Tuesday, December 31, 2013

ታኅሳስ ፳፪ - ብስራተ ገብርኤል (“ትጸንሲ”)


በቤተ ክርስቲያናችን አስተምሮ መሰረት ታኅሣስ 22 መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ጌታን እንደምትፀን የአበሰረበት ቀን ነው።  
‹‹እንዘ ትፈትል ወርቀ ወሜላተ ወሪዳ ምድረ ቆላ ገብርኤል መጽአ እንዘ ይረውጽ በሰረገላ ክንፎ ክንፎ ክንፎ ጸለላ ተፈስሒ ተፈስሒ ለድንግል ይቤላ፤ ወደ ቆላው ምድር ወርዳ እመቤታችን ወርቅን ከሐር ጋር አስማምታ እየፈተለች ሳለች መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በሰረገላ እየሮጠ መጣ፣ ክንፉንም እያማታ እየሰገደ ድንግል ሆይ ደስ ይበልሽ አላት›› እንዲል ደራሲው አንድም “ተፈሥሒ ፍሥሒት ኦ ምልዕተ ጸጋ፤ ጸጋን የሞላብሽ ሆይ ደስ ይበልሽ” ሉቃ 1፡28 “ስብሃት ለኪ ማርያም እሙ ለፀሃየ ጽድቅ ለአብ ሙሽራው ለወልድ ወላዲቱ ለመንፈስ ቅዱስ ጽርሃ ቤቱ ተፈስሂ ደስ ይበልሽ” እንዳሉ አበው፡፡
እመቤታችን የብፅዓት ልጅ ናት። ሶስት ዓመት ሲሆናት አባት እናቷ ለካህን ሰጥተዋታል፤ ካህናትም በቤተ መቅደስ ከመካነ ደናግል አስገብተዋት ፲፪ ዓመት በቅዱስ ፋኑኤል አማካኝነት ኅብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ሰማያዊ እየመጣላት ያን እየተመገበች መላእክት እየጎበኟት ኖራለች። ፲፭ ዓመት ሲሆናት ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ጌታን እንደምትወልድ በዚህ ቀን ብስራቱን ነገራት። ውሃ ቀድታ ስትመለስ የጠተማ ውሻ እያለከለከ ሲመጣ በወርቅ ጫማዋ ለዛ ለተጠማው ውሻ ውሃ ስታጠጣ አብሯት የነበሩ ሴቶች ማድጋሽን አጎደልሺው፤ ቀድቼ እሞለዋለሁ እንዳትይ ጉድጓዱ ጥልቅ ነው መቅጃም የለሽም አሏት። “ውሃ የሚገኘው ከወደላይ ነው እንጂ ከወደታች ነውን ፍጥረቱን ያጠጣ ጌታ ይሞላልኛል” አለቻቸው። በተዓምራትም ሞልቶላታል። “በዚህ ዘመን አምላክ ከድንግል ይወለዳል ይላሉ ካንቺ ይሆን?” ብለው ዘበቱባት። ወዲያ ከወደኋላዋ ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ “ትጸንሲ” አላት። ዞር ብትል አጣችው። አባቴ አዳምን እናቴ ሔዋንን ያሳተ ጠላት ይሆናል ብላ ሄደች።
ከቤት ደርሳ ማድጋዋን ስታስቀምጥ ዳግመኛ “ትጸንሲ” አላት። ይህ ነገር ደጋገመኝ እንዲህ ያለውን ነገር ቤተ መቅደስ ሄደው ሊረዱት ይገባል ብላ ወደ ቤተ መቅደስ ሄዳ በወርቅ ወንበሯ ተቀምጣ ከደናግለ እስራኤል ጋር የተካፈለችውን ወርቅና ሐር እያስማማች ስትፈት ቅዱስ ገብርኤል ተገልጾ “ተፈሥሂሒ ፍሥሒት ኦ ምልዕተ ጸጋ፤ መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ። ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት። እርስዋም ባየችው ጊዜ ከንግግሩ በጣም ደነገጠችና። ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው? ብላ አሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት። ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም። ማርያምም መልአኩን። ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት። መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። እነሆም ዘመድሽ ኤልሳቤጥ፥ እርስዋ ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፥ ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና። ማርያምም። እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለች። መልአኩም ከእርስዋ ሄደ።” ሉቃስ ፩፡፳፰-፴፰ እንዲል ወንጌል።
“ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ፤ ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም፤ በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ፡፡(አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም)
አበው አባቶችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስተቲያን እንሚያስረዱንና እንደሚያስተምሩን መልአኩ ብስራቱን የነገጋት መጋቢት 29 ቀን በዕለተ እሁድ ከቀኑ ሦስት ሰዓት ላይ ነው። ታዲያ ዛሬ ለምን እናከብረዋለን ለሚለው ጥያቄ፤ ምንጊዜም ወርሃ መጋቢት ታላቁ ዓቢይ ጾም የሚውልበት ወር ነው፤ በዚህ በዓቢይ ጾም ደግሞ ሐዘን፤ ለቅሶ፤ ጾም፤ ጸሎት እንጂ ደስታ፤ ፌሽታ እልልታ፤ ጭብጨባ የለም። ፍጹም የሐዘን ወራት ነው፤ ታቦት አውጥቶ በዓል ማክበርም ስህተት ነው። ፍትሃ ነገስት አንድምታ አንቀጽ 15 ተመልከት ፤ ታዲያ ቅዱሳን አባቶቻችን እንደዚህ ዓይነት ስርዓት ሰሩ፤ የመጋቢት 27 ስቅለቱን ጥቅምት 27 ቀን እንዲሁም የመጋቢት 5 አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ዕረፍት ቀን ወደ ጥቅምት 5 ቀን ዞሮ እንዲከበር አደረጉ፡፡ የመጋቢት 29 ብስራቱን ደግሞ ታህሳስ 22 ቀን ዞሮ እንዲከበር ያደረገው ታላቁ አባት የጥልጥልያ ኤጲስ ቆጶስ ደቅስዮስ ይባላል። ደቅሲዮስ በተጨማሪም የእመቤታችንን ተዓምራቶቿን የጻፉ ታላቅ አባት ነው። በእመቤታች ፍቅር ልቡ የነደደ ታላቅ ጻድቅም ነው። የእመቤታችንን ታአምራቷን የሚናገር መጽሐፍ የሰበሰበ አባት ነው፡፡ የጌታን ልደት ከመከበሩ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ብስራቱ መከበር አለበት ብሎ ስርዓት ሰራ። አገሬውንም ሰብስቦ ታላቅ የደስታ በዓል አደረገ። እመቤታችን ተገለጸችለት ወዳጄ ደቅስዮስ ባንተ ደስ አለኝ። እንዳከበርከኝ እኔም አከብርሃለው አለችው። ሰማያዊ ልብስና ሰማያዊ ወንበር ሰጠችው ይህችን ልብስ ካንተ ሌላ ማንም አይለብሳትም፤ ይህችንም ወንበር ካንተ ሌላ ማንም አይቀመጥባትም አለችው። የዚህ ታላቅ አባት ዕረፍቱ ታህሳስ ፳፪ በዛሬዋ ቀን ነው። ከእርሱ በኋላ ሌላ ኤጲስ ቆጶስ ተሾመ ልብሱን እለብሳለው በወንበሩም እቀመጣለው አለ፤ ተው ይቅርብህ እመቤታችን እንዲህ ብላ ተናግራለች ይሉታል፤ እርሱም ሰው እኔም ሰው እርሱም ኤጲስ ቆጶስ እኔም ኤጲስ ቆጶስ ብሎ በትዕቢት ልብሱን ለበሰው። በወንበሩም ተቀመጠ ክፉኛ አወዳደቅ ወደቀ ሞተም። ይህን ያዩ እመቤታችንን በጣም ፈሯት ይላል ተዓምረ ማርያምን ተመልከት፡፡ ደቅስዮስ ሰርቶልን ያለፈውን ስርዓት ቤተክርስቲያን ተቀብላ ይኸው ዛሬም ድረስ ታከብረዋለች። በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ ብስራተ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ታቦተ ህጉ ወጥቶ በደማቅ ተከብሮ ይውላል፡፡ 
ከእመቤታችን ከወላዲተ አምላክ እንዲሁም ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፡ አሜን!

No comments:

Post a Comment