Wednesday, July 9, 2014

አንድነት በአዲስ ስልት

በየመን ታሪክ በማይረሳ ህገወጥ ድጋፍና ትብብር የግንቦት 7 የፍትህ፣ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ጽሐፊ የሆኑትንና የብርታኒያ ዜግነት ያላቸውን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ለወያኔ ለሞትና ለስቃይ አሳልፎ መስጠት የሰሞኑ አነጋጋሪና ስሜት ቀስቃሽ ዜና ሁኗል።  ይህ ክስተት ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ለነጻነትና ለፍትህ የሚታገሉ ሁሉ ድርጊቱን በመተቸት ላይ ናቸው፤ በተለያየ መልኩ የድርጊቱን አስከፊነትና ለአቶ አንዳርጋቸው ያላቸውን ድጋፍ በመግለጽ ላይ ይገኛሉ። ብርታኒያም ዜጋዋን ከወያኔ እጅ ለማስለቀቅ የምትወስደው እርምጃ በጉጉት እየተጠበቀ ነው። በተለይ በንቅናቄው አባላት ከፍተኛ ቁጣን አስነስቷል። ይህ ቁጣም በድርጊት እንደሚገለጽ ንቅናቄው በመግለጫ አሳውቋል። መግለጫውን ከዚህ መመልከት ይቻላል!

ወያኔዎች/ሕወሓቶች የሥልጣን ጊዜን ለማራዘም የማይቆፍሩት ጉድጓድ፣ የማይፈነቅሉት ድንጋይ፣ የማይከተሉት ስልት፣ የማይወዳጀጁት ኃይል እንደማይኖር ለሁላችንም የማይሰወር ገሃዳዊ እውነታ ነው።  በተለይ ደግሞ ለሥልጣናቸው ስጋትና ጭንቀት የሚፈጥሩትን ድርጅቶች በአሸባሪነት እስከመክሰስ እና አባላሎቻቸውንም በስቃይና በመከራ ወደ እስር ቤት መወርወር የዘወትር ተግባራቸው ነው። ይህንንም ተግባራቸው ዛሬም በአቶ አንዳርጋቸው ላይ በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፤ ነግም ማነህ ባለ ባለሳምንት/ተራ ማለታቸው አይቀርም።
ስለዚህ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት እያንዳንዳችን ከዚህ አስከፊ ሥርዓት ለመላቀቅ እና ፍትህ፣ ነጻነትና ዲሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለማየት አዲስ ስልት በወኔና በቁርጠኝነት ለመከተል መንደፍ ይኖርብናል። ይህ ካልሆነ ግን ወያኔ 23 ዓመት ኢትዮጵያውያንን እንደፈለገ ከፋፍሏል፣ አሰቃይቷል፣ ድርጅቶችን ዘግቷል፣ ተቋማትን አዳክሟል እኛንም ግዝቶናል ነግም ይቀጥላል።
የግንቦት 7 ንቅናቄ ፦
  1. ምንም እንኳ ንቅናቄው ታላቅ መሪ ቢያጣም በመግለጫው ተግባራዊ የመጀመርያ እርከን የትግል ጥሪ በተግባር ላይ እንዲውል ከማስተባበር በተጨማሪ በመረጋጋትና በማስተዋል ዘላቂ ስልቶችን መንደፍ(የአጭርና የረጅም)፣ የትግል ስልትና የመዋቅር አደረጃጀትም በተወሰነ ደረጃ መቀየር፣ 
  2. አባላት በግልጽ ባይታወቁም ከአንዳርጋቸው መያዝ ጋር ተያይዞ  በሚያደርጉት የስሜት መለዋወጥ እንዳይጋለጡ በጥበብና በጥንቃቄ እንዲጓዙ ማሳሰብ(በተለይ ኢትዮጵያ ለሚገኙ አባላት)፣
  3. ብርታኒያ የድፕሎማሲውን ሥራ እና የአቶ አንዳርጋቸውን ደህንነት ሁኔታ እንዲከታተሉ በጥብቅ ከመረጃ ጋር(የወያኔን የእስር ቤት ድብደባ፣እንግልትና ስቃይ በጥልቀት እንዲገነዘቡት) ግፊት ማድረግ፣
  4. ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር በስፋትና በጥልቀት የጎረቤት አገሮችን ሁኔታ ማጤን እና ወዘተ...
ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች፦
  1. የቱንም ያክል የሀሳብ ልዩነት ቢኖርም በመርህ ደረጃ ኢትዮጵያን ነጻ ማውጣትና ህዝቧ ነጻነትና ፍትህ እንዲያገኝ እስከሆነ ድረስ ድርጅቶች ሁሉ በመጀመርያ ህብረት ፈጥሮ ወያኔን ማስወገድ የሚቻልበትን ተግባራዊ አንድነት መፍጠር፣
  2. የብሔር ፖለቲካ እኛም አለን ከማለት ውጭ እንደ ኢትዮጵያ ታላቅ ታሪክ ያላት አገር በቀላሉ ብሔርን ገንጥሎ መሔድና መታገል ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችሉ ማሰብና አገራዊ ስሜትን መላበስ፣ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” የሚለውን ብሂል በተግባር ማዋል በእጅጉ ውጤታማ ያደርጋል፣
  3. የድፕሎማሲው ስራ በተጨማሪ ከሁሉም የሚጠበቅ ነው፣
ከሁሉም ኢትዮጵያዊ፦
  1. የራስን መብት በራስ ማስከበር በሚል መርህ ቃል ሁላችንም መብታችንን ለማስከበር ቆርጦ መነሳት። ለመብታችን  እስራትን፣ እንግልትን፣ ድብደባን በጸጋ መቀበልና አገራዊ ስሜት ተላብሰን እንደ አባቶቻችን ድልን ለመቀናጀት የበኩላችንን ድርሻ መወጣት! በሌላ አነጋገር ሁላችንም አንዳርጋቸው ጽጌን፣ አንዷለም አራጌን፣ እስክንድር ነጋን፣ እርዮት ዓለሙንና ሌሎችን ሁነን መነሳት።
  2. አገራዊ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግና የሥራ ማቆም አድሚያ ማድረግ! ለመብት፣ ለነጻነት፣ለፍትህ ሲባል መደረግ የሚገባቸውን ነገሮች ሁሉ ማድረግና የኢትዮጵያን ታሪክ መመለስ። 
በአጠቃላይ ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ የተከሰተው ድርጊት የወያኔን ውርደትና ውድቀት የሚያፋጥን እና  የኢትዮጵያን ነጻነትና ፍትህ የሚያጎናጽፍ ሊሆን እንደሚችል አመላካች ነው የሚል እምነት በብዙዎች ላይ አሳድሯል። ስለዚህ ሁሉም ለኢትዮጵያ ነጻነት የቀመና ፍትህ ፈላጊ ሁሉ ይህን በአቶ አንዳርጋቸው ላይ የተከሰተውን ድርጊት እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ አንድነትና ህብረት በመመስረት ለለውጥ በአዲስ ስልት፣ በአዲስ መንፈስ፣ በአዲስ ትግል መጓዝና መራመድ ይኖርብናል። ይህ ከሆነ ከአለምንም ቅድመ ሁኔታ ነጻነትና ፍትህ እንጎናጸፋለን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!

ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች!

No comments:

Post a Comment