የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል (መዝ 111፥6)
ከአባታቸው ከካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ቅድስት እግዚእ ኃረያ መጋቢት 24 ቀን ተፀንሰው፡በ1215 ዓ.ም ታሕሣሥ 24 ቀን ተወለዱ፡፡ ወላጆቻቸውም ፍስሐ ጽዮን አሏቸው፡ ትርጓሜውም የጽዮን ተድላዋ ደስታዋ ማለት ነው፡፡ ተክለ ሃይማኖት ማለት ተክለ አብ፣ ተክለ ወልድ፣ ተክለ መንፈስ ቅዱስ / የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ተክል/ፍሬ/ ማለት ነው፡፡ በተወለዱ በሦስት ቀናቸው ከእናታቸው እቅፍ ወርደው «አሐዱ አብ ቅዱስ፣አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ» ብለው ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ አመት ከ3 ወር ሲሆናቸው በተወለዱበት በሽዋ በጽላሎሽ አካባቢ ብርቱ ረሀብ ሆነ፡፡ እናቱ እግዚያራ የቅዱስ ሚካኤል በዓል ሊታጎልብኝ ነው ቢላ እያዘነች እያለቀሰች እያለ በእጃቸው እያመለከቱ ወደቤት እድታገባቸው አመለከቷት ይዛቸውም ገባች፡፡ እፍኝ የስንዴ ዱቄት የነበረበትን እንቅብ እጃቸውን ቢጭኑበት ሞልቶ ፈሰሰ::9 እንቅብ አምጥታ ብታቀርብላቸው እየዘገኑ ቢያረጉበት ዘጠኙም ሞልተው ተገኝተዋል፡፡ የቅቤውንም ማሰሮ በተመሳሳይ በበረከት ሞልቶውታል፡፡ በዚህም ሁኔታ መጋቢት 12 የቅዱስ ሚካኤልን በዓለ ዝክር ያለፈና ያገደመውን ሁሉ እያበሉና እያጠጡ በሰላምና በደስታ በዓሉን አውጥተውታል፡፡በወላጅ አባታቸው በካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብ ግብረ ዲቁናን ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ሲያጠኑ ቆይተው በአሥራ አምስት ዓመታቸው ከእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ /ጌርሎስ/ ዲቁናን ተቀብለዋል፡፡ በዚህም ቅድስት ቤተክርስቲያንን በወጣትነት ዕድሜያቸው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከጓደኞቻቸው ጋር ወደ ዱር አደን ሄደው ሳለ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ ለኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ሐዲስ ሐዋርያ አድርጎ መረጣቸው። ስማቸውንም «ተክለ ኃሃይማኖት» አለው፡፡ ትርጓሜውም የኃይማኖት ፍሬ ማለት ነው፡፡
አባታችንም ሐዋርያዊ ጉዟቸውን ሲጀምሩ፦«አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደተከፈተ ተውኩልህ . . . ደካማ ለሆንኩ ለእኔ ያለ አንተ የሚያፀናኝ የለም። ለምፍገመገም ለእኔ ያለ አንተ ደጋፊ የለኝም። ለወደቅሁ ለእኔ ያለአንተ የሚያነሳኝ የለም። ለአዘንኩ ለእኔ ያለአንተ የሚያረጋጋኝ የለም። ለድሀው ለእኔ ያለ አንተ መጠጊያ የለኝም፡፡» ይህን ብለው ትሕትና በተሞላበትና በተሰበረ ልብ ወደ ፈጣሪያቸው ከለመኑ በኋላ በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገራት ከኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ፣ ከክህደት ወደ ሃይማኖት መልሰዋል፡፡ በዚህም የተነሣ ለኢትዮጵያውያን ብርሃን ፀሐይ ተብለዋል፡፡ ይህን ሁሉ ገድልና ትሩፋት እየፈጸሙ ዕረፍታቸውም በደረሰ ጊዜ ደቀመዝሙሮቻቸውን «ልጆቼ ሆይ ሁሉም መነኮሴ መንግሥተ ሰማይ ይገባል ማለት አይደለም፤ ዓለምን በሚገባ የናቀ ብቻ ይገባል እንጂ መጀመሪያ የእግዚአብሔርን ጽድቁን ብቻ ፈልጉ፤ ጾምና ጸሎትን አዘውትሩ፤ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ ትእዛዛቱንም አጥብቃችሁ ጠብቁ እያሉ ይመክሯቸው ነበር. . .» በኋላም «ለዓለም ጨው ለራሴ አልጫ ሆንኩ፤ ለዓለም ብርሃን ለራሴ ጨለማ ሆንኩ፣ ከእውነተኛው ዳኛ ከጌታዬ ፊት ስቆም ምን እመልሳለሁ?» እያሉ በፍጹም ትህትና እና በልዩ መንፈሳዊ ተመስጦ ይጸልዩ ነበር፡፡
በመጨረሻም ከበዓታቸው ገብተው ወደፊት ወደኋላ ቁጭ ብድግ እንዳይሉ ከፊት ከኋላቸው ከግራ ከቀኛቸው ስምንት ጦር ተክለው ሱባኤ ያዙ፡፡ ከመቆም ብዛት የተነሳ አንድ እግራቸው ተቆረጠ፡፡ በአንድ እግራቸው ቆመው ለ7 አመት ጸልየዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ነሀሴ 24 በ 99 አመታቸው ጻድቁ አባታችን ዐርፈዋል፡፡ በዚህም መሠረት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ዕረፍታቸው በእግዚአብሔር ፊት ለከበረና ብዙ ክብር ለተሰጣቸው ለጻድቁ ተክለ ሃይማኖት በየዓመቱ በነሐሴ ፳፬ ቀን በዓለ ዕረፍታቸውን በታላቅ ድምቀት ታከብራለች፡፡
የጻድቁ አባታችን በረከታቸው፣ረድኤታቸውና አማላጅነታቸው አይለየን፡ አሜን!!!
No comments:
Post a Comment