Showing posts with label Religion. Show all posts
Showing posts with label Religion. Show all posts

Monday, August 19, 2013

ደብረ ታቦር


ደብረ ታቦር ማለት የታቦር ተራራ ማለት ነው። ከ9ኙ ዓበይት በአላት መካከል አንዱ ነው። ታሪኩም በአጭሩ፦ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል ብሎ በጠየቃቸው በሰባተኛው ቀን ከነቢያትም አንዱ ነህ ብለውታልና የነቢያት አምላካቸው እንደሆነ ለማጠየቅ፤ በቅዱስ ጴጥሮስ የተነገረውን በጌታ ቃል ለማስመስከር ሶስቱን ባለሟሎቹን (ቅዱስ ጴጥሮስን፣ ቅዱስ ያዕቆብንና ቅዱስ ዮሓንስን) ለብቻቸው ወደ ተራራ ይዟቸው ወጣ። መልኩም በፊታቸው ተለወጠ አካሉም ምሉዕ ብርሃን ሆነ፤ ገጹም እንደ ፀሐይ ብሩህ ልብሱም እንደ በረድ ፀዓዳ። 
ይህ ሁሉ ጌትነቱን ሲገልጽላቸው ነው። እነሆም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ሙሴ የእኔን የሙሴን ጌታ ማን ሙሴ ይልሃል የሙሴ አምላክ ይበሉህ እንጂ፤ ኤልያስም የእኔን የኤልያስን ጌታ ማን ኤልያስ ይልሃል የኤልያስ አምላክ ይበሉህ እንጂ ሲሉ ተሰምተዋል። ቅዱስ ጴጥሮስም በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው አለው። እርሱም ገና ሲናገር ብሩህ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው ፥ ከደመናውም- በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት የሚል ድምጽ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሰምተው ደነገጡ ፈጽመው ፈሩ በፊታቸውም ወደቁ። ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸው፤ አይዟችሁ ተነሡ አላቸው። ዓይናቸውንም አቅንተው ሲያዩ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አዩ እንጂ መነንም ማን አላዩም። በዚህ ሁኔታ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነቱን በታቦር ተራራ ገለጸላቸው። ይኸውም “ታቦርና አርሞንዔም በስምህ ደስ ይላቸዋል” (መዝ 88፡ 12-13) ተብሎ በቅዱስ ዳዊት የተነገረውን ትንቢት ሊፈጽም ነው። ስለምን በተራራ አደረገው ቢሉ ተራራ የወንጌል፣ የመንግስተ ሰማያት፣ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ነው። ተራራ ሲወጡት ይከብዳል ከወጡት በኋላ ግን ሜዳውንና ጭንጫውን ኮረብታውን ሲያሳይ ደስ ያሰኛል ወንጌልም ሲማሯት ታጽራለች፤ ከተማሯት በኋላ ግን ጽድቅና ኃጢያትን ለይታ ስታሳውቅ ደስ ታሰኛለችና። አንድም ተራራ በብዙ ፃእር እንዲወጡት መንግስተ ሰማይንም በብዙ መከራ ያገኟታልና ነው። በዚህም ተራራ ከነቢያት ሁለቱን ከሐዋርያት ሶስቱን ማምጣቱ በቤተ ክርስቲያን ብሉይና ሐዲስ እንዲነገር ለማጠየቅ ነው። መንግስተ ሰማያትንም ነቢያትና ሐዋርያት፤ ደናግላን እንደ ኤልያስና መዓስባን እንደ ሙሴ ያሉ፤ ሕያዋን እንደ ኤልያስና ምውታን እንደ ሙሴ ያሉ በአንድነት እንዲወርሷት ለማስረገጥ ነው። ማቴ 17፡1_
እግዲህ ይህ ታላቅ በዓል ብዙ ሚስጥር የተገለጠበት ስለሆነ ቅድስት ቤተክርስትያን በዜማና በመዝሙር ታከብረዋለች። በምናከብርበትም ጊዜ ቡሄ በሉ እያልን፣ ሙልሙል ይዘን፣ ችቦ እያበራን እናከብራለን። ምሳሌውም፦

ቡሄ፦
 ይህ ቦታ ጌታ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ተራራ ነው። በዚህ ምክንያት ያቺ ዕለት ቡሄ የሚለውን ስያሜ አገኘች ቡሄ ማለት ገላጣ፣ የተገለጠ ማለት ነው።

የሙልሙሉ እና የችቦው ምሳሌ ደግሞ፦
 ጌታችን ብርሃነ መለኮቱ በገለጠበት ዕለት ጊዜው ምሽት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እረኞች ከብርሃኑ የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም ነበር። የልጆቹን መዘግየት ያዩ ወላጆች ችቦ አብርተውና ዳቦ ይዘው ፍለጋ ወጡ። አሁን ታዲያ «ቡሄ» ለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠውና ችቦ በማብራት በዓሉን የምናከብረውም ከዚህ በመነሣት ነው።

ልጆች በገጠርም ሆነ በከተማ ጅራፍ የሚያጮኹበት ሁኔታም አለ። የጅራፉ ምሳሌ አብ «የምወደው ልጄ ይህ ነው፡፡ እርሱን ስሙት» ብሎ ሲናገር የነበረው ድምጽ ምሳሌ ነው። ሙሴና ኤልያስ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ያዕቆብ ደንግጠው ነበር። ያን ለማሰብ ጅራፍ እናጮሀለን።

አንቺ ደብረ ታቦር ምንኛ ታደልሽ
ጌታ መለኮቱን የገለጠብሽ
ያገቡ ድንግላይ ሁሉን ሰበሰብሽ፣
በብርሃን ተመልተሽ በመገኘትሽ
ለመንግስተሰማይ ምሳሌ ሆንሽ።
ዓለም እንዲያምንበት ባምላክነቱ
እነሆ በታቦር ታየ ጌትነቱ፣
አብ መሰከረለት በደመና አውሎ
የምወደው ልጄ ይህ ነው ስሙት ብሎ፣
ሙሴና ኤልያስ ካያሉበት መጥተው
ቆመው መሰከሩ በቀኝ በግራው።
በአጠቃላይ ደብረ ታቦር/በታቦር ተራራ ላይ
  1. "ታቦርና አርሞንኤም በአንተ ስም ደስ ይላቸዋል" መዝ 89:12 ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ።
  2. መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክነቱን ገለጠ።
  3. ምስጢረ ስላሴ ተገለጠ/አብ በደመና ድምጹን በማሰማት፣ መንፈስ ቅዱስ በብርሃን፣ ወልድ በአካል/።
  4. ሙሴ፦ "እኔ ማሕር ብከፍልም፣ ጠላት ብገድልም፣ ደመና ብጋርድም፣ መና ባወርድም፣ እስርኤልን ከክፋታቸው መልሶ ማዳን አልተቻለኝም። ለአንተ ግን ሁሉ ይቻልሃል። ደግሞስ የኔን ፈጣሪና ጌታ እንዴት ሙሴ ይሉሃል? የሙሴ ጌታ ይበሉህ እንጂ" በማለት የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት መሰከረ።
  5. ኤልያስ፦ "እኔ ሰማይ ብለጉም፣ እሳት ባዘንብም እስራኤልን ከክፋታቸው መልሶ ማዳን አልተቻለኝም። ለአንተግን ይቻልሃል። ደግሞስ የኔን ፈጣሪና ጌታ እንዴት ኤልያስ ይሉሃል? የኤልያስ ጌታ ይበሉህ እንጂ" በማለት የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት መሰከረ።
  6. በህይወት፣በእምነት፣ በቤተ ክርስቲያንና በአገልግሎት መኖር መልካም እንደሆነ ቅዱስ ጴጥሮስ "በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው" በማለት ተናገረ።
  7. የእግዚአብሔር መንግሥት ሕግን ጠብቀው ለሚኖሩ ለሁሉም መሆናን ሙሴን ከአገቡት፣ ኤልያስን ከደናግልና ሐዋርያትን ከአለም አምጥቶ አሳየን።
  8. ደብረ ታቦር የወንጌል፣ የመንግሥተ ሰማያትና የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ መሆኗን፤ ነብያት በትንቢትና በምሳሌ፣ ሐዋርያት በግልጥና በተግባር የሰበኳት መሆኑን ገለጠ።
ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን፤
ብርሃነ መለኮቱን እንደገለጠ ለኛም ምስጥርን ይግለፅልን። አሜን!!!

Tuesday, August 13, 2013

ፅንሰታ ለማርያም

ቅዱሳን አባቶቻችን ስለ እመቤታችን ነገር በውዳሴያቸውና በቅዳሴያቸው እንዲህ ተናግረዋል፤ ቅዱስ ያሬድ “ማርያምሰ ተኀቱ እምትካት ውስተከርሱ ለአዳም ከመ ባሕርይ ጸዓዳ:- ማርያምስ ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች" አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም "ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ጸነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ:- ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም ፤በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ" "እኔስ የማርያምን ነገር እናገራለሁ በማብዛት አይደለም በማሳነስ ነው እንጂ፣ በማርዘም አይደለም በማሳጠር ነው እንጂ " በማለት በተአምረ ማርያም ላይ የእመቤታችን ነገር እፁብ ድንቅ መሆኑን ዘወትር በዕለተ ሰንበት ያበስሩናል።

በኢየሩሳሌም አገር የሚኖሩ ኢያቄምና ሐና የተባሉ በጣም ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡ አንድ ልጅ እንኳ ስላልነበራቸው እጅግ ያዝኑ ነበር፡፡ ወደ ቤተመቅደስ እየሄዱ እግዚአብሔር ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ አጥብቀው ይለምኑት ነበር፡፡ መባ ይዘው ለሊቀ ካህኑ ሮቤል ሲሰጡት ሊቀ ካህኑ እንኳ ሳይቀር እግዚአብሔር ብዙ ተባዙ ያለውን ህግ በእናንተ ላይ እንዳይፈጸም አድርጎ ልጅ የከለከላችሁ ኃጢአተኛ ብትሆኑ ነውና መባችሁን አልቀበልም ብሎ በእጅጉ አሳዝኗቸዋል። 
በሊቀ ካህኑ እያዘኑና እየተከዙ ሲመለሱ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ ዛፍ ስር ተቀመጠው ሳለ እርግቦች ጫጩቶቻቸውን ሲያጫውቱ ተመልክተው “ለነዚኽ ወፎች እንኳ ልጆችን የሰጠህ አምላክ ለእኛስ መች ይሆን ልጅ የምትሰጠን?” ብለው እጅግ አምርረው አለቀሱ፡፡ ሐምሌ 30 እሷ እርሱ ግምጃ ሲያስታጥቃት መቋሚያው አፍርታ ፍጥረት ፍሬዋን ሲመገቡ፣ እሱ ለእሷ ነጭ ርግብ ሰባቱን ሰማያት ሰንጥቃ መጥታ በቀኝ ጆርዋ ገብታ በማኅፀንዋ ስታድር ሕልም አለሙ። ሄደው ለመፈክረ ሕልም/ ሕህልም ተርጓሚ ሲነግሩት የከበረች ልጅ እንደሚወልዱ ነገራቸው። እነእርሱም ነገሩ እንግዳ ነገር ስለሆነባቸው ጊዜ ይፍታው ብለው ተመለሱ። የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲሆንላቸው በጸሎት ጠየቁ፡፡ እግዚአብሔር ወንድም ሆነ ሴት ልጅ ቢሰጣቸው አድጎ/አድጋ እኛን ያገልግለን/ታገልግለን  ሳይሉ ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ እንዲሆን እንደሚሰጡት ቃል ገቡ፡፡
ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ አብርሃምን እና ሳራን የተመለከተ አምላክ በኢያቄምና ሃና አማካኝነት ለዓለም ድህነት ምክንያት የሆነችውን እና ዓለም ሳይፈጠር በአምላክ ልቦና ታስባ ትኖር የነበረች የተነገረላት ትንቢት ሊፈጸም የአባት የእናቷ የቅድመ አያቶቿ ራዕይ ሊተረጎም ጌታ የፈቀደበት ጊዜ ሲደርስ እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም እሁድ እለት ነሐሴ 7 ቀን በ16 ዓ.ዓ ተፀነሰች፡: ሐና በእርጅናዋ ጊዜ መፅነሷ የተመለከቱ ዘመዶቿና ያገሯ ሰዎች ተገርመው እየመጡ ይጠይቋት ነበር፡፡
እመቤታችን ማርያም በፅንስ እያለች ታምራትን አድርጋለች። ከእነዚህም መካከል ዐይነ ስውር የነበረችው የአርሳባን ልጅ ወደ ሐና መጥታ እውነትም ሐና መጸነሷን ለማረጋገጥ ሆዷን ዳሰሰቻት፡፡ በአድናቆትም ሳታስበው ዐይኗን ስትነካ ዐይኗ በራላት፡፡ በሌላ ጊዜም የአጎቷ ልጅ በህመም ምክንያት ይሞትና ሐና ትወደው ስለነበር ልታለቅስ ወደአረፈበት ቤት ትሔዳለች፡፡ እንደደረሰችም አስክሬኑ በተቀመጠበት መካከል አልጋ ዙሪያ ስታለቅስ ሳለ ድንገት ጥላዋ ቢያርፍበት የሞተው ሰው ተነስቶ ሐና የአምላክ እናት የምትሆን እመቤታችንን እንደምትወልድና በዚህም ሐና እጅግ የከበረችና ምስጋና የሚገባት መሆኗን መሰከረ፡፡ ከዚህም በኋላ እመቤታችን ግንቦት 1 ቀን በክብር ተወለደች።


እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ  ከልጅሽ ከወዳጅሽ ይቅርታው፣ ቸርነቱ፣ ምህረቱ በእኛ ላይ እንዲያድር ለምኝልን፡ አሜን!!!

Monday, July 29, 2013

ብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ ካልዕ (፲፱፻፴፪ - ፲፱፻፹፪)

                                                          የሕይወት ታሪክ እና አገልግሎታቸው
                                                                      
   መግቢያ

ዛሬ የሚያውቋቸው ሲቃ ይተናነቃቸዋል። ዓይናቸው በእንባ ይሞላል። ስለብፁዕነታቸው ሲያወጉ ውለው ቢያድሩ አይሰለቹም። እንኳን ዘዋይ ደርሰው የመጡት ፊታቸውን እንኳን አይተው የማያውቁት የብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስን ዜና ሕይወት መተረክ ያስደስታቸዋል። ለምን ይሆን? ብዙዎች በአካል ሳያውቋቸው ጣፋጭ ትምህርታቸውን ከአንደበታቸው ሳያዳምጡ በማለፋቸው ይቆጫሉ። ሌሎች ደግሞ ትምህርታቸውን፣ ምክራቸውን፣ ሓሳባቸውን ሁሉ በምስል እና በድምጽ ሳያስቀሩ በማለፋቸው ይጸጸታሉ። ሐዋርያዊ ተጋድሎዋቸው እና መንፈሳዊ አርበኝነታቸውን በቅርብ ላስተዋለ እና ዜና ሕይወታቸውን ላዳመጠ ብፁህነታቸው ዘወትር የሚነበቡ ታላቅ መጽሐፍ ነበሩ። የቅንጦት እና የቅምጥል ሕይወት ሳይናፍቃቸው በፍጹም ገዳማዊ ጠባይ የላመ የጣመ ሳይመገቡ፣ በትኅርምት እየኖሩ ወላጅ አልባ እና ችግረኛ ህጻናትን ሰብስበው እያሳደጉ ቢንቢ እየወረሳቸው ዋዕዩ በሚፋጅበት የወባ በሽታ ባየለበት ሌላው ቀርቶ ጣፋጭ እና ንጹህ ውሃ እንኳን በማይገኝበት ስፍራ ራሳቸውን ጥለው በበሽታ ሲሰቃዩ አንድ ቀን እንኳን ሳይሰለቹ እና ሳይማረሩ በተጋድሎ የኖሩ እጅግ ትሁት የነበሩ አባት ነበሩ። በመንፈስ የወለዷቸው፣ በሃይማኖት ያሳደጓቸው ልጆቻቸው ከልብ በመነጨ ፍጹም ፍቅር “ጎርጎሪ” እያሉ ሲጠሩዋቸው የሰማ የብፁዕነታቸውን ታሪክ ለማወቅ ይጓጓል።

ልደት እና አስተዳደግ
ብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ በ1932 ዓ.ም በደቡብ ወሎ ሃገረ ስብከት በደሴ ከተማ ከአቶ ገበየሁ አየለ እና ከወ/ሮ አሰለፈች ካሳ ተወለዱ። ወላጆቻቸው ወንዶች ልጆች ሲወልዱ እየሞቱባቸው በጣም ተቸግረው ስለነበር ለፈጣሪያቸው ልመና አቅርበው በስዕለት ወንድ ልጅ ወልደው ለማሳደግ በቁ። ለልጃቸው ከነበራቸው ፍቅር የተነሳም “ተስፋዬ” በማለት ስም አወጡላቸው። ብርቅዬ የስእለት ልጅ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ በህጻንነታቸው ወራት የወላጆቻቸውን፣ የዘመዶቻቸውን እና የሌሎችም ሰዎች ዓይን ማረፊያ ነበሩ። ከእድሜ እኩያዎቻቸው ጋር ከቤት ወጥተው ሲጫወቱ የእንጨት መስቀል ሰርተው ጓደኞቻቸውን ለማሳለም ይሞክሩ ነበር። አንድ ቀን ብቻቸውን ሲሆኑ ደግሞ የመምህራቸውን የአለቃ ድንቁን የድጓ መጽሐፍ ገልጠው ሲያዩ የተመለከቱት አለቃ ድንቁ “ዕድሜ ሰጥቶኝ የዚህን ህጻን መጨረሻ ባሳየኝ” ብለው ነበር።

የትምህርት ሕይወት

ዕድሜያቸው ለት/ት ሲደርስ በደሴ መድኃኔአለም ቤ/ክ ፊደል ለመቁጠር፣ የግዕዝ ንባብ ለመማር ሄዱ። ብፁዕ አባታችንም ይህን ትምህርት ሲማሩ በቀለም አያያዛቸው የደብሩ መምህራን በጣም ያደንቋቸው ነበር።ብፁዕነታቸው በኮከብ አዕምሮአቸው የጀመሩትን ት/ት የበለጠ ሊገፉበት ስለፈለጉ በህጻንነታቸው ት/ት ፍለጋ የተወለዱበትን መንደር፣ ያደጉበትን ቀዬ ትተው ወደ ላስታ ሄዱ። በልጅነት ዕድሜያቸው ምናኔ የጀመሩት በዚያን ጊዜ ከላስታ ወደ ደሴ መጥተው የነበሩትን አባ ክፍለ ማርያም የሚባሉትን መምህር ተከትለው ነበር። አባ ክፍለ ማርያም ከደሴ ወደ ላስታ ገነተ ማርያም፣ ነአኩቶ ለአብ ገዳም ሲመለሱ አባ ጎርጎሪዮስ ተከትለዋቸው ላስታ በር ይደርሳሉ። አባ ክፍለ ማርያም ጸሎት ሊያደርሱ ወደ ተቀመጡበት ስፍራ ሲያመሩ አባ ጎርጎሪዮስም ቀረብ ብለው “ጤና ይስጥልኝ” ይላሉ አባ በጸሎት ሰዓት የሚያናግራቸውን ሰው የሚያናግሩት በግዕዝ ነበር እና “መኑኬ” አሏቸው። አባ ጎርጎሪዮስም በድንጋጤ ዝም ሲሉ ሌሎች ተማሪዎች “ማነህ” ነው የሚሉህ አሏቸው። አባ ጎርጎሪዮስም “እኔ ነኝ እርስዎን ተከትዬ ልሔድ ከደሴ መጥቼ ነው” አሉ። በዚህን ጊዜ አባ ክፍለ ማርያምም ደንገጥ በለው “እረ ሎቱ ስብሐት! ከደሴ እስከዚህ ድረስ እኛን ስትከተል!” በማለት በውሳኔያቸው ተገርመው ወደ ላስታ አባ ቡሩክ ገዳም ይዘዋቸው ይገባሉ። ደሴ የተጀመረው ትምህርት ወደ ላስታ ሲመጡ በቀላሉ የሚታለፍ አልነበረም። የተማሪ ቤት ሕይወት በትህትና የተሞላ፣ አንዱ ለሌላው ወንድሙ በመጨነቅ የሚኖርበት ሕይወት ነው። ተማሪ ቤት ምቾት በሌለው መኝታ፣ ያለመብራት በጨለማ እያፈጠጡ፣ ጠዋት ምግብ ፍለጋ ሲወጡ ከውሾች ጋር እየታገሉ በረሃብ እና በጥም፣ በወረርሽኝ እየተንገላቱ የሚማሩበት፣ ብዙ ችግር እና መከራ የሚያሳልፉበት፣ የነገውን ማንነት በብዙ ድካም የሚቀርጹበት እና ዘወትር የማይጠፉ ብዙ ትዝታዎችን የሚሰበስቡበት ሕይወት ነው። የተማሪ ቤቱን ትዝታ ብጹዕ አባታችን እራሳቸው በእንግሊዘኛ ባቀረቡት አንድ ጥናታዊ ጽሁፋቸው እንዲህ ገልጸውት ነበር።
“ለቋንቋ ዕድገት በቅድሚያ መምህር ቀጥሎም የማስተማሪያ መሳሪያዎች፣ ት/ቤት፣ ወረቀት፣ ብዕር እና ቀለም አስፈላጊ መሆናቸው ይታወቃል። ዘመናዊ የማስተማሪያ መሳሪያዎች ባልነበሩበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያን የዛፍ ጥላዎች እና የመቃብር ቦታዎችን በት/ቤነት ተጠቅማለች። አንድ ሰው ሲሞት በቤ/ክ ግቢ ይቀበራል። ዘመዶቹም በመቃብሩ ላይ ለእንግዶች እና ለመንገደኞች ማደሪያ የሚሆን ቤት ይሰራሉ። የቀድሞ የቤ/ክ ሊቃውንትም ሲያስተምሩ እና ሲማሩ የኖሩት እንደዚህ ባሉ የመቃብር ቤቶች ውስጥ ነበር። ወረቀት ባይኖርም ካህናቱ ፍየል እና የበግ ቆዳ እና ሌጦ አድርቀው፣ ቀፈው እና ፍቀው ብራና አዘጋጅተው ፊደል ጽፈውበታል። ገብስ ቆልተው፣ ፈጭተው፣ በውሃ በጥብጠው ከከሰል ጋር ደባልቀው ቀለም አዘጋጅተዋል። ቀጭን መቃ ቆርጠው፣ ቀርጸው፣ ጫፉን ሰንጥቀው ከቀርነ በግዑ እየጠቀሱ የሚጽፉበት ብዕር አዘጋጅተዋል። አያሌ የኢትዮጵያ መጻሕፍት የተጻፉት እንደዛሬው በኅትመት መሳሪያ ሳይሆን በሊቃውንቱ እጅ ነበር።” ብጹዕ አባታችን ከታዋቂው መምህር ክፍሌ (አባ ክፍለ ማርያም) ዘንድ የውዳሴ ማርያም እና የቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ፣ አዕማደ ምስጢራትና ባህረ ሐሳብን ተምረዋል። ብጹዕነታቸው በተማሪ ቤት እጅግ በሚያስደንቅ ፍጥነት እና ጉጉት የሚነገራቸውን ቀለም ከመያዛቸውም ሌላ ከእርሳቸው በላይ በትምህርት የገፉት ተማሪዎች ሲማሩ በሚያደምጡት ብቻ ቀለሙን ይዘው ተማሪዎቹ ሲሳሳቱ ያርሙ እና ይመልሱ ነበር። ብጹዕነታቸው ዘወትር ጥያቄ መጠየቅ ይወዱ ስለነበር መምህራቸው የሚነግሯቸውን ሁሉ ልቅም አድርገው ይይዙ ነበር። በዚህ ችሎታቸው የተደነቁት መምህራቸው በቤተሰባቸው የወጣላቸውን ተስፋዬ ገበየሁ የሚለውን ስም መዝገበ ሥላሴ ክፍሌ በማለት በራሳቸው ስም እንዲጠሩ አድርገዋል።
ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ በዘመኑ ከነበሩት ከብጹዕ አቡነ ይስሐቅ ማዕረገ ዲቁናን ከተቀበሉ በኋላ ሌሎች ትምህርቶችን ለመቀጸል ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም መጥተዋል። በገዳሙም በ1956 ዓ.ም ምንኩስናን ተቀብለዋል። ከምንኩስናም በኋላ ለት/ት የነበራቸው ከፍተኛ ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ ወደ አዲስ ዓለም ደብረ ጽዮን ማርያም ሄደው ከታላቁ የቅኔ መምህር ከአፈወርቅ መንገሻ ዘንድ ቅኔ ከነአገባቡ ጠንቅቀዋል። ከዚያም ወደ ደብረ ሊባኖስ ተመልሰው የሐዲሳት ትርጓሜና ትምህርተ ሃይማኖት ከመምህር ገ/ሕይወት ሲቀጽሉ፣ መጽሐፈ ሊቃውንትን ደግሞ ከመምህር ቢረሳው አሂደውታል። ቀጥሎም ወደ ደብረ ጽጌ ማርያም በመሄድ ዜማ፣ ምዕራፍ፣ ጾመ ድጓን ከመሪጌታ አብተው ላሊታግዳን መዝገበ ቅዳሴን ከመምህር ልዑል ተምረዋል።
ብጹዕነታቸው ከቤ/ክ ሊቃውንት እግር ሥር እየተቀመጡ በብዙ ድካም እና ችግር ከሃገር ወደ ሃገር እየተዘዋወሩ የገበዩት ዕውቀት ታላቅ የቤ/ክ ዓምድ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ በፍቅረ እግዚአብሔር የተቃጠሉ እጅግ ትሁት እና አስተዋይ አባት ነበሩ። በደብረ ሊባኖስ ገዳም በነበሩበት ጊዜ በዕድሜ የገፉትን መነኮሳት ሊጥ አብኩተው፣ ዳቤ ጋግረው እና ሌሎችም ተግባራት በመፈጸም ይራዱ ነበር። በብህትውና ዘመናቸው የሰገዱበት የእጃቸው ፈለግ ቀንበር የዋለበት የበሬ ጫንቃ ይመስል እንደነበር ገዳማዊ ሕይወታቸውን በቅርብ የሚያውቁ አባቶች ይናገራሉ። በ1957 ዓ.ም ወደ አ/አ በመምጣት ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማዕረገ ቅስናን ተቀብለዋል። ከዚያም ከመምህር ፍስሐ ወደ ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ተልከው ሐረርጌ በሔዱበት ጊዜ ከመንፈሳዊ ሕይወታቸው ጎን ለጎን በደሴ አቋርጠውት የነበረውን የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ት/ታቸውን ተከታትለዋል። በዘመናዊ ት/ቤት ቆይታቸውም ሌት ተቀን ተግተው በትኩረት የሚከታተሉ መሆናቸውን ያወቁት ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ከፍተኛ ሞራል በመስጠት ይንከባከቧቸው ነበር። በተጨማሪም ወደቤታቸው እያስጠሩ ያስተምሯቸው ነበር። ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ የቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ አስተዳዳሪ በመሆንም አገልግለዋል። የብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዎስን የአዕምሮ ብስለት እና ከፍተኛ የትምህርት ጉጉት የተረዱት ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ በ1963 ዓ.ም ለከፈተኛ ት/ት ወደ ግሪክ ልከዋቸዋል።

ትምህርት በባህር ማዶ

በሕጻንነታቸው ት/ት ፍለጋ ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ከተወለዱበት መንደር ርቀው መሄድ፣ ከክፍለ ሃገር ክፍለ ሃገር መዘዋወር የለመዱት ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ አገር አቋርጠው ባህር ተሻግረው ወደ ግሪክ በመሄድ በተለያዩ ኮሌጆች እየተዘዋወሩ ለቤ/ክናቸውና ለሃገራቸው የሚጠቅም ከፍተኛ እውቀት ገብይተዋል። ብጹዕነታቸው በግሪክ ቆይታቸው፦
በደሴተ ፍጥሞ ለሁለት ዓመታት መንፈሳዊ ት/ት ተምረው ዲፕሎማ፣
በአቴንስ ዩኒቨርስቲ ለአራት ዓመታት የስነ መለኮት ት/ት ተምረው ማስትሬት ዲግሪ፣
በሲውዘርላንድ ፍሪበሪን ዩኒቨርስቲ የፈረንሳይኛ ቋንቋ አጥንተው የምስክር ወረቀት፣
በኢየሩሳሌም ደብረ ጽዮን የግሪክ መንፈሳዊ ኮሌጅ የአረቢኛ ቋንቋ አጥንተው የምስክር ወረቀት አግኝተዋል።
የብጹዕ አባታችን አገልግሎት መጀመር
ከዚያም በኢየሩሳሌም በሚገኙት የኢትዮጵያ ገዳማት በተለይም በደብረ ገነት ኪዳነ ምህረት የኢትዮጵያውያንን ልጆች በማሰባሰብ ኢትዮጵያዊ ባህላቸውንና ቋንቋቸውን ያስተምሩ ነበር። ከዚያም በተጨማሪ ለገዳሙ የገቢ ምንጭ እንዲሆን የዕጣንና የከርቤ ቅመማ ያካሂዱ ነበር። እግዚአብሔር በየትኛውም ቦታ እና ጊዜ ሰወች አሉት። ሰወች ቤ/ክን ለመጣል ሲነሱ እግዚአብሔር ደግሞ ሊያነሳት የራሱን ሰወች ያስነሳል። ቤ/ክ በወቅቱ ሥልጣን በያዘው ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ተጽዕኖ የከፋ ችግር ላይ በወደቀችበት ጊዜ በደሙ የመሰረታት ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱ የሆኑ ሰወች አምጥቶ ሰጥቷታል። ከነዚህም ውስጥ ብጹዕነታቸው አንዱ ናቸው። ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ ካልዕ ቤ/ክ በተቸገረችበት ጊዜ ያገኘቻቸው፣ “እግዚአብሔር የቤ/ክ ጠላቶችን ያሳፍር ዘንድ ለተዋህዶ ሃይማኖታችን ጠበቃ አድርጎ ያስነሳቸው ምሁር አባት ነበሩ።” ቤ/ክ አስተዳደሯ ተቀልብሶ ተቸግራ ልጆቿን ስትጠራ በፈቃደ እግዚአብሔር ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዎስም ከባህር ማዶ ቅድስት ሃገር ከኢየሩሳሌም ተጠርተው መጡ። ብጹዕነታቸው ስለአመጣጣቸው ሲገልጹ፦ “አንድ ቀን ሌሊት ከተኛሁበት ክፍል ውስጥ አንድ ሰው ስሜን ጠርቶ ይቀሰቅሰኛል። ስነቃም ከራስጌ በኩል አንድ ቀላ ያለ ረጅም ሰው ቆሟል፤ ክፍሉም በነጭ ደመና የተሞላ ነበርና እጅግ በድንጋጤ ላይ እንዳለሁ ሰውየው “ተነሳ ወደ ኢትዮጵያ እንሂድ” ይለኛል። ለምን? በማለት ስጠይቀው ወንጌል እናስተምራለን። አሁን ከዚህ የምትቀመጥበት ጊዜ አይደለምና ተነሳ እንሂድ ይለኛል። በጥያቄው እና በትዕዛዙ ግራ በመጋባት አንተ ማነህ? ብዬ ስጠይቀው “ኤፍሬም ሶሪያዊ ነኝ” ብሎኝ ተሰወረብኝ። የሆነውን ነገር ማሰላሰል ጀመርኩ። በእንዲህ ሁኔታ ሌሊቱ አልፎ ንጋቱ ተተካ በበነጋውም ጥሪ ይደርሰኛል። ጥሪውም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ መንበረ ፓትሪያርክ ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘንድ ነበር። ብለዋል። በዚህ ሁኔታ ወደ አ/አ የመጡት ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ልዩ ልዩ መንፈሳዊ አገልግሎት ማበርከት ጀመሩ። በጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የአስራ ሶስት ኤጲስ ቆጶሳት ሥርዓተ ሲመት ተፈጽሟል። ቤ/ክ በአንድ ጊዜ 13 ኤጲስ ቆጶሳት ስትሾም የመጀመሪያዋ ነው። በዕለቱ አባ መዝገበ ሥላሴ ክፍሌም ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ ካልዕ የሸዋ ሃገረ ስብከት ኤጲስ ቆጶስ ተብለው ተሹመዋል።

በኢትዮጵያ ቤ/ክ “ጎርጎሪዮስ” በሚል ስያሜ የተጠሩት አራቱ ሊቃነ ጳጳሳት፦
ነሐሴ 25 ቀን 1952 ዓ.ም የተሾሙት አቡነ ጎርጎሪዎስ ቀዳማይ የከፋ ሊቀ ጳጳስ
ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም የተሾሙት ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ ካልዓይ የሸዋ ሊቀ ጳጳስ
ጥር 18 ቀን 1983 የተሾሙት ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ ሣልሳይ
ኅዳር 4 ቀን 1987 ዓ.ም የተሾሙት ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ ራብዓይ የምስራቅ ሸዋ ሊቀ ጳጳስ ናቸው።

የጵጵስናና የዝዋይ ካህናት ማሰልጠኛ አገልግሎት
ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ ካልዕ ለጵጵስና ሲመረጡ የጠበቃቸው እጅግ ከባድ ኃላፊነትና መሥዋዕትነትን የሚጠይቅ ፈተና ነበር። ደርግ አርቆ አስተዋይ፣ ቆራጥና ፍጹም መንፈሳዊ አባቶችን በኃይል አስወግዶ ቤ/ክንን ባዶ ሊያደርጋት ሲያስብ እግዚአብሔር ባወቀው የቀደሙትን አባቶች አሠረፍኖት የሚከተሉ አርቆ አስተዋይ፣ ቆራጥና ፍጹም መንፈሳዊ አባት ተተኩ። ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ ዛሬ በአራት አህጉረ ስብከት ተከፍሎ በአራት ሊቃነ ጳጳሳት የሚተዳደረውን የሸዋ ሃገረ ስብከት በአንድ ላይ ይዘው ከየካቲት ወር 1971 ዓ.ም ጀምሮ መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን ጀምረዋል። ብጹዕነታቸው የቅዱስ ፓትሪያርኩ እንደራሴ እና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ሆነው በመሾማቸው ከሃገረ ስብከታቸው ጋር ተደራራቢ ኃላፊነትን ተሸክመዋል። ብጹዕነታቸው በእርሻ ውስጥ ልብሳቸውን እንቧይ እየቧጠጠው እሾህ እየቀደደው ከተማሪዎች ጋር ይጓዙ ነበር። በስራ ጊዜ መንገድ አይመርጡም። አትክልቱን ዘወትር ጠዋት እና ማታ ይጎበኙት ነበር። ኮርሰኞች ጠዋት ከእንቅልፋቸው ሲነሱ ብጹዕነታቸውን የሚያገኙዋቸው በአትክልቱ ውስጥ ነበር። ብጹዕነታቸው ብዙ ጊዜ ከአትክልት ውስጥ ስለማይጠፉ በወባ ተይዘው ክፉኛ በመታመማቸው ለህክምና ወደ አ/አ ሔደው ነበር። ህክምና አግኝተው ሲሻላቸው ብጹዕ አቡነ ተ/ሃይማኖት “ከአሁን በኃላ ወደ ዘዋይ አይሂዱ። ለማሰልጠኛው ጥሩ አባት ሰይመው፣ አ/አ ተቀምጠው በስልክ መመሪያ እየሰጡ የከታተሉ” ብለዋቸው ነበር። ብጹዕነታቸው ግን “የምሞተው እዚያው በልጆቼ መካከል ነው። ለወባ ብዬ ክርስቶስ ያሸከመኝን መስቀል ጥዬ ልጆቼን በትኜ አ/አ አልቀመጥም” በማለት ወደ ዘዋይ ተመልሰዋል። ብጹዕነታቸው በየጢሻው የለበሱትን ልብስ ለብሰው ሲሔዱ ጋሬጣ እንኳን ሲይዘው መለስ ብለው አያዩትም ነበር። “ትርጉሙ ምን እንደሆነ ባይገባኝም ዘወትር ትዝ የሚለኝ ነገር ልብሴን እንጨት ይዞታል ብለው እንኳን ዘወር ብለው አለማየታቸው ነው። ብቻ ወደፊት ለሥራ መሄድ እንጂ ልብሴ ይቀደዳል፣ ይበላሻል በሚል ስጋት ወደኋላ የሚሸሹ አባት አልነበሩም። ብጹዕነታቸው ልብሳቸው ቢቀደድ ቢተረተር እንዴት ይህን ለብሼ እታያለሁ ብለው የሚጨነቁ ሳይሆኑእንደ ትጉኅ ገበሬ ተራ ልብስ፣ የተሸታተፈ ቀሚስ ለብሰው ነጠላቸውን አደግድገው ታጥቀው በመካከላችን የሚገኙ አባት ነበሩ”። ብጹዕነታቸው በቤ/ክ፣ በአደባባይ ዘወትር የማይለዋወጥ አቋቋም ነበራቸው። በትረ ሙሴያቸውን በቀኝ ክርናቸው ተደግፈው፣ በግራ እጃቸው የበትረ ሙሴውን ጫፍ ይዘው መስቀላቸውን በቀኝ እጃቸው ይዘው ጫፉን ጉንጫቸው ላይ አሳርፈው ይቆማሉ። ሲቀመጡም በፍጹም እግራቸውን አዛንፈው ወይም አነባብረው አይቀመጡም። እግርን ማዛነፍ እና ማነባበር በእርሳቸው ዘንድ ታላቅ ኃጢያት ነው። ይህ በራሱ የጸሎት የጸሎት ሥርዓት ነውና ። ብጹዕ አባታችን ለተማሪዎች ከፍተኛ ፍቅር የነበራቸው አባት ነበሩ። ከኢትዮጵያ ውጪ ሔደው ሲመለሱ ከቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባም ሲወጡ ቀኑ በጣም መሽቶ ዝዋይ ገብቶ ለማደር አስቸጋሪ ካልሆነ በስተቀር አዲስ አበባ ማረፍ አይፈልጉም። ለምን አ/አ ትንሽ ቀናት አያርፉም? ተብለው ሲጠየቁ “ ከልጆቼ ስለይ እሳሳለሁ” ይላሉ። ዝዋይ ሲገቡም ቤ/ክ ተሳልመው ወደቤት ገብቼ ትንሽ ልረፍ፣ ልብሴን ልቀይር ሳይሉ በቀጥታ ወደ ክፍል ገብተው ተማሪዎቹን ያዩ ነበር። ማታ ከሰርክ ጸሎት በኃላ ደግሞ ከዘዋይ የሄዱበትን ምክኒያት ያጋጠማቸውን ሁኔታ እና ተማሪዎቹ ሊያውቁ የሚገባቸውን ነገሮች ይገልጹላቸው ነበር። ብጹዕነታቸው ከተማሪዎቻቸው መለየት ስለማይሆንላቸው የሚመገቡትም ከተማሪዎች ጋር በአንድነት የምግብ አዳራሽ ውስጥ ነበር። ከተማሪዎቹ የሚለዩት በሚቀመጡበት ጠረጴዛ ብቻ ሲሆን የሚመገቡት ለተማሪዎቹ የተዘጋጀውን ምግብ፣ የሚጠጡት በበርሜል የተፈላውን ሻይ እንጂ የተለየ ነገር አይዘጋጅላቸውም ነበር። ብጹዕነታቸው የላመ የጣመ የሚመገቡ፣ ይህ ያስፈልገኛል፣ ይህ ይዘጋጅልኝ በማለት የሚጠይቁ አባት አልነበሩም። ሰውነታቸው የገዘፈው በጸጋ እግዚአብሔር እንጂ በምግብ አልነበረም። በመጨረሻ አካባቢ ብጹዕነታቸው በብርድ በመታመማቸው በምግብ አዳራሽ ተቀምጠው መመገብ ቢያቆሙም ከቤታቸው ሄዶ የሚመገቡት ያንኑ ለተማሪዎች የተዘጋጀውን ምግብ ነበር። መነኮሳት የምግብ አዳራሽ ውስጥ በሚገኘው አንድ ክፍል ተቀምጠው ሲመገቡ መጽሐፈ መነኮሳት እየተነበበላቸው ሥርዓተ አበውን ይማሩ ነበር። ስለዚህ በምግብ አዳራሽ ውስጥ ምንም አይነት ድምጽ ማሰማት አይፈቀድም። ሲመገብ ወጥ ያነሰው፣ ውሃ የፈለገ ቢኖር እጁን አንስቶ መጋቢውን ወይም አሳላፊውን በጥቅሻ ጠርቶ ያስጨምራል እንጂ ድምጽን አሰምቶ መጣራት፣ ማውራት አይፈቀድም። ተመጋቢዎች በፍጹም ወጥ ማስተረፍ አይፈቀድላቸውም፣ በሳህን ላይ ያወጣውን ወጥ የመጨረስ ግዴታ ነበር። ብጹዕነታቸው ለተማሪዎች የስነ ምግባር ት/ት ከፍተኛ ትኩረት ይሰጡ ነበር። የገዳሙ ተማሪዎች ሁሉ ለገዳሙ ሕግና ስርዓት ተገዥ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ሕግ ተላልፎ፣ ሥርዓት ጥሶ የተገኘ ተማሪ ጥብቅ የሥነ ስርዓት እርምጃ ይወሰድበታል። ብጹዕነታቸው በብልሹ ተማሪዎች ላይ የማያዳግም ውሳኔ በመስጠት ልጆችን በሥርዓት ማሳደግ እንጂ ጥፋትን ሸፋፍኖና አለባብሶ ማለፍ አይወዱም። ውሳኔያቸው የግል ጥቅሜን ያስቀርብኛል፣ ክብሬን ይጋፋኛል ከሚል ስጋት የመነጨ ሳይሆን ልጆቼን ያበላሽብኛል ብለው ስለሚፈሩ፣ እንዲሁም የተጀመረው ዓላማ እንዳይጨናገፍ ስለሚፈልጉ ነው እንጂ ሰወችን ለማሳዘን፣ ለመጉዳትና ለመግፋት ፍላጎት ኖሯቸው አይደለም። ብጹዕነታቸው ፈጽሞ ሰወችን ማጉላላና ደጅ ማስጠናት አይሹም። ለማንም የሚገባውን አይከለክሉትም፣ የማይገባው ከሆነ ደግሞ ሌላ ዕድል ሞክር በማለት ቁርጥ ያለና ግልጽ ውሳኔ ይወስናሉ። አንድ ጊዜ ለኮርስ ከመጡ ተማሪዎች መካከል አንዱ በማሰልጠኛው የሚሰጠውን ት/ት የማጠቃለያ ፈተና ሲወስድ ውጤቱ ለምረቃ ሊያበቃው አልቻለም። ሌላው ቀርቶ ንባብ እንኳን አያውቅም ነበር። ስለዚህ ብጹዕነታቸው እንደገና እንዲማር ይወስናሉ። ይህንን የሰሙ ብዙ ሰወች በሽምግልና መጥተው ምንም የማያውቀው ተማሪ እንዲመረቅ ይለምኑአቸዋል። ብጹዕነታቸው ግን “ተማሪውን ለማሳዘን ፈልጌ ሳይሆን ምንም ነገር የማያውቅ ሰው መርቆ መላክ በቤ/ክ አገልግሎትና በራሱ በሰው ህይወት መቀለድ ነው።” በማለት ልጁ ዳግመኛ እንዲማር አድርገዋል። ለዚህም ብጹዕነታቸው ብዙ ጊዜ “እዚህ በረሃ የወደቅኩት ሰው አፈራ በማለት እንጂ አልጫ ፍትፍት ብፈልግ ኖሮ መሃል ከተማ አልወጣም ነበር?” በማለት ሃሳባቸውን ያስረዱ ነበር። ብጹዕነታቸው ከገዳሙ ጀርባ ቦጨሳ ከሚባለው መንደር ብዙ ልጆችን ተቀብለው አሳድገዋል፤ አስተምረውም ለቁም ነገር አብቅተዋል። ሌሎች ደግሞ ምግብ እየተመገቡ፣ አልባሳት እየተሰጣቸው በተመላላሽነት ያድጉ ነበር። እነዚህ ልጆች አንድ ቀን ማታ ከገዳሙ ዕቃ ሰርቀው ይወጣሉ። በዚያ ድቅድቅ ጨለማ የገዳሙ ተማሪዎች በየአቅጣጫው ልጆቹን ፍለጋ ተሯሩጠው ይይዙዋቸዋል። ከሰረቁት ዕቃ ጋርም ወደ ገዳሙ አምጥተው ለብጹዕነታቸው ያስረክባሉ። ጠዋት በግቢ ውስጥ ያሉት ሰወች ተጠርተው ይሰበሰባሉ።ብጹዕነታቸው ልጆቹን “ይህ ቤት የምትበሉበት፣ የምትጠጡበትና የምትለብሱበት አይደለም? ለምን ይህን አደረጋችሁ?” በማለት ጠየቋቸው እና መጋቢውን ጠርተው ዕቃውን ተረክበው ልጆቹን በነጻ ወደቤታቸው እንዲያሰናብቷቸው ይወስናሉ። የያዝዋቸው ተማሪዎች ግን የብጹዕነታቸውን ውሳኔ ሲሰሙ ተናደዱ። ያን ያህል ሮጠውና ደክመው ሌቦቹን ከያዙ በኋላ ወደ ፖሊስ ጣቢያ መሄድ ሲገባቸው በነጻ በመለቀቃቸው ይከፋሉ። ሌቦቹ ከተለቀቁ በኋላ ብጹዕነታቸው “ልጆቹ በመለቀቃቸው ማዘን የለባችሁም። በእርግጥ ልጆቹን ፖሊስ ጣቢያ ወስደን ማሳሰር እንችል ነበር። ነገር ግን ፖሊስ ዘንድ ተካሰን ስንቀርብ ኦርቶዶክሶች ተሰራርቀው፣ ተካሰው ቀረቡ እንባላለን። እራሳችንን ለጠላት መሳለቂያ እናደርጋለን። በሌላ በኩል ልጆቹን አሳልፈን የምንሰጠው ፈሪሃ እግዚአብሔር ለሌላቸው ፈራጆች በመሆኑ በጣም ሊሰቃዩ እና ሊጎዱ ይችላሉ። ልጆቼ የእናንተ ፊት እና የእናንተ ዓይን እራሱ ታላቅ ዳኛ ነው። ከፊታችን በመቆማቸው የተቀጡት ቅጣት በጣም ከባድ ነው” በማለት ተማሪዎቹን አሰናበቱ። ልጆቹ ባይሰርቁ ኖሮ እንዲህ አይነቱን ት/ት ለምንግዜውም አያገኙትም ነበርና ብዙ ተማሪዎች በድርጊቱ እግዚአብሔርን አመሰገኑ። ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ ተማሪዎቻቸውን “ለትምህርት ጊዜ አትስጡ የምንኖረው በፖለቲካ ዓለም ውስጥ ነው። ገማቾች ጥያቄ ያቀርቡብናል። ያን ሁሉ ካልተቋቋምን እግዚአብሔር አይደሰትብንም። በመማር ብቁ እንሁን” በማለት በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ እንዲሆኑ ያበረታቷቸው ነበር። የቅኔ ተማሪዎችን፣ የዜማ ተማሪዎችን በሥራ እያወዳደሩ ሽልማት ይሰጡዋቸው ነበር። ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ ተማሪዎችን አስተምሮና መርቆ ማሰናበት ብቻ ሳይሆን ከምረቃም በኋላ የተማሪዎችን ሕይወት በሚገባ የሚከታተሉ አባት ነበሩ። ተማሪዎች ከምረቃ በኋላ ከብጹዕነታቸው ጋር እንዴት መገናኘት እንዳለባቸው ያጋጠማቸውን ችግር፣ የሥራ ፍሬ (ምን ያህል ኢአማንያንን እንዳጠመቁ፣ ያጋጠማቸውን የመናፍቃን እንቅስቃሴና መሰናክል) በጽሁፍ አዘጋጅተው ወደ መንበረ ጵጵስናቸው (ዝዋይ ገዳም) እንዲያመጡ ምክር ይሰጡ ነበር። ከከፍተኛ ት/ት ተቋማት በክረምት ወራት መጥተው የሚማሩ ተማሪዎችን እንቅስቃሴም እንዲሁ በየክረምቱ አንድ ትልቅ መንፈሳዊ የውይይት መርሐ ግብር አዘጋጅተው እንዴት እንዳስተማሩ፣ ያጋጠማቸውን ችግር እያነሱ ከተወያዩ በኋላ ያለፈው ስርዓት ለሃይማኖት አስቸጋሪ ስለነበር በብልሃት በመንፈሳዊ ጥበብ እንዴት መመላለስ እንዳለባቸው ይመክሯቸው ነበር። ዓመቱ ደርሶ ተማሪዎች ተመልሰው እስኪመጡ ድረስ በደብዳቤ እየተጻጻፉ መመሪያ ይሰጡዋቸው ነበር። ብጹዕነታቸው በአባትነታቸው የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለተማሪዎቻቸው አድርገዋል።

ብጹዕ አባታችን በዓለም ዙርያ
ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ ካልዕ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ታላቅነትና ማንነት በዓለም ያሳወቁ የቤ/ክ መልዕክተኛ ነበሩ። ብጹዕ አባታችን ከአምስት በላይ የተለያዩ ቋንቋዎች ተሰጥኦና ልዩ ልዩ የንግግር ጸጋ፣ ሰብኮ የማሳመንና ተናግሮ የማሳሰብ ሃብት ስለነበራቸው ቅዱስ ሲኖዶስ በየጊዜው በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎች የኢትዮጵያን ቤ/ክ ወክለው እንዲገኙ በወሰነው መሰረት፦

ግንቦት 7 ቀን 1972 ዓ.ም በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ላይ በደረሰው ችግርና ፈተና የኢትዮጵያ ቤ/ክ ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰማውን ጥልቅ ሃዘንና የቅዱስ ፓትሪያርኩን መልዕክት እንዲያደርሱ ተልከዋል።
ሚያዝያ 20 ቀን 1973 ዓ.ም በሩማንያ በተዘጋጀው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያን ቤ/ክ ወክለው ተገኝተዋል።
ከመስከረም 27 እስከ ጥቅምት 10 1974 ዓ.ም በምዕራብ አውሮፓ በጀርመንና በኦስትርያ በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተ/ሃይማኖት መሪነት በተደረገው ጉብኝት ከተጓዘው ልዑካን መካከል አንዱ ነበሩ።
ታህሳስ 1 ቀን 1978 ዓ.ም በጄኔቫ ላይ በተደረገው የመላው ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ስብሰባ ላይም የኢትዮጵያን ቤ/ክ ወክለው ተሳትፈዋል።
ግንቦት 26 ቀን 1979 ዓ.ም በለንደን ከተማ ባለችው የኢትዮጵያ ቤ/ክ የተከሰተውን ችግር ለማጥናት እና ለመፍታት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንዲሔዱ ተደርጎ ብጹዕነታቸው የአጥቢያ ቤ/ክኒቱ የምትጠናከርበትና የምታድግበትን ሁኔታ ከቅዱስ ሲኖዶስ ደንብና መመሪያ ጋር በማጣጣም ለችግሩ መፍትሔ ሰጥተዋል።
ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት የእምነትና የሥርዓት ጉባኤ ቋሚ አባል ሰለነበሩ ከነሐሴ 1 ቀን እስከ ነሐሴ 15 ቀን 1981 ዓ.ም በጉባኤው ተካፋይ ሆነዋል።
ሐምሌ 16 ቀን 1979 ዕም በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሰረት በፓሪስ በተደረገው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ጥናት ላይ ተገኝተው በእንግሊዘኛ ቋንቋ “የኢትዮጵያ ቤ/ክ ማህበራዊ አገልግሎት ትላንትናና ዛሬ” በሚል ጥናታዊ ጽሁፍ አዘጋጅተው አቅርበዋል።
ከጥቅምት 13 ቀን 1984 ዓ.ም(እኤአ) በኤች ሚዚን በተካሄደው የምስራቅ ኦርቶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ተሳታፊ ሆነዋል።
ሐምሌ 6 ቀን 1990 ዓ.ም ለአለም አብያተ ክርስቲያናት 7ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ለተደረገው አህጉራዊ ዝግጅት ወደ ጋና ተጉዘው ስብሰባውን ተካፍለዋል።
ሞስኮ ውስጥ ዓለም ከኒውክሊየር ስጋት ነጻ እንድትሆን፣ የሰው ዘር ከእልቂት እንዲተርፍ በጦር መሳሪያው ምርት ላይ ማዕቀብ ለመጣል በተካሄደው ዓለም አቀፋዊ ስብሰባ ላይ ተካፋይ ሆነዋል።
በ1979 ዓ.ም በለንደን ከተማ ለምትገኘው ቅድስት ማርያም ቤ/ክ ጃማይካውያን ዲያቆናትን እንዲያሰለጥኑ በቅዱስ ሲኖዶስ በታዘዙት መሰረት በዝዋይ ካህናት ማሰልጠኛ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የኢትዮጵያ ቤ/ክንን ታሪክ እምነትና ትውፊት አስተምረው በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተ/ሃይማኖት አንብሮተ ዕድ ማዕረገ ቅስና እንዲቀበሉ አድርገዋል። ብጹዕ አባታችን ወደተለያዩ የውጭ ሃገራት ለስብሰባ ሲሄዱ በሚሰጣቸው የጉዞ አበል ለራሳቸው የሚሆኑ በርካታ ነገሮችን ይዘው መምጣት ሲችሉ የሚያስጨንቃቸው የቤ/ክና የልጆቻቸው ነገር ብቻ በመሆኑ ከቦስተን የብረት ድስት ገዝተውተሸክመው መምጣታቸውን በተጨማሪም የተለያዩ ምዕመናንን በማስተባበር፣ ከውጭ ሃገር ዕርዳታ በማሰባሰብ ለገዳሙ ተማሪዎች አልባሳት እና መመገቢያ ዕቃዎችን አሰባስበዋል።

የብጹዕ አባታችን የግል ጠባይ
 ብጹዕ አባታችን በደስታ የመፈንደቅ በኅዘን የመቆራመድ ጠባይ የላቸውም። በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ ብዙ ህዝብ ሲቀበላቸው ተሰብስቦ ሲመጣ በማየታቸው ኩራት አይሰማቸውም። ራሳቸውን የገዙ በዓላማ የሚጓዙ ጽኑዕ አባት ነበሩ። ብጹዕነታቸው በደስታ የሚፈነጥዙ አባት ስላልነበሩ ሰወች በዚህን ጊዜ ተደሰቱ በዚህን ጊዜ ተከፉ ብለው በቀላሉ መናገር አይችሉም ነበር። ብጹዕነታቸው በጣም ጨዋታ አዋቂ ናቸው። እንግዶች ሲመጡ “የቀድሞ አባቶች እንዲህ ያደርጉ ነበር፣ እንዲህ ይሉ ነበር።” የሚሉ ወጎችን እያነሱ ሲጫወቱ መጠነኛ ፈገግታ ይታይባቸዋል እንጂ ብዙም አይስቁም ነበር። ዘወትር ተመሳሳይ አባታዊ ገጽታ ይታይባቸው ነበር እንጂ ደስታቸውም ሃዘናቸውም አይታወቅም። ነገር ግን ብጹዕነታቸው በገዳሙ የሚገኙትን ሕጻናትና ተማሪዎች በማግኘታቸው ደስትኛ እንደሆኑ ሲናገሩ ይደመጡ ነበር። ብጹዕ አባታችን ጠላት በዝቶብን፣ ወራሪ ተነስቶብን የሚገባንን ያህል ባለመንቀሳቀሳችን በጣም ያዝኑ እንደነበር ለተማሪዎቻቸው ነግረዋቸዋል። ብጹዕነታቸው የቤ/ክ ጉዞ በዓለም ላይ እንዴት እንደነበረ፣ በውስጥ በአፍዓ የነበረውን ሕይወት በጥልቀት ያውቁ ስለነበር በቤ/ክ ውስጥ የጎደለው ነገር የሚሟላው መቼ ነው በማለት፤ ቤ/ክ ሐዋርያዊት እና ጥንታዊት እንደመሆኗ ክብሯ በዓለም ዙሪያ እንዲታወቅ፣ የእግዚአብሔር መንግስት ወንጌል በዓለም እንዲሰበክ ከነበራቸው ከፍተኛ ጉጉት የተነሳ እንደ ዮሐንስ ፍቁረ እግዚእ በህይወት ዘመናቸው ሙሉ ስለ ቤ/ክ ያዝኑ ነበር። ብጹዕነታቸው ተማሪዎች እንዳሰቡት ትምህርታቸውን ሳይቀበሉ ሲቀሩ ሥርዓተ ቤ/ክ ሲጣስ እንዲሁም ቤ/ክ በቂ አገልግሎት፣ የተዋጣ አመራር የምታገኘው መቼ ነው? እንደቀድሞው በዓለም ዙሪያ ሰፍታ የምትታየው መቼ ነው? እያሉ ዘወትር ያዝኑ ነበር። ብጹዕነታቸው ወደ ውጭ ሃገር ለስብሰባ ሄደው ሲመለሱ በሃይማኖት የማይመስሉን ሰወች በጉልበት የዘረፉንን፣ በስርቆሽ የወሰዱብንን የብራና መጽሐፍት፣ የወርቅና የብር መስቀሎች፣ የተለያዩ አክሊላትና የነገስታት ዘውዶች፣ ቅዱሳት ስዕላትና ታቦታት የራሳቸው እንደሆነ አድርገው በቤተመዘክራቸው አስቀምጠው በታሪካችን ሲነግዱበትና እኛን ሲያስጎበኙን ማየታቸው በጣም አሳዝኖአቸው ይህን ስሜታቸውን በት/ታቸው ገልጠውት ነበር። የብጹዕነታቸው የዘወትር ሃዘን በቤ/ክ ጉዳይ እንጂ በግል ሕይወታቸው “ይህ ቀረብኝ፣ ይኽኛው አነሰኝ፣ አልተመቸኝም ” ከሚል ሃሳብ የመነጨ አልነበረም። ብዙ ጊዜ የሚያውቋቸው ሰወች ብጹዕነታቸው በቤ/ክ በመጣ ነገር፣ በስርዓት መጣስ ሲበሳጩ በቀኝ እጃቸው በያዙት መስቀል የግራ እጃቸውን መዳፍ መታ መታ ያደርጋሉ።” በማለት አልፎ አልፎ ስሜታቸውን መረዳት እንደሚችሉ ይናገራሉ። አንዳንዶች ደግሞ ብጹዕነታቸው “ኃይለኛ ቁጠኛና ጨካኝ” እንደነበሩ የገልጻሉ። በዘመናችን በመቶዎች የሚቆጠሩ ልጆችንና ተማሪዎችን ጠባይዕ ማረቅ አቅቷቸው የሚማረሩ፣ በንዴት ተገቢ ያልሆነ ቅጣት የሚቀጡ ወላጆች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ቤት ይቁጠረው! ልጆችን በአግባብ፣ በሥርዓት ማሳደግ በጣም ከፍተኛ ኃላፊነት ይጠይቃል። ብጹዕነታቸው በገዳሙ የሚገኙትን ህጻናት፣ መደበኛ ተማሪዎች እና ኮርሰኞች ተቆጣጥረው ከመያዛቸው ባሻገር ዛሬ በአራት ሊቃነ ጳጳሳት የሚተዳደረውን የሸዋን ሃገረ ስብከት መንፈሳዊ አገልግሎትና አስተዳደር ይዘው የሚጠበቅባቸውን ሐዋርያዊ ግዴታ እየተወጡ ነበር። ታዲያ በዚህ እጅግ ከባድ ሃላፊነት ውስጥ ሆነው በተወሰነ ዓላማ እንዲጓዝ፣ በሥርዓት እንዲመራ ብዙ ደክመው፣ መክረው ያሳደጉት ተማሪ ድካማቸውንና ልፋታቸውን ሁሉ ገደል ሰዶ በማይሆን ቦታ ሲያገኙት በአባትነታቸው ቢቆጡት፣ ቢቆነጥጡት ምን ክፋት አለው? ቅጣታቸውስ አግባብ አይሆን ይሆን? ልጁን የማይቀጣስ ይኖር ይሆን? አንዳንዶች ብጹዕነታቸው ሰው መሆናቸውን ፈጽመው ሳይዘነጉት አልቀሩም። ብጹዕነታቸው ያ ሁሉ ድካም፣ ልፋት “ነገ ሰው አገኛለሁ” በሚል ተስፋ በዚያ በረሃ መንገላታታቸው፣ ልጆችን ለመመገብ በሰው አይን መገረፍ ውጤት አልባ ሲሆን መቆጣታቸው፣ መበሳጨታቸው ከሰው የተለየ ተፈጥሮ ኖሮዋቸው ይሆን? ጌታም በቤተ መቅደስ የማይገባ ነገር ሲፈጸም በዝምታ አልተመለከተም። ጅራፉን አንሥቶ ሥርዓት አልበኞችን እየገረፈ አስወጥቷል። ደቀ መዛሙርቱም የማይገባ ነገር ሲፈጽሙ ተቆጥቷቸዋል። የብጹዕ አባታችንን ሕይወት ቀረብ ብሎ ለተመለከተ፣ ታሪካቸውን ላጠና ሰው በጣም ሩኅሩኅ፣ ለሰው አዛኝ፣ ሰለሰው ራሳቸውን መስዋዕት አድርገው የሚያቀርቡ አባት እንደሆኑ ያስረዳል። ውሳኔያቸው ሁሉ በገዳሙ የሚገኙት ልጆች እንዳይበላሹ ከመስጋት፣ የልጆቹን ደህንነት ከመጠበቅ አንጻር እንደሆነ ይገነዘባል።

ብጹዕ አባታችን ለፍሬ ያበቋቸው ጳጳሳት
የብጹዕነታቸውን ት/ትና ምክር ሰምተው፣ የዓለምን ደስታ ንቀው ንጽህናንና ድንግልናን ገንዘብ ያደረጉ ወጣቶች በርካታ ናቸው። ብጹዕነታቸውን በእግር ሳይሆን በገቢር ተከትለው ከአጥቢያ ቤ/ክ አስተዳዳሪነት እስከ ሊቀ ጵጵስና የደረሱ ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተዋል። ለአብነትም፦
ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ ራብዕ የምስራቅ ሸዋ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
በቅርቡ ያረፉት ብጹዕ አቡነ መልኬጼዴቅ ካልዕ የከምባታ ሐድያና ጉራጌ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ብጹዕ አቡነ ኤልያስ ሣልስ የወለጋ ሃገረ ስብከት ጳጳስ እና ሌሎችም
የብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ የዝዋይ ፍሬዎች ናቸው።

ብጹዕ አባታችን ለወጣቱ
ወጣቱ ወደ ቤ/ክ እንዴት መቅረብ፣ ማስተማር ማገልገል እንደሚችል እያሰቡ የተለያዩ ዘዴዎችን በመቀየስ፣ ለወጣቱ የሚጠቅም ነገር ለማዘጋጀት ከመጨነቅ፣ “እናንት የሰ/ት/ቤ ተማሪዎች የቤ/ክ የስስት ልጆች፣ የቤ/ክ ችግኞች ናችሁ::” እያሉ ከማበረታታት ሌላ ውዳሴ ከንቱን የሚሹ አባት አልነበሩም:: ውዳሴ ከንቱ ብዙዎችን የሚጥል፣ የሚያደክምና የሚጎዳ ታላቅ ደዌ መሆኑን ስለሚያውቁ ነው።

በ1980 ዓ.ም በምስካየ ኅዙናን መድሃኔአለም ገዳም በተምሮ ማስተማር ሰ/ት/ቤ ለመጀመሪያ ጊዜ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የምረቃ መርሐ ግብር ሲዘጋጅ ከተገኙት ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት አንዱ ብጹዕ አባታችን ነበሩ:: በዕለቱ ብጹዕነታቸው “በዚህ ዘመን እግዚአብሔር አምላካችን ብሎ ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ በቤ/ክ መሰብሰብ ሰማዕትነት ነው።” በማለት ሰፊ ት/ት ሰጥተው ነበር። በ1979 ዓ.ም በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ወደ ዝዋይ ገዳምና ካህናት ማሰልጠኛ ገብተው ለመማር ጠይቀው በጊዜና በሁኔታ አለመመቻቸት ዕድሉን ያላገኙት ተማሪዎች በዕለቱ ጥያቄያቸውን በድጋሚ አነሡ በዚህን ጊዜ ብጹዕነታቸው “እኔ ደስታውን አልችለውም:: የዩኒቨርስቲ ተማሪ ቤ/ክ ልማር ብሎ መጥቶ ነው?! በእርግጥ የማለብሳቸው ልብስ፣ የማበላቸው ጥሩ ምግብ የለኝም:: የማሳርፍበት ቦታም የለኝም:: ግን እዚያ ከማሳድጋቸው ህጻናት የተረፈውንም ቢሆን ንፍሮ ቀቅዬ አበላቸዋለሁ፣ ድንኳን ተክዬም ቢሆን አስተኛቸዋለሁ:: እመጣለሁ ብሎ የሚመጣ ተማሪ ካለ ይምጣ” በማለት መልስ በመስጠታቸው 12 ተማሪዎች ወደ ዝዋይ ገብተው ሊማሩ ችለዋል። በየክረምቱም በህይወተ ስጋ እስከነበሩበት ሐምሌ 1982 ዓ.ም ድረስ በሦስት ጊዜያት 69 የዩኒቨርሲቲና የኮሌጅ ተማሪዎችን በማስተማር ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት አብቅተዋል። ብጹዕ አባታችን ለቤ/ክ ከነበራቸው ታላቅ ፍቅር አኳያ ወጣቶቹን ሰብስበው በሚያስተምሩበት ወቅት ከተለያዩ አቅጣጫዎች ብዙ ፈተና ስለገጠማቸው ወጣቱ ትውልድ ወደ ቤ/ክ ገብቶ ጉልዕ ድርሻ ሲያበረክት እስኪያዩና ያሰቡት እስኪሳካላቸው ድረስ እንቅስቃሴያቸውን ለማንም እንዳይገልጡ ይመክሯቸው ነበር።

ብጹዕ አባታችን የፃፏቸው መጽሐፍት
ብጹዕነታቸው እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘእንዚናዙ ነገረ መለኮትን አብራርተው ባፍ በመጣፍ ያስተማሩ፤ ለነገ የሚጠቅመውን ነገር ሥራ መፍታት በማይወዱት እጆቻቸው ስምንት መጽሐፍትን ያዘጋጁ አባት ነበሩ።

የታተሙ መጽሐፎቻቸው፦
መሠረተ እምነት ለሕጻናት፦ ት/ተ ሃይማኖትን ለማስተማር የተዘጋጀ፤
የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ታሪክ፦ ከዘመነ ብሉይ እስከ አለንበት ጊዜ ድረስ የተጓዘችበትን ሂደት፣ የቤ/ክኒቱን መሠረት እምነትና ትውፊታዊ ሥርዓት እንዲሁም የኢኮሚኒዝምን መሰረተ ሃሳብ የሚያብራራ፤
የቤ/ክ ታሪክ በዓለም መድረክ፦ የቤ/ክ ትርጉምና አመሰራረት ጉዞና መሰናክሎች፣ የተዋህዶ እምነት ከየት መጣ? እና ት/ቱን በሰፊው ያስረዳል።
ሳይታተሙ የቀሩ መጽሐፎቻቸው፦
ሥርዓተ ኖሎት
ነገረ ሃይማኖት
ኦርቶዶክሳዊ የስብከት ዘዴ
የሰ/ት/ቤ መመሪያና
ቤ/ክህን ዕወቅ የተባሉት ናቸው።

የብጹዕ አባታችን አባባሎች

ብጹዕ አባታችን በተለያዩ ርዕሶች ላይ የተናገሯቸው በርካታ ድንቅ አባባሎች ነበሯቸው።
“ስለ እመቤታችን መናገር የምንችለው ስለ ሰው እና ስለ እግዚአብሔር ስናውቅ ብቻ ነው።”
“የቤ/ክ ሕይወት በመስቀል ላይ ስለሆነ ፈተና ይበዛበታል። ስለዚህ ከግል ህይወታችሁ ይልቅ የቤ/ክአችሁን አቋም አጠናክሩ።”
“ሰው ፍላጎቱን ካላሸነፈ የእግዚአብሔር መሆን አይችልም።”
“ሥጋዊ ፍላጎቶችን ማሸነፍ ለአክሊለ ሕይወት የሚያበቃ ሰማዕትነት ነው።”
“ኢትዮጵያ ለእግዚአብሔር የምስጢር ሃገር ናት” በማለት የተናገሯቸውን መጥቀስ ይቻላል።

የብጹዕ አባታችን ድንገተኛ እረፍት
ሐምሌ 22 ቀን 1982 ጠዋት ለቤ/ክ አስደንጋጭ እና እጅግ አሳዛኝ ዕለት ነበር። ብጹዕ አባታችን በዚሁ ቀን ከጠዋቱ 1:30 በመቂ ደብረ አሚን ቅዱስ ጊዮርጊስና በቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ ለሚገኙ ምዕመናን ት/ተ ወንጌል ለመስጠት ሲሄዱ በድንገተኛ የመኪና አደጋ በተወለዱ በ50 ዓመታቸው። እስከ ኅልፈተ ዓለም ላይነቁ አንቀላፉ። ያ በርቀት የተያዘ ዕቅድ በአጭር ተቋጨ፣ ያ ሁሉ እረፍት የሌለው ሩጫ ተገደበ፣ ያ ብሩዕ ሃሳብ በድንገት ከሰመ። ከብጹዕነታቸው ጋር ለአገልግሎት አብረው የነበሩት ዲያቆን ጳውሎስ በቀለና የመኪናው አሽከርካሪ ዲያቆን ኤፍሬም ዘውዴም በደረሰው አደጋ በለጋ ዕድሜያቸው በመንገድ ላይ አለፉ። ሐምሌ 23 1982 ዓ.ም ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፣ ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች ካህናት እና ምዕመናን በተገኙበት በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቤተ መቅደስ ውስጥ ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል።

በብጹዕነታቸው ሳይሰሩ የቀሩ ዕቅዶች
የካህናት ማሰልጠኛ ቁጥር ከፍ በማድረግ ያሉትንም አቅም ወደ ኮሌጅና ዩኒቨርስቲ ደረጃ ማሳደግና ሥርዓተ ት/ት በማዘጋጀት ከየአህጉረ ስብከቱ የሚመጡትን ካህናት በብቃትና በጥራት ማሰልጠን ሚቻልበትን ሁኔታ ያስቡ ነበር::
በዜግነት ኢትዮጵያዊ ሳይሆኑ የኢኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ እምነትና ሥርዓት ተከታይ የሆኑትን የውጭ ዜጎች ነጻ የት/ት ዕድል በመስጠት በዝዋይ ማሰልጠን
ወጣቶችን ከተለያዩ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች በማሰባሰብ ያለምንም ተጨማሪ በጀት አሰልጥነው በማስመረቅ ነገ ቤ/ክንን ያለምንም ክፍያ እንዲያገለግሉ ማዘጋጀት
ከዝዋይ ገዳም በቅርብ ርቀት በሚገኘው በደሴተ ገሊላ የሴቶች ገዳም ለመገደም ከፍተኛ ምኞት ነበራቸው
ለዝዋይ ገዳምና ለከተማ ነዋሪዎች አገልግሎት የሚሰጥ ዳቦ መጋገሪያ ለመስራት እና የጤና ጣቢያ በገዳሙ ለማቋቋም
ለገዳሙ ሕጻናት፣ ዲያቆናትና መነኮሳት ዘመናዊ ት/ት ቤ/ት ማሰራት
ዘመናዊ ት/ት ለተማሩ መነኮሳት የውጭ ሃገር የት/ት ዕድል እንዲያገኙ መርዳት
እና ሌሎችም ቤ/ክንን የሚያሳድጉ ብዙ ዕቅዶች ነበሯቸው።


የአባታችን በረከት ይደርብን!
ዕቅዶቻቸውን የምንፈጽምበትን ሃይልና ጥበቡን ያድለን
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!



ምንጭ፦ Abune Gorgoreyos II አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ (ታላቁ አቡነ ጎርጎርዮስ ኢትዮጵያዊ) FB Page

Tuesday, June 11, 2013

የዘንድሮው ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ውሳኔ ተግባር ላይ ከዋለ ለቤተክርስቲያን አስትዋጾው የጎላ ነው


የቅዱሳን ጳጳሳት ተግባር "በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።"(ሐዋ 20:28)  ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተገለጸው የዘንድሮ ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖደስ ጉባኤ ከመነሻው እስከ ፍጻሜው ይኽን የማሳይና የሚያረጋግጥ ነበር።
ጉባኤው ሲጀመር ፓትርያሪኩ ያነሷቸውን ነጥቦች ስንመለከተ ለዚች ቅድስት ቤተክርስቲያን ችግር ለሚያሳስበው ለሚያንገበግበው እውነተኛ የቤተክርስቲያን ልጅ የዘወትር ጥያቄዎች ነበሩ። ዘመን አመጣሹን(ዘረኝነቱን)ና የተለያዩ ችግሮችን ወደኋላ በመተው ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅማትን የመወያያ አጀንዳ አድርገው ጉባኤውን በመጀመራቸው ቅዱስ ፓትርያሪኩን ልናመሰግናቸው ይገባል። እግዚአብሔር በእርሳቸው ላይ አድሮ ቤተ ክርስትያኗ ከአለችበት ከተለያዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሊታደጋት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።
ቅዱስ ፓትርያሪኩ በዋናነት ያነሷቸው ነጥቦች፦
  1.  መንፈሳዊነትን የለቀቁ/ ብልሹ አሠራርን ማረምና ማስወገድ
  2. አስተዳደሩን በአዲስ መልክ ማዋቀር
  3.  የፋይናንስ አያያዝን ማስተካከል
  4. የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን እንደገና ማዋቀር 
እነዚህ 4ቱም ነጥቦች የቤተ ክርስቲያን መሰረታዊና ቤተ ክርስቲያኗን ወደፊት እንዳትጓዝ ያደረጉ ችግሮች ናቸው። የቤተ ክርቲያኗ የበላይ ጠባቂ ጳጳሳት በእነዚህና ሌሎች ጉልህ ችግሮች ላይ መወያየታቸውና ለችግሮች  መፍትሔ የሚሆኑ ዝርዝር ተግባራትን ማስቀመጣቸው የቤተ ክርስትያንን የነገ ጉዞ ያመላክተናል። ምንም እንኳ የቤተ ክርስቲያን ጉዞ የመስቀል ጉዞ ቢሆንም ውስጣዊ ችግሯን ማስወገድ ግን የአባቶቻችን እና የእያንዳንዳችን ተሳትፎ ጉልህ አስትዋጾ አለው።
ጉባኤው ከብዙ ውይይትና ምክክር በኋላ ለቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ ናቸው ብሎ ያመነበትን ውሳኔዎች ወስኖ መግለጫ ስጥቷል። ከውሳኔዎችም መካከል፦
  • በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የሚታዩ ብልሹ የአስተዳደርና የአሰራር ችግሮችን  እንዲሻሻሉ ማድረግ፤ 
  • ጥራት የጎደለውን የፋይናንስ አያያዝን በተገቢው መልኩ ማስተካከል እንዳለበት፤ 
  • ሙስናንና ለብክነት የተጋለጡ/መንፈሳዊነትን የለቀቁ አሰራሮችን ለመቅረፍ ዓብይ ኮሚቴ ማዋቀርና ችግሮች እንዲቀረፉ ማድረግ
  • የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአንድ ሀገረ ስብከት፤ በአንድ የቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እንዲመራ መድረግ 
  • የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ ምርጫ
  • ከሀገር ውጪ ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር የተጀመረው የሰላም ውይይት ጥረት መቀጠል እንዳለበት 
  • በመካከለኛው ምሥራቅና በሌሎች የዓለም ክፍሎች ለሥራ ፍለጋ በሕገ ወጥ መንገድ በሚሄዱ ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰውን ዘግናኝ ድርጊት ለማስቆም በኹኔታው ጎጂነት ላይ ግንዛቤ የሚፈጥር ትምህርት በስፋት እንዲሰጥ ቅ/ሲኖዶስ ለመምህራን፣ ካህናትና ሰባክያን ሁሉ መመሪያ ሰጥቷል
ይህ ውሳኔ  ተግባራዊ ከሆነ ቤተ ክርስቲያናችን ከመቸውም በበለጠ ተጠቃሚ ትሆናለች። አገራችን ኢትዮጵያም በእድገት ወደፊት ትገሰግሳለች። ምክንያቱም 
  1. ዘመን አመጣሹንና የዘመኑ ፖለቲካ ያመጣውን የዘረኝነት መንፈስ አሶግዳ አገራዊ ስሜት ያለውና በህገ እግዚአብሔር የሚመራ ዜጋ መፍጠር ስለምትችል፤
  2. ከሙስና እና አለማዊነት የተላቀቀ የአሰራር መርህ መዘርጋት ስለምትችል፤
  3. ለ21 ዓመታት በአስተዳድር ጉዳይ የተለያዩት አባቶችና በቅዱስ ሲኖዶስ መዋቅር ስር የማይተዳደሩ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ወደ ቀደምት አንድነታቸው መምጣት ስለሚችሉ፤
  4. በተጠቀሱት ችግሮች  ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን የራቁ ምዕመናን ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መመለስና መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን መቀጠል ስለሚችሉ፤ 
  5. ህዝበ ክርስቲያኑ በሙሉ ከሥጋዊ አስተሳሰቦች ርቆ በመንፈሳዊ ሕይወት እየተጋ ለልማትና ለአገር እድገት መሥራት ስለሚችል ቤተ ክርስቲያናችንና አገራችን በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተጠቃሚ ይሆናሉ።

ቅዱስ ሲኖዶስ ቢያስብበት፦

ቅዱስ ሲኖዶስ በውጭ ሀገር በልዩነት ከሚገኙ አባቶች ጋር የሰላም ውይይት መቀጠል እንዳለበት መወሰኑ  ይበል የማሰኝ ነው።  አባት ልጅን ይፈልጋል፤ ኢየሱስ ክርስቶስ 99ኙን ነገደ መላእክት ትቶ አንድ ልጁን አዳምን ፍለጋ ከሰማየ ሰማያት እንደ ወረደ፤ ለሰሚና ለአጠራር በማይመች መልኩ ቤተ ክርስቲያንን ገለልተኛ ብለው ራሳቸውን ያገለሉ ወገኖቻችንን በቅዱስ ሲኖዶስ ስር እንዲተዳደሩ ያለመሰልቸት በተደጋጋሚ የአንድነት ጥሪ ቢያስተላልፍ መልካም ነው።  

በውጭ ለምትገኙ ብፅዕዋን አባቶች፡

ልዩነቱን ትታችሁ፣ ቅዱሳን አባቶቻችን እንዳስተማሩት በትህትና ራሳችሁን ዝቅ አድርጋችሁ፣ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ስትሉ ይህ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሁሉንም የሚያስማማ ስለሆነ ሰላምና አንድነት የምትፈጥሩበትን ሁኔታ አመቻቹልን። እናንተም ከታሪክ ተወቃሽነት ነጻ ትሆናላችሁ እኛም ልጆቻችሁ ከእናንተ ትህትናንና እርቅን በተግባር እንድንማር አድርጉ።

ገለልተኞች፦

ምንም እንኳ ገለልተኛ የሚለው ትርጉም ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጥና የሚመች ባይሆንም አትፍረዱ ይፈረድባችኋል የሚለውን ቃል በማስታውስ እኔም እንደናንተ ከትችት ራሴን አግልዬ፤ 
ለመገለላችሁ እንደ አንድ ምክንያት ስታቀርቡ የነበረው ብልሹ አስተዳደርን ነበር፤ ዛሬ ግን ቅዱስ ሲኖዶስ በዋናነት የአስተዳደር ችግሩን አጀንዳ አድርጎ  ስለተወያየበትና ውሳኔ ስለሰጠበት ተግባራዊ ይሆን ዘንድ የእናንተም አስትዋጾ በእጅጉ ያስፈልጋል። ስለሆነም ቅዱስ ጳውሎስ "ሁሉም በአግባብና  በስርዓት ይሁን" (1ኛ ቆሮ 14:40) ብሎ እንዳስተማረው እናተም መገለሉን ትታችሁ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ትመሩ ዘንድ የታናሽነት መልእክቴን በእግዚአብሔር ስም ማስተላለፍ እወዳለሁ። መገለል ከክፉ ሥራ፣ መገለል ከተንኮል፣ መገለል ከአለማዊነትና መገለል ከኃጢአት እንጂ ከቅዱስ ሲኖዶስ ሊሆን አይገባምና። 

ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስ በመግለጫው ለቤተ ክርስቲያን ክብርና ሉዓላዊነት መጠበቅ፣ ለህልውናዋ መቀጠልና ለዕድገትዋ መስፋፋት የሚቆረቆሩ የቤተ ክርስቲያናችን አገልጋዮችና ምእመናን በሙሉ ቅ/ሲኖዶስ የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎች ለመተግበር አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ በጠየቀው መሰረት ሁላችንም ውሳኔው ተግባር ላይ እንዲውል ርብርብ ልናደርግ ይገባል።

                                        ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

Saturday, May 25, 2013

መነኰሳትን አይቻለሁ

 ከእለታት አንድ ቀን ጻድቁ አባታችን አባ መቃርዮስ ከግብጽ አስቄጥስ ወደ ኒጥርያ ተራራ አባ ፖምቦን ፈልጎ ሄደ። አባ ፖምብም "አባታችን እስኪ ለመነኰሳቱ የሆነ ቃል በላቸው" አለው። አባ መቃርዮስም "እኔ ራሴ ገና መነኩሴ አልሆንኩም ነገር ግን መነኰሳትን አይቻለው" አለ። ያየውንም እንዲህ በማለት ነገራቸው፦ "ብቻዬን በበኣቴ ውስጥ ተቀምጨ እያለሁ ባለሁበት በርሃ ውስጥ ማን እንዳለ ለማወቅ በማሰብ ወደ በርሃ እንድሄድ ሃሳቤ አስቸገረኝ። እኔም ይህ ሃሳብ ከአጋንንት የመጣ ጸብአ ፍልሰት/ከብኣቴ ሊያስወጣኝ/ እንዳይሆን ብዬ በመስጋት ለአምስት ዓመት ያህል ከዚያ ከሚያስቸግረኝ ሃሳብ ጋር ስታገል ቆየሁ። ነገር ግንነገሩ ከእግዚአብሔር እንደሆነ ስረዳ ወደ ውስጠኛው በርሃ ለመሄድ ከበኣቴ ወጣሁ። አርባ ቀናት ተጉዤ ወደውስጠኛው በርሃ ደርሼ ጸሎት ካደረስኩ በኋላ ስኳዝ ከአንድ ወንዝ አጠገብ ደረስኩ።
ከዚያም ከመካከሉ ደሴት አለውና ጥቂት ውኃ አገኘሁ። የበርሃ አራዊቱም ወደዚያ በመምጣት ይጠጣሉ። ውኃ ሊጠጡ ከሚመጡት አራዊት መካከልም ሁለት እርቃናቸውን የሆኑ፣ ሰውነታቸው በጣም የከሳና ፀጉራቸው የረዘመ፣ የእጅና የእግር ጥፍራቸው እንደ እንስሳት በጣም የረዘመ ሰዎች አየሁና ታላቅ ፍርሃትን ፈራሁ፤ ሰውነቴም ተንቀጠቀጠ፣ እነርሱ መናፍስት ናቸው ብዬ ነበርና። ነገር ግን እኔን ባዩኝ ጊዜ ተንቀሳቀሱ፣ እነርሱም በስሜ ጠርተው እንዲህም አሉኝ።
  • "መቃሪ ሆይ! አትፍራ እኛም እንደ አንተ ሰዎች ነን። ወደዚህ እንዴት መጣህ? ከዚህስ ምን ትሰራለህ?" አሉኝ።
  • እኔም የፈለግኩትን ከእኔ ያላራቀ እግዚአብሔር እውነተኛ ቅዱሳን የሆናችሁትን አያችሁ ዘንድ ፈቀደልኝ። በረከታቸው ትድረሰኝ አልኩና ቀርቤ ዳሰስኳቸው፣ መንፈስ እንዳይሆኑ ብዬ ሰግቼ ነበርና። እኔም በበርሃ የሚኖሩ ቅዱሳንእንደሆኑ ባወቅሁ ጊዜ ወደ እርሳቸው ቀርቤ እጅ ነሣኋቸው፣ እነርሱም ባረኩኝ፣ ብዙ ነገርም ነገሩኝ። በዚህ በርሃ ከመጣን ጀምሮ ከአንተ በቀር ከአንድም ሰው ጋር ተገናኝተን አናውቅም አሉኝ። 
  • እኔም "ከየት መጣችሁ? ከዚህ በርሃስ እንዴት መጣችሁ?" አልኳቸው።
  • እነርሱም እንዲህ አሉኝ፦ የመጣነው ከገዳም ነው፣ ሁለታችንም ተስማምተን ከዚህ ከመጣን አርባ አመታችን ነው። አንዳችን ግብጻዊ ስንሆን ሌላችን ሊቢያዊ ነን" አሉኝ። " ዓለም እንዴት ናት?? ዝናብ በወቅቱ ይዘንባልን ብለው ጠየቁኝ።
  • እኔም የጠየቁኝን መለስኩላቸውና እንዴት መነኩሴ መሆን እችላለሁ? ብዬ ጠየቅኋቸው።
  • እነርሱም "በዓለም ያሉትን ነገሮች በሙሉ ካላቆምክ መነኩሴ መሆን አትችልም" አሉኝ።
  • እኔም እኔ ደካማ ነኝ፣ እናንተ እንደምትሠሩት ልሰራ አልችልም አልኳቸው።
  • እነርሱም "እንደኛ መሆን ካልቻልክ በበኣትህ ተቀመጥና ስለ ኃጢያትህ  አልቅስ" አሉኝ።
  • እኔም ክረምት ሲመጣ አይበርዳችሁምን? በጋስ ሲሆን ሙቀቱ ሰውነታችሁን አያቃጥለውምን? አልኳቸው። 
  • እነርሱም "ይህን ዓይነት አኗኗር እግዚአብሔር ለእኛ አዘጋጀልን፣ ክረምት ሲመጣ አይበርደንም፣ በጋ ሲሆንም ሙቀቱ አይ ጎዳንም" አሉኝ።
ከዚህም የተነሣ አባ መቃርዮስ "እኔ መነኰሴ አይቼ መጣሁ እንጂ ገና መነኰሴ አልሆንኩም" አለ። ዛሬ ስንቶች ናቸው የአባታችን የአባ መቃርስ ትህትና፣ ትዕግስት፣ ማስተዋል፣ ራስን መግዛትና ጸጋቸውን መለየት ተስኗቸው/ረስተው ያልሆኑትንና ያልነበሩበትን ሲሰብኩና ሲናገሩ የምንሰማቸው? ስንቶች ናቸው የተቀደሰውን ገዳማዊ ሕይወት ሲያራክሱ የምንሰማቸው? የቀደሙት አባቶቻችን ግን የመንፈስ ፍሬን ገንዘብ አድርገው፣ የሆኑትን እንኳ በትህትና እራሳቸውን ዝቅ አድርገው እኛ ኃጢያተኛ ነን፣ አልበቃንም፣ መንፈስን መለየት ይገባናል እያሉ ነበር ይችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያስረከቡን። እኛም ዛሬ እንደ አባታችን አይቻለሁ እንጂ እኔ አይደለሁም እያልን ለመሆን ትጋቱንና ብርታቱን ያድለን ዘንድ አምላከ ቅዱስ መቃርስን  በጸሎት እንማጸነው።

የጻድቁ አባታችን ጸሎቱ፣ ረድኤቱና አማላጅነቱ አይለየን፡ አሜን።

Wednesday, May 15, 2013

የፌድራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖት ተቋማትን ለመመዝገብ ያወጣው ረቂቅ መመሪያ

አንብቡና የራሳችሁን አስተያየት ስጡበት

ይህን መመሪያ ስመለከት በ2000 ዓም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሃይማኖት ጉዳይ የወጣውን መመሪያ እንዳስታውስ አደረገኝ። በዚያን ወቅት ማንኛውም ሃይማኖትን ሊገልጹ የሚችሉ ነገሮችን የሚቃወም ስለነበር  የከፍተኛ ት/ት ተቋማት  ተማሪዎችን በእጅጉ ያሳዘነ፣ ያስቆጣና እምነትንም የሚፃረር  እንደነበር አስታውሳለሁ። 






Friday, May 3, 2013

ዕለተ ዓርብ/ስቅለት


ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ «አውቀውስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት» /1ቆሮ.1-18/፡፡ እንዳለ ይህ ዕለት የአይሁድ ካህናት ያለበደል ያለጥፋት ንጹሕና ጻድቅ የሆነውን ጌታ የሰቀሉበት ዕለት ነው፡፡ ዕለቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ሁሉ መድኃኒት ለአዳምና ለልጆቹ ሲል በመልእልተ መስቀል በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ መዋሉን የምናስብበት ታላቅ ቀን ነው፡፡ /ማቴ.27-35-75/፡፡ በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ፡፡ እነርሱ ግን እኛስ ምን አግዶን? አንተው ተጠንቀቅ አሉ፡፡ ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሔደና ታንቆ ሞተ፡፡ የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም አሉ፡፡ ተማክረውም የሸክላ ሠሪ መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት፡፡ ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተባለ፡፡ /ማቴ.27-3-9/
የሰው ልጆች በዘር ኃጢአት /ቁራኝነት/ ይኖሩበት የነበረው የጨለማ ሕይወት ያከተመበት ፍጹም ድኅነት ያገኙባት ታላቅ ዕለት ናት፡፡ ክርስቲያኖች ሁልጊዜም ዕለተ ዓርብ ሲመጣ ሕማሙን ስቅለቱን ሞቱን የሚያስቡበት ጊዜ ነው፡፡ በሮማውያን ሕግና ሥርዓት መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የሕይወት መቅጫ አርማ ሆኖ ሳለ ለእኛ የዲያብሎስ ድል መንሻ ስላደረገው በስቅለቱና በሞቱም ሕይወትን ስለአገኘን በዚህም ምክንያት መልካሙ ዓርብ በመባል እንደሚታወቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያትታሉ፡፡
በመስቀል ላይ ሳለ 7 ነገሮችን ተናገረ/7ቱ "አጽርሐ መስቀል" በመባል ይታወቃሉ። እነሱም፦
" አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ" ማቴ 17፦46
" አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው" ሉቃ 23፦34
" ዛሬ በገነት ከኔ ጋር እንድትኖር በእውነት እነግርሀለሁ" ሉቃ 23፦4
" አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ" ሉቃ 23፦ 46
" እነሆ ልጅሽ እነኋት እናትህ" ዮሐ 19፦26
" ተጠማሁ" ዮሐ 19፦28
" ሁሉ ተፈጸመ " ዮሐ 19፦ 30
ጌታ ሁሉ ተፈጸመ ብሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ስጋው በራሱፈቃድ ከለየ በኋላ አምላክነቱን ለመግለፅ የታዩ ተአምራት የሚከተሉት ናቸው፤

በሰማይ፤ /ማቴ 24፦29 እና 27፦45/
1. ፀሐይ ጨለመች
2. ጨረቃ ደም ሆነች
3. ከዋክብት ረገፉ

በምድር፤/ማቴ 27፦51_53/
1. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይእስከ ታች ተቀደደ
2. ምድር ተናወጠች
3. መቃብሮች ተከፈቱ
4. ሙታን ተነሱ


ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ክንዋኔዎች በሰሙነ ሕማማት
በዐቢይ ጾም ከሠርክ ሆሣዕና ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ዕለታት የሚገኙበት ሳምንታት ሰሙነ ሕማማት ይባላሉ፡፡ ዕለታቱም የዓመተ ፍዳ፣ የዓመተ ኩነኔ መታሰቢያ ናቸው፡፡ በእነዚህ ዕለታት ውስጥ የተለያዩ ትውፊታዊ እና ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች አሉ፡፡ ከነዚህ ክንዋኔዎች ውስጥ አለ መሳሳም፣ አክፍሎት፣ ቄጤማ ማሰር፣ ጥብጣብ፣ ጉልባን እና ሕጽበተ እግር ይገኙበታል፡፡ ስለእነዚህ ክንዋኔዎች በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስላለው ትውፊታዊ አፈጻጸም መዛግብት አገላብጠን እና በኢትዮጵያ ኣርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ አባል የሆኑትን ሊቀ ካህሃት ክንፈ ገብርኤል አልታዬን አነጋግረን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
አለመሳሳም
በሰሙነ ሕማማት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች መስቀል እንደማይሳለሙት ሁሉ መጨባበጥ፣ መሳሳምና የትከሻ ሰላምታ መለዋወጠን አይፈጽሙም፡፡ ሰላምታ የማንለዋወጥበት ምክንያት፣ አይሁድ ጌታን ለመስቀል ሰኞ እና ማክሰኞ መከሩ አልሠመረላቸውም፡፡ ምክራቸው የተፈጸመው ረቡዕ ነው፡፡
ስለዚህ አይሁድ አያንሾካሾኩ “እንስቀለው… አንግደለው” ብለው ይማከሩ ነበር፡፡ ያነን ለማስታወስ ሰላምታ አንለዋወጥም፡፡ መስቀልም አንሳለምም፡፡ ሳምንቱ የክፋት ምክር የተመከረበት እንጂ የፍቅርና የደስታ ሰላምታ የታየበት ባለመሆኑ ይህንን በማሰብ ሰላምታ አንለዋወጥም፡፡
ይሁዳ ጌታን በጠላቶቹ ለማስያዝ “እኔ የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት” ብሎ በሰላምታው ምልክት ሰጣቸው ይህ ሰላምታ አምሐ ቅድሳት አይደለም፤ ተንኮል የተሞላበት እንጂ፡፡ የዲያቢሎስም ሰላምታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሔዋንን “ሰላም ለኪ” ብሎ ነው ያታለላት፣ የዲያቢሎስ እና የይሁዳ ሰላምታ ሰይጣናዊ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ወቅትና ሁኔታ ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ሰላምታ ልውውጥ የለም፡፡ ዛሬ እየተስተዋለ ያለው ይኸው ሰላምታ ያለመለዋወጥ ሁኔታ ሥርወ መሠረቱ ይህ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ እዚህ ትውልድ ላይ ደርሷል ይቀጥላልም፡፡

ሕጽበተ እግር
ጌታ በፍጹም ትሕትና የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበት፣ ከሐዋርያት ጋር ግብር የገባበትና የክርስትና ሕይወት ማሕተም የሆነውን ምሥጢረ ቁርባን ያከናወነበት ዕለት ነው ጸሎተ ሐሙስ፡፡
ሕጽበተ እግር ጌታችን በዚህ ዕለት “አናንተ ለወንድማችሁ አንዲህ አድርጉ” ለማለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ምክንያት የተሰጠ ምሳሌ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው “አኔ ለአናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና፤ እውነት እውነት እላችኋለሁ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም፣ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም፤ ይህን ብታውቁ ብታደርጉትም ብፁዓን ናቸሁ” /ዮሐ.13÷16-17/ በማለት ትሕትናውን አሳይቷል፡፡
ጌታ በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር ሲያጥብ “እኔ መምህራችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኳችሁ አርአያዬን ሰጥቻችኋለሁ፤ እናንተም የወንድማችሁን እግር ታጥቡ ዘንድ ይገባል፡፡ ነገር ግን ከእናንተ አንዱ ለሞት አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም “ማን ይሆን?” አሉ፡፡ ጌታም “ኅብስት ቆርሼ፣ ከወጡ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው” አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ደነገጡ፡፡ ይሁዳን ማመልከቱ ደነገጡ፡፡ ይሁደን ማመልከቱ ነበር፤ ለጊዜው አልገባቸውም፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን የሐዋርያቱን እግር በማጠብ ትሕትናን ካስተማራቸው በኋላ፤ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሰጣቸው፤ የኦሪትን መሥዋዕት የሻረው እና መሥዋዕተ ሐዲስን የሠራው በዚሁ ዕለት ነው፡፡
በዚህ ሃይማኖታዊ መነሻነትም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚከናወኑ ድርጊቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- በወሎና በጎንደር ከጉልባን በተጨማሪ በተለይ በጸሎተ ሐሙስ ዕለት ብቻ የሚጋገር የተለየ ዳቦ አለ፡፡ ይህ ልዩ ዳቦ በወሎ “ትኩሴ” በጎንደር ደግሞ “ሙጌራ” ይባላል፡፡ ይህ ዳቦ ጌታ ለሐዋርያት የሰጣቸው ኅብስት አምሳያ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ከዚህ ቀን ውጪ በሌላ ጊዜ አይጋገርም፡፡ በመሆኑም ሰው ሁሉ ዳቦውን ለመብላት የሚጠባበቀው በታላቅ ጉጉት ነው፡፡ አልፎ አልፎ ግን ሃይማኖታዊ ሥርዓት በሚከበርባቸው እንደ ማኅበርና ሰንበቴ በመሳሰሉት መንፈሳዊና ማኅበራዊ ትውፊቶች የሚቀርብበት ጊዜ አለ፡፡
በትግራይ በዕለተ ስቅለት ከተለመደው የጾምና የስግደት ሥርዓት በተጨማሪ የሚከናወኑ ድርጊቶች አሉ፡፡ በዕለቱ ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት መታሰቢያ ሲባል ወንዶች ልጆች በሙሉ ፀጉራቸውን እንዲላጩ ይደረጋል፡፡ ያን ቀን ያልተላጨ ልጅ “ኃጢአት ይሆንበታል” ስለሚባል ሳይላጭ የሚውል ልጅ የለም። ልጃገረዶች በበኩላቸው በዛፍ ላይ ገመድ በማሰር ዥዋዥዌ ይጫወታሉ፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት የጌታን እንግልትና መስቀል ለማዘከር ነው ይባላል፡፡
እነሆ ይህንን ዕለት በማስታወስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሐዶ ቤተ ክርስቲያን ከሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ እስከ ቀሳውስት ያሉት አባቶች በያሉበት አጥቢያ /ደብር/ በመገኘት በመዓርግ የሚያንሷቸውን የካህናት፣ ዲያቆናት እና የምእመናንን እግር ያጥባሉ፤ የሚያጥቡትም የወይራ እና የወይን ቅጠል በመዘፍዘፍ ነው፡፡

አክፍሎት
በሰሙነ ሕማማት ዕለተ ዓርብ ከስግደት በኋላ ምእመናን በየቤታቸው ጥቂት ነገር ለቁመተ ሥጋ ቀምሰው እስከ እሑድ /የትንሣኤ ሰዓት/ ይሰነብታሉ፡፡ ይህ አክፍሎት ይባላል፡፡ ብዙው ምዕመን ከዓርብ ጀምሮ የሚያከፍል ሲሆን አንዳንዶች ግን ከሐሙስ ጀምረው ያከፍላሉ፡፡ ይህም እመቤታችን፣ ያዕቆብ እና ዮሐንስ የጌታን ትንሣኤ ሳናይ እህል ውኃ አንቀምስም ብለው እስከ ትንሣኤ መቆየታቸውን ተከትሎ የመጣ ትውፊት ነው፡፡
ይህንን ትውፊት አስመልክቶ ሄሬኔዎስ፣ አውሳብዮስ የተባሉ ጸሐፍት፤ ሐዋርያት በሰሙነ ሕማማት ከደረቅ ዳቦ አና ከትንሽ ውኃ በቀር እንደማይመገቡ እና ከሐሙስ ጀምረው እንደሚያከፍሉ ጽፈዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሐዋርያት ሌሎቹንም እንዲያከፍሉ እንዳሳሰቡና ከሐሙስ ጀምሮ ያልተቻለው ቢያንስ ከዓርብ ጀምሮ እንዲያከፍል ማዘዛቸውን ጽፈዋል፡፡ የእኛ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትም ይኸው ነው፡፡ ቅዳሜ ይበላል ማለት ግን ቅዳሴው ሌሊት ስለሆነ በልቶ ማስቀደስ ነውና በልቶ እንደመቁረብ ይቆጠራል፡፡

ጉልባን እና ቄጤማ
ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚባላ ንፍሮ ነው፡፡ የጉልባን ትውፊት እስራኤላውያን ከግብፅ ተሰደው በሚወጡበት ጊዜ በችኮላ ስለነበር፤ አቡክተው ጋግረው መብላት ያለመቻላቸውን ሁኔታ ያመለክታል፡፡ ያን ጊዜ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መብላት፤ ንፍሮም ቀቅለው ስንቅ መያዝ ተግባራቸው ነበር፡፡ ይህን ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ቂጣና ጉልባን በማዘጋጀት በዓሉ ይታሰባል፡፡
በጸሎተ ሐሙስ ይህንን መሠረት በማድረግ የሚዘጋጀው ጉልባን አንዲህም ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ጨው ውኃ የሚያስጠማ በመሆኑ የጌታን መጠማት ያስታውሳል፡፡ ይህ ትውፊታዊ ሥርዓት ከእስራኤላውያን የመጣ ሲሆን በኢትዮጵያም አብዛኛዎቹ የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ሥርዓቱ ዛሬም ይከበራል፡፡
ጥብጣብ
በሰሙነ ሕማማት ዕለተ ዓርብ የስቅለቱ መታሰቢያ ነው፡፡ ምእመናኑ በሰሙነ ሕማማት የሠሩትን ይናዘዛሉ፡፡ ካህናቱም በወይራ ቅጠል ትከሻቸወን እየጠበጠቡ ቀን ከሰገዱት ስግደት በተጨማሪ ሌላ ስግደት ያዟቸዋል፡፡ ጥብጠባው የተግሳፅ ምሳሌ ነው፡፡ ጥብጣብ የሚደረግለት ሰው በሕማማቱ ወቅት የፈጸመው በደል ወይንም ኃጢአት ካለ ይህንኑ በመናገር የስግደቱ ቁጥር ከፍ እንዲል ይደረጋል፡፡
ይህ በስቅለት ቀን የሚፈጸም ሥነ ሥርዓት ሲሆን፤ ጠብጣቤ ማለት ቸብ ቸብ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዕለተ ስቅለት ሲሰግድ ሲጸልይ፣ ሲያነብ ከዋለ በኋላ ሰርሆተ ሕዝብ /የሕዝብ መሰነባበቻ/ ከመሆኑ በፊት፤ በወይራ ቅጠል እያንዳንዱን ምእመን ጀርባ ቸብ ቸብ መደረጉ፣ የጌታን ግርፋት ያስታውሳል፡፡

ቀጤማ
በቀዳም ስዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለ ዓዋዲ/ እየመቱ “ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሃደ” የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር፤ ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደሰጠን እና ትንሣኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር፤ ቀጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመናኑም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ፡፡ ቀጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ የደፉበትን ድርጊት የሚያስታውስ ነው፡፡
በዚህ ዕለት ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲያቆናት ቀጤማ ተሸክመው ቃጭል ሲያቃጭሉ መታየታቸው ዕለተ ትንሣኤውን ለሚናፍቅ ምእመን ትልቅ ብስራት ነው፡፡

                                    ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ እግዚአብሔር በሰላም!
(ምንጭ፦ ስምዐ ጽድቅ ልዩ እትም ዘሰሙነ ሕማማት መጋቢት 2002/ከማኅበረ ቅዱሳን ድኅረ ገጽ )

Thursday, May 2, 2013

ዕለተ ሐሙስ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዕለት ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ለመግለጥ እና ለአርአያነት ጸሐፍት ፈሪሳውያን የአይሁድ ካህናት መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ጸሎተ ሐሙስ በመባል ይታወቃል፡፡ ትሕትና ፍቅር መታዘዝ እንዲሁም የአገልግሎትን ትርጉም ለማስረዳትና ለማስገንዘብ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ሕጽበተ ሐሙስ በመባልም እንደሚጠራ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይናገራሉ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም  «እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ እንዲህም አላቸው ያደረግሁላችሁን ታስተውሉታላችሁን?... እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ እናንተ ደግሞ እርስ በእርሳችሁ ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል ሲል ተናግሯል፡፡ /ዮሐ.13-12-20/፡፡

ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱ ጠጡ በማለት ምሥጢረ ቁርባንን የመሠረተበት ወይም ራሱ ምስጢረ ቁርባንን የጀመረበት ቀን በመሆኑ የምስጢር ቀን ተብሎ ይጠራል፡፡ ይኸውም የሰው ልጆች ሥጋውንና ደሙን ተቀብለን ከእርሱ ጋር አንድነትና ኅብረት እንዲኖረን ጥንተ ጠላት ዲለብሎስንም ፍጹም ድል ነሥተን ሰማያዊት ርስት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ለማስቻል ነው፡፡ /ማቴ.26-26-29/፡፡ የሚለምን ሥጋን የተዋሐደው አምላክ ፍፁም ሰውም መሆኑን ለመግለፅና ለአርያነት በጌቴ ሰማኒ ጸሎት አደረገ። ዕለቱ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ስለሆነ የነፃነት ሐሙስም ይባላል።

አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ በእነርሱ ጥበብና ፍላጐት ቀስ ብለው መጥተው የያዙበት ቀን ስለሆነ በዚህ ዕለት በለሆሳስ /ብዙ የድምጽ ጩኸት ሳይሰማ/ የቅዳሴ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡ ስለሆነም መላው ሕዝበ ክርስቲያን በዚህ የሕጽበት፣ የምስጢር፣ የጸሎት ቀን በተባለው በዚህ ዕለት በንስሓ ታጥበው ሥጋ ወደሙ እንዲቀበሉ ቤተ ክርስቲያን በአጽንኦት ታስተምራለች፡፡

Wednesday, May 1, 2013

ሰሙነ ሕማማት(ዘረቡዕ)

          በመምህር ኃይለማርያም ላቀው/በማኅበረ ቅዱሳን መካነ ድር ላይ የወጣ
 
በቅዱስ ማቴዎስና በቅዱስ ማርቆስ አዘጋገብ መሠረት ሦስት ነገሮች በዕለተ ረቡዕ ተደርገዋል፤ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡

1. የካህናት አለቆች÷ የሕዝብ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ፈሪሳውያን በጌታችን ላይ ተማክረዋል፤
2. ጌታችን በስምዖን ዘለምጽ ቤት ሳለ አንዲት የተጸጸተች ሴት ሽቱ ቀብታዋለች፡፡
3. ከዳተኛው ይሁዳ ጌታችንን አሳልፎ ለመስጠት ከጸሐፍት ፈሪሳውያንና ከካህናት አለቆች ዘንድ 30 ብር ተመዝኖለታል፡፡
የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሹማምንት በጌታችን ላይ ይሙት በቃ ለመወሰን የሰበሰቡት ሸንጐ “ሲኒሃ ድርየም” ይባላል፡፡ በዚህ ሸንጐ ላይ በአብዛኛው የተሰየሙት ሰዱቃውያን ሲሆኑ የተቀሩቱ ደግሞ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ነበሩ፡፡ ሸንጐው በአጠቃላይ 72 አባላት የነበሩት ሲሆን የሚመራው በሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ነበር፡፡
በዕለቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት ይዘው እንደ ሚገድሉት መክረዋል፡፡ ከዳተኛው ይሁዳ በጸሐፍት ፈሪሳውያንና በካህናት አለቆች ዘንድ ይጉላላ የነበረውን ጥላቻ ያውቁ ስለነበር “ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ” በማለት ጌታችን አሳልፎ ሊሰጣቸው እንደሚችል ተዋውሏል፡፡ የአስቆሮቱ ይሁዳ ጌታችን ያስተምር በነበረበት ወቅት ከተለያዩ ሰዎች የሚገባውን ገንዘብ ሰብሳቢ /ዐቃቤ ንዋይ/ ነበር፡፡ ከሚሰበሰበው ሙዳየ ምጽዋት ለግል ጥቅሙ እየቀረጠ የማስቀረት የእጅ አመል ነበረበት፡፡ ይሁዳ ፍቅረ ንዋይ እንደሚያጠቃው ድብቅ አመሉ ጎልቶ የወጣው ጌታችን በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው ውድ የሆነ ሽቱ በቀባችው ጊዜ ይሁዳ የተቃውሞ ድምፅ ካሰሙት አንዱ ነበር፡፡ “ይህ ሽቱ ተሽጦ ለድሆች ቢሰጥ መልካም ነበር” በማለት ያቀረበው ሐሳብ “አዛኝ መሳይ ቅቤ አንጓች” እንደ ሚባለው ነበር፡፡ ሽቱ ሲሸጥ የሚያገኘው ጥቅም አለ፤ ሽቶ ከፈሰሰ የሚተርፈው የለም፡፡ ይህ በመሆኑ ተቆርቋሪ መስሎ ያቀረበው ሐሳብ ተቀባይነት ስላጣ ማኩረፊያ ያገኘ መስሎት በቀጥታ ከካህናት አለቆች ዘንድ ሄዶ ተዋዋለ፡፡ ብር 30 ተመዘነለት፡፡ ይህ አሳዛኝ ታሪክ በሦስቱ ወንጌላት ውስጥ በሚከተሉት ጥቅሶች ቀጽፎ እናገኛለን፡፡ ማቴ.26÷3-16፤ ማር.14÷1-11፤ ሉቃ.22÷1-6 ይመልከቱ፡፡
የአስቆሮቱ ይሁዳ እንደ ሌሎች ሐዋርያት ከጌታችን እግር ስር ተምሯል፡፡ በረከተ ኅብስቱን ተመግቧል፡፡ የተለያዩ ገቢረ ተአምራት በጌታችን እጅ ሲደረጉ ሁሉ ተመልክቷል፡፡ ጌታችንም ከሌሎቹ ሁሉ ሳይለየው እግሩን አጥቦታል፤ ከዳተኛው ይሁዳ ግን ለሐዋርያነት የጠራውን ተንበርክኮ እግሩን ያጠበውን ጌታውን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ “የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል÷ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት እንደ ተባለ፡፡” ማቴ.26÷24፡፡ ሌሎች ሐዋርያት ከጌታችን ዘንድ ፍቅሩን ገንዘብ ሲያደርጉ ይሁዳ ግን እርግማንን ነው ያተረፈው፡፡ “ገንዘብ የኃጢአት ስር ነው” ተብሎ አንደ ተነገረ ይህ የኃጢአት ስር የክርስቲያኖችን ሕይወት ሊያደርቅ ስለሚችል ለገንዘብ ያለን ፍቅር በልኩ ሊሆን ይገባል፡፡ ሰው ይህን ህልም ቢያተርፍ ነፍሱን ከጐዳ ምን ይጠቅመዋል ተብሎ የተነገረውን ቃል ልብ ማለት ጠቃሚ ነው፡፡
ክርስቲያን ነን በማለት የክርስትናውን ስም በመያዝ እምነታቸውን፣ የቆሙበትን ዓላማ በመገንዘብ የሚለውጡ ሰዎች ዛሬም እንደ ይሁዳ ጌታችንን እየሸጡት እንደሆነ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ለድሆች መመጽወት ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ ዳሩ ግን በድሆች ስም የሰውን ገንዘብ ለግል ጥቅም ማዋል እጅግ የከፋ ኃጢአት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ለገንዘብ ብለው ድሆችን ለረሃብ ለችግር ባልንጀራቸውን ለመከራ እና ለሞት አሳልፈው ሲሰጡ ምንም አይጸጽታቸውም፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን ሕይወታችንን ለገንዘብ ፍቅር ሳይሆን ለእምነታችንና ለባልንጀራችን አሳልፈን መስጠት ይኖርብናል፡፡ በፍቅረ ንዋይ ተጠምደን ሰዎችን አሳልፎ በመስጠት ለአይሁዳዊ ሸንጐ ምቹ ሆነን መገኘት እንደሌለብን መገንዘብ አለብን፡፡

                              ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ እግዚአብሔር በሰላም

Tuesday, April 30, 2013

ሰሙነ ሕማማት (ዘሰሉስ)

ማክሰኞ
ይህ ቀን ጌታችን ሰኞ በተናገረውና ባደረገው ላይ አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት እርሱም መልስ በመስጠት ያስተማረበት ዕለት ነው። በዚህም ምክንያት የጥያቄ እና የትምህርት ቀን በመባል ይታወቃል፡፡ በቅዱስ ማቴዎስ፣ በቅዱስ ማርቆስና በቅዱስ ሉቃስ አዘጋገብ መሠረት ስድስት ነገሮች በዕለተ ሰሉስ/ማክሰኞ ተደርገዋል።
እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡
  1. በማለዳ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ደቀ መዛሙርቱ ጌታ ሰኞ የረገማትን በለስ አይተው ሲደነቁ ስለ እምነት ትምህርት ሰጣቸው። /ማቴ 21፡ 20-22፣ ማር 11፡20-26/
  2.  ወደ ኢየሩሳሌም ገብቶ በመቅደስ ሲመላለስ ለቀረበለት የተለያዩ ጥያቄዎች መልስ ሰጠ። /ማቴ 21፡23-27፣ ማር 11፡25፣ ሉቃ 20፡1-40/
  3. ጌታችን መድኃኒታች ኢየሱስ ስክርስቶ ስለራሱ ማንነት ጠየቋቸው መልስ አሳጣቸው። /ማቴ 22፡41-46፣ ማር 12፡35-37፣ ሉቃ 20-41-44/
  4. ፈሪሳውያንን በግብዝነታቸው ምክንያት ገሰፃቸው። /ማቴ 23፡1-39፣ ማር 12፡38-40፣ ሉቃ 20፡45-47/
  5. የድኃዋን መበለት ስጦታ አደነቀ። /ማር 12፡41-44፣ ሉቃ 21፡1-4/
  6. ስለ ዳግም ምፅአት ሠፊ ትምህርት ትምህርት አስተምሯል። /ማቴ 24፡1-25፣ ማር 13፡1-25፣ ሉቃ 21፡5-36/
በዚህ ዕለት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱሱ ክርስቶስ ስለ ሥልጣኑ ተጠይቋል፡፡ ጠያቂዎቹ የካህናት አለቆችና የሕዝብ አለቆች ናቸው፡፡ ጥያቄውም “በማን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን የሰጠህ ማነው?” የሚል ነበር፡፡ የካህናት አለቆች ያቀረቡት ጥያቄ ነበር፡፡ ጌታችን ሰኞ ዕለት ሁለት ነገሮችን ማድረጉን ተያይዞ የተነሣ ጥያቄ ነው፡፡ ሰኞ ከቅጠል ብቻ በቀር ፍሬ ያላገኘባትን ዕፀ በለስ ረግሟል፤ በማስከተል ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን አስወጥቷል፡፡ ማቴ.21÷23-25፤ ማር.11÷27፣ ሉቃ.20÷1-8፡፡ ከላይ እንደ ተገለጸው ጌታችን ሲያደርጋቸው የነበሩት ተአምራትና የኃይል ሥራዎች የካህናት አለቆችን ስላስቀናቸው ጌታችንን ከሮማ መንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር ለማጋጨት የቀየሱት ስልት ነው፡፡
ጌታችን በቤተ መቅደስ የነበሩትን ነጋዴዎችን አባሯል፤ መደባቸውን ገለባብጧል፡፡ ነጋዴን ማባረርና መደብን ማስለቀቅ መንግሥታዊ ሥራ ነው፡፡ በአንድ አገር የንግድ ቦታን የሚያጸድቅ መንግሥት መሆኑ እሙን ነው፡፡ ጌታችን ፈሪሳውያን ላቀረቡት ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ አልመለሰም፡፡ ምክንያቱም ጥያቄው ለከሳሾቹ አመቺ ሁኔታን ስለሚፈጥር ጥያቄውን በጥያቄ መልሷል፡፡ “በመባሕተ መኑ ትገብር ዘንተ፤ በማን ሥልጣን ነው ይህን የምታደርገው?” ነበር ያሉት፡፡ በራሴ ሥልጣን ቢላቸው ፀረ መንግሥት አቋም አለው በማለት ከሮማ መንግሥት ዘንድ ለማሳጣት ነበር ዕቅዳቸው፡፡
ጌታችን እኩይ የሆነውን የፈሪሳውያንን አሳብ በመረዳት “የዮሐንስ ጥምቀት ከየት ነው ከሰማይ ነው ወይስ ከምድር ሲል” ጠይቋቸዋል፡፡ ከሰማይ ያልነው እንደ ሆነ ለምን አላመናችሁበትም ይለናል÷ ከሰው ያልነው ከሆነ ሕዝቡ ይጣላናል፡፡ ምክንያቱም ሕዝቡ ዮሐንስን እንደ አባት ይፈሩት እንደ መምህር ያከብሩት ነበርና ከዚህ የተነሣ ያቀረቡት የፈተና ጥያቄ ግቡን ሳይመታ ከሽፎባቸዋል፡፡ 
ዛሬም ቢሆን መልካም ሥራን በሠራን ጊዜ ከልዩ ልዩ ወገኖች የሚመጡ ፈተናዎች ለመልካም ሥራችን እንቅፋት ሊሆን እንደሚችሉ መገንዘብ አለብን፡፡ ብዙ ወገኖች ለቅን አሳባችን ለምን ሰዎች ክፉ ነገር ይመልሱልናል በማለት ሲጠይቁ ይሰማል፡፡ ለቅን ዐሳባችን ከዓለም ዘንድ የተገላቢጦሽ ነገር እንደ ሚጠብቀን “ዓለም የሚወደው የገዛ ወገኑን ነው” የሚለውን የጌታችንን ትምህርት ልብ ይሏል፡፡ ይህ በመሆኑ በዘመናችን አሳልፈው ሊሰጡን የሚፈልጉ ሰዎች ፈታኝ ጥያቄ እንደሚያቀርቡልን ከወዲሁ ልንገነዘብ ይገባል

Sunday, April 28, 2013

ሰሙነ ሕማማት


ጌታችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ከገባ ጀምሮ ያሳለፈውና ከትንሳኤው በፊት ያለው አንድ ሳምንት ወይም የመጨረሻ ሳምንት " ሰሙነ ሕማማት " ይባላል፡፡ በጌታ ላይ የሞት ምክር የተመከረበትና በብዙ መከራና ሕማማት ለመግደል የወሰኑበትና የተገደለበት ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህም ሰሙነ ሕማማት የሚለው ስያሜ ጌታ የተቀበለውን ፀዋትዎ መከራን ለማዘከር የሰተጠ ስያሜ ነው፡፡ የጌታ የመስቀሉ ሕማሞች ወይም " ሕማማት መስቀል " ተብለው የሚዘከሩት አሥራ ሦስት ሲሆኑ እነዚህም፦ 
1. በብረት ሐብለ መጋፊያና መጋፊያው እስኪጋጠም ድረስ የኋሊት መታሰሩ
2. ከአፍንጫው ደም እስኪውጣ ድረስ 25 ጊዜ በጡጫ መመታቱ
3. 65 ጊዜ ከግንድ ማጋጨታቸው
4. 120 ጊዜ በድንጋይ ፊቱን መመታቱ
5. 365 ጊዜ በሽመል መደብደቡ
6. 80 ጊዜ ጽህሙን መነጨቱ
7. 6666 ጊዜ መገረፉ
8. አክሊለ ሦክ በራሱ ላይ መደፋቱ
9. 136 ጊዜ በምድር ላይ መውደቁ
10. ሳዶር፡ አላዶር፡ ኤዴራ፡ ዳናትና ሮዳስ በሚባሉ 5ቱ ቅንዋተ መስቀል በችንካር መቸንከሩ
11. መራራ ሐሞትን መጠጣቱ
12. መስቀሉን ተሸክሞ መንገላታቱ
13. በመስቀል መሰቀሉ ናቸው።
በዚህ ሳምንት ውስጥ ካህናትና ምዕመናን በአፀደ ቤተ ክርስትያን ተሰብስበው ከሀጥያት ርቀው ከምግብና ከመጠጥ ተቆጥቦ በጾምና በጸሎት የሕማሙን ነገር የሚያወሳውን ዜማ ሲያዜሙ ግብረ ሕማም የሚባለውን መጽሐፍ እያነበቡ ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ።
ከአባታችን አዳም በደል ወይንም ስሕተት በኋላ በሕማማት፣ በደዌያት፣ በመቅሰፍታት፣ ወዘተ በብዙ መከራ የሰው ልጅ ሊኖርባቸው ግድ የሆነባቸው ዘመናት ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ ጥሮ ግሮ ወጥቶ ወርዶ ለፍቶ ማስኖ የዕለት ጉርስ የቀን ልብስ ማግኘት እጅግ አዳጋች ነበር፡፡ ሁልጊዜ የሰው ልጅ ቢያጠፋ ቢበድል ከሕገ እግዚአብሔር ቢወጣ እንኳ የዋህ፣ ታጋሽ፣ ቸር፣ አዛኝ የሆነ አምላክ የጠፋውን ሊፈለግ የተራበውን ሊያጠግብ የታረዘውን ሊያለብስ፣ ፍቅር ያጣውን ፍጹም ፍቅር ሊለግስ፣ ሰላም ለሌለው ፍጹም ሰላም ሊሰጥ፣ ተስፋ የሌለውን ተስፋ ሊያጐናጽፍ ከሰማይ ወረደ፤ ከድንግል ማርያም ተወለደ፤ በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ ቀንና ሌሊት ጾመ፡፡ በጾሙም የኃጢአት ሥሮች ወይም ራሶች የተባሉትን ስስትን፣ ትዕቢትንና ፍቅረ ንዋይን ድል አደረገልን፡፡ እኛ እርሱ የጾመውን ጾም እንድናከብር እንድንጾም ምሳሌ ሆነን፡፡ ዲያብሎስን ድል አድርጐ ድል እንድንነሣው ኃይልና ምሳሌ ሆነን፡፡

ሰሙነ ሕማማት ማለት፦
ሰመነ ስምንት /ሳምንት/ አደረገ ማለት ነው፡፡ ይኸውም ከዕለተ ሆሣዕና ሰርክ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ያለውን ጊዜ ወይም ቀናት የሚያመለክት ነው፡፡ ሐመ ማለት ታመመ ማለት ሲሆን ይህም የሰውን ዘር ሁሉ ከዲያብሎስ ባርነት ነፃ ለማውጣት ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ የተቀበላቸውን ጸዋትወ መከራዎች የሚያሳስብ ነው፡፡ ዕለታቱ የዓመተ ኩነኔ ወይም የዓመተ ፍዳ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ውለታ እያሰቡ እጅግ የሚያዝኑበት፣ የሚያለቅሱበት፣ የሚሰግዱበት ቤት ንብረታቸውን ትተው ከሌላው ቀናትና ጊዜያት በተለየ መልኩ ቤተ ክርስቲያናቸውን የሚማጸኑበት፤ ጧት ማታ ደጅ የሚጠኑበት፤ ኃጢአታቸውን በቤተ ክርስቲያን አደባባይ ለካህኑ የሚናዘዙበት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ሳምንት ነው፡፡

በዚህ ሳምንት ብዙ አዝማደ መባልእት አይበሉም፤ ይልቁን በመራብ በመጠማት በመውጣት በመውረድ በመስገድ በመጸለይ በመጾም በየሰዓቱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራዎች በማሰብ አብዝቶ ይሰገዳል፡፡ መከራውን፣ ሕማሙን፣ ድካሙን የሚያስታውሱ ከቅዱሳት መጻሕፍት ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ መዝሙረ ዳዊት ግብረ ሕማማት ወዘተ በየሰዓቱ ይነበባል፡፡

መስቀል መሳለም የለም፡፡ ካህናትም እግዚአብሔር ይፍታህ አይሉም የሳምንቱ ሥርዓተ ፍትሐት አይደረግም፡፡ ይኸውም ይህ ሳምንት ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት ከጨለማ ወደ ብርሃን የተጓዝንበት የመሸጋገሪያ ወቅት ምሳሌ በመሆኑ ነው፡፡ በዕለተ ምጽአት መላእክት የመለከት ድምጽ በማሰማት የዳግም ምጽአትን ዕለት ለማሳሰብ ምእመናን ጥሪውን ሰምተው ለዚህም አስቀድመው ተዘጋጅተው የበዓሉ ታዳሚዎች መሆናቸውን በማጠየቅ በዚህ ሳምንት ዲያቆኑ ቃጭል እየመታ በየሰዓቱ ምእመናኑን በጸሎት ተግተው፣ ምግባር ቱሩፋት ሰርተው፤ በይቅርታውና በምህረቱ ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን እንዲወርሱ ያሳስባል፡፡
በሰሙነ ሕማማት የሚገኙ ዕለታትና ስያሜያት
             ዕለተ ሰኑይ /ሰኞ/
ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ በዚህ ዓለም ሲመላለስ በሆሳዕና ማግሥት ጌታችን ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሁለት ነገሮችን አድርጓል፡፡ አንደኛ ከቅጠል በስተቀር ፍሬ ያልተገኘባትን ዕፀ በለስ ረግሟል፡፡ ሁለተኛ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን አስወጥቷል፡፡/ማቴ.21÷12-17፤ ማር.11÷17፤ ሉቃ.19÷45-46፡፡ በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል ላይ እንደተገለጸው  ይህንም ምሳሌ አለ "ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው ፍሬም ሊፈልግባት ወጥቶ ምንም አላገኘም፡፡" ሉቃ 13፡6 በማለት በበለስ ስለተመሰለ የሰው ልጅ ሕይወት በማሰብ እንዲመለስ ንስሐ እንዲገባ በሕይወትም እንዲኖር እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ማሳሰቡን ያጠይቃል፡፡ ንስሐ አልገባም አልመለስም ያለም በለሷ እንደጠወለገችና እንደተቆረጠች ሁሉ ፍሬ ባለማፍራታቸው እንደሚቆረጡ እንዲሁም ወደ እሳት እንደሚጣሉ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳል፡፡ በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ፍሬ የተባለ ደግሞ ሃይማኖትና ምግባርን ነው፡፡ ሁላችን ቤተ እስራኤላውያን ፍሬ ሃይማኖት ወምግባር አስተባብረን ይዘን መገኘት ይገባናል፡፡ ፍሬ አልባ እንዳንሆን ጌታ ሲመጣም እንዳናፍር የመጽሐፉን ቃል ልንጠብቅና ልንፈጽም ይገባናል፡፡ በዚህ የሕማማት የመጀመሪያ ቀን ዕለተ ሰኑይ የምናስበው የምንዘክረው የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ በቸልተኝነት እንዳይደክም እንዳይጠወለግ እንዳይደርቅ ወደ እሳትም እንዳይጣል ማድረግ ይገባናል፡፡
 ጌታችን መድኃኒታችን ወደ ቤተ መቅደስ ግብቶ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን እንዳስወጣ ሁሉ፤ ዛሬ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ጌታችን ወደ መቅደስ ሕይወታችን ቢመጣ ምን ያገኝ ይሆን? ፍሬ ወይስ ቅጠል? የእግዚአብሔር ቃል ግን ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ ይለናል። ማቴ 3፡8 ስለዚህ አምከ ቅዱሳን ከእኛ የሚፈልገውን የመንፈስ ፍሬ እናፍራ። ገላ 5፡22 



Saturday, April 27, 2013

How to Benefit Spiritually from Passion/holy Week


How do we enjoy the most spiritual week of the year? by His Holiness Pope Shenouda III


1. Our behavior inside and outside church:


It is very noticeable that many people during Passion Week act very differently inside church than they do outside church. Inside church… black curtains, sad hymns, solemn readings, and complete concentration on the suffering of Christ. However, outside of church, we often laugh, joke around, socialize, think and talk about many worldly issues. We lose all the spiritual depth that we gained inside church. Let us concentrate our thoughts, conversations, and meditations around the events of this Holy Week and the passion of our Savior.

2. Retreat:


During our regular fasting days, we put the words of the Bible before us, "Consecrate a fast, call a sacred assembly " (Joel 1: 14). How much more then should we apply this commandment during Holy Week? This week should be characterized by solitude and retreat with God by staying away from idle discussions, various means of entertainment and pleasures. Reserve your time for God and to spiritual activities worthy of this week.

3. Follow the steps of Christ:


Meditate on the events of the week one by one, from Palm Sunday when Christ refused His worldly kingdom and the Jews gave up their hopes in Him, until they crucified and buried Him. On Palm Sunday, ask yourself: Is Christ King and Lord over everything in my life? Do I, like Christ, turn down worldly glory for spiritual and eternal glory? And during the "general funeral" afterwards, consider yourself attending your own funeral (because during this week the church will not hold funeral services). Also, when the church denounces Judas' betrayal with a kiss on the eve of Wednesday's Pascha, ask yourself in prayer, "How often, O Lord, have I betrayed You?" "How many times have I told You words of love in prayers, while my actions show the opposite and my heart is far away from You?"

4. Share in the fellowship of His suffering:


St. Paul said "That I may know Him and the power of His resurrection, and the fellowship of His suffering, being conformed to His death" (Philippians 3:10). Can we give ourselves an exercise this week to share in the fellowship of His suffering and be conformed to His death? (source of this article: St-Takla.org) Can we follow Him in His suffering and ascend with Him to the cross? Can we say with St. Paul "With Christ I have been crucified; it is no longer I who live, but Christ lives in me" (Gal. 2:20). Therefore, in order for Christ to live in us, we have to carry our cross and follow Him. If you have a cross in your life, don't complain about it, but rather rejoice in it and bear it for Christ’s sake. "For to you it has been granted on behalf of Christ, not only to believe in Him but to suffer for His sake" (Phil. 1:29).

5. Asceticism:


Whoever puts the suffering of Christ before Him will not take any pleasure in eating, drinking or pampering the body. But in order to succeed in pursuing asceticism,

we must satisfy our souls with spiritual food so that it may thrive and overcome physical hunger.

6. Spiritual readings:                                                         


Spiritual readings are also food for the soul. The church has organized for us a treasure of appropriate readings for every day of Holy Week. This consists of Gospel readings, Old Testament prophecies that correspond to the events of each day, spiritual explanations and sermons of the church fathers and on Holy Saturday (Apocalypse night) the church reads the entire book of Revelation.

7. Hymns:                                                                           


The hymns of Passion Week are moving and full of spiritual depth. Also, Hymns, like reading, preserve thoughts from wandering and guides them in a spiritual dire.

8. Prayer:                                                                            


Since the prayers of the Agpeya are not used during Holy Week, we are to substitute personal prayers in their place. This is in addition to the intensive prayers of the church asking the Lord, who bore the sins of the world and died for us, to forgive and have mercy upon us according to His great mercy.


Tuesday, April 23, 2013

የተግባር ፍቅር


ፍቅርን የሃይማኖት አባቶች፣ የፍልስፍና ሰዎችና ዘመናዊ ወጣቶች በተለያየ መልኩ ይገልጹታል፤ እኛም ሁላችን ፍቅርን ግለጹ ተብሎ ጥያቄ ቢቀርብልን በተረዳነው መጠንና በሚመቸን መልኩ እንገልጸዋለን። ነገር ግን የገለጽነውን፣ የተረጎምነውን፣ የተረክነውን በተግባር መኖር እንችላለን ወይ የሚለው ለሁሉም ሰው ትልቅ ጥያቄ ነው።
ስለ ፍቅር መጻፍ ቅዱስ ከዘፍጥረት እስከ እራይ ዮሐንስ በግልጽና በምንረዳው መልኩ ተገልጾልናል። ብርሃን ዓለም ቅዱስ ጶውሎስ ስለ ፍቅር በአስተማረበት አንቀጹ በ1ኛ ቆሮ 13፡1 ጀምሮ_ ፍቅርን በሚገባ ከተረጎመው በኋላ "እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ፍቅር ግን ከሁሉም ይበልጣል። ዛሬ ላይ የሁሉ ሰው ጥያቄ ሊሆን የሚገባው ይህን ከሁሉ የሚበልጠውን ፍቅርን ምን ያክል በተግባር እየተገበርነው ነው? በምን መልኩ እየኖርንበት ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ይገባናል።
  ዓለም ይህን ታላቅ የእግዚአብሔር ስጦታ በተግባር ተግብሮ የሚያሳያት ብታገኝ ኑሮ ባልጠፋች፤ ከብርሃን ወደ ጨለማ፣ ከሰላም ወደ ጠብና ክርክር፣ ከጽድቅ ወደ ኩነኔ፣ ባአጠቃላይ ወደ መከራ፣ ችግር፣ረሃብ፣ ቸነፈር፣ ጦርነትና ራስን ማጥፋት ደረጃ ባልደረሰች ነበር።
በትዳራችንና በጓደኝነታችን መካከል ወደድኩሽ፡ ወደድኩህ፣ ወደድኩህ ወደድኩሽ ከሚለው አልፈን ፍቅርን በተግባር መተግበር ብንችል ትዳራችን እንደ አብርሃምና ሳራ ተብሎ እንደተዘመረልን ሰላምን፣ ደስታንና መተሳሰብን ተጎናጽፈን እከመጨረሻው የጸናን እንሆን ነበር ዳሩ ግን ፍቅራችን የንግግር እንጂ የተግባር ስላልሆነ ፍቅር ከመካከላችን ቀዝቅዛ ዓለም በምቀኝነትና በጥላቻ ወድቃ፤ በትዳራችንና በእኛነታችን ውስጥ ያለው ፍቅር የታይታና የውሸት ፍቅር እየሆነ በመምጣቱ መተማመን እንዲጎለን አድርጎታል።
አባቶቻችን ስለፍቅር ሲናገሩ፡ "ፍቅርን ይኖሩታል እንጂ በቃላት አይገልጹትም" ብለው ፍቅርን በተግባር እንጂ ለሰዎች ማሳየት/መግለጽ የምንችለው በቃላት፣ በንግግር፣ በሐተታ መግለጽ እንደማይቻል ያስረዳሉ። ፍቅርን በተግባር የሚተገብሩ ምንኛ የታደሉ ናቸው? ምክንያቱም ፍቅር ማለት ራሱ እግዚአብሔር ነውና። «እግዚአብሔር ፍቅር ነው፣ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፡ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል» 1ዮሐ 4፡16። ሁላችንም ቢሆን ፍቅርን በቃላት እናውቀዋለን፣ እንናገረዋለን፣ እንተርከዋለን ነገር ግን ተግባር ላይ የለም፤ አንኖርበትም። እግዚአብሔር አምላክ እንደሚወደን፣ እንደሚያፈቅረን ነገረን በተግባር በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ነፍሱን ስለኛ ሲል በፈቃዱ ሰጦ ፍቅርን ገለጸልን። እኛ ዛሬ የዘመኑን የሀሰት ፍቅር ከየት አመጣነው? ከማን ወረስነው? መጨረሻችንስ ምን ይሆን? እና መሰል ጥያቄዎችን ለመመለስ የተግባር ፍቅር ያስፈልገናል።

የተግባር ፍቅር ከአባቶች፦ አባቶቻችን በትምህርታቸው፣ በስብከታቸው፣ በንግግራቸው ሁሉ ፍቅርን ይገልጻሉ። ነገር ግን ፍቅርን በተግባር ተግብሮ የሚያሳየን አባት ያስፈልገናል። አርያና ምሳሌ የሚሆን አባት ለቤተ ክርስቲያን፣ ለመንግሥትና ለዓለም ያስፈልጋል። አባቶች ፍቅር በተሞላ አገልግሎታቸው ዓለምን የመለወጥ ጸጋውም ልምዱም ብቃቱም አላቸው ነገር ግን ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረ "ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?" ገላ 3፡1 ፍቅርን በተግባር በእውነት እንዳንተገብር ፖለቲካው፣ ዘረኝነቱና አለማዊነቱ አዚም ሁኖብናል። አባቶች ዓለም ከዚህ እንድትወጣ ቁልፉ እናተ ጋር ነውና በጸሎታችሁና በፍቅር ሳቡን፤ እኛ ዓለሙንና ምኞቱን ወደናልና ዘላለማዊ ሞትና መከራ እንዳያገኘን።
የተግባር ፍቅር ከመምህራንና ከሰባኪያን፦ እውነት ነው በሁሉም የመድረክና የጉባኤ አስተምሯችሁ ላይ ፍቅርን በአንደበታችሁ ትመሰክራላችሁ። ነገር ግን ፍቅርን በተግባር የሚያሳየን መምህርና ሰባኪ እኛ ተማሪዎቻችሁና ተሰባኪያን እንፈልጋለን። ፍቅርን ከቃላት ይልቅ ተግብራችሁ አሳዩን፤ ፍቅርን በስብከታችሁ ብቻ ሳይሆን በህይወታችሁ አሳዩን፤ አርያና ምሳሌ ሁኑን። የዘመኑ ትውልድ መስማት ብቻ ሳይሆን ማየት ይፈልጋል፤ ማስረጃን ይሻል። የአማላካችን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ሰባኪዮች ናችሁና እንደ አምላካችን እያደረጋችሁና እየተገበራችሁ "ከእኔ ተማሩ" ልትሉን ይገባል።
የተግባር ፍቅር ከመንግሥት፦ መንግሥት ሆይ መንግሥት ከአለህዝብ ሊኖር አይችልምና ለግዛትህ ምክንያት የሆነልህን ህዝብ በፍቅር ግዛው። ህዝቤን እወዳለሁ ብለህ በአንደበትህ በመገናኛ ብዙኃን እንደምትነግረን በተግባር አሳየን። መድሎው፡ ሙስናው፡ዘረኝነቱና በቀሉ ይቅርና እንደምትወደን በተግባር አሳየን። ሁሉም ብሄር፣ ሁሉም የእድሜ ክልል፣ የተማረ ያልተማረ ለግዛትህ ያስፈልግሃልና በህዝብህ ላይ መከራና ስቃይ አታብዛብን። መንግሥት ሆይ "ሺህ ዓመት ንገሥ" ብሎ ህዝህ የሥልጣን ዘመንህን እንዳራዝምልህ ፍቅርን በተግባር አሳየን።
የተግባር ፍቅር ከሁላችን፦ "እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይቺ ናት" ዮሐ 15:12 ብሎ አምላካችን እንዳስተማረን ማንንም ሳንመለከት በመስቀል ላይ የተሰቀለውን የክርስቶስን ፍቅር እየተመለከትን ሁላችንም እርስ በእርሳችን እንዋደድ፣ እንፋቀር። ፍቅርን በተግባር ተግብረን ለሌሎችም አርያ እንሁን።

የፍቅር ሰው እንድንሆን የአምላካችን መልካም ፈቃድ፤ የቅዱሳን ተራዳኢነት አይለየን።