ደብረ ታቦር ማለት የታቦር ተራራ ማለት ነው። ከ9ኙ ዓበይት በአላት መካከል አንዱ ነው። ታሪኩም በአጭሩ፦ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል ብሎ በጠየቃቸው በሰባተኛው ቀን ከነቢያትም አንዱ ነህ ብለውታልና የነቢያት አምላካቸው እንደሆነ ለማጠየቅ፤ በቅዱስ ጴጥሮስ የተነገረውን በጌታ ቃል ለማስመስከር ሶስቱን ባለሟሎቹን (ቅዱስ ጴጥሮስን፣ ቅዱስ ያዕቆብንና ቅዱስ ዮሓንስን) ለብቻቸው ወደ ተራራ ይዟቸው ወጣ። መልኩም በፊታቸው ተለወጠ አካሉም ምሉዕ ብርሃን ሆነ፤ ገጹም እንደ ፀሐይ ብሩህ ልብሱም እንደ በረድ ፀዓዳ።
ይህ ሁሉ ጌትነቱን ሲገልጽላቸው ነው። እነሆም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ሙሴ የእኔን የሙሴን ጌታ ማን ሙሴ ይልሃል የሙሴ አምላክ ይበሉህ እንጂ፤ ኤልያስም የእኔን የኤልያስን ጌታ ማን ኤልያስ ይልሃል የኤልያስ አምላክ ይበሉህ እንጂ ሲሉ ተሰምተዋል። ቅዱስ ጴጥሮስም በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው አለው። እርሱም ገና ሲናገር ብሩህ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው ፥ ከደመናውም- በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት የሚል ድምጽ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሰምተው ደነገጡ ፈጽመው ፈሩ በፊታቸውም ወደቁ። ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸው፤ አይዟችሁ ተነሡ አላቸው። ዓይናቸውንም አቅንተው ሲያዩ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አዩ እንጂ መነንም ማን አላዩም። በዚህ ሁኔታ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነቱን በታቦር ተራራ ገለጸላቸው። ይኸውም “ታቦርና አርሞንዔም በስምህ ደስ ይላቸዋል” (መዝ 88፡ 12-13) ተብሎ በቅዱስ ዳዊት የተነገረውን ትንቢት ሊፈጽም ነው። ስለምን በተራራ አደረገው ቢሉ ተራራ የወንጌል፣ የመንግስተ ሰማያት፣ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ነው። ተራራ ሲወጡት ይከብዳል ከወጡት በኋላ ግን ሜዳውንና ጭንጫውን ኮረብታውን ሲያሳይ ደስ ያሰኛል ወንጌልም ሲማሯት ታጽራለች፤ ከተማሯት በኋላ ግን ጽድቅና ኃጢያትን ለይታ ስታሳውቅ ደስ ታሰኛለችና። አንድም ተራራ በብዙ ፃእር እንዲወጡት መንግስተ ሰማይንም በብዙ መከራ ያገኟታልና ነው። በዚህም ተራራ ከነቢያት ሁለቱን ከሐዋርያት ሶስቱን ማምጣቱ በቤተ ክርስቲያን ብሉይና ሐዲስ እንዲነገር ለማጠየቅ ነው። መንግስተ ሰማያትንም ነቢያትና ሐዋርያት፤ ደናግላን እንደ ኤልያስና መዓስባን እንደ ሙሴ ያሉ፤ ሕያዋን እንደ ኤልያስና ምውታን እንደ ሙሴ ያሉ በአንድነት እንዲወርሷት ለማስረገጥ ነው። ማቴ 17፡1_
እግዲህ ይህ ታላቅ በዓል ብዙ ሚስጥር የተገለጠበት ስለሆነ ቅድስት ቤተክርስትያን በዜማና በመዝሙር ታከብረዋለች። በምናከብርበትም ጊዜ ቡሄ በሉ እያልን፣ ሙልሙል ይዘን፣ ችቦ እያበራን እናከብራለን። ምሳሌውም፦
ቡሄ፦
ይህ ቦታ ጌታ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ተራራ ነው። በዚህ ምክንያት ያቺ ዕለት ቡሄ የሚለውን ስያሜ አገኘች ቡሄ ማለት ገላጣ፣ የተገለጠ ማለት ነው።
የሙልሙሉ እና የችቦው ምሳሌ ደግሞ፦
ጌታችን ብርሃነ መለኮቱ በገለጠበት ዕለት ጊዜው ምሽት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እረኞች ከብርሃኑ የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም ነበር። የልጆቹን መዘግየት ያዩ ወላጆች ችቦ አብርተውና ዳቦ ይዘው ፍለጋ ወጡ። አሁን ታዲያ «ቡሄ» ለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠውና ችቦ በማብራት በዓሉን የምናከብረውም ከዚህ በመነሣት ነው።
ልጆች በገጠርም ሆነ በከተማ ጅራፍ የሚያጮኹበት ሁኔታም አለ። የጅራፉ ምሳሌ አብ «የምወደው ልጄ ይህ ነው፡፡ እርሱን ስሙት» ብሎ ሲናገር የነበረው ድምጽ ምሳሌ ነው። ሙሴና ኤልያስ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ያዕቆብ ደንግጠው ነበር። ያን ለማሰብ ጅራፍ እናጮሀለን።
አንቺ ደብረ ታቦር ምንኛ ታደልሽ
ጌታ መለኮቱን የገለጠብሽ
ያገቡ ድንግላይ ሁሉን ሰበሰብሽ፣
በብርሃን ተመልተሽ በመገኘትሽ
ለመንግስተሰማይ ምሳሌ ሆንሽ።
ዓለም እንዲያምንበት ባምላክነቱ
እነሆ በታቦር ታየ ጌትነቱ፣
አብ መሰከረለት በደመና አውሎ
የምወደው ልጄ ይህ ነው ስሙት ብሎ፣
ሙሴና ኤልያስ ካያሉበት መጥተው
ቆመው መሰከሩ በቀኝ በግራው።
በአጠቃላይ ደብረ ታቦር/በታቦር ተራራ ላይ
- "ታቦርና አርሞንኤም በአንተ ስም ደስ ይላቸዋል" መዝ 89:12 ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ።
- መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክነቱን ገለጠ።
- ምስጢረ ስላሴ ተገለጠ/አብ በደመና ድምጹን በማሰማት፣ መንፈስ ቅዱስ በብርሃን፣ ወልድ በአካል/።
- ሙሴ፦ "እኔ ማሕር ብከፍልም፣ ጠላት ብገድልም፣ ደመና ብጋርድም፣ መና ባወርድም፣ እስርኤልን ከክፋታቸው መልሶ ማዳን አልተቻለኝም። ለአንተ ግን ሁሉ ይቻልሃል። ደግሞስ የኔን ፈጣሪና ጌታ እንዴት ሙሴ ይሉሃል? የሙሴ ጌታ ይበሉህ እንጂ" በማለት የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት መሰከረ።
- ኤልያስ፦ "እኔ ሰማይ ብለጉም፣ እሳት ባዘንብም እስራኤልን ከክፋታቸው መልሶ ማዳን አልተቻለኝም። ለአንተግን ይቻልሃል። ደግሞስ የኔን ፈጣሪና ጌታ እንዴት ኤልያስ ይሉሃል? የኤልያስ ጌታ ይበሉህ እንጂ" በማለት የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት መሰከረ።
- በህይወት፣በእምነት፣ በቤተ ክርስቲያንና በአገልግሎት መኖር መልካም እንደሆነ ቅዱስ ጴጥሮስ "በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው" በማለት ተናገረ።
- የእግዚአብሔር መንግሥት ሕግን ጠብቀው ለሚኖሩ ለሁሉም መሆናን ሙሴን ከአገቡት፣ ኤልያስን ከደናግልና ሐዋርያትን ከአለም አምጥቶ አሳየን።
- ደብረ ታቦር የወንጌል፣ የመንግሥተ ሰማያትና የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ መሆኗን፤ ነብያት በትንቢትና በምሳሌ፣ ሐዋርያት በግልጥና በተግባር የሰበኳት መሆኑን ገለጠ።
ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን፤
ብርሃነ መለኮቱን እንደገለጠ ለኛም ምስጥርን ይግለፅልን። አሜን!!!
No comments:
Post a Comment