Tuesday, April 1, 2014

ስደት (ክፍል ፪)


ስደትን በተመለከተ በክፍል ፩( በጻፍኩት ጽሁፍ ላይ ትልቁን ለሰው ልጅ የአእምሮ ረፍትና የወደፊት ተስፋ የሚሆነውን ነጻነት መነፈግ ለኢትዮጵያ ህዝም ብሎም ለዓለም ህብረተሰብ አስቸጋሪ በመሆኑ ለስደት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ገልጨ ነበር። ጠቅለል ባለመልኩ እኛ ኢትዮጵያውያን የመተሳሰብ፣ አብሮ የመብላት፣ በነጻነት የመስራትና የመንቀሳቀስ፣ መሰረታዊ የሰው ልጅ የእዉቀት ደረጃዎችን ማለትም የመጻፍና የመናገር፣ እንዲሁም መንግሥት እራሱ በእራሱ ህገ መንግሥት ነው ብሎ ባረቀቀው "መንግሥት በሀይማኖት ጣልቃ አይገባም ሃይማኖትም እንዲሁ/The state shall not interfere in religious masters and religion shall not interfere in state affairs"(አንቀጽ 113) ያለውን የእራሱን ህግ ሳይቀር በመጣስ የማምለክ ነጻነታችንን በበሬ ወለድ ምክንያት ሲገፍ እና አንድነታችንን፣ ባህላችንንና ለነገ የሚያስበውን ትውልድ ሲያስር፣ ሲያንገላታና ለስደት ሲዳርግ ብሎም ሲገድል ድፍን 23 ዓመት አስቆጠረ።

ይህ የስቃይና የመከራ ዘመን የሚያበቃበትን ቀን እና ስዓት የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያመልከውን አምላክ በመማጸን ላይ ነው። በተቃራኒው የህወሓት አገዛዝ ዘላለማዊ ነኝ ማለቱን ተያይዞታል። ታግሎ ነጻነቱን እንዳያስከብር ከጫካ ጀምሮ የሰራበትን የሥልጣን እድሜ ማራዘሚያ የብሔር ተኮር የዘር የእርስ በእርስ ግጭትና የሀይማኖት ተቋማትን የማፍረስ ፖለቲካ በህዝቡ ላይ በማሰራጨቱ ለነጻነት በህብረት በአንድነት እንዳንታገል አድርጎናል። እርስ በእርሳችን እንዳንተማመን አድርጎናል፤ ከፋፍሎናል። ህብረት አንድነት እንዳይኖረን በማድረግ ለስደት ዳርጎናል።

ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንዳትኖር እና ካርታ እንዳይኖራት አድርጓታል። መለያ ምልክቷን ሰንደቅ ዓላማዋን ቀይሮባታል። በቅኝ ግዛት ያልተንበረከኩ ህዝቦቿን መከራ እና ስቃይ በማብዛት በግድ ለባርነት/ለስደት ዳርጓቸዋል። ሰላም የጠፋበት፣ ተስፋ የሌለው፣ ለማንነቱ የማይጨነቅ፣ ለአገር ለወገኑ የማያስብ ትውልድ መናኽርያ እንድትሆን አድርጓል። በራብ አለንጋ ሳይቀር ሰፊውን ህዝብ እየቀጣ ነው። ከራብ ጦር ይሻላል እንዲሉ ከራብ፣ ከጭቆና ነጻነት ከማጣት ስደትን መረጠ፣ በየአገሩ ስደተኛ ተብለው እንድንኖር አደረገን። አይ ህወሓት የስራችሁን ይስጣችሁ ሌላ ምን ይባላል.....የባለ ዕራዩን (የአምላካችሁን) መለስ ተብዬው እጣ ፈንታ ይስጣችሁ እንዳንል እርግማን ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ የዋህ እና በፈጣሪው የሚያምን ነው እርግማን ፈጽሞ ይጠላል፤ ድህነታችሁን እንጂ ሞታችሁን አንሻም። ስቃዩን፣ መከራውን፣ እስራቱን አቅሉልን እንጂ ጣን ልቀቁ የማይል ህዝብ ነው። እንዳለመታደል ሁኖ እንጂ እንዴት ለዚህ ህዝብ ነጻነቱን ይገፈፋል፣ ማንነቱንና ታሪኩን እንዲያጣ ይደረጋል።

ለአገር እድገትና ብልጽግና ዋነኛ መሰረት ሙያዊ ነጻነት(academic freedom) መሆኑን የዘርፉ ሙህራን ይስማሙበታል። የሰው ልጅ በተፈጥራዊም ሆነ በግላዊ ጥረት እራሱን፣ ቤተሰቡን ከዚያም አልፎ አገርን መለወጥ መቀየር የሚያስችል እውቀት/ሙያ አለው። ሙያዊ ነጻነት ከደሞዝ፣ ከክፍያና ከማንኛውም ጥቅማ ጥቅም በላይ ነው፣ ከሹመትና ሽልማት በላይ ነው። ሁሉም ማለት ይቻላል ሙያዊ እውቀት ለማግኘት ወደ / ዓለም ሲገባ የሚያስደስተውን እና ቢሰራበት የበለጠ ውጤት ማምጣት ወደሚችልበት የት/ መስክ ይገባል። ለዚህ ትውልድ ያገኘውን እውቀት ካለንም ተጽዕኖ መስራት የሚችልበትን መልካም ከባቢያዊ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እና ማስተካከል የነበረበት ዲሞክራሲያዊ እና ልማታዊ ነኝ የሚለው መንግሥት ነኝ ባዩ ፈላጭ ቆራጩ የህወሓት ቡድን ነበር። በተቃራኒው ግን እየሰራ ያለው ገና በለጋ እድሜያቸው ሳይቀር ተማሪዎችን የእርሱ ተከታዮች እንዲሆኑና የብሔር ፖለቲካን ሲዘራባቸው ይታያል። ወደከፍተኛ / ሲገቡም ሲወጡም ለጊዜው ለመኖር ዋስትና (green card) የሆነችውን ቁራጭ ወረቀት (የአባልነት መታወቂያ መሆኗ ነው) ይዘው እንዲወጡና የስራ ዕድል እጣ ፈንታ በዚያ እንደሚወሰን አጠንክሮ መልእክቱን ያስተላልፋል። ለማሳያም ያክል በየከፍተኛ / ተቋማት ውስጥ የመንግሥት ተልኮን የሚያራምዱትን አድር ባዮች ካለሙያቸው፣ ካለ እውቀታቸውና ካለችሎታቸው ከፌደራል እስከ ቀበሌ የየመስርያ ቤቱ ኃላፊዎች እያደረገ ይሾማል። የተለየ ጥቅማጥቅም ይሰጣቸዋል። በሙስና የተጨማለቁ እንዲሆኑ እና በፍራቻ የስርዓቱ ሎሌዎች አድርጓቸዋል።

ይህን እና መሰል ሁኔታወችን በማየት ሁሉም በሚያስብል መልኩ የከፍተኛ / ተቋማት ተማሪዎች ከልባቸውም ባይሆን የገዥው ፓርቲ ደጋፊ እና ተላላኪ እንዲሆኑ ተደርገዋል። ከዛም አልፎ በስራ ላይ ሰራተኛውን ስራውን በአግባቡ እንዳይሰራ ጀርባው እና የሚያደረገውን እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ለማጥናት የስለላ ስራ እንዲሰሩ ይደረጋል። አንድ ለአምስት(15) በሚል ሚስጥራዊ የህወሓት ቡድን ሁሉም እንዲካተቱ እና የፓርቲው አገልጋዮች ተደርገዋል። የቀሩትም ከእጅ ወዳፍ ለማግኘት ሲሉ ወደው ሳይሆን ተገደው በቡድኑ ውስጥ ተካተዋል። በዚህ ቡድን እና ተመሳሳይ እኩይ ተግባር አንተባበርም ያሉት ኢትዮጵያውያን እና እድገቷን የሚሹ እውነተኛ ልጆች ስቃይና መከራ ሲበዛባቸው እና ከእስርና ከሞት የተረፉት ለስደት ተዳርገዋል።

በዚሁ ከቀጠለ አገራዊ ስሜት እና እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ይገኛል ብሎ ማሰብ እጅግ ከባድ ይመስለኛል። ምክንያቱም ለእኛ አገራችንን ከእነ ሙሉ ክብሯ እና ከእነ ታሪኳ ያስረከቡን የደም መሰዋትዕነት ከፍለው ነው። 40ዎች ዓመታት በፊት የነበሩት መንግስታት ምንም እንኳ የራሳቸው ችግር ቢኖርባቸውም ለአገር አንድነትና እድገት፣ ለሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጾ አድርገዋል። እንደ ህወሓት ፓርቲ አገሪቱን አልሸጡም፣ ይልቁንም ለክብሯና ለታሪኳ ይጨነቁ ነበር እንጂ። ህዝቦቻንም እንዲህ በይፋ ለስደት አልዳረጉም። አገርን የሚወድ ትውልድ እንጂ አገርን የሚክድና የሚሸጥ፣ ታሪክን የሚያጠፋ፣ አንድነትን የሚለያይ፣ ባህልን እና ሀይማኖትን የሚንቅ ትውልድ አላፈሩም። ው ነገር ግን መንግሥት ነኝ ባዩ ወያኔ/ኢህአዲግ የቀደሙ ነገሥታትን ሲተችና ታሪካቸውን ሲያጠፋ በይፋ ይታያል።

ወያኔ/ኢህአዲግ ግን ሙያዊ ነጻነት እንኳ ሳይቀር ተነፍገን ተመራማሪዎች እንዳይመራመሩ፣ ደራስያን እንዳይደርሱ፣ ተዋንያን እንዳይተውኑ፣ ጋዜጠኞች እንዳይዘግቡ፣ ነጋዴዎች እንዳይነግዱ(ከእርሱ አባላት በስተቀር) መምህራን እንዳያስተምሩ፣ እና ሁሉም በየሙያ ዘርፉ በነጻነት ሰርተው እንዳይበሉ አደረገ። ከእርሱ ዓላማ እና ተልእኮ ውጭ ማንም ምንም እንዳያደርግ የሞት፣ የእስር፣ የአክራሪነትና አሸባሪነት ህግ አጸደቀ። እስራትና ሞት ፈርተን ብዙዎች ተሰደድን ከስደት እንዳንመለስም ህይወት ናትና ፈራን።

ትናት ስደተኛ፣ ዛሬም ስደተኛ፣ ነገስ??? ነገ ምን አልባት ሙሴ ህዝበ እስራኤልን ከፈርኦን የመከራና የጭንቀት አገዛዝ ነጻ እንዳወጣቸው ሁሉ ኢትዮጵያውያንንም ነጻ የሚያወጣ ታምራዊ ኃይል ሊፈጠር እንደሚችል ባለሙሉ ተስፋዎች ነን። ህዝብ ታምራዊ የለውጥ ኃይል መሆን ይችላል። እያንዳንዱ ዜጋ ለመብቱ፣ ለነጻነቱ ከታገለ ታምራዊ ኃይል ሁኖ ይህን ጨቁኖ የሚገዛን መንግሥት በቀናት ውስጥ ማስወገድ ይችላል።

የኢትዮጵያ አምላክ ሆይ ከስደት የሚታደገንን ሙሴን ላክልን!

እውነተኛ ፍርድ የሚሰጠውን ዳዊትን ላክልን!

በጥበብና በማስተዋል የሚመራውን ሰሎሞንን ላክልን!

No comments:

Post a Comment