Wednesday, November 20, 2013

ቅዱስ ሚካኤል

                        (በመልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው)

 ፩፦ ድርሳን ዘቅዱስ ሚካኤል
 ቅዱስ ማለት ልዩ፥ ክቡር ማለት ነው፤ ሚካኤል ማለት ደግሞ «መኑ ከመ አምላክ፥ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማነው?» ማለት ነው። ሚካኤል የሚለው ስም ቃሉ የዕብራይስጥ ነው፤ ሚ - የሚለው «መኑ» ማለት ነው፥ ካ - የሚለው «ከመ» ማለት ሲሆን፥ ኤል - ማለት ደግሞ «አምላክ» ማለት ነው። ይህን ማለትም የቅዱስ ሚካኤልን ስም በጠራን ቊጥር የምንመሰክረው ስለ እግዚአብሔር ነው፤ በመሆኑም እግዚአብሔርን በባሕርይ የሚመስለው፥ በሥልጣንም የሚተካከለው፥ በምድርም በሰማይም እንደሌለ የሚናገር ልዩ፥ ክቡር ስም ነው። የነቢያት አለቃ ሙሴ ባሕረ ኤርትራን ለሁለት ከፍሎ ሕዝቡን ያሻገረለትንና ፈርዖንን ከነሠራዊቱ ያሰጠመለትን አምላክ እግዚአብሔርን በመዝሙር ሲያመሰግን፥ «አቤቱ በአማልክት መካከል (በስም አማልክት ከሚባሉ፥ በስመ አማልክት ከሚጠሩ፥ አንድም አማልክት ዘበጸጋ ከተባሉ ከነቢያት ከካህናት መካከል) አንተን የሚመስል ማነው? በቅዱሳንም ዘንድ እንደ አንተ የከበረ ማነው?» ብሏል። ዘጸ ፲፭፥፲፩። ቅዱስ ዳዊትም፦ «አቤቱ፥ ከአማልክት የሚመስልህ የለም፤» ብሏል። መዝ ፹፭፥፰።


፩፥፩፦ «ስሜ ድንቅ ነውና ለምን ትጠይቃለህ?» መሳ ፲፫፥፲፯
የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ በመሥራታቸው፥ እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን እጅ ለአርባ ዓመት አሳልፎ ሰጥቷቸው ነበር.። በዚህ ዘመን ከዳን ወገን ማኑሄ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፥ ሚስቱም መካን ስለነበረች ልጅ አልወለደችም ነበር። የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ እንደምትፀንስ፥ ወንድ ልጅም እንደምትወልድ፥ ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ እንደሚሆን ነገራት። የሚያሰክር መጠጥ እንዳትጠጣ፥ የረከሰም ነገር እንዳትበላ፥ በልጁም ራስ ላይ ምላጭ እንዳይደርስ (ፀጉሩን እንዳትላጨው) አስጠነቀቃት። እርሷም ተመልሳ የሆነውን ሁሉ ለባሏ ነገረችው፤ «የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኔ መጣ፥ መልኩም እንደ እግዚአብሔር መልአክ እጅግ የሚያስደነግጥ ነበረ፤ ከወዴትም እንደመጣ ጠየቅሁት፥ እርሱም ስሙን አልነገረኝም፤» አለችው።
ማኑሄም፥ «ጌታ ሆይ፥ ወደ እኛ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው እባክህ እንደገና ወደ እኛ ይምጣ፤ ለሚወለደውም ልጅ ምን እንደምናደርግ ያስገንዝበን፤» ብሎ ወደ እግዚአብሔር ለመነ። እግዚአብሔርም የማኑሄን ቃል ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ በእርሻ ውስጥ ሳለች እንደገና ወደ ሴቲቱ መጣ፥ እርሷም ፈጥና ባሏን ጠራችው፥ «እነሆ፥ አስቀድሞ ወደ እኔ የመጣው ያ ሰው ደግሞ ተገለጠልኝ፤» ብላ ነገረችው። እርሱም፦ «ከሚስቴ ጋር የተነጋገርህ አንተ ነህን?» ብሎ ቢጠይቀው «እኔ ነኝ፤» ሲል መለሰለት። ማኑሄም፦ «እነሆ ቃልህ በደረሰ ጊዜ የልጁ ነገር፥ ግብሩስ ምንድነው?» ብሎ ዳግመኛ ጠየቀ። መልአኩም ለሴቲቱ ነግሯት የነበረውን ሁሉ መልሶ ነገረው። ማኑሄ ለመልአኩ የፍየል ጠቦት ለማዘጋጀት ቢፈልግም፦ «አንተ የግድ ብትለኝ እህልህን አልበላም፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ብታደርግ ለእግዚአብሔር አቅርብ፤» አለው። ምክንያቱም ቅዱሳን መላእክት ቅድሚያ የሚሰጡት ለእግዚአብሔር ክብር ነው። እነርሱን ግን እግዚአብሔር ራሱ እንደሚያከብራቸው እንደሚያስከብራቸውም ያውቃሉ።
ማኑሄ የተገለጠላቸው የእግዚአብሔር መልአክ እንደሆነ አላወቀም፥ ሚስቱም አላወቀችም። በመሆኑም፦ «ነገርህ በደረሰ ጊዜ እንድናከብርህ ስምህ ማን ነው?» በማለት ጠየቀው። የእግዚአብሔርም መልአክ፥ «ስሜ ድንቅ ነው፥ ለምን ትጠይቃለህ?» ብሎታል። ማኑሄም የፍየሉን ጠቦትና የእህሉን ቊርባን በድንጋይ ላይ ለእግዚአብሔር አቀረበ። መልአኩም ተአምራት አደረገ፥ ማኑሄና ሚስቱም ይመለከቱ ነበር። ነበልባሉም ከመሠዊያው ላይ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በመሠዊያው ነበልባል ውስጥ ወደ ሰማይ ዐረገ፥ ማኑሄና ሚስቱም ተመለከቱ፥ በምድርም በግንባራቸው ወደቁ። (ሰገዱለት)። ይህ መልካም የምሥራችን የተናገረ፥ የተለያዩ ተአምራትን ያደረገ፥ መሥዋዕታቸውንም ወደ ሰማይ ያሳረገ፥ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ነው። ሚካኤል ማለት በሁለተኛ ትርጉሙ «የእግዚአብሔር ነገሩ ዕፁብ ድንቅ ነው፤» ማለት ነውና። መሳ ፲፫፥፩-፳። በዚህም የስሙ ትርጓሜ ነገረ እግዚአብሔር መሆኑን እንረዳለን።
፩፥፪፦ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ፤ ኢያ ፭፥፲፬
ከነቢያት አለቃ ከሙሴ በኋላ በእርሱ እግር ተተክቶ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የመራው ኢያሱ ነው። የመረጠውም ሰው ሳይሆን እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔርም፦ «በሕይወትህ ዘመን ሁሉ የሚቋቋምህ የለም፤ ከሙሴ ጋር እንደነበርሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ አልጥልህም፥ ቸልም አልልህም፤» ብሎታል። ኢያ ፩፥፭። ይህ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የሆነለት ታላቅ ሰው ኢያሱ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት አስፈልጐታል። ምክንያቱም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ለመሆኑ ምልክቱ ቅዱሳን መላእክት ናቸውና። እግዚአብሔር ባለበት ቅዱሳን መላእክት አሉ፥ ቅዱሳን መላእክትም ባሉበት እግዚአብሔር አለ። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደባት ሌሊት የምሥራቹን «እነሆ፥ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደሰታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ እነሆ፥ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት ተወልዶላችኋል፤ ይኸውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ ነው።» በማለት ለእረኞች የነገሯቸው ቅዱሳን መላእክት ናቸው። እረኞቹም፦ «እስከ ቤተልሔም እንሂድ፥ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን ነገር እንወቅ፥ አሉ።» ሉቃ ፪፥፮-፲፭። በዚህም ቅዱሳን መላእክት የገለጡላቸውን ምሥጢር እግዚአብሔር ገለጠልን ብለዋል።
ኢያሱ ወልደ ነዌ፥ ሕዝቡን እየመራ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ ዐይኑን አንሥቶ ቢመለከት እነሆም የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው በፊቱ ቆሞ አየ። ወደ እርሱም ቀርቦ «ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህን?» አለው። እርሱም «እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ነኝ፤ አሁንም ወደ አንተ መጥቻለሁ፤» ብሎታል። ኢያ ፭፥፲፫-፲፭። የእግዚአብሔር ሠራዊት የሚባሉት ቅዱሳን መላእክት ናቸው። «ያዕቆብም መንገዱን ሄደ፥ በዓይኖቹም የእግዚአብሔርን ሠራዊት ከትመው አየ፥ የእግዚአብሔር መላእክትም ተገናኙት። ያዕቆብም ባያቸው ጊዜ እነዚህ የእግዚአብሔር ሠራዊት ናቸው አለ፤» ይላል። ዘፍ ፴፪፥፩-፪። ቅዱስ ዳዊትም፦ «ሠራዊቱ ሁሉ፥ ፈቃዱን የሚያደርጉ አገልጋዮቹ፥ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤» ብሏል። መዝ ፩፻፪፥፳፩። የእነዚህም (የእግዚአብሔር ሠራዊት) አለቃቸው ቅዱስ ሚካኤል ነው። ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ይሁዳ «የመላእክት አለቃ ሚካኤል» በማለት መስክሮለታል። ይሁዳ ፩፥፲፪።
፩፥፫፦ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉት፤ ራእ ፲፪፥፯
ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በደሴተ ፍጥሞ በግዞት ሳለ በተመለከተው ራእይ ሃላፊያትና መጻእያት ተገልጠውለት ስለነበረ፥ «በሰማይም ሰልፍ (ጦርነት) ሆነ፤» ካለ በኋላ «ሚካኤልና መላእክቱም ዘንዶውን ተዋጉት፥ ዘንዶውም ከነሠራዊቱ ተዋጋቸው። አልቻላቸውምም፥ ከዚያም በኋላ በሰማይ ቦታ አልተገኘላቸውም። ዓለሙን ሁሉ የሚያስተው ዲያቢሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፥ ወደ ምድርም ተጣለ፥ መላእክቱም (የዘንዶው ሠራዊት) ከእርሱ ጋር ተጣሉ፤» ብሏል። ራእ ፲፪፥፯-፱።
ታሪክ፦ ሰይጣን በክህደቱ አጥቶት እንጂ ክብርም ፥ ኃይልም፥ ሥልጣንም ነበረው። በአሥሩ የመላእክት ከተሞች በተሾሙ አሥር የመላእክት አለቆች ላይ የአለቃ አለቃ ነበረ። የተፈጠረው የመላእክት አለቃ ሆኖ ነው። ይኽንንም ቀሌምንጦስ ተናግሮታል። እግዚአብሔር መላእክትን በነገድ መቶ ፥ በከተማ አሥር አድርጐ ፈጥሮ ተሰወራቸው። ይህም ካልፈለጉኝ አልገኝም ፥ ባሕርዬም አይመረመርም ሲላቸው ነው። ወዲያው፦ «እኛ ምንድር ነን? ከየት መጣን ? ማንስ ፈጠረን? በራስ በራሳችን ተፈጠርን ? ወይስ ከሌላ ነው?» አሉ። ሳጥናኤል ከበታቹ እንዲህ ሲሉ ሰማ። ከበላዩ ደግሞ «ፈጠርኳችሁ፤» የሚል አጣ። በቦታው ከሁሉ በላይ አድርጎ ፈጥሮት ነበርና «እኔ ፈጠርሁ፤» ብሎ አሰበ ፥ አስቦም አልቀረ «እኔ ፈጠርኋችሁ፤» አለ። ይኽን ሰምተው «ሰጊድ ይገባዋል፤» ያሉ አሉ። «እኛም እንደ እርሱ ነን፤» ያሉም አሉ። « አምላክ ነኝ ያለስ ከእርሱ በቀር ሌላ የለምና ፥ ይሆንን?» ብለው የተጠራጠሩ አሉ። ሀልዎተ እግዚአብሔርን ሳይመረምሩ የቀሩም አሉ። እኲሌቶቹ ግን ፦ «በምን ፈጠርኋችሁ ይለናል፥ በቦታ ከበላይ በመሆን ፈጠርኋችሁ እንዳይለን ፥ እኛ የበታቾቻችንን መቼ ፈጠርናቸውና ነው?። በዚያውስ ላይ ምቀኞቹ አይደለንም፤ በእውነት ፈጣሪ ከሆነ ፈጥሮ ያሳየን ።» ብለው፦ «ፈጥረህ አሳየን፤» አሉት። እርሱም እፈጥራለሁ ብሎ ፥ እጁን ወደ እሳት ቢጨምር ፈጀውና « ዋይ» አለ። በዚህን ጊዜ «በአፍአ ያለውን (የሚነገረውንና እና የሚሠራውን ብቻ የሚያውቅ) አምላክ ቢሆን ነው እንጂ ውሳጣዊውን (ልብ ያሰበውን የሚያውቅ) አምላክ ቢሆን ኖሮ ገና ሳስበው ለምን አሰብከው ፥ ባለኝ ነበር ፤» አለ። ወዲያው ልቡን ተሰማውና «ዋይ» አለ። እግዚአብሔር ግን ፈወሰው። ይህንንም ማድረጉ ንስሐ ቢገባ እንደሚምረው ሲነግረው ነበር።
ከዚህ በኋላ በመላእክት ሽብር ቢጸናባቸው፦ መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል፦ «ንቁም በበህላዌነ እስከ ንረክቦ ለአምላክነ ፤ አምላካችንን እስክናገኘው ድረስ በየህልውናችን ጸንተን እንቁም ፤» በማለት አጽንቷቸዋል። ይህም በጎ አርበኛ ጦር በተፈታ ጊዜ «አይዞህ ባለህበት ጽና፤» ብሎ እንደሚያጸናው ማለት ነው።« ወበእንተዝ ደለዎ ይፁር ዜናሃ ለማርያም ፤ በዚህ ምክንያት የድንግል ማርያምን ዜና ያደርስ ፥ ብሥራቷን ይናገር ዘንድ ተገባው ፤ » እንዲል ፥ ብሥራት ተሰጥቶታል። «በስድስተኛው ወር (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ፥ ስድስተኛው ሺህ ደግሞ ሲጀምር) መልአኩ ገብርኤል . . . ወደ አንዲት ድንግል ተላከ» ይላል። ሉቃ ፩፥፳፮።
እግዚአብሔርም ጨርሶ ሳያስታቸው ብሎ እርሱ (ሳጥናኤል) በሌለበት በኲል በምሥራቅ ባሕረ ብርሃንን አፍስሶላቸዋል። ከዚህም ጋር ስሙ የተጻፈበት መጽሔተ ብርሃን ቢሰጣቸው አንድነቱ ሦስትነቱ(ምሥጢረ ሥላሴ) ተገልጦላቸው « አሐዱ አብ ቅዱስ ፥ አሐዱ ወልድ ቅዱስ ፥ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፤» ብለው አመስግነውታል። እርሱን ግን ባደረው ጨለማ ጠቅልሎ በዕለተ እሑድ ከኢየሩሳሌም ሰማያዊት ወደ ኢዮር አውርዶታል። ከሰባቱ ሰማያት ሦስቱ ፦ ኢዮር ፥ራማ፥ ኤረር የመላእክት ናቸው። በውስጣቸውም አስር የመላእክት ከተሞች አሉ። በእነርሱም ላይ አስር አለቆች ተሹመዋል። እግዚአብሔር ሳጥናኤል በሌለበት በኲል ባሕረ ብርሃንን ያፈሰሰላቸው «እኔ ፈጠርኩ » እንዳይል ነው።
ሳጥናኤል በኢዮር ሆኖ በዕለተ ሠሉስ የተፈጠሩ ዕፅዋት፥ አዝርዕት ፥ አትክልት ፥ጽጌያትን አይቶ እንዳያደንቅ፦ «እንዲህ አድርጐ አከናውኖ የፈጠረለት ቢኖር ነው፥ » አለ። እግዚአብሐርም «ከወደድሃት በዚያ ላኑርህ ፤» ቢለው «ደገኛይቱን ማን ከልክሎኝ ፤» አለ። ከዚህ በኋላ ለሚካኤልና ለገብርኤል «እናንተ ኢየሩሳሌም ሰማያት ይሏችኋል ፥ ሰባቱ ሰማያት እንኳ አያህሏትም። እኛ ከጩኸት በቀር የተጠቀምነው የለም። ገዢ ነኝ የሚለውን ወግተን እጅ እናድርግ።» ብሎ ላከባቸው። እነርሱም የተላኩትን ከንጉሥ ከተማ እንደገባ ዕብድ ውሻ አድርገው ሰደዷቸው። ተመልሰውም አልተቀበሉንም ቢሉት ፦ «ቀለምጺጸ እሳት (የእሳት ፍንጣሪ) የሆኑ ሚካኤል ገብርኤል በእኔ ዘንድ ምን ቁም ነገር ናቸው። ይልቁንስ ኑ ተሸከሙኝና እንሂድ ፤» አላቸው። በዚህን ጊዜ በአርባዕቱ እንስሳ (በኪሩቤል) አምሳል አራት ሁነው ተሸክመውት ሽቅብ እወጣለሁ ቢል ኃይል ተነሥቶታል። ወደ ታች እንጂ ወደ ላይ መውጣት የማይቻለው በመሆኑም ፦ «ጐየ እግዚእ ምስለ አርያሙ፤ እግዚአብሔር ሰማዩን (ጽርሐ አርያምን) ጠቅልሎ ሸሸ፤» ብሎ ተመለሰ።
ቅዱሳን መላእክት ግን ፍጥረትን ሲፈጥር እያዩ ያመሰግኑ ነበር። በዕለተ ረቡዕ ፀሐይ ፥ ከዋክብት ፥ ጨረቃ ፥ ሲፈጠሩ አይተው አመስግነው አመስግን ቢሉት ፦ «አንሰ ዕድው (ውፁዕ) እምዝንቱ ኅሊና፤» እንዲል፦ «እኔ ከዚህ ውጪ ነኝ ፥ ባይሆን አራተኛ አድርጋችሁ ብታመሰግኑኝ እወዳለሁ፤» አላቸው። እነርሱም «ይህ ስሑት ፍጥረት እንዲህ እያለ እስከ መቼ ሲታበይ ይኖራል?» ብለው ሄደው ቢገጥሙት ድል አደረጋቸው። ሁለተኛም ቢገጥሙት ዳግመኛ ድል አደረጋቸው። በዚህን ጊዜ፦ «እኛስ ለአምላክነትህ ቀንተን ነበረ ፥ አንተ ግን ፈቃድህ ሳይሆን ቀረ፤» ብለው ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክቱ ፦ «ፈቃዳችሁ ፈቃዴ ነው ፥ ነገር ግን ድል የሚነሣበትን (የሚሸነፍበትን) ታውቁ ዘንድ ነው፤» ብሎ ስሙ የተጻፈበትን ትእምርተ መስቀል ሰጣቸው። ያን ይዘው በዕለተ ረቡዕ ወደዚህ ዓለም አውርደውታል። በዚህን ጊዜ የእርሱ ወገኖች ለሦስት ተከፍለዋል። ሀለዎተ እግዚአብሔርን ሳይመረምሩ የቀሩ በአየር ቀርተዋል። ይሆን ፥ አይሆን ብለው የተጠራጠሩ በዚህ ዓለም ቀርተዋል። « አምላክ ነው ፥ ሰጊድ ይገባዋል፤» ያሉ አብረው እንጦሮጦስ ወርደዋል።
፩፥፬፦ ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል፤ ዳን ፲፪፥፩
ቅዱስ ሚካኤል ለእግዚአብሔር መንጋ እረኛቸው ነው። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት፦ በመዝ ፴፫፥፯ ላይ «የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት (ፈሪሃ እግዚአብሔር ባላቸው) ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ (ይከትማል፥ የእሳት አጥር ይሆናል)፥ ያድናቸውማል፤» እንዳለ፥ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በተለይም በፍጻሜ ዘመን ከሚመጣው መከራ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ያድናል። ይህ ምሥጢር የተገለጠለት ነቢየ እግዚአብሔር ዳንኤል፦ «በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው (በአማላጅነት በተራዳኢነት የሚቆመው) ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል፥ ሕዝብም በምድር ከተፈጠረ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን ይሆናል፤» ብሏል። ዳን ፲፪፥፩። በዚህም፦ ገናና መልአክ፥ የመላእክት አለቃ፥ አማላጅና ተራዳኢ መሆኑን መስክሮለታል። ስለዚያች ቀን፥ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ «ያንጊዜ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከዛሬ ያልተደረገ፥ ከእንግዲህም ወዲያ የማይደረግ ታላቅ መከራ ይሆናል፤» ካለ በኋላ፥ «መላእክቱንም ከታላቅ የመለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥ የተመረጡትንም ከሰማይ ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ መዐዝን ይሰበስቧቸዋል።» ብሏል። ማቴ ፳፬፥፳፩-፴፩። ቅዱስ ዮሐንስም ስለ ሓሳዊ መሲሕ ዘመን ተገልጦለት፥ «ከዚህ በኋላ ሌላ አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፤ . . . ለአውሬውም (ለፊተኛው አውሬ) ምስል ያልሰገደውን ሁሉ እንዲገደሉ ያደርጋቸዋል፤» ብሏል። ራእ ፲፫፥፲፩፣ ፲፭። እንግዲህ የዚህን ክፉ ዘመን መከራ ሥጋ ለባሽ የሆነ ሁሉ ስለማይቋቋመው የመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤልና የሠራዊቱ ተራዳኢነት አስፈልጓል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «መላእክት ሁሉ መናፍስት አይደሉምን? የዘለዓለም ሕይወትን ይወርሱ ዘንድ ስለ አላቸው ሰዎችስ ይላኩ የለምን?»ያለው ለዚህ ነው። ዕብ ፩፥፲፬።
፩፥፭፦ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፤ ዳን ፲፥፲፫
ነቢዩ ዳንኤል፥ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በሦስተኛው ዓመተ መንግሥት በራእይ ምሥጢር ተገልጦለታል፥ ነገሩም ከእግዚአብሔር በመሆኑ ምሥጢር ነበረ፥ ታላቅ ኃይልና ማስተዋልም በራእዩ ውስጥ ተሰጥቶታል። ነቢዩ ዳንኤል ስለ ሕዝቡ ኃጢአትና ሊመጣ ስላለው መከራ ሶስት ሳምንት ሙሉ አዝኗል። (ጾም ጸሎት ይዟል)። ማለፊያ እንጀራ አልበላም፥ ሥጋና የወይን ጠጅም በአፉ አልገባም፥ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ራሱን ዘይት አልተቀባም። ከልጅነቱ ጀምሮ ጾም ጸሎትን አጥብቆ የያዘ ነቢይ ዳንኤል በራእይ የተገለጠለት ምሥጢረ ሥጋዌ ነው። «ዳንኤልም ከንጉሡ ማእድ እንዳይበላ፥ ከሚጠጣውም ጠጅ እንዳይጠጣ ልቡ ጨከነ፥ እንዳያበላውም የጃንደረቦቹን አለቃ ለመነው፥ እግዚአብሔርም በጃንደረቦቹ አለቃ ፊት ለዳንኤል ሞገስንና ምሕረትን ሰጠው። . . . ይህንም ነገራቸውን ሰምቶ ዐሥር ቀን ፈተናቸው። ከዐሥር ቀንም በኋላ ከንጉሡ ማዕድ ከበሉ ብላቴኖች ሁሉ ይልቅ ሰውነታቸው አምሮ ሥጋቸው ወፍሮ ታየ። አሚሳድም መብላቸውንና የሚጠጡትን ጠጅ አስቀርቶ ጥራጥሬውን ሰጣቸው፤» ይላል። ዳን ፩፥፰-፲፮።
በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ ዐሥር ቊጥር ፲፫ ላይ፦ «ዳንኤል ሆይ! አትፍራ፥ ልብህ ያስተውል ዘንድ፥ ሰውነትህም በአምላክህ ፊት ይዋረድ ዘንድ ከአደረግህበት ከመጀመሪያው ቀን (ኀዘን፥ ጾም፥ ጸሎት ከጀመርክበት ዕለት) ጀምሮ ቃልህ (ጸሎትህ፥ ምልጃህ) ተሰምቷል፥ እኔም ስለ ቃልህ መጥቻለሁ። የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሃያ አንድ ቀን በፊቴ ነበር። እነሆም ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፥ እኔም ከፋርስ ንጉሥ ጋር በዚያ ተውሁት።» የሚል እናገኛለን። ይኽንንም የተናገረው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ነው። ነቢዩ ዳንኤል ጾም ጸሎት በሚይዝበት ጊዜ ዘወትር ወደ እርሱ እንደሚመጣ «ገብርኤል ሆይ! ራእዩን ለዚህ ሰው ግለጥለት፤ . . . እኔም ገና ስናገርና ስጸልይ፥ በኃጢአቴና በሕዝቤም በእስራኤል ኃጢአት ስናዘዝ፥ በአምላኬም በእግዚአብሔር ፊት ስለ ተቀደሰው ስለ አምላኬ ተራራ ይቅርታን ስጠይቅ፥ ገናም በጸሎት ስናገር አስቀድሜ በራእይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል እነሆ አየበረረ መጣ፥ በማታም መሥዋዕት ጊዜ ዳሰሰኝ።» የሚል አብነት ይገኛል። ዳን ፰፥፲፮፣ ፱፥፳።
ቅዱሳን መላእክት ሁልጊዜ ከዲያቢሎስና ከሠራዊቱ ጋር ይዋጋሉ፥ ያሸንፉማል። ቅዱስ ገብርኤል ወደ ነቢዩ ዳንኤል ሳይመጣ ለሶስት ሳምንት የዘገየበትን ምክንያት ሲነግረው «የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሃያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ፤» ብሏል። ይህም በፋርስ ንጉሥና በሠራዊቱ ካደሩ አጋንንት ጋር ሲዋጋ መሰንበቱን ያመለክታል። ይኸውም ዕለቱን ማሸነፍ ተስኖት ሳይሆን ሰይጣን ኢዮብን በከሰሰበት መንገድ እስራኤልን እየከሰሰ ቀኑን አዘግይቶበታል። ታላቁ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ሰይጣን አዘገየኝ፤» ያለው ከዚህ ተመሳሳይ ነው። ቅዱስ ገብርኤል በሦስተኛው ሳምንት መጨረሻ ሊመጣ የቻለበትን ምክንያት ሲናገር ደግሞ «ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፥ እኔም ከፋርስ ንጉሥ ጋር በዚያው ተውሁት፤» ብሏል። በዚህም ቅዱሳን መላእክት እንኳ እርስ በርስ እንደሚረዳዱ እንማራለን። ይህም ድካም ተሰምቷቸው አንዳቸው የሌሎቹን እርዳታ ይፈልጋሉ ማለት ሳይሆን የአገልግሎት አንድነታቸውን የሚያጠይቅ ነው። ይህ እንዲህ ከሆነ እጅግ ደካማ የሆኑ የሰው ልጆች የኃያላን መላእክት ተራዳኢነት እንዴት አያስፈልገንም ይላሉ? በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ አብነት ለመሆን በጌቴሴማኔ አጸድ በጸለየበት ጊዜ «የሚያበረታታው የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ታየው፤» ይላል። ሉቃ ፳፪፥፵፫። እንግዲህ እርሱንስ ምን ሊሉት ነው?
፩፥፮፦ ከአለቃችሁ ከሚካኤል በቀር የሚረዳኝ ማንም የለም። ዳን ፲፥፳፩
ሰይጣን ሠራዊቱን አሰማርቶ በአሕዛብ ነገሥታት እያደረ የእግዚአብሔር ሕዝብ የተባሉ እስራኤልን ዘወትር በጦርነት ያስጨንቃቸው ነበር። በዚህም ምክንያት ሲወድቁ ሲነሡ፥ ሲነቀሉ ሲተከሉ፥ ሲፈርሱ ሲገነቡ፥ ሲበተኑ ሲሰበሰቡ፥ ሲሰበሩ ሲጠገኑ ኖረዋል። በዚያ ዘመን መጋቤ ብሉይ ተብሎ የሚታወቀው ቅዱስ ሚካኤል ነው። እርሱም ዘወትር ከቅዱስ ገብርኤል ጋር ሆኖ ሕዝቡን ይረዳቸው ነበር። ይኽንንም «ወደ አንተ የመጣሁት ለምን እንደሆነ ታውቃለህን? አሁንም የፋርስን አለቃ እዋጋው ዘንድ እመለሳለሁ፥ እኔም ስወጣ እነሆ የግሪኮች አለቃ ይመጣል። (ሰይጣን በግሪክ ንጉሥ አድሮ ሌላ ጦርነት ይጀምራል)። ነገር ግን በእውነት ጽሑፍ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፥ በዚህም ነገር ከአለቃችሁ (ከመላእክት አለቃ) ከሚካኤል በቀር የሚያጸናኝ የለም።» በማለት ቅዱስ ገብርኤል ለነቢዩ ለዳንኤል ነግሮታል። ቅዱስ ገብርኤል እንዲህ ካለ እኛስ ምን እንበል?
፩፥፯፦ በመላእክት አለቃ ድምጽ፥ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳል፤ ፩ኛ ተሰ ፬፥፲፮
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለጻድቃን ሊፈርድላቸው፥ በኃጥአን ሊፈርድባቸው ዳግም እንደሚመጣ ቅዱሳት መጻሕፍት በመተባበር ይመሰክራሉ። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት፦ «እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል። አምላካችንም ዝም አይልም፥ (ይፈርዳል)፥ እሳት በፊቱ ይነድዳል፥ በዙሪያውም ብዙ አውሎ አለ።» ብሏል። መዝ ፵፱፥፫። ነቢዩ ዘካርያስም በበኲሉ የሚመጣው ከቅዱሳን ሁሉ ጋር እንደሆነ ሲናገር፦ «አምላኬ እግዚአብሔር ከቅዱሳኑ ጋር ይመጣል፤» ብሏል። ዘካ ፲፬፥፮። በአዲስ ኪዳን ደግሞ ራሱ ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ እመሕያው) በጌትነቱ ቅዱሳን መላእክትን ሁሉ አስከትሎ በሚመጣበት ጊዜ፥ ያንጊዜ በጌትነቱ ዙፋን ይቀመጣል፤» ብሏል። ማቴ፳፭፥፴፩። በዕርገቱ ጊዜም ቅዱሳን መላእክት ለደቀመዛሙርቱ ተገልጠው፦ «እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እያያችሁ ለምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ ሲያርግ እንዳያችሁት እንዲሁ ዳግመኛ ይመጣል፤» ብለዋቸዋል። የሐዋ ፩፥፲፩። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ትንሣኤ ሙታን ባስተማረበት ትምህርቱ፦ «ወንድሞቻችን ሆይ፥ ስለ ሞቱ ሰዎች፥ ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች እንዳታዝኑ ልታውቁ እንወዳለን። ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ እንደተነሣ ካመንን፥ እንዲሁ እግዚአብሔር ሙታንን በኢየሱስ ያስነሣቸዋል። ይህንንም በእግዚአብሔር ቃል እንነግራችኋለን፥ ጌታችን በሚመጣ ጊዜ ሕያዋን ሆነን የምንቀር እኛ የሞቱትን አንቀድማቸውም።» ካለ በኋላ «ጌታችን ራሱ በትእዛዝ፥ በመላእክትም አለቃ ድምፅ፥ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፤» ብሏል። ፩ኛ ተሰ ፬፥፲፫-፲፮። ይህ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ነው። እንዲህ እስከመጨረሻው ከጌታ የማይለየውን መልአክ «ለምን ስሙ ተጠራ?» ማለት ራስን ከጌታ መለየት ነው።
፩፥፰፦ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ከሰይጣን ጋር ተከራከረ፤ ይሁ ፩፥፱
የያዕቆብ ወንድም ይሁዳ፥ ቅዱስ ሚካኤልና ሰይጣን የተከራከሩበትን ምክንያት ሲናገር፦ «የመላእክት አለቃ ሚካኤል እንኳን ስለ ሙሴ ሥጋ ከሰይጣን ጋር በተከራከረ ጊዜ የስድብን ቃል ሊናገር አልደፈረም፥ እግዚአብሔር ይገሥጽህ አለው እንጂ። እነዚህ ግን የማያውቁትን በመሳደብ ይበድላሉ፤» ብሏል። ይሁ ፩፥፱። ቅዱስ ይሁዳ፥ በዘመኑ ላሉትም ሆነ እስከ ዓለም ፍጻሜ ለሚነሡት ተሳዳቢዎች እንደተናገረው፥ የመናፍቃን ሥራቸው፥ እንደ ግብር አባታቸው እንደ ዲያቢሎስ ቅዱሳንን መርገም ነው።
የነቢያት አለቃ ሙሴ ከዚህ ዓለም በሞት የሚለይበት ጊዜ ሲደርስ፥ ከሞዓብ ሜዳ በኢያሪኮ ፊት ለፊት ወዳለው ወደ ናባው ተራራ ወደ ፈስጋ ራስ ወጣ፤ እግዚአብሔርም የከነዓንን ምድር ካሳየው በኋላ፦«ለዘርህ እሰጣታለሁ ብዬ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማልሁላቸው ምድር ይህች ናት፤ እነሆም፥ በዐይንህ እንድታያት አደረግሁህ፥ ነገር ግን ወደዚያች አትገባም፤» አለው። የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴም እንደ እግዚአብሔር ቃል በዚያ በሞዓብ ምድር ሞተ። በቤተ ፌጎርም አቅራቢያ በናባው ምድር ቀበሩት፥ እስከዛሬም ድረስ መቃብሩን ማንም የሚያውቅ የለም። ዘዳ ፴፬፥፩-፯። የሙሴ መቃብር እንዴት ሊታወቅ አልቻለም? የቀበረውስ ማነው?
ታሪክ፦ እግዚአብሔር የሙሴን መቃብር ከእስራኤል ሰውሮባቸዋል፥ የሰወረበትም ምክንያት ካላቸው ጽኑዕ ፍቅር የተነሣ መቃብሩን እንዳያመልኩ ነው። አንድም የተቀበረበትን ቦታ ካወቁ ጧት ማታ እየሄዱ ከመቃብሩ ላይ እያለቀሱ ኀዘን እንዳይጸናባቸው ብሎ ነው። የነቢያት አለቃ ሙሴ ወደ ተራራው ሲወጣ ሁለት መላእክት በአረጋውያን ተመስለው መቃብር ሲቆፍሩ አገኛቸው። መላእክት መሆናቸውን ግን አላወቀም። «አክብር ገጸ አረጋዊ» የሚለውን ሕግ ስለሚያውቅ «ላግዛችሁ፤» ብሎ መቃብሩን ቆፍሮ ጨረሰላቸው። እነርሱም፦ «ልክ ይዘን አልመጣንም፥ ስለዚህ ሟቹ በግምት አንተን ስለሚያክል ውስጡ ተኝተህ ለካልን፤» አሉት። እርሱም «እሺ፥በጀ፤» ብሎ ተኝቶ ሲለካ በዚያው ነፍሱ ከሥጋው ተለይታ አርፏል። ከዚህ በኋላ አፈር መልሰውበታል። የሙሴ መቃብር በሰው ዘንድ ያልታወቀው በዚህ ምክንያት ነው።
እስራኤል ዘሥጋ ከሞቱ ይልቅ የመቃብሩ መሰወር አሳዝኖአቸዋል። በዚህን ጊዜ የሰውን ችግር መግቢያ በር አድርጐ መግባት የሚያውቅበት ሰይጣን ወደ ሕዝቡ የሚቀርብበትን ምክንያት አገኘ። ቀርቦም «ኑ፥ ተከተሉኝና የሙሴን መቃብር ላሳያችሁ፤» አላቸው። እንዲህም ማለቱ ለእነርሱ አዝኖላቸው ሳይሆን፥ የሚሆንለት መስሎት፥ በሙሴ ሥጋ አድሮ ሊመለክ ፈልጐ ነው። ሕዝቡም እውነት መስሏቸው ተከተሉት። በዚህ ቅጽበት የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወርዶ ሰይጣንን ተቃወመው። «በቅዱሱ በሙሴ ሥጋ ማደር አትችልም፥ እርሱ የእግዚአብሔር ማደሪያ ነው፤» ብሎ ተከራከረው። በመጨረሻም ሦስት ጊዜ «እግዚአብሔር ይገሥጽህ፤» ቢለው ሰይጣን እንደ ትቢያ ተበትኖ ርቆላቸዋል። ይህ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ፍላጐታችንን ምክንያት አድርጐ ባልሆነ መንገድ እንዳይመራን ሰይጣንን ይቃወምልናል፥ ተከራክሮም ያሸንፍልናል ብለን እናምናለን። እንኳን በሕይወት እያለን ሞተንም በመቃብር ይጠብቀናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
፩፥፱፦ በእስራኤል ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ፤ ዘጸ ፲፬፥፲፱
ከባርነት ቤት ከግብፅ የወጡትን ሕዝብ፥ እግዚአብሔር፦ ቀኑን በደመና ዓምድ፥ ሌሊቱን ደግሞ በብርሃን ዓምድ መርቷቸዋል። የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን እስራኤልን «ሂዱ፤» ብሎ ከለቀቃቸው በኋላ መልሶ ስለጸጸተው ሠራዊቱን ይዞ ተከተላቸው። ፈርዖንም በቀረበ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ዓይናቸውን አንሥተው ግብፃውያን ሲከተሉአቸው አዩ፤ እጅግም ፈርተው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። ምክንያቱም ሸሽተው እንዳያመልጡ ከፊት ለፊታቸው ያለው ባሕር ነው። በዚህ ላይ ፈርዖን ከነሠራዊቱ የተከተላቸው በፈረስ በሰረገላ በመሆኑ ሸሽተውም ቢሆን ማምለጥ አይችሉም። መሸሻ ሜዳ፥ መሸሎኪያ ቀዳዳ፥ መመከቻ ጋሻ፥ መሸሸጊያ ዋሻ አልነበራቸውም። ሙሴንም፦ «በግብፅ መቃብር ስላልኖረ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ አወጣኸንን? ከግብፅ ታወጣን ዘንድ ይህ ያደረግህብን ምንድነው? በምድረ በዳ ከምንሞት ብንገዛላቸው ይሻለናልና፦ ተወን፥ ለግብፃውያን እንገዛ፥ ብለን በግብፅ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን?» አሉት። ሙሴም ለሕዝቡ «አትፍሩ፥ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘለዓለም አታዩአቸውምና ቁሙ፤ (በእምነት ጽኑ)፤ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ።» አላቸው። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ «ለምን ትጮኽብኛለህ? ከብቶቻቸውን እንዲነዱ ለእስራኤል ልጆች ንገር። አንተም በትርህን አንሣ፥ እጅህንም በባሕሩ ላይ ዘርጋ፥ ክፈለውም፥ የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ ውስጥ በየብስ ያልፋሉ። እነሆም እኔ የፈርዖንን እና የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፥ በስተኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሰረገሎቹ፥ በፈረሰኞቹም ላይ እከብራለሁ። (ኃይሌን ገልጬ እመሰገናለሁ)። ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ፥ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር ባገኘሁ (ኃይሌን ገልጬ በተመሰገንሁ) ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ (ኃያልና ገናና ፈጣሪ መሆኔን) ያውቃሉ፤» አለው። በእስራኤልም ሠራዊት ፊት ይሄድ (ይመራቸው፥ ይጠብቃቸው) የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ (ከፈርዖንና ከሠራዊቱ በክንፈ ረድኤቱ ጋረዳቸው)፤ የደመናውም ዐምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ፥ በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፥ በዚያም ጭጋግና ጨለማ ነበረ፤ ሌሊቱም አለፈ፥ ሌሊቱንም ሁሉ እርስ በርሳቸው አልተቃረቡም። ሲነጋም እግዚአብሔር አስቀድሞ እንደተናገረ በበትረ ሙሴ ላይ ኃይለ እግዚአብሔር ተገልጦ ባሕረ ኤርትራ ለሁለት ተከፈለ፥ ውኃው ግራና ቀኝ እንደ ግድግዳ ቆሞ፥ እስራኤል በደረቅ ተሻገሩ፥ ግብፃውያን ሰጥመው ቀሩ። ዘጸ ፲፬፥፩-፴፩።
እስራኤል ዘሥጋን በመንገዳቸው ሁሉ የጠበቃቸው፥ መና ከሰማይ ያወረደላቸው፥ ተአምራትን ያደረገላቸው፥ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ርስታቸው የመራቸው፥ በደመና መጋረጃ የጋረዳቸው፥ በክንፎቹም የሸፈናቸው መጋቤ ብሉይ የተባለ ቅዱስ ሚካኤል ነው። እኛንም ከዲያቢሎስና ከሠራዊቱ ይጠብቀናል፥ ከአሽክላው ይሰውረናል፥ ወደ ምድረ ርስት ገነት መንግሥተ ሰማያት ይመራናል፥ ብለን እናምናለን። ኅዳር አሥራ ሁለት ቀን በየዓመቱ በማኅሌት እና በቅዳሴ የምናከብረው ይኽንን ለእስራኤል ዘሥጋ የተደረገውን በማሰብ ነው። የበለጠው ደግሞ እስራኤል ዘነፍስ ለምንባል ክርስቲያኖች ይደረግልናል።
የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማላጅነት፥ የቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት አይለየን አሜን።

No comments:

Post a Comment