Monday, September 30, 2013

400,000 ብር እና አዲስ ፕሬዝዳንት

በአዲስ ዓመት እንደ አገርም እንደ ግለሰብም አዲስ ሥራ ለመሥራት ይታቀዳል። በዚህ አመት ደግሞ ልዩ የሚያደርገው አገራችን ኢትዮጵያ ፕሬዝዳንታዊ "ምርጫ" (ምርጫ የሚለውን ቃል የተጠቀምኩት ሕገ መንግሥቱን ለማክበር እንደ ሆነ ይታወቅልኝ) የምታካሂድበት ጊዜ መሆኑ ነው። መንግሥት (አገራችን ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ ስለሚሆን ነው) በሕገ መንግሥቱ መሰረት በየስድስት ዓመቱ የአዲስ ፕሬዝዳንት ምርጫ ያካሂዳል። በዚህ አመትም ክቡር ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የ12 አመት የፕሬዝዳትነት ስልጣናቸውን የሚለቁበት ጊዜ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ 2 አነጋጋሪ ጉዳዮች ጎልተው ወጥተዋል።

1. ቀጣይ አገሪቱን በፕሬዝዳትነት ማን ይምራት

 ለአገራችን እድገትና ሰላም የሚያስቡና የሚቆረቆሩ ምሁራን በተለያየ መልኩ አገሪቱን ማን ቢመራት የተሻለ ሊሆን ይችላል ብለው ሃሳባቸውን በማካፈል ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል በኖርዎይ ኦስሎ, ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሴር ተክሉ አባተ በጡመራ ድረ ገጻቸው ላይ ሃሳባቸውን አስቀምጠዋል።

በአንድም በሌላም አገራችንን የተሻለ ሰው ቢመራት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ምኞት ነው። ነገር ግን ማነው የተሻለውን ሰው በፕሬዝዳንትነት ቦታ ላይ እንዲቀመጥ ማድረግ የሚችል የሚለው ትልቁ ጥያቄ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ መቀመጥ ቢችልስ አቅሙንና እውቀቱን ተጠቅሞ መስራት የሚችልበት ከባቢያዊ አየር አለ ወይ ነው። በግልጽ ቋንቋ መንግሥት እንዲህ አይነት ሰዎችን ይፈልጋል ወይ የሚለው የሁላችንም ገሃዳዊ ጥያቃችን ነው።

ስለ አዲስ ፕሬዝዳንት ስናነሳ በስፖርቱ አለም ታዋቂነትን ያተረፈውና አገራችን ኢትዮጵያን ለአለም ስሟን ያስተዋወቀው አንበሳው ኃይሌ ገ/ስላሴ በምርጫው እንደሚሳተፍ የተገለጸበት ሌላው ትልቁ ወቅታዊ ጉዳይ ነው።



ኃይሌ ገ/ስላሴ Google pic

ኃይሌ ገ/ስላሴ በህብረተሰቡ በኩል ትልቅ ቦታና ክብር ያለው ሰው እንደ መሆኑ መጠን በዚህ ምርጫ የሚሳተፍ ከሆነ ብዙ ነገሮችን መመልከትና መወሰን ይኖርበታል።

  1. የመንግሥትንና የህብረተሰቡን የአንድነት ሁኔታ
  2. የመንግሥትን ምንነት(እውቀቱንና ስልጣኑን በነጻነት መጠቀም መቻሉን)
  3. በመንግሥትና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ያለውን ልዩነት
  4. በመንግሥትና ውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውን መካከል ያለውን ልዩነት
  5. ለቀጣይ 6 ወይም 12 አመት አገሪቱን በፕሬዝዳትነት ለመምራት የሚያስችል በቂ እውቀት መኖሩን ...ወዘተ
ወደ ምርጫ ከመግባቱ በፊት እነዚህንና መሰል ነገሮችን በሚገባ ማጤን ይኖርበታል። ነገሮችን ሳይመለከት ቢገባ ግን ክብሩንና የወደፊት ጉዞውን በቀላሉ ሊያጣ እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ምክንያቱም የአገራችን መንግሥት በህብረተሰቡ ዘንድ በተለያየ መልኩ ተቀባይነቱ በእጅጉ የቀነሰበት ሁኔታ ላይ በመሆኑ የኃይሌንም የወደፊት ጉዞ አስቸጋሪ እንዳያደርግበት የብዙዎች ሃሳብ ነው።

2. የክቡር ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የወደፊት የኑሮ ሁኔታ




የክቡር ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የወደፊት ሕይወት ነው። ከኃላፊነት የተነሱት የአገርና የመንግሥት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የምክር ቤት አባላትና ዳኞች የሚያገኙዋቸውን መብቶችና ጥቅሞች ለመወሰን መንግሥት ባወጣው አዋጅ መሰረት ለተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ቤት በወር 400,000 ብር መከራየቱን ጠቅሳል፡፡ ይህ ከፍተኛ የቤት ኪራይ ወጪ ግን ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ሲገናዘብ ለማመንና ለመቀበል አስቸጋሪ ነው። እኔ ግን ትልቅ ጥያቄ የፈጠረብኝ መንግሥት ለፕሬዝዳንቱ የተከራየው ቤት መኖርያ ወይስ የንግድ የሚለው ነውና ደሞዛቸውስ ስንት ነበር የሚለው ነው። መኖርያ ቤት እንደሆነ ደግሞ ተገልጾልናል፤ ነገር ግን መኖርያ ቤት ይህን ያክል ወጪ እንዴት ሊያወጣ ቻለ የሚለው የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
ስለዚህ አገሪቱ ለአንድ ከኃላፊነት ለለቀቀ ባለስልጣን ለቤት ኪራይ፣ ለመኪና፣ ለሰራተኛ፣ለህክምና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ጨምሮ ከፍተኛ ገንዘብ በወር ወጪ ታደርጋለች ማለት ነው። ይህን ጉዳይ መንግሥት ለአገራችን በምን ያክል መጠን እንደሚያስብ በጥልቀት ለመረዳት በጎ አጋጣሚ ፈጥሮልናል።
በዚህ ዙርያ የእኔ ሃሳብ ይህን ያክል የአገሪቱን ገንዘብ ወጪ ከማድረግ ይልቅ መንግሥት ከኃላፊነት ለሚለቁ ከፍተኛ ኃላፊዎች የሚሆን ቤት ቢያስገነባ የተሻለ ይሆናል። ምክንያቱም የሚገነባዉ ቤት ለወደፊት የአገሪቱ ቋሚ ንብረት ይሆናል፤ ከዚያም በላይ ለኪራይ በየወሩ የሚወጣውን ከፍተኛ ገንዘብ ይቀንሳል።



Saturday, September 14, 2013

ሰው እና ሕገ ሕሊና/ተፈጥሯዊ ሕግ

ሰው ማነው? ብሎ ለጠየቀ “ሰው ንግግሩን ይመስላል” እንዳትለኝ ንግግሩ እምነቱንና ሃሳቡን ሙሉ በሙሉ የሚያመለክት ዕውቀት አይሆነውምና ነው፡፡ በተለይ ከዘመኑ ድርጊታችን ስንመለከተው ንግግራችን እና ድርጊታችን ፍጹም ተቃራኒ ሁኖ እናገኘዋለን። ለሰው ባሕርያዊ ተፈጥሮና ዕውቀት ምስክሩ ውስጣዊ የአዕምሮ አቋምና የሕሊና ሕግ ነው ብለንም አንደመድምም፡፡ ሰው እንዲያውቅ የተመደበለት የሕግ ተፈጥሮ ዕውቀት መጀመሪያ ክፍል መልካምን ማወቅ፡፡ ሁለተኛ ክፋትን ንቆ መልካምን ገንዘብ ማድረግ፡፡ ሦስተኛ መልካምን በግብር መግለጽ ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቱያን ሊቃውንት ይሁዳን ሲገልጹ “በአፍ አምኖ በልቡ የካደ” ይሉታል፡፡ ባህላችን “አፈ ቅቤ፤ ሆደ ጩቤ” እንዲል፡፡ ይሁዳ በጊዜያዊ ጥቅም ተታሎ ለሕሊናው መገዛት ስላልቻለ አምላክን ያህል ጌታ ለሞትና ለስቅላት አሳልፎ ሸጠ። ከሐዋርያት ማኅበርም በእራሱ ድርጊት ተለየ።
የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር መሠረት ሕገ ልቦና/ሕሊና ስንል ያለ ትምህረት በተፈጥሮ የሚሰጥ ሲሆን ይህም ሕገ ልቦና፤ ሕገ ህሊና፤ ሕገ ተፈጥሮ ወይንም ሕገ ጠብዓያዊ በመባል ይታወቃል፡፡ ሕገ ኦሪትና ሕገ ወንጌል፤ ሕገ ሕሊናን ይተረጉማሉ፡፡ ለአብነት ብንጠቅስ አዳምና ሔዋን ቅዱስ ዳዊትትን፣ ቅዱስ ጴጥሮስንና ይሁዳን፤ ከመጸጸት ክፉዎችን ከማዘን የምታደርሳቸው የሕሊና ኮሽታ ነች፡፡ በኑሮ ሂደት ሀዘን፣ ጸጸት ርትዕ በምናደርግበት ጊዜ ልዩ መንፈሳዊ ጥበብ አልያም ዕውቀት በመታደል ሳይሆን ሰው በመሆናችን በሕሊና ውስጥ የተቀረጸ በህሊና ሚዛን የሚሰጥ ፍርድ በመኖሩ ነው፡፡ ለምሳሌ አብርሃምን ስንመለከት ምንም የተጻፈ ሕግ፣ ሰባኪና መምህር ባልነበረበት ወቅት በሕገ ልቦና/ሕሊና ተመርቶና ተመራምሮ ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር ችሏል። አባቱ ታራ ይከተለው የነበረው መንገድ እጅግ ስህተት መሆኑን ተረዳ። ለከዚህም በተጨማሪ ሕገ ሕሊና በጽሑፍ ከተሰጡን ሕግጋት /ሕገ ኦሪት፣ ሕገ ወንጌል፣ ማሕበራዊ ሕግ/ በላይ ሰማያዊና ምስጢርን ለመጠበቅ ሲያገለግል እናገኘዋለን፡፡ የቤተ ክርስቲያን የሀገር የግል ምስጢር ይጠበቅ ዘንድ መንፈሳዊ ሕግና ማህበረሰባዊ ሕግ ይደነግጋል፡፡ የአምላክ እናት ድንግል ማርያም ያለ ምድራዊ ሕግ አስገዳጅነት በሕገ ልቦና ዳኝነት ለሰማያዊ ምስጢር የታመነች ነበረች “እናቱ ማርያም በልቧ ትጠብቀው ነበር” እንዲል፡፡ /ሉቃ.2÷19/፡፡
“ሰው ራሱ መጽሐፍ ነው” የሚለው የአነጋገር ስልት የሚያስተላልፈው ሰው ይነበባል፤ ይጠናል፤ ይተነተናል፤ ይጸድቃል፤ ይሻራል ለማለት ነው፡፡ ከሌሎች ሥነ ፍጥረታት በላይም አስተማሪና ሚስጢራዊ ነው። እነዚህን ተግባራት ለሌሎችም ሆነ ለራሳችን ለድርጊታችን ብያኔ ፍርድ ለመስጠት ረቂቅ የሕሊና ልጓም እንደ መሠረት ሆኖ ያገለግላል፡፡ ሰው በውስጡ የሚያረጋግጣት እውነት በክበበ አዕምሮ በሚጨበጥ ሕገ ባሕርይ ከመገለፅ እምቢ አትልም፡፡ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት እምነት በቅድሚያ እንዲገኝ ግድ ቢሆንም በተግባር ወይንም በድርጊት ካልተዋሃደ ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ፍሬ ቢስ፤ ረብ የሌለው ከንቱ ድካም ይሆናል፡፡ ለመሆኑ እምነታችን ከድርጊታችን ለምን ተዛነፈ? በጽናት የምናምነውን እምነት አጥቦ የመውሰድ ብቃት ያለው ሃይል ይኖር ይሆን? በዕለት ተዕለት ማኅበራዊ መስተጋብር የምንወስናቸው መጠነ ሰፊ ጥቃቅን ውሳኔዎች ውህደ ሃይማኖት ምግባር የታሹ ወይስ የስሜት ውጤቶች ናቸው? እርግጥ ነው ስሜት አልባ ሰብአዊ ፍጡር ሊሆን አይችልም፡፡ 
ነገር ግን ነፍስን ደስ የሚያሰኝ ሰማያዊ እውነት ከስሜት በላይ ነው፡፡ እውነት ደግሞ በሕገ ሕሊና ያለ አምላካዊ ሕግ ነው። ሕጉን ያለመፈጸም እንጂ መካድ አይቻልም ምክንያቱም ተፈጥሮአዊ ሕግ ነውና። ሰው ድርጊቱን ምክንያታዊ ቢያደርገውም እውነቱን ግን በትክክል ሕሊናው ይነግረዋል። ከሰው ሊሰወር ይችላል ከሕሊናው ግን መሰወር አይችልም። ብዙ ሰዎች ትክክል ያልሆነ ድርጊት ለመፈጸም ከአሰቡበት ጊዜ ጀምሮ ከራሳቸው ጋር ይሟገታሉ፤ ልፈጽመው ወይስ ይቅርብኝ በማለት። እውነቱንና ትክክለኛውን መንገድ ግን ሕሊናቸው በተለያየ መንገድ ያሳውቃቸዋል። ቅዱስ ጳውሎ እንደተናገረው "እነርሱም ሕሊናቸው ሲመሰክርላቸው፥ አሳባቸውም እርስ በርሳቸው ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ።"(ሮሜ 2፥15)
በገሃዱ ዓለም በብዙዎቻችን ሕይወት የሚታየው ውሳኔዎቻችን በድካም ባካበትነው ዕውቀት፤ መንፈሳዊ አስተምህሮ፤ ዓለማዊ ጥበብ፤ የቅዱሳን ሕይወት ሳይሆን ለስሜት ያጋደለ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለሁለት ጌታ መገዛት አይቻልም የሚለውን ኃይለ ቃል ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተማረው ይሁዳ ለ30 ብር ሸጦታል ለምን ትለኝ እንደሆን ሰው ክፉን ነገር እስኪሰራ ሰው ልበ ሙሉ ይሆናልና ነው፡፡ ሁለተኛው የህሊና ዓይን ከነፍስ ባይለይም በኃጢአት ምክንያት ይጨልማል ይደክማልና ነው፡፡ በአጭር አገላለጽ ድርጊታችንን የሚቆጣጠረው በዕለቱ ስሜታችንን ያቀጣጠለው ኃይል እንጂ በጥረት ያካበትነው ትምህርት ወይም ዕውቀት ሆኖ አይታይም፡፡
ሰው በሕገ ሕሊና፣ በሕገ ኦሪት፣ በሕገ ወንጌልና በሕገ ማህበራዊ መገዛቱን ትቶ በጊዜአዊ ስሜት ለጥቅምና ለስልጣን፣ ለክብርና ለእይታ ማደር ከጀመረ ለአገርም፣ ለቤተሰቡም ለራሱም ሳይሆን በቅዠትና በሰላም እጦት ሕይወቱ እንዲሁ ያልፋል። ሰው ሆይ ከምንም በላይ ለተፈጥሮአዊ ሕግ ተገዢ ሁን፤ ሕሊናህ ይዳኝህ፤ ለመልካም ነገር ትጋ፤ እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ!!!  

ምንጭ፦ ማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ (ሚያዝያ 26፣2003ዓ.ም)

Tuesday, September 10, 2013

አዲስ ዓመት፣ አዲስ ዕቅድ

በየአመቱ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ከእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት ቀጥለን በአዲስ ዓመት ዕቅድህ/ሽ ምንድን ነው? የሚለው የተለመደ ጥያቄ ነው። መልሳችንም እንደ ሥራ መስካችንና አመለካከታችን የተለየ መልክና ይዘት ይኖረዋል። በአዲስ ዓመት በት/ት ገበታ ላይ የሚገኙ ሁሉ ጥሩ ውጤት ማስመስገብን፣ አርሶ አደሮች ጥሩ ምርት ማምረትን፣ በንግዱ ዓለም የሚገኙ ትርፋማነትን፣ ማኅበርተኞች የማኅበራቸውን ዓላማና ግብ መሳካትን፣ ፖለቲከኞች መልካም አስተዳደርንና የተቀናቃኛቸውን ክስረት፣ መንግሥት የስልጣን ዘመን ማራዘሚያ መንገዶችን እና ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪን/ትምህርትን  በአጽንኦት ይሻሉ ይመኛሉ።
አሁን  በአለንበት ዘመን  ምኞታችንን  ሁሉ እውን  ለማድረግ በእጅጉ ከባድ ነው። ሆኖም ግን ልናተኩርባቸው  የሚገቡ ነገሮችን ለይቶ  ለስኬት የሚያበቃንን መንገድ መከተል  ብልህነት ነው። በአጭር ከዚህ በታች ልናተኩርባቸው የሚገቡ ነገሮችን ለመነሻ ያክል ጥቂት ልበል።

እንደ  ክርስቲያን በአዲሱ ዓመት ልናተኩርባቸው የሚገቡ፦
  • ከበፊቱ በበለጠ ከጠላታችን ዲያቢሎስ ጋር የምንዋጋበትን እቃ ጦር ለመልበስ ታጥቀን የምንነሳበት፣ 
  • ቤተ ክርስቲያንን ከበፊቱ በበለጠ ልናገለግልና ልንገለገልባት በጽዕኑ ዓላማ ቆርጠን የምንነሳበት፣
  • ቤተ ክርስቲያን የሁከት፣ ፀረ ሰላም፣ ፀረ ልማት እንዳይደለችና የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት ት/ቤት እንደሆነች በኩራት የምንመሰክርበትና የምንገልጽበት፣ 
  • ቤተ ክርስቲያን አክራሪነትን የምትቃወም እንጂ አክራሪነት የሚለው ቃል ፈጽሞ ሊሰጣት እንደማይገባ በድፍረት የምንመሰክርበት፣ 
  • ከሰዎች ጋር መታረቅና ፍቅርን በስጦታ መልክ መለገስ፣
  • ሰውነታችንን በንስሃ ታጥበን በአምላክ ቅዱስ ሥጋና ክብር ደም ታትመን አዲስ ሕይወትና አዲስ መንፈስ የምንይዝበት ዘምን እንዲሆን ይፈለጋል።
እንደ  መንግሥት በአዲስ ዓመት፦
  • መልካም አስተዳደር ለማስፈን መጣር፣
  • ሕግን ከወረቀት ባለፈ በተግባር ማዋል፣
  • የህዝቡን ብሶት ሰምቶ ለችግሩ ደራሽ መሆን፣
  • አገራዊ ስሜትን ለህብረተሰቡ ማስገንዘብ፣
  • ለዲሞክራሲ ግንባታና ለአገራዊ እድገት የሚጥሩ ተቀናቃኝ/ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማበረታታት፣
  • በሃይማኖት ጣልቃ ገብነትን ማቆም፣
  • ለሰባዊ መብት ተቆርቋሪ መሆን፣
  • ከአላግባብ የታሰሩ እስረኞችን መፍታት፣
  • ትክክለኛ መረጃ ሳይኖር ሰዎችን፣ድርጅቶችንና ተቋማትን  ያልሆነ ስም ሰጥቶ ማሸማቀቅን ማቆም፣
  • ስልጣን የህዝብ መሆኑን በተግባር ማሳየት እና መሰል ተግባሮችን የሚተገብርበት ዘምን እንዲሆን ይፈለጋል። 
እንደ ሰራተኛ በአዲስ ዓመት፦
  • ለሌላ ሁለተኛ ወይም ሦስተኛ አካል ሳይሆን ለህሊና መስራት፣
  • በማነኛውም የሥራ መስክ ህዝብን እንደምናገለግል  በሚገባ መገንዘብ፣
  • ለሕገ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ለሕገ አምላክም መገዛት፣
  • ማጭበርበር፣ ሙስና እና ጥቅመኝነትን አምርሮ  መጥላትና ማጋለጥ፣
  • ፍቅርን  በስጦታ መልክ ለሰዎች መለገስ፣
  • በማነኛውም መልኩ ለእውነት ለመስራት እራስን ዝግጁ ማድረግ ይገባል።
እንደ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲ በአዲሱ ዓመት፦
  • ለህዝብና ለሃገር መቆማችሁን በትክክል ሊያስረዳ  በሚችል መልኩ ዓላማችሁን መግለጽ፣
  • የመንግሥት አካላትን በፖሊሲና በዓላማ እንጂ  በማንነታቸው አለመተቸት፣
  • ማንኛውንም ድርጅት ወይም ተቋም ለፖለቲካ ቅስቀሳ አለመጠቀም፣
  • ስድብንና ዛቻን ትቶ ሙህራዊ የአነጋገር ዘይቤ መጠቀም፣
  • ድርጅታችሁ ከብሔር ይልቅ  አገራዊ እንዲሆን  ማድረግ፣
  • የመንግሥትን  መልካም ሥራዎች ካሉ ማበረታታትና መደገፍ፣
  • ለዲሞክራሲ፣ ለሰላምና ለአድነት ቆርጦ መነሳት ከእናተ በአዲስ ዓመት ይጠበቃል
ሁላችንም 2006 ዓምን እነዚህንና ሌሎች አስፈላጊ ተግባራትን ለመተግበር አቅደን አዲሱን ዓመት መቀበል ይገባናል።   

ዘመነ ማርቆስ/2006 ዓም የሰላም፣ የፍቅር፣ የደስታ፣ የአንድነት፣ የሕይወት ብልጽግና   እንዲሆንልን አምላከ ቅዱሳን በቸርነቱ  ይርዳን፡አሜን!።

Sunday, September 8, 2013

የዘመን መለወጫ በዓል፤ ዕንቍጣጣሽ፤ የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።


 +++ እንኳን ለ፳፻፮ ዓም  በሰላም አደረሳችሁ!+++

 ይህ ከዚህ በታች ስለ አዲስ ዓመትና የኢትዮጵያ የዘመን አቀጣጠር በተመለከተ ሰፋ ያለ ጽሁፍ ታላቁ የቤተክርስቲያን አባት አለቃ አያሌው ታምሩ ያስተማሩት ት/ ት ሲሆን በእርሳቸው ስም ከተከፈተው መካነ ድር ላይ በቀጥታ የተወሰደ ነው። መልካም ንባብ....... 





«በመለከት ድምፅ መታሰቢያ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ።» (ዘሌ ፳፫፥፳፫-፳፬።)

መግቢያ
በኢትዮጵያ የእምነት ትምህርት እየሰፋና እየጸና የቆየ በመሆኑ ምክንያት ከትምህርትነት ዐልፎ ወደ ባህልነት ተለውጦአል። እንዲያውም አብዛኛው የእምነት ትምህርት ትምህርት ነው ከሚባል ይልቅ ባህል ነው በሚባለው ስሙ የታወቀ ሆኖ ይገኛል። የባህል ዘርፎች ከሆኑ የእምነት መገለጫዎች አንዱ በዓል ነው። በዓል በሞላው የሰው ዘር ዘንድ የባህል መሠረቶች ከሆኑት አንዱ ክፍል ነው። እምነት ያለው በእምነቱ፥ እምነት የሌለውም በልማዱ የባህል ሥነ ሥርዐት የሌለው የሰው ዘር የለም። ግን በመሠረቱ የባህል መነሻው እምነት ነው። እያደር እየዋለ ወደ ልዩ ልዩ ልማድ እየገባ መሠረቱን ለቆ ይገኝ እንደ ሆነ ነው እንጂ በዓል ሲባል መሠረቱ እምነት ነው። በእምነት ላይ ነው ሁሉም የሚመሠረተው። ከበዓላትም ተቀዳሚ ሆኖ የሚገኘውን የዘመን መለወጫ በዓልን ስንመለከት በልዩ ልዩ ክፍለ ዓለማት፥ በልዩ ልዩ የሰው ዘሮች ባህል ውስጥ የታወቀ፥ ጸንቶ የኖረና የሚኖር ሆኖ እናገኘዋለን። የሰው ልጆች እንደ ጠባያቸው፥ እንደ ባህላቸው፥ እንደ ልማዳቸው እና እንደ እምነታቸው መሠረት ያዳበሩት፤ አንዳንድ ጊዜም ነገሥታት ወይም አምባገነን መሪዎች በሚያመጡት የሥርዐት ጠቀስ ሁኔታ እየተፈጠረ ጸንቶ የኖረ የዘመን መለወጫ ሥርዐት በየአገሩ ይገኛል። በእምነት ክፍል ግን የምንመለከታቸው እጅግ አነስተኞች ናቸው። እነዚህ እምነቶች የሚቀራረቡበትም የሚለያዩበትም ነገር አለ። ለምሳሌ ክርስቲያኖች ከአይሁድ ጋራ መሲሕ ይመጣል የሚሉትን በትንቢት እምነት ሲቀበሉ ከኖሩ በኋላ ጊዜው ሲደርስ፤ ጊዜ ደረሰ፥ ተስፋ ተፈጸመ፥ አምላክ ሥጋ ለበሰ ብለው በማመናቸው፤ እንዲሁም እግዚአብሔር በአካል ሦስት፥ በባሕርይ አንድ ነው፤ አብ ወልድን መንፈስ ቅዱስን አስገኘ፥ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ተገኝተዋል፤ እንዲህ ቢሆን ግን መቅደም መቀዳደም፥ መብለጥ መበላለጥ የለም ብለው በማስተማራቸው ክርስቲያኖች የተለየ ፈለግ የሚከተሉ ናቸው። ይህም ስለ ሆነ እምነታቸው ጠባብ በር፥ ጠባብ መንገድ ይባላል። ጠባብ በር፥ ጠባብ መንገድ ይሁን እንጂ መጨረሻው ደግሞ መዝለቂያው ሕይወት መሆኑን ራሱ መድኃኒታችን ስለ ገለጠ የክርስትና እምነት ዘላቂ ሕይወት ያለውና የሚሰጥ መሆኑ የታመነበት ነው።

የዘመን መለወጫ በዓል

የዘመን መለወጫ በዓልን በተመለከተ የተለያዩ የእምነት ክፍሎች የየራሳቸው መነሻ ምክንያት አላቸው።
በአይሁድ የዘመን መለወጫ ተብሎ የሚከበረው መባቻ ተብሎ ከሚጠራው ቀን የተለየ ነበረ። እነሱ የዘመን መለወጫን የሚያከብሩት በሚያዝያ ነው። ይህንንም ያደረጉበት ምክንያት አባቶቻቸው ወደ ግብጽ ተሰደው ሁለት መቶ ዐሥራ ዐምስት ዓመት በግብጽ ከኖሩ በኋላ እንደገና ከግብጽ ወጥተው ወደ ኢየሩሳሌም ሲገቡ እግዚአብሔር እነሱን ከግብጽ አውጥቶ፥ ባሕር ከፍሎ፥ ደመና ጋርዶ ወደ ምድረ ርስት ለማድረስ ከግብጽ ያወጣበትን ቀን ልክ ነጻነታቸውን እንዳገኙበት ቀን አድርገው በየዓመቱ የዘመን መለወጫ ብለው እንዲያከብሩትና ወሩንም የወሮች መጀመሪያ እንዲያደርጉት ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ስለ ተሰጣቸው በዚህ መሠረት ሚያዝያን ያከብራሉ።
ክርስቲያኖች ግን የዘመን መለወጫ በዓላቸውን በልዩ ልዩ አገር እንደ መሆናቸው መጠን አላስተባበሩም። በተለይም ጎላ ብሎ የሚታየው የጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር ከሌሎች አቆጣጠር የተለየ መልክ ያለው ነው። አውሮፓውያን የጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር የሚባለውን የሚከተሉ ሲሆን ይህ አቈጣጠር የዓመተ ምሕረት መለወጫ እንጂ ጠቅላላ የዘመን መለወጫ አለመሆኑ በግልጽ ይታያል። ያንንም ቢሆን እንደ ጠባዩ፥ እንደ አጠራሩና እንደ ፍላጎታቸው ልክ በመድኃኒታችን ልደት አልጀመሩም። የልደትን በዓል እንደ ቀን አቆጣጠራቸው ካከበሩ በኋላ እንደገና በስምንተኛው ቀን የዘመን መለወጫ ብለው ያከብራሉ። ይህም የጎርጎሮሳውያን የዘመን አቈጣጠር በክርስቶስ ልደት ላይ አለመመሥረቱን፥ ሌላ ጠባይ ወይም ሰው ሠራሽ ሥርዐት የተቀላቀለበት መሆኑን ያሳያል። ክርስትናን ተመርኩዞ ቢነሣ ኖሮ በእርግጥ የመድኃኒታችንን ልደት መነሻ አድርጎ ሊዘምት በተገባው ነበር። ይህ ባለመሆኑ ግን አሁንም ቢሆን የልደቱን በዓል ለብቻ አክብረው እንደገና ከሳምንት በኋላ የዘመን መለወጫ በዓልን ያከብራሉ። ከዚህም በተጨማሪ የወሮችና የቀኖች ስያሜአቸው ከእምነታቸው ጋራ ምንም የሚገናኝ አይደለም። እንዲያውም በአብዛኛው የሮማን አስተዳደር ጠባይ የተከተለ ፍንጭ ይታይበታል። ለምሳሌ ያህል ሰንዴይ የሚሉት ቀን ፀሐይን ያመልኩ ስለ ነበረ ከዚያ ጠባይ ተወርሶ የዚያን ምልክት ይዞ የሚኖር ሆኖ ነው የምናገኘው። ወሮችም በዚሁ ዐይነት አቅጣጫ የተሰየሙ መሆናቸውን እናያለን። ለምሳሌ በነጁልዮስ ቄሣር፥ በነ አውግስጦስ ቄሣር፥ በነ ኦክታብዮስ ቄሣር ስያሜ ጁላይ፥ ኦገስት፥ ኦክቶበር እያሉ የሰየሟቸው ስያሜዎች እዚያ ውስጥ ይገኛሉ። በዚህ ዐይነት ውሥጡ ሲመረመር ሰም ለበስ ሰው ሠራሽ ሥርዐት እንጂ የእምነት መሠረት ያለው ሆኖ አናገኘውም። በጎርጎሮሳውያን የዘመን አቈጣጠር ውሥጥ መሠረቱ ከእምነት ጠባይ ጋር የሚመሳሰል መንሥኤ ያላቸው አንዳንድ መነሻዎች ያሉ መስለው ይታያሉ። በዚያን ጊዜ የነበሩ የሮማ ነገሥታት ሁሉ አውግስጦስ የሚባለውን ስም የወሰዱት አምላክ ነን ለማለት ነበር። እና እያንዳንዳቸው መሥዋዕት ይቀርብላቸው፥ ዕጣን ይታጠንላቸው ስለ ነበረ መነሻው እምነት መሰል ምክንያት ሆኖ ይታያል። ከሮማ ነገሥታት አንዱ ጥጦስ የኢየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ ባቃጠለ ጊዜ አይሁድ ተስፋ እንዲቆርጡ ጭፍሮቹ ቅድስተ ቅዱሳኑ ከመቃጠሉ አስቀድሞ በመሬት ውሥጥ ለውሥጥ ገብተው እቤተ መቅደሱ ላይ የእሱን ምስል አቁመው ለእሱ መሥዋዕት ሠውተው፥ እሱን አመስግነው እግዚአብሔርን እንዲሰድቡ አድርጓል። ይህ ድርጊትም የአይሁድን መንፈስ በከፍተኛ ደረጃ እንደ ሰበረ ይነገራል። እንግዲህ የጎርጎሮሳውያን የዘመን አቈጣጠር በዚህ ዓይነት የተመሠረተ ጠባይ ነው የሚታይበት።

የኢትዮጵያ ዘመን አቈጣጠር

ወደ ራሳችን እንመለስና ስለ ኢትዮጵያ በዓል አከባበር ደግሞ እንመልከት። የኢትዮጵያ እምነታዊ ባህል የሚወረሰው በሦስት ዐይነት ጠባይ ነው። አንዱ ሕገ ልቡና ይባላል። ከመጽሐፍ በፊት የነበረ ነው። ከአበው ቃል በቃል የተወረሰ ነው። ሁለተኛው በሕገ ኦሪት ከኦሪት የተቀዳ ነው። ሦስተኛው በሕገ ወንጌል ከወንጌል የተማርነው ነው። እና በሦስት ዐይነት ጠባይ የሚመራ ነው። በዚህ ዐይነት ከወረስናቸው በዓላት ማለት በሦስቱም ጠባያት ከወረስናቸው በዓላት የየራሳቸው መልክ ያላቸው አሉ። ለምሳሌ ልደት፥ ጥምቀት፥ ዕርገት፥ ደብረ ታቦር እነዚህን የመሳሰሉት ከወንጌል የተማርናቸው ናቸው፤ በብሉይ የሉም። ፋሲካ፥ በዓለ ጰራቅሊጦስ ደግሞ ከኦሪት የተማርናቸው ናቸው። የዘመን መለወጫ በዓል ግን ከሕገ ልቡና ቃል በቃል ተምረን፥ በኦሪት የመጽሐፍ መሠረት አግኝተንለት በወንጌልም አጽንተን ይዘነው የኖርነው ሦስት የሥራ ዘመን ክፍል የተላለፈና እዚህ የደረሰ ነው። ምንም እንኳ ከሳይንቲስቶች አቈጣጠር ባይስማማም እኛ የዘመን መለወጫ ብለን በሀገራችን ባህል የምናከብረው ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር የተገኘበት፥ ብርሃን፥ ጊዜ፥ ዕለት፥ ሰዓት የተፈጠሩበት፤ ለብርሃን፥ ለጊዜ፥ ለዕለት፥ ለወር ለዓመት ጥንት መሠረት የሆነ ቀን ነው። ይህንን ሁሉ በማስገኘት እግዚአብሔር ራሱን የገለጠበት፥ ዓለምን በመፍጠር ከሃሊነቱን ያረጋገጠበት ቀን ነው ብለን ነው የምናከብረው። ስለዚህም ጥንተ ብርሃን፥ ጥንተ ዕለት፥ ጥንተ ጊዜ፥ ጥንተ ፍጥረት ርእሰ ዐውደ ዓመት ብለን ነው የምናከብረው። በዚህ ስያሜ በዓሉ ርእሰ ዐውደ ዓመት፥ ቅዱስ ዮሐንስ፥ የዘመን መለወጫ ብለን እናከብረዋለን።
ርእሰ ዐውደ ዓመት የምንለው፤ ዐውድ ማለት በግእዙ ቋንቋ ዙሪያ፥ ክብ የሆነ ነገር ማለት ነው። የዓመት ጠቅላላ ቀኖች መሠረታውያን ቀኖች የሚባሉት ሦስት መቶ ስድሳ አራት ቀኖች ናቸው። እነዚህም በኀምሳ ሁለት ሱባዔ ተከፍለው ለእያንዳንዱ ቀን በዓመት ውስጥ ለሰባቱ ዕለታት ኀምሳ ሁለት ኀምሳ ሁለት ቀን ይደርሳቸዋል። ከነዚህ ቀኖች የተሳሳበ የሴኮንድ፥ የደቂቃ፥ የሰዓት ዕላፊ ተጠራቅሞ ሦስት መቶ ስድሳ ዐምስተኛዋን የዘመን ማገጣጠሚያ ቀን ያስገኛል። ይህቺ ቀን እንግዲህ ዙሪያ፥ ክብ መግጠሚያ ናት ማለት ነው። በዚህች ቀን አማካይነት ወደ ዐዲሱ ዘመን መጀመሪያ እንተላለፋለን። ይህቺ ቀን ዕለት አዕዋዲት፥ ዕለተ ምርያ የመዘዋወሪያ ቀን ወይም የመጨረሻ ቀን ተብላ ትጠራለች። በአራት ዓመት ደግሞ ከዚህች መሳሳብ የምትገኝ አንዲት ቀን ትመጣለች። ሦስት መቶ ስድሳ ስድስተኛ። ይህቺ ቀን ዕለተ ሰግር ትባላለች። መረማመጃ ማለት ነው። አንድ ቀን ታስተላልፋለች። እንግዲህ እነዚህን ሁለቱን ቀኖች ተከትሎ የሚመጣው ቀን የዘመን መጀመሪያ፥ የዘመን ክብ መነሻና መድረሻ ተብሎ ርእሰ ዐውደ ዓመት ተብሎ በግእዙ ይጠራል። እነዚህ ቀኖች በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ተጠቃለው አንድ ጊዜ የሚገኙ ናቸው።
የኢትዮጵያ ቍጥር መሠረቱ መጽሐፈ ሔኖክ የሚባለው ነው። መጽሐፈ ሔኖክ በ፲፱፥ ፳፥ ፳፩ እና ፳፪ ምዕራፎች የሚሰጠን የፀሐይን፥ የጨረቃን ጉዞ መነሻ አድርጎ የወሮችን፥ የዕለታትን፥ የዓመታትን መነሻ፥ መድረሻ፥ መዘዋወሪያ ብተታቸውን፥ ጥንታቸውን ነው የሚያሳየው። ስለዚህም በሔኖክ ቍጥር የወር ቀኖች ቍጥር ሠላሳ ናቸው። በሦስት በሦስት ወር ግን አንድ ቀን ትከተላቸዋለች። እና ዓመቱ ለአራት ይከፈላል። በዘጠና አንድ በዘጠና አንድ ቀን። ጠቅላላው ይሄ ድምር ሦስት መቶ ስድሳ ስድስት ቀን ይመጣል። ይህ ካለቀ በኋላ አንዲት ቀን ለዘመን ማገጣጠሚያ ዕለተ ምርያ የምትባለው ትመጣለች። እንግዲህ በኢትዮጵያውያን ቍጥር ወሩ ከሠላሳ አያንስም፤ ከሠላሳ አይተርፍም። ለዓመቱም ሦስት መቶ ስድሳ ዐምስት ቀን መደበኛው አቆጣጠር ነው ማለት ነው። ይህ ነገር በአውሮፓውያን ቍጥርም አለ። ግን እነሱ ከዓመት ወሮች ሰባቱን ሠላሳ አንድ ሠላሳ አንድ አድርገው አራቱን ደግሞ ሠላሳ ሠላሳ አድርገው አንዷን ወር ሦስቱን ዓመት ሃያ ስምንት፥ በአራተኛው ዓመት ሃያ ዘጠኝ አድርገው ያጣጧታል። እንግዲህ የአቀማመጡ ለውጥ ካልሆነ በስተቀር በቍጥር አካሄድ ዞሮ ዞሮ የዓመት ቀኖች ሦስት መቶ ስድሳ ዐምስት ወይም ሦስት መቶ ስድሳ ስድስት በመሆን አንድ ሆነዋል ማለት ነው። ልዩነቱ ግን የአቀማመጥ ለውጥ ነው። በኢትዮጵያ አቈጣጠር ግን ጠቅላላውን ፲፪ ወሮች መደባቸው ሠላሳ ብቻ ነው። እነዚያ በሔኖክ መጽሐፍ በጣልቃ ገብነት የነበሩት አራት ቀኖች ተጠቅለው ጳጉሜን በሚባል በዓመቱ መጨረሻ ላይ ተገኝተዋል። ዐምስተኛዪቱ ቀንም ከእነሱ ጋር ተገኝታለች። ይህም ለቍጥር ተራ ቅምር መቅናት የተደረገ እንጂ ቀኑን የሚለውጥ ምንም ነገር የለበትም። እና ከእነዚህ ቀኖች በኋላ የምናገኘው ቀን ርእሰ ዐውደ ዓመት ይባላል። ይህንን በዓል ከአዳም ጀምሮ እስከ ኖኅ ድረስ የነበሩ ዐሥሩም አበው በዐሥሩ ትውልድ እስከ ማየ አይኅ ድረስ ሲያከብሩት እንደ ቆዩና ኋላም የኖኅ ልጆች ከአባታቸው ተቀብለው ሲያከብሩት እንደ ነበረ ኩፋሌ የተባለው መጽሐፍ በምዕራፍ ፯ ያስረዳናል። እንግዲህ ኢትዮጵያ ይህንን ቀን የወረሰችው ከአበው ነው የምንለው በዚህ ምክንያት ነው።
በሰናዖር ሕንጻ ጊዜ የሰው ዘሮች ሁሉ ተበታትነው በየክፍለ ሀገራቸው ሲገቡ ኢትዮጵያውያን አባቶችም ወደ ኢትዮጵያ በገቡ ጊዜ ከኖኅ በቃል ያገኙትን የእምነት መሠረት ይዘው ገብተዋል። ያን ጊዜ ይዘዋቸው ከገቡ ነገሮችም አንዱ የዘመን መለወጫ በዓል ነው። ይህም በክረምቱ መጨረሻ በየዓመቱ የሚከበር ነው። በዚያ ጊዜም ኖኅ ከመርከብ በወጣ ጊዜ በሰኔ ወር መሥዋዕት ሠውቶ ሰውንና እግዚአብሔርን ካስታረቀ በኋላ እግዚአብሔርም በዕርቁ መሠረት፤ «ከእንግዲህ ወዲህ ክረምትና በጋ፥ ብርድና ሙቀት፥ መዝራትና ማጨድ፥ መዓልትና ሌሊት ሰዓታቸውን ጠብቀው ይፈራረቃሉ እንጂ የሰው ዘር ጨርሶ ከምድር የሚጠፋበት ፍጹም ቍጣ የሚደረግበት ጊዜ የለም፤» ብሎ ቃል ኪዳን እንደ ሰጠው ወዲያውኑ ክረምቱ በሰኔ ተጀምሯል። እስከዚያ ድረስ ሰማይ በደመና የሚሸፈንበት ቀን አልታየም ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ምድርን ውሥጥ ለውሥጥ የምታጠጣ የመስኖ ውሃ ነበረች እንጂ በሰማይ ደመና አይታይም ነበር። ኖኅ ከመርከብ ከወጣና መሥዋዕት ሠውቶ ሰውና እግዚአብሔር ከታረቁ በኋላ ግን ሰማይ በደመና ተሸፈነ፤ በዚያ ጊዜም የእግዚአብሔር የቀስቱ ምልክት በደመና ላይ ይታይ ጀመረ። ክረምትም እንደ እግዚአብሔር ቃል ሦስቱን ወሮች ጠብቆ ይመላለስ ጀመረ። እንግዲህ፤ «የዕዳሪ ዕርሻ ምስክር አያሻ፤» እንደሚባለው የኢትዮጵያ ክረምት ትናንትና ነበረ የሚባል ሳይሆን ዛሬም እኛ ደርሰንበት በሰኔ ተጀምሮ በመስከረም የሚፈጸም መሆኑን እንመለከታለን።

ዕንቍጣጣሽና መስከረም


በዚያም ጊዜ የነበሩ ኖኅና ልጆቹ ሰማዩ በደመና በመክበዱ ምክንያት ማየ አይኅ እንደገና ይመጣ ይሆን፥ የጥፋት ውሃ እንደገና ይዘንም ይሆን እያሉ ሲደነግጡ ከርመው በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ሙሉ የፀሓይ ብርሃን ስላዩ፥ ምድር በአበባ አሸብርቃ ስለ ተገለጠችና በዚህም የእግዚአብሔርን ቸርነት፥ የቃል ኪዳኑን መጽናት ስለ ተረዱ ይህንን በዓል ቀድሞ ከአባቶቻቸው እንደ ወረሱት ያው ጥንተ ብርሃን፥ ጥንተ ዓመት፥ ጥንተ ዕለት አድርገው አክብረውታል። ሲያከብሩትም እንግጫ ነቅለው፥ አበባ ጐንጕነው መጀመሪያ መሥዋዕት ይሠዉነት ከነበረው ቦታ ሄደው ለእግዚአብሔር ገጸ በረከት አቅርበው ከዚያ በኋላ ግን እርስ በርሳቸው የአበባ ስጦታ በመለዋወጥ አክብረውታል። ሲያከብሩትም ዕንቍጣጣሽ በሚል ቃል እውነት የመልካም ሞኞታቸውን ይገላለጡበት ነበር። ዕንቍጣጣሽ ማለትንም ብዙ ታሪክ ጸሓፊዎች በልዩ ልዩ መልክ ተርጕመውታል። እንዲያውም ንጉሡ ሰሎሞን ለሳባ ንግሥት የዕንቍ ቀለበት ሰጥቷት ነበርና «ዕንቍ ለጣትሽ» ማለት ነው ብለው የጻፉ ብዙ ሰዎችም አሉ፤ የሚናገሩም አሉ። ነገሩ ግን እንዲህ አይደለም። ዕንቍጣጣሽ ማለት ተንቈጠቈጠ፥ አንቈጠቈጠ ከሚለው ቃል ተወስዶ ምድር በአበባ አጌጠች፥ ሰማይም በከዋክብት አሸበረቀ እንደ ማለት ሰማይን በከዋክብት ያስጌጠ አምላክ ምድርንም በአበቦች አጎናጸፋት ለማለት የተሰጠ ቃል ነው እንጂ ስለ ሳባ ንግሥት የተሰጠ አይደለም። ሁለተኛም አባቶቻችን ኢትዮጵያን በሙሉ ሀብት ተረክበዋት ነበርና፤ «ዕንቍ ዕጣ ወጣሽ፤» ሲሉ ወደ አገራቸው ሲገቡ ለአገራቸው መታሰቢያ አድርገው የተጠቀሙበት ቃል ነው ይባላል። በመሠረቱ ግን ያ የጥፋት ውሃ ቀርቶ ምድር ጸንታ፥ አበባ ቋጥራ፥ ፍሬ ለመስጠት ተዘጋጅታ መገኘቷን የሚያበሥር ቃል ነው።
መስከረም የሚባለው ወርም ኖኅ በመርከብ ውሥጥ በነበረ ጊዜ እንደ ዕብራውያን አቈጣጠር ሰባተኛ በሆነው በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ መርከቢቱ አራራት ከሚባለው ተራራ ላይ ዐርፋ ምድር ጨብጣለች። በግእዝ ቋንቋ መርከብ መስቀር ይባላል። ከዘመን ብዛት በኋላ «ቀ» ወደ «ከ» ተለውጦ መስከረም ተባለ እንጂ መስቀርም ምድር አገኘች፥ መርከብም ምድር ነካች ለማለት የተሰጠ የወሩ ስያሜ ነው።
በዚህ መሠረት አባቶቻችን ፊትም ከአበው እንደ ተቀበሉ፥ ኋላም ከሕገ መጽሐፍ ደግሞ ተቀብለውታል። ይህን ከአዳም እስከ ኖኅ፥ ከኖኅ እስከ አብርሃም ቃል በቃል ሲተላለፍና ሲያከብሩት የቈዩትን የመባቻ በዓል ጌታ ለሙሴ በመጽሐፍ ሰጥቶታል። ይህንንም በኦሪት ዘሌዋውያን ምዕራፍ ፳፫ ከቍጥር ፳፫ ና ፳፬ እናገኘዋለን። ስሙም በዓለ መጥቅዕ ይባል ነበር። «በሰባተኛው ወር በወሩ በመጀመሪያው ቀን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ በዓል ይሁንላችሁ፤» ብሎ እግዚአብሔር ለሙሴ በሰጠው ትእዛዝ ጸንቶ ሲከበር ቈይቷል። በጠቅላላ በዚህ በዓል መነሻነት በመስከረም የምናከብራቸውን በዓላት ሁሉ የሚጠቁመው ምንባብ የሚገኘው በዚሁ ክፍል ነው። በኦሪት ዘሌዋውያን ምዕራፍ ፳፫ ከቍጥር ፳፫ እስከ ፴፯ የተጻፈው እንዲህ ይነበባል። «እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት፥ በመለከት ድምፅ መታሰቢያ፥ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት፤ ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባንን አቅርቡ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፤ በዚህ በሰባተኛው ወር ዐሥረኛው ቀን የማስተስረያ ቀን ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ ሰውነታችሁንም አስጨንቋት፤ ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባንን አቅርቡ። በአምላካችሁም በእግዚአብሔር ፊት ማስተስረያ ይሆንላችሁ ዘንድ የማስተስረያ ቀን ነውና በዚያ ቀን ሥራ ሁሉ አትሥሩ። በዚያም ቀን የማይዋረድ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። በዚያም ቀን ሥራ የሚሠራውን ሰው ሁሉ ከሕዝቡ መካከል አጠፋዋለሁ። ሥራ ሁሉ አታድርጉበት፤ ከምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዐት ነው። የዕረፍት ሰንበት ይሁንላችሁ፤ ሰውነታችሁንም አዋርዱ፤ በወሩ በዘጠነኛው ቀን በማታ ጊዜ፥ ከማታ ጀምራችሁ እስከ ማታ ድረስ ሰንበታችሁን አድርጉ። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ በዚህ በሰባተኛው ወር ከ፲፭ኛው ቀን ጀምሮ ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር የዳስ በዓል ይሆናል። በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁን፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት። ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር የእሳት ቁርባንን አቅርቡ፤ በስምንተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ። ለእግዚአብሔርም የሚቃጠለውን ቍርባን አቅርቡ፤ ዋና ጉባኤ ነው፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት። የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የእኽሉንም ቍርባን፥ መሥዋዕቱንም፥ የመጠጡንም ቍርባን፥ በየቀኑ የእሳት ቁርባን ወደ እግዚአብሔር ታቀርቡባቸው ዘንድ የተቀደሱ ጉባኤዎች እንዲሆኑ የምታውጇቸው የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው።» (ዘሌ፤ ም ፳፫፥ ቍ ፳፫ - ፴፯።) እንግዲህ ከላይ በተጠቀሰው ጥቅስ ላይ ሦስት ቀኖች እናያለን። አንደኛ፤ ከወሩ በመጀመሪያ ቀን በመለከት ድምፅ የሚከበር ለእግዚአብሔር መታሰቢያ የሆነ ቀን፤ ሁለተኛ በሰባተኛው ወር በዐሥረኛው ቀን የሚከበር ሰው ሁሉ የሚዋረድበት፥ ትሕትና የሚያደርግበት፥ ንስሐ የሚገባበት የሥርየት ቀን፤ ሦስተኛው በሰባተኛው ወር ከዐሥራ ዐምስተኛው ቀን ጀምሮ ለስምንት ቀን የሚከበር ዳስ ተተክሎ፥ ድንኳን ተጥሎ የሚከበር በዓል፤ ሦስት በዓሎች ናቸው።እነዚህም በአንድ ወር ውሥጥ የሚከበሩ ናቸው። ይህ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው ትእዛዝ ትኩረት የሚያሻው ነው። ይህንን ትእዛዝ እግዚአብሔር ለሙሴ በመጽሐፍ ሰጠው። ከሙሴ ወዲህ በመጽሐፍ ተቀረጸ እንጂ ከዚያ በፊት የነበሩ አበው ግን በመጽሐፈ ኩፋሌና በመጽሐፈ ሔኖክ እንደሚገለጠው ቃል በቃል በተወረሰው መሠረት ብቻ ያከብሩት ነበረ። የመጀመሪያው ቀን፤ በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን በመለከት ድምፅ የሚከበር በዓል ይደረግ የሚለውን ቃል ስንመለከት በመለከት ድምፅ የሚሉ ቃላት እናገኛለን። መለከት የሚለው ቃል በአማርኛው ቋንቋ ይነጥላል፤ አንድ ክፍልን ብቻ ይመለከታል። በግእዙ ቋንቋ ግን መጥቅዕ ነው የሚለው። በዓለ መጥቅዕ ነው የሚባል። መጥቅዕ ማለት መለከትንም፥ ዕንቢልታንም፥ ነጋሪትንም የሚያጠቃልል ነው። በእንዲህ ዐይነት ሥርዐት የሚከበር የዘውድ በዓል ነው። ሌላም በድሮው ቋንቋ ተናገርኩት እንጂ የአንድ መሪ በዓል ነው ማለት ነው። የአንድ ብሔራዊ የአመራር በዓል ማለት ነው። ዘመን አየሠለጠነ፥ ዓለም እየሠለጠነ ከሄደ ወዲህ ግን በመድፍ ድምፅ ነው ብሥራቱ የሚከፈተው። ይሄ መሪዎች ራሳቸው የጦር ሰዎች ስለ ሆኑ ከእምነታቸው ይልቅ ጦርነትን ወይም ደግሞ ከእምነት እነሱ ኀይልን ስለሚመለከቱና በኀይል ስለሚደገፉ የመድፍ ድምፅ ጨመሩበት እንጂ በዓሉ የእምነት እንደ መሆኑ መጠን የነጋሪት፥ የመለከት፥ የዕንቢልታ ድምፅ እንጂ የመድፍ ድምፅ አይፈልግም ነበር። እና በመለከት፥ በዕንቢልታ፥ በነጋሪት ድምፅ የሚከበር፥ አንድ መሪ ሥልጣን የጨበጠበትን ቀን የሚያስታውስ በዓል ነው። እንግዲህ ይሄ በዓልም ለሰው ሳይሆን ወይም ለሥርየት ሳይሆን ወይም ለሌላ ምክንያት ሳይሆን ለእግዚአብሔር በመለከት ድምፅ የሚከበር በዓል ነው። ምን ማለቱ ነው? እግዚአብሔር ዓለምን ፈጥሮ፤ መላእክት ባደረው ጨለማ ተውጠው ሲጨነቁ በነበረ ጊዜ፤ «እቤ አነ እግዚአብሔር፤ ለይኩን ብርሃን፤» «እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ብርሃን ይሁን፤» ብሎ ድምፁን በማሰማት አምላክነቱን፥ ከሃሊነቱን፥ ጌትነቱን፥ ሥልጣኑን፤ በጠቅላላውም የማያልፍ፥ የማይሻር፥ የማይለወጥ መንግሥቱን ያወጀበት ቀን ስለ ሆነ ለእግዚአብሔር በመለከት ድምፅ የሚከበር በዓል ነው ይባላል። ሰባተኛ ወር የሚለው ግን ዕብራውያን እንዲወጡበት ለታዘዘው፥ እነሱ ሚያዝያ እኛ መጋቢት ለምንለው ወር ነው እንጂ ለጠቅላላው የዓለም ወሮች አይደለም። በእስራኤል ቍጥር ነው ሰባተኛ ያለው። በእኛ ግን የወሮች መጀመሪያ ነው። ለእስራኤላውያንም ቢሆን ያኛውን የወሮች መጀመሪያ ይሁናችሁ ሲል ይህንን ግን የመባቻ በዓል መጀመሪያ አድርጎታል። መባቻ ማለትም መግቢያ፥ ብተት፥ የወር መጀመሪያ ስለ ሆነ የወር መጀመሪያ የዓመት መጀመሪያ እንደ መሆኑ መጠን እንግዲህ የመባቻ በዓል እንዲከበር ያዘዘው እግዚአብሔር በዚሁ ቀን በመሆኑ የኢትዮጵያ በዓል አመሠራረት ጥንታዊና ቀዳማዊ፥ ዘለዓለማዊ፥ በጽኑ መሠረት ላይ የቈመ መሆኑን የሚያመለክተን ቀዋሚ ምልክት ነው። ከሕገ ልቡና እንደ ተቀበልነው በሕገ ኦሪትም አጽንተነዋል ማለት ነው።
ሌላው ከወሩ በዐሥረኛው ቀን የሚለው እነሱ በዚሁ ወር በዐሥረኛው ቀን የጾም ቀን አድርገው ያከብሩት ነበረ። የእስራኤል ዜጋ ወይም የእስራኤልን እምነት የተቀበለ ሁሉ ይህን ቀን የስንሐ ቀን መግቢያ አድርጎ ይጠቀምበት ነበረ። በዘመነ ወንጌል ግን በሱ ፈንታ በዓለ ስቅለት ተተክቶበታል። ይህም ሆኖ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዓሉ አለ። የቈየበትም በሁለት ጠባይ ነው። አንዱ እንደ ዛሬው መገናኛ ሙሉ በሙሉ የተካከለና የተሻሻለ ባለ መሆኑ ምክንያት ሕዝብ ሁሉ ክረምቱን ጨርሰው ወደ ከተማ የሚመጡበት፥ መሪያቸውን የሚያገኙበት፥ ስለ ሀገሪቱ በጠቅላላ በክረምት ተዘግቶ የነበረውን ሁሉ የሚወያዩበት ቀንና መሪውንም እንኳን አደረሰህ የሚሉበት ቀን ስለ ነበረ እስከ ዘመናችንም ተቀጸል ጽጌ እየተባለ ይጠራ ነበረ። በኋላ ግን የጌታችን ግማደ መስቀሉ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ በዐፄ ዳዊት ዘመን ስለ ገባበት በዓለ መስቀል ተተክቶበታል። መስከረም ፲ ቀን ማለት ነው።
ሦስተኛው ከ፲፭ ቀን ጀምሮ ለስምንት ቀን አክብሩ ተብሎ በታዘዘው በበዓለ መጸለት ፈንታ የመስቀል በዓል ተተክቶበት ከደመራው ጀምሮ እስከ መስከረም ፳፬ ቀን ስምንት ቀን ሙሉ በቤተ ክርስቲያን በዓለ መስቀል፥ ዘመነ መስቀል እየተባለ ነው የሚከበረው። እንዲያውም በአንዳንድ ጎሣዎች ይኸውም ጸድቆ ስምንት ቀን ሙሉ በዓል ሆኖ ሲሠራበት የነበረ እንዳለ ይታወቃል። እንግዲህ እነዚህ በዓላት ሦስቱም በፊት በዓለ መጥቅዕ፥ የሥርየት ቀን፥ የቂጣ በዓል ተብለው ይጠሩ የነበሩት በእኛ ቤተ ክርስቲያን ርእሰ ዐውደ ዓመት፥ የዐጤ መስቀል፥ መስቀል ተብለው የሚከበሩት በዓላት ናቸው። በዚህ ዐይነት እነዚህ መሠረታውያን የባህል በዓላት ከሕገ ልቡና ወደ ሕገ ኦሪት፥ ከሕገ ኦሪትም ወደ ሕገ ወንጌል ተላልፈው እዚህ የደረሱ ናቸው። እንግዲህ ርእሰ ዐውደ ዓመት የምንለው የዘመን መለወጫ ከምንለው ጋራ አንድ ነው።

ቅዱስ ዮሐንስ

የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ በዓል ሌላው ስሙ ቅዱስ ዮሐንስ ይባላል። ቅዱስ ዮሐንስ የሚባልበትም ሁለት ጠባይ አለው። አንዱ፤ መጥምቁ ዮሐንስ በሄሮድስ አንቲጳስ ጊዜ ከጳጉሜን ፩ ቀን ጀምሮ ታስሮ ሰንብቶ በመስከረም ፩ ቀን ዐሳብ ስለ ተቆረጠበትና በመስከረም ፪ ቀን እንዲሞት ውሳኔ ስለ ተሰጠበት አንገቱን በሰይፍ ተቆርጦ ስለ ሞተ ሊቃውንት ይህንን በዓል እሱ ራሱ ለኦሪትና ለወንጌል መገናኛ መምህር ስለ ነበረ ይህም በዓል ላለፈው ዘመን መሸኛ፥ ለሚመጣው ዘመን መቀበያ እንዲሆን ብለው በመስከረም ፩ ቀን እንዲከበር ስላደረጉ በሱ ስም ቅዱስ ዮሐንስ እየተባለ ይጠራል። በሁለተኛው ግን ከአራቱ ወንጌላውያን አንዱ ወንጌላዊ ዮሐንስ የተሰየመበት ስለ ሆነ በአቆጣጠርም ተራ ወደ ኋላ ተመልሶ ቢቈጠር ዓለም የተፈጠረበት ዘመን በዘመነ ዮሐንስ እንዳጋጣሚ ሆኖ ስለሚገኝ ቅዱስ ዮሐንስ ተብሎ ይጠራል።

ዓመተ ዓለምና ዓመተ ምሕረት

በዘመናት አቈጣጠር ውሥጥ ሌላው የምንመለከተው የዓመተ ዓለምና የዓመተ ምሕረት ቍጥር ነው። አውሮፓውያን ምንም እንኳ ቀኑን ዕለፍ ተቀደም ቢያደርጉትም ዓመተ ምሕረትን የሚቈጥሩ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነው። ከዚያ በፊት ያለውን ግን እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አራት ሺሕ ዓመት ቢሉም፥ ወይም በሳይንሱ ጠባይ ልዩ ልዩ መልክ ቢሰጡትም ተከታታይ ቍጥር አድርገው አይዘምቱበትም። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ወረሰችው ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረውን ፭ ሺ ፭፻ ዘመን፥ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ያለውን ፳፻፪ ዘመን በማለት አጠቃላ ዓለም ከተፈጠረ ፸፭፻፪ (ሰባት ሺሕ ዐምስት መቶ ሁለት) ዓመት ነው ትላለች። ለዓመተ ምሕረትም፥ ለዓመተ ዓለምም መነሻ የምታደርገው ያንኑ መስከረምን ነው። ለምን? የዘመናት ቍጥር ጥንት የዕለት፥ የሰዓት መሠረት ባደረገችው በዚያው ቀን የተነሣች፥ በዚያው ወር የጀመረች ስለ ሆነ ነው። ዓመተ ምሕረትንም በዚያው ማጽደቋ እመቤታችን ጌታን ፀንሳ ሳለች ወደ ኤልሳቤጥ ቤት በሄደች ጊዜ ኤልሳቤጥን ሰላምታ ስትላት ኤልሳቤጥም የእመቤታችንን ድምፅ ስትሰማ ዮሐንስ በማሕፀኗ ሳለ ለጌታ ሰግዶ ነበርና ይህንኑ መሠረት አድርጋ የዓመተ ምሕረት ለውጡ ከልደት ብቻ ሳይሆን ከፅንስ ጀምሮ ነው በማለት ያንኑ በማጽናት ተቀብላዋለች። የሰባት ዓመት ዕለፍ ተቀደም ቍጥሮች ልዩነት መነሻው አሁንም ቢሆን ከአውሮፓውያን የቊጥር ውሳኔ እንጂ ከኢትዮጵያውያን የቍጥር ውሳኔ አይደለም። ማለትም አውሮፓውያን የቤተ መቅደስን መፍረስ ሲናገሩ ከዕርገት በኋላ በ፵፬ ዓመት፥ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ፸፯ ዓመት ነው ብለዋል። ስለዚህ ውጥን ጨራሽ ቍጥር ተውጦ የሚቀር በመሆኑ ይህ ከእነሱ የፈለቀ እንጂ ከኢትዮጵያውያን አይደለም። ኢትዮጵያ ግን ከመሠረቱ ያንን ይዛ በመጣችው እስካሁንም ድረስ ደርሳበታለች። ይህም የተለወጠው ከውጪው ሥርዐት አያያዝ ነው ማለት ነው። በዚህ ዐይነት ይህንን የዘመን መለወጫ በዓል ስናከብር ቈይተናል።

ዓመታት በአራቱ ወንጌላውያን ስም ስለ መሰየማቸው

ቀደም ሲል ሰዎች በልዩ ልዩ ምልክት ይጠቀሙ ነበረ። በተለይም ሕዝቅኤልና ኢሳይያስ የኪሩቤልን ሥዕል፥ የኪሩቤልን መልክ በትንቢት ራእይ ዐይተው አንዱ አንበሳ፥ አንዱ ላም፥ አንዱ ሰው፥ አንዱ አሞራ ይመስላል ብለው በመናገራቸው ወደ እምነት የተቃረቡ ሰዎች ሁሉ በዚህ መሠረት አድርገው የኪሩቤል ጌታ፥ የእኛ ፈጣሪ፥ በሰማየ ሰማያት ላይ የሚኖር በኪሩቤል የሚመሰገን ነው ለማለት በዚህ ይጠቀሙ ነበረ።
በሐዲስ ኪዳን ደግሞ የቤተ ክርስቲያን መሠረት በአራቱ ማዕዘን በምሥራቅና በምዕራብ፥ በሰሜንና በደቡብ ያለ የሰው ዘር ሁሉ በሚጠቀምበት በወንጌል ትምህርት ላይ የተመሠረተ ስለ ሆነና ዓለም በአጠቃላይ የሚመራበት ቅዱስ ወንጌልም በአራቱ ወንጌላውያን የተጻፈ ስለ ሆነ ቤተ ክርስቲያን ወንጌሉን ስትቀበል ጸሓፊዎችንም ለክርስቲያኖች ቃል በቃል ለማስጠናት እንድትችል ዘመኑ በአራቱ ወንጌላውያን እንዲሰየም ሆኗል። ይህም ስለ ሆነ ማቴዎስ፥ ማርቆስ፥ ሉቃስ፥ ዮሐንስ በዘመናት ላይ መታሰቢያ አግኝተዋል።
ማቴዎስ በገጸ ብእሲ፥ ሰው በሚመስለው ኪሩብ ይመሰላል። ምክንያቱም የአብርሃም ልጅ፥ የዳዊት ልጅ ብሎ አምላክ ሰው መሆኑን የሚያስተምር፥ ትምህርቱንም በዚህ የጀመረ ስለ ሆነ ነው።
ማርቆስ በገጸ አንበሳ ይመሰላል። ምክንያቱም በግብጽ የላምና የበሬ ምስል ይመለክ ነበረና ያንን አጥፍቶ በዚያች አገር ወንጌል እንድትስፋፋ ስላደረገ ማርቆስ በገጸ አንበሳ፥ በአንበሳው ምስል በተመሰለው ኪሩብ ተመስሏል።
ሉቃስ ላም በሚመስለው ኪሩብ ተመስሏል። በተለይ በወንጌሉ በምዕራፍ ፲፭ ስለ በደለኛው ልጅ ሲጽፍ በደለኛው ልጅ ወደ አባቱ በመጣ ጊዜ አባቱ ያን በደለኛ ልጅ ሳይጸየፍ፤ «በሉ ሰውነቱን እጠቡት ልብሱን አልብሱት፥ ፍሪዳ አምጡና እረዱ፤ እንብላ፤ እንጠጣ። ይህ ልጄ ሞተ ስለው ድኗል፤ ጠፋ ስለው ተገኝቷል፤» ብሎ በምሳሌ ባስተማረው ትምህርት መሠረት ጠፍቶ የተገኘው ልጅ አዳም፥ የተቀበለው እግዚአብሔር አብ፥ መሥዋዕት ሆኖ አባቱንና ልጁን ያስታረቀው እግዚአብሔር ወልድ ነው ብሎ ትምህርት ስለ ሰጠ በዚህ አንጻር በላም መልክ በተመሰለው ኪሩብ ተተክቶ ሉቃስ ተጠርቶበታል።
በአሞራ መልክ በተመሰለው ኪሩብ የተጠራው ዮሐንስ ነው። በተለይም ንስር የሚባለው አሞራ ከወፎች ሁሉ በላይ ርቆና መጥቆ ይሄዳል ይባላል። እንዲህም ሆኖ ምንም ዐይነት ነገር ከመሬት ወድቆ ቢያይ አይሠወረውም፤ ወርዶ በፍጥነት ሊያነሣው ይችላል ይባላል። ዮሐንስም ሌሎች ወንጌላውያን ከደረሱበት፥ ከመረመሩት ምስጢር በላይ ረቆ፥ መጥቆ የምስጢረ ሥላሴን ነገር አምልቶ፥ አስፍቶ፥ አጕልቶ ስለ ጻፈና ስላስተማረ፥ ብዙ ራእይም ስለ ገለጠ በንስር በተመሰለው ኪሩብ ተመስሏል።
የእነዚህ ወንጌላውያን ትምህርት ክርስቲያንን ሁሉ፥ የሰውን ልጅ ሁሉ ለእግዚአብሔር ልጅነት የሚያበቃ፥ ሰውና እግዚአብሔርን የሚያዋሕድና የሚያዛምድ ሆኖ ስለ ተገኘ እንግዲህ ራሱ መድኃኒታችን፤ «ራሱን የካደ፥ ቤትን፥ ንብረትን፥ ወገንን ትቶ የተከተለኝ ሁሉ በዚህ ዓለም መቶ ዕጥፍ ዋጋ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘለዓለም ሕይወት ያገኛል፤» ሲል በሰጠው ቃል ኪዳን መሠረት እነዚህ ወንጌላውያንም ለክርስቶስና ለቤተ ክርስቲያን ባቀረቡት አገልግሎት መሠረት በዓለም የተሰጣቸው ልዩ መታሰቢያ ነው። ልዩ መታሰቢያ፥ ሽልማታቸው ነው ማለት ነው። በዚህ መሠረት መምህሮቻችንን ለማስታወስ እንድንጠቀምባቸው የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አዝዘዋል። ይህን ትእዛዝ ኢትዮጵያ አጽንታ ኖራለች። ያዘዙም ጠቅላላው የዓለም ሊቃውንት ናቸው።

መጥቅዕና አበቅቴ

መጥቅዕና አበቅቴ የሚባሉት በዘመናት ቍጥር ውሥጥ በልዩ ልዩ መልክ የመጡ ነገሮች ናቸው። ሁሉም ከዓመታት የሚተርፉ ቀኖች ናቸው። አበቅቴ የሚባለው በጨረቃ ከሚቈጠረው ቍጥር የሚተርፈው ነገር ነው። መጥቅዕ ማለት ግን የዓመቱን በዓላት ለማውጣት የምንጠቀምባቸው መሠረታዊ ቀንና ተጨማሪዎቹ ነገሮች ናቸው። በዚህ ትምህርት መግቢያ ላይ በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን በመለከት ድምፅ ለእግዚአብሔር በዓል አድርጉ የሚል ጥቅስ አይተን ነበረ። ይህንን በዓል እስራኤል በኦሪት ዘመን በሚያከብሩበት ጊዜ ከአሉበት ዓመት ጀምሮ እስከ ሰባት ዓመት በዓላቱ ተዘዋውረው የሚውሉበትን ቀን፥ ይልቁንም በሰባተኛው ዓመት ባሮች የነበሩ ነጻ የሚወጡበት፥ በወለድ አገድ፥ በዋስትና፥ በብድር ወለድ ምክንያት ተይዘው የነበሩ ርስቶች፥ ቤቶች ሁሉ በነጻ ወደ ባለቤቱ እንዲመለሱ እግዚአብሔር ያዘዘው ትእዛዝ የሚፈጸምበት፥ ዐዋጅ ሁሉ የሚታወጅበት ቀን ነበር። ዛሬ ደግሞ ይህ የመስከረም መጀመሪያ ቀን በዓመቱ ውሥጥ ያሉትን አጽዋማትን፥ በዓላትን ቤተ ክርስቲያን በዐዋጅ ለክርስቲያኖች የምታስታውቅበት፥ የምትገልጽበት ስለ ሆነ ያ ቀን መጥቅዕ ተብሎ ተጠርቷል። ስለ ሆነም መጥቅዕ ሲመታ፥ ደወል ሲደወል፥ ነጋሪት ሲመታ፥ ሲጎሸም፥ ዕንቢልታ ሲነፋ የመሰብሰብ ጥሪ ስለ ሆነ ሁሉ በየመልኩ የሰልፍ እንደ ሆነ የሰልፍ፥ የበዓል እንደ ሆነ የበዓል መልኩንና ሥርዐቱን ይዞ ተጠሪው ሊሰበሰብ እንደሚችል በዚህም ምክንያት አጽዋማት፥ በዓላት ተሰብስበው የሚገኙበት ስለ ሆነ መጥቅዕና አበቅቴ ተብለው ይጠራሉ ማለት ነው።

ስለ ቅዱስ ድሜጥሮስ ቀመር

ቀመር ማለት በግእዙ ቋንቋ ቍጥር ማለት ነው። ሒሳብ እንደ ማለት። የቍጥር ዐይነት ማለት ነው። የቍጥር ዐይነቱ የድሜጥሮስ ብቻ አይደለም። ዐሥራ ዘጠኝ ዐይነት የቀመር ዐይነቶች አሉ። ግማሾቹ ከነቢያት፥ ግማሾቹ ከሐዋርያት፥ ግማሾቹ ከሊቃውንት የተገኙ ናቸው። የቍጥር ደረጃም አላቸው። የሔኖክ፥ የሙሴ፥ የኢያሱ፥ የሕዝቅኤል፥ የዳንኤል፥ የዳዊት፥ የኤርምያስ፥ የድሜጥሮስ፥ የዮሐንስ አቡቀለምሲስ ተብለው በልዩ ልዩ መልክ ይጠራሉ። እነዚህ ቍጥሮች እንደ ዐይነታቸው ሥራ ተሠርቶባቸዋል።
ከመጀመሪያዎቹ ሰዎች ሔኖክ አጠቃሎ ከጥፋት ውሃ ጀምሮ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የትውልዱን በትውልድ፥ የዘመኑን በዘመን ተራ ቈጥሮ የሰውን ልጅ ተስፋ አብሥሮበታል። ከሔኖክ በኋላ የተነሡ ነቢያት ደግሞ ሰዎች በተስፋ የመድኅንን መምጣት ይጠባበቁ ነበርና ቍጥር እየሰጡ እንዲጠባበቁ አድርገዋቸዋል። ለምሳሌ በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ ፱ እንደ ተጻፈው ዐይነት የተወሰነ ዘመን እየሰጡ ሲጠባበቁ ቈይተዋል። በዮሐንስ ራእይም ሰባት ማኅተም፥ ሰባት መጥቅዕ፥ ሰባት ጽዋ ብሎ ክፍለ ዘመኑን በሰባት በሰባት መድቦ ይህ ዓለም እስከሚፈጸም ድረስ የሚደርሰውን በውሥጡ ያቀፈ ትምህርት ሰጥቶበታል።
የቅዱስ ድሜጥሮስ ግን ሐዋርያት በትምህርት ሰጥተውት ከሥራ ላይ ለማዋል በስብከት መፋጠን ምክንያት ሳይተካከል ቀርቶ አንድ መቶ ሰማንያ ዓመት ሙሉ ተዘበራርቆ የነበረውን ሥርዐት ያስተካከለበት ቍጥር ነው። ሐዋርያት ዲድስቅልያ በተባለው የሥርዐት መጽሐፋቸው የትንሣኤ ዐቢይ ጾምና ጾመ ሐዋርያት፥ ጾመ ነነዌም መነሻቸው ከሰኞ እንዳይወጣ፤ ደብረ ዘይት፥ ሆሣዕና፥ ትንሣኤ፥ ጰራቅሊጦስ እሑድን እንዳይለቁ፤ ስቅለት ዐርብን፥ ርክበ ካህናት ረቡዕን፥ ዕርገት ኀሙስን እንዳይለቁ ብለው ወስነዋል። ነገር ግን በዚያ ጊዜ በነበረው ስደትና በስብከት መፋጠን ምክንያት ሐዋርያትም በሰይፍ፥ በእሳት፥ በስለት እየተገደሉ፥ ተከታዮቻቸውም እየታደኑ ብዙ ችግር ስለ ነበረ ይህንን ወስኖ ለክርስቲያኖች የሚሰጣቸው አልነበረም። ስለ ሆነም የወሩን ብተት ተከትለው ልደትን እንዳከበሩ ወዲያው ጥምቀትን ያከብሩ ነበር። ጥምቀትን ካከበሩ በኋላ ደግሞ በማግሥቱ ዐቢይ ጾምን ይጾሙና በመኻል ደግሞ ዐርፈው እንደገና ከመጋቢት ፳፪ ቀን ጀምረው ሰሙነ ሕማማትን አክብረው በዓለ ስቅለትን፥ በዓለ ትንሣኤን ያከብሩ ነበረ። ኋላ ቅዱስ ድሜጥሮስ በእስክንድሪያ መንበር በተቀመጠ ጊዜ ስለዚህ ጉዳይ ብዙ ያስብና ይቈረቈር ስለ ነበረ የእግዚአብሔር መልአክ ይህንን በሱባኤ፥ በጸሎት፥ በቀኖና እንዲጠይቅ አዘዘውና በሱባኤ፥ በጸሎት፥ በቀኖና ሆኖ ከእግዚአብሔር ስለ ጠየቀ ተገልጾለት ይህንን ቀመር ሰጥቶአል። እና በእያንዳንዱ በዓል መካከል መዘዋወሪያ ቀኖች አድርጎ እነዚህ ቀኖች ለዚያ መውጪያ መውረጃ እንዲሆኑ፤ ጾመ ነነዌ ወደ ኋላ ቢመጣ ጥር ፲፮ን እንዳይነካ፥ ወደ ፊት ቢሄድ ደግሞ ከየካቲት ፲፱ እንዳያልፍ ፤ ዐቢይ ጾም ምንም ወደ ኋላ ቢመጣ የካቲት ፪ን እንዳይነካ፥ ከመጋቢት ፮ ደግሞ እንዳያልፍ እንደዚህ በሆነ ሥርዐት ስለ ወሰነው ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በዚሁ ዐይነት ይመላለሳል። ይሁን እንጂ ሌሎች የዓለም ክርስቲያኖች ይህን ሳይጠብቁ ሚያዝያ በባተ በመጀመሪያው ቀን የተገኘውን እሑድ ተከትለው በዓለ ትንሣኤን ሲያከብሩ ይኖራሉ። በኢትዮጵያ ግን ይሄ ተጠብቆ ያለ ነው፤ እስከ አሁን ድረስ አልተለወጠም።
እንግዲህ በዓላችን በመሠረቱ ከአበው፥ ከመጽሐፍ የወረስነው ነው እንጂ እንደ እንግዳ ድንገተኛ ደራሽ፥ እንደ ወንዝ ድንገተኛ ፈሳሽ አለመሆኑን በዚህ መረዳት አለብን። ይህም ከሆነ ያለንን ከትውልድ ወደ ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት ደግሞ ከእያንዳንዳችን የሚፈለግ ነው። እንግዲህ እያንዳንዳችን ከአባቶቻችን የተቀበልነውን ይህን አኩሪ እምነትና ሥርዐት ለልጆቻችን የማውረስ ግዴታ አለብን።
የሚያስፈልግ ሆኖ ከተገኘ ከአውሮፓውያንም ሆነ ከሌሎች ሥልጡኖች እንደ ተግባረ እድ ያለውን የሙያ ማዳበሪያ መቀበል ይገባናል። ግን ልንቀበለው የማይገባንን መቀበል፥ ልንተወው የማይገባንን መተው፥ ልናፈርሰው የማይገባንን ማፍረስ ይሄ ከቁም ነገር አይቈጠርም። «የዝንጀሮ ሰነፍ ያባቱን ዋሻ ይጠየፍ፤» ይባላል። እኛ መቼም ቆዳችንን፥ ቀለማችንን እስካለወጥን ድረስ ኢትዮጵያውያን ነን። ይህን ማመን አለብን። ኢትዮጵያዊነት ደግሞ እኛን የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር አይደለም። ስለ ኢትዮጵያ ቀዋሚውን ምስክር፥ ዓለም ያመነም ያላመነም ተስማሞቶ የሚቀበለውን መጽሐፍ ቅዱስን ብንመረምር በቍጥር በርከት ባሉ ቦታዎች ላይ ተጠቅሳ፥ ያውም በቅድስና መልክ ተቈጥራ የምትገኝ ኢትዮጵያ ናት። በተለይም፤ «ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፤» የሚለው ቃል ብዙ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋራ የተገናኘንባቸውን ብዙ ነጥቦች፥ ብዙ ታሪኮች፥ ብዙ ሥራዎች ያቀፈ ስለ ሆነ ይህ ብቻ ራሱ ሊያጓጓን ይገባዋልና እንግዲህ ከባህል የወረስናቸውን ማንኛቸውንም ሥርዐቶች ጠንቅቀን ለልጆቻችን ማውረስ ይጠበቅብናልና እግዚአብሔር ይህን ለመፈጸም ይርዳን። አሜን።

ምንጭ፦ http://www.aleqayalewtamiru.org/new_year_2003.html

Tuesday, September 3, 2013

የሃማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ አስፈላጊ ነበር???

ይህ ጉባኤ በዋናነት የተቋቋመው ለአገር ሰላምና በእምነት ተቋማቸው ለሚያስተዳድሩት ህብረተሰብ(የእምነት ተቋም) ደህንነት እንጂ ለመንግሥት ወይም ለአንድ የፖለቲካ ድርጅት አይደለም። በተለይ ደግሞ ይህ ጉባኤ በእምነት ተቋማት መካከል አለመግባባት እንዳይፈጠር እና ወደ አልተፈለገ ግጭት/እሰጣ ገባ/ ውስጥ እንዳይገባ ሁሉም የየራሱን የሃይማኖት አስተምሮ በመቻቻል እንዲሁም ሰላምና ፍቅር በተሞላበት መንገድ እንዲያካሂዱ ለማድረግ የተቋቋመ ይመስለኛል።
በትናትናው እሁድ ማለትም በ26/12/2005 ዓም የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ግን ከዓላማው በእጅጉ የራቀ እና ሁኔታዎችን ያላገናዘበ መስሎ ይታያል። እርግጥ ነው ይህ ጉባኤ አገራዊ ሰላም ሊያደፈርሱ ይችላሉ ብሎ ያመነባቸውን ጉዳዮች ለህዝብ ይፋ ማድረጉ የሚበረታታና ለወደፊትም ሊቀጠልበት የሚገባ ተግባር ነው። ነገር ግን ይፋ ከማድረጉ በፊት የሃይማኖት ኮሚቴ እንደመሆኑ መጠን በርካታ ቅድመ ስራዎች ሊኖሩት ይገባል። የህብረተሰቡን ነባራዊ ሁኔታ፣ የእምነት ተቋማት አመለካከትና የፖለቲካ አቅጣጫን በሚገባ ማጤን ከዚህ ትልቅ ከሚቴ ቀርቶ ከአንድ ግለሰብ ሊሰወር የማይገባ ነገር ነው።
የህብረተሰቡን ነባራዊ ሁኔታ በትክክል መገንዘብ ያስፈልጋል ሲባል የተፈጠረውን ችግር ህብረተሰቡ በምን መልኩ ነው የተረዳዉ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ሊያስወጣ በሚችል መልኩ ነው? ውይስ የግንዛቤ እጥረት አለበት? ወይስ በሌላ አቅጣጫ ነው የተረዳው? የሰላማዊ ሰልፍ አስፈላጊነት? እና መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት ህብረተሰቡ ያላበትን የግንዛቤ ደረጃ መለካት፣ ማጤንና መመልከት ይገባል። እንዲሁም ህብረተሰቡን ግንዛቤ ከማስጨበጥ አንጻርም ይህ ኮሚቴ ትልቅ ኃላፊነት አለበት። ሰላማዊ ሰልፍ ወይም ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት የችግሩን አሳሳቢነት ማለትም በአገርና በሃይማኖት ተቋማት ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ችግር በሚገባ በተለያየ መልኩ ማስረዳትና ማሳወቅ፣ መግለጽና ማስተላለፍ ይኖርበታል። ምናልባት ኮሚቴው ይህን አድርጊያለሁ ቢልም በቂ ነው ብዬ አላምንም። በዚህ መልኩ ህብረተሰቡን ማንቃትና ወደ አንድ የግንዛቤ መንፈስ እንዲመጣ ሳያደርጉ ውሳኔ መወሰን ይባስ ብሎ አገራዊ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራት ከጥቅሙ ጉዳቱ እጅግ የከፋ ይሆናል።
የእምነት ተቋማት አመለካከት ምን ይመስላል የሚለውንም በሚገባ መረዳት የኮሚቴው ተቀዳሚ ተግባር ነው። የዚህን ኮሚቴ የእያንዳንዱ አባል የወከለው የእምነት ተቋሙ ነው። ስለዚህ ከእምነት ተቋሙ ጋር መነጋገር፣ መወያየት፣ የችግሩን አመጣጥና ሁኔታ፣ በተቋሙ ላይ ሊያስከትለው የሚችለውን ችግር በሚገባ ማየትና ተደጋጋሚ ውይይቶች ያስፈልጋሉ። ችግሩ ተፈጠረ ከተባለበት ተቋም ወይም ቦታ ድረስ በመሄድ ችግሩን በውውይት ለመፍታት መሞከር ይኖርበታል። በእኔ አመለካከት የሃይማኖት ተቋማት ከመንግሥትም በላይ ለሰላምና ለህብረተሰቡ ደህንነት የሚቆሙ ናቸው። ስለዚህ ችግሩን በውይይት፣ በትምህርትና በተግሳጽ ለመፍታት መጣር ያስፈልጋል። ኮሚቴው እንደኮሚቴ ከመወሰኑ በፊት ከወከለው የእምነት ተቋም ጋር ግልጽ ውይይት አድርጎ ችግሩን ሊፈታ በሚችል መልኩ አንድ አቋም መያዝ ይኖርበታል። በእውነት የትናቱ ሰላማዊ ሰልፍ ግን የተፈጠረውን ችግር ሊፈታ ይችል ነበር??? መልሱን ለእናንተ ትቸዋለሁ።
ይህ ኮሚቴ ከፖለቲካ ነጻ እንደመሆኑ መጠን / በወረቀት ደረጃ ማለቴ ነው/ አንድ ውሳኔ በሚወስንበት ጊዜ የፖለቲካ አቅጣጫውን መመልከት ያስፈልገዋል። ምንም እንኳ ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ ናቸው ቢባልም መንግሥት ከሃይማኖት ነጻ ሁኖ ስለማያውቅ አቅጣጫውን እና ሂደቱን ከውሳኔ በፊት መረጃዎችን መሰብሰብና መፈተሽ ያስፈልጋል። የህብረተሰቡ የፖለቲካ አመለካከት ምን ይመስላል? የገዢው ፓርቲ ያለበት ደረጃ? የተቀዋሚ የፖለቲካ እንቅስቃሴና ሌሎችንም ተያያዝ ነገሮችን መፈተሽ ይኖርበታል። እነዚህ ሁኔታወችን ሳይገነዘብ ወደ ውሳኔ ከገባ ግን በአንድ ተጽዕኖ ውስጥ ሊገባ ይችላል፤ ይኸው ገባም። የሃይማኖት ተቋም የሰላም ኮሚቴ ተብሎ በአንድ ተጽዕኖ ውስጥ ዥው ብሎ መግባት ግን ችግሩ እንዲበባስ ያደርገዋል፤ በተጫማሪም ሌላ ችግር ይፈጥራል እንጂ መፍትሔ ሊያመጣ አይችልም።
ጉባኤው መመልከት ያልቻላቸው ግልጽ ነገሮች፦
1. ችግሩን፦ ጉባኤው በአዲስ አበባ በ10 ክፍለ ከተሞችና በ116 ወረዳዎች በተካሄደው ህዝባዊ የሰላም ኮንፈረንስ እንዲሁም ከፍትህ ቢሮ ጋር በመተባበር ከነሐሴ 15-16 በተካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ ላይ የሃይማኖት መሪዎችና ተከታዮቻቸው «ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማችን እየታየ ያለው የአክራሪነትና የፅንፈኝነት እንቅስቃሴ የሀገራችንን ሰላምና ልማት የሚያውክ፣ በሰላም አብሮ የመኖር እሴቶቻችንን የሚያናጋና የሃይማኖት መልክ የሌለው የጥፋት እንቅስቃሴ ከመሆኑም በላይ በህገ መንግሥታችን የተደነገገውን የሃይማኖት እኩልነትና የእምነት ነፃነት የሚፃረር ስለሆነ በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሟችንን ማሰማት እንፈልጋለን» ተብሎ በአቋም መግለጫ የተላለፈውን መሰረት በማድረግ ሰልፉ እንደተዘጋጀ በጋዜጣዊ መግለጫ ስለሰልፉ አስፈላጊነትም በማብራራት ሰላማዊ ሰልፉ በመጪው እሁድ ከንጋቱ 12 ሰዓት በመስቀል አደባባይ የሚካሄድ ሲሆን፤ በከተማው ውስጥ ያሉ የሃይማኖት ተቋማት በሙሉ በጋራ በመሆን ለሰላም፣ ለልማት፣ ለመቻቻልና ለአብሮነት ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚገልጹበት የሰላም መድረክ ነው//፤ በማለት የጉባኤው ኮሚቴ በገለጸልን መልኩ ችግሩን ሙሉ በሙሉ እንውሰደው ብንል እንኳ የሃይማኖት አክራሪነት ከመቼ ወዲህ ነው በሰላማዊ ሰልፍ ሊገታ የሚችለው። ኃያላን አገራት እንኳ በተደራጀና ዘመናዊ ስልትን በመጠቀም አክራሪነትን ማቆም ሳይችሉ እኛ እንዴት ነው በሰላማዊ ሰልፍ ልናቆመው የምንችለው። እንደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሰላማዊ ሰልፍ ለሰላማዊ ትግልም ልንጠቀምበት አልታደልንም። ስለዚህ ጉባኤው የሃይማኖት አክራሪነትን በሰላማዊ ሰልፍ ለመግታት መሞከሩ የችግሩን ምንነት አለመረዳት ነው። ችግሩን በሚገባ ሳይረዱ ደግሞ ውሳኔ መወሰኑ ከመፍትሔው ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ብዙ መናገር የሚያስፈልግ አይመስለኝም። ችግሩም መቶ ፐርሰንት/100%/ አክራሪነት ነው ብሎ ለመፈረጅ ማስረጃ የሚያጥር ይመስለኛል። በግሌ አክራሪነት የለም፣ አይኖርም የሚል አመለካከትና ግንዛቤ የለኝም። ቢሆንም ግን በሰላማዊ ሰልፍ ከችግሩ እንወጣለን የሚል እምነት ፍጽሞ አይኖረኝም።
2. ስዓት፦ ሰላማዊ ሰልፉ እንዲጀመር የተደረገበትን ስዓት እንኳን ስንመለከተው ጉባኤው ከወከለዉ የእምነት ተቋም ጋር ጥብቅ ውይይት አለማድረጉን በቀላሉ መመልከት እንችላለን። በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ያን እና ሌሎችም ማለት ይቻላል በየሳምንቱ እሁድ ጥዋት የአምልኮት ስርዓታቸውን የሚፈጽሙበት ስዓት ነው። ስለዚህ ስዓቱን እንኳ ያገናዘበ ሰላማዊ ሰልፍ አለመጥራት የግደለሽነት ያስመስላል። ወይም በሌላ ተጽዕኖ ውስጥ መሆኑን በግልጽ ለመረዳት አያዳግትም። በተጽዕኖዎችና በግደለሽነት የሚደረጉ ማንኛውም ነገሮች ደግሞ ችግርፈጣሪ እንጂ ችግር ፈቺ መቸውንም አይሆኑም።
3. ቀን፦ በሰላማዊ ሰልፉ አስፈላጊነት ጉባኤው ካመነ በቀላሉ ሊመለከተው የሚገባው ነገር የሚደረግበትን ቀን ነው። በዚያ ቀን ምን ተያያዥ ነገር አለ? ቀኑ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል፣ ለእምነት ተቋማትና ለፖለቲካ ፓርቲዎች ምቹ ነው? የሚለውን ጥያቄ ጉባኤው ከመወሰኑ በፊት መመልከት ይኖርበት ነበር። ጉባኤው ግን በተቃራኒው የተጓዘ ይመስላል። ይህ ቀን ማለትም 26/12/2005 ዓ.ም ግን ሰማያዊ ፓርቲ የአገር ሰላም እንዲሰፍን፣ ሰባአዊ መብት እንዲከበር፣ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ከአላግባብ የታሰሩ ዜጎች እንዲፈቱ፣ እኩልነት እንዲረጋገጥ፣ ሙስናና አገርን ወደ ኋላ ሊጎትቱ የሚችሉ ችግሮችን ለመቅረፍና ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር ከመንግሥት እንኳ ሳይቀር ፍቃድ ጠይቆ ለ2ተኛ ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ የጠራበት ቀን ነበር። ጉባኤው ግን ይህን ሳያገናዝብ በመጥራቱ ለፓርቲው አባላት እስራት፣ እንግልትና ድብደባ ምክንያት ሁኗል። ፓርቲው የጠራው ሰላማዊ ሰልፍም በእስራትና በድብደባ እንዲቀየር አድርጎታል። ሙሉ በሙሉ ጥፋቱ የመንግሥት ቢሆንም የጉባኤው አባላት ለዚህ ተግባር ተባባሪ በመሆናቸው ተጥያቂ አድርጓቸዋል። ሌሎችን እናተ ጨምሩበት.......
በአጠቃላይ የጉባኤው ሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ አስፈላጊ ነበር የሚለውን ሁላችንም በራሳችን አስተያየት እንስጥበት እና እንማርበት። አስፈላጊ አልነበረም ለምንል ሰዎች ወደፊት እንዲህ አይነት ተያያዥ ክስተቶች እንዳይፈጠሩ ምን እናድርግ ለማለት ሃሳብ መለዋወጡ መልካም ስለሚሆን ለመነሻ ያክል የግሌን ሃሳብ አቅርቢያለሁ።