Friday, April 11, 2014

ስደት (ክፍል ፫)


ስደትን በተመለከተ በክፍል (Part 1)እና ፪(Part 2) በጻፍኳቸው መጣጥፎች ላይ ለስደት ያበቁንና ዛሬም ብዙ ኢትዮጵያውያንን ከአገራቸው እንዲሰደዱ እያደረጉ ያሉትን ጉዳዮች ጠቅለል አድርጌ ለማቅረብ ሞክሪያለሁ  የስደትን አስከፊነትም በመጠኑም ቢሆን ሳልጠቅስ አላለፍኩም። ዛሬም እኛ ኢትዮጵያዊያንን  ከስደት ሊታደገን የሚችል ሰማያዊ ኃል ካልመጣ በስተቀር የምንወዳትን አገራችንን ጥለን ወደ ባዕድ አገር መፍለሱን ተያይዘነዋል። ዓለምም ዋነኛ የዜና ክፍል አድርጎ ሲነግረን እንሰማለን።
ስደት ዘርፈ ብዙ ነው፤ አይነቱም መገለጫውም የተለያየ ነው። መንገዱም እንዲሁ አድካሚ፣ ውስብስብ፣ እልህ አስጨራሽና ለምን ወደዚህ ዓለም አመጣኸኝ እያሉ ከፈጣሪ ጋር ክርክር የሚያስነሳ ነው። ስደትን ሁሉንም በአንድ ላይ ጠቅልሎ  መግለጽ እጅግ ከባድና አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ስደት በተለያየ መልኩ ሊገለጽ ይችላልና፤ የአካል ስደተኛ፣ የመንፈስ ስደተኛ፣ የአዕምሮ  ስደተኛ  በማለት መዘርዘር ይቻላል። በዋናነት ግን  የፖለቲካ  ስደተኛ(political migrant) እና የኢኮኖሚ ስደተኛ(Economic migrant) ብሎ ከአገራችን ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁናቴ ማየት ይቻላል።
የፖለቲካ ስደተኛ ማለት በአጭሩ አንድ ሰው በፖለቲካ እንቅስቃሴ ምክንያት በመደገፍም ሆነ በመቃዎሙ በአገሩ መኖር ባለመቻሉ ህይወቱን እና እራሱን ነጻ አድርጎ መኖር ይቻላል ብሎ ወደሚያስበው አገር መሰደድ ማለት ነው። አንድ ሰው ከወንጀል በስተቀር የሚፈልገውን ነገር በነጻነት ማከናወን እና በነጻነት መኖር ካልቻለ ግዴታ ወደማይፈልገው የስደት ሕይወት ይገባል። በተለይ በማደግ ላይ የአሉ አገሮች የዚህ ችግር ሰለባዎች ናቸው። በአገራችንም የምናየው ዋነኛ ችግር ይህ ነው።
ሕወሓት በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ በነጻነት መናገር፣ በነጻነት መጻፍ፣ በነጻነት መወያየት፣ በነጻነት መቃወም፣ በነጻነት መደገፍ፣ በነጻነት መስራት፣ በነጻነት መማር፣ በነጻነት መደራጀትና በነጻነት ማምለክ ፈጽሞ የማይሞከሩ ነገሮች ናቸው። በሌላ አነጋገር ሕወሓት እና ነጻነት አይተዋወቁም። ዲሞክራሴ ማለት ለወያኔ/ኢህአዴግ ህዝብን ካለምክንያት ማሰር፣መግደል፣ ማሰቃየት ማለት ነው። ነጻነት ለእነሱ እነሱን መደገፍ፣ ከእነርሱ ጋር አብሮ በሙስና መጨማለቅ ነው።መጻፍናመናገር ነጻነት ለእነርሱ ለፓርቲያቸው ውዳሴ ማቅረብ ነው ልማት ለእነርሱ በተግባር ሳይሆን በቃል ብቻ 11% ማደግ አገርን መሸጥ እና ሰባዊ መብትን ከመገንባት ይልቅ ህንጻና መንገድ መገንባት ማለት ነው። ማምለክ ለእነርሱወያኔ ወይም/እናባለዕራዩ መለስ ማምለክና መስገድ ብቻ ነው። ይህ ብቻ ነው ለሕወሓት ዲሞክራሲ፣ ነጻነትና ልማት። ይህ ነው ለእነርሱ ብልጽግና እድገት።
በኢህአዴግ/ወያኔ የአገዛዝ በደል እና የዘር ፖለቲካ ባመጣው መዘዝ ለአገር እድገት መልካም የሚያስብ ሰው በቀላሉ መኖር አልቻለም። እንዲኖርም አይፈቀድለትም። ብዙ ሰዎች ሥርዓቱን በመቃወም፣ አስተዳደራዊ ለውጥ፣ የፖሊሲ ለውጥ ያስፈልጋል ብለው የሚታገሉ ብዙ ሰዎች አፋቸውን እንዲዘጉ ተደረጉ፣ ታሰሩ፣ ተገደሉ የቀሩትም ከአገር እንዲወጡ ተደረገ። ሚዲያዎች፣ድረ ገጾች፣ የግል ኮምፒወተሮችና የስልክ መስመሮች ሳይቀሩ ሲዘጉና ተጠልፈው በእነርሱ ቁጥጥር ስር እንዲሆኑ አድርገዋል በዚህም ምክንያት ሰው እራሱን እንኳ መጠራጠር ጀምሯል።
እንዲሁም የምጣኔ ሃብት ስደተኛ (economic migrant's) ማለት ደግሞ በምጣኔ ሃብት እጦት ምክንያት ይበላውና ይጠጣው ያጣ ከእጅ ወደአፍ ለማግኘት ከቦታ ወደቦታ የሚያደርገው ፍልሰት ነው። እንደአገራችን ተጫባጭ ሁኔታ ስንመለከት ብዛት ያላቸው ወጣቶች ወደ ተለያዩ  የዓለም ክፍላት ሲጓዙ እንመለከታለን። ብዙዎችም በርሀ ለበርሀ ከአሰቡበት ሳይደርሱ በመንገድ ቀርተዋል፤ በአረብያውያን ቅኝ ግዛት ወድቀው የስቃይና የመከራ ድምጽ በማሰማት ላይ ያሉትን መጥቀስ ከበቂ በላይ ነው። 
እዚህ ላይ ግን የኢትዮጵያን የድህነት ሁኔታ ሳይሆን ማንሳት የፈለኩት መንግስት ነኝ ባዩ አገራችን  ኢትዮጵያ ስመዘገበች ንን ፈጣን እድገት(11%)  እና ዛሬ ላይ ያለውን የኑሮ ውድነት እንዲሁም ወጣቱ ትውልድ በሥራ አጥነት ሳቢያ ያደርገውን ስደት በቀላሉ ማነጻጸር እንድንችል ነው። በእውነት እድገት፣ ልማት የሚጠላ ሰባዊ ፍጡር የለም። ማንም ሰው ማደግመለወጥ የተሻለ ኑሮ መኖር በእጅጉ ይፈልጋል ይሻልም ውጥ እድገት መፈለግ ተፈጥሮአዊ ባህርይ ነው።
ታዲያ አገራችን ኢት ከአደገች፣ ፈጣን እድገት ካስመዘገበች፣ ለውጥና ነጻነት ካለ በየትኛው መመዘኛ ነው ህዝቦቿ ስደትን የመረጡት??? በምን ምጣኔ ሃብታዊ ቀመር ነው ህዝቦቿ በርሀብ አለንጋ የሚሰቃዩት? የዘርፉ ሙህራን እንደሚናገሩት የአንድ አገር እድገት የሚለካው ህንጻ በመገንባት ሳይሆን የህብረተሰቡ የእለት ከእለት ኑሮ መለወጥና ሰባዊ መብቶች ሲከበሩና ሲጠበቁ ነው። ሰባዊ መብቶች እየተገፈፉ፣ ርሀብና የኑሮ ውድነት ተባብሶ ልማት፣ ፈጣን እድገት፣ ብልጽግና የለም። እርግጥ ነው ሕወሓትና ደጋፊዎቹ የአገሪቱን ንብረት በመሰብሰብ ይህ ነው የማይባል ሀብት አካብተዋል፤ ነጻነቱንም ለግላቸው አድርገዋል።
በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ ምክንያት የኢትዮጵያ ህዝብ ስደትን እንዲመርጥ የተገደደው በሕወሓት አሳፋሪና አስነዋሪ የአስተዳደር ሥርዓት ነው። አስተዳደሩም ሆነ  ልማቱ ህዝብ ተጠቃሚ በሚሆን መልኩ ማስኬድና ለውጥ ማምጣት በእጅጉ ይቻላል። ነገር ግን ቅን ልቦና የለም፤ የህብረተሰቡን መለወጥም አይፈለጉም። ምክንያቱም ድርጅቱ ራስ ወዳድ እንጂ አገራዊ ስሜት የለውም። አገሪቱን እርሱ እና መሰሎቹ እንደፈለጉ አድርገው እየተጠቀሙባት ነው የተረፈውን ደግሞ ለውጭ ባለሀብት በዶላር ቆራርሰው እየሸጧት ነው (Land grabbing )። ዜጋው ግን በብሔር፣ በተቃማሚ ፖለቲካ ስም ስቃይና መከራን በማብዛት ከቦታው እንዲፈናቀል ይደረጋል ተደርጓልም። ፖለቲካዊ ነጻነት እና እንደ ዜጋ የአገሩን ሃብትና ንብረት በነጻነት መጠቀም የሚባል ነገር ፈጽሞ ባለመኖሩ ትውልዱ ስደትን መረጠ።

በአጠቃላይ እኛው እራሳችን ነጻነታችን ማወጅ ይኖርብናል እንጂ ሌላ ታምራዊ ኃይል ሊመጣና ከስደት ሊታደገን ከቶ አይችልም። እርግጥ ነው ፈጣሪ የህዝቡን ዋይታና እሮሮ ሰምቶ ለነጻነት ምክንያት የሚሆን ሰው ሊያስነሳ ይችላል። ነገር ግን እኛ ዝም ብለን የፈጣሪን ሥራ መጠበቅ ግን በእራሳችን ላይ የመከራ ጊዜን እንደማራዘም ይቆጠራል። ፈጣሪ የራሱን ሥራ  በራሱ ጊዜ ይሰራል። እኛም የራሳችንን ሥራ መስራት ይጠበቅብናል። ነጻነታችንን ማስጠበቅ፣ አገራችንን መታደግ፣ለወገናችን መድረስ ሰባዊ መብታችን ነው። ስለዚህ ሰባዊ መብታችንን ተጠቅመን ይህን ፈላጭ ቆራጭ መንግስት ነኝ ባይ የዘር ፖለቲካ አራማጅ ሕወሓትን በቃህ፣ ስደት ይብቃ ልንለው ይገባል።

Tuesday, April 1, 2014

ስደት (ክፍል ፪)


ስደትን በተመለከተ በክፍል ፩( በጻፍኩት ጽሁፍ ላይ ትልቁን ለሰው ልጅ የአእምሮ ረፍትና የወደፊት ተስፋ የሚሆነውን ነጻነት መነፈግ ለኢትዮጵያ ህዝም ብሎም ለዓለም ህብረተሰብ አስቸጋሪ በመሆኑ ለስደት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ገልጨ ነበር። ጠቅለል ባለመልኩ እኛ ኢትዮጵያውያን የመተሳሰብ፣ አብሮ የመብላት፣ በነጻነት የመስራትና የመንቀሳቀስ፣ መሰረታዊ የሰው ልጅ የእዉቀት ደረጃዎችን ማለትም የመጻፍና የመናገር፣ እንዲሁም መንግሥት እራሱ በእራሱ ህገ መንግሥት ነው ብሎ ባረቀቀው "መንግሥት በሀይማኖት ጣልቃ አይገባም ሃይማኖትም እንዲሁ/The state shall not interfere in religious masters and religion shall not interfere in state affairs"(አንቀጽ 113) ያለውን የእራሱን ህግ ሳይቀር በመጣስ የማምለክ ነጻነታችንን በበሬ ወለድ ምክንያት ሲገፍ እና አንድነታችንን፣ ባህላችንንና ለነገ የሚያስበውን ትውልድ ሲያስር፣ ሲያንገላታና ለስደት ሲዳርግ ብሎም ሲገድል ድፍን 23 ዓመት አስቆጠረ።

ይህ የስቃይና የመከራ ዘመን የሚያበቃበትን ቀን እና ስዓት የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያመልከውን አምላክ በመማጸን ላይ ነው። በተቃራኒው የህወሓት አገዛዝ ዘላለማዊ ነኝ ማለቱን ተያይዞታል። ታግሎ ነጻነቱን እንዳያስከብር ከጫካ ጀምሮ የሰራበትን የሥልጣን እድሜ ማራዘሚያ የብሔር ተኮር የዘር የእርስ በእርስ ግጭትና የሀይማኖት ተቋማትን የማፍረስ ፖለቲካ በህዝቡ ላይ በማሰራጨቱ ለነጻነት በህብረት በአንድነት እንዳንታገል አድርጎናል። እርስ በእርሳችን እንዳንተማመን አድርጎናል፤ ከፋፍሎናል። ህብረት አንድነት እንዳይኖረን በማድረግ ለስደት ዳርጎናል።

ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንዳትኖር እና ካርታ እንዳይኖራት አድርጓታል። መለያ ምልክቷን ሰንደቅ ዓላማዋን ቀይሮባታል። በቅኝ ግዛት ያልተንበረከኩ ህዝቦቿን መከራ እና ስቃይ በማብዛት በግድ ለባርነት/ለስደት ዳርጓቸዋል። ሰላም የጠፋበት፣ ተስፋ የሌለው፣ ለማንነቱ የማይጨነቅ፣ ለአገር ለወገኑ የማያስብ ትውልድ መናኽርያ እንድትሆን አድርጓል። በራብ አለንጋ ሳይቀር ሰፊውን ህዝብ እየቀጣ ነው። ከራብ ጦር ይሻላል እንዲሉ ከራብ፣ ከጭቆና ነጻነት ከማጣት ስደትን መረጠ፣ በየአገሩ ስደተኛ ተብለው እንድንኖር አደረገን። አይ ህወሓት የስራችሁን ይስጣችሁ ሌላ ምን ይባላል.....የባለ ዕራዩን (የአምላካችሁን) መለስ ተብዬው እጣ ፈንታ ይስጣችሁ እንዳንል እርግማን ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ የዋህ እና በፈጣሪው የሚያምን ነው እርግማን ፈጽሞ ይጠላል፤ ድህነታችሁን እንጂ ሞታችሁን አንሻም። ስቃዩን፣ መከራውን፣ እስራቱን አቅሉልን እንጂ ጣን ልቀቁ የማይል ህዝብ ነው። እንዳለመታደል ሁኖ እንጂ እንዴት ለዚህ ህዝብ ነጻነቱን ይገፈፋል፣ ማንነቱንና ታሪኩን እንዲያጣ ይደረጋል።

ለአገር እድገትና ብልጽግና ዋነኛ መሰረት ሙያዊ ነጻነት(academic freedom) መሆኑን የዘርፉ ሙህራን ይስማሙበታል። የሰው ልጅ በተፈጥራዊም ሆነ በግላዊ ጥረት እራሱን፣ ቤተሰቡን ከዚያም አልፎ አገርን መለወጥ መቀየር የሚያስችል እውቀት/ሙያ አለው። ሙያዊ ነጻነት ከደሞዝ፣ ከክፍያና ከማንኛውም ጥቅማ ጥቅም በላይ ነው፣ ከሹመትና ሽልማት በላይ ነው። ሁሉም ማለት ይቻላል ሙያዊ እውቀት ለማግኘት ወደ / ዓለም ሲገባ የሚያስደስተውን እና ቢሰራበት የበለጠ ውጤት ማምጣት ወደሚችልበት የት/ መስክ ይገባል። ለዚህ ትውልድ ያገኘውን እውቀት ካለንም ተጽዕኖ መስራት የሚችልበትን መልካም ከባቢያዊ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እና ማስተካከል የነበረበት ዲሞክራሲያዊ እና ልማታዊ ነኝ የሚለው መንግሥት ነኝ ባዩ ፈላጭ ቆራጩ የህወሓት ቡድን ነበር። በተቃራኒው ግን እየሰራ ያለው ገና በለጋ እድሜያቸው ሳይቀር ተማሪዎችን የእርሱ ተከታዮች እንዲሆኑና የብሔር ፖለቲካን ሲዘራባቸው ይታያል። ወደከፍተኛ / ሲገቡም ሲወጡም ለጊዜው ለመኖር ዋስትና (green card) የሆነችውን ቁራጭ ወረቀት (የአባልነት መታወቂያ መሆኗ ነው) ይዘው እንዲወጡና የስራ ዕድል እጣ ፈንታ በዚያ እንደሚወሰን አጠንክሮ መልእክቱን ያስተላልፋል። ለማሳያም ያክል በየከፍተኛ / ተቋማት ውስጥ የመንግሥት ተልኮን የሚያራምዱትን አድር ባዮች ካለሙያቸው፣ ካለ እውቀታቸውና ካለችሎታቸው ከፌደራል እስከ ቀበሌ የየመስርያ ቤቱ ኃላፊዎች እያደረገ ይሾማል። የተለየ ጥቅማጥቅም ይሰጣቸዋል። በሙስና የተጨማለቁ እንዲሆኑ እና በፍራቻ የስርዓቱ ሎሌዎች አድርጓቸዋል።

ይህን እና መሰል ሁኔታወችን በማየት ሁሉም በሚያስብል መልኩ የከፍተኛ / ተቋማት ተማሪዎች ከልባቸውም ባይሆን የገዥው ፓርቲ ደጋፊ እና ተላላኪ እንዲሆኑ ተደርገዋል። ከዛም አልፎ በስራ ላይ ሰራተኛውን ስራውን በአግባቡ እንዳይሰራ ጀርባው እና የሚያደረገውን እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ለማጥናት የስለላ ስራ እንዲሰሩ ይደረጋል። አንድ ለአምስት(15) በሚል ሚስጥራዊ የህወሓት ቡድን ሁሉም እንዲካተቱ እና የፓርቲው አገልጋዮች ተደርገዋል። የቀሩትም ከእጅ ወዳፍ ለማግኘት ሲሉ ወደው ሳይሆን ተገደው በቡድኑ ውስጥ ተካተዋል። በዚህ ቡድን እና ተመሳሳይ እኩይ ተግባር አንተባበርም ያሉት ኢትዮጵያውያን እና እድገቷን የሚሹ እውነተኛ ልጆች ስቃይና መከራ ሲበዛባቸው እና ከእስርና ከሞት የተረፉት ለስደት ተዳርገዋል።

በዚሁ ከቀጠለ አገራዊ ስሜት እና እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ይገኛል ብሎ ማሰብ እጅግ ከባድ ይመስለኛል። ምክንያቱም ለእኛ አገራችንን ከእነ ሙሉ ክብሯ እና ከእነ ታሪኳ ያስረከቡን የደም መሰዋትዕነት ከፍለው ነው። 40ዎች ዓመታት በፊት የነበሩት መንግስታት ምንም እንኳ የራሳቸው ችግር ቢኖርባቸውም ለአገር አንድነትና እድገት፣ ለሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጾ አድርገዋል። እንደ ህወሓት ፓርቲ አገሪቱን አልሸጡም፣ ይልቁንም ለክብሯና ለታሪኳ ይጨነቁ ነበር እንጂ። ህዝቦቻንም እንዲህ በይፋ ለስደት አልዳረጉም። አገርን የሚወድ ትውልድ እንጂ አገርን የሚክድና የሚሸጥ፣ ታሪክን የሚያጠፋ፣ አንድነትን የሚለያይ፣ ባህልን እና ሀይማኖትን የሚንቅ ትውልድ አላፈሩም። ው ነገር ግን መንግሥት ነኝ ባዩ ወያኔ/ኢህአዲግ የቀደሙ ነገሥታትን ሲተችና ታሪካቸውን ሲያጠፋ በይፋ ይታያል።

ወያኔ/ኢህአዲግ ግን ሙያዊ ነጻነት እንኳ ሳይቀር ተነፍገን ተመራማሪዎች እንዳይመራመሩ፣ ደራስያን እንዳይደርሱ፣ ተዋንያን እንዳይተውኑ፣ ጋዜጠኞች እንዳይዘግቡ፣ ነጋዴዎች እንዳይነግዱ(ከእርሱ አባላት በስተቀር) መምህራን እንዳያስተምሩ፣ እና ሁሉም በየሙያ ዘርፉ በነጻነት ሰርተው እንዳይበሉ አደረገ። ከእርሱ ዓላማ እና ተልእኮ ውጭ ማንም ምንም እንዳያደርግ የሞት፣ የእስር፣ የአክራሪነትና አሸባሪነት ህግ አጸደቀ። እስራትና ሞት ፈርተን ብዙዎች ተሰደድን ከስደት እንዳንመለስም ህይወት ናትና ፈራን።

ትናት ስደተኛ፣ ዛሬም ስደተኛ፣ ነገስ??? ነገ ምን አልባት ሙሴ ህዝበ እስራኤልን ከፈርኦን የመከራና የጭንቀት አገዛዝ ነጻ እንዳወጣቸው ሁሉ ኢትዮጵያውያንንም ነጻ የሚያወጣ ታምራዊ ኃይል ሊፈጠር እንደሚችል ባለሙሉ ተስፋዎች ነን። ህዝብ ታምራዊ የለውጥ ኃይል መሆን ይችላል። እያንዳንዱ ዜጋ ለመብቱ፣ ለነጻነቱ ከታገለ ታምራዊ ኃይል ሁኖ ይህን ጨቁኖ የሚገዛን መንግሥት በቀናት ውስጥ ማስወገድ ይችላል።

የኢትዮጵያ አምላክ ሆይ ከስደት የሚታደገንን ሙሴን ላክልን!

እውነተኛ ፍርድ የሚሰጠውን ዳዊትን ላክልን!

በጥበብና በማስተዋል የሚመራውን ሰሎሞንን ላክልን!

Monday, March 24, 2014

ለምን ከምንወዳት አገራችን እንሰደዳለን? ክፍል 1

ከምንወዳት፣ ከአደግንባት፣ የማይረሳ የልጅነት ጊዜያችንን ካሳለፍንባትና አገራችንን ጥለን/ለቀን በባዕድ አገር በስደት በእምነት፣ በባህል፣ በቋንቋ እንዲሁም በአመለካከት ከማይመስሉን ጋር በተለያየ  ፈተናና ውጣ ውረድ እና ለአፍታ በማይዘነጋ አገራዊ ትዝታ እንድንኖር ያደረገን ትልቅ ምክንያት ይኖረናል፤አለንም። ማንም ሰው በአገሩ በሰላም እና በደስታ ባሳደገው ማህበረሰባዊ ባህል መኖር እና ማደግ ይፈልጋል። የራሱ የሆነ በቂ ምክንያት ከሌለው በስተቀር ስደትን ቤቴ ብሎ የሚኖር የለም። ባገሩ በሰላም መኖር የሚችል ሰው የስደትን አስከፊነት እና ትግዕስት አስጨራሽነት ተቋቁሞ መኖር ባልቻለ ነበር። ግን እርሱ ባለቤቱ የሚያውቀው አሳማኝ ምክንያት አለው። 

በእርግጥ ዛሬ ላይ ዓለም ሁሉ ለስደት የዳረገንን ምክንያት ዘመኑ በወለዳቸው ብዙኃን መገናኛዎች ምስክርነት መስጠት ከጀመሩ ጊዜያትን አሳልፈዋል። እውነታውንም በሚገባ ተገንዝበው ለሰሚዓን ምስክርነቱን ቀጥለውበታል። ከፊሎች ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ስሜት የለለውን የመንግስትን ከእውነታ የራቀ ተራ ወሬ ተከትለው ስደተኞችን ሲተቹ እና ሲያንገላቱ ይታያል። እርግጥ ነው ብዙዎች የአፍሪካ መሪዎች የስልጣን ዘመናቸውን የሚያስረዝሙት በሀሰት እና በኃይል ረግጠው እናስተዳድረዋለን እንመራዋለን በሚሎት ህዝብ ላይ የመከራ ቀንበር በመጫን እና በማስጨነቅ ነው። የኢትዮጵያ መሪዎችም የስልጣን ዘመናቸውን ለማስረዘም ያዋጣናል የሚሉትን ማንኛውም መንገድ ይጠቀማሉ። ሲፈልጉ ያጸድቃሉ፤ ሲፈልጉ ይኮንናሉ፤ይሾማሉ፣ይሽራሉ፤ ይገድላሉ፣ ያኖራሉም።

በአገራችን አንድ ገሀዳዊ እውነታ አለ። ህዝቡ አገሩ ከመኖር ይልቅ ወደ ስደት ዓለም የሚሄድባቸውን መንገዶች በማፈለለግ ከጊዜ ወደ ጊዜ የስደተኛው ቁጥር በእጅጉ እየበዛ እና እየጨመረ መምጣቱ ዓለም በአንድ ድምጽ የሚመሰክረው እውነታ ነው። አገርን ያሳድጋል ያለማል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የተማረው ዜጋም ስደትን በመቀላቀል ግንባር ቀደም ቦታን ይዟል። ለአንድ አገር እድገት አይደለም የተማረ ዜጋ ቀርቶ ማንኛም ሰው በተፈጥሮአዊ እውቀቱ፣ ጉልበቱ እና ገንዘቡ አገርን የመለወጥ አቅም አለው። የአደጉ አገሮችን ታሪክ ብንመለከት ወደ ብልጽግናው ዓለም የተቀላቀሉ ያላቸውን የሰው ኃይል በሙሉ በነጻነት ለአገሩ ተቆርቋሪ ሁኖ በቻለው መጠን እንዲሰራ በማድረጋቸው ነው። 
ወደ ኢትዮጵያ አገራችን ስንገባ ግን በተቃራኒው ሁኖ እናገኘዋለን። በጣም የሚያሳዝነው የሚሰራ ሰው፣ የሚናገር ሰው፣ ለእውነት የቆመ ሰው እንዲኖርባት ያልታደለች አገር መሆኗ ነው። የዓለም መነጋገርያ የሆነውን የትናቱን የረዳት አብራሪ ኃይለመድህን አበራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ‪ET702‬ ይዞ ኢጣሊያ መግባት የነበረበትን ወደ ሲዊዝ ጀነባ መሄዱን መመልከት ከበቂ በላይ የነጻነት እጦትን ያረጋግጣልናል።


በብዙ ምክንያቶች ዜጎቿ ስደተኞች ሁነውል። በሚገርም ሁኔታ በአገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎቿም አብዛኞቹ ወደ ስደት የሚወጡበትን አጋጣሚዎች በመጣባበቅ የመንፈስ ስደተኞች ሁነዋል። በተለያየ አጋጣሚ ወደ ውጭ የሚወጣው ዜጋ ወደ አገሩ የሚመለሰው ቁጥር በእጅጉ አናሳ መሆኑን ጥናታዊ ባልሆነ መንገድ የምንሰማቸው እና የምናያቸው መረጃዎች ህያው ምስክሮች ናቸው። ግን ለምን? እንዴት? እስከ መቼ? ህዝቦቿ በስደት የሚሰቃዩት መልስ የለለው የዘወትር ጥያቄየ ነው። ለስደት የዳረገንን አንዱን እና ትልቁን ምክንያት ለማንሳት እሞክራለሁ። 
  
ነጻነት፣ ነጻነት፣ ነጻነት???

ነጻነት የሚለውን ቀጥተኛ ትርጉም በአጭሩ ከዚህ በፊት "ነጻነት ወይስ ቅኝ ግዛት" በሚል ባወጣውት ጽሁፌ ላይ ለመግለጽ ሞክሬ ነበር። (ነጻነት ወይስ ቅኝ ግዛት/ባርነት) በዚህ ጽሁፌ ደግሞ የነጻነት እጦት ምን ያክል ለስደት እንደዳረገን ውስጣዊ ስሜቴን ለመግለጽ እዎዳለሁ።
ነጻነት ተፈጥሮአዊ ነው። እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጠው ትልቁ ጸጋ ነጻነት ነው። እሱን እንድናመልከው እንኳ ነጻ ፈቃድ ሰጥቶናል፤ አላስገደደንም። እግዚአብሔር የፈጠረውን ፍጥረት ሳያስገድድ የኢትዮጵያ መሪዎች ግን እነሱ ባልፈጠሩት፣ ባልሰሩት፣ ምንም ዋጋ በአልከፈሉበት ህዝብ ላይ አምባ ገነናዊ አገዛዛቸውን አስፍተው እኛን ሲጨቁኑን እና መከራ ሲያበዙብን እናያለን። እነርሱ እና የእነርሱ አጫፋሪዎች በነጻነት ይኖራሉ። ብዙኃኑ ህዝብ ግን በነጻነት እጦት ብዙዎች ተሰደዱ፣ ተንገላቱ፣ መከራን ተቀበሉ። ብዙዎችም ነጻነት ይኑር ብለው በመናገራቸው ተገደሉ፣ ታሰሩ፣ ሃብት ንብረታቸው ተወረሰ፣ የሚናገሩበት አንደበት እንዲዘጋ ተደረጉ፣ ለነጻነት የሚጽፉበት ብዕራቸው ተወረወረ እጃቸውም ታሰረ። ቤተ እምነቶችም ሳይቀሩ ነጻነትን በመስበካቸው የአምልኮ ስርዓታቸውን እንዳያካህዱ ተደረጉ። የአምልኮ ቦታዎች በምክንያት እንዲፈርስ ተደረገ። ባህላችንን፣ ታሪካችንን እና ማንነታችንን እንድናጣ ተደረግን። 

የኢትዮጵያ ህዝብ በሁሉም መስክ ነጻነቱ ተገፏል፤ በነጻነት መናገር፣ በነጻነት መጻፍ፣ በነጻነት መደራጀት፣ በነጻነት መሰብሰብ፣ በነጻነት ማህበራዊ ተግባራትን ማካሄድ፣ በነጻነት መስራት እና በነጻነት መንቀሳቀስ እንዲሁም በነጻነት ማምለክ ታሪክ ሆኖብናል። ህዝቡ በእጅጉ ነጻነትን ይፈልጋል። ነጻነት ፍለጋም ስደትን እንደ አንድ ዓቢይ ምርጫ አድርጎ በየቀኑ በብዙዎች የሚቆጠሩ ይፈልሳሉ። የስደትን አስገፊ ህይወት በጸጋ ተቀብሎ መኖር አማራጭ የለለው መፍትሔ አድርገነዋል። የዱር እንስሳት እንኳ ሳይቀሩ የእለት ከእለት ኗሯቸውን በነጻነት ማካሄድ የማይችሉበት ሁኔታ ሲፈጠር ነጻነት ወደሚያገኙበት ቦታ/ጫካ ይሰደዳሉ። የሰው ልጅ ደግሞ ከእንስሳት በተለየ የአስተሳሰብ አድማሱ ሰፊ በመሆኑ ነጻነትን ከምንም በላይ ይፈልጋል። "ጎመን በጤና ይላል" እንዲሉ ነጻነትን ተነፍጎ የቁም እስረኛ ከመሆን ይልቅ በነጻነት በድህነት መኖር አእምሯዊ ረፍት ይሰጣል። 

ስለዚህ የስደታችን ዋነኛ ምክንያት የነጻነት እጦት ነው። የህዝብ ነጻነት እስካልተመለሰ ድረስ ከስደት ወደኋላ ይላል ብሎ ማሰብና መፍረድ የቁም እስረኛ ሁኑ ብሎ እንደመፍረድ ይቆጠራል። ህዝብ ነጻነቱን ካገኘ ሁሉን ነገር ማድረግ ይችላል፤ ሰርቶ ድህነትን ማሸነፍ ይችላል፤ ማህበራዊ ህይወቱ ሰላማዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እድገቱ እውነታ ያለው እድገት እና ፖለቲካዊ አመለካከቱ የሰላ እና ዲሞክራሲያዊ ይሆናል።

 የኢትዮጵያ መንግስት ሆይ ነጻነታችንን መልሱልን!
አገራዊ ስሜታችንን ጠብቁል እናተም አገራዊ ስሜት ይኑራችሁ!
ተውን በነጻነት እንጻፍ፣ እንናገር፣ እንቀሳቀስ፣ እንስራ!
አምልኮታችንንም ለአምላካችን በነጻነት እናቅርብ!