Saturday, August 16, 2014

የራስን መብት በራስ ማስከበር!

እኔ ሰው ነኝ፣ ያለፍርሃት የመናገር፣ በራሴ መንገድ በነፃ የማምለክ፣ ስህተት የሆነው የመቃወም፣ ያገር ገዢዎችን በነፃነት የመምረጥ፣ ይህንን የነፃነት ቅርስ ለራሴ እና ለማንኛውም የሰው ልጅ ለመጠበቅ ቃል እገባለሁ፡፡” የቀድሞው ካናዳዊ ጠቅላይ ሚኒስትር  ጆን ዳይፍን ቤከር

የግንቦት 7 የፍትህ፣ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ጽሐፊ የሆኑትንና የብርታኒያ ዜግነት ያላቸው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ለመብትና ነጻነት ከቆሙበት ትግል ላይ ወያኔ ለሞትና ለስቃይ ተባባሪ ከሆነችው የመን ከወሰዳቸው 2 ወራትን ሊያስቆጥሩ ነው። 
ይህ ክስተት ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ለነጻነትና ለፍትህ የሚታገሉ አገራዊና የብሔር ድርጅቶች ሁሉ ድርጊቱን በመተቸትና በመቃዎም ላይ ናቸው፤ በተለያየ መልኩ የድርጊቱን አስከፊነትና ለአቶ አንዳርጋቸውና በስቃይ ውስጥ ላሉ ውድ ኢትዮጵያዊ ያላቸውን ድጋፍና አድናቆት ካለመሰልቸት በመግለጽ ላይ ይገኛሉ። ለመብታችን መታገልና በራሳችን መቃዎም እንዳለብን አመላካች ድርጊቶች ይስተዋላሉ። 
ከራሳቸ መብትና ክብር ይልቅ ለኢትዮጵያውያን መብትና ነጻነት የቆሙ ሁሉ አስከፊውን የወያኔ አስተዳደር ለመቃወም የቻሉትን ሁሉ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ብዙዎችም ሞትን ቀምሰዋል፣ እስር ቤትን ቤቴ ብለው ተቀምጠዋል። ነጻነትን፣ ክብርን፣ መብትን ከመገፈፍ የበለጠ ሌላ ምንም ነገር የለምና።
ወያኔዎች/ሕወሓቶች የሥልጣን ጊዜን ለማራዘም የማይቆፍሩት ጉድጓድ፣ የማይፈነቅሉት ድንጋይ፣ የማይከተሉት ስልት፣ የማይወዳጀጁት ኃይል እንደማይኖር ለሁላችንም የማይሰወር ገሃዳዊ እውነታ ነው። በተለይ ደግሞ ለሥልጣናቸው ስጋትና ጭንቀት የሚፈጥሩትን ድርጅቶች በአሸባሪነት ይከሳሉ፤ አባላሎቻቸውንም በስቃይና በመከራ ወደ እስር ቤት መወርወር የዘወትር ተግባራቸው አድርገውታል። ይህን ርካሽ ተግባራቸው በአቶ አንዳርጋቸው፣ በጋዜጠኞች፣ ጦማሪዎች፣በነጻነት ታጋዮች፣ በፍትህ ናፋቂዎች፣ በጋዜጣ አዘጋጆች ላይ ፈጸመዋል፤ በመፈጸም ላይም ይገኛሉ።
ከላይ ያየናቸው የወያኔ አስከፊ ድርጊት አዲስና እንግዳ ነገር ሁኖ አይደለም። ድርጅቱ ስልጣን ከያዘበት ጀምሮ ያለና የነበረ ነው። ነገር ግን እኛ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከስሜታዊነት ተላቀን፣ በቀልን አርቀን፣ጥላቻን አሶግደንና ወኔን ሰንቀን የራሳችንን መብት በራሳችን ማስከበር ይኖርብናል የሚል ጥልቅ እምነት አለኝ።
ስለዚህ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት እያንዳንዳችን ከዚህ አስከፊ ሥርዓት ለመላቀቅ እና ፍትህ፣ ነጻነትና ዲሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለማየት ጣንካራ ሀገራዊና ቆራጥ ልብ ያስፈልገናል። አዲስ ስልት ዘይደን ለመብታችን መታገልና መቆም አለብን። ብዙዎች ለብዙኃኑ መብት ሲሉ ነጻነታቸውን፣ መብታቸውን ተነጥቀው በእስር ቤት ይማቅቃሉ። ለነጻነትና ዲሞክራሲ የቆሙ ወገኖችን ፍርሃትን አሶግደን ቢያንስ ለራሳችን መብት መቆምና መከተል ይኖርብናል። ይህ ካልሆነ ግን ወያኔ 23 ዓመት ኢትዮጵያውያንና ህዝቦቿን እንደፈለገ ከፋፍሏል፣ አሰቃይቷል፣ ድርጅቶችን ዘግቷል፣ ተቋማትን አዳክሟል እኛንም ገዝቶናል ነግም ይቀጥላል።
ይህ እንዳይሆን ከተፈለገ መብታችንን በራሳችን ማስከበር ትልቅ የቤት ስራ አድርገን መነሳት ይኖርብናል።

ይህን ለማድረግ፦
መብታችንን ጠንቅቀን ማዎቅ
እኔ ሰው በመሆኔ ብቻ ተፈጥሮአዊና ሰባዊ መብት እንዳለኝ በሚገባ መገንዘብ። በሰውነቴ ከሁሉም ጋር እኩል ነኝ። መኖር፣ መንቀሳቀስ፣ መብላትና መጠጣት፣ መናገር፣ማዳመጥ፣ መስማት፣ መቃዎም ተፈጥሮአዊ መብቴ ነው። ይህን አንድ ድርጅት/መንግሥት የሰጠኝ መብት አይደለም። መብቴን ማስከበር ያለብኝ እራሴ ብቻ ነኝ።
የአለም አቀፍ የሰባዊ መብት ሕግ ስለሰባዊ መብት ምን ይላል???
አንቀጽ ፫፤

እያንዳንዱ ሰው የመኖር፣ በነጻነትና በሰላም የመኖሩ መጠበቅ መብት አለው።
አንቀጽ ፭፤
ማንም ሰው ቢሆን የጭካኔ ስቃይ እንዳይደርስበት ወይም ከሰብዓዊ አፈጻጸም ውጭ የሆነ የተዋረድ ተግባር ወይም ቅጣት አይፈጸምበትም።
አንቀጽ ፯፤
ሰው ሁሉ በሕግ ፊት እኩል ነው። ያለአንዳች ልዩነትም ሕጉ ደህንነቱን እንዲጠበቅለት እኩል የሆነ መብት አለው። ይህንን ውሳኔ በመጣስ ከሚደረግ ልዩነት ለማድረግ ከሚነሳሳ እንዲጠበቅ ሁሉም የእኩል መብት አለው።
አንቀጽ ፱፤
ማንም ሰው ያለፍርድ ተይዞ እንዲታሰር ወይም በግዛት እንዲኖር አይደረግም።
አንቀጽ ፲፤
እያንዳንዱ ሰው በመብቶቹና በግዴታዎቹ አፈጻጸም እንዲሁም በሚከሰስበት ማንኛውም ዓይነት የወንጀል ክስ ነጻ በሆነና በማያዳላ የፍርድ ሸንጎ በትክክለኛና በይፋ ጉዳዩ እንዲሰማለት የሙሉ እኩልነት መብት አለው።
አንቀጽ ፲፩፤
፩/፡ በወንጀል ክስ የተከሰሰ ማንኛውም ሰው ለመከላከያው አስፈላጊዎች የሆኑትን ሁሉ አቅርቦ በሚከራከርበት የይፋ ፍርድ ቤት በሕግ መሠረት ወንጀለኛ መሆኑ እስቲረጋገጥበት ድረስ ከወንጀል ነጻ እንደሆነ የመቆጠር መብት አለው።
አንቀጽ፡፲፬፤
፩/፡ እያንዳንዱ ሰው ከጭቆና ሸሽቶ በሌሎች አገሮች ጥገኝነትን የመጠየቅና በደህና የመኖር መብት አለው።
አንቀጽ፡፲፰፤
እያንዳንዱ ሰው የሀሳብ፣ የህሌናና የሃይማኖት ነፃነት  አለው። ይህም መብት ሃይማኖቱን ወይም እምነቱን የመለወጥ ነጻነትንና ብቻውን ወይም ከሌሎች ጋር በኀብረት በይፋ ወይም በግል ሆኖ ሃይማኖቱን ወይም እምነቱን የማስተማር፣ በተግባር የመግለጽ የማምለክና የማክበር ነጻነትን ይጨምራል።
አንቀጽ፡፲፱፤
እያንዳንዱ ሰው የሐሳብና ሐሳቡን የመግለጽ መብት አለው። ይህም መብት ያለጣልቃ ገብነት በሐሳብ የመጽናትንና ዜናን ወይም ሐሳቦችን ያላንዳች የድንበር ገደብ የማግኘትን የመቀበልን ወይም የማካፈልን ነጻነትም ይጨምራል።
አንቀጽ፡፳፤
፩/፡ እያንዳንዱ ሰው በሰላም የመሰብሰብና ግንኙነት የማድረግ ነጻነት መብት አለው።
፪/፡ ማንም ሰው የአንድ ማኀበር አባል እንዲሆን አይገደድም።
አንቀጽ፡፳፩፤
፪/፡ እያንዳንዱ፡ ሰው፡ በአገሩ፡ የህዝብ፡ አገልግሎት፡ እኩል፡ የማግኘት፡ መብት፡ አለው።
፫/፡ የመንግስት፡ ሥልጣን፡ መሠረቱ፡ የሕዝቡ፡ ፈቃድ፡ መሆን፡ አለበት። 

ከላይ በአንቀፅ ከአየናቸው የሰባዊ መብቶች ወያኔ አንዱንም አያከብርልንም። እኛም ስሜታዊና ጊዜአዊ በሆነ መልኩ መጮህና ለውጥ በማያመጣ ትግል ውስጥ መድከም እንጂ ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት አልቻልንም። ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት መብታችንን ጠንቅቀን ማወቅና መረዳት አለብን። መብታችንን ስናውቅ ለመብታችን እንቆማለን፣ ከእኛም አልፈን ለሌሎችም እንታገላለን።
በመቀጠልም
1. የራስን መብት በራስ ማስከበር በሚል ሁላችንም መብታችንን ለማስከበር ቆርጦ መነሳት። ለመብታችን እስራትን፣ እንግልትን፣ ድብደባን በጸጋ መቀበልና አገራዊ ስሜት ተላብሰን እንደ አባቶቻችን ድልን ለመቀናጀት የበኩላችንን ድርሻ መወጣት! በሌላ አነጋገር ሁላችንም አንዳርጋቸው ጽጌን፣ አንዷለም አራጌን፣ እስክንድር ነጋን፣ እርዮት ዓለሙንና ሌሎችን ሁነን መነሳት። “ስለሚያገባን እንጦምራለን” እንዲሉ ዞን 9 ጦማርያን እኛም ስለሚያስፈልገን መብታችንን እናስከብራለን እንበል!!!
2. ሊያዋጣ የሚችል አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ። ይህ ህዝባዊ አመጽንም ይጨምራል። ህዝብ በአንድነት ሁኖ አገዛዙን መቃዎምና አስተዳደሩ እንዲስተካከል የማድረግ ታላቅ ኃይል አለው። ይህን ታላቅ ኃይል ተጠቅሞ ፍትህ፣ ነጻነት፣ ዲሞክራሲና ሰላም እንዲሰፍን፣ በግፍ የታሰሩ ወገኖቻችን እንዲፈቱ ማድረግ የሁሉ ኢትዮጵያዊ ድርሻና ኃላፊነት ነው። በዚህ መልኩ ብዙዎች የነጻነት በር ተከፍቶላቸዋል።

3. የሥራ ማቆም አድማ ማድረግ! መብት፣ ነጻነት፣ፍትህ ሳይኖር መደበኛ ሥራ መስራት እጅግ ከባድና አስቸጋሪ እንደሆነ ይታወቃል። ሥራ የመስራት መብት ሳይጠበቅ እንዴት ሊሰራ ይችላል። ስለዚህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መብታችን እስካልተከበረ ድረስ ሥራ አልሰራም ብሎ በህብረት ማቆም ቢቻል መንግሥት ሊወስደው የሚችለው ጊዜአዊ እስራትና ማስፈራርያ ቢሆንም በዋናነት ግን መብትን ማክበር እንደሚሆን እርግጠኛ ሁኖ  መናገር ይቻላል። ስለዚህ አንድነቱና ህብረቱ ካለ መብትን በዚህ መልኩ ማስከበርና ነጻነትን ማግኘት ይቻላል። ለመብትና ለነጻነት መደረግ የሚገባቸውን ነገሮች ሁሉ ማድረግ ተገቢና ኢትዮጵያነትም ነው።
በአጠቃላይ ወቅታዊና ጊዜው የሚጠይቀውን መንገድ በመከተል መብታችንን ለማስከበር ደፋ ቀና ማለት አለብን። ለመብታችን ሰማያዊ ኃይልም ሆነ ሌላ አካል መጠበቅ የለብንም። በጊዜአዊ ጥቅምም ልንደለል፤ ባለማዎቅም መብታችንን ልንነጠቅ ከቶ አይገባም። ንቁና ቁጡ ኢትዮጵያዊ ልንሆን ይገባል። መብቴን እንዳትነካ ብለን ከተነሳን ወያኔዎች ሁሉንም ሰው ሊገድሉ፣ ሊያስሩና ሊያሰቃዩ አይችሉም፤ አቅሙም መብቱም የላቸውም።   

“እኔ ሰው ነኝ፣ ያለፍርሃት የመናገር፣ በራሴ መንገድ በነፃ የማምለክ፣ ስህተት የሆነው የመቃወም፣ ያገር ገዢዎችን በነፃነት የመምረጥ፣ ይህንን የነፃነት ቅርስ ለራሴ እና ለማንኛውም የሰው ልጅ ለመጠበቅ ቃል እገባለሁ፡፡” የቀድሞው ካናዳዊ ጠቅላይ ሚኒስትር  ጆን ዳይፍን ቤከር

ሰላምና ዲሞክራሲ ለኢትዮጵያ!!!

No comments:

Post a Comment