Tuesday, December 31, 2013

ታኅሳስ ፳፪ - ብስራተ ገብርኤል (“ትጸንሲ”)


በቤተ ክርስቲያናችን አስተምሮ መሰረት ታኅሣስ 22 መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ጌታን እንደምትፀን የአበሰረበት ቀን ነው።  
‹‹እንዘ ትፈትል ወርቀ ወሜላተ ወሪዳ ምድረ ቆላ ገብርኤል መጽአ እንዘ ይረውጽ በሰረገላ ክንፎ ክንፎ ክንፎ ጸለላ ተፈስሒ ተፈስሒ ለድንግል ይቤላ፤ ወደ ቆላው ምድር ወርዳ እመቤታችን ወርቅን ከሐር ጋር አስማምታ እየፈተለች ሳለች መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በሰረገላ እየሮጠ መጣ፣ ክንፉንም እያማታ እየሰገደ ድንግል ሆይ ደስ ይበልሽ አላት›› እንዲል ደራሲው አንድም “ተፈሥሒ ፍሥሒት ኦ ምልዕተ ጸጋ፤ ጸጋን የሞላብሽ ሆይ ደስ ይበልሽ” ሉቃ 1፡28 “ስብሃት ለኪ ማርያም እሙ ለፀሃየ ጽድቅ ለአብ ሙሽራው ለወልድ ወላዲቱ ለመንፈስ ቅዱስ ጽርሃ ቤቱ ተፈስሂ ደስ ይበልሽ” እንዳሉ አበው፡፡
እመቤታችን የብፅዓት ልጅ ናት። ሶስት ዓመት ሲሆናት አባት እናቷ ለካህን ሰጥተዋታል፤ ካህናትም በቤተ መቅደስ ከመካነ ደናግል አስገብተዋት ፲፪ ዓመት በቅዱስ ፋኑኤል አማካኝነት ኅብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ሰማያዊ እየመጣላት ያን እየተመገበች መላእክት እየጎበኟት ኖራለች። ፲፭ ዓመት ሲሆናት ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ጌታን እንደምትወልድ በዚህ ቀን ብስራቱን ነገራት። ውሃ ቀድታ ስትመለስ የጠተማ ውሻ እያለከለከ ሲመጣ በወርቅ ጫማዋ ለዛ ለተጠማው ውሻ ውሃ ስታጠጣ አብሯት የነበሩ ሴቶች ማድጋሽን አጎደልሺው፤ ቀድቼ እሞለዋለሁ እንዳትይ ጉድጓዱ ጥልቅ ነው መቅጃም የለሽም አሏት። “ውሃ የሚገኘው ከወደላይ ነው እንጂ ከወደታች ነውን ፍጥረቱን ያጠጣ ጌታ ይሞላልኛል” አለቻቸው። በተዓምራትም ሞልቶላታል። “በዚህ ዘመን አምላክ ከድንግል ይወለዳል ይላሉ ካንቺ ይሆን?” ብለው ዘበቱባት። ወዲያ ከወደኋላዋ ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ “ትጸንሲ” አላት። ዞር ብትል አጣችው። አባቴ አዳምን እናቴ ሔዋንን ያሳተ ጠላት ይሆናል ብላ ሄደች።
ከቤት ደርሳ ማድጋዋን ስታስቀምጥ ዳግመኛ “ትጸንሲ” አላት። ይህ ነገር ደጋገመኝ እንዲህ ያለውን ነገር ቤተ መቅደስ ሄደው ሊረዱት ይገባል ብላ ወደ ቤተ መቅደስ ሄዳ በወርቅ ወንበሯ ተቀምጣ ከደናግለ እስራኤል ጋር የተካፈለችውን ወርቅና ሐር እያስማማች ስትፈት ቅዱስ ገብርኤል ተገልጾ “ተፈሥሂሒ ፍሥሒት ኦ ምልዕተ ጸጋ፤ መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ። ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት። እርስዋም ባየችው ጊዜ ከንግግሩ በጣም ደነገጠችና። ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው? ብላ አሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት። ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም። ማርያምም መልአኩን። ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት። መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። እነሆም ዘመድሽ ኤልሳቤጥ፥ እርስዋ ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፥ ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና። ማርያምም። እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለች። መልአኩም ከእርስዋ ሄደ።” ሉቃስ ፩፡፳፰-፴፰ እንዲል ወንጌል።
“ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ፤ ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም፤ በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ፡፡(አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም)
አበው አባቶችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስተቲያን እንሚያስረዱንና እንደሚያስተምሩን መልአኩ ብስራቱን የነገጋት መጋቢት 29 ቀን በዕለተ እሁድ ከቀኑ ሦስት ሰዓት ላይ ነው። ታዲያ ዛሬ ለምን እናከብረዋለን ለሚለው ጥያቄ፤ ምንጊዜም ወርሃ መጋቢት ታላቁ ዓቢይ ጾም የሚውልበት ወር ነው፤ በዚህ በዓቢይ ጾም ደግሞ ሐዘን፤ ለቅሶ፤ ጾም፤ ጸሎት እንጂ ደስታ፤ ፌሽታ እልልታ፤ ጭብጨባ የለም። ፍጹም የሐዘን ወራት ነው፤ ታቦት አውጥቶ በዓል ማክበርም ስህተት ነው። ፍትሃ ነገስት አንድምታ አንቀጽ 15 ተመልከት ፤ ታዲያ ቅዱሳን አባቶቻችን እንደዚህ ዓይነት ስርዓት ሰሩ፤ የመጋቢት 27 ስቅለቱን ጥቅምት 27 ቀን እንዲሁም የመጋቢት 5 አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ዕረፍት ቀን ወደ ጥቅምት 5 ቀን ዞሮ እንዲከበር አደረጉ፡፡ የመጋቢት 29 ብስራቱን ደግሞ ታህሳስ 22 ቀን ዞሮ እንዲከበር ያደረገው ታላቁ አባት የጥልጥልያ ኤጲስ ቆጶስ ደቅስዮስ ይባላል። ደቅሲዮስ በተጨማሪም የእመቤታችንን ተዓምራቶቿን የጻፉ ታላቅ አባት ነው። በእመቤታች ፍቅር ልቡ የነደደ ታላቅ ጻድቅም ነው። የእመቤታችንን ታአምራቷን የሚናገር መጽሐፍ የሰበሰበ አባት ነው፡፡ የጌታን ልደት ከመከበሩ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ብስራቱ መከበር አለበት ብሎ ስርዓት ሰራ። አገሬውንም ሰብስቦ ታላቅ የደስታ በዓል አደረገ። እመቤታችን ተገለጸችለት ወዳጄ ደቅስዮስ ባንተ ደስ አለኝ። እንዳከበርከኝ እኔም አከብርሃለው አለችው። ሰማያዊ ልብስና ሰማያዊ ወንበር ሰጠችው ይህችን ልብስ ካንተ ሌላ ማንም አይለብሳትም፤ ይህችንም ወንበር ካንተ ሌላ ማንም አይቀመጥባትም አለችው። የዚህ ታላቅ አባት ዕረፍቱ ታህሳስ ፳፪ በዛሬዋ ቀን ነው። ከእርሱ በኋላ ሌላ ኤጲስ ቆጶስ ተሾመ ልብሱን እለብሳለው በወንበሩም እቀመጣለው አለ፤ ተው ይቅርብህ እመቤታችን እንዲህ ብላ ተናግራለች ይሉታል፤ እርሱም ሰው እኔም ሰው እርሱም ኤጲስ ቆጶስ እኔም ኤጲስ ቆጶስ ብሎ በትዕቢት ልብሱን ለበሰው። በወንበሩም ተቀመጠ ክፉኛ አወዳደቅ ወደቀ ሞተም። ይህን ያዩ እመቤታችንን በጣም ፈሯት ይላል ተዓምረ ማርያምን ተመልከት፡፡ ደቅስዮስ ሰርቶልን ያለፈውን ስርዓት ቤተክርስቲያን ተቀብላ ይኸው ዛሬም ድረስ ታከብረዋለች። በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ ብስራተ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ታቦተ ህጉ ወጥቶ በደማቅ ተከብሮ ይውላል፡፡ 
ከእመቤታችን ከወላዲተ አምላክ እንዲሁም ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፡ አሜን!

Sunday, December 29, 2013

ከሳውዲ አረቢያ በግፍ ተገፍተው ለተመለሱ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ምን እየተደረገ ነው?

                                     ፎቶ፡ ምሳ ግብዣ በማኅበረ ቅዱሳን

የተለያዩ የዜና ምንጮች እንደገለጹት ከሳውዑዲ አረቢያ በግፍ ተገፍተው የተመለሱ ኢትዮጵያን ቁጥር ከመቶ በላይ ደርሰዋል። አሁን በዋናነት ማንሳት የፈለኩት ስለ ቁጥር መጠናቸው ትክክለኛነት፣ ያሳለፉትን ስቃይና መካራ፣ ማን በአስቸኳይ ደረሰላቸው ወይም በምን መልኩ ትውልድ ሀገራቸው ተመለሱ የሚለውን የትናት ገሀዳዊ እውነታ መተረክ ሳይሆን ለእነዚህ ወገኖቻችን ምን የተደረገላቸው ነው የሚለውን ቄ አዘል ሃሳቤን ለማካፈል ነው።
ለእነዚህ ለተጎዱ ወገኖቻችን በህብረትና በግል የውስጥ ሃዘናችንን በእንባ፣ በልቅሶ፣ በጩኸት የዓለም ጀሮ በቃኝ እስኪል ድረስ ገልጸናል፤ ተናግረናል፤ ጽፈናልም። መቼም ቢሆን ሀዘኑና ድርጊቱ ከልባችን አይጠፋም። ይህ በራሱ አንዱ የአንድነታችን መገለጫ ነው። ይህን አንድነታችንንና ሃዘናችንን ወደ ተግባር ቀይረን ማሳየት ብንችል የበለጠ ለእኛ ለህሌናችን ውስጣዊ እርካታ፤ ለተጎዱ ወገኖቻችን ደግሞ መጠገኛ/መቋቋሚያ ይሆናቸዋል።
በእርግጥ ድርጊቱ ከተፈጸበት ጊዜ ጀምሮ በተለያየ መልኩ ከግለሰብ እስከ ተለያዩ ማህበራት ድረስ እርዳታ ለመስጠት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። ይህ ጥረት ግን ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ሁላችንም ልዩ ትኩረት ልንሰጥበት የሚገባ ተግባር ነው። እንዴትና በምን መልኩ ለወገኖቻችን ልንደርስላቸው እንደ ሚገባ ግልጽ ታማኒነት ባለው መልኩ እንቅስቃሴያችንን ማስኬድ ይኖርብናል። ለዚህ ተግባር ግልጽነትና አንድነት ባራዊ የሆነ ሥራ ለመስራት በእጅጉ ያስፈልጉናል።

  ሀ. አንድነት፦ ለዚህ በጎ ተግባር ድጋፍ ለማድረግ ሰው መሆን ብቻ በራሱ በቂ ነው። ችግሩን በትክክል ለተገነዘበ ሰው ሌላ የተለየ ቅስቀሳ አያስፈልገውም በተለይ ደግሞ  በውጭው ዓለም ያለ ሰው በአንድም በሌላም የችግሩ አካል በመሆኑ ለዚህ ተግባር ግንባር ቀደም ድጋ ሰጭ እንደሚሆን እርግጠኛ ሁኖ መናገር ይቻላል። አስተባባሪ አካላት ግን መንግስት፣ ተቃዋሚ፣ ጾታ፣ ብሄር፣ ሃይማኖት፣ ድርጅት፣ ማህበር የውጭ የውስጥ ብሎ ልዩነት ሳይፈጥሩ አንድማስተባበር ከቻሉ በቀላሉ ተጎጅዎችን ማቋቋም የሚቻልበትን መስመር መዘርጋት ይቻላል።  ይህ ችግር ሃገራዊ እንጂ የአንዱን ቡድን ብቻ መለከ አይደለም። ቢሆንም እንኳ ከጠባብነት የአስተሳሰብ ጎራ ተላቀን ለዚህ በጎ ተግባር አንድነት መፍጠር ይኖርብናል። ይህን ችግር ምክንያት አድርጎ ፖለቲካዊም ሆነ ሌላ የተለየ ጥቅም ለማግኘት መሞከር ሰባዊ ት ወደ እንስሳዊነት ባህሪ የመቀየርን ያክል አሳፋሪ ይሆናል  ስለዚህ ሁላችንም በተለይ አስተባባሪ አካላት በመካከላችን የቱንም ያህል ልዩነት ቢኖርም ለዚህ አንገብጋቢ ተግባር ከማነኛውም ሰው ጋር በቅንጅት ድጋፍ ለማድረግ መወሰን እና መስራት ይኖርብናል። 
  ለ. ግልጽነት፦ በዚህ በአለንበት ዘመን የቱንም ሥራ ለመስራት ግልጽነት ያስፈልጋል። ግልጽት የጎደላቸው ተግባሮች ሁሉ ውጤታቸው እዚህ ግባ የባይባል ነው። ለዚህ በጎ ተግባር ገንዘብ ከመሰብሰብ ጀምሮ እንዴትና በምን መልኩ ለተቸገሩ ወገኖቻችን ሊደርሳቸውና ምን አይነት ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደታሰበ በግልጽ ለእኛንዳንዱ ህብረተሰብ ር ያስፈልጋል ግልጽ መሆናችን 3 ጥቅሞች አሉት። አንድ ድጋፍ የሚሰጡ ሁሉ ራቻከጥርጣሬ እና ከሌላ እይታ አልፈው የተቻላቸውን ያክል ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ያደርጋል። ሁለት ለአስተባባሪዎችም ሆነ ገንዘብ ለሚሰበስቡት ሁሉ ታማኝነት ያገኛሉ። ነጻ ሁነው ማንኛውንም ሰው ለዚህ ድጋፍ ተባባሪ እንዲሆን መጠየቅ ይችላሉ። ሦስት ድጋፍ የሚደረግላቸው ወገኖች የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። ምክንያቱም በግልጽነት የምንሰበስበው የገንዘብ መጠን የተሻለ እና የታሰበውን ፕሮጀክት መሸፈን የሚችል በቂ ገንዘብ መሰብሰብ ስለሚቻል ነው። ግልጽነትን ካለምክንያት አላነሳሁትም ለዚህ ድጋፍ ተብሎ ር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም የተለያዩ ተቋማትና ግለዘቦች ገንዘብ ለመሰብሰብ በመቀሳቀላይ ናቸው። እየሰበሰቡ ያሉም አሉ ነገር ግን ገንዘብ ከመሰብሰብ ውጭ እንዴት፣ በምን መልኩ እና ግንኙነቱ ከማን ጋር የሚሉ መሰረታዊ ጥያቂዎችን በግልጽ ለማወቅ አልተቻለም። ስለዚህ ለእነዚህ እና ለመሳሰሉት ጥያቄዎች ግልጽነታችን በጣም አስፈላጊ ስለሚሆን እያንዳንዷን እንቅስቃሴ በግልጽነት ማካሄድ ትን መስመር ዘርግቶ መንቀሳቀስ ከምንም በላይ ትኩረት ልንሰጥበት የሚገባ ተግባር ነው።

ከላይ ያነሳኋቸውን መሰረታዊ ነገሮች አንድትን እና ግልጽነትን ሰንቀን ድጋፋችን ዘላቂነት እንዲኖረው ኃላፊነቱን ደረጃ በደረጃ መውሰድ ይኖርብናል።
1.      መንግሥት፦  ምንም እንኳ አስተዳደራዊም ሆነ ሌሎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች በአገሪቱ ውስጥ ቢሰፍኑም ለዚህ ችግር ግንባር ቀደም መፍትሄ ሊሰጥ የሚገባው አካል መንግሥት ነው። ይህን ማድረግ አልነበረበትም? የችግሩ መንስኤ መንግሥት ራሱ ነው? እና ሌሎችንም ጥያቄዎች በትችት መልክ ሁልጊዜ ማንሳቱ ለውጥ ሊያመጣልን አልቻለም። በእርግጥ በተለያየ መልኩ አቅጣጫ የሚያሳዩ ኢትዮጵያውያዊ ሙህራን በርካታ ናቸው። ምናልባት አብዛኞቹ ከትችት ስለሚጀምሩ ሃሳባቸውን ላለመቀበል ምክንያት ሊሆን ይችል ይሆናል። ሆኖም ግን ጠቃሚ ሃሳቦችን መውሰድ ደግሞ ብልህነት ነው።
መንግሥት እንደ መንግሥት ካሰበ በግፍ ወደ ሃገራቸው ለተመለሱ ወገኖች ዘላቂነት ባለው መልኩ ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል። በአጭሩ ሦስት ተግባራትን መከተል ቢቻል ዘላቂነት ያለው ድጋፍ ማድረግ ይችላል።
Ø  ወደ አገር የተመለሱትን ስም ዝርዝርና በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉበትን አድራሻ መያዝና ስለ እያንዳንዱ በቂ መረጃ መሰብሰብ(የት/ት ደረጃ፣ የሥራ መስክ፣ የቤተሰብ ሁኔታ፣ ፍላጎት)። ከምንም አድሎአዊነት ነጻ ሁኖ በትክክል እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ማወቅና መለየት።
Ø   በሰበሰብነው መረጃ መሰረት ሁሉን ሊያካትት የሚችልና ዘላቂ ፕሮጀክት መቅረጽ። ለምሳሌ፦ ለውጭ ባለ ሃብቶች የምንሰጠውን መሬት ማለትም የእንስሳት ልማት፣ የአበባ ልማት፣ እና የተለያዩ የንግድ ሥራወችን  ዘመናዊ በሆነ መልኩ ሊሰሩ የሚችሉበትን እድል ማመቻቸት። እንዲሁም መማር ለሚፈልጉ ነጻ የትምህርት እድል መስጠት።
Ø    ፕሮጀክቱ ዘላቂነት እንዲኖረው እና ትርፋማ ሁኖ በትክክል ለተፈለገው ዓላማ እንዲውል የባለሙያ ድጋፍና ክትትል እንዲያገኝ ማድረግ። 

2.   ማህበራትና ተቋማት፦ ሊታይና ሊቆጠር የሚችል ፕሮጀክት ቀርጾ ገንዘብ መሰብሰብ። ፕሮጀክቱ የት፣ ለእነማንና በምን መልኩ ሊተገበር እንደሚችል ይፋ ማድረግና ገንዘብ ሊገኝ ከሚችልባቸው የመንግሥትም ሆነ የግል ድርጅቶች፤ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ መሰብሰብ። ለዚህ ተግባር ይመለከታቸዋል ከምንላቸው ድርጅቶች ጋር በቅንጅት መስራት ድጋፋችንን ዘላቂነት እንዲኖረው ያደርግልናል።
በተለይ በውጭው ዓለም ገንዘብ ከመሰብሰብ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግ በተለያየ መልኩ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። ይህን እንቅስቃሴ ተግባራዊ ለማድረግ አገር ውስጥ ከአሉ ድርጅቶች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ማድረግ እና በውጭ በተለያዩ  ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ዘላቂነት ባለው መንገድ የሰባዊ መብት ጥሰትን ማስቆም የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ትልቅ ተግባርና ሃላፊነት ነው።

3.   ባለሙያዎች፦ ለዚህ በጎ ተግባር ዘላቂነት ያለው ፕሮጀክት ከመቅረጽ ጀምሮ ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ በራስ ተነሳሽነት ለሚመለከታቸው አካላት ሃሳባችንን ማካፈል። ሁሉም የሙያ ዘርፍ በተለያየ መልኩ ስለሚያስፈልግ እኔ አላስፈልግም ሳንል ለወገኖቻችን ድጋፍ መስጠት ከቻለን በቀላሉ ለችግሩ መፍትሔ ማግኘት የሚቻልበትን አማራጮች ማስቀመጥ ይቻላል።

በአጠቃላይ በግፍ ወደ ሃገራቸው ለተመለሱትም ሆነ በዓለም ላይ ኢ_ሰባዊ ድርጊት የሚፈጸምባቸውን ኢትዮጵያውያንን ለመታደግ የእያንዳንዳችን ድርሻ ወሳኝ መሆኑን ተረድተን ዜጋዊ ኃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል። የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ መረጃ ከመስጠት ጀምሮ ኢ_ሰባዊ ድርጊቶችን ማስቆም የሚቻልበትን መንገድ ማመቻቸት ጊዜ የማይሰጠው ተግባር መሆን ይኖርበታል የሚል ጽዕኑ እምነት አለኝ። ኮሚቴ ማቋቋም ብቻ ትርጉም የለውም። እንዲህ ሰሩ ለመባል ሳይሆን ተግባራዊ ስራ ሰርተን አገራዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ።   


Saturday, December 7, 2013

ኔልሰን ማንዴላ

ይህንን ፎቶ ሳነሳ ሁለት አይነት ስሜት ተሰማኝ። የመጀመርያው የኩራት፣የደስታ ስሜት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሃዘን ስሜት ተሰማኝ። ብዙ አፍሪካውያን በዓለም በበርካታ ስራዎች የሚታወቁ ሰዎች እንዳሉ ቢታወቅም እንደ ኔልሰን ማንዴላ ግን በመሪነት ደረጃ ለአለም ምሳሌና አርያ የሆነ የለም። በዚያ ላይ ከብዙ ስቃይና መከራ ፣ እንግልትና እስር በኋላ የሰላም፣ የነጻነት፣ የአንድነት፣ የይቅርታ አባት መሆን በእጅጉ ታላቅነት ነው። የበደሉትን፣ያሰቃዩትን፣ አንተ ጥቁር ሰው አይደለህም ከነጮች ጋር አብረህ ልትኖር፣ ልትማር ፣ በአንድ ባስ ውስጥ ልትጓዝ አይገባይህም ብለው አዋጅ አውጀው በመላ ጥቁር ደቡብ አፍርካውያን ላይ ከባድ ወንጀል የፈጸሙትን ለሰላምና ለአንድነት ሲል በይቅርታ እንዲታለፉ ያደረገ ታላቅ የይቅርታ አባት መሆኑን ዓለም ሁሉ በአንድ አፍ ሲመሰክር ሳይ በባዕድ አገር የደስታ ስሜት ተሰማኝ።

በተቃራኒው ደግሞ ይህን ታላቅ ሰው እርጅና የሚሉት በሽታ፣ ሞት የሚሉት ለሰው ልጅ አይቀሬ እጣ ፈንታ ሲነጥቀን ያለ ቢሆንም ሐዘን ተሰማኝ፡፡ በይበልጥ ግን ዓልም ይቅርባይነት ጠፍቶባት፣ መቻቻል አቅቷት፣የበቀልና የጥላቻ መንፈስ ነግሶባት እያየ ታላቁ ማንዴላ አንድ ሰው እንኳ ሳይተካ ማለፉን ሳስብ ደግሞ ሐዘኔ ይበልጥ በረታ። ግን እኮ ማንዴላ ፍቅርን፣ ይቅርባይነትን፣ መቻቻልን፣ የውይይት/ድርድር ልምድን በተግባር አሳይቶናል። እኛ እንዴት ከእሱ መማር አቃተን? ምነው ለይቅርታ ዘገየን? ምነው ለበቀል ቸኮልን?
ታላቁን የሰላም አባት ማንዴላን ለማስታወስ በኖርዎይ ኦስሎ ዩኒቨርስቲ ብሊንደር ላይበራሪ መግቢያ በር ላይ በትልቅ ጠረጴዛ የእርሱ ፎቶና ስለ እርሱ የተጻፉ መጻሕፍት ከተቀመጠበት በ06/12/2013 እኤአ ያነሳኋቸው ፎቶዎች ናቸው።


Wednesday, December 4, 2013

ሰንደቅ ዓላማ

ከከበደ ሚካኤል (ታሪክና ምሳሌ ፩ኛ መጽሐፍ የተወሰደ)
ሰንደቅ ዓላማ የነጻነት ምልክት፣ የአንድ ህዝብ ማተብ፣ የኅብረት ማሰርያ ጥብቅ ሐረግ ነው።
              "ተመልከት ዓላማህን፤ ተከተል አለቃህን"
ነጋሪቱ እየተጎሰመ፣ ሠራዊቱ እየተመመ ሲሄድ ሰንደቅ ዓለማ ትምህርተ ኃይል፣ ትምህርተ መዊዕ ነው።
ሰንደቅ ዓላማችን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሦስት ቀለማትን ይዟል። ምሳሌአቸውም አረንጓዴው ተስፋ፣ ልምላሜ ሃብት፤ ቢጫው ሀይማኖት፣ አበባና ፍሬ፤ ቀዩ ፍቅር፣ መሥዋዕትነትና ጀግንነት ነው።