Saturday, February 15, 2014

የጉባኤው ጥቅም ወይስ የአባ ሰረቀ ደብዳቤ?



 የአባ ሰረቀ ደብዳቤ ማኅበረ ቅዱሳን ለአብነት መምህራን ለታላቅ ዓላማ ያዘጋጀውን ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ እንዲታገድ ምክንያት ሆነ። ጉባኤው ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጠውን ሁለተናዊ ጥቅም ወደጎን በመተው ምንም ረብ ለሌለው ደብዳቤ ቅድሚያ በመስጠት ጉባኤው እንዲታገድ የመንግሥት/ፖሊስ እገዛን መጠየቅ ቤተ ክርስቲያንን ያስተዳድራሉ ይመራሉ ተብለው ከሚጠበቁ ብፁዓን አባቶች ቀርቶ ከአንድ የቤተክርስቲያን ምእመን የሚጠበቅ ተግባር አልነበረም አይደለምም።
የጉባኤው አላማ ለማንም የተሰወረ አልነበረም። በማኅበረ ቅዱሳን አሰራርም የሚያከናውናቸውን መንፈሳዊ ተግባራት ሁሉ አስቀድሞ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ ቅዱስ ሲኖደስ ድረስ አሳውቆና ምክር ጠይቆ እንደሚሰራ ይታወቃል። በዚህም መሰረት ይህም የምክክር ጉባኤ ቀደም ብሎ የታቀደና መቼ፣ እንዴትና በምን ዙርያ እንደሆነ አባ ሰረቀም እራሳቸው በሚገባ ያውቁታል።

በእርግጥ የአባ ሰረቀና የማኅበረ ቅዱሳን የአለመግባባት ጉዳይ ዛሬ የተከሰተ እንግዳ ነገር አይደለም፤ ለአመታት የዘለቀ፣ የሰ/ት ት/ቤቶች ማደራጃ መምርያ ኃላፊ በነበሩበት ጊዜ የማኅበሩን አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ እስከማስቆም ድረስ ጽኑ አላማ ይዘው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር እና ተመሳሳይ ደብዳቤዎችን ይጽፉ እንደነበር መቼም የማይረሳ የዘወትር ትዝታ ነው።
አባ ሰረቀ በኃላፊነት የያዙትን መምርያ/የሰ/ት/ቤቶች ማ/መምርያ በትክክል ባለመምራታቸው፣ ለማኅበረ ቅዱሳንም መንፈሳዊነቱን የለቀቀ የእግድና የማስጠንቀቃ ደብዳቤ በተደጋጋሚ በመጻፋቸው እና ሌሎች ከአንድ መንፈሳዊ መሪ ነኝ ከሚል አባት የማይጠበቁ ተግባራትን ምክንያት በማድረግ በ2004 ዓም በተካሄደው የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ከመምርያ ኃላፊነታቸው እንዲወርዱ በመወሰኑ ከሥልጣናቸው በአስቸኳይ እንደለቀቁ የማይዘነጋ ሃቅ ነው። በዚሁ ጉባኤም የእምነት ችግር አለባቸው ተብሎ በሚከሰሱበት ከኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነት ውጪ ነው የሚባለውን እምነታቸውን የሚመረምር ሊቃነ ጳጳሳት የሚገኙበት ኮሚቴ ተቋቁሞ እንደነበርም ይታወሳል። እንዲህ አይነት ሰዎችን ግን በመምርያ ኃላፊነት ማስቀመጥ በራሱ ለቤተ ክርስቲያን የሚፈጥረውን ችግር ቅዱስ ሲኖዶስ ቢመለከተው መልካም ነው።
በአንጻሩ ማኅበረ ቅዱሳን ደግሞ ቅዱስ ሲኖዶስ የሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት እውቀቱን፣ ገንዘቡንና ጉልበቱን ለቤተ ክርስቲያን በመስጠት ቤተ ክርስቲያንን ለማገዝ ደፋ ቀና የሚል ማኅበር ነው። ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት፣ የአብነት ት/ቤቶችንና ገዳማትን በመርዳት፣ ምእመናን በምክረ አበው ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ፣ የተለያዩ የውይይትና ምክክር ጉባኤያትን በማድረግ ለቤተ ክርስቲያን የበኩልን ድርሻ በመወጣት ላይ የሚገኝ ማኅበር ነው።

ቅዱስነታቸው ይህን ጉዳይ ሳይረዱና ሳይመረምሩ የቤተ ክርስቲን አይን እና ጀሮ የሆኑትን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ማኅበረ ቅዱሳን እንድትወያዩ፣ እንድትመካከሩ፣ በአካል እንድትገናኙ ማድረጉ ስህተት ነውና ተመልሳችሁ ሂዱ፣ ልፋታችሁ፣ ድካማችሁ ከንቱ ይሁን ብለው የእግድ ደብደቤ መጻፋቸው በእውነት ምክንያቱ ተሰውሮብኛል። በእየ ገዳማቱ የሚገኙ ሊቃውንት ምክራቸው የማይሰለች፤ቃላቸው የማይጠገብ አንደበተ ርዕቱ አባቶቻችንን ዛሬ ምነው በአደባባይ እንዳይመክሩን ታገዱ??? ምነው ቅዱስነትዎ ለቤተ ክርስቲያን የደም ሰማዕትነትም ቢሆን መስጠት የሚችሉ አባቶቻችንን እንዳይናገሩ፣ እንዳይወያዩ አደረጉ? እንዴት ከጉባኤው ጥቅም ይልቅ የአባ ሰረቀ ረብ የለሽ ነጠላ ደብዳቤ ሚዛን ደፋ?

ዛሬ ላይ የቤተ ክርስቲያኗ ትልቁ ችግር እንደ አባ ሰረቀ እና መሰል ችግር ፈጣሪ ሰዎችን የመምርያ ኃላፊ፣ የአድባራትና ገዳማት እንዲሁም የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ተደርገው መሾማቸው ነው። ከአጥቢያ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምርያ ሰራተኞች በእየዘርፉ ችግር ፈጣሪ አካላት አሉባት። ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ችግሯን ሊረዳላት ይገባል። እንዲህ አይነት ሰዎችን በማነኛውም መመዘኛ በኋላፊነት መመደቡ ለቤተ ክርስቲያን ውድቀት እንጂ ለውጥና እድገት አይመጣም።


ማኅበረ ቅዱሳን እኮ አባ ሰረቀ የሚመሩት የመምርያ ክፍል በዋናነት በእቅድ ይዞ ሊሰራው የሚገባውን ተግባር በጀት ሳይጠይቅ በራሱ በጀት ሊቃውንቱን ለውይይት መጋበዙ ምስጋና ያስችረው  ነበር እንጂ ጉባኤውን ለማሳገድ ብዕር አያስነሳም ነበር። እንዲሁም በትብብር አብሮ ለመስራትና የሊቃውንቱን ምክር ለመቀበል በጋራ ማስኬድ የሚቻልበት መልካም አጋጣሚ ነበር። ግን ምን ዋጋ አለው ቅናዊ አስተሳሰብ ጠፋ፣ ሁልግዜም የማኅበሩን አገልግሎት ለማዳከም እንቅልፍ በአይናቸው አልዞር ያላቸው እኒህ አባት ሊቃውንቱን አሳዘኑ። ማኅበሩ ግን የአባቶች በረከት አልቀረበትም ይልቁንም በእንዲህ አይነት አባት ነን ባዮች እየተፈተነ እንደሚያገለግል ገዳማውያን አባቶቻች በሚገባ እንዲረዱና በጸሎታቸው እንዲያስቡት ጥሩ ምክንያት ሆነለት።  

ቅዱስነታቸውም ቢሆን የጉባኤውን ዓላማና አስፈላጊነት በሚገባ እያወቁና እየተረዱ ለማይሰራና ለማያሰራ የመምርያ ኃላፊ እኔ መሥራት ያላብኝን ተግባር ማኅበረ ቅዱሳን አከናወኑብኝ በሚል ተልካሻ ምክንያት ለተጻፈ ደብዳቤ ቅድሚያ ሰጥተው ሊቃውንቱ እንዲበተኑ ማድረጋቸው ምናልባትም በዘመነ ፕትርክናቸው ከሰሩት ሥራዎች ለታሪክ መጥፎ አሻራ ይሆንባቸው ይሆናል። እንዲያ ባይሆን ኑሮማ ደብዳቤ እንደ ደረሳቸው ሁለቱንም ጠርተው አባታዊ ቡራኬና ምክር ሰጠው ጉባኤውን በጋራ በመተባበር እንዲካሄድ ማድረግ ይችሉ ነበር። ወይም ጉባኤው ከተካሄደ በኋላ ለማኅበሩ ይህን ጉባኤው የትምህርትና ሓዋርያዊ አገልግሎት ስልጠና መምርያ ማለትም አባ ሰረቀ በሃላፊነት ሊያከናውኑት እንደሚችሉ መልእክት ማስተላለፍ ይችሉ ነበር።  

አባቶቻችን ሆይ እኛ በዓለም የምንኖር ልጆቻችሁ በዚህ እና መሰል ፈተናወች ውስጥ ነውና ያለን በጸሎታችሁ አስቡን አትርሱን! መቻሉን፣ ትግዕስትን፣ አስተዋይነትን እንዲያድለን ለምኑልን!
ቤተ ክርስቲያንን እንመራለን እናስተዳድራለን ለሚሉ ሁሉ መልካም መሪ እንዲሆኑ ጸልዩላቸው!


EOTC Radio "ወቅታዊ ጉዳይ" ስለ ሦስተኛው ሀገር አቀፍ የአብነት መምህራን ጉባኤ መታገድ
Hara tewahdo;ማኅበረ ቅዱሳን ለአብነት መምህራን ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ታገደ
http://www.danielkibret.com/2014/02/blog-post_14.html

Monday, January 6, 2014

“እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል” (ሉቃ.2፡11)


“ዘሎቱ ሰብአ ሰገል ሰገዱ ሎቱ፤ አማን መንክር ስብሐተ ልደቱ፤
ለእርሱ ሰብአ ሰገል የሰገዱለት፣ የልደቱ ክብር ድንቅ ነው።”

እግዚአብሔርን በእምነት ደስ ያሰኙ ቅዱሳን ከእስራኤላውያን ተነሥተው ነበር።(ዕብ.11) የአባቶች አለቃ ከሆነው ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ጌታችን ሰው መሆን (ዘመነ ሥጋዌ) ድረስ ብዙ ታላላቅ አባቶችና እናቶች በእስራኤል ዘንድ ተገኝተዋል።

የእስራኤል ታሪክ ሁልጊዜ መልካም ታሪክ ብቻ ግን አይደለም፤ እግዚአብሔርን ያሳዘኑባቸው ጊዜያት ጥቂቶች አይደሉም። በዚህ ጊዜ በዙሪያቸው ባሉ ነገሥታት እየተማረኩ ወደ ፋርስ፣ ባቢሎንና ግብጽ እየወረዱ ለአሕዛብ የተገዙበትና የገበሩበት ጊዜም ነበር። ንስሐ ገብተው ወደ እግዚአብሔር ሲመለሱ ደግሞ እግዚአብሔር ከእነርሱ መካከል ሰው እያስነሣ ያድናቸው ነበር። ለአባቶቻቸው የገባውን የዘለዓለም ቃልኪዳን እያሰበ ይረዳቸውም ነበር። (መዝ.77 (78))
እነሆ በዚህ የታሪክ መስመር ውስጥ ወደር የሌለው፣ ሁለተኛ በዓለም ታሪክ የማይደገም ታላቅ ነገር ተከሰተ። የእግዚአብሔር ልጅ የሰውን ሥጋ ለብሶ እንደ ሰው በምድር ላይ ተገለጠ። ጥበበኛው ሰሎሞን “አበባ በምድራችን ታየ” ብሎ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ፤ አበባ ክርስቶስ ምድር በተባለ ሥጋችን ተገልጧልና(መኃ.2፥12)። የዓለም መድኃኒት እግዚአብሔርነቱን ሳይተው ሰው ሆነ። እነሆ የእግዚአብሔር ልጅ የአብርሃም ልጅ ተባለ፤ የዳዊት ጌታ የዳዊት ልጅ ተባለ። (ማቴ.1፥1) የዳዊት ፈጣሪ በዳዊት ከተማ በቤተልሔም በከብቶች በረት ተወለደ። አባቶቻቸው በአንድ ዘመን ዳዊት የነገሠባትን ከተማ ያፈረሱ፣ የዳዊትን ልጆች በባርነት የገዙ የፋርስና የአረብ ነገሥታት የዳዊትን መንግሥት ለዘለዓለም ለሚያጸናው ሕፃን ለኢየሱስ ክርስቶስ ሰገዱ፤ ተገዙ።

ልጁን ለእግዚአብሔር መስዋዕት አድርጎ ለማቅረብ እንኳ እንቢ ያላለውን፣ የአብርሃምን ልጆች ያስገበሩት የአሕዛብ ነገሥታት ዛሬ ለአብርሃም ልጅ ወርቅ፣ እጣን፣ ከርቤ ገበሩ። (ማቴ.1፥11) በበደለኞች እስራኤላውያን ልጆቻቸው ኃጢአት ምክንያት ዝቅ ዝቅ ያለው የእስራኤል ክብር ከእነርሱ ዘር ሥጋን በነሣው በኢየሱስ ክርስቶስ ለዘላለም ከፍ ከፍ አለ።

የክርስቶስ ሰው መሆን ግን ከእስራኤል ታሪክ ያለፈ የሰው ልጅ ሁሉ ደስታ ነው። እነሆ ሰው የመሆኑ ዜና የሰው ልጆችን ሁሉ ደስታ አሰኘ “እነሆ ለህዝቡ ሁሉ የሚሆንchristmas ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።” የሚል ዜና በሰማያውያን መላእክት ተሰበከ። (ለቃ.2፥11) የምድር ኃያላን ነገሥታት በከብቶች በረት ውስጥ በጨርቅ ተጠቅልሎ ለተኛው ሕፃን መብዐ አቀረቡ። ንጹሐንና ኃያላን የሚሆኑ የሰማይ መላእክት እግዚአብሔር ለሰው ፍቅር ሲል እንደ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ሲያዩ በታላቅ ትሕትና ከእረኞች ጋር ዘመሩ። (ሉቃ.2፥13)

“ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ፣ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ።” ያለው የዳዊት ጸሎት መልስ አገኘ (መዝ. 42፥3)። ማንም ሊቀርበው በማይችል ዘለዓለማዊ ብርሃን ዉስጥ ከአባቱ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የሚኖር ብርሃን ወልድ ለጨለማው ዓለም ብርሃን ይሆን ዘንድ ተወለደ። ወደ ጽድቅ ፀሐይ ያደርሳቸው ዘንድ የእርሱ የሆነው ኮከብ ሰብአ ሰገልን ከምሥራቅ መራቸው። እነሆ ለዘለዓለም የሚያበራው ፀሐይ በቤተ ልሔም ወጣ። ነቢዩ ኢሳይያስ “በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው” ብሎ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ (ኢሳ.9፥2)። እርሱ የቅድስናው ተራራና ማደሪያው ወደ ሆነች ወደ መንግሥተ ሰማያት ይወስደናል፤ በዚች የዘለዓለም አገራችንም የሚያበራልን ፀሐይ እርሱ ነው(ራእይ.21፥23)።

በዳዊት ከተማ በቤተልሔም ድንቅ ነገር ተደረገ። ዳዊት በወርቅ ያጌጠ የተልባ እግር መጎናጸፊያ የለበሰባት ቤተልሔም የሰማይና የምድር ፈጣሪ በጨርቅ ተጠቅልሎ ተገኘባት። ቤተልሔም ከዳዊት ዘመን አብልጣ ከበረች፤ የእግዚአብሔር ክብር አብርቶባታልና፤ የልዑላን መላእክት ዝማሬ ተሰምቶባታልና።(ሚክ.5፥2)

Picture2“የእሥራኤል እረኛ ሆይ አድምጥ …በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ” ብሎ የለመነው የዳዊት ልመና በእውነት ተፈጸመ።(መዝ.70(71)፥1) የእስራኤል እረኛ በእረኞች መካከል በከብቶች በረት ተወለደ። (ሉቃ.2፥7)እረኞች ለእረኛቸው ዘመሩ፤ ላሞችና በጎች በበረት የተኛውን ሕፃን በትንፋሻቸው አሟሟቁት። በኦሪት ድንኳን በሙሴ ሕግ መሠረት ለመስዋዕት ይቀርቡ የነበሩ እንስሳት በልደቱ ደስ ተሰኙ፤ የእነርሱን መሥዋዕት የሚያስቀር አማናዊው የእግዚአብሔር በግ ተወልዷልና።

ለሰው ሁሉ ብርሃን የሚሰጥ እግዚአብሔር በጨለማው ዓለማችን ተወለደ።(ዮሐ.1፥9-14) ነቢያትና መምህራን ጠፍተውባት፣ የኃጢአት ጨለማ ዉጧት፣ በድንቁርና ባሕር ውስጥ ሰጥማ በነበረችው የሰው ልጆች ዓለም የእውነት ፀሐይ ወጣ። እነሆ ይህን ይገልጥ ዘንድ መድኅን በእኩለ ሌሊት ተወለደ፤ በተወለደ ጊዜ ግን የእግዚአብሔር ክብር በዙርያው አበራ። (ሉቃ.2፥8-9)

ለመንግሥቱ ወርቅ ተገበረለት። ኃያል መንግሥቱን ግን በምድር ላይ በትሕትና ገለጠው፤ በከብቶች በረት በመወለድና በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ በመሄድ።Picture1 (ሉቃ.19፥28-38) የአባታችን የዳዊት መንግሥት ያለልክ ከፍ ከፍ አለች፤ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ የዳዊት ልጅ ሆኗልና። ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት ድንግል ማርያምን ባበሠራት ጊዜ “እርሱ ታላቅ ይሆናል፣ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፣ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለዓለም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለዉም” ብሎ የተናገረው ዛሬ ተፈጸመ(ሉቃ.1፥32) በባሕርይው የፍጥረት ሁሉ ገዥ የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ ከዳዊት ልጅ ሥጋን ነሥቶ ሰው በሆነ ጊዜ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን እስከ ጽርአ አርያም ድረስ ከፍ ከፍ አደረጋት። እነሆ ንጉሥ ክርስቶስ በያዕቆብ ቤት(በምዕመናን) ላይ ለዘለዓለም ነገሠ። ለመንግሥቱ የአሕዛብ  ነገሥታት ተገዙላት፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ናትና ፍጥረታት ሁሉ ይገዙላታል።(ኤር.23፥5)

ለክህነቱ እጣን ተሰጠው። ክህነቱም የአበውን እና የሌዋውያንን ክህነት የምትፈጽም የዘለዓለም ሰማያዊት ሥራው ናት። እነሆ የአብ ሊቀ ካህናት እርሱ የሰውን ባሕርይ ከራሱ ጋር አስማማ። ራሱ ካህን፣ ራሱ መስዋዕት፣ ራሱ ተቀባይ ሆኖ የፈጸማት የክህነት ሥራው የዘለዓለም ድኅነትን አስገኘች።

ለሞቱ ከርቤ ቀረበለት። እነሆ እግዚአብሔር ሰው የሆነበት ዋናው ምክንያት በሞቱ ሞትን ድል ለመንሣት ነውና በልደቱ ሞቱ ተሰበከ። ከርቤ ለሞቱ ሲቀርብለት የማይሞተው እርሱ ለሰው ልጆች ሲል የሚሞት ሥጋን እንደለበሰ ታወቀ።

የአሕዛብ ነገሥታት ወርቅ ገበሩለት፤ ምእመናን ደግሞ ጽሩይ፣ ንጹሕ፣ ሰማያዊ የሆነ ልቦናን እና እምነትን ለእርሱ እናቀርባለን። (1ኛ ጴጥ.1፥6) ሰብዐ ሰገል እርሱ የፈጠረውን ወርቅ ገበሩለት፤ እኛም በርሱ ጸጋና ሥራ ያገኘነውን ንጹሕና ሰማያዊ እምነታችንን እናቀርብለታለን።(ይሁ.3)

ነገሥታቱ ዕጣን ገበሩለት፤ ምእመናን ደግሞ ቂም በቀል የሌለበትን፣ ከመልካም እና ንጹሕ ልብ የሚወጣ የምስጋና ጸሎት እናቀርባለን፤ “ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ፥ እጅ መንሣቴንም እንደ ሠርክ መስዋዕት ትሁን።” እንዳለ ንጉሥ ዳዊት።(መዝ.140፥2)

ስለሰው ልጆች ፍቅር ሲል ለሚቀበለው ሞት ከርቤ ገበሩለት፤ ምእመናን ደግሞ ለእግዚአብሔርና ለሰው ልጆች ያለንን ፍቅር ለእርሱ እናቀርባለን። ነገሥታቱ እርሱ ከፈጠረው ከርቤ ወስደው እጅ መንሻ አቀረቡ፤ ምእመናን ደግሞ ከእርሱ ከተማርነው፣ ከመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ከተቀበልነው ፍቅር መልሰን ለእርሱ እናቀርባለን። “እርሱ ስለኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቷልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል(1ኛ ዮሐ.3፥16)።”

ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክብር አሜን!!!

 ምንጭ፦ ማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ታኅሣሥ 27/2004 ዓ.ም

Tuesday, December 31, 2013

ታኅሳስ ፳፪ - ብስራተ ገብርኤል (“ትጸንሲ”)


በቤተ ክርስቲያናችን አስተምሮ መሰረት ታኅሣስ 22 መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ጌታን እንደምትፀን የአበሰረበት ቀን ነው።  
‹‹እንዘ ትፈትል ወርቀ ወሜላተ ወሪዳ ምድረ ቆላ ገብርኤል መጽአ እንዘ ይረውጽ በሰረገላ ክንፎ ክንፎ ክንፎ ጸለላ ተፈስሒ ተፈስሒ ለድንግል ይቤላ፤ ወደ ቆላው ምድር ወርዳ እመቤታችን ወርቅን ከሐር ጋር አስማምታ እየፈተለች ሳለች መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በሰረገላ እየሮጠ መጣ፣ ክንፉንም እያማታ እየሰገደ ድንግል ሆይ ደስ ይበልሽ አላት›› እንዲል ደራሲው አንድም “ተፈሥሒ ፍሥሒት ኦ ምልዕተ ጸጋ፤ ጸጋን የሞላብሽ ሆይ ደስ ይበልሽ” ሉቃ 1፡28 “ስብሃት ለኪ ማርያም እሙ ለፀሃየ ጽድቅ ለአብ ሙሽራው ለወልድ ወላዲቱ ለመንፈስ ቅዱስ ጽርሃ ቤቱ ተፈስሂ ደስ ይበልሽ” እንዳሉ አበው፡፡
እመቤታችን የብፅዓት ልጅ ናት። ሶስት ዓመት ሲሆናት አባት እናቷ ለካህን ሰጥተዋታል፤ ካህናትም በቤተ መቅደስ ከመካነ ደናግል አስገብተዋት ፲፪ ዓመት በቅዱስ ፋኑኤል አማካኝነት ኅብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ሰማያዊ እየመጣላት ያን እየተመገበች መላእክት እየጎበኟት ኖራለች። ፲፭ ዓመት ሲሆናት ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ጌታን እንደምትወልድ በዚህ ቀን ብስራቱን ነገራት። ውሃ ቀድታ ስትመለስ የጠተማ ውሻ እያለከለከ ሲመጣ በወርቅ ጫማዋ ለዛ ለተጠማው ውሻ ውሃ ስታጠጣ አብሯት የነበሩ ሴቶች ማድጋሽን አጎደልሺው፤ ቀድቼ እሞለዋለሁ እንዳትይ ጉድጓዱ ጥልቅ ነው መቅጃም የለሽም አሏት። “ውሃ የሚገኘው ከወደላይ ነው እንጂ ከወደታች ነውን ፍጥረቱን ያጠጣ ጌታ ይሞላልኛል” አለቻቸው። በተዓምራትም ሞልቶላታል። “በዚህ ዘመን አምላክ ከድንግል ይወለዳል ይላሉ ካንቺ ይሆን?” ብለው ዘበቱባት። ወዲያ ከወደኋላዋ ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ “ትጸንሲ” አላት። ዞር ብትል አጣችው። አባቴ አዳምን እናቴ ሔዋንን ያሳተ ጠላት ይሆናል ብላ ሄደች።
ከቤት ደርሳ ማድጋዋን ስታስቀምጥ ዳግመኛ “ትጸንሲ” አላት። ይህ ነገር ደጋገመኝ እንዲህ ያለውን ነገር ቤተ መቅደስ ሄደው ሊረዱት ይገባል ብላ ወደ ቤተ መቅደስ ሄዳ በወርቅ ወንበሯ ተቀምጣ ከደናግለ እስራኤል ጋር የተካፈለችውን ወርቅና ሐር እያስማማች ስትፈት ቅዱስ ገብርኤል ተገልጾ “ተፈሥሂሒ ፍሥሒት ኦ ምልዕተ ጸጋ፤ መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ። ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት። እርስዋም ባየችው ጊዜ ከንግግሩ በጣም ደነገጠችና። ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው? ብላ አሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት። ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም። ማርያምም መልአኩን። ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት። መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። እነሆም ዘመድሽ ኤልሳቤጥ፥ እርስዋ ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፥ ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና። ማርያምም። እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለች። መልአኩም ከእርስዋ ሄደ።” ሉቃስ ፩፡፳፰-፴፰ እንዲል ወንጌል።
“ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ፤ ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም፤ በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ፡፡(አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም)
አበው አባቶችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስተቲያን እንሚያስረዱንና እንደሚያስተምሩን መልአኩ ብስራቱን የነገጋት መጋቢት 29 ቀን በዕለተ እሁድ ከቀኑ ሦስት ሰዓት ላይ ነው። ታዲያ ዛሬ ለምን እናከብረዋለን ለሚለው ጥያቄ፤ ምንጊዜም ወርሃ መጋቢት ታላቁ ዓቢይ ጾም የሚውልበት ወር ነው፤ በዚህ በዓቢይ ጾም ደግሞ ሐዘን፤ ለቅሶ፤ ጾም፤ ጸሎት እንጂ ደስታ፤ ፌሽታ እልልታ፤ ጭብጨባ የለም። ፍጹም የሐዘን ወራት ነው፤ ታቦት አውጥቶ በዓል ማክበርም ስህተት ነው። ፍትሃ ነገስት አንድምታ አንቀጽ 15 ተመልከት ፤ ታዲያ ቅዱሳን አባቶቻችን እንደዚህ ዓይነት ስርዓት ሰሩ፤ የመጋቢት 27 ስቅለቱን ጥቅምት 27 ቀን እንዲሁም የመጋቢት 5 አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ዕረፍት ቀን ወደ ጥቅምት 5 ቀን ዞሮ እንዲከበር አደረጉ፡፡ የመጋቢት 29 ብስራቱን ደግሞ ታህሳስ 22 ቀን ዞሮ እንዲከበር ያደረገው ታላቁ አባት የጥልጥልያ ኤጲስ ቆጶስ ደቅስዮስ ይባላል። ደቅሲዮስ በተጨማሪም የእመቤታችንን ተዓምራቶቿን የጻፉ ታላቅ አባት ነው። በእመቤታች ፍቅር ልቡ የነደደ ታላቅ ጻድቅም ነው። የእመቤታችንን ታአምራቷን የሚናገር መጽሐፍ የሰበሰበ አባት ነው፡፡ የጌታን ልደት ከመከበሩ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ብስራቱ መከበር አለበት ብሎ ስርዓት ሰራ። አገሬውንም ሰብስቦ ታላቅ የደስታ በዓል አደረገ። እመቤታችን ተገለጸችለት ወዳጄ ደቅስዮስ ባንተ ደስ አለኝ። እንዳከበርከኝ እኔም አከብርሃለው አለችው። ሰማያዊ ልብስና ሰማያዊ ወንበር ሰጠችው ይህችን ልብስ ካንተ ሌላ ማንም አይለብሳትም፤ ይህችንም ወንበር ካንተ ሌላ ማንም አይቀመጥባትም አለችው። የዚህ ታላቅ አባት ዕረፍቱ ታህሳስ ፳፪ በዛሬዋ ቀን ነው። ከእርሱ በኋላ ሌላ ኤጲስ ቆጶስ ተሾመ ልብሱን እለብሳለው በወንበሩም እቀመጣለው አለ፤ ተው ይቅርብህ እመቤታችን እንዲህ ብላ ተናግራለች ይሉታል፤ እርሱም ሰው እኔም ሰው እርሱም ኤጲስ ቆጶስ እኔም ኤጲስ ቆጶስ ብሎ በትዕቢት ልብሱን ለበሰው። በወንበሩም ተቀመጠ ክፉኛ አወዳደቅ ወደቀ ሞተም። ይህን ያዩ እመቤታችንን በጣም ፈሯት ይላል ተዓምረ ማርያምን ተመልከት፡፡ ደቅስዮስ ሰርቶልን ያለፈውን ስርዓት ቤተክርስቲያን ተቀብላ ይኸው ዛሬም ድረስ ታከብረዋለች። በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ ብስራተ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ታቦተ ህጉ ወጥቶ በደማቅ ተከብሮ ይውላል፡፡ 
ከእመቤታችን ከወላዲተ አምላክ እንዲሁም ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፡ አሜን!

Sunday, December 29, 2013

ከሳውዲ አረቢያ በግፍ ተገፍተው ለተመለሱ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ምን እየተደረገ ነው?

                                     ፎቶ፡ ምሳ ግብዣ በማኅበረ ቅዱሳን

የተለያዩ የዜና ምንጮች እንደገለጹት ከሳውዑዲ አረቢያ በግፍ ተገፍተው የተመለሱ ኢትዮጵያን ቁጥር ከመቶ ሺ በላይ ደርሰዋል። አሁን በዋናነት ማንሳት የፈለኩት ስለ ቁጥር መጠናቸው ትክክለኛነት፣ ያሳለፉትን ስቃይና መካራ፣ ማን በአስቸኳይ ደረሰላቸው ወይም በምን መልኩ ትውልድ ሀገራቸው ተመለሱ የሚለውን የትናት ገሀዳዊ እውነታ መተረክ ሳይሆን ለእነዚህ ወገኖቻችን ምን እየተደረገላቸው ነው የሚለውን ጥያቄ አዘል ሃሳቤን ለማካፈል ነው።
ለእነዚህ ለተጎዱ ወገኖቻችን በህብረትና በግል የውስጥ ሃዘናችንን በእንባ፣ በልቅሶ፣ በጩኸት የዓለም ጀሮ በቃኝ እስኪል ድረስ ገልጸናል፤ ተናግረናል፤ ጽፈናልም። መቼም ቢሆን ሀዘኑና ድርጊቱ ከልባችን አይጠፋም። ይህ በራሱ አንዱ የአንድነታችን መገለጫ ነው። ይህን አንድነታችንንና ሃዘናችንን ወደ ተግባር ቀይረን ማሳየት ብንችል የበለጠ ለእኛ ለህሌናችን ውስጣዊ እርካታ፤ ለተጎዱ ወገኖቻችን ደግሞ መጠገኛ/መቋቋሚያ ይሆናቸዋል።
በእርግጥ ድርጊቱ ከተፈጸበት ጊዜ ጀምሮ በተለያየ መልኩ ከግለሰብ እስከ ተለያዩ ማህበራት ድረስ እርዳታ ለመስጠት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። ይህ ጥረት ግን ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ሁላችንም ልዩ ትኩረት ልንሰጥበት የሚገባ ተግባር ነው። እንዴትና በምን መልኩ ለወገኖቻችን ልንደርስላቸው እንደ ሚገባ በግልጽና ታማኒነት ባለው መልኩ እንቅስቃሴያችንን ማስኬድ ይኖርብናል። ለዚህ ተግባር ግልጽነትና አንድነት ተግባራዊ የሆነ ሥራ ለመስራት በእጅጉ ያስፈልጉናል።

  ሀ. አንድነት፦ ለዚህ በጎ ተግባር ድጋፍ ለማድረግ ሰው መሆን ብቻ በራሱ በቂ ነው። ችግሩን በትክክል ለተገነዘበ ሰው ሌላ የተለየ ቅስቀሳ አያስፈልገውም። በተለይ ደግሞ  በውጭው ዓለም ያለ ሰው በአንድም በሌላም የችግሩ አካል በመሆኑ ለዚህ ተግባር ግንባር ቀደም ድጋፍ ሰጭ እንደሚሆን እርግጠኛ ሁኖ መናገር ይቻላል። አስተባባሪ አካላት ግን መንግስት፣ ተቃዋሚ፣ ጾታ፣ ብሄር፣ ሃይማኖት፣ ድርጅት፣ ማህበር ፣ የውጭ የውስጥ ብሎ ልዩነት ሳይፈጥሩ በአንድነት ማስተባበር ከቻሉ በቀላሉ ተጎጅዎችን ማቋቋም የሚቻልበትን መስመር መዘርጋት ይቻላል።  ይህ ችግር ሃገራዊ እንጂ የአንዱን ቡድን ብቻ የሚመለከት አይደለም። ቢሆንም እንኳ ከጠባብነት የአስተሳሰብ ጎራ ተላቀን ለዚህ በጎ ተግባር አንድነት መፍጠር ይኖርብናል። ይህን ችግር ምክንያት አድርጎ ፖለቲካዊም ሆነ ሌላ የተለየ ጥቅም ለማግኘት መሞከር ደግሞ ከሰባዊ ነት ወደ እንስሳዊነት ባህሪ የመቀየርን ያክል አሳፋሪ ይሆናል።  ስለዚህ ሁላችንም በተለይ አስተባባሪ አካላት በመካከላችን የቱንም ያህል ልዩነት ቢኖርም ለዚህ አንገብጋቢ ተግባር ከማነኛውም ሰው ጋር በቅንጅት ድጋፍ ለማድረግ መወሰን እና መስራት ይኖርብናል። 
  ለ. ግልጽነት፦ በዚህ በአለንበት ዘመን የቱንም ሥራ ለመስራት ግልጽነት ያስፈልጋል። ግልጽነት የጎደላቸው ተግባሮች ሁሉ ውጤታቸው እዚህ ግባ የባይባል ነው። ለዚህ በጎ ተግባር ገንዘብ ከመሰብሰብ ጀምሮ እንዴትና በምን መልኩ ለተቸገሩ ወገኖቻችን ሊደርሳቸውና ምን አይነት ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደታሰበ በግልጽ ለእኛንዳንዱ ህብረተሰብ መንገር ያስፈልጋል። ግልጽ መሆናችን 3 ጥቅሞች አሉት። አንድ ድጋፍ የሚሰጡ ሁሉ ከፍራቻ፣ ከጥርጣሬ እና ከሌላ እይታ አልፈው የተቻላቸውን ያክል ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ያደርጋል። ሁለት ለአስተባባሪዎችም ሆነ ገንዘብ ለሚሰበስቡት ሁሉ ታማኝነት ያገኛሉ። ነጻ ሁነው ማንኛውንም ሰው ለዚህ ድጋፍ ተባባሪ እንዲሆን መጠየቅ ይችላሉ። ሦስት ድጋፍ የሚደረግላቸው ወገኖች የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። ምክንያቱም በግልጽነት የምንሰበስበው የገንዘብ መጠን የተሻለ እና የታሰበውን ፕሮጀክት መሸፈን የሚችል በቂ ገንዘብ መሰብሰብ ስለሚቻል ነው። ግልጽነትን ካለምክንያት አላነሳሁትም ለዚህ ድጋፍ ተብሎ አገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም የተለያዩ ተቋማትና ግለዘቦች ገንዘብ ለመሰብሰብ በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። እየሰበሰቡ ያሉም አሉ። ነገር ግን ገንዘብ ከመሰብሰብ ውጭ እንዴት፣ በምን መልኩ እና ግንኙነቱ ከማን ጋር የሚሉ መሰረታዊ ጥያቂዎችን በግልጽ ለማወቅ አልተቻለም። ስለዚህ ለእነዚህ እና ለመሳሰሉት ጥያቄዎች ግልጽነታችን በጣም አስፈላጊ ስለሚሆን እያንዳንዷን እንቅስቃሴ በግልጽነት ማካሄድ የሚቻልበትን መስመር ዘርግቶ መንቀሳቀስ ከምንም በላይ ትኩረት ልንሰጥበት የሚገባ ተግባር ነው።

ከላይ ያነሳኋቸውን መሰረታዊ ነገሮች አንድነትን እና ግልጽነትን ሰንቀን ድጋፋችን ዘላቂነት እንዲኖረው ኃላፊነቱን ደረጃ በደረጃ መውሰድ ይኖርብናል።
1.      መንግሥት፦  ምንም እንኳ አስተዳደራዊም ሆነ ሌሎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች በአገሪቱ ውስጥ ቢሰፍኑም ለዚህ ችግር ግንባር ቀደም መፍትሄ ሊሰጥ የሚገባው አካል መንግሥት ነው። ይህን ማድረግ አልነበረበትም? የችግሩ መንስኤ መንግሥት ራሱ ነው? እና ሌሎችንም ጥያቄዎች በትችት መልክ ሁልጊዜ ማንሳቱ ለውጥ ሊያመጣልን አልቻለም። በእርግጥ በተለያየ መልኩ አቅጣጫ የሚያሳዩ ኢትዮጵያውያዊ ሙህራን በርካታ ናቸው። ምናልባት አብዛኞቹ ከትችት ስለሚጀምሩ ሃሳባቸውን ላለመቀበል ምክንያት ሊሆን ይችል ይሆናል። ሆኖም ግን ጠቃሚ ሃሳቦችን መውሰድ ደግሞ ብልህነት ነው።
መንግሥት እንደ መንግሥት ካሰበ በግፍ ወደ ሃገራቸው ለተመለሱ ወገኖች ዘላቂነት ባለው መልኩ ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል። በአጭሩ ሦስት ተግባራትን መከተል ቢቻል ዘላቂነት ያለው ድጋፍ ማድረግ ይችላል።
Ø  ወደ አገር የተመለሱትን ስም ዝርዝርና በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉበትን አድራሻ መያዝና ስለ እያንዳንዱ በቂ መረጃ መሰብሰብ(የት/ት ደረጃ፣ የሥራ መስክ፣ የቤተሰብ ሁኔታ፣ ፍላጎት)። ከምንም አድሎአዊነት ነጻ ሁኖ በትክክል እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ማወቅና መለየት።
Ø   በሰበሰብነው መረጃ መሰረት ሁሉን ሊያካትት የሚችልና ዘላቂ ፕሮጀክት መቅረጽ። ለምሳሌ፦ ለውጭ ባለ ሃብቶች የምንሰጠውን መሬት ማለትም የእንስሳት ልማት፣ የአበባ ልማት፣ እና የተለያዩ የንግድ ሥራወችን  ዘመናዊ በሆነ መልኩ ሊሰሩ የሚችሉበትን እድል ማመቻቸት። እንዲሁም መማር ለሚፈልጉ ነጻ የትምህርት እድል መስጠት።
Ø    ፕሮጀክቱ ዘላቂነት እንዲኖረው እና ትርፋማ ሁኖ በትክክል ለተፈለገው ዓላማ እንዲውል የባለሙያ ድጋፍና ክትትል እንዲያገኝ ማድረግ። 

2.   ማህበራትና ተቋማት፦ ሊታይና ሊቆጠር የሚችል ፕሮጀክት ቀርጾ ገንዘብ መሰብሰብ። ፕሮጀክቱ የት፣ ለእነማንና በምን መልኩ ሊተገበር እንደሚችል ይፋ ማድረግና ገንዘብ ሊገኝ ከሚችልባቸው የመንግሥትም ሆነ የግል ድርጅቶች፤ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ መሰብሰብ። ለዚህ ተግባር ይመለከታቸዋል ከምንላቸው ድርጅቶች ጋር በቅንጅት መስራት ድጋፋችንን ዘላቂነት እንዲኖረው ያደርግልናል።
በተለይ በውጭው ዓለም ገንዘብ ከመሰብሰብ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግ በተለያየ መልኩ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። ይህን እንቅስቃሴ ተግባራዊ ለማድረግ አገር ውስጥ ከአሉ ድርጅቶች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ማድረግ እና በውጭ በተለያዩ  ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ዘላቂነት ባለው መንገድ የሰባዊ መብት ጥሰትን ማስቆም የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ትልቅ ተግባርና ሃላፊነት ነው።

3.   ባለሙያዎች፦ ለዚህ በጎ ተግባር ዘላቂነት ያለው ፕሮጀክት ከመቅረጽ ጀምሮ ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ በራስ ተነሳሽነት ለሚመለከታቸው አካላት ሃሳባችንን ማካፈል። ሁሉም የሙያ ዘርፍ በተለያየ መልኩ ስለሚያስፈልግ እኔ አላስፈልግም ሳንል ለወገኖቻችን ድጋፍ መስጠት ከቻለን በቀላሉ ለችግሩ መፍትሔ ማግኘት የሚቻልበትን አማራጮች ማስቀመጥ ይቻላል።

በአጠቃላይ በግፍ ወደ ሃገራቸው ለተመለሱትም ሆነ በዓለም ላይ ኢ_ሰባዊ ድርጊት የሚፈጸምባቸውን ኢትዮጵያውያንን ለመታደግ የእያንዳንዳችን ድርሻ ወሳኝ መሆኑን ተረድተን ዜጋዊ ኃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል። የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ መረጃ ከመስጠት ጀምሮ ኢ_ሰባዊ ድርጊቶችን ማስቆም የሚቻልበትን መንገድ ማመቻቸት ጊዜ የማይሰጠው ተግባር መሆን ይኖርበታል የሚል ጽዕኑ እምነት አለኝ። ኮሚቴ ማቋቋም ብቻ ትርጉም የለውም። እንዲህ ሰሩ ለመባል ሳይሆን ተግባራዊ ስራ ሰርተን አገራዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ።   


Saturday, December 7, 2013

ኔልሰን ማንዴላ

ይህንን ፎቶ ሳነሳ ሁለት አይነት ስሜት ተሰማኝ። የመጀመርያው የኩራት፣የደስታ ስሜት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሃዘን ስሜት ተሰማኝ። ብዙ አፍሪካውያን በዓለም በበርካታ ስራዎች የሚታወቁ ሰዎች እንዳሉ ቢታወቅም እንደ ኔልሰን ማንዴላ ግን በመሪነት ደረጃ ለአለም ምሳሌና አርያ የሆነ የለም። በዚያ ላይ ከብዙ ስቃይና መከራ ፣ እንግልትና እስር በኋላ የሰላም፣ የነጻነት፣ የአንድነት፣ የይቅርታ አባት መሆን በእጅጉ ታላቅነት ነው። የበደሉትን፣ያሰቃዩትን፣ አንተ ጥቁር ሰው አይደለህም ከነጮች ጋር አብረህ ልትኖር፣ ልትማር ፣ በአንድ ባስ ውስጥ ልትጓዝ አይገባይህም ብለው አዋጅ አውጀው በመላ ጥቁር ደቡብ አፍርካውያን ላይ ከባድ ወንጀል የፈጸሙትን ለሰላምና ለአንድነት ሲል በይቅርታ እንዲታለፉ ያደረገ ታላቅ የይቅርታ አባት መሆኑን ዓለም ሁሉ በአንድ አፍ ሲመሰክር ሳይ በባዕድ አገር የደስታ ስሜት ተሰማኝ።

በተቃራኒው ደግሞ ይህን ታላቅ ሰው እርጅና የሚሉት በሽታ፣ ሞት የሚሉት ለሰው ልጅ አይቀሬ እጣ ፈንታ ሲነጥቀን ያለ ቢሆንም ሐዘን ተሰማኝ፡፡ በይበልጥ ግን ዓልም ይቅርባይነት ጠፍቶባት፣ መቻቻል አቅቷት፣የበቀልና የጥላቻ መንፈስ ነግሶባት እያየ ታላቁ ማንዴላ አንድ ሰው እንኳ ሳይተካ ማለፉን ሳስብ ደግሞ ሐዘኔ ይበልጥ በረታ። ግን እኮ ማንዴላ ፍቅርን፣ ይቅርባይነትን፣ መቻቻልን፣ የውይይት/ድርድር ልምድን በተግባር አሳይቶናል። እኛ እንዴት ከእሱ መማር አቃተን? ምነው ለይቅርታ ዘገየን? ምነው ለበቀል ቸኮልን?
ታላቁን የሰላም አባት ማንዴላን ለማስታወስ በኖርዎይ ኦስሎ ዩኒቨርስቲ ብሊንደር ላይበራሪ መግቢያ በር ላይ በትልቅ ጠረጴዛ የእርሱ ፎቶና ስለ እርሱ የተጻፉ መጻሕፍት ከተቀመጠበት በ06/12/2013 እኤአ ያነሳኋቸው ፎቶዎች ናቸው።