Friday, August 30, 2013

ተክለ ሃይማኖት

የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል (መዝ 111፥6)
ከአባታቸው ከካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ቅድስት እግዚእ ኃረያ መጋቢት 24 ቀን ተፀንሰው፡በ1215 ዓ.ም ታሕሣሥ 24 ቀን ተወለዱ፡፡ ወላጆቻቸውም ፍስሐ ጽዮን አሏቸው፡ ትርጓሜውም የጽዮን ተድላዋ ደስታዋ ማለት ነው፡፡ ተክለ  ሃይማኖት ማለት ተክለ አብ፣ ተክለ ወልድ፣ ተክለ መንፈስ ቅዱስ / የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ተክል/ፍሬ/ ማለት ነው፡፡ በተወለዱ በሦስት ቀናቸው ከእናታቸው እቅፍ ወርደው «አሐዱ አብ ቅዱስ፣አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ» ብለው ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ አመት ከ3 ወር ሲሆናቸው በተወለዱበት በሽዋ በጽላሎሽ አካባቢ ብርቱ ረሀብ ሆነ፡፡ እናቱ እግዚያራ የቅዱስ ሚካኤል በዓል ሊታጎልብኝ ነው ቢላ እያዘነች እያለቀሰች እያለ በእጃቸው እያመለከቱ ወደቤት እድታገባቸው አመለከቷት ይዛቸውም ገባች፡፡ እፍኝ የስንዴ ዱቄት የነበረበትን እንቅብ እጃቸውን ቢጭኑበት ሞልቶ ፈሰሰ::9 እንቅብ አምጥታ ብታቀርብላቸው እየዘገኑ ቢያረጉበት ዘጠኙም ሞልተው ተገኝተዋል፡፡ የቅቤውንም ማሰሮ በተመሳሳይ በበረከት ሞልቶውታል፡፡ በዚህም ሁኔታ መጋቢት 12 የቅዱስ ሚካኤልን በዓለ ዝክር ያለፈና ያገደመውን ሁሉ እያበሉና እያጠጡ በሰላምና በደስታ በዓሉን አውጥተውታል፡፡
በወላጅ አባታቸው በካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብ ግብረ ዲቁናን ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ሲያጠኑ ቆይተው በአሥራ አምስት ዓመታቸው ከእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ /ጌርሎስ/ ዲቁናን ተቀብለዋል፡፡ በዚህም ቅድስት ቤተክርስቲያንን በወጣትነት ዕድሜያቸው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከጓደኞቻቸው ጋር ወደ ዱር አደን ሄደው ሳለ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ ለኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ሐዲስ ሐዋርያ አድርጎ መረጣቸው። ስማቸውንም «ተክለ ኃሃይማኖት» አለው፡፡ ትርጓሜውም የኃይማኖት ፍሬ ማለት ነው፡፡
አባታችንም ሐዋርያዊ ጉዟቸውን ሲጀምሩ፦«አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደተከፈተ ተውኩልህ . . . ደካማ ለሆንኩ ለእኔ ያለ አንተ የሚያፀናኝ የለም። ለምፍገመገም ለእኔ ያለ አንተ ደጋፊ የለኝም። ለወደቅሁ ለእኔ ያለአንተ የሚያነሳኝ የለም። ለአዘንኩ ለእኔ ያለአንተ የሚያረጋጋኝ የለም። ለድሀው ለእኔ ያለ አንተ መጠጊያ የለኝም፡፡» ይህን ብለው ትሕትና በተሞላበትና በተሰበረ ልብ ወደ ፈጣሪያቸው ከለመኑ በኋላ በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገራት ከኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ፣ ከክህደት ወደ ሃይማኖት መልሰዋል፡፡ በዚህም የተነሣ ለኢትዮጵያውያን ብርሃን ፀሐይ ተብለዋል፡፡ ይህን ሁሉ ገድልና ትሩፋት እየፈጸሙ ዕረፍታቸውም በደረሰ ጊዜ ደቀመዝሙሮቻቸውን «ልጆቼ ሆይ ሁሉም መነኮሴ መንግሥተ ሰማይ ይገባል ማለት አይደለም፤ ዓለምን በሚገባ የናቀ ብቻ ይገባል እንጂ መጀመሪያ የእግዚአብሔርን ጽድቁን ብቻ ፈልጉ፤ ጾምና ጸሎትን አዘውትሩ፤ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ ትእዛዛቱንም አጥብቃችሁ ጠብቁ እያሉ ይመክሯቸው ነበር. . .» በኋላም «ለዓለም ጨው ለራሴ አልጫ ሆንኩ፤ ለዓለም ብርሃን ለራሴ ጨለማ ሆንኩ፣ ከእውነተኛው ዳኛ ከጌታዬ ፊት ስቆም ምን እመልሳለሁ?» እያሉ በፍጹም ትህትና እና በልዩ መንፈሳዊ ተመስጦ ይጸልዩ ነበር፡፡
በመጨረሻም ከበዓታቸው ገብተው ወደፊት ወደኋላ ቁጭ ብድግ እንዳይሉ ከፊት ከኋላቸው ከግራ ከቀኛቸው ስምንት ጦር ተክለው ሱባኤ ያዙ፡፡ ከመቆም ብዛት የተነሳ አንድ እግራቸው ተቆረጠ፡፡ በአንድ እግራቸው ቆመው ለ7 አመት ጸልየዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ነሀሴ 24 በ 99 አመታቸው ጻድቁ አባታችን ዐርፈዋል፡፡ በዚህም መሠረት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ዕረፍታቸው በእግዚአብሔር ፊት ለከበረና ብዙ ክብር ለተሰጣቸው ለጻድቁ ተክለ ሃይማኖት በየዓመቱ በነሐሴ ፳፬ ቀን በዓለ ዕረፍታቸውን በታላቅ ድምቀት ታከብራለች፡፡
የጻድቁ አባታችን በረከታቸው፣ረድኤታቸውና አማላጅነታቸው አይለየን፡ አሜን!!!

Wednesday, August 21, 2013

ፍልሰታ

ፍልሰታ የሚለው ቃል የሚገልጸው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለቆ መሔድን መሰደድን መፍለስን ያመለክታል። ይህም የእመቤታችንን ሥጋ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መፍለሱን በኋላም በገነት በዕፀ ሕይወት ስር ከነበረበት መነሳቱን ለማመልከት ይነገራል።
ጾመ ፍልሰታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 64 ዓመት በዚች ምድር ኖራ እንደ አንድ ልጇ መሞቷን መነሳቷንና ማዕረጓን ያዩ ዘንድ ሐዋርያት የጾሙት ጾም ነው። ጾሙ ከነሐሴ 1 ቀን እስከ ነሐሴ 16 ቀን ሲጾም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዋጅ ከደነገገቻቸው ሰባቱ አጽዋማትም አንዱ ነው።
እመቤታችን ከአባቷ ከኢያቄም እና ከእናቷ ከሐና ነሐሴ 7 ቀን ተጸንሳ ግንቦት 1 ቀን በሊባኖስ ተወልዳለች። እምቤታችን በእናት አባቷ ቤት ሦስት/፫/ ዓመት፤ በቤተ መቅደስ አሥራ ሁለት/12/ ዓመት፤ ከልጇ ከወዳጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር/33 ከ3 ወር/ ፡ ከዮሐንስ ወልደ ዘብዴዎስ ዘንድ አሥራ አራት ዓመት ከዘጠኝ ወር/14 ከ9 ወር/ ቆይታ በ 64 ዓመት ዕድሜዋ በ49 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች። የእመቤታችንን ስም የሚገልጹ የውዳሴ ጽሑፎችም በእድሜዋ ልክ ተደርሰዋል። ለምሳሌ የውዳሴ ማርያም ቁጥር 64 ነው፤ የመልክአ ማርያም ቁጥርም 64 ነው።
ባረፈች ጊዜ ቅዱሳን ሐዋርያት ተሰባስበው አስከሬኗን ይዘው ወደ ጌቴሴማኒ መቃብር ለማሳረፍ ሲሄዱ አይሁድ ለተንኮል አያርፉምና ተተናኮሏቸው። ቀድሞ ልጇ ሞቶ ተነሳ፣ አረገ እያሉ ሲያስቸግሩን ይኖራሉ: ደግሞ አሁን እሷም ተነሳች፣ አረገች ሊሉ አይደል በማለት አይሁድ ተሰባስበው አስከሬኗን ለማቃጠል ሲተናኮሉ እግዚአብሔር በተአምር ከነዚያ አይሁዶች አድኗቸዋል ። ከሁሉ አንዱ ታውፋኒያ የተባለው ተራምዶ አጎበሩን ጨበጠው የታዘዘ መልአክ ሁለት እጁን በሰይፍ ቀጣው። ከአጎበሩ ተንጠልጥሎ ቀረ። በድያለው ማሪኝ ብሎ ቢማጸናት ራሷን ዘንበል አድርጋ ጴጥሮስን እንደነበረ አድርግለት አለችው። ቢመልሰው ድኖ ተነስቷል። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር የእመቤታችንንም አስከሬን ነጥቆ ከሐዋርያው ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር በገነት በዕፀ ህይወት ስር አኑሯቸዋል ። ከዚያ በኋላ ሐዋርያት ሥጋዋን አግኝተው ይቀብሩት ዘንድ በአረፈች በስምንተኛው ወር ከነሐሴ 1 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 14 ቀን ድረስ ሁለት ሱባዔ ይዘው በአሥራ አራተኛው ቀን ሥጋዋን ከጌታ ተቀብለው በጸሎትና በምህላ በፍጹም ደስታ በጌቴሰማኔ አሳረፉት ። በሦስተኛውም ቀን ተነስታ ስታርግ ከሰዱቃውያን ወገን የሆነው ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ አያት። እርሱም በቀብር ስርዓቱ ጊዜም አልነበረም። ሀገረ ስብከቱ ህንድ ስለነበር ሊያስተምር ወደዛው ሂዶ ነበርና። በዚያም ሲያስተምር ሰንብቶ በደመና ተጭኖ ሲመጣ ያገኛታል። ትንሳኤዋን ከርሱ ሰውራ ያደረገች መስሎት አዝኖ «ቀድሞ የልጅሽን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁ አሁን ደግሞ ያንቺን ትንሳኤ ሳላይ ቀርቼ ነውን ?» ብሎ ቢያዝንባት እመቤታችንም ከርሱ በቀር ማንንም ትንሳኤዋን እንዳላየ ነግራ አጽናናችው። ለሌሎቹ ሐዋርያትም እንዲነግራቸው ለምልክትም /ለምስክርም እንዲሆነው ሰበኗን /መግነዟን ሰጥታው አረገች። ቶማስም ኢየሩሳሌም ደርሶ ሐዋርያትን «የእመቤታችን ነገርስ እንደምን ሆነ?» ሲል ቢጠይቅ «አግኝተን ቀበርናት እኮ» አሉት። እርሱ ምስጢሩን አዉቆ ደብቆ «ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር» እንዴት ይሆናል ? አይደረግም ይላቸዋል። ሊያሳያቸውም መቃብሩ ዘንድ ሂደው ቢከፍቱት አጧት። እርሱም «አታምኑኝም ብዬ እንጂ እርሷስ ተነስታ አርጋልች»በማለት ሁኔታውን ተረከላቸውና ለምስክር ይሁንህ ብላ የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው። ከዚህ በኋላ ለበረከት ይሆናቸው ዘንድ ሰበኑን ተካፍለው ወደየአህገረ ስብከታቸው ሄዱ። ዛሬ በቅዳሴ ጊዜ ዲያቆኑ በሚይዘው የመጾር መስቀል ላይ በሁለት ቀዳዳዎች አልፎ ተጠምጥሞ የምናየው መቀነት መሰል ጨርቅ የዚያ ሰበን ምሳሌ ነው።
በዓመቱ ሐዋርያት ከያሉበት ተሰባስበው ቶማስ ትንሣኤሽን አይቶ እኛስ እንዴት ይቀርብናል ብለው ከነሐሴ 1 ቀን ጀምርው ሱባዔ ቢይዙ ከሁለት ሱባዔ በኋላ እንደገና ትንሳኤዋንና እርገቷን ለማየት በቅተዋል። ሐዋርያዊት የሆነች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናም ምእመኖቿ ከእመቤታችን በረከትን እንዲያገኙ ይጾሙ ዘንድ ይህን ሐዋርያት የጾሙትን ጾም እንዲጾሙ አውጃለች። ምእመናንም በተለየ መልኩ በጾም በጸሎት በሱባዔ  ሆነው ይህን ወቅት ያሳልፋሉ።
የእመቤታችን ትንሣኤ ድንገት እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውሀ ፈሳሽ የተደረገ ሳይሆን በቅዱሳት መጻሕፍት በትንቢተ ነቢያት የተገለጸ ነው። ነቢዩ ዳዊት በመዝሙር 131፡1 ላይ «አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህ ታቦ» ይላል። በዚህም ምዕመናንን ወደ ምታሳርፍበት ወደ መንግሥተ ሰማያት የመቅደስህ ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነስ አለ። ታቦት የጽላት ማደርያ እንደሆነ ሁሉ እምቤታችንም ለክርስቶስ ማደርያ በመሆኗ አማናዊት ታቦት ትባላለች።
ንጉስ ሰሎሞንም መኃ 2፡10 ላይ «ውዴ እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፤ ወዳጄ ሆይ ተነሽ፡ ውበቴ ሆይ ነይ» ብሏል። እዚህ ላይ«ወዳጄ ...ዉበቴ» የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት ። ክቡር ዳዊት መዝሙር 44፡9 ላይ «በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች» እንደሚል ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም ቤዛነቱን ከፈጸመ በኋላ ወደ ቀደመ ክብሩ እንዳረገ እመቤታችን ቅድስት ድንገል ማርያምም በቀኙ ትቀመጥ ዘንድ «ተነሽ ነይ» አላት ። እንግዲህ ይህንና የመሰለዉን ሁሉ ይዘን የእናታችንን እረፍቷን ትንሣኤዋን በጾም በጸሎት እንዘክራለን እንመሰክራለንም።
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤቷ፣ በረከቷ፣ አማላጅነቷ አይለየን፡ አሜን።

Monday, August 19, 2013

ደብረ ታቦር


ደብረ ታቦር ማለት የታቦር ተራራ ማለት ነው። ከ9ኙ ዓበይት በአላት መካከል አንዱ ነው። ታሪኩም በአጭሩ፦ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል ብሎ በጠየቃቸው በሰባተኛው ቀን ከነቢያትም አንዱ ነህ ብለውታልና የነቢያት አምላካቸው እንደሆነ ለማጠየቅ፤ በቅዱስ ጴጥሮስ የተነገረውን በጌታ ቃል ለማስመስከር ሶስቱን ባለሟሎቹን (ቅዱስ ጴጥሮስን፣ ቅዱስ ያዕቆብንና ቅዱስ ዮሓንስን) ለብቻቸው ወደ ተራራ ይዟቸው ወጣ። መልኩም በፊታቸው ተለወጠ አካሉም ምሉዕ ብርሃን ሆነ፤ ገጹም እንደ ፀሐይ ብሩህ ልብሱም እንደ በረድ ፀዓዳ። 
ይህ ሁሉ ጌትነቱን ሲገልጽላቸው ነው። እነሆም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ሙሴ የእኔን የሙሴን ጌታ ማን ሙሴ ይልሃል የሙሴ አምላክ ይበሉህ እንጂ፤ ኤልያስም የእኔን የኤልያስን ጌታ ማን ኤልያስ ይልሃል የኤልያስ አምላክ ይበሉህ እንጂ ሲሉ ተሰምተዋል። ቅዱስ ጴጥሮስም በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው አለው። እርሱም ገና ሲናገር ብሩህ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው ፥ ከደመናውም- በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት የሚል ድምጽ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሰምተው ደነገጡ ፈጽመው ፈሩ በፊታቸውም ወደቁ። ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸው፤ አይዟችሁ ተነሡ አላቸው። ዓይናቸውንም አቅንተው ሲያዩ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አዩ እንጂ መነንም ማን አላዩም። በዚህ ሁኔታ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነቱን በታቦር ተራራ ገለጸላቸው። ይኸውም “ታቦርና አርሞንዔም በስምህ ደስ ይላቸዋል” (መዝ 88፡ 12-13) ተብሎ በቅዱስ ዳዊት የተነገረውን ትንቢት ሊፈጽም ነው። ስለምን በተራራ አደረገው ቢሉ ተራራ የወንጌል፣ የመንግስተ ሰማያት፣ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ነው። ተራራ ሲወጡት ይከብዳል ከወጡት በኋላ ግን ሜዳውንና ጭንጫውን ኮረብታውን ሲያሳይ ደስ ያሰኛል ወንጌልም ሲማሯት ታጽራለች፤ ከተማሯት በኋላ ግን ጽድቅና ኃጢያትን ለይታ ስታሳውቅ ደስ ታሰኛለችና። አንድም ተራራ በብዙ ፃእር እንዲወጡት መንግስተ ሰማይንም በብዙ መከራ ያገኟታልና ነው። በዚህም ተራራ ከነቢያት ሁለቱን ከሐዋርያት ሶስቱን ማምጣቱ በቤተ ክርስቲያን ብሉይና ሐዲስ እንዲነገር ለማጠየቅ ነው። መንግስተ ሰማያትንም ነቢያትና ሐዋርያት፤ ደናግላን እንደ ኤልያስና መዓስባን እንደ ሙሴ ያሉ፤ ሕያዋን እንደ ኤልያስና ምውታን እንደ ሙሴ ያሉ በአንድነት እንዲወርሷት ለማስረገጥ ነው። ማቴ 17፡1_
እግዲህ ይህ ታላቅ በዓል ብዙ ሚስጥር የተገለጠበት ስለሆነ ቅድስት ቤተክርስትያን በዜማና በመዝሙር ታከብረዋለች። በምናከብርበትም ጊዜ ቡሄ በሉ እያልን፣ ሙልሙል ይዘን፣ ችቦ እያበራን እናከብራለን። ምሳሌውም፦

ቡሄ፦
 ይህ ቦታ ጌታ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ተራራ ነው። በዚህ ምክንያት ያቺ ዕለት ቡሄ የሚለውን ስያሜ አገኘች ቡሄ ማለት ገላጣ፣ የተገለጠ ማለት ነው።

የሙልሙሉ እና የችቦው ምሳሌ ደግሞ፦
 ጌታችን ብርሃነ መለኮቱ በገለጠበት ዕለት ጊዜው ምሽት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እረኞች ከብርሃኑ የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም ነበር። የልጆቹን መዘግየት ያዩ ወላጆች ችቦ አብርተውና ዳቦ ይዘው ፍለጋ ወጡ። አሁን ታዲያ «ቡሄ» ለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠውና ችቦ በማብራት በዓሉን የምናከብረውም ከዚህ በመነሣት ነው።

ልጆች በገጠርም ሆነ በከተማ ጅራፍ የሚያጮኹበት ሁኔታም አለ። የጅራፉ ምሳሌ አብ «የምወደው ልጄ ይህ ነው፡፡ እርሱን ስሙት» ብሎ ሲናገር የነበረው ድምጽ ምሳሌ ነው። ሙሴና ኤልያስ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ያዕቆብ ደንግጠው ነበር። ያን ለማሰብ ጅራፍ እናጮሀለን።

አንቺ ደብረ ታቦር ምንኛ ታደልሽ
ጌታ መለኮቱን የገለጠብሽ
ያገቡ ድንግላይ ሁሉን ሰበሰብሽ፣
በብርሃን ተመልተሽ በመገኘትሽ
ለመንግስተሰማይ ምሳሌ ሆንሽ።
ዓለም እንዲያምንበት ባምላክነቱ
እነሆ በታቦር ታየ ጌትነቱ፣
አብ መሰከረለት በደመና አውሎ
የምወደው ልጄ ይህ ነው ስሙት ብሎ፣
ሙሴና ኤልያስ ካያሉበት መጥተው
ቆመው መሰከሩ በቀኝ በግራው።
በአጠቃላይ ደብረ ታቦር/በታቦር ተራራ ላይ
  1. "ታቦርና አርሞንኤም በአንተ ስም ደስ ይላቸዋል" መዝ 89:12 ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ።
  2. መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክነቱን ገለጠ።
  3. ምስጢረ ስላሴ ተገለጠ/አብ በደመና ድምጹን በማሰማት፣ መንፈስ ቅዱስ በብርሃን፣ ወልድ በአካል/።
  4. ሙሴ፦ "እኔ ማሕር ብከፍልም፣ ጠላት ብገድልም፣ ደመና ብጋርድም፣ መና ባወርድም፣ እስርኤልን ከክፋታቸው መልሶ ማዳን አልተቻለኝም። ለአንተ ግን ሁሉ ይቻልሃል። ደግሞስ የኔን ፈጣሪና ጌታ እንዴት ሙሴ ይሉሃል? የሙሴ ጌታ ይበሉህ እንጂ" በማለት የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት መሰከረ።
  5. ኤልያስ፦ "እኔ ሰማይ ብለጉም፣ እሳት ባዘንብም እስራኤልን ከክፋታቸው መልሶ ማዳን አልተቻለኝም። ለአንተግን ይቻልሃል። ደግሞስ የኔን ፈጣሪና ጌታ እንዴት ኤልያስ ይሉሃል? የኤልያስ ጌታ ይበሉህ እንጂ" በማለት የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት መሰከረ።
  6. በህይወት፣በእምነት፣ በቤተ ክርስቲያንና በአገልግሎት መኖር መልካም እንደሆነ ቅዱስ ጴጥሮስ "በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው" በማለት ተናገረ።
  7. የእግዚአብሔር መንግሥት ሕግን ጠብቀው ለሚኖሩ ለሁሉም መሆናን ሙሴን ከአገቡት፣ ኤልያስን ከደናግልና ሐዋርያትን ከአለም አምጥቶ አሳየን።
  8. ደብረ ታቦር የወንጌል፣ የመንግሥተ ሰማያትና የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ መሆኗን፤ ነብያት በትንቢትና በምሳሌ፣ ሐዋርያት በግልጥና በተግባር የሰበኳት መሆኑን ገለጠ።
ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን፤
ብርሃነ መለኮቱን እንደገለጠ ለኛም ምስጥርን ይግለፅልን። አሜን!!!

Tuesday, August 13, 2013

ፅንሰታ ለማርያም

ቅዱሳን አባቶቻችን ስለ እመቤታችን ነገር በውዳሴያቸውና በቅዳሴያቸው እንዲህ ተናግረዋል፤ ቅዱስ ያሬድ “ማርያምሰ ተኀቱ እምትካት ውስተከርሱ ለአዳም ከመ ባሕርይ ጸዓዳ:- ማርያምስ ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች" አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም "ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ጸነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ:- ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም ፤በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ" "እኔስ የማርያምን ነገር እናገራለሁ በማብዛት አይደለም በማሳነስ ነው እንጂ፣ በማርዘም አይደለም በማሳጠር ነው እንጂ " በማለት በተአምረ ማርያም ላይ የእመቤታችን ነገር እፁብ ድንቅ መሆኑን ዘወትር በዕለተ ሰንበት ያበስሩናል።

በኢየሩሳሌም አገር የሚኖሩ ኢያቄምና ሐና የተባሉ በጣም ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡ አንድ ልጅ እንኳ ስላልነበራቸው እጅግ ያዝኑ ነበር፡፡ ወደ ቤተመቅደስ እየሄዱ እግዚአብሔር ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ አጥብቀው ይለምኑት ነበር፡፡ መባ ይዘው ለሊቀ ካህኑ ሮቤል ሲሰጡት ሊቀ ካህኑ እንኳ ሳይቀር እግዚአብሔር ብዙ ተባዙ ያለውን ህግ በእናንተ ላይ እንዳይፈጸም አድርጎ ልጅ የከለከላችሁ ኃጢአተኛ ብትሆኑ ነውና መባችሁን አልቀበልም ብሎ በእጅጉ አሳዝኗቸዋል። 
በሊቀ ካህኑ እያዘኑና እየተከዙ ሲመለሱ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ ዛፍ ስር ተቀመጠው ሳለ እርግቦች ጫጩቶቻቸውን ሲያጫውቱ ተመልክተው “ለነዚኽ ወፎች እንኳ ልጆችን የሰጠህ አምላክ ለእኛስ መች ይሆን ልጅ የምትሰጠን?” ብለው እጅግ አምርረው አለቀሱ፡፡ ሐምሌ 30 እሷ እርሱ ግምጃ ሲያስታጥቃት መቋሚያው አፍርታ ፍጥረት ፍሬዋን ሲመገቡ፣ እሱ ለእሷ ነጭ ርግብ ሰባቱን ሰማያት ሰንጥቃ መጥታ በቀኝ ጆርዋ ገብታ በማኅፀንዋ ስታድር ሕልም አለሙ። ሄደው ለመፈክረ ሕልም/ ሕህልም ተርጓሚ ሲነግሩት የከበረች ልጅ እንደሚወልዱ ነገራቸው። እነእርሱም ነገሩ እንግዳ ነገር ስለሆነባቸው ጊዜ ይፍታው ብለው ተመለሱ። የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲሆንላቸው በጸሎት ጠየቁ፡፡ እግዚአብሔር ወንድም ሆነ ሴት ልጅ ቢሰጣቸው አድጎ/አድጋ እኛን ያገልግለን/ታገልግለን  ሳይሉ ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ እንዲሆን እንደሚሰጡት ቃል ገቡ፡፡
ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ አብርሃምን እና ሳራን የተመለከተ አምላክ በኢያቄምና ሃና አማካኝነት ለዓለም ድህነት ምክንያት የሆነችውን እና ዓለም ሳይፈጠር በአምላክ ልቦና ታስባ ትኖር የነበረች የተነገረላት ትንቢት ሊፈጸም የአባት የእናቷ የቅድመ አያቶቿ ራዕይ ሊተረጎም ጌታ የፈቀደበት ጊዜ ሲደርስ እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም እሁድ እለት ነሐሴ 7 ቀን በ16 ዓ.ዓ ተፀነሰች፡: ሐና በእርጅናዋ ጊዜ መፅነሷ የተመለከቱ ዘመዶቿና ያገሯ ሰዎች ተገርመው እየመጡ ይጠይቋት ነበር፡፡
እመቤታችን ማርያም በፅንስ እያለች ታምራትን አድርጋለች። ከእነዚህም መካከል ዐይነ ስውር የነበረችው የአርሳባን ልጅ ወደ ሐና መጥታ እውነትም ሐና መጸነሷን ለማረጋገጥ ሆዷን ዳሰሰቻት፡፡ በአድናቆትም ሳታስበው ዐይኗን ስትነካ ዐይኗ በራላት፡፡ በሌላ ጊዜም የአጎቷ ልጅ በህመም ምክንያት ይሞትና ሐና ትወደው ስለነበር ልታለቅስ ወደአረፈበት ቤት ትሔዳለች፡፡ እንደደረሰችም አስክሬኑ በተቀመጠበት መካከል አልጋ ዙሪያ ስታለቅስ ሳለ ድንገት ጥላዋ ቢያርፍበት የሞተው ሰው ተነስቶ ሐና የአምላክ እናት የምትሆን እመቤታችንን እንደምትወልድና በዚህም ሐና እጅግ የከበረችና ምስጋና የሚገባት መሆኗን መሰከረ፡፡ ከዚህም በኋላ እመቤታችን ግንቦት 1 ቀን በክብር ተወለደች።


እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ  ከልጅሽ ከወዳጅሽ ይቅርታው፣ ቸርነቱ፣ ምህረቱ በእኛ ላይ እንዲያድር ለምኝልን፡ አሜን!!!

Thursday, August 8, 2013

የችግሮች መንስኤ እኛ እራሳችን ነን

ዛሬ ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግር እየጨመረ መምጣቱ ዓለምን ስጋትና ጭንቀት ውስጥ ከቷታል። ለአንዱ ችግር መፍትሔ ይሆናል ተብሎ የቀረበው ሃሳብ በሌላ በኩል ሊፈታ የማይችል ችግር ፈጣሪ ሲሆን መመልከት የተለመደ ነገር ነው። ምንም እንኳ /ከተለዩ ሰዎች በስተቀር/ ሰው በራሱ ችግር ለመፍጠር ተነሳሽ ባይሆንም ለመፍትሔም የዘገኘና ቆራጥነት የማይታይበት በመሆኑ ለችግሩ መበባስ መንስኤም ምክንያትም ነው። በዚህች አጭር ጽሁፍም የእኛ የችግር መንስኤነትን በአጭሩ ለማሳየት እሞክራለሁ። ሙህራን በዚህ ዙርያ ሰፊ ጥናት በማድረግ እንዲያቀርቡልን ግብዣየ በደስታ ነው።
  • እንደሚታወቀው እንደ አህጉራችን አፍሪካና አገራችን ኢትዮጵያ ሁላችንንም የሚያሳስበንና ጎልቶ የሚታየው የአስተዳደር/ፖለቲካዊ ችግር ነው። ሁሉም የፖለቲካ ድርጅት/ገዢው ፓርቲ/ ለነጻነት፣ ለሰላም፣ ለአንድነት፣ ለሰባዊ መብትና ለዲሞክራሲ እቆማለሁ ብሎ መነሳቱንና የህዝብ ድጋፍ ማግኘቱን ረስቶ የበፊቱንና የአለፈውን የአስተዳደር ዘመን በእጅጉ የሚያስመሰግን ሁኖ እናገኘዋለን። ዘረኝነትንና አድሎአዊነትን ለመዋጋት የተነሳ ድርጅት ከበፊቱ በበለጠ ችግር ፈጣሪ ሲሆን ጎልቶ ይታያል። ሙስናን ለመዋጋት የተነሳ ድርጅት ለሙስና መስፋፋት ዋነኛ ተዋናይ መሆኑ በእጅጉ ያሳስባል። ድህነትን ለማጥፋት የተነሳ ድርጅት ራሱን ከማበልጸግ ባለፈ የህዝቡን የኑሮ ደረጃ ከቲዮሪ/theory/ ባለፈ መቀየር አልቻለም። ዲሞክራሲን አሰፍናለሁ ብሎ የተነሳ ድርጅት ሚድያ ላይ ከመናገር ባሻገር ህብረተሰቡን የዲሞክራሲ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ግን አልቻለም። ምን አልባት ኢትዮጵያ በዲሞክራሲዊ አስተዳድር ስርዓት ትመራለች፣ ድህነት ቀንሷል ልንል እንችል ይሆናል፤ እውነት ነው የእኛም ትልቁ ችግራችን ይህ ነው። በመካከላችን 100% ልዩነት መኖሩ የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል በምቾት፣ በሰላም፣ በደስታ፣ በነጻነትና ዲሞክራሲ ሲኖር አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ በእጅጉ በሚያሳዝን ሁኔታ በርሀብ፣ በችግር፣ በስቃይ፣ በአድሎአዊነትና በነጻነት እጦት ውስጥ መኖሩ ችግሩ ጎልቶ እንዲታይ አድርጎታል።
ለችግር መንስኤዎች እኛው ነን ያልኩበት ምክንያትም የፓርቲውን/የድርጅቱን ዓላም በሚገባ ሳንረዳና ሳንገነዘብ ከመጀመሪያው ጀምረን ይሁን ብለን ድጋፍ እና እንክብካቤ በማድረጋችን ነው። ግማሾቻችን ደግሞ ሳይመቸን እንደ ተመቸን፣ ሳንጠግብ እንደ ጠገብን፣ ነጻነትና ዲሞክራሲ ሳይኖር በነጻነት እንደምንኖር ሁሉ እንደ ሄሮዶሳውያን ሺ ዓመት ንገስ፣ ከአለአንተ አገር ትገለበጣለች፣ ለህዝቡ ተቆርቋሪ የለም እያልን ችግሩን እንዲያስተካክል በግልጽ ከመናገር ይልቅ የማይገባውን የምስጋና ቅኔ ስለምናቀርብ፤ ከፊሎች ደግሞ በጊዜያዊ ጥቅም ተይዘው ችግሩን እንዳንመለከት ከለላ ስለሆነብንና መሰል ችግሮች ስላሉብን ለችግሩ መባባስ ዋነኛ ተጠያቂዎችም መንስኤዎችም እኛው እራሳችን ነን።
  • ለተለያዩ ችግሮች የመፍትሔ ሃሳብ ከምንጠብቅባቸው የእምነት ተቋማት ሳይቀር በመሪዎቻችን መካከል ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እናገኛለን። ጥቂት የእምነት መሪዎች/አባቶች ነን ባዮች ከአለም ባለስልጣናት ባልተለየ መልኩ አስተዳደራዊ በደል በእምነት ተቋማቸው ላይ ሲያደርሱ መመልከት የተለመደ ነገር ሁኗል። ዘረኝነትንና ሙስናን ይዋጉልናል ያልናቸው ሰዎች ለችግሩ መፋጠን ዋነኛ አካል ሁነዋል። ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር በተሰጠችው መመርያ ተጠቅማ ለአለም ሰላም የማደል ፀጋ ቢኖራትም ዳሩ ግን እነዚያ ጥቅመኞች ፀጋዋን ለዓለም እንዳታድል አዚም ሁነውባታል።
ለዚህም ችግር መንስኤ እኛው የእምነቱ ተከታዮች ነን። ለምን ቢባል በተለያየ ዘርፍ ላይ ለሚገኙ የእምነት ተቋም አስተዳዳሪዎች ፊት በሙስና፣ በስርቆትና በብልሹ አስተዳደር ስለበለጸጉ ሰዎች እናወራለን፣ እንተርክላቸዋለን። በእነዚህ ነውረኛ ሰዎች ላይም ምንም አይነት የእምነት ሃላፊነታችንንና ግዴታችንን መወጣት ባለመቻላችን ሌሎች እንደማበረታቻ ቆጥረውታል። በእነዚህ እና መሰል ምክንያቶች ችግሮች እንዲበባሱ የእኛ አስተዋጾ ቀላል እንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል።
  • ወደ ባዕድ ሀገር በስደት የሚጎርፈው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ሀገር ቤት ሰው የማይኖር እስኪመስል ድረስ ፍላጎቱና ፍልሰቱ ከፍተኛ ሁኗል። ለዚህ ችግር በዋናነት የመንግሥት አስተዳደራዊ ድክመት ቢሆንም እኛም የበኩላችንን ድርሻ ባለመወጣታችን የመጣ ትልቅ ችግር ነው። በስደት የሚኖሩ ወገኖች የስደትን አስከፊነት እያወቁ ነገር ግን በሀገር ቤት ለሚኖሩ ወገኖቻቸው ችግሩን በሚገባ አለማስረዳት፣ ወደ ሀገር ቤት በሚሄዱበት ጊዜም የተለየ ለብሰውና መስለው መታየታቸው እና የሚሰሩትን የሥራ አይነት እንኳ በትክክል አድካሚነቱንና አሰልችነቱን አለመናገር ለሌሎች ከሀገር መውጣት ምክንያት ሁኗቸዋል። ስለዚህ የሆነውንና የሚሆነውን በትክክል መረጃ መስጠት ብንችል ወገኖቻችን በይሆናልና በማይሆን ተስፋ ከሀገር ወጥተው የስደትን አስከፊ ህይወት ተጠቂ ባልሆኑ ነበር። ስደት ምንልባት በኢኮኖሚ የተሻለ ነገር ሊኖረን ይችል ይሆናል እንጂ የሰላም ኑሮ ግን መኖር የሚቻለው ተወልደው በአደጉበት ሀገር ነው። በስደት ህይወት የባህል፣ የእምነት፣ የአለማዊነትና የቋንቋ ተፅዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ የተረጋጋና ሰላማዊ ህይወት መምራት በጣም አስቸጋሪና ከባድ ነው። በዚህም የተነሳ በጭንቀትና በውጥረት የሚኖሩ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ስለዚህ ሰውን ወደ ስደት ህይወት መጋበዝ በጭንቀትና በሃሳብ እንዲኖር መፍረድ   የሚል  ድምዳሜ  ቢሰጥ  ያንሳል  እንጂ ማጋነን አይሆንም።
በአጠቃላይ እኛ ሁላችንም ብንችል የችግር መፍትሔዎች እንድንሆን ባንችል ደግሞ የችግር መንስኤዎች እንዳንሆን የራሳችንን በጎ አስትዋጾ ማድረግ ይኖርብናል። ለችግር መፍትሔ ይሆናሉ ያልካቸውን 2 ላንሳና ሌላውን እናንተ ቀጥሉበት።
  1. ችግሩን በትክክል መረዳት፦ ችግሩን ከስር መሰረቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ በአጠቃላይ ሀገራዊ ጉዳቱን መረዳትና ችግሩ እንዳይበባስ የራሳችንን አስተዋጾ ለማድረግ ችግሩን በትክክል መረዳት ይጠበቅብናል። ሙህራን “ችግሩን ማዎቅ የመፍትሔ 50% ነው” እንዲሉ ችግሩን በትክክልና በጥልቀት መረዳት ካልቻልን መፍትሔ በቀላሉ ለማግኘት አስቸጋሪ ስለሚሆን የችግሩን የት፣ መቼ፣ እንዴትና ወዴት የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት ችግሩን ከመሰረቱ ማዎቅ ከሁላችን የሚጠበቅ ተግባር ነው።
  2. ችግሩን ለማሶገድ በቆራጥነት መነሳት፦ ችግሩን በትክክል ከተረዳን መፍትሔ ለማምጣት ደግሞ በቆራጠነት መነሳት ይኖርብናል። ፍራትን፣ ቸልተኝነትን፣ አይሆንም ባይነትን፣ አድርባይነትን፣ ጥቅመኝነትንና ዘረኝነትን ከውስጣችን አሶጥተን ለሀገርና ለተተኪ ትውልድ በሁሉም በኩል የበለጸገች ሀገር ለማስረከብ ቆራጥነትና ሰማትዕነት ያስፈልጋል። የማንም ርዳታ ሳያሻን በራሳችን ተነሳሽነት ሀገራዊ ሃላፊነታችንን ለመወጣት እና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ሁላችንም ቆርጠን መነሳት ይኖርብናል።.........................+++