Monday, November 19, 2012

ጾመ ነብያት/ጾመ ድኅነት/የገና ጾም


ይህ ጾም ከ7ቱ የቤተክርስትያናችን የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ ነው። ይህን ጾም በዋናነት ነብያት  የጌታችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መውረድ፣ መወለድ በትንቢት መነጸር እየተመለከቱ የጾሙት ታላቅ ጾም ስለሆነ ጾመ ነብያት ተባለ። ጾመ ድኅነት መባሉም መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ/የአዳም እዳ በደል/ ጠፍቶ ድኅነት ስለተገኘበት ነው። እንዲሁም ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም አምላክን በመሀጸኔ ተሸክሜ ልጾም ልጸልይ ይገባኛል ብላ ለ40ቀን እስከ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ድረስ የጾመችው ጾም ገና ጾም ተባለ። ስለዚህም ይህ ጾም ስለጌታችን መውረድ፣ የአምላክ ሰው መሆንን/መወለዱን/ የምንረዳበት ጾም ነው። ጾሙም ከህዳር 15 እስከ ጌታችን ልደት ድረስ እንዲጾም ቅድስት ቤተክርስትያናችን በስርዓት ደንግጋ አስቀምጣልናለች።

ለምን ጾሙን ከህዳር 15 ቀን ጀመርን?

ስንክሣር ዘህዳር፤ “ አመ ዐስሩ ወሃምስቱ ለሓዳር በዛቲ ዕለት ጥንተ ጾሙ ስብከተ ጌና ልደቱ ለእግዚእነ ዘሠሩ ክርስትያን ያዕቆባውያን ዘግብፅ ሳህሉ ወምህረቱ የሃሉ ምስሌነ ለዓለም” ህዳር 15 ቀን  የግብፅ ክርስትያን ያዕቆባውያን እንደሰሩት ይህ ዕለት የልደት ጾም መጀመሪያ ነው ማለት ነው። ደግሞም
ፍትሐ ነገስት አንቀጽ  13 ገጽ 218 እና 219፡ ”ወውቱ ጾመ ዘይቀድም እምልደት ወጥንተ ዚአሁ መንፈቀ ህዳር”  የልደት ጾም የሚጀምረው ከህዳር 15 ነው ማለት ነው።

ጾሙ ለምን ከ40 ቀን በለጠ?

አንደኛ፦ ሐዋርያው ፊልጶስ ህዳር 16 ቀን በሰማዕትነት አሳርፈውት ሊያቃጥሉት ሲሉ መልአከ እግዚአብሔር ሰወረው። ደቀመዛሙርቶቹ/ ተማሪዎቹ/ ከዕለቱ ጀምረው ሶስት ቀን እንደጾሙ በ18 ሰጣቸውና ቀበሩት ስለዚ 3 ቀን ጾመ ፊልጶስ ተብሎ ተጨመረ ማለትም ህዳር 16፣17 እና 18።
 ሁለተኛው፦ ህዳር 15 ደግሞ ልደት ሁልጊዜ ረዕቡና አርብ ባይውልም አበው ስርዓት ከሰሩ አይልዋወጥምና አንድም ደግሞ አንዴ ሲጾም አንዴ ሲበላ እንዳይረሳ  ብለው ሁልጊዜም ጾሙ ከህዳር 15 እንዲጀመር አድርገው አፀኑት። ስለዚህ  አንድ ቀን በጾሙ ጨምረው ጥንታውያን ክርስትያኖች በዕግብፅ ከህዳር 15 ቀን ጀምረው ጾሙት። ለእኛም አርዕያ ሆኑ ስርዓትም ሆኖ ተሰራልን።

       ልደት

የጌታችን የመድኅኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ታህሳስ 29 ቀን ነው። አባቶች በሰሩልን ስርዓት መሰረት ከ4 ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ዮሐንስ ታህሳስ 28 ቀን ይከበራል። ይህም የሆነበት ዋናው ምክንያት  ልደት የሚውለው ሁልጊዜም  “ዕለተ ምርያ” በዋለችበት ቀን ነው። ዕለተምርያ የምትውለው ምንጊዜም ጳጉሜ 5 ቀን ነው። ጳጉሜ 5 ቀን ሰኞ ቢውል ልደትም መዋል ያለበት ሰኞ ቀን ነው። ይህን በዘመነ ዮሐንስ ስንቆጥረው ዕለተምርያ በዋለችበት የሚውለው ታህሳስ 29 ቀን ሳይሆን ታህሳስ 28 ቀን ስለሚሆን ልደት በዚያ ተወሰነ። ዕለተምርያ ማለት የመድሀኒት ዕለት ማለት እንደሆነ ነብያት ተናግረዋል። በዚህም ዕለት በዋለችበት የዓለም መድሀኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ይወርዳል ይወለዳል እያሉ ትንቢት ስለተናገሩ ነው።  

ጾሙን በሰላም፣ በፍቅር፣ በአንድነት፣ በመተሳሰብ እንድንጾምና ከጾሙ ረድኤት በረከት እንድናገኝ የእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ይሁንልን፤ የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡አሜን።

 

No comments:

Post a Comment