ሰሙነ ሕማማት
ጌታችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ከገባ ጀምሮ ያሳለፈውና ከትንሳኤው በፊት ያለው አንድ ሳምንት ወይም የመጨረሻ ሳምንት " ሰሙነ ሕማማት " ይባላል፡፡ በጌታ ላይ የሞት ምክር የተመከረበትና በብዙ መከራና ሕማማት ለመግደል የወሰኑበትና የተገደለበት ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህም ሰሙነ ሕማማት የሚለው ስያሜ ጌታ የተቀበለውን ፀዋትዎ መከራን ለማዘከር የሰተጠ ስያሜ ነው፡፡ የጌታ የመስቀሉ ሕማሞች ወይም " ሕማማት መስቀል " ተብለው የሚዘከሩት አሥራ ሦስት ሲሆኑ እነዚህም፦
1. በብረት ሐብለ መጋፊያና መጋፊያው እስኪጋጠም ድረስ የኋሊት መታሰሩ
2. ከአፍንጫው ደም እስኪውጣ ድረስ 25 ጊዜ በጡጫ መመታቱ
3. 65 ጊዜ ከግንድ ማጋጨታቸው
4. 120 ጊዜ በድንጋይ ፊቱን መመታቱ
5. 365 ጊዜ በሽመል መደብደቡ
6. 80 ጊዜ ጽህሙን መነጨቱ
7. 6666 ጊዜ መገረፉ
8. አክሊለ ሦክ በራሱ ላይ መደፋቱ
9. 136 ጊዜ በምድር ላይ መውደቁ
10. ሳዶር፡ አላዶር፡ ኤዴራ፡ ዳናትና ሮዳስ በሚባሉ 5ቱ ቅንዋተ መስቀል በችንካር መቸንከሩ
11. መራራ ሐሞትን መጠጣቱ
12. መስቀሉን ተሸክሞ መንገላታቱ
13. በመስቀል መሰቀሉ ናቸው።
በዚህ ሳምንት ውስጥ ካህናትና ምዕመናን በአፀደ ቤተ ክርስትያን ተሰብስበው ከሀጥያት ርቀው ከምግብና ከመጠጥ ተቆጥቦ በጾምና በጸሎት የሕማሙን ነገር የሚያወሳውን ዜማ ሲያዜሙ ግብረ ሕማም የሚባለውን መጽሐፍ እያነበቡ ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ።
ከአባታችን አዳም በደል ወይንም ስሕተት በኋላ በሕማማት፣ በደዌያት፣ በመቅሰፍታት፣ ወዘተ በብዙ መከራ የሰው ልጅ ሊኖርባቸው ግድ የሆነባቸው ዘመናት ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ ጥሮ ግሮ ወጥቶ ወርዶ ለፍቶ ማስኖ የዕለት ጉርስ የቀን ልብስ ማግኘት እጅግ አዳጋች ነበር፡፡ ሁልጊዜ የሰው ልጅ ቢያጠፋ ቢበድል ከሕገ እግዚአብሔር ቢወጣ እንኳ የዋህ፣ ታጋሽ፣ ቸር፣ አዛኝ የሆነ አምላክ የጠፋውን ሊፈለግ የተራበውን ሊያጠግብ የታረዘውን ሊያለብስ፣ ፍቅር ያጣውን ፍጹም ፍቅር ሊለግስ፣ ሰላም ለሌለው ፍጹም ሰላም ሊሰጥ፣ ተስፋ የሌለውን ተስፋ ሊያጐናጽፍ ከሰማይ ወረደ፤ ከድንግል ማርያም ተወለደ፤ በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ ቀንና ሌሊት ጾመ፡፡ በጾሙም የኃጢአት ሥሮች ወይም ራሶች የተባሉትን ስስትን፣ ትዕቢትንና ፍቅረ ንዋይን ድል አደረገልን፡፡ እኛ እርሱ የጾመውን ጾም እንድናከብር እንድንጾም ምሳሌ ሆነን፡፡ ዲያብሎስን ድል አድርጐ ድል እንድንነሣው ኃይልና ምሳሌ ሆነን፡፡
ሰሙነ ሕማማት ማለት፦
ሰመነ ስምንት /ሳምንት/ አደረገ ማለት ነው፡፡ ይኸውም ከዕለተ ሆሣዕና ሰርክ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ያለውን ጊዜ ወይም ቀናት የሚያመለክት ነው፡፡ ሐመ ማለት ታመመ ማለት ሲሆን ይህም የሰውን ዘር ሁሉ ከዲያብሎስ ባርነት ነፃ ለማውጣት ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ የተቀበላቸውን ጸዋትወ መከራዎች የሚያሳስብ ነው፡፡ ዕለታቱ የዓመተ ኩነኔ ወይም የዓመተ ፍዳ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ውለታ እያሰቡ እጅግ የሚያዝኑበት፣ የሚያለቅሱበት፣ የሚሰግዱበት ቤት ንብረታቸውን ትተው ከሌላው ቀናትና ጊዜያት በተለየ መልኩ ቤተ ክርስቲያናቸውን የሚማጸኑበት፤ ጧት ማታ ደጅ የሚጠኑበት፤ ኃጢአታቸውን በቤተ ክርስቲያን አደባባይ ለካህኑ የሚናዘዙበት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ሳምንት ነው፡፡
በዚህ ሳምንት ብዙ አዝማደ መባልእት አይበሉም፤ ይልቁን በመራብ በመጠማት በመውጣት በመውረድ በመስገድ በመጸለይ በመጾም በየሰዓቱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራዎች በማሰብ አብዝቶ ይሰገዳል፡፡ መከራውን፣ ሕማሙን፣ ድካሙን የሚያስታውሱ ከቅዱሳት መጻሕፍት ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ መዝሙረ ዳዊት ግብረ ሕማማት ወዘተ በየሰዓቱ ይነበባል፡፡
መስቀል መሳለም የለም፡፡ ካህናትም እግዚአብሔር ይፍታህ አይሉም የሳምንቱ ሥርዓተ ፍትሐት አይደረግም፡፡ ይኸውም ይህ ሳምንት ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት ከጨለማ ወደ ብርሃን የተጓዝንበት የመሸጋገሪያ ወቅት ምሳሌ በመሆኑ ነው፡፡ በዕለተ ምጽአት መላእክት የመለከት ድምጽ በማሰማት የዳግም ምጽአትን ዕለት ለማሳሰብ ምእመናን ጥሪውን ሰምተው ለዚህም አስቀድመው ተዘጋጅተው የበዓሉ ታዳሚዎች መሆናቸውን በማጠየቅ በዚህ ሳምንት ዲያቆኑ ቃጭል እየመታ በየሰዓቱ ምእመናኑን በጸሎት ተግተው፣ ምግባር ቱሩፋት ሰርተው፤ በይቅርታውና በምህረቱ ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን እንዲወርሱ ያሳስባል፡፡
በሰሙነ ሕማማት የሚገኙ ዕለታትና ስያሜያት
ዕለተ ሰኑይ /ሰኞ/
ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ በዚህ ዓለም ሲመላለስ በሆሳዕና ማግሥት ጌታችን ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሁለት ነገሮችን አድርጓል፡፡ አንደኛ ከቅጠል በስተቀር ፍሬ ያልተገኘባትን ዕፀ በለስ ረግሟል፡፡ ሁለተኛ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን አስወጥቷል፡፡/ማቴ.21÷12-17፤ ማር.11÷17፤ ሉቃ.19÷45-46፡፡ በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል ላይ እንደተገለጸው ይህንም ምሳሌ አለ "ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው ፍሬም ሊፈልግባት ወጥቶ ምንም አላገኘም፡፡" ሉቃ 13፡6 በማለት በበለስ ስለተመሰለ የሰው ልጅ ሕይወት በማሰብ እንዲመለስ ንስሐ እንዲገባ በሕይወትም እንዲኖር እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ማሳሰቡን ያጠይቃል፡፡ ንስሐ አልገባም አልመለስም ያለም በለሷ እንደጠወለገችና እንደተቆረጠች ሁሉ ፍሬ ባለማፍራታቸው እንደሚቆረጡ እንዲሁም ወደ እሳት እንደሚጣሉ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳል፡፡ በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ፍሬ የተባለ ደግሞ ሃይማኖትና ምግባርን ነው፡፡ ሁላችን ቤተ እስራኤላውያን ፍሬ ሃይማኖት ወምግባር አስተባብረን ይዘን መገኘት ይገባናል፡፡ ፍሬ አልባ እንዳንሆን ጌታ ሲመጣም እንዳናፍር የመጽሐፉን ቃል ልንጠብቅና ልንፈጽም ይገባናል፡፡ በዚህ የሕማማት የመጀመሪያ ቀን ዕለተ ሰኑይ የምናስበው የምንዘክረው የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ በቸልተኝነት እንዳይደክም እንዳይጠወለግ እንዳይደርቅ ወደ እሳትም እንዳይጣል ማድረግ ይገባናል፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ወደ ቤተ መቅደስ ግብቶ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን እንዳስወጣ ሁሉ፤ ዛሬ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ጌታችን ወደ መቅደስ ሕይወታችን ቢመጣ ምን ያገኝ ይሆን? ፍሬ ወይስ ቅጠል? የእግዚአብሔር ቃል ግን ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ ይለናል። ማቴ 3፡8 ስለዚህ አምከ ቅዱሳን ከእኛ የሚፈልገውን የመንፈስ ፍሬ እናፍራ። ገላ 5፡22
Very quіckly ths site ωill bee famouѕ among alll blоgging annd site-bui&X6c;ding viewers, due to it's pleasant articleѕ or revieωs
ReplyDelete&X46;eеl free to visit mу site Free Microsoft Points Here