Showing posts with label social. Show all posts
Showing posts with label social. Show all posts

Saturday, September 14, 2013

ሰው እና ሕገ ሕሊና/ተፈጥሯዊ ሕግ

ሰው ማነው? ብሎ ለጠየቀ “ሰው ንግግሩን ይመስላል” እንዳትለኝ ንግግሩ እምነቱንና ሃሳቡን ሙሉ በሙሉ የሚያመለክት ዕውቀት አይሆነውምና ነው፡፡ በተለይ ከዘመኑ ድርጊታችን ስንመለከተው ንግግራችን እና ድርጊታችን ፍጹም ተቃራኒ ሁኖ እናገኘዋለን። ለሰው ባሕርያዊ ተፈጥሮና ዕውቀት ምስክሩ ውስጣዊ የአዕምሮ አቋምና የሕሊና ሕግ ነው ብለንም አንደመድምም፡፡ ሰው እንዲያውቅ የተመደበለት የሕግ ተፈጥሮ ዕውቀት መጀመሪያ ክፍል መልካምን ማወቅ፡፡ ሁለተኛ ክፋትን ንቆ መልካምን ገንዘብ ማድረግ፡፡ ሦስተኛ መልካምን በግብር መግለጽ ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቱያን ሊቃውንት ይሁዳን ሲገልጹ “በአፍ አምኖ በልቡ የካደ” ይሉታል፡፡ ባህላችን “አፈ ቅቤ፤ ሆደ ጩቤ” እንዲል፡፡ ይሁዳ በጊዜያዊ ጥቅም ተታሎ ለሕሊናው መገዛት ስላልቻለ አምላክን ያህል ጌታ ለሞትና ለስቅላት አሳልፎ ሸጠ። ከሐዋርያት ማኅበርም በእራሱ ድርጊት ተለየ።
የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር መሠረት ሕገ ልቦና/ሕሊና ስንል ያለ ትምህረት በተፈጥሮ የሚሰጥ ሲሆን ይህም ሕገ ልቦና፤ ሕገ ህሊና፤ ሕገ ተፈጥሮ ወይንም ሕገ ጠብዓያዊ በመባል ይታወቃል፡፡ ሕገ ኦሪትና ሕገ ወንጌል፤ ሕገ ሕሊናን ይተረጉማሉ፡፡ ለአብነት ብንጠቅስ አዳምና ሔዋን ቅዱስ ዳዊትትን፣ ቅዱስ ጴጥሮስንና ይሁዳን፤ ከመጸጸት ክፉዎችን ከማዘን የምታደርሳቸው የሕሊና ኮሽታ ነች፡፡ በኑሮ ሂደት ሀዘን፣ ጸጸት ርትዕ በምናደርግበት ጊዜ ልዩ መንፈሳዊ ጥበብ አልያም ዕውቀት በመታደል ሳይሆን ሰው በመሆናችን በሕሊና ውስጥ የተቀረጸ በህሊና ሚዛን የሚሰጥ ፍርድ በመኖሩ ነው፡፡ ለምሳሌ አብርሃምን ስንመለከት ምንም የተጻፈ ሕግ፣ ሰባኪና መምህር ባልነበረበት ወቅት በሕገ ልቦና/ሕሊና ተመርቶና ተመራምሮ ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር ችሏል። አባቱ ታራ ይከተለው የነበረው መንገድ እጅግ ስህተት መሆኑን ተረዳ። ለከዚህም በተጨማሪ ሕገ ሕሊና በጽሑፍ ከተሰጡን ሕግጋት /ሕገ ኦሪት፣ ሕገ ወንጌል፣ ማሕበራዊ ሕግ/ በላይ ሰማያዊና ምስጢርን ለመጠበቅ ሲያገለግል እናገኘዋለን፡፡ የቤተ ክርስቲያን የሀገር የግል ምስጢር ይጠበቅ ዘንድ መንፈሳዊ ሕግና ማህበረሰባዊ ሕግ ይደነግጋል፡፡ የአምላክ እናት ድንግል ማርያም ያለ ምድራዊ ሕግ አስገዳጅነት በሕገ ልቦና ዳኝነት ለሰማያዊ ምስጢር የታመነች ነበረች “እናቱ ማርያም በልቧ ትጠብቀው ነበር” እንዲል፡፡ /ሉቃ.2÷19/፡፡
“ሰው ራሱ መጽሐፍ ነው” የሚለው የአነጋገር ስልት የሚያስተላልፈው ሰው ይነበባል፤ ይጠናል፤ ይተነተናል፤ ይጸድቃል፤ ይሻራል ለማለት ነው፡፡ ከሌሎች ሥነ ፍጥረታት በላይም አስተማሪና ሚስጢራዊ ነው። እነዚህን ተግባራት ለሌሎችም ሆነ ለራሳችን ለድርጊታችን ብያኔ ፍርድ ለመስጠት ረቂቅ የሕሊና ልጓም እንደ መሠረት ሆኖ ያገለግላል፡፡ ሰው በውስጡ የሚያረጋግጣት እውነት በክበበ አዕምሮ በሚጨበጥ ሕገ ባሕርይ ከመገለፅ እምቢ አትልም፡፡ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት እምነት በቅድሚያ እንዲገኝ ግድ ቢሆንም በተግባር ወይንም በድርጊት ካልተዋሃደ ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ፍሬ ቢስ፤ ረብ የሌለው ከንቱ ድካም ይሆናል፡፡ ለመሆኑ እምነታችን ከድርጊታችን ለምን ተዛነፈ? በጽናት የምናምነውን እምነት አጥቦ የመውሰድ ብቃት ያለው ሃይል ይኖር ይሆን? በዕለት ተዕለት ማኅበራዊ መስተጋብር የምንወስናቸው መጠነ ሰፊ ጥቃቅን ውሳኔዎች ውህደ ሃይማኖት ምግባር የታሹ ወይስ የስሜት ውጤቶች ናቸው? እርግጥ ነው ስሜት አልባ ሰብአዊ ፍጡር ሊሆን አይችልም፡፡ 
ነገር ግን ነፍስን ደስ የሚያሰኝ ሰማያዊ እውነት ከስሜት በላይ ነው፡፡ እውነት ደግሞ በሕገ ሕሊና ያለ አምላካዊ ሕግ ነው። ሕጉን ያለመፈጸም እንጂ መካድ አይቻልም ምክንያቱም ተፈጥሮአዊ ሕግ ነውና። ሰው ድርጊቱን ምክንያታዊ ቢያደርገውም እውነቱን ግን በትክክል ሕሊናው ይነግረዋል። ከሰው ሊሰወር ይችላል ከሕሊናው ግን መሰወር አይችልም። ብዙ ሰዎች ትክክል ያልሆነ ድርጊት ለመፈጸም ከአሰቡበት ጊዜ ጀምሮ ከራሳቸው ጋር ይሟገታሉ፤ ልፈጽመው ወይስ ይቅርብኝ በማለት። እውነቱንና ትክክለኛውን መንገድ ግን ሕሊናቸው በተለያየ መንገድ ያሳውቃቸዋል። ቅዱስ ጳውሎ እንደተናገረው "እነርሱም ሕሊናቸው ሲመሰክርላቸው፥ አሳባቸውም እርስ በርሳቸው ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ።"(ሮሜ 2፥15)
በገሃዱ ዓለም በብዙዎቻችን ሕይወት የሚታየው ውሳኔዎቻችን በድካም ባካበትነው ዕውቀት፤ መንፈሳዊ አስተምህሮ፤ ዓለማዊ ጥበብ፤ የቅዱሳን ሕይወት ሳይሆን ለስሜት ያጋደለ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለሁለት ጌታ መገዛት አይቻልም የሚለውን ኃይለ ቃል ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተማረው ይሁዳ ለ30 ብር ሸጦታል ለምን ትለኝ እንደሆን ሰው ክፉን ነገር እስኪሰራ ሰው ልበ ሙሉ ይሆናልና ነው፡፡ ሁለተኛው የህሊና ዓይን ከነፍስ ባይለይም በኃጢአት ምክንያት ይጨልማል ይደክማልና ነው፡፡ በአጭር አገላለጽ ድርጊታችንን የሚቆጣጠረው በዕለቱ ስሜታችንን ያቀጣጠለው ኃይል እንጂ በጥረት ያካበትነው ትምህርት ወይም ዕውቀት ሆኖ አይታይም፡፡
ሰው በሕገ ሕሊና፣ በሕገ ኦሪት፣ በሕገ ወንጌልና በሕገ ማህበራዊ መገዛቱን ትቶ በጊዜአዊ ስሜት ለጥቅምና ለስልጣን፣ ለክብርና ለእይታ ማደር ከጀመረ ለአገርም፣ ለቤተሰቡም ለራሱም ሳይሆን በቅዠትና በሰላም እጦት ሕይወቱ እንዲሁ ያልፋል። ሰው ሆይ ከምንም በላይ ለተፈጥሮአዊ ሕግ ተገዢ ሁን፤ ሕሊናህ ይዳኝህ፤ ለመልካም ነገር ትጋ፤ እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ!!!  

ምንጭ፦ ማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ (ሚያዝያ 26፣2003ዓ.ም)

Tuesday, September 10, 2013

አዲስ ዓመት፣ አዲስ ዕቅድ

በየአመቱ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ከእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት ቀጥለን በአዲስ ዓመት ዕቅድህ/ሽ ምንድን ነው? የሚለው የተለመደ ጥያቄ ነው። መልሳችንም እንደ ሥራ መስካችንና አመለካከታችን የተለየ መልክና ይዘት ይኖረዋል። በአዲስ ዓመት በት/ት ገበታ ላይ የሚገኙ ሁሉ ጥሩ ውጤት ማስመስገብን፣ አርሶ አደሮች ጥሩ ምርት ማምረትን፣ በንግዱ ዓለም የሚገኙ ትርፋማነትን፣ ማኅበርተኞች የማኅበራቸውን ዓላማና ግብ መሳካትን፣ ፖለቲከኞች መልካም አስተዳደርንና የተቀናቃኛቸውን ክስረት፣ መንግሥት የስልጣን ዘመን ማራዘሚያ መንገዶችን እና ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪን/ትምህርትን  በአጽንኦት ይሻሉ ይመኛሉ።
አሁን  በአለንበት ዘመን  ምኞታችንን  ሁሉ እውን  ለማድረግ በእጅጉ ከባድ ነው። ሆኖም ግን ልናተኩርባቸው  የሚገቡ ነገሮችን ለይቶ  ለስኬት የሚያበቃንን መንገድ መከተል  ብልህነት ነው። በአጭር ከዚህ በታች ልናተኩርባቸው የሚገቡ ነገሮችን ለመነሻ ያክል ጥቂት ልበል።

እንደ  ክርስቲያን በአዲሱ ዓመት ልናተኩርባቸው የሚገቡ፦
  • ከበፊቱ በበለጠ ከጠላታችን ዲያቢሎስ ጋር የምንዋጋበትን እቃ ጦር ለመልበስ ታጥቀን የምንነሳበት፣ 
  • ቤተ ክርስቲያንን ከበፊቱ በበለጠ ልናገለግልና ልንገለገልባት በጽዕኑ ዓላማ ቆርጠን የምንነሳበት፣
  • ቤተ ክርስቲያን የሁከት፣ ፀረ ሰላም፣ ፀረ ልማት እንዳይደለችና የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት ት/ቤት እንደሆነች በኩራት የምንመሰክርበትና የምንገልጽበት፣ 
  • ቤተ ክርስቲያን አክራሪነትን የምትቃወም እንጂ አክራሪነት የሚለው ቃል ፈጽሞ ሊሰጣት እንደማይገባ በድፍረት የምንመሰክርበት፣ 
  • ከሰዎች ጋር መታረቅና ፍቅርን በስጦታ መልክ መለገስ፣
  • ሰውነታችንን በንስሃ ታጥበን በአምላክ ቅዱስ ሥጋና ክብር ደም ታትመን አዲስ ሕይወትና አዲስ መንፈስ የምንይዝበት ዘምን እንዲሆን ይፈለጋል።
እንደ  መንግሥት በአዲስ ዓመት፦
  • መልካም አስተዳደር ለማስፈን መጣር፣
  • ሕግን ከወረቀት ባለፈ በተግባር ማዋል፣
  • የህዝቡን ብሶት ሰምቶ ለችግሩ ደራሽ መሆን፣
  • አገራዊ ስሜትን ለህብረተሰቡ ማስገንዘብ፣
  • ለዲሞክራሲ ግንባታና ለአገራዊ እድገት የሚጥሩ ተቀናቃኝ/ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማበረታታት፣
  • በሃይማኖት ጣልቃ ገብነትን ማቆም፣
  • ለሰባዊ መብት ተቆርቋሪ መሆን፣
  • ከአላግባብ የታሰሩ እስረኞችን መፍታት፣
  • ትክክለኛ መረጃ ሳይኖር ሰዎችን፣ድርጅቶችንና ተቋማትን  ያልሆነ ስም ሰጥቶ ማሸማቀቅን ማቆም፣
  • ስልጣን የህዝብ መሆኑን በተግባር ማሳየት እና መሰል ተግባሮችን የሚተገብርበት ዘምን እንዲሆን ይፈለጋል። 
እንደ ሰራተኛ በአዲስ ዓመት፦
  • ለሌላ ሁለተኛ ወይም ሦስተኛ አካል ሳይሆን ለህሊና መስራት፣
  • በማነኛውም የሥራ መስክ ህዝብን እንደምናገለግል  በሚገባ መገንዘብ፣
  • ለሕገ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ለሕገ አምላክም መገዛት፣
  • ማጭበርበር፣ ሙስና እና ጥቅመኝነትን አምርሮ  መጥላትና ማጋለጥ፣
  • ፍቅርን  በስጦታ መልክ ለሰዎች መለገስ፣
  • በማነኛውም መልኩ ለእውነት ለመስራት እራስን ዝግጁ ማድረግ ይገባል።
እንደ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲ በአዲሱ ዓመት፦
  • ለህዝብና ለሃገር መቆማችሁን በትክክል ሊያስረዳ  በሚችል መልኩ ዓላማችሁን መግለጽ፣
  • የመንግሥት አካላትን በፖሊሲና በዓላማ እንጂ  በማንነታቸው አለመተቸት፣
  • ማንኛውንም ድርጅት ወይም ተቋም ለፖለቲካ ቅስቀሳ አለመጠቀም፣
  • ስድብንና ዛቻን ትቶ ሙህራዊ የአነጋገር ዘይቤ መጠቀም፣
  • ድርጅታችሁ ከብሔር ይልቅ  አገራዊ እንዲሆን  ማድረግ፣
  • የመንግሥትን  መልካም ሥራዎች ካሉ ማበረታታትና መደገፍ፣
  • ለዲሞክራሲ፣ ለሰላምና ለአድነት ቆርጦ መነሳት ከእናተ በአዲስ ዓመት ይጠበቃል
ሁላችንም 2006 ዓምን እነዚህንና ሌሎች አስፈላጊ ተግባራትን ለመተግበር አቅደን አዲሱን ዓመት መቀበል ይገባናል።   

ዘመነ ማርቆስ/2006 ዓም የሰላም፣ የፍቅር፣ የደስታ፣ የአንድነት፣ የሕይወት ብልጽግና   እንዲሆንልን አምላከ ቅዱሳን በቸርነቱ  ይርዳን፡አሜን!።

Monday, July 22, 2013

ትውልድ የማድን ሃላፊነት የማን ነው?

ትውልዱ ከበፊቱ በበለጠ መሪ የሚፈልግበት ዘመን ነው። ጊዜውንና ዘመኑን የዋጀ ወላጅ፣ መሪና ህብረተሰብ ይፈልጋል። የዘመኑን ትውልድ በጥሩ ሥነ ምግባር፣ ለአገር ተቆርቁሪና በማንነቱ የሚኮራ አድርጎ ለማሳደግ ሃላፊነት ሊወስድ የሚችል አካል ያስፈልጋል።
የነገ ሃገር ተረካቢ ትውልድ ግን ወደየት እሄደ እንደሆነ የሚያሳዩ በርካታ ምልክቶችን መጥቀስ ይቻላል። የትናቱንና የበፊቱን ትውልድ በማነኛውም መልኩ በእጅጉ የሚያስመሰግን ከሆነ ውሎ አድሯል/የበፊቱን ስርዓት ናፋቂ ባትሉኝ ደስ ይለኛል/። ትውልዱ በአለማዊነት ተፅዕኖ ውስጥ ወድቆ ማንነቱን የረሳ ትውልድ እንደሆነ በመሰረተ ሃሳቡ የምንስማማ ይመስለኛል። ከተስማማን መንስኤውና መፍትሄው ምን ይሁን? የሁላችን መሰረታዊ ጥያቄ ይሆናል።

መንስኤው፦
  1. አለማዊነት፦ ትውልዱ አለማዊነት የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ በሚገባ ከአለማወቅ የመጣ ችግር ነው። ይህንን ሃላፊነት ወስዶ ሊያስገነዝበው የሚችል አካል በማጣቱ የመጣ ትልቅ ክስረት ነው። ወላጅ እንደ ወላጅ፣ መንግሥት እንደ መንግሥት፣ እያንዳንዱ ዜጋ እንደ ዜጋ ሃላፊነቱን በየደረጃው መወጣት ስላልቻለ አንድ ትውልድ በማጣት ላይ እንገኛለን። ይህን ደግሞ በአካባቢያችንና በሰፈራችን የምናያቸውን ነገሮች መጥቀስ ከበቂ በላይ ማስረጃዎች ናቸው። ልጅን በሃይማኖት ማሳደግ እንደኋላ ቀርነት ተቆጠረ፤ልጆችም ስለእምነትና ባህል መነጋገርንና መወያየትን ትተው ስለአለማዊነት "ስለ ግብረ ሰዶምና ሰይጣናዊነት" መነጋገር ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ይህንና መሰል አስነዋሪ ድርጊቶች ሲከናወኑ እያየን ዝም በማለታችን ለትውልዱ መጥፋት በየደረጃው ተጠያቂዎች ነን። የመጀመሪያዉና ትልቁ ለትውልዱ መጥፋት መንስኤው ይህ ነው።
  2. ትምህርት ቤቶች፦ ተማሪዎችን በጥሩ ሥነ ምግባርና ባህልን ከማሳዎቅ አንጻር አስተምሯቸው ዝቅተኛና ከዚህ ግባ የማይባል መሆኑ ለትውልዱ መጥፋት ሌላው መንስኤ ነው። እንደሚታወቀው ትውልዱ ጥሩ ዜጋ እንዲሆንና እምነቱንና ባህሉን አክባሪ አድርጎ በማነጽ በኩል ት/ቤቶች ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። ዛሬ ግን ትምህርት ቤቶችን ስንመለከት ከተቀረጸላቸው ሥርዓተ ት/ት ጀምሮ ትውልድን ለመቅረጽ ቀርቶ በዜግነት ደረጃም እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚናገር ትውልድ እንዳይጠፋ ስጋቴ ከፍ ያለ ነው።  ከዚህ ባለፈም አንዳንድ ት/ቤቶች የብልግና ድርጊት ተባባሪዎች በመሆናቸው ለትውልዱ መጥፋት ተቆርቋሪ አካል መጥፋቱን ያመላክታል /በህጻናት ላይ ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ መምህራን የሚገኙበት ት/ትቤቶች/። ወላጅም ልጆቻቸውን የሃይማኖት ት/ት ቤት ልኮ ሥነ ምግባር እንዲማሩ የማድረጉ ተግባር አናሳ ነው።    ከፍተኛ  ት/ት ተቋማትም የተማረና አገርን ሊረከብ የሚችል ዜጋ ይፈራበታል ብሎ ማሰብ ቅዥት እየሆነ መጥቷል፤ የመጥፎ ሱስ ተገዥዎች ቁጥር በግቢ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመር ላይ ነው፤ እንደ አንዳንድ ከተሞች በግቢ ውስጥም የዝሙት መፈጸሚያ ቦታውች ስም ተሰጥቷቸው እና እንስሳዊ ባህሪ ሲፈጸምባቸው እየታየ  ችግሩን ለመቅረፍ ግን የሚወሰድ እርምጃ የለም።   
  3. መንግሥት፦ ትውልዱ ጥሩ ዜጋ እንዲሆን የማድረግ ሃላፊነትም ግዴታም ያለበት መንግሥት ነው። አገሪቱን እያስተዳደረ ያለው እርሱ እስከሆነ ድረስ አገር ተረካቢ ዜጋ የመፍጠሩ ስራ በዋናነት የመንግሥት ነው፤ ምንአልባት "እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል" ካልሆነ ነገሩ። ሃገራዊ ስሜት ያለው ዜጋ ለመፍጠር ይህን ስሜት ሊፈጥር የሚችል ሥርዓተ ት/ት፣ ሊተገብሩ የሚችሉ ትምህርት ቤቶችንና የማስተማር ብቃት ያላቸው  መምህራንን ማደራጀት እንዲሁም ለተማሪዎች ከምረቃ በኋላ የሥራ ዕድል ማመቻቸት የመንግሥት ግዴታ ነው። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግን ለትውልዱ መጥፋት የመንግሥት ተቆርቋሪነት ጎልቶ የሚታይበት አጋጣሚዎች ባለመኖሩ ችግሩ ሥር መስደዱና በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑን እንመለከታለን። መንግሥት ግን ትውልዱ ጥሩ ዜጋ እንዲሆን ራዕይ የለውም? የዘወትር ጥያቄዬ ነው። 
  4. ወጣቶችን ወደ አልተፈለገ ህይወት የሚመሩ ነገሮችን ቸል ማለት፦ በት/ት ቤቶችና ወጣቶች በሚያዘወትሩበት አካባቢ የሥነ ምግባር ብልሹነት ሊያጋልጡ የሚችሉ ነገሮችን ተቆጣጣሪ  አካል በመጥፋቱ ችግሩ እንዲባባስ አድርጎቷል። ለምሳሌ ጫት ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶች፣ አሽሽ ቤቶችና የሴተኛ አዳሪ ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ መጨመሩና ወደ እነዚህ ቦታወች መሄድ ከነውርነት አልፎ እንደ  ዘመናዊነት በመቆጠሩ ትውልዱ በግልጽና በድፍረት የድርጊቱ ተሳታፊ ሁኗል። 
  5. ማህበራዊ መገናኛዎች/ social medias/፦ ማህበራዊ መገናኛዎች ትውልዱን የማዳንም የመግደልም አቅም አላቸው። ይህን ተገንዝቦ ለትውልዱ መዳን የሚሰሩ መገናኛዎች ግን ጎልተው አይታዩም። በተለይ የዘመኑ  መገናኛ ዜዴ በእጅጉ ትውልዱን ሰነፍና በአለማዊነት ተጽኖ ውስጥ እንዲገባ አድርጎቷል። ወደ አገራችን ኢትዮጵያ ስንገባ ደግሞ ጥበብ የሞላበት አጠቃቀም አይደለም የምንጠቀምው ከጊዜ ማጥፋት ጀምሮ እስከ አጉል ሱስነት ውስጥ እንድንገባ አድርጎናል። የፌስ ቡክና ትዊተር ተጠቃሚዎች በእጅጉ ታውቁታላችሁ። ትውልዱ ወደ አልተፈለገ ህይወት ውስጥ እንዳይገባ በማህበራዊ መገናኛ ዙርያም ትልቅ ሥራ ሊሰራ ይገባል።
መፍትሔው፦ በአጠቃላይ ከላይ በጥቂቱ የተዘረዘሩትን ችግሮች በሚገባ ማጤንና አገራዊ ጉዳቱን በመረዳት ትውልዱን ለማዳን ከቤተሰብ፣ ከጎረቤትና አካባቢ በመጀመር ግዴታችንን መወጣት መቻል ነው። ልጆቻችንን ዘመኑን በዋጀ መልኩ ማሳደግ፣ መከታተልና በመንከባከብ በጊዜ ሂደት ችግሩን ልንቀንሰው እንችላለን፤ ፈጽሞ  ማጥፋት ግን የሚታሰብ አይሆንም። ምክንያቱም ዓለም ሰይጣናዊነትን አሜን ብላ ስለተቀበለችሁ የዛ ነጸብራቅ ወደ ልጆቻችን መድረሱ አይቀርምና። ቢሆንም ግን ወላጆች ልጆቻችንን የት፣ ከማን ጋር እና በምን መልኩ መሄድ እንዳለባቸው ቀስ አድርገን በሚገባቸው መልኩ በማስረዳት በጥሩ ሥነ ምግባር ማሳደግ ይቻላል። ችግሩ ግን እኛስ ማን ነንና ለልጆቻችን አርያ የሚሆን ህይወት አለን? በፍቅርና ግልጽ በሆነ መልኩ ልጆቻችንን እያሳደግን ነው? ፍቅር የሞላበት የትዳር ህይወት፣ የጸሎት ህይወት አለን?                          


Friday, April 26, 2013

ማነው ጥፋተኛ


ይህ የሁለት ባለትዳሮች እውነተኛ ታሪክ ነው። ለእኛም አስተማሪ ሊሆን ስለሚችል ስማቸውን ሳልጠቅስ ታሪካቸውን በአጭር አስፍሬዋለሁ።
ለሚስት የተለያዩ መስፈርቶች ቢኖራትም በዋናነት ለእርሷ ባል ማለት ከጓደኞቹ ጋር አምሽቶ የሚገባ፣ ሳያበዛ በትንሹ የሚጠጣና አንዳንዴ ካልሆነ በስተቀር በጊዜ እቤቱ የማይገባ ነው። ባል ተብየው ደግሞ ይህ አይነት ፀባይ አይመቸውም። ምንም አይነት ሱስ ስለሌለበት ማምሸትም ሆነ ከቤቱና ከባለቤቱ ውጭ የሚያስደስተው ነገር የለም። ይህ ፀባዩ ሚስቱን ብቻም ሳይሆን ከጓደኞቹም ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳይኖረው እንቅፋት ሁኖበታል። ሚስቱ በጊዜ በመጣ ቁጥር ጭቅጭቅና ንትርክ ታበዛበታለች ለምን እንደጓደኞችህ ተጫውተህና አመሻሽተህ አትመጣም ትለዋለች። እርሱም በተደጋጋሚ እንደማይመቸውና ጥሩም እንዳልሆነ እንዲሁም የሚያስደስተው ከርሷ ጋር ማምሸትና ከሥራ ውጪ አብረው ማሳለፍ እንደሆነ ደጋግሞ ቢነግራትም ልትረዳው አልቻለችም።
ብዙ እህቶችና ወንድሞች ባለቤታቸውን ወይም እጮኛቸውን እንዲህ ብታደርግ/ብታደርጊ ደስ ይለኛል፤ እንዲህ አይነት ፀባይ ያስደስተኛል ሲሉ ይሰማሉ። እኔ የምወደው ፀባይ እንዲህ አይነት ነው እያሉ ብዙዎች መስፈርት ያወጣሉ። ነገር ግን መስፈርታቸው ወይም የሚፈልጉት ፀባይ ለትዳር ህይወታቸ  ይጥቅማል ወይስ አይጠቅምም ብለው ትኩረት የሚሰጡ በቁጥር እጅግ አናሳ ናቸው። መታየት ያለበት ግን የሚያስደስተን ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ለትዳር ህይወታችን፣ ለጓደኝነታችን፣ ለማህበራዊ ግንኝነታችን፣ ለቤተሰባዊ ፍቅር ወዘተ ጥቅም አለው ወይስ የለውም የሚለው ነው። እኔን የሚያስደስተኝ የትዳር አጋሬን ያስደስተዋል/ያስደስታታል ወይስ ያስከፋዋል/ያስከፋታል የሚሉ ጥያቄዎችን በደንብ ማየትና መመርመር ያስፈልጋል። ከትዳር አጋራችን የምንፈልገው መስፈርት በመካከላችን  መተሳሰብ፣ ውይይትና ፍቅር የተሞላበት እንዲሆን ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ ተገቢ ነው። ከዚህ ከአለፈ ግን ከሰላም ይልቅ ጠብና ክርክር፣ ከአንድነት ይልቅ መለያየት፣ ከመተሳሰብ ይልቅ ግደለሽነት ሊያስገባን ይችላል።
የእነዚህ ባለትዳሮችን ህይወት ስንመለከት የሚስትን ጭቅጭና ለእርሱ የምትሰጠው አክብሮት የቀነሰ ስለመሰለውና እሷን የሚያስደስታት ከሆነ ከጓደኞቹ ጋር ቀስ በቀስ ማምሸት ጀመረ። በዚያን ወቅት የነበረ አንድ ወንድም እንደነገረኝ ሰውየው መጠጥ የመጀመሪያው ስለነበረ እጅግ ቢራው ከመምረሩ የተነሳ ለመጠጣት የቀመሰውን ቢራ እንደተፋው የአይን ምስክር ሁኖ ይናገራል። ሆኖም ግን ቀስ በቀስ መልመዱ አልቀረም ለመደ። ሚስት ባለቤቷ አመሻሽቶ በመምጣቱ እጅግ ተደሰተች። የኔ ባለቤትም እንደሌሎች ወግ ደረሰው እያለች መኩራራት ጀመረች።
"ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም" እንደሚባለው ከጊዜ ወደጊዜ ሰውዬው መጠጥን ጓደኛው አደረገው፤ እጅግም ተዋህደው። የዚህን ጊዜ ሚስት ተብየዋ እሷ ከምትፈልገው ስዓት ዘግይቶ ስለሚመጣ ደስታዋ ብዙም አልዘለቀም። አሁንም ተመልሳ ወደ መጀመሪያው ጭቅጭቅና ንትርክ ገባች፤ ለምን በጊዜ አትገባም፣ እኔ የተወሰነ አምሽተህና ከጓደኞችህ ጋር ተጫውተህ እንድትመጣ እንጂ እንደዚህ ዘግይተህና ሰክረህ ይባስ ብለህ አድረህ እንድትመጣ አልነበረም የኔ ፍላጎት ማለት ጀመረች። ባለቤቷ ግን በመጠጥ ሱስ  ተይዟልና ሊሰማትና ቃሏንም ተግባራዊ ማድረግ አልቻለም።
ዛሬ ላይ ትዳራቸው እጅግ አስከፊና አደጋ ላይ ወድቋል። የወር ደሞዙን ከመቀበሉ በፊት ይጨርሰዋል። በቤታቸው ሰላም የሚባል ነገር ጠብና ክርክር ነግሦአል። "ድሮ  ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ" እንደሚባለው እሷ የዘወትር ስራዋ ማልቀስና አምላኳን ማማረር ሁኗል። ለዚህ ጥፋት ተጠያቂው ማነው? ሚስት ወይስ ባል? እኛስ የምንፈልገው መስፈርት ለትዳራችን ምን ያክል አስተማማኝ ይሆን?

እንወያይበት