላሉ መቅረፍ ይቻላል። ሌሎች የሲቪክ ማህበራትም ሆነ የፖለቲካ ድርጅቶችም ይህን ይፈጽሙ ዘንድ ትችት ብቻም ሳይሆን እገዛ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብየ አምናለሁ። ከዚያ ውጪ ግን ልቅሶ፣ዋይታ፣ መከራና እንግልት የዘወትር ተግባራችን እንደሆነ ይቀጥላል ማለት ነው።
  • በዜጎቻችን ላይ ኢ_ሰባዊ ድርጊት ፈጻሚዎችን በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት መጠየቅ፦ ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን እንዲሉ...አገሪቱንና መንግሥትን ቢንቁ እንጂ በዚህ በ21ኛ ክፍለ ዘመን ማን የማነን ዜጋ ከሕግ ውጭ ይነካል። ሕጋዊ ባይሆንና ወንጀል እንኳ ቢሰራ በሕግ አግባብ ይቀጡታል እንጂ እንደ አሸባሪ በአገኙበት ቦታ ደሙን አያፈሱም፣ አካልን አያጎሉም። ምክንያቱም የሰባዊ መብት፣ የዓለም አቀፍ ሕግ አይፈቅድላቸውምና። እኛን ግን ተቆርቋሪና መንገሥት እንደሌለን ካለ ሕግ በአደባባይ ገደሉን፣ ወገሩን፣ ደፈሩን። እንደ እንስሳ ውሻ እየተባልን ክብራችን ይዋረዳል። የማንነታችን መገለጫ የሆነው ባንዲራችን በደም ታጠበ። በዚህ በሰለጠነ ዘመን ሴት እህቶቻችን በየመንገዱ እንዲወልዱ ተደረገ፤ ተደፈሩም። ስለዚህ ይህን ዘግናኝና አሰቃቂ ድርጊት ፈጻሚዎችንና የአገሪቱ መንግሥትን በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት መጠየቅና ለተባበሩት መንግሥታት አቤት ማለት። ይህን ደግሞ ከአገራችን መንግሥት ስለማንጠብቅ ሙያዊና ተሰሚነት እንዲሁም አቅሙ ያላቸውን ሰዎች በጊዛዊ ኮሚቴ አቋቁሞ ክስ መመስረትና ጉዳዩን መከታተል ከተቻለ ለዘላቂም መፍትሔ ትልቅ አስትዋጾ ያደርጋል፤ ለተጎዱ ወገኖቻችንም በዚህ መልኩ አለን ልንላቸው ይገባል። 
  • ጸሎት ወደ ፈጣሪያችን ማቅረብ እና በሰላማዊ መንገድ ድምጻችንን ለዓለም ሁሉ ማሰማቱ እንደተጠበቀ ሁኖ........

Monday, November 11, 2013

ነጻነት ወይስ ቅኝ ግዛት/ባርነት

ቅኝ ግዛት ማለት የአንድ ሃገር ህዝቦች የሌላውን ሃገር ህዝቦች በቁጥጥር ስር በማዋል የሚደረግ ግዛትን የማስፋፋት ስርዓት ነው። በዋናነት ቅኝ ግዛት የሚገልጸው ከ15ኛው እስከ 20ኛ ክ/ዘመን ያለውን የአውሮፓ ሀገሮች የአፍሪካን፣ ሰሜን አሜሪካን እና የእስያ ሃገሮችን የተቆጣጠሩበትን ዘመን ነው። በዚያ ዘመን ቅኝ ገዥዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያን የራሳቸው ግዛት ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሙከራ አድርገዋል። ለምሳሌ፦
ከ1521_1535 ግራኝ መሐመድ በቱርኮች እገዛ ያደረገው ጦርነት
ከ1824_1832 የግብጦች ተደጋጋሚ ወረራ /በባሕረ ነጋሽ እንዲሁም በ1867_68 ጉንዳጉንዲትና ጉራዕ ላይ
በ1877 ከደርቡሾች ጋር በተካሄደው እልህ አስጨራሽ ጦርነት ኢትዮጵያውያን አርበኞች ድል ነስተው ሰንደቃላማ ከፍ አድርገው አውለብልበዋል።
እንዲሁም ምዕራባውያን የውርደት ካባ የተከናነቡበትን የ1896 የአድዋ፣ የ1928_1935 የነበረውን የኢጣሊያ ጦርነት በቃላት መግለጽ ከምንችለው በላይ ጀግኖች አባቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው በአሸናፊነት ከእነሙሉ ክብሯ አገራቸውን ለትውልድ ማስተላለፋቸው ኢትዮጵያ አገራችን ለአፍሪካውያን የነጻነት ምሳሌ ለምዕራባውያን ደግሞ የውርደት ካባ ያከናነበች መሆኗን በታሪክ ትጠቀሳለች። በዚህ ምክንያት ዛሬ እኛም ስለ አገራችን መናገር ስንጀምር በቅኝ ግዛት ያልወደቀች ብቸኛ አፍርካዊት አገር ብለን ለንግግራችን መግቢያ እናደርገዋለን። በመቀጠልም የራሷ ያልተከለሰ ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነትና ታሪክ ያላት ብለን አፋችንን ሞልተን እንናገራለን።
የጽሁፌ መነሻ ግን በተለያየ መልኩ ስለምናውቀው የቅኝ ግዛት ታሪክ መተረክ አይደለም። በዚህ ዙርያ በርካታ የታሪክ ሙህራን በስፋት መዝግበው አስቀምጠውልናል። ነገር ግን ዛሬ ላይ ማየት ያለብን ትልቁ ነገር ትናት በአባቶቻችን ጀግንነት በቅኝ ግዛት ያልተደፈረች አገር ዛሬ ምን ደረጃ ላይ አለች? ህዝቧ በነጻነት እየኖረ ነው? ዛሬም ከግዞት ነጻ ናት? ወይስ ታሪክ ብቻ የሚለውን በአጭሩ የራሴን እይታ ለማስቀመጥ ነው።
በመጀመርያ ነጻነት ማለት ምን ማለት ነው? ነጻነት የሚለውን ቃል ሰዎች የተለያየ አተረጓጎም ሊሰጡት ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን ነጻነት ማለት ከግዞት መውጣት፤ ከሌሎች ተጽኖዎች መውጣት፤ በራስ መወሰን ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ማንም ሌላ ሰው ሳያስገድደን እና የማንንም መብት ሳንነፍግ በነገሮች ላይ በራስ ወይም በጋራ መወሰን መቻል ነው፡፡ ደሞክራሲ ሊባልም ይችላል፡፡ ነጻነት አለ ካልን ሃሳባችን ወይም ተሳትፏችን ተሰሚነትና ተቀባይነት አለው ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ይህንን በተግባር ለመተርጎም እኛ መብታችንን ማወቅ ግዴታችንን ደግሞ መወጣት ይኖርብናል፡፡
ይህንን ጥሬ ትርጉም ይዘን በኢትዮጵያ ላይ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት "ነጻነት" የሚለውን ቃል እንኳ ለመጠቀም አስቸጋሪ ነው ብዬ አምናለሁ። በእርግጥ ትናት አይካድም ቅኝ ግዛት አልተገዛንም፤ የማንነት ችግር አልነበረብንም፤ በሌሎች ዜጎች ዘንድ ከበሬታና መፈራት ነበረን፤ ይህን ያክል የጎላ የምጣኔ ሃብት ችግር አልነበረብንም፤ ተስፈኞችና ሰላማውያን ነበርን፤ ለታሪክ፣ ለሃገር፣ ለወገንና ለማንነቱ የሚጨነቅና የሚቆረቆር ትውልዶች ነበርን። ዛሬ ግን ይህ ሁሉ ከእኛ ርቋል። አይዞህ ባይ ጠበቃ የሌለው፣ ተስፋው የጨለመ፣ ለሃገሩና ለማንነቱ የማይጨነቅ ተስፋ ቢሶች ሆነናል። በሀገር ውስጥም ሆነ በስደት አንገታችንን ደፍተን ነጻነታችንን አጥተን ሰሚ ያጣን ትውልዶች ሁነናል። ትናንት አባቶቻችን በተለያየ መልኩ በስደት ከሃገር ሲወጡ ዜግነታቸውን ሲጠየቁና ኢትዮጵያዊ ብለው ሲናገሩ ኢትዮጵያ የሚለው ስም የኩራት ስሜትና ክብር ያገኙበት ነበር።
ዛሬ ላይ ግን በተቃራኒው ሁኗል። ኢትዮጵያዊ ነኝ ለማለት የውስጥም የውጭም ችግሮች አጣብቂኝ ሁነውብናል። ግን ለምን? እንዴት? መከበርያ የነበረች ሀገር ዛሬ ህዝቦቿ በሄድንበት ሁሉ ዋይታ፣ ሰቆቃ፣ መከራና ስቃይ ስለምን በዛብን???
"እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የዋይታና የመራራ ልቅሶ ድምፅ በራማ ተሰማ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች።" (ኤር 31፥15) የተባለው ተፈጸመ። (ማቴ 2፥17) ተብሎ የተነገረው ለኢትዮጵያውያን ይሆን እንዴ እያልኩ አለመሆኑን እያወኩ ግን እራሴን እጠይቃለሁ። ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን እስራኤላውያን በእነ ያዕቆብና በልጁ በዮሴፍ ጊዜ ታላቅ ክብርና ዝና ነበራቸው። ያዕቆብና ዮሴፍን የማያውቅ ጨካኝና አረመኔ ንጉሥ በተነሳ ጊዜ ያ የነበራቸው ክብር፣ ሰላምና ነጻነት አጥተው በተቃራኒው ዋይታና ሰቆቃ ሆነ። ራሔልና መሰሎቿ ከስቃያቸው መብዛት የተነሳ እጅግ አለቀሱ። እግዚአብሔርም ልቅሷቸውን ሰማ ከባርነትም ነጻ ይወጡ ዘንድ ሙሴን፣ እያሱንና ካሌብን አስነሳ፤ ነጻም ወጡ። የእኛም ነገር ዛሬ ይኸው ነው፤ የአባቶቻችን ጀግንነት፣ታሪክ፣ መልካም ሥራ ሁሉ ተረስቶ የፈርዖያውያን መቀለጃና እልህ መውጫ የሆነው። እስራኤላውያን በራሔል ልቅሶ በሙሴ አማካኝነት ነጻ እንደወጡ ሁሉ ለእኛም ሙሴና ራሔል ያስፈልጉናል።

                            ራሔል ራሔል እስኪ አልቅሽ?


አልቅሽ እንጂ ራሔል የምን ዝምታ ነው
ልጆችሽ በስቃይ ነጻነት ናፍቃቸው 
ልጆችሽ በስደት ወሃ እየጣማቸው
እንዲሁም በእስር ቤት ዱላ ቀለባቸው  
ከፊሎች በቤት ውስጥ ስቃይ በዝቶባቸው
ሌሎች ብቸኝነት እያሰቃያቸው 
የሚናገሩበት አንደበት አጥሯቸው 
ጾታዊም ጥቃት ሲደረግባቸው
ዓለም በአንድ ጎራ ሁሉም ሲንቃቸው
አያውቁም! እነሱ ኋላ ቀሮች ናቸው
መጤ ህገ ወጦች....
...እያለ የዓለም ህዝብ በግፍ ሲገፋቸው 
ይኸው የልጆች ተደፋ አንገታቸው
ቀና ብሎ መሄድ እኮ ተሳናቸው
 ራሔል እስኪ አልቅሽ ይህንን ለውጭው። 

አይ ራሔል እንዳልሰማሽ ዝም አልሽ
አጣሽ እንዴ ይህን ታሪክ የሚነግርሽ 
የልጆችሽን የበደል ፅዋ የሚያዋይሽ
ጠፋ እንዴ ደግ ሰው የሚነግርሽ
ነው አንቺም እንደሌሎች ዝም አልሽ?
 ራሔል በዛብን መከራ ከልብ አልቅሽ።

አምላክ ሆይ እባክህ ሰው አስነሳ 
ለሀገር ለወገን የሚያስብ የሚሳሳ
ጀግና ጎበዝ እንደ ሳምሶን አንበሳ
ለወገኖቹ የሚቆም ዘብ አለኝታ 
እንደ ሙሴ የሚሆን መከታ 
ፈጣሪ እባክህ ሰው አስነሳ 
የራሔል እንባማ አለቀና ሳሳ።
ካለእሱ አይሆንም ሙሴን ላክላቸው
አረመኔዎችን ጸጥ እንዲያስላቸው
ለያሱም ለካሌብ ሙሴ አለ በላቸው
ለራሔልም ልጆች እሱ ነው ኃይላቸው።

በሉ የራሔል ልጆች ተዘጋጁ
ሁሉም ያለውን ይያዝ በእጁ
ስደት መከራ ይብቃ ነጻነትን አውጁ።

ራሔል ሆይ አቤት በይ እንጂ ኢትዮጵያ
የልጆሽ ደራሽ የጭንቀት ማረፊያ
አለሁ በይን እንጂ አንቺ የኛ መግቢያ
 ራሔል እስኪ አልቅሽ ለእምዬ ኢትዮጵያ
ለእናት ሀገራችን ለእኛ መከበርያ።


በእውነት ዛሬ በእጅጉ የራሔል ልቅሶና ሙሴ ያስፈልገናል። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን በአረብ ሃገራት በተለይ ደግሞ የሰሞኑ በሳውድ አረቢያ የሚደርስባቸው ግፍና መከራ፣ እንግልት፣ ስቃይና ሞት ከበቂ በላይ ማስረጃ ነው። ኢትዮጵያ ለዜጎቿ የሚቆረቆር መሪ ባለመኖሩ ዜጎቿ ያለምህረት በፖሊስና በህዝቡ እየታረዱና አካላቸው እስኪጎድል ደማቸው እንደጎርፍ እስኪወርድ ድረስ እየተደበደቡ ነው።
 ማን ሃይ ይበልላት? ማን ያልቅስላት? ማን ይጩህላት? መሪ ነን ባዮች ራሳቸው ችግሩ የጎላ እንዳልሆነ ለአለም መንግሥታት በመገናኛ ቢዙኃናቸው አዋጅ እየተናገሩ በየት በኩል ዓለም ይረዳን።
የቀደሙ ነገስታት ግን ለአገራቸው፣ ለዜጋቸው ሲሉ ራሳቸውን አሳልፈው እስከ መስጠት ደርሰው ነበር፤ ሰጥተዋልም። ዛሬ ላይ ያለው መሪ፣ መንግሥት ነኝ ባዩ ግን ለወጣቱ የስደት፣ ለቀሩት ደግሞ የሃዘን፣ የስቃይና የችግር ምክንያት ሆኗል።

በአጭሩ እኛ ምን እናድርግ???
  1. ከመንግሥት፦ ከኢትዮጵያ መንግሥት ምንም መፍትሔ ስለማልጠብቅ ብዙ ባልል ደስ ይለኛል። ከኢትዮጵያ መንግሥት ይልቅ መንግሥት አልባዋ የሶማሊ ዜጎች ተከብረው ይኖራሉ። እኛ ግን አንቱ የተባለ መንግሥት እያለን ( አንቱታው በእነርሱ አነጋገር/ በእየ ክፍለ ዓለማቱ በእንግልትና በስቃይ ውስጥ እየኖርን ነው። በእየ ሀገሩ ያሉት ኢምፓሲዎች፣ ዲፕሎማቶችና አምባሳደሮች ለገቢ ማሰባሰቢያ እንጂ የዜጎች ችግርና መከራ ቅጣት ታክል አይገዳቸውም። በዚህ ሁኔታ መፍትሔ ከመንግሥት መጠበቅ የዋህና ቂል ያስመስላል። ከቻለ እና ቅንነቱ ካለ ለስደት ምክንያት መሆኑን ተረድቶ ራሱን
    ማስተካከልና መፈተሽ ቢችል ትልቁ መፍትሔ ከእርሱ ጋር መሆኑን መረዳት ይችላል።
  2. ከቤተ እምነቶች፦ ከእነርሱ የሚጠበቀው በተለያየ ስቃይና መከራ ውስጥ ላለው ህዝብ የ ራሔልን እንባ የተቀበለ አምላክ የእኛንም ልቅሶና ጩኸት ይቀበል ሰንድ ወደ ፈጣሪ በጸሎት ማሳሰብ።
  3. ከታዋቂና ተሰሚነት ካላቸው ሰዎች፦ ምንም እንኳ በተለያየ ጊዜ ለዓለም መንግሥታትና በቀጥታ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ችግሮችን ማሰማቱን ባታቆሙም ዛሬም ያለመሰልቸት ተደጋጋሚ ግፊት ማድረግና ችግሩን ማሳዎቅ።
  4.  ከእኛ ከሁላችን፦ ነግ በእኔ ብለን በጸሎት ወደ ፈጣሪ፣ እንዲሁም ባለንበት ቦታ ሁሉ በሰላማዊ መንገድ ድርጊቱ ኢ_ሰባዊ እንደሆነ ለዓለም መንግሥታትና ህዝብ ጩኸታችንን ማሰማት።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያውያን ላይ በአገር ውስጥ የአገር ውስጥ ቅኝ ገዥዎች፣ በውጭ የእነርሱ ቢጤዎች በዜጎቿ ላይ የመከራ ሸክም እየጫኑብን፤ ሰሚ በማጣታችን ተስፋ ቆርጠን እንገኛለን። ማንም እንደለለን ተረድተን ችግሩን ተቋቁመን ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ቆርጠን መነሳት ይኖርብናል።ነጻነታችንን የምንጎናጸፈው እንዴት? መቼ? በምን መልኩ? የሚለውን ጥያቄ ሁላችንም እንወያይበት,,,,,,,,,,,,,