Tuesday, April 1, 2014

ስደት (ክፍል ፪)


ስደትን በተመለከተ በክፍል ፩( በጻፍኩት ጽሁፍ ላይ ትልቁን ለሰው ልጅ የአእምሮ ረፍትና የወደፊት ተስፋ የሚሆነውን ነጻነት መነፈግ ለኢትዮጵያ ህዝም ብሎም ለዓለም ህብረተሰብ አስቸጋሪ በመሆኑ ለስደት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ገልጨ ነበር። ጠቅለል ባለመልኩ እኛ ኢትዮጵያውያን የመተሳሰብ፣ አብሮ የመብላት፣ በነጻነት የመስራትና የመንቀሳቀስ፣ መሰረታዊ የሰው ልጅ የእዉቀት ደረጃዎችን ማለትም የመጻፍና የመናገር፣ እንዲሁም መንግሥት እራሱ በእራሱ ህገ መንግሥት ነው ብሎ ባረቀቀው "መንግሥት በሀይማኖት ጣልቃ አይገባም ሃይማኖትም እንዲሁ/The state shall not interfere in religious masters and religion shall not interfere in state affairs"(አንቀጽ 113) ያለውን የእራሱን ህግ ሳይቀር በመጣስ የማምለክ ነጻነታችንን በበሬ ወለድ ምክንያት ሲገፍ እና አንድነታችንን፣ ባህላችንንና ለነገ የሚያስበውን ትውልድ ሲያስር፣ ሲያንገላታና ለስደት ሲዳርግ ብሎም ሲገድል ድፍን 23 ዓመት አስቆጠረ።

ይህ የስቃይና የመከራ ዘመን የሚያበቃበትን ቀን እና ስዓት የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያመልከውን አምላክ በመማጸን ላይ ነው። በተቃራኒው የህወሓት አገዛዝ ዘላለማዊ ነኝ ማለቱን ተያይዞታል። ታግሎ ነጻነቱን እንዳያስከብር ከጫካ ጀምሮ የሰራበትን የሥልጣን እድሜ ማራዘሚያ የብሔር ተኮር የዘር የእርስ በእርስ ግጭትና የሀይማኖት ተቋማትን የማፍረስ ፖለቲካ በህዝቡ ላይ በማሰራጨቱ ለነጻነት በህብረት በአንድነት እንዳንታገል አድርጎናል። እርስ በእርሳችን እንዳንተማመን አድርጎናል፤ ከፋፍሎናል። ህብረት አንድነት እንዳይኖረን በማድረግ ለስደት ዳርጎናል።

ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንዳትኖር እና ካርታ እንዳይኖራት አድርጓታል። መለያ ምልክቷን ሰንደቅ ዓላማዋን ቀይሮባታል። በቅኝ ግዛት ያልተንበረከኩ ህዝቦቿን መከራ እና ስቃይ በማብዛት በግድ ለባርነት/ለስደት ዳርጓቸዋል። ሰላም የጠፋበት፣ ተስፋ የሌለው፣ ለማንነቱ የማይጨነቅ፣ ለአገር ለወገኑ የማያስብ ትውልድ መናኽርያ እንድትሆን አድርጓል። በራብ አለንጋ ሳይቀር ሰፊውን ህዝብ እየቀጣ ነው። ከራብ ጦር ይሻላል እንዲሉ ከራብ፣ ከጭቆና ነጻነት ከማጣት ስደትን መረጠ፣ በየአገሩ ስደተኛ ተብለው እንድንኖር አደረገን። አይ ህወሓት የስራችሁን ይስጣችሁ ሌላ ምን ይባላል.....የባለ ዕራዩን (የአምላካችሁን) መለስ ተብዬው እጣ ፈንታ ይስጣችሁ እንዳንል እርግማን ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ የዋህ እና በፈጣሪው የሚያምን ነው እርግማን ፈጽሞ ይጠላል፤ ድህነታችሁን እንጂ ሞታችሁን አንሻም። ስቃዩን፣ መከራውን፣ እስራቱን አቅሉልን እንጂ ጣን ልቀቁ የማይል ህዝብ ነው። እንዳለመታደል ሁኖ እንጂ እንዴት ለዚህ ህዝብ ነጻነቱን ይገፈፋል፣ ማንነቱንና ታሪኩን እንዲያጣ ይደረጋል።

ለአገር እድገትና ብልጽግና ዋነኛ መሰረት ሙያዊ ነጻነት(academic freedom) መሆኑን የዘርፉ ሙህራን ይስማሙበታል። የሰው ልጅ በተፈጥራዊም ሆነ በግላዊ ጥረት እራሱን፣ ቤተሰቡን ከዚያም አልፎ አገርን መለወጥ መቀየር የሚያስችል እውቀት/ሙያ አለው። ሙያዊ ነጻነት ከደሞዝ፣ ከክፍያና ከማንኛውም ጥቅማ ጥቅም በላይ ነው፣ ከሹመትና ሽልማት በላይ ነው። ሁሉም ማለት ይቻላል ሙያዊ እውቀት ለማግኘት ወደ / ዓለም ሲገባ የሚያስደስተውን እና ቢሰራበት የበለጠ ውጤት ማምጣት ወደሚችልበት የት/ መስክ ይገባል። ለዚህ ትውልድ ያገኘውን እውቀት ካለንም ተጽዕኖ መስራት የሚችልበትን መልካም ከባቢያዊ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እና ማስተካከል የነበረበት ዲሞክራሲያዊ እና ልማታዊ ነኝ የሚለው መንግሥት ነኝ ባዩ ፈላጭ ቆራጩ የህወሓት ቡድን ነበር። በተቃራኒው ግን እየሰራ ያለው ገና በለጋ እድሜያቸው ሳይቀር ተማሪዎችን የእርሱ ተከታዮች እንዲሆኑና የብሔር ፖለቲካን ሲዘራባቸው ይታያል። ወደከፍተኛ / ሲገቡም ሲወጡም ለጊዜው ለመኖር ዋስትና (green card) የሆነችውን ቁራጭ ወረቀት (የአባልነት መታወቂያ መሆኗ ነው) ይዘው እንዲወጡና የስራ ዕድል እጣ ፈንታ በዚያ እንደሚወሰን አጠንክሮ መልእክቱን ያስተላልፋል። ለማሳያም ያክል በየከፍተኛ / ተቋማት ውስጥ የመንግሥት ተልኮን የሚያራምዱትን አድር ባዮች ካለሙያቸው፣ ካለ እውቀታቸውና ካለችሎታቸው ከፌደራል እስከ ቀበሌ የየመስርያ ቤቱ ኃላፊዎች እያደረገ ይሾማል። የተለየ ጥቅማጥቅም ይሰጣቸዋል። በሙስና የተጨማለቁ እንዲሆኑ እና በፍራቻ የስርዓቱ ሎሌዎች አድርጓቸዋል።

ይህን እና መሰል ሁኔታወችን በማየት ሁሉም በሚያስብል መልኩ የከፍተኛ / ተቋማት ተማሪዎች ከልባቸውም ባይሆን የገዥው ፓርቲ ደጋፊ እና ተላላኪ እንዲሆኑ ተደርገዋል። ከዛም አልፎ በስራ ላይ ሰራተኛውን ስራውን በአግባቡ እንዳይሰራ ጀርባው እና የሚያደረገውን እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ለማጥናት የስለላ ስራ እንዲሰሩ ይደረጋል። አንድ ለአምስት(15) በሚል ሚስጥራዊ የህወሓት ቡድን ሁሉም እንዲካተቱ እና የፓርቲው አገልጋዮች ተደርገዋል። የቀሩትም ከእጅ ወዳፍ ለማግኘት ሲሉ ወደው ሳይሆን ተገደው በቡድኑ ውስጥ ተካተዋል። በዚህ ቡድን እና ተመሳሳይ እኩይ ተግባር አንተባበርም ያሉት ኢትዮጵያውያን እና እድገቷን የሚሹ እውነተኛ ልጆች ስቃይና መከራ ሲበዛባቸው እና ከእስርና ከሞት የተረፉት ለስደት ተዳርገዋል።

በዚሁ ከቀጠለ አገራዊ ስሜት እና እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ይገኛል ብሎ ማሰብ እጅግ ከባድ ይመስለኛል። ምክንያቱም ለእኛ አገራችንን ከእነ ሙሉ ክብሯ እና ከእነ ታሪኳ ያስረከቡን የደም መሰዋትዕነት ከፍለው ነው። 40ዎች ዓመታት በፊት የነበሩት መንግስታት ምንም እንኳ የራሳቸው ችግር ቢኖርባቸውም ለአገር አንድነትና እድገት፣ ለሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጾ አድርገዋል። እንደ ህወሓት ፓርቲ አገሪቱን አልሸጡም፣ ይልቁንም ለክብሯና ለታሪኳ ይጨነቁ ነበር እንጂ። ህዝቦቻንም እንዲህ በይፋ ለስደት አልዳረጉም። አገርን የሚወድ ትውልድ እንጂ አገርን የሚክድና የሚሸጥ፣ ታሪክን የሚያጠፋ፣ አንድነትን የሚለያይ፣ ባህልን እና ሀይማኖትን የሚንቅ ትውልድ አላፈሩም። ው ነገር ግን መንግሥት ነኝ ባዩ ወያኔ/ኢህአዲግ የቀደሙ ነገሥታትን ሲተችና ታሪካቸውን ሲያጠፋ በይፋ ይታያል።

ወያኔ/ኢህአዲግ ግን ሙያዊ ነጻነት እንኳ ሳይቀር ተነፍገን ተመራማሪዎች እንዳይመራመሩ፣ ደራስያን እንዳይደርሱ፣ ተዋንያን እንዳይተውኑ፣ ጋዜጠኞች እንዳይዘግቡ፣ ነጋዴዎች እንዳይነግዱ(ከእርሱ አባላት በስተቀር) መምህራን እንዳያስተምሩ፣ እና ሁሉም በየሙያ ዘርፉ በነጻነት ሰርተው እንዳይበሉ አደረገ። ከእርሱ ዓላማ እና ተልእኮ ውጭ ማንም ምንም እንዳያደርግ የሞት፣ የእስር፣ የአክራሪነትና አሸባሪነት ህግ አጸደቀ። እስራትና ሞት ፈርተን ብዙዎች ተሰደድን ከስደት እንዳንመለስም ህይወት ናትና ፈራን።

ትናት ስደተኛ፣ ዛሬም ስደተኛ፣ ነገስ??? ነገ ምን አልባት ሙሴ ህዝበ እስራኤልን ከፈርኦን የመከራና የጭንቀት አገዛዝ ነጻ እንዳወጣቸው ሁሉ ኢትዮጵያውያንንም ነጻ የሚያወጣ ታምራዊ ኃይል ሊፈጠር እንደሚችል ባለሙሉ ተስፋዎች ነን። ህዝብ ታምራዊ የለውጥ ኃይል መሆን ይችላል። እያንዳንዱ ዜጋ ለመብቱ፣ ለነጻነቱ ከታገለ ታምራዊ ኃይል ሁኖ ይህን ጨቁኖ የሚገዛን መንግሥት በቀናት ውስጥ ማስወገድ ይችላል።

የኢትዮጵያ አምላክ ሆይ ከስደት የሚታደገንን ሙሴን ላክልን!

እውነተኛ ፍርድ የሚሰጠውን ዳዊትን ላክልን!

በጥበብና በማስተዋል የሚመራውን ሰሎሞንን ላክልን!

Monday, March 24, 2014

ለምን ከምንወዳት አገራችን እንሰደዳለን? ክፍል 1

ከምንወዳት፣ ከአደግንባት፣ የማይረሳ የልጅነት ጊዜያችንን ካሳለፍንባትና አገራችንን ጥለን/ለቀን በባዕድ አገር በስደት በእምነት፣ በባህል፣ በቋንቋ እንዲሁም በአመለካከት ከማይመስሉን ጋር በተለያየ  ፈተናና ውጣ ውረድ እና ለአፍታ በማይዘነጋ አገራዊ ትዝታ እንድንኖር ያደረገን ትልቅ ምክንያት ይኖረናል፤አለንም። ማንም ሰው በአገሩ በሰላም እና በደስታ ባሳደገው ማህበረሰባዊ ባህል መኖር እና ማደግ ይፈልጋል። የራሱ የሆነ በቂ ምክንያት ከሌለው በስተቀር ስደትን ቤቴ ብሎ የሚኖር የለም። ባገሩ በሰላም መኖር የሚችል ሰው የስደትን አስከፊነት እና ትግዕስት አስጨራሽነት ተቋቁሞ መኖር ባልቻለ ነበር። ግን እርሱ ባለቤቱ የሚያውቀው አሳማኝ ምክንያት አለው። 

በእርግጥ ዛሬ ላይ ዓለም ሁሉ ለስደት የዳረገንን ምክንያት ዘመኑ በወለዳቸው ብዙኃን መገናኛዎች ምስክርነት መስጠት ከጀመሩ ጊዜያትን አሳልፈዋል። እውነታውንም በሚገባ ተገንዝበው ለሰሚዓን ምስክርነቱን ቀጥለውበታል። ከፊሎች ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ስሜት የለለውን የመንግስትን ከእውነታ የራቀ ተራ ወሬ ተከትለው ስደተኞችን ሲተቹ እና ሲያንገላቱ ይታያል። እርግጥ ነው ብዙዎች የአፍሪካ መሪዎች የስልጣን ዘመናቸውን የሚያስረዝሙት በሀሰት እና በኃይል ረግጠው እናስተዳድረዋለን እንመራዋለን በሚሎት ህዝብ ላይ የመከራ ቀንበር በመጫን እና በማስጨነቅ ነው። የኢትዮጵያ መሪዎችም የስልጣን ዘመናቸውን ለማስረዘም ያዋጣናል የሚሉትን ማንኛውም መንገድ ይጠቀማሉ። ሲፈልጉ ያጸድቃሉ፤ ሲፈልጉ ይኮንናሉ፤ይሾማሉ፣ይሽራሉ፤ ይገድላሉ፣ ያኖራሉም።

በአገራችን አንድ ገሀዳዊ እውነታ አለ። ህዝቡ አገሩ ከመኖር ይልቅ ወደ ስደት ዓለም የሚሄድባቸውን መንገዶች በማፈለለግ ከጊዜ ወደ ጊዜ የስደተኛው ቁጥር በእጅጉ እየበዛ እና እየጨመረ መምጣቱ ዓለም በአንድ ድምጽ የሚመሰክረው እውነታ ነው። አገርን ያሳድጋል ያለማል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የተማረው ዜጋም ስደትን በመቀላቀል ግንባር ቀደም ቦታን ይዟል። ለአንድ አገር እድገት አይደለም የተማረ ዜጋ ቀርቶ ማንኛም ሰው በተፈጥሮአዊ እውቀቱ፣ ጉልበቱ እና ገንዘቡ አገርን የመለወጥ አቅም አለው። የአደጉ አገሮችን ታሪክ ብንመለከት ወደ ብልጽግናው ዓለም የተቀላቀሉ ያላቸውን የሰው ኃይል በሙሉ በነጻነት ለአገሩ ተቆርቋሪ ሁኖ በቻለው መጠን እንዲሰራ በማድረጋቸው ነው። 
ወደ ኢትዮጵያ አገራችን ስንገባ ግን በተቃራኒው ሁኖ እናገኘዋለን። በጣም የሚያሳዝነው የሚሰራ ሰው፣ የሚናገር ሰው፣ ለእውነት የቆመ ሰው እንዲኖርባት ያልታደለች አገር መሆኗ ነው። የዓለም መነጋገርያ የሆነውን የትናቱን የረዳት አብራሪ ኃይለመድህን አበራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ‪ET702‬ ይዞ ኢጣሊያ መግባት የነበረበትን ወደ ሲዊዝ ጀነባ መሄዱን መመልከት ከበቂ በላይ የነጻነት እጦትን ያረጋግጣልናል።


በብዙ ምክንያቶች ዜጎቿ ስደተኞች ሁነውል። በሚገርም ሁኔታ በአገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎቿም አብዛኞቹ ወደ ስደት የሚወጡበትን አጋጣሚዎች በመጣባበቅ የመንፈስ ስደተኞች ሁነዋል። በተለያየ አጋጣሚ ወደ ውጭ የሚወጣው ዜጋ ወደ አገሩ የሚመለሰው ቁጥር በእጅጉ አናሳ መሆኑን ጥናታዊ ባልሆነ መንገድ የምንሰማቸው እና የምናያቸው መረጃዎች ህያው ምስክሮች ናቸው። ግን ለምን? እንዴት? እስከ መቼ? ህዝቦቿ በስደት የሚሰቃዩት መልስ የለለው የዘወትር ጥያቄየ ነው። ለስደት የዳረገንን አንዱን እና ትልቁን ምክንያት ለማንሳት እሞክራለሁ። 
  
ነጻነት፣ ነጻነት፣ ነጻነት???

ነጻነት የሚለውን ቀጥተኛ ትርጉም በአጭሩ ከዚህ በፊት "ነጻነት ወይስ ቅኝ ግዛት" በሚል ባወጣውት ጽሁፌ ላይ ለመግለጽ ሞክሬ ነበር። (ነጻነት ወይስ ቅኝ ግዛት/ባርነት) በዚህ ጽሁፌ ደግሞ የነጻነት እጦት ምን ያክል ለስደት እንደዳረገን ውስጣዊ ስሜቴን ለመግለጽ እዎዳለሁ።
ነጻነት ተፈጥሮአዊ ነው። እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጠው ትልቁ ጸጋ ነጻነት ነው። እሱን እንድናመልከው እንኳ ነጻ ፈቃድ ሰጥቶናል፤ አላስገደደንም። እግዚአብሔር የፈጠረውን ፍጥረት ሳያስገድድ የኢትዮጵያ መሪዎች ግን እነሱ ባልፈጠሩት፣ ባልሰሩት፣ ምንም ዋጋ በአልከፈሉበት ህዝብ ላይ አምባ ገነናዊ አገዛዛቸውን አስፍተው እኛን ሲጨቁኑን እና መከራ ሲያበዙብን እናያለን። እነርሱ እና የእነርሱ አጫፋሪዎች በነጻነት ይኖራሉ። ብዙኃኑ ህዝብ ግን በነጻነት እጦት ብዙዎች ተሰደዱ፣ ተንገላቱ፣ መከራን ተቀበሉ። ብዙዎችም ነጻነት ይኑር ብለው በመናገራቸው ተገደሉ፣ ታሰሩ፣ ሃብት ንብረታቸው ተወረሰ፣ የሚናገሩበት አንደበት እንዲዘጋ ተደረጉ፣ ለነጻነት የሚጽፉበት ብዕራቸው ተወረወረ እጃቸውም ታሰረ። ቤተ እምነቶችም ሳይቀሩ ነጻነትን በመስበካቸው የአምልኮ ስርዓታቸውን እንዳያካህዱ ተደረጉ። የአምልኮ ቦታዎች በምክንያት እንዲፈርስ ተደረገ። ባህላችንን፣ ታሪካችንን እና ማንነታችንን እንድናጣ ተደረግን። 

የኢትዮጵያ ህዝብ በሁሉም መስክ ነጻነቱ ተገፏል፤ በነጻነት መናገር፣ በነጻነት መጻፍ፣ በነጻነት መደራጀት፣ በነጻነት መሰብሰብ፣ በነጻነት ማህበራዊ ተግባራትን ማካሄድ፣ በነጻነት መስራት እና በነጻነት መንቀሳቀስ እንዲሁም በነጻነት ማምለክ ታሪክ ሆኖብናል። ህዝቡ በእጅጉ ነጻነትን ይፈልጋል። ነጻነት ፍለጋም ስደትን እንደ አንድ ዓቢይ ምርጫ አድርጎ በየቀኑ በብዙዎች የሚቆጠሩ ይፈልሳሉ። የስደትን አስገፊ ህይወት በጸጋ ተቀብሎ መኖር አማራጭ የለለው መፍትሔ አድርገነዋል። የዱር እንስሳት እንኳ ሳይቀሩ የእለት ከእለት ኗሯቸውን በነጻነት ማካሄድ የማይችሉበት ሁኔታ ሲፈጠር ነጻነት ወደሚያገኙበት ቦታ/ጫካ ይሰደዳሉ። የሰው ልጅ ደግሞ ከእንስሳት በተለየ የአስተሳሰብ አድማሱ ሰፊ በመሆኑ ነጻነትን ከምንም በላይ ይፈልጋል። "ጎመን በጤና ይላል" እንዲሉ ነጻነትን ተነፍጎ የቁም እስረኛ ከመሆን ይልቅ በነጻነት በድህነት መኖር አእምሯዊ ረፍት ይሰጣል። 

ስለዚህ የስደታችን ዋነኛ ምክንያት የነጻነት እጦት ነው። የህዝብ ነጻነት እስካልተመለሰ ድረስ ከስደት ወደኋላ ይላል ብሎ ማሰብና መፍረድ የቁም እስረኛ ሁኑ ብሎ እንደመፍረድ ይቆጠራል። ህዝብ ነጻነቱን ካገኘ ሁሉን ነገር ማድረግ ይችላል፤ ሰርቶ ድህነትን ማሸነፍ ይችላል፤ ማህበራዊ ህይወቱ ሰላማዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እድገቱ እውነታ ያለው እድገት እና ፖለቲካዊ አመለካከቱ የሰላ እና ዲሞክራሲያዊ ይሆናል።

 የኢትዮጵያ መንግስት ሆይ ነጻነታችንን መልሱልን!
አገራዊ ስሜታችንን ጠብቁል እናተም አገራዊ ስሜት ይኑራችሁ!
ተውን በነጻነት እንጻፍ፣ እንናገር፣ እንቀሳቀስ፣ እንስራ!
አምልኮታችንንም ለአምላካችን በነጻነት እናቅርብ! 

Saturday, February 15, 2014

የጉባኤው ጥቅም ወይስ የአባ ሰረቀ ደብዳቤ?



 የአባ ሰረቀ ደብዳቤ ማኅበረ ቅዱሳን ለአብነት መምህራን ለታላቅ ዓላማ ያዘጋጀውን ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ እንዲታገድ ምክንያት ሆነ። ጉባኤው ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጠውን ሁለተናዊ ጥቅም ወደጎን በመተው ምንም ረብ ለሌለው ደብዳቤ ቅድሚያ በመስጠት ጉባኤው እንዲታገድ የመንግሥት/ፖሊስ እገዛን መጠየቅ ቤተ ክርስቲያንን ያስተዳድራሉ ይመራሉ ተብለው ከሚጠበቁ ብፁዓን አባቶች ቀርቶ ከአንድ የቤተክርስቲያን ምእመን የሚጠበቅ ተግባር አልነበረም አይደለምም።
የጉባኤው አላማ ለማንም የተሰወረ አልነበረም። በማኅበረ ቅዱሳን አሰራርም የሚያከናውናቸውን መንፈሳዊ ተግባራት ሁሉ አስቀድሞ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ ቅዱስ ሲኖደስ ድረስ አሳውቆና ምክር ጠይቆ እንደሚሰራ ይታወቃል። በዚህም መሰረት ይህም የምክክር ጉባኤ ቀደም ብሎ የታቀደና መቼ፣ እንዴትና በምን ዙርያ እንደሆነ አባ ሰረቀም እራሳቸው በሚገባ ያውቁታል።

በእርግጥ የአባ ሰረቀና የማኅበረ ቅዱሳን የአለመግባባት ጉዳይ ዛሬ የተከሰተ እንግዳ ነገር አይደለም፤ ለአመታት የዘለቀ፣ የሰ/ት ት/ቤቶች ማደራጃ መምርያ ኃላፊ በነበሩበት ጊዜ የማኅበሩን አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ እስከማስቆም ድረስ ጽኑ አላማ ይዘው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር እና ተመሳሳይ ደብዳቤዎችን ይጽፉ እንደነበር መቼም የማይረሳ የዘወትር ትዝታ ነው።
አባ ሰረቀ በኃላፊነት የያዙትን መምርያ/የሰ/ት/ቤቶች ማ/መምርያ በትክክል ባለመምራታቸው፣ ለማኅበረ ቅዱሳንም መንፈሳዊነቱን የለቀቀ የእግድና የማስጠንቀቃ ደብዳቤ በተደጋጋሚ በመጻፋቸው እና ሌሎች ከአንድ መንፈሳዊ መሪ ነኝ ከሚል አባት የማይጠበቁ ተግባራትን ምክንያት በማድረግ በ2004 ዓም በተካሄደው የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ከመምርያ ኃላፊነታቸው እንዲወርዱ በመወሰኑ ከሥልጣናቸው በአስቸኳይ እንደለቀቁ የማይዘነጋ ሃቅ ነው። በዚሁ ጉባኤም የእምነት ችግር አለባቸው ተብሎ በሚከሰሱበት ከኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነት ውጪ ነው የሚባለውን እምነታቸውን የሚመረምር ሊቃነ ጳጳሳት የሚገኙበት ኮሚቴ ተቋቁሞ እንደነበርም ይታወሳል። እንዲህ አይነት ሰዎችን ግን በመምርያ ኃላፊነት ማስቀመጥ በራሱ ለቤተ ክርስቲያን የሚፈጥረውን ችግር ቅዱስ ሲኖዶስ ቢመለከተው መልካም ነው።
በአንጻሩ ማኅበረ ቅዱሳን ደግሞ ቅዱስ ሲኖዶስ የሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት እውቀቱን፣ ገንዘቡንና ጉልበቱን ለቤተ ክርስቲያን በመስጠት ቤተ ክርስቲያንን ለማገዝ ደፋ ቀና የሚል ማኅበር ነው። ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት፣ የአብነት ት/ቤቶችንና ገዳማትን በመርዳት፣ ምእመናን በምክረ አበው ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ፣ የተለያዩ የውይይትና ምክክር ጉባኤያትን በማድረግ ለቤተ ክርስቲያን የበኩልን ድርሻ በመወጣት ላይ የሚገኝ ማኅበር ነው።

ቅዱስነታቸው ይህን ጉዳይ ሳይረዱና ሳይመረምሩ የቤተ ክርስቲን አይን እና ጀሮ የሆኑትን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ማኅበረ ቅዱሳን እንድትወያዩ፣ እንድትመካከሩ፣ በአካል እንድትገናኙ ማድረጉ ስህተት ነውና ተመልሳችሁ ሂዱ፣ ልፋታችሁ፣ ድካማችሁ ከንቱ ይሁን ብለው የእግድ ደብደቤ መጻፋቸው በእውነት ምክንያቱ ተሰውሮብኛል። በእየ ገዳማቱ የሚገኙ ሊቃውንት ምክራቸው የማይሰለች፤ቃላቸው የማይጠገብ አንደበተ ርዕቱ አባቶቻችንን ዛሬ ምነው በአደባባይ እንዳይመክሩን ታገዱ??? ምነው ቅዱስነትዎ ለቤተ ክርስቲያን የደም ሰማዕትነትም ቢሆን መስጠት የሚችሉ አባቶቻችንን እንዳይናገሩ፣ እንዳይወያዩ አደረጉ? እንዴት ከጉባኤው ጥቅም ይልቅ የአባ ሰረቀ ረብ የለሽ ነጠላ ደብዳቤ ሚዛን ደፋ?

ዛሬ ላይ የቤተ ክርስቲያኗ ትልቁ ችግር እንደ አባ ሰረቀ እና መሰል ችግር ፈጣሪ ሰዎችን የመምርያ ኃላፊ፣ የአድባራትና ገዳማት እንዲሁም የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ተደርገው መሾማቸው ነው። ከአጥቢያ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምርያ ሰራተኞች በእየዘርፉ ችግር ፈጣሪ አካላት አሉባት። ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ችግሯን ሊረዳላት ይገባል። እንዲህ አይነት ሰዎችን በማነኛውም መመዘኛ በኋላፊነት መመደቡ ለቤተ ክርስቲያን ውድቀት እንጂ ለውጥና እድገት አይመጣም።


ማኅበረ ቅዱሳን እኮ አባ ሰረቀ የሚመሩት የመምርያ ክፍል በዋናነት በእቅድ ይዞ ሊሰራው የሚገባውን ተግባር በጀት ሳይጠይቅ በራሱ በጀት ሊቃውንቱን ለውይይት መጋበዙ ምስጋና ያስችረው  ነበር እንጂ ጉባኤውን ለማሳገድ ብዕር አያስነሳም ነበር። እንዲሁም በትብብር አብሮ ለመስራትና የሊቃውንቱን ምክር ለመቀበል በጋራ ማስኬድ ት መልካም አጋጣሚ ነበር። ግን ምን ዋጋ አለው ቅናዊ አስተሳሰብ ጠፋ፣ ሁልግዜም የማኅበሩን አገልግሎት ለማዳከም እንቅልፍ በአይናቸው አልዞር ያላቸው እኒህ አባት ሊቃውንቱን አሳዘኑ። ማኅበሩ ግን የአባቶች በረከት አልቀረበትም ይልቁንም በእንዲህ አይነት አባት ነን ባዮች እየተፈተነ እንደሚያገለግል ገዳማውያን አባቶቻች በሚገባ እንዲረዱና በጸሎታቸው እንዲያስቡት ጥሩ ምክንያት ሆነለት።  

ቅዱስነታቸውም ቢሆን የጉባኤውን ዓላማና አስፈላጊነት በሚገባ እያወቁና እየተረዱ ለማይሰራና ለማያሰራ የመምርያ ኃላፊ እኔ መሥራት ያላብኝን ተግባር ማኅበረ ቅዱሳን አከናወኑብኝ በሚል ተልካሻ ምክንያት ለተጻፈ ደብዳቤ ቅድሚያ ሰጥተው ሊቃውንቱ እንዲበተኑ ማድረጋቸው ምናልባትም በዘመነ ፕትርክናቸው ከሰሩት ሥራዎች ለታሪክ መጥፎ አሻራ ይሆንባቸው ይሆናል። እንዲያ ባይሆን ኑሮማ ደብዳቤ እንደ ደረሳቸው ሁለቱንም ጠርተው አባታዊ ቡራኬና ምክር ሰጠው ጉባኤውን በጋራ በመተባበር እንዲካሄድ ማድረግ ይችሉ ነበር። ወይም ጉባኤው ከተካሄደ በኋላ ለማኅበሩ ይህን ጉባኤው የትምህርትና ሓዋርያዊ አገልግሎት ስልጠና መምርያ ማለትም አባ ሰረቀ በሃላፊነት ሊያከናውኑት እንደሚችሉ መልእክት ማስተላለፍ ይችሉ ነበር።  

አባቶቻችን ሆይ እኛ በዓለም የምንኖር ልጆቻችሁ በዚህ እና መሰል ፈተናወች ውስጥ ነውና ያለን በጸሎታችሁ አስቡን አትርሱን! መቻሉን፣ ትግዕስትን፣ አስተዋይነትን እንዲያድለን ለምኑልን!
ቤተ ክርስቲያንን እንመራለን እናስተዳድራለን ለሚሉ ሁሉ መልካም መሪ እንዲሆኑ ጸልዩላቸው!


EOTC Radio "ወቅታዊ ጉዳይ" ስለ ሦስተኛው ሀገር አቀፍ የአብነት መምህራን ጉባኤ መታገድ
Hara tewahdo;ማኅበረ ቅዱሳን ለአብነት መምህራን ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ታገደ
http://www.danielkibret.com/2014/02/blog-post_14.html

Monday, January 6, 2014

“እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል” (ሉቃ.2፡11)


“ዘሎቱ ሰብአ ሰገል ሰገዱ ሎቱ፤ አማን መንክር ስብሐተ ልደቱ፤
ለእርሱ ሰብአ ሰገል የሰገዱለት፣ የልደቱ ክብር ድንቅ ነው።”

እግዚአብሔርን በእምነት ደስ ያሰኙ ቅዱሳን ከእስራኤላውያን ተነሥተው ነበር።(ዕብ.11) የአባቶች አለቃ ከሆነው ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ጌታችን ሰው መሆን (ዘመነ ሥጋዌ) ድረስ ብዙ ታላላቅ አባቶችና እናቶች በእስራኤል ዘንድ ተገኝተዋል።

የእስራኤል ታሪክ ሁልጊዜ መልካም ታሪክ ብቻ ግን አይደለም፤ እግዚአብሔርን ያሳዘኑባቸው ጊዜያት ጥቂቶች አይደሉም። በዚህ ጊዜ በዙሪያቸው ባሉ ነገሥታት እየተማረኩ ወደ ፋርስ፣ ባቢሎንና ግብጽ እየወረዱ ለአሕዛብ የተገዙበትና የገበሩበት ጊዜም ነበር። ንስሐ ገብተው ወደ እግዚአብሔር ሲመለሱ ደግሞ እግዚአብሔር ከእነርሱ መካከል ሰው እያስነሣ ያድናቸው ነበር። ለአባቶቻቸው የገባውን የዘለዓለም ቃልኪዳን እያሰበ ይረዳቸውም ነበር። (መዝ.77 (78))
እነሆ በዚህ የታሪክ መስመር ውስጥ ወደር የሌለው፣ ሁለተኛ በዓለም ታሪክ የማይደገም ታላቅ ነገር ተከሰተ። የእግዚአብሔር ልጅ የሰውን ሥጋ ለብሶ እንደ ሰው በምድር ላይ ተገለጠ። ጥበበኛው ሰሎሞን “አበባ በምድራችን ታየ” ብሎ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ፤ አበባ ክርስቶስ ምድር በተባለ ሥጋችን ተገልጧልና(መኃ.2፥12)። የዓለም መድኃኒት እግዚአብሔርነቱን ሳይተው ሰው ሆነ። እነሆ የእግዚአብሔር ልጅ የአብርሃም ልጅ ተባለ፤ የዳዊት ጌታ የዳዊት ልጅ ተባለ። (ማቴ.1፥1) የዳዊት ፈጣሪ በዳዊት ከተማ በቤተልሔም በከብቶች በረት ተወለደ። አባቶቻቸው በአንድ ዘመን ዳዊት የነገሠባትን ከተማ ያፈረሱ፣ የዳዊትን ልጆች በባርነት የገዙ የፋርስና የአረብ ነገሥታት የዳዊትን መንግሥት ለዘለዓለም ለሚያጸናው ሕፃን ለኢየሱስ ክርስቶስ ሰገዱ፤ ተገዙ።

ልጁን ለእግዚአብሔር መስዋዕት አድርጎ ለማቅረብ እንኳ እንቢ ያላለውን፣ የአብርሃምን ልጆች ያስገበሩት የአሕዛብ ነገሥታት ዛሬ ለአብርሃም ልጅ ወርቅ፣ እጣን፣ ከርቤ ገበሩ። (ማቴ.1፥11) በበደለኞች እስራኤላውያን ልጆቻቸው ኃጢአት ምክንያት ዝቅ ዝቅ ያለው የእስራኤል ክብር ከእነርሱ ዘር ሥጋን በነሣው በኢየሱስ ክርስቶስ ለዘላለም ከፍ ከፍ አለ።

የክርስቶስ ሰው መሆን ግን ከእስራኤል ታሪክ ያለፈ የሰው ልጅ ሁሉ ደስታ ነው። እነሆ ሰው የመሆኑ ዜና የሰው ልጆችን ሁሉ ደስታ አሰኘ “እነሆ ለህዝቡ ሁሉ የሚሆንchristmas ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።” የሚል ዜና በሰማያውያን መላእክት ተሰበከ። (ለቃ.2፥11) የምድር ኃያላን ነገሥታት በከብቶች በረት ውስጥ በጨርቅ ተጠቅልሎ ለተኛው ሕፃን መብዐ አቀረቡ። ንጹሐንና ኃያላን የሚሆኑ የሰማይ መላእክት እግዚአብሔር ለሰው ፍቅር ሲል እንደ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ሲያዩ በታላቅ ትሕትና ከእረኞች ጋር ዘመሩ። (ሉቃ.2፥13)

“ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ፣ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ።” ያለው የዳዊት ጸሎት መልስ አገኘ (መዝ. 42፥3)። ማንም ሊቀርበው በማይችል ዘለዓለማዊ ብርሃን ዉስጥ ከአባቱ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የሚኖር ብርሃን ወልድ ለጨለማው ዓለም ብርሃን ይሆን ዘንድ ተወለደ። ወደ ጽድቅ ፀሐይ ያደርሳቸው ዘንድ የእርሱ የሆነው ኮከብ ሰብአ ሰገልን ከምሥራቅ መራቸው። እነሆ ለዘለዓለም የሚያበራው ፀሐይ በቤተ ልሔም ወጣ። ነቢዩ ኢሳይያስ “በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው” ብሎ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ (ኢሳ.9፥2)። እርሱ የቅድስናው ተራራና ማደሪያው ወደ ሆነች ወደ መንግሥተ ሰማያት ይወስደናል፤ በዚች የዘለዓለም አገራችንም የሚያበራልን ፀሐይ እርሱ ነው(ራእይ.21፥23)።

በዳዊት ከተማ በቤተልሔም ድንቅ ነገር ተደረገ። ዳዊት በወርቅ ያጌጠ የተልባ እግር መጎናጸፊያ የለበሰባት ቤተልሔም የሰማይና የምድር ፈጣሪ በጨርቅ ተጠቅልሎ ተገኘባት። ቤተልሔም ከዳዊት ዘመን አብልጣ ከበረች፤ የእግዚአብሔር ክብር አብርቶባታልና፤ የልዑላን መላእክት ዝማሬ ተሰምቶባታልና።(ሚክ.5፥2)

Picture2“የእሥራኤል እረኛ ሆይ አድምጥ …በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ” ብሎ የለመነው የዳዊት ልመና በእውነት ተፈጸመ።(መዝ.70(71)፥1) የእስራኤል እረኛ በእረኞች መካከል በከብቶች በረት ተወለደ። (ሉቃ.2፥7)እረኞች ለእረኛቸው ዘመሩ፤ ላሞችና በጎች በበረት የተኛውን ሕፃን በትንፋሻቸው አሟሟቁት። በኦሪት ድንኳን በሙሴ ሕግ መሠረት ለመስዋዕት ይቀርቡ የነበሩ እንስሳት በልደቱ ደስ ተሰኙ፤ የእነርሱን መሥዋዕት የሚያስቀር አማናዊው የእግዚአብሔር በግ ተወልዷልና።

ለሰው ሁሉ ብርሃን የሚሰጥ እግዚአብሔር በጨለማው ዓለማችን ተወለደ።(ዮሐ.1፥9-14) ነቢያትና መምህራን ጠፍተውባት፣ የኃጢአት ጨለማ ዉጧት፣ በድንቁርና ባሕር ውስጥ ሰጥማ በነበረችው የሰው ልጆች ዓለም የእውነት ፀሐይ ወጣ። እነሆ ይህን ይገልጥ ዘንድ መድኅን በእኩለ ሌሊት ተወለደ፤ በተወለደ ጊዜ ግን የእግዚአብሔር ክብር በዙርያው አበራ። (ሉቃ.2፥8-9)

ለመንግሥቱ ወርቅ ተገበረለት። ኃያል መንግሥቱን ግን በምድር ላይ በትሕትና ገለጠው፤ በከብቶች በረት በመወለድና በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ በመሄድ።Picture1 (ሉቃ.19፥28-38) የአባታችን የዳዊት መንግሥት ያለልክ ከፍ ከፍ አለች፤ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ የዳዊት ልጅ ሆኗልና። ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት ድንግል ማርያምን ባበሠራት ጊዜ “እርሱ ታላቅ ይሆናል፣ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፣ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለዓለም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለዉም” ብሎ የተናገረው ዛሬ ተፈጸመ(ሉቃ.1፥32) በባሕርይው የፍጥረት ሁሉ ገዥ የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ ከዳዊት ልጅ ሥጋን ነሥቶ ሰው በሆነ ጊዜ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን እስከ ጽርአ አርያም ድረስ ከፍ ከፍ አደረጋት። እነሆ ንጉሥ ክርስቶስ በያዕቆብ ቤት(በምዕመናን) ላይ ለዘለዓለም ነገሠ። ለመንግሥቱ የአሕዛብ  ነገሥታት ተገዙላት፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ናትና ፍጥረታት ሁሉ ይገዙላታል።(ኤር.23፥5)

ለክህነቱ እጣን ተሰጠው። ክህነቱም የአበውን እና የሌዋውያንን ክህነት የምትፈጽም የዘለዓለም ሰማያዊት ሥራው ናት። እነሆ የአብ ሊቀ ካህናት እርሱ የሰውን ባሕርይ ከራሱ ጋር አስማማ። ራሱ ካህን፣ ራሱ መስዋዕት፣ ራሱ ተቀባይ ሆኖ የፈጸማት የክህነት ሥራው የዘለዓለም ድኅነትን አስገኘች።

ለሞቱ ከርቤ ቀረበለት። እነሆ እግዚአብሔር ሰው የሆነበት ዋናው ምክንያት በሞቱ ሞትን ድል ለመንሣት ነውና በልደቱ ሞቱ ተሰበከ። ከርቤ ለሞቱ ሲቀርብለት የማይሞተው እርሱ ለሰው ልጆች ሲል የሚሞት ሥጋን እንደለበሰ ታወቀ።

የአሕዛብ ነገሥታት ወርቅ ገበሩለት፤ ምእመናን ደግሞ ጽሩይ፣ ንጹሕ፣ ሰማያዊ የሆነ ልቦናን እና እምነትን ለእርሱ እናቀርባለን። (1ኛ ጴጥ.1፥6) ሰብዐ ሰገል እርሱ የፈጠረውን ወርቅ ገበሩለት፤ እኛም በርሱ ጸጋና ሥራ ያገኘነውን ንጹሕና ሰማያዊ እምነታችንን እናቀርብለታለን።(ይሁ.3)

ነገሥታቱ ዕጣን ገበሩለት፤ ምእመናን ደግሞ ቂም በቀል የሌለበትን፣ ከመልካም እና ንጹሕ ልብ የሚወጣ የምስጋና ጸሎት እናቀርባለን፤ “ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ፥ እጅ መንሣቴንም እንደ ሠርክ መስዋዕት ትሁን።” እንዳለ ንጉሥ ዳዊት።(መዝ.140፥2)

ስለሰው ልጆች ፍቅር ሲል ለሚቀበለው ሞት ከርቤ ገበሩለት፤ ምእመናን ደግሞ ለእግዚአብሔርና ለሰው ልጆች ያለንን ፍቅር ለእርሱ እናቀርባለን። ነገሥታቱ እርሱ ከፈጠረው ከርቤ ወስደው እጅ መንሻ አቀረቡ፤ ምእመናን ደግሞ ከእርሱ ከተማርነው፣ ከመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ከተቀበልነው ፍቅር መልሰን ለእርሱ እናቀርባለን። “እርሱ ስለኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቷልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል(1ኛ ዮሐ.3፥16)።”

ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክብር አሜን!!!

 ምንጭ፦ ማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ታኅሣሥ 27/2004 ዓ.ም