Friday, April 11, 2014

ስደት (ክፍል ፫)


ስደትን በተመለከተ በክፍል (Part 1)እና ፪(Part 2) በጻፍኳቸው መጣጥፎች ላይ ለስደት ያበቁንና ዛሬም ብዙ ኢትዮጵያውያንን ከአገራቸው እንዲሰደዱ እያደረጉ ያሉትን ጉዳዮች ጠቅለል አድርጌ ለማቅረብ ሞክሪያለሁ  የስደትን አስከፊነትም በመጠኑም ቢሆን ሳልጠቅስ አላለፍኩም። ዛሬም እኛ ኢትዮጵያዊያንን  ከስደት ሊታደገን የሚችል ሰማያዊ ኃል ካልመጣ በስተቀር የምንወዳትን አገራችንን ጥለን ወደ ባዕድ አገር መፍለሱን ተያይዘነዋል። ዓለምም ዋነኛ የዜና ክፍል አድርጎ ሲነግረን እንሰማለን።
ስደት ዘርፈ ብዙ ነው፤ አይነቱም መገለጫውም የተለያየ ነው። መንገዱም እንዲሁ አድካሚ፣ ውስብስብ፣ እልህ አስጨራሽና ለምን ወደዚህ ዓለም አመጣኸኝ እያሉ ከፈጣሪ ጋር ክርክር የሚያስነሳ ነው። ስደትን ሁሉንም በአንድ ላይ ጠቅልሎ  መግለጽ እጅግ ከባድና አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ስደት በተለያየ መልኩ ሊገለጽ ይችላልና፤ የአካል ስደተኛ፣ የመንፈስ ስደተኛ፣ የአዕምሮ  ስደተኛ  በማለት መዘርዘር ይቻላል። በዋናነት ግን  የፖለቲካ  ስደተኛ(political migrant) እና የኢኮኖሚ ስደተኛ(Economic migrant) ብሎ ከአገራችን ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁናቴ ማየት ይቻላል።
የፖለቲካ ስደተኛ ማለት በአጭሩ አንድ ሰው በፖለቲካ እንቅስቃሴ ምክንያት በመደገፍም ሆነ በመቃዎሙ በአገሩ መኖር ባለመቻሉ ህይወቱን እና እራሱን ነጻ አድርጎ መኖር ይቻላል ብሎ ወደሚያስበው አገር መሰደድ ማለት ነው። አንድ ሰው ከወንጀል በስተቀር የሚፈልገውን ነገር በነጻነት ማከናወን እና በነጻነት መኖር ካልቻለ ግዴታ ወደማይፈልገው የስደት ሕይወት ይገባል። በተለይ በማደግ ላይ የአሉ አገሮች የዚህ ችግር ሰለባዎች ናቸው። በአገራችንም የምናየው ዋነኛ ችግር ይህ ነው።
ሕወሓት በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ በነጻነት መናገር፣ በነጻነት መጻፍ፣ በነጻነት መወያየት፣ በነጻነት መቃወም፣ በነጻነት መደገፍ፣ በነጻነት መስራት፣ በነጻነት መማር፣ በነጻነት መደራጀትና በነጻነት ማምለክ ፈጽሞ የማይሞከሩ ነገሮች ናቸው። በሌላ አነጋገር ሕወሓት እና ነጻነት አይተዋወቁም። ዲሞክራሴ ማለት ለወያኔ/ኢህአዴግ ህዝብን ካለምክንያት ማሰር፣መግደል፣ ማሰቃየት ማለት ነው። ነጻነት ለእነሱ እነሱን መደገፍ፣ ከእነርሱ ጋር አብሮ በሙስና መጨማለቅ ነው።መጻፍናመናገር ነጻነት ለእነርሱ ለፓርቲያቸው ውዳሴ ማቅረብ ነው ልማት ለእነርሱ በተግባር ሳይሆን በቃል ብቻ 11% ማደግ አገርን መሸጥ እና ሰባዊ መብትን ከመገንባት ይልቅ ህንጻና መንገድ መገንባት ማለት ነው። ማምለክ ለእነርሱወያኔ ወይም/እናባለዕራዩ መለስ ማምለክና መስገድ ብቻ ነው። ይህ ብቻ ነው ለሕወሓት ዲሞክራሲ፣ ነጻነትና ልማት። ይህ ነው ለእነርሱ ብልጽግና እድገት።
በኢህአዴግ/ወያኔ የአገዛዝ በደል እና የዘር ፖለቲካ ባመጣው መዘዝ ለአገር እድገት መልካም የሚያስብ ሰው በቀላሉ መኖር አልቻለም። እንዲኖርም አይፈቀድለትም። ብዙ ሰዎች ሥርዓቱን በመቃወም፣ አስተዳደራዊ ለውጥ፣ የፖሊሲ ለውጥ ያስፈልጋል ብለው የሚታገሉ ብዙ ሰዎች አፋቸውን እንዲዘጉ ተደረጉ፣ ታሰሩ፣ ተገደሉ የቀሩትም ከአገር እንዲወጡ ተደረገ። ሚዲያዎች፣ድረ ገጾች፣ የግል ኮምፒወተሮችና የስልክ መስመሮች ሳይቀሩ ሲዘጉና ተጠልፈው በእነርሱ ቁጥጥር ስር እንዲሆኑ አድርገዋል በዚህም ምክንያት ሰው እራሱን እንኳ መጠራጠር ጀምሯል።
እንዲሁም የምጣኔ ሃብት ስደተኛ (economic migrant's) ማለት ደግሞ በምጣኔ ሃብት እጦት ምክንያት ይበላውና ይጠጣው ያጣ ከእጅ ወደአፍ ለማግኘት ከቦታ ወደቦታ የሚያደርገው ፍልሰት ነው። እንደአገራችን ተጫባጭ ሁኔታ ስንመለከት ብዛት ያላቸው ወጣቶች ወደ ተለያዩ  የዓለም ክፍላት ሲጓዙ እንመለከታለን። ብዙዎችም በርሀ ለበርሀ ከአሰቡበት ሳይደርሱ በመንገድ ቀርተዋል፤ በአረብያውያን ቅኝ ግዛት ወድቀው የስቃይና የመከራ ድምጽ በማሰማት ላይ ያሉትን መጥቀስ ከበቂ በላይ ነው። 
እዚህ ላይ ግን የኢትዮጵያን የድህነት ሁኔታ ሳይሆን ማንሳት የፈለኩት መንግስት ነኝ ባዩ አገራችን  ኢትዮጵያ ስመዘገበች ንን ፈጣን እድገት(11%)  እና ዛሬ ላይ ያለውን የኑሮ ውድነት እንዲሁም ወጣቱ ትውልድ በሥራ አጥነት ሳቢያ ያደርገውን ስደት በቀላሉ ማነጻጸር እንድንችል ነው። በእውነት እድገት፣ ልማት የሚጠላ ሰባዊ ፍጡር የለም። ማንም ሰው ማደግመለወጥ የተሻለ ኑሮ መኖር በእጅጉ ይፈልጋል ይሻልም ውጥ እድገት መፈለግ ተፈጥሮአዊ ባህርይ ነው።
ታዲያ አገራችን ኢት ከአደገች፣ ፈጣን እድገት ካስመዘገበች፣ ለውጥና ነጻነት ካለ በየትኛው መመዘኛ ነው ህዝቦቿ ስደትን የመረጡት??? በምን ምጣኔ ሃብታዊ ቀመር ነው ህዝቦቿ በርሀብ አለንጋ የሚሰቃዩት? የዘርፉ ሙህራን እንደሚናገሩት የአንድ አገር እድገት የሚለካው ህንጻ በመገንባት ሳይሆን የህብረተሰቡ የእለት ከእለት ኑሮ መለወጥና ሰባዊ መብቶች ሲከበሩና ሲጠበቁ ነው። ሰባዊ መብቶች እየተገፈፉ፣ ርሀብና የኑሮ ውድነት ተባብሶ ልማት፣ ፈጣን እድገት፣ ብልጽግና የለም። እርግጥ ነው ሕወሓትና ደጋፊዎቹ የአገሪቱን ንብረት በመሰብሰብ ይህ ነው የማይባል ሀብት አካብተዋል፤ ነጻነቱንም ለግላቸው አድርገዋል።
በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ ምክንያት የኢትዮጵያ ህዝብ ስደትን እንዲመርጥ የተገደደው በሕወሓት አሳፋሪና አስነዋሪ የአስተዳደር ሥርዓት ነው። አስተዳደሩም ሆነ  ልማቱ ህዝብ ተጠቃሚ በሚሆን መልኩ ማስኬድና ለውጥ ማምጣት በእጅጉ ይቻላል። ነገር ግን ቅን ልቦና የለም፤ የህብረተሰቡን መለወጥም አይፈለጉም። ምክንያቱም ድርጅቱ ራስ ወዳድ እንጂ አገራዊ ስሜት የለውም። አገሪቱን እርሱ እና መሰሎቹ እንደፈለጉ አድርገው እየተጠቀሙባት ነው የተረፈውን ደግሞ ለውጭ ባለሀብት በዶላር ቆራርሰው እየሸጧት ነው (Land grabbing )። ዜጋው ግን በብሔር፣ በተቃማሚ ፖለቲካ ስም ስቃይና መከራን በማብዛት ከቦታው እንዲፈናቀል ይደረጋል ተደርጓልም። ፖለቲካዊ ነጻነት እና እንደ ዜጋ የአገሩን ሃብትና ንብረት በነጻነት መጠቀም የሚባል ነገር ፈጽሞ ባለመኖሩ ትውልዱ ስደትን መረጠ።

በአጠቃላይ እኛው እራሳችን ነጻነታችን ማወጅ ይኖርብናል እንጂ ሌላ ታምራዊ ኃይል ሊመጣና ከስደት ሊታደገን ከቶ አይችልም። እርግጥ ነው ፈጣሪ የህዝቡን ዋይታና እሮሮ ሰምቶ ለነጻነት ምክንያት የሚሆን ሰው ሊያስነሳ ይችላል። ነገር ግን እኛ ዝም ብለን የፈጣሪን ሥራ መጠበቅ ግን በእራሳችን ላይ የመከራ ጊዜን እንደማራዘም ይቆጠራል። ፈጣሪ የራሱን ሥራ  በራሱ ጊዜ ይሰራል። እኛም የራሳችንን ሥራ መስራት ይጠበቅብናል። ነጻነታችንን ማስጠበቅ፣ አገራችንን መታደግ፣ለወገናችን መድረስ ሰባዊ መብታችን ነው። ስለዚህ ሰባዊ መብታችንን ተጠቅመን ይህን ፈላጭ ቆራጭ መንግስት ነኝ ባይ የዘር ፖለቲካ አራማጅ ሕወሓትን በቃህ፣ ስደት ይብቃ ልንለው ይገባል።

No comments:

Post a Comment