የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ያገባኛል
ሁላችንም የእምነቱ ተከታዮች ማለትም የቤተ ክርስቲያን ችግርና ጉዳይ የሚያሳስበንና የሚያስጨንቀን ሁሉ ይህን አዋጅ አውጀን በሃዘንና በሃሳብ ውስጥ ከሰመጥን ብዙ ቀናትን በማሳለፍ ላይ እንገኛለን። በእርግጥ ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ደም የተመሰረተች ስለሆነች ፈተናዋም ልክ እንደ ኢየሱስ ክርስቶ ይበዛባታል ይጸናባታል። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይችን ቤተክርስቲያን በደሙ ለመመስረትና የአዳምን ዘር በሙሉ ድህነት ለማዎጅ ወደዚህ ዓለም ከመጣ ከውልደቱ ጀምሮ እስከ ትንሳኤው ድረስ በፈተና በመከራ ውስጥ እንደነበረ ሁላችንም እለት እለት የምናስታውሰው የእምነታችን መሰረት ነው። ስለዚህ ፈተና ለቤተ ክርስቲያን አዲስ እንግዳ ነገርም አይደለም፤ በተለያየ ጊዜ አይነቱንና መጠኑን እየቀያየረ አንገላቷታል፣ አሰቃይቷታል ልጆቿም አንገታቸውን ለሰይፋና ለስለት፣ ጀርባቸውን ለግርፋት ሰጥተው ሰማትዕነት ተቀብለውላታል። ዛሬም እኛ ይህንን አዋጅ ስናውጅ የክርስቶስን ጽዋትዎ መከራ፣ አባቶቻችን የተቀበሉትን ሰማዕትነት በማሰብ እንጂ ዝም ብለን ዛሬ ላይ ዘመኑ ያፈራቸውን ብሔርተኝነት፣ ወገንተኝነትና ፓለቲካ ተከትለን እንዳልሆነ የሚመለከተው ሁሉ እንዲያውቅልን በአጽንኦት መግለጽ እወዳለው።
ቤተ ክርስቲያን በዋናነት በዘመነ ሰማዕታት፣ በዘመነ ዮዲት፣ በዘመነ ግራኝ ሙሀመድ፣ በዘመነ ሱስንዮስ፤ የትናቱን እንኳ የቅርቡን የፋሽስት ኢጣሊያ እንዲሁም በተለያየ ጊዜ ከውስጥም ከውጭም የደረሰባትን ከባድ ፈተናዎች እንደ አመጣጣቸው አሳልፋለች ዛሬም በፈተና ውስጥ መኖሯ ለትክክለኛ አማኝ ብዙም ከባድ አይሆንም። ሆኖም ግን ዛሬ ላይ የገጠማት ፈተና እንዲህ በቀላሉ ልናልፈው የምንችለው ጉዳይ አይደለም። ምክንያቱም አባቶቻችን ከላይ ያነሳናቸውን ፈተናዎች ድል የነሱት በእግዚአብሔር ረዳትነት እና በአንድነት፣ በህብረትና በመወያየት እንጂ በመለያየት አልነበረም "ድር ቢያብር አንበሳ ያስር" የሚለውን ብሂል በመጠቀም እንጂ። አንድ ነገር ግን ማሰብ ያለብን አገርንም፣ ቤተክርስቲያንንም ማንኛውንም ነገር መለያየትና መከፋፈል የሚጎዳንን ያክል ሌላ ምንም ነገር አይጎዳንም። ታላቁ አባታችን ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በትምህርታቸው "የቤተ ክርስቲያን ሕይወት በመስቀል ላይ ስለሆነ ፈተና ይበዛባታል፤ ስለዚህ የቤተክርስቲያንን አቋም፡ አንድነት አጠናክሩ" በማለት ነበር ለቤተ ክርስቲያን ጠበቃ እንድንሆን ያስተማሩን። ለዛም ነው እኛ ሁላችንም "የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ያገባኛል" የሚል አዋጅ አውጀን በቻልነው መጠን ለቤተ ክርስቲያን ማነኛውም ችግር መፍትሔ ለማፈላለግ ወደኋላ የማንል መሆኑን እየገለጽን ያለነው። ነገር ግን የቃሉን አዋጅ እንዴት ወደተግባር ለውጠን ቤተ ክርስቲያንን ከመለያየት ወደ አንድነት፣ ወደ ፍቅር፣ ወደ ሰላምና መረጋጋት እናምጣ የሚለው የሁላችንም መልስ ያላገኘንለት ጥያቄ ነው። ለዚህ ጥያቄ በቀላሉ መልስ ለአለማግኘትና ለችግሩም መንስሄ የሆኑትን በጥቂቱም የሚከተሉትን ማንሳት ይቻላል።
- አባቶች ሰማዕትነትን ለመቀበል ዝግጁ ያለመሆን፦ ቤተ ክርስቲያን እንዳስተማረችን ሰማዕትነት የደም ብቻ አይደለም። ለቤተ ክርስቲያን በተለያየ መልኩ ሰማዕትነት መቀበል እንደሚያስፈልግ እኒሁ ዛሬ ሰማዕትነት ለመቀበል ዝግጁ ያልሆኑት አባቶች አስተምረውናል። ገና በፍራቻ ሥጋዊ ድሎታችን ሊነካብን ይችላል በማለት ለቤተ ክርስቲያን አንድነት መቆም ተስኗቸዋል ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ምናልባት የተለያየ ምክንያት ሲያቀርቡ ይሰማል፤ ነገር ግን ምንም ይሁን ምን የቤተ ክርስቲያንን አንድነትና ሰላም ሊነካ የሚችል ምክንያት በምዕመናን ዘንድ ተቀባይነት እንደማይኖረው በውጭም በውስጥም ያሉ አባቶች እንዲረዱልን እንፈልጋለን። የአባቶች ምክንያት ሰማዕትነት ለመቀበል ዝግጁ ያለመሆንና ድፍረት ማጣት ቤተ ክርስቲያን ለ21 ዓመታት ተለያይታ ዛሬም ነገም ወደፊትም በልዩነት እንድትቀጥል ፍርዳቸውን ለማጽናት ምክንያት እየደረደሩ ይገኛሉ። እኔም እንደ አንድ ምዕመን የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ያገባኛል ምክንያታችሁን ተው፣ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ስትሉ ሰማዕትነትን ተቀበሉ፣ አላውያን ነገስታትን አትፍሩ ለቤተ ክርስቲያን ዋጋ ክፈሉ እንዲህ ካደረጋችሁ እኛም ከእናተ ጋር ነን ሰማያዊ ዋጋችሁ እንደተጠበቀ ሁኖ።
- በምዕመናን መካከል አንድነት አለመኖር፦ በእኛ በምዕመናን ዘንድ ትልቁ ችግርና በሽታ በመካከላችን አንድነትና መተማመን አለመኖሩ ነው። ይህ ችግር ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ላይ የተከሰተውን ትልቅ ፈተና በህብረትና በአንድነት ለመወጣት መሰናክል ሆኖብናል። ማን እንደዘራብን እግዚአብሔር ይወቀውና ዘረኝነቱና ፖለቲካው በመካከላችን ነግሶብን የቤተ ክርስቲያንን ችግር ከወሬ የዘለለ ሥራ እንዳንሰራ እንቅፋት ከሆነብን ዘመናት ተቆጥረዋል። በመካከላችን አንድነት ቢኖር ኑሮ በአባቶች በኩል ድክመት ሲኖር በቀላሉ ልንደግፋቸው በቻልን ነበር። ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ያገባናል ይመለከተናል ካልን ሌሎች ልዩነቶችን ትተን ለቤተ ክርስቲያን በአንድነት በመቆም ከገባችበት ችግር ልንታደጋትና ልንቆምላት ይገባል።
- በውጭ የሚኖሩ ምዕመናንና በአገር ውስጥ ላሉ ችግሩ እኩል ስሜት አለመኖሩ፦ ምንም እንኳ ለ21 አመት የዘለቀውን የቤተ ክርስቲያን የታሪክ ጠባሳ በትንሹም ቢሆን የማያውቅ የለም ብሎ መናገር ቢከብድም በውጭና በአገር ውስጥ ያለን ሁላችንም እኩል ግንዛቤ ስለሌለን ለችግሩም መፍትሔ ለመፈለግ እኩል ተነሳሽነት የለንም። በተለይ በውጭው አለም የምንኖር ምዕመናን የመጀመሪያ ግንባር ቀደም የችግሩ ቀማሽ በመሆናችን ለዕርቀ ሰላሙ አጽንኦት ሰጠን ድምጻችንን ከፍ አድርገን ስንናገር እንሰማለን። በእርግጥ በአገር ውስጥ ለእርቀ ሰላሙ መሳካት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚደክሙ የሉም ለማለት አይደለም በንጽጽር ስናስቀምጠው ነው እንጂ። ያም ይሁን ይህ እርቀ ሰላሙ የቤተ ክርስቲያን የአንድነት ጉዳይ ነውና ሁላችንም ችግሩን እኩል በመገንዘብ ለመፍትሔው መሯሯጥ እጅግ አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ወርቃማ እድል ካመለጠን ሌላ ጊዜ ለማግኘት ምናልባት የማናውቀው ብዙ አስርት አመታት ሊፈጅብን ይችላልና።
- የመንግሥት ጣልቃ ገብነት፦ እዚህ ላይ ግን ብዙ መናገር አልፈልግም ምክንያቱም በቤተ ክርስቲያን የታሪክ ጉዞ ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ነጻ ሁና በራሷ የተመራችበት የታሪክ አጋጣሚ የለምና። ዛሬም ያለው መንግሥት ስልጣን ከያዘባት ከመጀመራይቱ ቀን ጀምሮ እስከ አሁኗ ስዓት ድረስ በአንድም በሌላም መንገድ እጁን ከቤተ ክርስቲያን ላይ አላወረደም። በመጀመሪያ ለቤተ ክርስቲያን መለያየትና መከፋፈል መንስኤ እንደሆነ ሁሉ ለእርቀ ሰላሙ እንቅፋት መሆኑም በተለያየ ጊዜ የምናያቸውና የምንሰማቸው ነገሮች ማረጋገጫዎች ናቸው። ሌላውን እንተወውና የክቡር ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊርጊስ ደብዳቤ ከበቂ በላይ ማስረጃችን ነው። ስለዚህ እኛ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ያገባናል የምንል ሰዎች በአገኘነው አጋጣሚ ሁሉ "መንግሥት ሆይ ከቤተ ክርስቲያን ላይ እጅህን አንሳ" ልንለው ይገባል።
- የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ዝምታ፦ አንዳንዴ በግሌ አባታችን ግን የት ናቸው? የሚል ጥያቄ ይፈጠርብኛል። ለመሆኑ የአባታችን ዝምታ እስከ መቼ ነው? ምናልባት እኮ መፍትሔው ከእርሳቸው ዘንድ ሊኖር ይችላል የሚል ግምት አለኝ። እስኪ ከሌላ ሰው በስማ በለው ከምንሰማው ይልቅ በራስዎ አንደበት ይንገሩን? ምን ደረሰብዎት? እንዴት ነበር? ሁኔታውን በአጭርና በግልፅ ቁንቋ ይንገሩንና ምዕመኑ አንድ ሁኖ ወደ እውነቱ በህብረት እንዝመት። ወይም ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም ሲሉ መቀበል ያለብዎትን ሰማዕትነት በጸጋ ይቀበሉና ቤተ ክርስቲያንን አንድ ያድርጉ፤ የ21 ዓመት ዝምታዎት ይብቃ።
የሰላም አምላክ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን ሰላምን ያድልልን፡ አሜን።