Saturday, October 5, 2013

ዘመነ ጽጌ

ከገነት የተሰደደውን አዳምን ወደ ቀደመ ክብሩና መንበሩ ከዚያም ወደ ሚበልጥ ክብር ለመመለስ የተወለደው ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ገና ከህፃንንቱ ጀምሮ ስደትን እና መከራን ተቀብሏል፡፡
ጌታ ሲወለድ ሰብአ ሰገል «የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት አለ? በምሥራቅ ኮከቡን አይተን ልንስግድለት መጥተናል» እያሉ በኮከብ እየተመሩ በመጡ ጊዜ በይሁዳ፣ በገሊላና በሰማርያ የሮማውያን ተወካይ የነበረው ንጉሥ ሄሮድስ የጌታችን ንግሥና ምድራዊ ንግሥና መስሎት መንግስቴን ሊቀማኝ ነው ብሎ ደነገጠ፡፡ ፊሪሳውያን «መሲህ ተወልዶ ከሮማውያን አገዛዝ ነጻ ያወጣናል፡፡» ብለው ያምኑ እንደነበር ስለሚያውቅም ይህ የተፈጸመ መስሎት ጭንቀቱ በረታ፡፡ የተወለደውን ሕፃንም ለመግደል ተነሳ፡፡
ስለዚህም ሰብአ ሰገልን አስጠርቶ «ሂዱ ሕፃኑን ፈልጉ ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔም እንድሰግድለት ወደ እኔ ተመልሳችሁ ያለበትን ንገሩኝ» በማለት በሽንገላ ተናገራቸው፡፡
ጠቢባኑም ከሄሮድስ ከተለዩ በኋላ በኮከቡ እየተመሩ ጉዞአቸውን ቀጥለው ጌታችንን ከእናቱ ጋር አገኙት ፤ ተንበርክከው ሰገዱለት፤ ወርቅ ፣ ዕጣን፣ ከርቤ እጅ መንሻ አቀረቡለት፡፡

የእግዚአብሔር መልአክ ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ፤ ነገር ግን መንገድ ቀይረው ወደ ሀገራቸው እንዲሄዱ በነገራቸው መሠረት በሌላ መንገድ ወደ መጡበት ተደብቀው ተመለሱ፡፡

«እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ «ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነስ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሸ፤ እስክነግርህም በዚያ ተቀመጥ አለው፡፡ » /ማቴ. 2 13 14/

ዮሴፍም ተነሣ፤ በዕድሜዋ በጣም ልጅ የነበረችው እመቤታችን ገና የተወለደውን ሕፃን አቅፋ የምትቀመጥበት አህያም ተዘጋጀ፡፡ ጉዞአቸውን ጀመሩ፡፡ ከእስራኤል ወደ ግብጽ በእግር ለመሔድ የሲናን በረሃ ማለፍ የግድ ነው፡፡ በዚያን ዘመን ከእስራኤል ወደ ግብጽ የሚወስዱ ሦስት የተለያዩ መንገዶች ነበሩ፡፡ በሽፍቶች ላለመጠቃት መንገደኞች በቡድን በቡድን ሆነው በእነዚህ መንገዶች ይሔዱ ነበር፡፡

እነርሱ ግን ንጉሥ ሔሮድስ ተከታትሎ ሊይዛቸው ስለሚችል በእነዚህ መንገዶች መሔድ እንደሌለባቸው ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህም በእግዚአብሔር መልአክ እየተመሩ ባልታወቁ መንገዶች መሔድ ነበረባቸው፡፡ ለበርካታ ቀናትና ሳምንታት ሸለቆዎችን በመውረድና ኮረብታዎችን እየወጡ ጉዛአቸውን ቀጠሉ፡፡ ሽማግሌው አናጢ ዮሴፍ ከፊት ሁኖ አህያዋን ባልተስተካከለውና ማለቂያ የሌለው በሚመስለው የበረሃ መንገድ ላይ ይመራ ነበር። ሰሎሜም ስንቃቸውን ይዛ ከኋላ ትከተል ነበር፡፡ በጣም አስቸጋሪ እና አስጨናቂ ጉዞ ነበር፡፡ ቀን ቀን የሚያቃጥለውን የፀሐይ ሐሩር ሌሊት ሌሊት ደግሞ የበረሀውን ውርጭ /ብርድ/ መታገል ነበረባቸው ምግባቸውንም በተአምራት ያገኙ ነበር፡፡

በመጨረሻም በመጽሐፈ ስንክሳር እንደተመዘገበው ግንቦት 24 ቀን ግብጽ ደረሱ፡፡ በግብጽም ባሉ የተለያዩ ከተሞች ተዘዋወሩ፣ ጌታም በተለያዩ ቦታዎች በርካታ ተአምራትን አደረገ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ተቀብለው ሲያስተናግዷቸው ሌሎች ደግሞ አሳደዋቸዋል፤ መከራንም አጽንተውባቸዋል፡፡ በዚሁ ስድታቸው ወቅት ጌታ እና እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያም መጥው ሀገራችንን ባርከዋል።

ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል በስደት ከቆዩ በኋላ ሄሮድስ ሞተ። ሄሮድስም ከሞተ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ «የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ አለው፡፡ እርሱም ተነስቶ ሕጻኑንና እናቱን ይዞ ወደ እስራኤል ሀገር ገባ» ማቴ 2-19-21/

ቅዱስ ዮሴፍ ይህንን «.. ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ..» የሚለውን የመልአኩን ቃል የሰማው ቁስቋም በምትባል በግብጽ ባለች ቦታ ነው፡፡

በኋላ በዚህች ቦታ ላይ የእመቤታችን ቤተክርስቲያን ተሰርቶ ቅዳሴ ቤቱ ኅዳር 6 ቀን ከብሯል። ሃያ ሦስተኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ቴዎፈሎስ /384-412 ዓ.ም/ ደግሞ በጌታ እና በእመቤታችን ስደት ወቅት የሆነውን ነገር እንዲገለጥለት ለብዙ ጊዜ ጸሎት ካደረገ በኋላ ህዳር 6 ቀን እመቤታችን ተገልጣለት በጉዞው ወቅት የሆነውን ነገር ሁሉ ነግራዋለች፡፡ ስለዚህ ኅዳር 6 ቀን በሁሉም ምሥራቃውያን አብያተ ክርስቲያናት የእመቤታችን ከስደት የመመለሷ ነገር የሚታሰብበት ሁኗል፡፡

በሀገራችን መስከረም 25 ቀን ዘመነ ክረምት አልፎ መስከረም 26 ቀን ዘመነ ጽጌ ይጀምራል፡፡ ጽጌ ማለት አበባ ማለት ሲሆን ዘመነ ጽጌ ማለት የአበባ ዘመን ማለት ነው፡፡ ዘመኑ አበቦች የሚያብቡበትና ሜዳዎችንና ተራሮችን የሚያስጌጡበት ዘመን ነው፡፡ ፍሬ የተባለ ጌታን ያስገኘች እመቤታችን በአበባ ትመሰላለችና ዘመኑ የጌታንና የእመቤታችንን ነገር በአበባና በፍሬ ለመመሰል የተመቸ ነው፡፡

ስለዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከመስከረም 26 ቀን ጀምሮ እስከ ኅዳር 6 ቀን ድረስ የጌታን እና የእመቤታችን ስደት ታስባለች፡፡

በዚህ ዘመን ቅዱስ ያሬድ እና አባ ጽጌ ድንግል ባዘጋጇቸው ድርሰቶች የጌታችን እና የእመቤታችን ስደት በማኅሌት ይታሰባል፤ ምስጋና እና ልመና ይቀርባል። እነዚህን ለየሳምንቱ በሚዘጋጁት ትምህርቶች እናቀርባቸዋለን፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ስደቱን ለማሰብና በረከት ለማገኘት በርካታ ክርስቲያኖች ዘመኑን በጾም ያሳልፉታል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በማቴዎስ ወንጌል ትርጓሜው /Homilies on the Gospel of Saint Mathew/ ይህንን ስደት አስመልክቶ ያስተማረውን ትምህርት ከዚህ ቀጥለን አቅርበናል፡፡

ሰብአ ሰገልም ከሄዱ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በህልም ለዮሴፍ ተገልጾ፡- ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሳና ሕፃኑን ከእናቱ ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ እስክነግርህም ድረስ በዚህ ተቀመጥ አለው እርሱም ተነስቶ ሕፃኑና እናቱን ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው ይፈጸም ዘንድ ወደ ግብፅ ሄደ። ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ።

ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደተሳለቁበት ባወቀ ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ /ጌታን ለማስገደል በማሰብ / ጌታ በተወለደባት ከተማ በቤተልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን ሕጻናትን አስገደለ፡፡ /ማቴ. 1.13-18/

እዚህ ላይ ሕፃኑን በተመለከተና ሰብአ ሰገልን በተመለከተ ልንጠይቃቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡ ለምን ሰብአ ሰገልም፣ ሕፃኑም /ጌታም/ በዚያው አልቆዩም? ለምን እነርሱ እንደ ተሳዳጅ /fugitive/ በድብቅ ወደ ፋርስ፣ እርሱም ከእናቱ ጋር ወደ ግብፅ ሄዱ?

ከዚህ ሌላ ምን መደረግ ነበረበት? ጌታ በሄሮድስ እጅ መውደቅና ከዚያ አለመገደል ነበረበት? እንዲህ ቢያደርግም ኖሮ ሥጋን መዋሃዱ ግልጽ አይሆንም ነበር፡፡ የክርስቶስ የማዳን ሥራም አይታመንም ነበር፡፡

ሥጋን መዋሃዱን የሚያሳዩ ይህን የመሳሰሉ በርካታ ነገሮች ተደርገው፣ ሥጋን ለበሰ /ተዋሃደ/ መባሉ ተረት /ውሸት/ ነው የሚሉ ካሉ ሁሉን ነገር እንደ አምላክነቱ ብቻ ቢያደርገውማ ከእነዚህ የሚበልጡ ብዙዎች በተሳሳቱ ነበር፡፡

ሰብአ ሰገልንም በፍጥነት የላካቸው አንደኛ ለፋርስ ሰዎች መምሀራን እንዲሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጌታን ለማስገደል ላሰበው ሄሮድስ እየሞከረ ያለው የማይቻል ነገርን መሆኑን አስረድቶ የሄሮድስን እብደት ለማቆምና ንዴቱን አስታግሶ ከከንቱ ድካሙ እንዲያርፍ ለማድረግ ነበር፡፡

ምክንያቱም አምላካችን ጠላቶቹን በግልጽ እና በኃይል ማስገዛት ብቻ ሳይሆን በቀላል እና ትንሽ በሚመስሉ ነገሮች ማሳመንም፣ ያውቅበታል፡፡

ለምሳሌ ግብጻውያንን በግልጽ /በኃይል/ ንብረታቸውን ለእስራኤል እንዲያስረክቡ ማድረግ ሲችል እርሱ ግን በጥበብ ያለ ጦርነት ይህንን እንዲያደርጉ አድርጎአቸል፡፡ ይህም አድራጎቱ ከሌሎቹ ተአምራት ባልተናነሰ ሁኔታ በጠላቶቹ ዘንድ የሚፈራ አድርጎታል፡፡

ለምሳሌ ፍልስጤማውያን ታቦተ ጽዮንን ማርከው በመውሰዳቸው በተቀጠቀጡ ጊዜ የሀገራቸውን ጠቢባን ከእግዚአብሔር ጋር ለመዋጋት እንዳይሞክሩ በነገሯቸው ጊዜ ከሌሎች ተአምራት ጋር ይህንን እግዚአብሔር በሥውር የሠራውንም ሥራ አንስተውታል፡፡ በግልጽ ከተደረጉት የተለየ አድርገው አላዩትም፡፡ 1ኛ ሳሙ. 6-6

በዚህ ጊዜም የተደረገው ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ደም የጠማውን ነፍሰ ገዳይ ሊያስደንቅ የሚችል ነገር ነበር፡፡ ሄሮድስ ሊያስብ የሚገባው እንዲህ ነበር፡፡ ሰብአ ሰገል እንደካዱት፣ እንደተናቀና መሳቂያ መሳለቂያ እንደሆነ ባወቀ ጊዜ መደንገጥ ትንፋሹ መቆም ነበረበት፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ካላሻሉት /ካላስተካከሉት/ ግን እርሱን ከጥፋቱ ለመመለስ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ያደረገ እግዚአብሔር በእርሱ ጥፋት ሊጠየቅ አይችልም፡፡ ሄሮድስ ከዚህ በኋላ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ ያደረገው የእብደቱ ብዛት እነዚህ ሁሉ እውነተኛ ግልጽ ነገሮች እንዲያሳምኑት ስላላደረገ ነው፡፡ ስለዚህ ከጥፋቱ መመለስ አልቻለም፡፡ በክፋቱ ስለ ቀጠለበትም ስለ ሞኝነቱ የከፋ ቅጣት ተቀብሏል፡፡

ሕፃኑ ለምን ወደ ግብጽ ሄደ? የመጀመሪያውን ምክንያት ወንጌላዊው ራሱ በግልጽ ይነግረናል፤ «ልጄን ከግብጽ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብጽ ሄደ» /ማቴ. 1-15/

ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ድርጊት ለዓለም መልካም ተስፋ ተሰብኳል፡፡ በዚያን ጊዜ በዓለም ካለው ቦታ ሁሉ በከፋ ሁኔታ ባቢሎን /ፋርስ/ እና ግብጽ በእምነተ ቢስነት /በአምላክ አልባነት/ ነበልባል ተቃጥለው ነበር፡፡ እርሱም ከመጀመሪያው ሁለቱንም እንደሚያስተካክል ምልክት ሰጥቶ ሰዎችን ማዳኑ /ስጦታዎቹ/ ለዓለሙ በሙሉ እንደሆኑ አውቀው በተስፋ እንዲጠብቁ አደረጋቸው፡፡ ለዚህም ወደ አንዱ /ባቢሎን፣ ፋርስ/ ሰብአ ሰገልን ላከ፣ ሌላውን /ግብጽን/ ራሱ ከእናቱ ጋር ጎበኘ፡፡

ከዚህም ሌላ በዚህ የምንማረው ሌላ ትምህርት አለ፤ ከፍ ያለ ጽናት ሊኖረን እንደሚገባ፡፡ ይህ ምን ዓይነት ነው? ክፉ ሃሳብ /ተንኮል/ እና ክፉ ድርጊት ገና በመጠቅለያ ካለበት ጊዜ ጀምሮ በእርሱ ላይ እንደሆነ ተመልከቱ፡፡ በልደቱ ጊዜ መጀመሪያ ክፉ ነፍሰ ገዳይ፣ ተነሳበት ከዚያም ስደት እና ሀገርን ትቶ መሄድ ተከተለ፡፡ ያለ ምንም ጥፋትና በደል ከቤቷ እንኳን ርቃ ተጉዛ የማታውቀው እናቱ ወደ አረመኔዎች /barbarians/ ሃገር ተሰደደች፡፡ አስጨናቂና አስቸጋሪ የሆነ ረጅም ጉዞ እንድታደርግ ታዘዘች፡፡ ይህንን የሰማ ሰው መንፈሳዊ አገልግሎት ሲፈጽም አስጨናቂ ችግሮችና ህመሞች ቢደርሱበትና ህመሞች ቢያጋጥሙት መሸበር የለበትም፡፡

«የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ስለፈጸምኩ መሸለም መከበርና ታዋቂ መሆን ሲገባኝ ለምን ይህ ሆነ?» ማለትም የለበትም፤ ነገር ግን ሁላችንም ይህንን እንደ ምሳሌ ወስደን ሁሉን ነገር በደስታ መቀበል አለብን፡፡ መንፈሳዊ ነገሮች ባሉበት ሁሉ ተቃዋሚ እንደማይጠፋ እና የመንፈሳዊ ነገሮች ሂደትም ይህ መሆኑንም መረዳት አለብን፡፡

ቢያንስ ይህ ነገር የሆነው በሕፃኑና በእናቱ ብቻ ላይ ሳይሆን በሰብአ ሰገልም ላይ መሆኑን እናስተውል፡፡ እነርሱም እንደ ተሳዳጅ /fugitive/ ሆነው በምስጢር እንዲሸሹ ሆነዋል፡፡

ሌላም አስደናቂ ነገር ተመልከቱ፡፡ የእግዚአብሔር ሐገር፣ የተስፋ ምድር የተባለችው ፍልስጤም በጌታ ላይ የተንኮል መረብ /ሤራ/ ስትዘረጋ የኀጢአትና የጣኦት አምልኮ ሀገር የሆነችው ግብጽ ደግሞ ተቀብላ አዳነችው፡፡

ጌታችን በእግረ ሥጋ በተመላለሰባቸው ዘመናት ያደረጋቸው አብዛኞቹ ነገሮች ወደፊት ሊመጡ ላላቸው ነገሮች ትንቢት ናቸው፡፡

ዮሴፍ ጌታንና እናቱን ይዞ ወደ ግብጽ እንዲሄድ በመልአክ ታዘዘ፡፡ ግብጽ በሥፋት ጣኦት የሚመለክባት ሀገር ነበረች፡፡ ይህም በኋላ ክርስትና በአምልኮት ባዕድ ወደ ነበሩ ህዝቦች /አሕዛብ/ ዘንድ ለመውሰዷ ትንቢት /ምልክት/ነው፡፡ እመቤታችን ጌታን ይዛ ወደማታውቀው ሀገር ስትሰደድ ቤተልሄም /ይሁዳ/ ሄሮድስ ባስገደላቸው ሕፃናት በሰማዕታት ደም ተጥለቅልቃለች፤ የሄሮድስ ጭፍጨፋና ሕፃናቱን መግደሉ ወደፊት ክርስቲያኖች በአይሁድ እጅ ለሚቀበሉት ሰማዕትነት ምሳሌ ነው፡፡

መልአኩ ተገልጦ የተነጋገረው ከእመቤታችን ጋር ሳይሆን ከዮሴፍ ጋር ነበር፡፡ ምን አለው? «ተነሳ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ..» የእመቤታችን በግብረ መንፈስ ቅዱስ መጽነስ ሲነግረው ያለው «እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ» ነበር፡፡ አሁን ግን እጮኛህን አላለውም «የሕፃኑን እናት» አለው እንጂ፡፡ ምክንያቱም እመቤታችን ጌታችንን ከወለደች እና በጌታ ልደት ጊዜ የሆኑትን ነገሮች /ኮከቡን፣ ሰብአ ሰገልን/ ካየ በኋላ ሁሉን ነገር ተረድቶ ተረጋግጦ ነበር፡፡ በቂ ነገር ዓይቶ፣ ባየው ነገር ተረጋግቶ ነበር፡፡ ስለዚህ መልአኩ አሁን በግልጽ ይናገራል «ልጅህን» ወይም «እጮኛህን» አላለም፡፡ «ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሂድ አለው» እንጂ፡፡ የስደቱንም ምክንያት አብሮ ይነግረዋል፤ «ሄርድስ የሕፃኑን ነፍስ ይፈልጋልና፡፡»

ዮሴፍ ይህንን ሲሰማ ቅር አልተሰኘም፤ «ይህን ነገር ለመረዳት ይከብዳል፤ ሕዝቦቹን ያድናቸዋል አላለከኝም ነበር? አሁን ደግሞ ራሱን እንኳን ማዳን አይችልምን? እኛም ከቤታችን ወጥተን ርቀን ለብዙ ጊዜ መሰደድ አለብን አሁን ያለት ነገሮች ከተሰጠው ተስፋ /ቃል/ ጋር ተቃራኒ ናቸው፡፡» አላለም ጻድቅ እና እውነተኛ አማኝ ነበርና፡፡

ምንም እንኳን መልአኩ መመለሻውን ግልጽ ሳያደርግ እስከምነግርህ ድረስ በዚያው ተቀመጥ ቢለውም ስለሚመለሱበት ጊዜ አልተጨነቀም፤ አልጠየቀምም፡፡ ዮሴፍ ፍርሃትም እንኳን አላሳየም፡፡ ሁሉንም ነገር በደሰታ ተቀበለ እንጂ፡፡

ሰውን ወዳጅ የሆነው እግዚአብሔር መከራንና ደስታን በሰዎች ሕይወት ላይ ያመጣል፡፡ በችግር ወይም በደስታ ብቻ አያኖርም፡፡ ነገር ግን ሁለቱንም ችግርን /ሀዘንን/ እና ደስታን /ሃሴትን/ እያፈራረቀ ያመጣል፡፡ አሁንም ያደረገው ይህንኑ ነገር ነው፡፡ ዮሴፍ ድንግልን ጸንሳ ባያት ጊዜ ተጨነቀ፤ ተረበሸ፤ ታወከ፡፡ በዚህ መሃል ግን መልአኩ ተገልጦ ፍርሃቱን አስወገደለት፡፡ ሕፃኑን ተወልዶ ባየ ጊዜም ከፍ ያለ ደስታ ተደሰተ፡፡ ደስታው ብዙም ሳይቆይ አደጋ መጣ፤ በሰብአ ሰገል መምጣት ከተማው ተረበሸ ንጉሡም ከእብደቱና ከክፋቱ የተነሳ የተወለደውን ሕፃን ሊገድል ተነሳ፡፡ ይህ ጭንቀት ደግሞ በደስታ ተተካ ኮከቡና የሰብአ ሰገል ለጌታ መስገድ እጅግ አስደሳች ነበሩ፡፡ ከዚህ ደስታ በኋላም ጭንቀትና ፍርሃት መጣ፡፡ መልአኩ «ንጉሥ ሄሮድስ የሕፃኑን ነፍስ ይፈልጋል፡፡» ብሎ ነገረው፡፡

በዚህ ጊዜ ጌታችን በሕዝብ ፊት ተዓምራት ለማድረግ ጊዜው ገና ነውና መሰደድ አስፈለገው፡፡ ምክንያቱም ገና በልጅነቱ ተአምራትን በአደባባይ /በሕዝብ ፊት/ ቢያደረግ፣ ሥጋን እንደተወሃደ አይታመንም ነበር፡፡

በአንድ ጊዜ ሁሉን ማድረግ ሲችል ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅጸን ያደረው፣ እንደ ሕፃናት ጡትን እየጠባ፣ በጥቂት በጥቂቱ ያደገው፣ ሥራውን እስኪጀምርም ሠላውን ዘመን በዝምታ /በስውር ተዓምራት/ ያሳለፈው፡- የተዋህዶን ነገር እንረዳ ዘንድ ነው፡፡

አይሁድ ትንቢቱን በተመለከተ ጥያቄ ቢያነሱ እና ልጄን ከግብጽ ጠራሁት የተባለው ስለ እኛ ነው ቢሉን ይህ የትንቢት አካሄድ /መንገድ/ ነው እንላቸዋለን፡፡ ብዙ ጊዜ ስለተወሰኑ ሰዎች የተናገረው የሚፈጸመው በሌሎች ነው፡፡ ያዕቆብ ሊሞት ሲል ልጆችን ሰብስቦ በኋለኛው ዘመን ምን እንደሚደርስባቸው ሲነገራቸው እንዲህ ብሎ ነበር፡-

ስምኦንና ሌዊ ወንድማማች ናቸው፤

ሰይፎቻቸው የአመጽ መሣሪያ ናቸው፡፡

ከምክራቸው ነፍሴ አትግባ፡፡

ከጉባኤያቸውም ጋር ክብሬ አትተባበር

በቁጣቸው ሰውን ገድለዋልና

በገዛ ፈቃዳቸው በሬን አስነክሰዋልና፡፡

በያዕቆብ እከፍላቸዋለሁ፡፡ በእስራኤልም እበትናቸዋለሁ፡፡ ዘፍ. 49-7

ይህ ግን በእነርሱ አልተደረገም በልጆቻቸው እንጂ፡፡ በዘፍ. 9-25 ላይ ተጽፎ እንደሚገኘውም ኖህ እንዲህ ብሎ ነበር፡- «ከነአን ርጉም ይሁን ለወንድሞቹም የባሪያዎች ባሪያ ይሁን» ይህ የተፈጸመው በከንአን ሳይሆን በእርሱ ዘሮች ነው፡፡

ይህ መቼ እና እንዴት እንደሆነ በመጽሐፈ ኢያሱ እና በመጽሐፈ ዜና መዋዕል፤ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ እንዲህም ሆነ በዮርዳኖስ ማዶ በተራራማው በቆላውም በታላቁ ባሕር ዳርና ሊባኖስ ፊት ለፊት የነበሩ ነገሥታት ሁሉ ኬጢያዊ፣ አሞራዊም፣ ከነአናዊም፣ ኢያቡሳዊም፣ ይህን በሰሙ ጊዜ ኢያሱንና እስራኤልን ሊወጉ ወጡ፡፡

በዚያም ቀን ኢያሱ ለማኅበሩ በመረጠው ሥፍራ እስከ ዛሬ ድረስ፣ ለእግዚአብሔር መሠዊያ እንጨት ቆራጮች ውኃም ቀጂዎች አደረጋቸው፡፡ /ኢያ. 9-1-27/

1ኛ ዜና.8-7 ሰሎሞንም ኬጤያውያንንም፣ አምራውያንንም፣ ፌርዜያውያንንም ኢያቡሳውያንንም የቀሩትን ከእስራኤል ወገን ያልሆኑትን ሕዝብ ሁሉ... ገባሮች አድርጎ መለመላቸው፡፡

ይስሐቅ «ለወንድሞችህ ጌታ ሁን፡፡ የእናትህም ልጆች ይስገዱልህ»፡፡ ብሎ ያዕቆብን የመረቀው ምርቃት የተፈፀመው በእርሱ ሳይሆን በልጆቹ ነው፡፡ ዘፍ. 27-19

ስለዚህ እርሱ ባይወለድ ኖሮ፣ ትንቢቱ ፍጻሜውን አያገኝም ነበር፡፡ ወንጌላዊውም ያለውን አስተውሉ፡- «ይፈፀም ዘንድ፡፡» ይህም እርሱ ባይመጣ አይፈፀምም ነበር ማለት ነው፡፡

በዚህኛውም ጊዜ የተደረገው /የሆነው/ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር ነው፡፡ መጀመሪያ ለእስራኤል የተነገረው ነገር በኋላ በጌታ ተፈጽሟል፡፡ ደግሞስ የእግዚአብሔር እውነተኛ ልጅ ሊባል የሚችለው የትኛው ነው? ጥጃን ያመለከና ለቤልሆር ልጆቹን የሰዋ? ወይስ በባሕሪው ልጅ የሆነና የወለደው አባቱ «የምወደው ልጄ» ብሎ የሚያመሰግነው?

ከዚህም ሌላ /ግብጽ መሄዳቸው/ እመቤታችን ከፍ ያለ ክብር ያላት እንደሆነች እንዲታወቅ ተደርጓል፡፡ ህዝቡ የሚመኩበትን ከእግዚአብሔር ያገኙትን ስጦታ እርሷም ለራሷ አግኝታለችና፡፡ ማለትም፣ እነርሱ ከግብጽ በመውጣታቸው /ከስደት በመመለሳቸው/ ይመኩና ይኮሩ ነበር፡፡ ይህንኑ የሚመኩበትን ነገር ለእመቤታችንም ስጣት፡፡

ያዕቆብና ህዝበ እስራኤል ወደ ግብጽ በመሄዳቸውና ከዚያም በመመለሳቸው የእርሱን ግብጽ ሄዶ መመለስ ምሳሌ እየፈጸሙ ነበር፡፡ እነርሱ ግብጽ የሄዱት በረሃብ /በድርቅ/ የመጣ መሞትን ለማምለጥ ነበር፡፡ እርሱ ደግሞ በተንኮል መሞትን ለማምለጥ ነው፡፡

እነሱ /ህዝበ እስራኤል/ ግብጽ መሄዳቸው ከረሃቡ /ከድርቁ/ ተርፈዋል፡፡ እርሱ ግን እዚያ በመሄዱ በኪዳተ እግሩ /በእግሩ በመርገጥ/ ምድሪቱን ቀድሷታል፡፡

በዚህ ራሱን ዝቅ በማድረጉ መሀልም ግን የአምላክነቱ ማሳያዎች /ምልክቶች/ ተገልጸዋል፡፡ ሰብአ ሰገልና እርሱን ለማምለክ በኮከብ እየተመሩ መጡ፤ አውግስጦስ ቄሳርም የሕዝብ ቆጠራ አዋጅ በማወጅ ልደቱ ቤተልሔም እንዲሆን አገለገለ፤ በግብጽም በርካታ ተዓምራት ተደርገዋል፡፡

አሁን ወደ ግብጽ ብንሄድ በረሃው ከማንኛውም የአትክልት ስፍራ የተሻለ ሥፍራ ያማረ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመላእክት አምሳል ያመሰግኑበታል የሰማእታት ብሔር፣ የደናግል በአት፣ የሰይጣን አገዛዝ ድል የተመታበትና የክርስቶስ መንግስት ደምቆ የሚያበራበት ቦታ ነው፡፡

በትምህርተ ሃይማኖታቸው /doctrine/ ካላቸው ትክክለኛነት በተጨማሪ፣ በህይወታቸውም ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያሉ፡፡ ያላቸውን ሁሉ ትተው ራሳቸውን ከዓለም ካገለሉና ለዓለሙ በሙሉ ከተሰቀሉ በኋላ በድጋሚ የተቸገሩትን ይረዱ ዘንድ የጉልበት ሥራ ይሠራሉ፡፡

ስለሚጾሙና ብዙ ጊዜ በተመስጦ ስለሚያሳልፉ፤ ቀናቱን /ጊዜን/ ሥራ በመፍታት /ቦዝነው/ ማሳለፍ ተገቢ ነው ብለው አያስቡም፡፡ ስለዚህም ቀኑን በጸሎት ሌሊቱንም በዝማሬና በትጋት ያሳልፉታል፡፡ ከዚህም የሐዋርያውን አሰር ይከተላሉ፡፡

«ከማንም ብር ወይም ወርቅ አላስፈለገኝም እነዚህ እጆቼ በሚያስፈልገኝ ነገር ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት እንዳገለገሉ እናንተ ታውቃላችሁ፡፡ እንዲህ እየደከማችሁ ድውያንን ልትረዱና፣ «እርሱ ራሱ ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብጽዕ ነው» የሚለው የጌታን የኢየሱስን ቃል ልታስቡ ይገባችሁ ዘንድ አሳየኋችሁ፤» ሐዋ. 10-34 ይህንን የሐዋርያውን ቃል ሲሰሙ በበረሃ ያሉት የግብጽ መነኮሳት እንዲህ ይላሉ፡- «እርሱ /ሐዋርያው/ በእግዚአብሔር ቃል እንዲመግባቸው ብዙዎች እየጠበቁት የእጅ ሥራ ይሠራ ከነበረ፣ መኖሪያችንን በገዳም፣ በዱር፣ በበረሃ ያደረግን፣ የከተማ ጾር /ፈተና/ የቀረልን እኛማ ከጸሎታችንና ከተመስጦአችን የተረፈንን ጊዜ ለተመሳሳይ ሥራ ልናውለው ምን ያህል ይገባናል)!»

እኛም ራሳችንን እንመርምር ሀብታምም ድሃም የሆንን እነዚህ መነኮሳት ከሰውነት /እጅና፣ እግር/ በስተቀር ምንም የሌላቸው ሲሆኑ የተቸገሩትን ለመርዳት እንዲህ ከወጡና ከወረዱ የተረፈንን እንኳን ለእነዚህ ሰዎች /ችግረኞች፣ ድውያን/ የማንሰጥ እኛ ለዚህ አድራጎታችን ምን ምክንያት፣ ምን ማስተባበያ ማቅረብ እንችላለን፡፡

ታላቁን አባት ቅዱስ እንጦንስን እናስታውስ፡፡ ይህ ሰው የተወለደው ፈርኦን በተወለደበት ሀገር ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ምክንያት እነርሱን አልመሰለም፡፡ የነበረው ሰማያዊ ራእይ ስለጠበቀው እግዚአብሔር በሚወደው መልኩ ህይወቱን አሳልፏል፡፡ ከጽድቁ የተነሳ ከእርሱ በኋላ የሚመጡ መነኮሳት ምን ዓይነት እንደሚሆኑ እግዚአብሔር አሳይቶታል፡፡

ጻድቁ እንጦንስን ታሪክ ማንበብና ማድነቅ ብቻ ሳይሆን በሕይወት መተርጎምም ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን አለመበርታት ቦታን፣ አለመማርን፣ የአባቶችን መርገም... ምክንያት አናድርግ፡፡
ነገሮችን በማስተዋል ስንመለከት እነዚህ ሁሉ ነገሮች ለእኛ መሰናክል መሆን አይችሉም፡፡ አብርሃም ጣኦት አምላኪ አባት ነበረው /ኢያ. 24-2/ ነገር ግን የአባቱን ክፋት አልወረሰም፣ የሕዝቅኤልም አባት አካዝ ኀጢአተኛ ሰው ነበር፡፡ ሕዝቅያስ ግን የእግዚአብሔር ወዳጅ ነበር፡፡

ዮሴፍም በግብጽ ሆኖ ራሱን በትምህርት አስጊጧል፡፡ ሦስቱ ሕፃናትም በባቢሎን ቤተመንግስት ሆነው ታላቅ ራስን መግዛት አሳይተውናል፡፡ ሙሴም በግብጽ ነበር፣ ቅዱስ ጳውሎስም በዓለም ነበር፤ ነገር ግን እነዚህን ሁሉ ያሉበት ቦታና ሁኔታ ከጽድቅ ጉዞአቸው አላደናቀፋቸውም፡፡


ዘመነ ጽጌ በዲ/ን ዳንኤል ክብረት

                                                        

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!

ምንጭ፦ ማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ

No comments:

Post a Comment