እኛ ኢትዮጵያውያን ዝምታ ወርቅ ነው
እየተባልን ማደጋችን የጠቀመንን ያክል ጉዳቱም በዚያው ልክ ከፍተኛ ሆኗል። እውነት ነው በዝምታ ውስጥ ትዕግስት ፣ ማስተዋልና አርቆ አሳቢነት
ይንጸባረቅበታል። ይህንን የማይረዱ አካላት ግን ፍርሃት ወይም ድንቁርና ይመስላቸውና ሰባዊና ዲሞክራሲያዊ መብታችንን ይገፋሉ፣ ይነጥቃሉ፣
ይጨቁናሉም። ሁልጊዜም በዝምታ ውስጥ እንድንኖር ይመክራሉ፣ ያበረታታሉ፣ ያስፈራራሉም። ዛሬ የመገናኛ ብዙኃን በረቀቀበትና በተስፋፋበት ዘመን ያለውን
እውነታ ግን በሚገባ እናውቃለን። ነገር ግን እውነትን በውስጣችን አፍነን መናገር እየቻልን እንዳንናገር፣ መስራት እየቻልን እንዳንሰራ፣
ለውጥ ማምጣት እየቻልን እንዳንለወጥ፣ ነጻነትና ዲሞክራሲን መጎናጸፍ እየቻልን የነጻነት እጦት እያሰቃየን ለዘመናት በአምባገነን
ስርዓት ተጉዘናል። ከመቼውም በበለጠ ደግሞ ዛሬ ላይ ችግሩ ገዝፎና እጥፍ ድርብ ሁኖ ለብዙ ወገኖቻችን የስደትና እስራት ምክንያት
ሁኗል።
እርግጥ ነው ዝምታን ሰብረው ስለ ነጻነት ብዙ የተናገሩ፣ የጻፉ እና በአደባባይ የመሰከሩ ሰዎች እጣ ፈንታቸው ወደ እስር
ቤት ተወርውረው የህሌና እስረኞች ሆነው ወርቃማ ጊዜያቸውን የአለግባብ እንዲያሳልፉ መደረጉ ይታወቃል። ለእነዚህም እውነተኛ ኢትዮጵያውያን
ስቃይና መከራ መብዛት አይነተኛ ምክንያት የእኛ የብዙዎቻችን ዝምታ መጨመሩ ነው። ምንም በደል ሳይገኝባቸው በሀገራቸው አረመኔያዊ
ቡድን ሲታሰሩ፣ ሲደበደቡ፣ ሲንገላቱ፣ ውድ ህይወታቸው በከንቱ ሲሰዋ እያየንና እየሰማን “ነግ በእኔ” የሚለውን እረስተን በዝምታ
ቁመን እንመለከታለን። ብዙዎቻችንም ችግሩን የግለሰብ ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች ወይም ደግሞ የሰባዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ብቻ እናደርገዋለን።
ምስጋና አይድረሳቸውና ወያኔዎች “እኩልነትን” በተግባር የሚያሳዩበት ትልቁ ተቋም እስር ቤት ነው። ማንኛውም ስርዓቱን የሚቃዎምም
ሆነ ግላዊ አስተያየት ሰጪ ሴት፣ ወንድ፣ ወጣት፣ ጎልማሳ፣ አዛውንት ሳይባል ሁሉም በእኩልነት ስቃይ፣ መከራና እስራት ይጠብቀዋል።ከመተቸት/
ከመቃወም እራሱን እስካልገታ ድረስ የወያኔ የማሰቃያ ቦታዎች በራችውን ከፍተው ዘወትር ይጠባበቃሉ። ወገኖቻችን ለነጻነት ብለው ሲታገሉ፣
ለዲሞክራሲ ብለው ሲደሙ፣ ለእኩልነት ብለው ህይወታቸውን አሳልፈው ሲሰጡ እኛ በምን አገባኝነት ቁመን እናያለን። ይህን እኩይ ተግባር
ለማስቆም ህዝብ እንደ ህዝብ በአንድነት ከመናገር ይልቅ ዝምታን ስለመረጠ ለወያኔዎች ጋሻና መከታ ሆኗቸዋል።
ወያኔዎች ለሥልጣን ማራዘሚያ አይነተኛ መሳርያ አድርገው የሚጠቀሙበት የህዝብን ዝምታ ነው። ጸሎት አይሉት ድሎት ህዝብ በአርምሞ
ውስጥ ”ተመሰገን ማለት ነው የባሰ እንዳይመጣ መጸለይ ነው“ እያለ እንዲኖር በተለይ የወያኔ ተላላኪ የሀይማኖት መሪዎች ሳይቀሩ
ህዝብን ለዝምታ ይገፋፋሉ። ወያኔወችም ዝምታን ለማስፈን በአጽንኦት ይሰራሉ፤ ተሳክቶላቸዋል ማለትም ይቻላል። ወያኔዎች ለክፋትና
ለተንኮል፣ ሀገርን ለማጥፋት ህዝብን ለመበደል ያእቀዱትን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የሚደርስባቸው የለም። ምክንያቱም ሰውን ለመግደልም
ሆነ ለማሰቃየት ምንም አይነት ሰባዊ ርህራሄ የሚባል ነገር በውስጣቸው የለምና።
መቼም በዚህ በአለንበት በሰለጠነው ዘመን የወያኔ አምባገነናዊ አገዛዝ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ይበጃል፣ ይጠቅማል፣ ይመጥናል
የሚል ህሊና ያለው እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብሎ መገመት ያዳግታል። ሥርዓቱ ከአምባገነናዊነት ባሻገር ብሄራዊ ቀውስ እና የሀገርርን
ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባ፣ የብዙ ንጹኃንን ደም ያፈሰሰ፣ ብዙዎችን ለስደትና እስራት የዳረገ አረመኔያዊ አገዛዝ ነው። በዓለም
አቀፍ ደረጃም ይህ የወያኔ እኩይ ተግባር የተገለጠና የተመሰከረለት ነው። ለዚህም መረጃም ማስረጃም እኛው እራሳችን ነን። በዝምታ
ውስጥ የማንኖር እና እንደ ሀገር የምናስብ ከሆነ በቀጥታ ማስፈራርያ፣ ዘለፋ፣ እስራትና እንግልት በወያኔዎችና ተላላኪዎች ደርሶብናል፤
እየደረሰብንም እንገኛለን። ነገር ግን ይህ ገደብ የለሽ ማስፈራርያ ለዝምታችን ምክንያት መሆን የለበትም፤ ይልቁንም ለመብት፣ ለነጻነትና
ለዲሞክራሲ እንድንነሳ ግፊት ያደርጋል እንጂ። እውነት ነው ፍርሃት እስኪመስል ድረስ ዝምታችን በእጅጉ በዝቷል፤ የዝምታችንም ውጤት
ለወያኔወች አረመኔያዊ ኃይል እንዲያገኙ እና በወገኖቻችን ላይ ሰይጣናዊ ድርጊት እንዲፈጽሙ፣ ጥጋብንና ማንአለብኝነትን እንዲላበሱ
እድል ፈጥሮላቸዋል።
እንደሚታወቀው በየአምስት ዓመቱ የይስሙላና የቅርጫ ምርጫ በደረሰ ጊዜ ለሀገርና ለወገን ዴንታ የሌለውን ጥቅመኛ ቡድን ፍትሃዊ
ምርጫ ለማስመሰል መራጭ በማድረግ አብዛኛውን ህብረተሰብ ደግሞ በዝምታ እንዲያሳልፍ ይደረጋል። ይህ ሥርዓት ለሀገር የሚበጅ ሥርዓት
አይደለምና ይወገድ ብሎ እንዳይናገር “ብንናገር እናልቃለን” የሚለውን የሞኝ ፈሊጥ እንዲያስተጋባ የዝምታ ካባ ይደረብለታል። ምርጫው
እንደሆነ የተበላ እቁብ መሆኑ ዓለም በሙሉ ያውቀዋል። በወያኔ “በጎ ፈቃድ” በምርጫ እንዲሳተፉ የተደረጉት ተቀዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችም
ምርጫውን ዲሞክራሲያዊ ለማስመሰል ቅመም ወይም ቅባት እንጂ ወያኔ በስልጣን ላይ እያለ መቀመጫ ወንበር አግኝተው ፓርላማውን እንዲቀላቀሉ
አይደለም። ውይይት፣ ትችት፣ ማካፈልና አብሮ መስራት የወያኔ ባህሪ
አይደለም። 24 ዓመታት የወያኔን ስርዓት በሚገባ አይተናል፤ ባህሪውንም ተረድተናል። “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንዳለች አህያ
ህዝብና ሀገር ለማጥፋት በአህያ አስተሳሰባቸው ተግተው እየሰሩ ነው።
የተባበሩት የዓለም መንግስታት፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ዲሞክራሲን የሚናፍቁ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ግለሰቦች የኢትዮጵያ ምርጫ
የይስሙላና ኢ-ፍትሃዊ እንደሆነ ከአለፉት ምርጫዎች ስላረጋገጡ ከመታዘብ እራሳቸውን አቅበዋል። እውነት ነው ለውጥ ለማይመጣ ነገር
ገንዘብ፣ ጉልበትና ጊዜ ማቃጠሉ ከንቱ ነው። እኛም በምርጫ ለውጥ እንደማይመጣ በሚገባ እናውቃለን፤ ግን ዝምታችን እስከ መቼ ይዘልቃል? በዝምታስ ለውጥ ማምጣት ይቻላልን? በዝምታ ለውጥ ያመጣ ሀገር
በታሪክ አጋጣሚ ተዘግቦ አላየንም። እውነት እላችኋለው “እውነትን እውነት፡ ሀሰትን ሀሰት” እስካላልን ድረስ ለውጥ ሊመጣ በፍጹም
አይችልም። ነጻነትን፣ ፍትህንና ለውጥን እኛ እናመጣዋለን እንጂ እራሱ በር አንኳኩቶ ሊመጣ አይችልም።
ጭቆናው ጨምሯል! ሰው በሰውነቱ፣ በኢትዮጵያውነቱ፣ በተግባሩና በሥራው ሳይሆን በማንነቱ፣ በሚናገረው ቋንቋ፣ በተወለደበት
አካባቢ ስም እየወጣለት ለስቃይና ለመከራ ይዳረጋል። የሥጋ ቆጠራ
ይመስል የዘር ግንዱ እየተመዘዘ፣ የተጸውዖ ስም ሳይቀር እየታየ አድሎ ይደረግበታል። ወያኔን የሚቃረን የፖለቲካ አመለካከት ማንጸባረቅ
እንኳ የማይታሰብ ነው። ወያኔዎች የጸረ ሽብር ህጉን ተፈጻሚ የሚያደርጉት በእንዲህ አይነት ሰዎች ላይ ነው። ይህን እያየንም፣ እያወቅንም
ዝምታ!
ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማርያን፣ የሰባዊ መብት ተሟጋቾች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ተማሪዎች፣ ነጋዴዎች፣ አርሶ አደሮችና
አያሌ ንጹሃን ዜጎች በግፍ ሲታሰሩ፣ ሲሰደዱና ሲገደሉ በዝምታ ከመመልከት በላይ ምን የከፋ ነገር ይኖራል። ፈሪ የሚል ቅጽል ስም
ቢወጣልንም ስህተት ነው የማለት የሞራል ድፍረት አይኖረንም። አዎ ብዙዎች በግፍ ሲታሰሩና ሲሰደዱ በዝምታ ተመልክተናል፤ ዛሬም ሰማያዊ
ወይም ምዕራባዊ ኃይል እየጠበቅን ይሆን እንጇ ቁመን እያየን ነው። ለውጥ ለሌለው የይስሙላ ምርጫ ጆሮአችንን ሰጠን የወያኔን ተራ
የሀሰት ወሬ በዝምታ ውስጥ ሆነን እየሰማን እንገኛለን።
በአጠቃላይ የእኛ ዝምታ ለወያኔች መከታ፣ ስልጣን ማራዘሚያ፣ ሃብት ማካበቻ፣ ድንቁርና፣ ማንአለብኝነት ማጎልበቻ ሲሆናቸው
ለሀገራችን ኢትዮጵያ ድህነት፣ ኋላ ቀርነት፣ ለውጭ ዜጎች ገነት ለልጆቿ ሲዎል እንድትሆን ሲያደርጋት ለእኛ ለህዝቧ ደግሞ እስራት፣
ስደት፣ እንግልት፣ መከራ፣ የነጻነትና ፍትህ እጦት፣ የመብት ጥሰት እና ውርደትን እንድናስተናግድ አድርጎናል። እኛ በሌሎች ሀገሮችም
ሳይቀር እንደ ሰው እንዳንታይ እና ክብር እንድናጣ ዝምታችን አሉታዊ አስተዋጾ አድርጓል።
ስለዚህ ዝምታን በመስበር “የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውን እንመሰክራለን” እንዲሉ ለሀገር የማይጠቅም ለህዝብ የማይሆን
ይህን አረመኔያዊ የወያኔ አገዛዝ ከስር መሰረቱ ማስወገድ ጊዜ የማይሰጠው የቀን ተቀንና የዕለት ተግባር ማድረግ ይገባናል። ሀገር
ለባዕድ ስትሸጥ፣ ህዝብ በድህነት ሲሰቃይ፣ ብዙዎች በግፍ ሲሰደዱ፣ ሲታሰሩና ሲገደሉ እያዩ እንዳላዩ፣ እየሰሙ እንዳልሰሙ መሆን የታሪክ ተወቃሽ ያደርጋልና ዝምታ ይብቃ።
ሌባን ሌባ ለማለት እንደምንደፍር ሁሉ ወያኔንም የሌቦች፣ የቀማኞችና የወንበደኞች አለቃ ነውና በቃ ከህዝብ ጫንቃ ላይ ውረድ ማለትን
እንድፈር።
ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል እንደሚባለው ዝምታን አስወግደው
ለነጻነትና ለፍትህ የሚናገሩ ብዙ ኢትዮጵያውያን በተለያየ ቦታ ዝምታ ይብቃ እያሉን ነው። በእስር ቤት ሆነውም ሀገራዊ መንፈሳቸው
ነጻነት! ነጻነት! ነጻነት! እያለ በአደባባይ ይሰብካል። እውነተኛ ኢትዮጵያዊ አንደበታቸው ወያኔን ያሸብራል። ሰውን ያክል ክቡር ፍጡር በእስር እያሰቃዩ ፍትሃዊ ምርጫ እያሉ ማውራት አግባብ እንዳልሆነ በዝዋይ፣ በቃሊቲ፣ በቂሊንጦ፣
በማዕከላዊ፣ በሽዋ ሮቢት እና በሁሉም የማሰቃያ እስር ቤቶች የሚገኙ ውድ ኢትዮጵያውያን ድምጻቸው ያስተጋባል። ለይስሙላ ምርጫ ከመሰለፍ
ይልቅ ለነጻነት ተሰለፉ ይሉናል።
ለነጻነትና ለዲሞክራሲ ግንባታ በርሃ ወርደው ብረት አንግበው የሚታገሉ ወገኖቻችን ኑ በህብረት ወያኔን እናስወግድ፤ ጉልበት
ያለህ በጉልበት፣ እውቀት ያለህ በእውቀት፣ ገንዘብ ያለህ በገንዘብ ተደጋግፈን ለተከበረች ኢትዮጵያ እንድረስላት በማለት ሀገራዊ
ጥሪ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። ነገር ግን በያለንበት ወያኔን ማሳደድና ማዋከብ ከቻልን ሁላችንም በርሃ መውረድ ላይጠበቅብን ይችላል።
በተለይ እኛ ወጣቶች!ጉልበታችንን፣ ኃይላችንንና አቅማችንን ተጠቅመን ወያኔን የምናስወግድበትን ስልት በመንደፍ ከሁልጊዜ
ስቃይና መከራ ለተወሰነ ጊዜ ትግል ማድረጉ በእጅጉ የተሻለ ነውና በህብረትና በአንድነት ሀገር የማዳንን ትግል እንቀላቀል። በሀገር
ተከብሮና ተዝናንቶ መኖር ሲቻል ስደትን አማራጭ መንገድ በማድረግ ለባህር ቀለብ፣ ለአሸባሪዎች የትንሳኤ በግ፣ ለአረብ የጥጋብ ማስታገሻ
መሆን የለብንም። በአጠቃላይ ዝምታን በማስወገድ ህዝብን በማስተባበር ነጻነትን ለማወጅ ቆርጠን እንነሳ እላለሁ።
ዝምታ ይብቃና የወያኔን የይስሙላ
ምርጫ በመቃወም ነጻነታችንን ለመጎናጸፍ አማራጭ መንገዶችን እንጠቀም!!!