ጾመ ፍልሰታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 64 ዓመት በዚች ምድር ኖራ እንደ አንድ ልጇ መሞቷን መነሳቷንና ማዕረጓን ያዩ ዘንድ ሐዋርያት የጾሙት ጾም ነው። ጾሙ ከነሐሴ 1 ቀን እስከ ነሐሴ 16 ቀን ሲጾም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዋጅ ከደነገገቻቸው ሰባቱ አጽዋማትም አንዱ ነው።
እመቤታችን ከአባቷ ከኢያቄም እና ከእናቷ ከሐና ነሐሴ 7 ቀን ተጸንሳ ግንቦት 1 ቀን በሊባኖስ ተወልዳለች። እምቤታችን በእናት አባቷ ቤት ሦስት/፫/ ዓመት፤ በቤተ መቅደስ አሥራ ሁለት/12/ ዓመት፤ ከልጇ ከወዳጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር/33 ከ3 ወር/ ፡ ከዮሐንስ ወልደ ዘብዴዎስ ዘንድ አሥራ አራት ዓመት ከዘጠኝ ወር/14 ከ9 ወር/ ቆይታ በ 64 ዓመት ዕድሜዋ በ49 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች። የእመቤታችንን ስም የሚገልጹ የውዳሴ ጽሑፎችም በእድሜዋ ልክ ተደርሰዋል። ለምሳሌ የውዳሴ ማርያም ቁጥር 64 ነው፤ የመልክአ ማርያም ቁጥርም 64 ነው።
ባረፈች ጊዜ ቅዱሳን ሐዋርያት ተሰባስበው አስከሬኗን ይዘው ወደ ጌቴሴማኒ መቃብር ለማሳረፍ ሲሄዱ አይሁድ ለተንኮል አያርፉምና ተተናኮሏቸው። ቀድሞ ልጇ ሞቶ ተነሳ፣ አረገ እያሉ ሲያስቸግሩን ይኖራሉ: ደግሞ አሁን እሷም ተነሳች፣ አረገች ሊሉ አይደል በማለት አይሁድ ተሰባስበው አስከሬኗን ለማቃጠል ሲተናኮሉ እግዚአብሔር በተአምር ከነዚያ አይሁዶች አድኗቸዋል ። ከሁሉ አንዱ ታውፋኒያ የተባለው ተራምዶ አጎበሩን ጨበጠው የታዘዘ መልአክ ሁለት እጁን በሰይፍ ቀጣው። ከአጎበሩ ተንጠልጥሎ ቀረ። በድያለው ማሪኝ ብሎ ቢማጸናት ራሷን ዘንበል አድርጋ ጴጥሮስን እንደነበረ አድርግለት አለችው። ቢመልሰው ድኖ ተነስቷል። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር የእመቤታችንንም አስከሬን ነጥቆ ከሐዋርያው ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር በገነት በዕፀ ህይወት ስር አኑሯቸዋል ። ከዚያ በኋላ ሐዋርያት ሥጋዋን አግኝተው ይቀብሩት ዘንድ በአረፈች በስምንተኛው ወር ከነሐሴ 1 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 14 ቀን ድረስ ሁለት ሱባዔ ይዘው በአሥራ አራተኛው ቀን ሥጋዋን ከጌታ ተቀብለው በጸሎትና በምህላ በፍጹም ደስታ በጌቴሰማኔ አሳረፉት ። በሦስተኛውም ቀን ተነስታ ስታርግ ከሰዱቃውያን ወገን የሆነው ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ አያት። እርሱም በቀብር ስርዓቱ ጊዜም አልነበረም። ሀገረ ስብከቱ ህንድ ስለነበር ሊያስተምር ወደዛው ሂዶ ነበርና። በዚያም ሲያስተምር ሰንብቶ በደመና ተጭኖ ሲመጣ ያገኛታል። ትንሳኤዋን ከርሱ ሰውራ ያደረገች መስሎት አዝኖ «ቀድሞ የልጅሽን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁ አሁን ደግሞ ያንቺን ትንሳኤ ሳላይ ቀርቼ ነውን ?» ብሎ ቢያዝንባት እመቤታችንም ከርሱ በቀር ማንንም ትንሳኤዋን እንዳላየ ነግራ አጽናናችው። ለሌሎቹ ሐዋርያትም እንዲነግራቸው ለምልክትም /ለምስክርም እንዲሆነው ሰበኗን /መግነዟን ሰጥታው አረገች። ቶማስም ኢየሩሳሌም ደርሶ ሐዋርያትን «የእመቤታችን ነገርስ እንደምን ሆነ?» ሲል ቢጠይቅ «አግኝተን ቀበርናት እኮ» አሉት። እርሱ ምስጢሩን አዉቆ ደብቆ «ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር» እንዴት ይሆናል ? አይደረግም ይላቸዋል። ሊያሳያቸውም መቃብሩ ዘንድ ሂደው ቢከፍቱት አጧት። እርሱም «አታምኑኝም ብዬ እንጂ እርሷስ ተነስታ አርጋልች»በማለት ሁኔታውን ተረከላቸውና ለምስክር ይሁንህ ብላ የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው። ከዚህ በኋላ ለበረከት ይሆናቸው ዘንድ ሰበኑን ተካፍለው ወደየአህገረ ስብከታቸው ሄዱ። ዛሬ በቅዳሴ ጊዜ ዲያቆኑ በሚይዘው የመጾር መስቀል ላይ በሁለት ቀዳዳዎች አልፎ ተጠምጥሞ የምናየው መቀነት መሰል ጨርቅ የዚያ ሰበን ምሳሌ ነው።
በዓመቱ ሐዋርያት ከያሉበት ተሰባስበው ቶማስ ትንሣኤሽን አይቶ እኛስ እንዴት ይቀርብናል ብለው ከነሐሴ 1 ቀን ጀምርው ሱባዔ ቢይዙ ከሁለት ሱባዔ በኋላ እንደገና ትንሳኤዋንና እርገቷን ለማየት በቅተዋል። ሐዋርያዊት የሆነች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናም ምእመኖቿ ከእመቤታችን በረከትን እንዲያገኙ ይጾሙ ዘንድ ይህን ሐዋርያት የጾሙትን ጾም እንዲጾሙ አውጃለች። ምእመናንም በተለየ መልኩ በጾም በጸሎት በሱባዔ ሆነው ይህን ወቅት ያሳልፋሉ።
የእመቤታችን ትንሣኤ ድንገት እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውሀ ፈሳሽ የተደረገ ሳይሆን በቅዱሳት መጻሕፍት በትንቢተ ነቢያት የተገለጸ ነው። ነቢዩ ዳዊት በመዝሙር 131፡1 ላይ «አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህ ታቦ» ይላል። በዚህም ምዕመናንን ወደ ምታሳርፍበት ወደ መንግሥተ ሰማያት የመቅደስህ ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነስ አለ። ታቦት የጽላት ማደርያ እንደሆነ ሁሉ እምቤታችንም ለክርስቶስ ማደርያ በመሆኗ አማናዊት ታቦት ትባላለች።
ንጉስ ሰሎሞንም መኃ 2፡10 ላይ «ውዴ እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፤ ወዳጄ ሆይ ተነሽ፡ ውበቴ ሆይ ነይ» ብሏል። እዚህ ላይ«ወዳጄ ...ዉበቴ» የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት ። ክቡር ዳዊት መዝሙር 44፡9 ላይ «በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች» እንደሚል ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም ቤዛነቱን ከፈጸመ በኋላ ወደ ቀደመ ክብሩ እንዳረገ እመቤታችን ቅድስት ድንገል ማርያምም በቀኙ ትቀመጥ ዘንድ «ተነሽ ነይ» አላት ። እንግዲህ ይህንና የመሰለዉን ሁሉ ይዘን የእናታችንን እረፍቷን ትንሣኤዋን በጾም በጸሎት እንዘክራለን እንመሰክራለንም።
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤቷ፣ በረከቷ፣ አማላጅነቷ አይለየን፡ አሜን።
No comments:
Post a Comment