Thursday, October 10, 2013

ማኅበረ ቅዱሳን – የሃይማኖት አጥባቂነት ወይስ የአክራሪነት




(ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፤ 19ኛ ዓመት ቁጥር 255፤ ነሐሴ 16 – ጳጉሜ 5 2004 ዓ.ም)

በዲ/ን ታደሰ ወርቁ*

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ መንግሥታዊ አካላት በወጡ ሰነዶችና በሚሰሙ ንግግሮች ማኅበረ ቅዱሳንን ‹‹የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት አክራሪዎች›› ማንጸርያ አድርጎ የመውሰድ አዝማሚያዎች እየታዩ ነው፡፡ ይህን የተሳሳተ አቻ ፈጠራበመጠቀም አፅራረ ቤተ ክርስቲያንም የራሳቸውን ፍላጎት ሲያራግቡበት ይታያል፡፡ ተከታዩ ጽሑፍ መንግሥት አቋሞቹን የገለጸባቸውን ሰነዶችና የማኅበረ ቅዱሳንን የኅትመት ውጤቶች በመፈተሽ ማኅበረ ቅዱሳን የሃይማኖት አጥባቂነት እንጂ የሃይማኖት አክራሪነት ትእምርት እንዳልኾነና ሊኾንም እንደማይችል ያስረዳል፡፡
* * *


ዲ/ን ታደሰ ወርቁ

አክራሪነት አሉታዊ ትርጉም ሲኖረው የራስን እምነትና አመለካከት በሌሎች ላይለመጫን መሞከር ነው፡፡ ሃይማኖት መንግሥታዊ ቅርጽ ይዞ እንዲወጣ ለማድረግ መሞከር ራሱ አክራሪነት እንደኾነ የዘርፉ ዐዋቆች ይሞግታሉ፡፡ አክራሪነት በአሉታዊ መልኩ የፖሊቲካ ገጽታ ያለው ነው፡፡ ኾኖም ግን ሃይማኖትን ማጥበቅ አክራሪነት አይደለም፡፡ሃይማኖት ፍጹም እውነታን በፍጹም እምነት ስለሚቀበል ከሌሎች ግላዊ አስተሳሰቦች የተለየ ነው፡፡ የሃይማኖት መገለጫዎችን መጠቀም የዚያን ሃይማኖት ጥልቀት የሚያሳይ እንጂ እንደ ችግርም የሚወሰድ ወይም አክራሪነት ሊኾን አይችልም፡፡ «መጾም፣ መጸለይ፣ ሥርዓተአምልኮን መፈጸም ለሃይማኖቱ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንጂ አክራሪነት ሊባልአይችልም፤» ይላሉ የዘርፉ ምሁራን፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትም የሃይማኖት አክራሪነትን ለመቃወም ባዘጋጃቸው ሰነዶች የአክራሪነትና የአጥባቂነት ፅንሰ ሐሶቦች በጥሩ ኹኔታ ተለይተው ተገልጸዋል፡፡ ሰነዶቹ አክራሪነትንና አጥባቂነትን በአግባቡ ለይተውና ተንትነው ያስቀምጣሉ፡፡ በዚሁ መሠረትአጥባቂነትን፣ ‹‹የግል ሃይማኖትን ሃይማኖቱ በሚያዘው መሠረት ሳይንጠባጠብ ሁሉንም ትእዛዛት መፈጸም ነው፤» በማለት ሲፈታው አክራሪነትን ደግሞ፣ «ከራስ እምነት ወጥቶ ሌላውን መተንኮስና የሌሎችን ሃይማኖት መኖር አለማመንና አለመፍቀድወይም ሌሎቹን አስገድዶ የራስ እምነት ተከታዮች ለማድረግ መጣር ነው፤» ይላል፡፡

ከዚህ ብያኔ ስንነሣ ሙስሊምም ኾነ ክርስቲያን ከርሱ ውጭ የኾኑትን የሌሎቹን መኖር የማይቀበልና ከግለሰቦቹ ፈቃድ ውጭ አስገዳጅ እስከኾነ ድረስ እርሱን አክራሪ ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ መልኩ አክራሪው ይህንኑ ድርጊት ሊፈጽም የተነሣውን ቡድን ብቻ እንጂ «አክራሪው ቡድን» የወጣበትን/የተገኘበትን ቤተ እምነት ሊወክል አይችልም፡፡ ስለዚህ የአክራሪ እስልምና ቡድን መኖር የእስልምና ተከታዮችን በሙሉ «አክራሪ» አስብሎ ሊያስፈርጃቸው አይችልም፤ ለሌላው ቤተ እምነትም እንዲሁ፡፡

የሃይማኖት አክራሪነትንና አጥባቂነትን በዚህ መልኩ ከተረዳን ማኅበረ ቅዱሳን የሃይማኖት አክራሪነት ወይስ አጥባቂነት ትእምርት የሚለውን ወቅታዊ ጥያቄ መመለስ ግድ ይለናል፡፡ ይኸውም መንግሥት የተለያዩ መግለጫዎችን ከማውጣት አንሥቶ ውይይቶችን እያካሔደና ሌሎች ርምጃዎችንም እየወሰደ ይገኛል፡፡ ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ማኅበረ ቅዱሳንን በአክራሪነት ለማስፈረጅና ከመንግሥት ጋራ ለማጋጨት ቆርጠው የተነሡ አካላት እንዳሉ ከአንዳንድ የውይይት መድረኮች፣ ሰነዶች፣ [የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ] ብሎጎችና የደብዳቤ መጻጻፎች ለመረዳት ተችሏል፡፡

በተለይ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሚያዝያ 9 ቀን 2004 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስድስት ወር ሪፖርት በሚያቀርቡበት ወቅት የሃይማኖት አክራሪነትንና የመንግሥታቸውን የፀረ አክራሪነት እንቅስቃሴ በተመለከተ ለምክር ቤቱ አባላት ሰፊ ማብራሪያ ሲሰጡ፣ «. . . አንዳንድ የሰለፊ እምነት ተከታዮች . . . በተለያየ መንገድ አንዳንድ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት የሚያራምዱትንግልባጭ ሲያራምዱ ታይቷል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው ሙስሊም ነው፡፡ የስታቲስቲክስ መሥሪያ ቤት ያቀረበው መረጃ ውሸትነው፡፡ አብዛኛው ሕዝብ ሙስሊም ስለኾነ የእስላም መንግሥት ነው መቋቋም ያለበት የሚል ቅስቀሳ በሰፊው ነው የሚካሔደው፡፡በእነዚህ አክራሪዎች፡፡. . .» ብለው መጥቀሳቸውን ተከትሎ የስም ማጥፋት ዘመቻው ከወትሮው ተባብሷል፡፡

ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን አክራሪነትን ከመቃወም አንጻር ምን እንደ ሠራ ከዚህም ጋራ በማኅበሩ ላይ ያሉ ብዥታዎችን በማጥራት የማኅበሩን አጠቃላይ ኹኔታ ለመግለጽ ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ ኾኗል፡፡ ይህ ጽሑፍም ማኅበሩ በሃይማኖት አክራሪነት ጉዳይ ያለውን አቋም፣ የማኅበሩን እውነተኛ ማንነትና ትክክለኛ ገጽታ ከድርጊቱና ከወሰዳቸው አቋሞች አንጻር ለማስረዳት የተዘጋጀ ነው፡፡ ሦስት መሠረታዊ መነሻዎችን እናቅርብ፡፡

የፍረጃው አዝማሚያና የቅርብ መነሻ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት መኾኑ፤

በምክር ቤቱ ማብራሪያ ውስጥ አቶ መለስ ማኅበረ ቅዱሳንን የሰለፊ ማንጸርያ አድርገው ያቀረቡት ከሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት አንጻር ብቻ ነው፡፡ ይህም ቢኾን በራሱ ማኅበረ ቅዱሳንን እንደ ተቋም አክራሪ አያሰኘውም፤ ስለ ሁለት ነገር፤ የመጀመሪያው፣ አቶ መለስ «አንዳንድ የማኅበረ ቅዱስን አባላት» አሉ እንጂ ማኅበረ ቅዱሳን አላሉም፡፡ ይህም ግለሰባዊ ሓላፊነትን እንጂ ተቋማዊ ሓላፊነትን አይገልጽም፡፡ ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ማኅበር የሃይማኖት አክራሪነት ትእምርት ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡

ሁለተኛው፣ የሕዝብና ቤት ቆጠራውን ውጤት ከአለመቀበል ጋራ ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ተቋም «አክራሪ» ተብሏል በሚለው ብንሔድ እንኳን የመረጃና የማስረጃ ዳጥን ከማሳበቅ ውጭ ማኅበረ ቅዱሳንን የሃይማኖት አክራሪ አያሰኘውም፡፡ ምክንያቱም የሕዝብና ቤት ቆጠራው ውጤት ላይ «ጥርጣሬ አለኝ» ያለችው /ይህም ቢኾን አክራሪ አያስብልም/ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንጂ ማኅበረ ቅዱሳን ወይም አንዳንድ የማኅበረ ቅዱሳንአባላት አይደሉም፡፡

በወቅቱ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወክለው መግለጫ የሰጡት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ መጋቤ ሥርዐት ዳንኤል ወልደ ገሪማ ቤተ ክርስቲያኒቱ በውጤቱ ላይ ያላትን ጥርጣሬ ሲገልጹ፣ «መንግሥት የሕዝብና ቤት ቆጠራ በሚያካሒድበት ወቅት ከቦታ ርቀት የተነሣበገዳም የሚገኙ መነኮሳትና መነኮሳዪያትን፣ የቆሎ ተማሪዎች ቁጥር ካለማካተቱም ባሻገር በተለያዩ ምክንያቶች ያልተቆጠሩምእመናን ተካተዋል ለማለት ስለሚያጠራጥር ቤተ ክርስ ቲያኗ መንግሥት ይፋ ያደረገውን ውጤት ሙሉ ለሙሉ ለመቀበልይቸግራታል፤» በማለት ነው፡፡ የማኅበሩ ልሳን የኾነችው ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በወቅቱ «የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንበሕዝብ ቆጠራ ውጤት ጥርጣሬ እንዳላት አስታወቀች» በሚል ርእስ ዘግባለች፡፡ /16ኛ ዓመት ቁጥር 71፣ ቅጽ 16 ቁጥር 168፤ከታኅሣሥ 16 – 30 ቀን 2001 ዓ.ም/፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ መግለጫው የተሰጠው በቤተ ክርስቲያኒቱ ነው፡፡ ይህም መግለጫ በራሱ አክራሪ አያሰኝም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም ይህን ከመግለጽ/ከማስታወቅ አልፎ የሰጠው መግለጫ የለም፡፡ በምንም መስፈርት የማኅበረ ቅዱሳንን ተቋማዊ ሰውነት ወይም የማኅበሩን አባላት የሃይማኖት አክራሪነት ትእምርት አድርጎ አያስወስድም፡፡

የመንግሥት የሃይማኖት አክራሪነት ብያኔ ማኅበረ ቅዱሳንን አይገልጽም

የኢትዮጵያ መንግሥት ራሱ በየሰነዶቹ እንደገለጸው፣ የሃይማኖት አክራሪነትን የሚመለከተው ከሃይማኖት ሳይኾን ከልማት፣ ዴሞክራሲና ሰላም አንጻር ብቻ ነው፡፡ ምንም እንኳን እንዲህ ዓይነቱ ኀልዮት አከራካሪ ቢኾንም መንግሥት፣ «እኔ አንድን ተቋም ወይም ግለሰብ የሃይማኖት አክራሪ ነው የምልበት የራሴ የብያኔ መስፈርት አለኝ» ካለ መብቱ ነው፡፡ የትኛውም ሀገር ከራሱ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ኹኔታዎች አንጻር መበየን ስለሚችል፡፡ መስፈርቱንም «የሃይማኖት አክራሪነትና የፀረ አክራሪነት ትግላችን» በሚል ርእስ ለመንግሥት አመራሮች ሥልጠና በቀረበው ሰነድ እና «ልማት፣ ዴሞክራሲና የሃይማኖት አክራሪነት» በሚል ርእስ በፌዴራል ጉዳዮች የሃይማኖት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀው ጽሑፍ እንዲሁም በአዲስ ራእይ የንድፈ መጽሔትም ሲያትተው እንደሚከተለው ይላል፡-
  • በዜጎች የእምነት ነጻነት አለማመን፤ በማስገደድ የራስን እምነት ለማስያዝ መንቀሳቀስ፤ እምነት ለመያዝ ያለውን ነጻነትበኀይል በማስገደድ መገደብ ወይም መከላከል፤
  • በሃይማኖት እኩልነት አለማመን፤ የእኔ ይበልጣል የሌላኛው ያንሳል በሚል መንቀሳቀስ፤ ሁሉም እኩል መኾኑ የእኔንሃይማኖት ክብርና ሞገስ ይቀንሳል በሚል ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማካሔድ፤
  • መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው የሚለውን መንግሥታዊ መርሕ በመጣስ መንግሥታዊ ሃይማኖት ካልሆንኩ ወይምሃይማኖታዊ መንግሥት ከሌላ በሚል ይህንኑ ለማሳካት በተግባር መንቀሳቀስ፤

በእነዚህ የመንግሥት የሃይማኖት አክራሪነት መስፈርትነት ማኅበረ ቅዱሳን ሲመዘን ማኅበሩ አንዱንም አሟልቶ አይገኝም፤ ወይም ሦስቱም የብያኔ መስፈርቶች ማኅበረ ቅዱሳንን አይመለከቱም፡፡ እስኪ አንድ በአንድ እንመልከታቸው፡፡

በዜጎች የእምነት ነጻነት አለማመን፤ ከዚህ አንጻር ማኅበረ ቅዱሳን ሲታይ እምነቱን ከመግለጽ አልፎ ለዜጎች እምነት ነጻነት መከበር የድርሻውን ተወጥቷል፡፡ ይኸውም ሌሎችን በማስገደድ የራሱን እምነት ለማስያዝ መንቀሳቀስ ወይም የሌሎችን የእምነት ነጻነት በኀይል መገደብ ፀረ ሕገ መንግሥታዊ ብቻ ሳይኾኑ ኢ-ሃይማኖታዊ ድርጊት መኾኑን በይፋ የገለጸ ማኅበር ነው፡፡ ያለአንዳች ማጋነን በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ተቋቁሞ የሕገ መንግሥት ትምህርት ከመጀመሩ በፊት፣ ማኅበረ ቅዱሳን የእምነት ነጻነት በሕገ መንግሥቱ ብቻ ሳይኾን በሌሎቹም የሀገሪቱ ሕጎች ያለውን ቦታ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በመጽሔቱና በጋዜጣው አስተምሯል፡፡ ይህን ያደረገው ደግሞ በመንግሥት ወይም በሌላ ኀይል ትእዛዝ አይደለም፡፡ የዜጎችን የእምነት ነጻነት በመሠረቱ ከማመን ነው፡፡

ማኅበሩ ይህን እምነቱን «ሐመረ ጽድቅ» በሚል ርእስ በ1996 ዓ.ም ባሳተመው የሐመር መጽሔትና የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ልዩ የጋራ ዕትም፣«የእምነት ነጻነት በኢትዮጵያ ሕግ» በሚል በተዘጋጀው መጣጥፍ ላይ፣ «የእምነት ነጻነት ሰፋ ባለ መልኩ ሲታይ የኅሊና ነጻነትማለትም ማንም ሰው ያለፍላጎቱ ማንኛውንም ዐይነት ሃይማኖት ወይም እምነት እንዲቀበል አይገደድም ማለት ነው፡፡ ማንም ሰውበማንኛውም መንገድ አንድን ሃይማኖት ከሌላው በመምረጡ ወይም ምንም ዐይነት ሃይማኖት እንዳይኖረው በመፈለጉ ምክንያትበምንም መንገድ አይቀጣም፡፡ የአንድ ሰው የሃይማኖት እምነት የግል ጉዳይ እንጂ በመንግሥት ባለሥልጣናት ወይም በሌሎችሰዎች አስገዳጅነት የሚመረጥ ወይም የሚተውና የሚለውጥ ጉዳይ አይደለም፤» ሲል ገልጿል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ማኅበሩ በዚሁ መጣጥፍ ላይ የእምነት ነጻነት በሀገራችን ያለውን ሕጋዊ ይዞታና ጥበቃ ሲያትት እንዲህ ብሏል፡-

የእምነት ነጻነት በሕገ መንግሥቱ ልዩ ቦታ ከተሰጣቸው መሠረታዊ የሰው ልጆች መብቶችና ነጻነቶች አንዱ ነው፤. . . በሀገራችን ማንም ሰው የመረጠውን እምነት የመከተል፣ የማስተማርና የማስፋፋት መብት አለው፡፡ መንግሥትን ጨምሮ ማንኛውም ሰውጣልቃ በመግባት በሌላው ሰው የእምነት ነጻነት ላይ ተጽዕኖ እንዳይደረግበት የሕግ ጥበቃ አለ፡፡ ስለዚህ በሕጉ መሠረትየሌሎችን ሰዎች ነጻነትና መብት ለመጠበቅ ከተቀመጠው ገደብ ውጭ ማንም ሰው በማንኛውም ቦታና ጊዜ ሥርዐተ አምልኮቱንእንዳይፈጽም ሊከለከል ወይም ማንኛውም ተጽዕኖ ሊደረግበት አይገባም፡፡ /ሐመረ ጸድቅ፣ 1996፣55/፡፡

ከዚህ ሁሉ መረዳት የሚቻለው ማኅበረ ቅዱሳን በሃይማኖት አክራሪነት ስሜት የሌሎችን የእምነት ነጻነት መብት አለመቀበል ወይም መገደብ ይቅርና የራስን እምነት አጽንቶ ከመያዝ ጋራ ኦርቶዶክሳውያን በሙሉ የሌሎችን የእምነት ነጻነት እንዲያከብሩ ብርቱ ጥረት ማድረጉን ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንድ መንግሥታዊ ያልኾኑ አካላት እንዲህ ዐይነቱን ሕገ መንግሥታዊ መብት መጣሳቸውንም በዚህ ጽሑፍ እንዲህ ሲል አጋልጧል፡፡

አንዳንድ መንግሥታዊ ያልኾኑ ገባሬ ሠናይ ድርጅቶች በሚሰጡአቸው ማኅበራዊ አገልግሎቶች ዜጎችን በድርጅቶቹ የሚደገፈውንእምነት ካልተቀበሉ አድልዎ ይፈጽሙባቸዋል፡፡ በተለይ ትምህርት፣ በማናቸውም ረገድ ከሃይማኖት፣ ከፖለቲካ አመለካከትናከባህላዊ ተጽዕኖ ነጻ በኾነ መንገድ መካሔድ እንዳለበት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 90/2/ በግልጽ ተደንግጎ እያለ በአሁኑ ሰዓትበአንዳንድ መንግሥታዊ ባልኾኑ በጎ አድራጊ ድርጅቶችና የእምነት ተቋማት በተቋቋሙ ት/ቤቶች የሚማሩ ሕፃናትና ወጣቶችከወላጆቻቸው የወረሱትን ሃይማኖት እንዲለውጡ ይገደዳሉ፡፡ ፈቃደኛ ካልኾኑ ደግሞ ሌሎች ምክንያቶች እየተፈለጉ ከትምህርትገበታቸው እንዲወገዱ የሚደረግበት አጋጣሚ እየታየ ነው፡፡ በአንዳንድ የመንግሥት የትምህርት ተቋማትም ሓላፊዎችበተማሪዎቻቸው የእምነት ነጻነት ላይ የሀገሪቱ ሕግ ከሚፈቅደው ውጭ ገደብ የሚጥሉበት ኹኔታ አለ፡፡

እነዚህ ድርጊቶች የሀገሪቱ የበላይ ሕግ የኾነው የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ የሚጥሱ በመኾናቸው የድርጊቱን ፈጻሚዎች ተጠያቂነትየሚያስከትል ነው፡፡ እዚህ ላይ መብቱን የማስከብር ሓላፊነትና ግዴታ የተጣለባቸው በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናትተጠያቂነት ስላለባቸው ተገቢውን የእርምት ርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡


ማኅበረ ቅዱሳን የራሱን እምነት በሌሎች ላይ ለመጫን እንዲያመቸው የሌሎችን የእምነት ነጻነት በኀይል ወይም በጉልበት ሊገድብ ይቅርና በአመለካከት እንኳን እንዲህ ዐይነቱ ኢ-ሃይማኖታዊ ድርጊት የሚታይበት ማኅበር አለመኾኑን በግልጽ መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ አኳያ ማኅበረ ቅዱሳን የሃይማኖት መከባበር ትእምርት እንጂ የሃይማኖት አክራሪነት ትእምርት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ማኅበር አለመኾኑን ብያኔው ይገልጣል፡፡

ሌላው የመንግሥት የሃይማኖት አክራሪነት ብያኔ በሃይማኖት እኩልነት አለማመን ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ጥንቱንም ቢኾን በዚህ ረገድ የአመለካከትም ኾነ የተግባር ችግር የለበትም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን በሃይማኖት ልዩነት መከባበር ላይ ያለውን እምነት በተለያዩ ጊዜ ገልጿል፡፡ በሃይማኖት ልዩነት መከባበርን የሚተነትኑ ጽሑፎችን በልሳኖቹ አስተናግዷል፡፡ በሐመር መጽሔት መስከረም/ጥቅምት፣ 1999 ዓ.ም. ዕትሙ «ሽብር ሃይማኖት የለውም» በሚል ርእስ ስለ ሽብርተኝነትና የሽብር መሣሪያ ስለኾኑት አክራሪነትና ጽንፈኝነት የሚተነትነውን ጽሑፍ ማስታወስ ብቻ በቂ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ስለ ሃይማኖት እኩልነት የሰፈረውን ሐሳብ እንመልከት፡፡

. . .ስለዚህ ማንኛውምና የየትኛውም እምነት ተከታይ የእምነቱን አስተምህሮ በመከተል በራሱ የተስተካከለ ሕይወት ሊኖርናየተቻለውን ሊያደርግ ይገባል፡፡ የራሱን ሃይማኖት አጥብቆ ሊከተልና የሌሎችንም ሃይማኖት ሊያከብር ይገባል፡፡ ከመወያየት ይልቅከአንተ የኔ ይሻላል ወይም ይበልጣል እያሉ ሳይፎካከሩና ሳይወራረዱ እርስ በርስ ተከባብረው ሊኖሩ ይገባል፡፡ ሃይማኖትን ሽፋንአድርገው የሚነሡ ጽንፈኛ ቡድኖችና ግለሰቦች ለመከላከል ዋናው መንገድ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ በልዩነት መቻቻልንና አንድነትንመስበክ፣ ማስተማርና በተለያዩ እምነት መሪዎች መካከል መከባበርንና መዋደድን ማስፈን ነው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን እንዲህ ዓይነቱን የሃይማኖት እኩልነት መርሕን ያከበረና የሚተነትን ጽሑፍ ብቻ አይደለም ያስተናገደው፡፡ ከሀገሪቱ ሕግ አንጻር የሃይማኖት እኩልነት ሲባል ምን ማለት እንደኾነ ለሁሉም በሚኾን መልኩ ያስተማረ ማኅበር ነው፡፡ ይህንንም በ2001 ዓ.ም በታተመው «ሐመረ ተዋሕዶ የሐመር መጽሔት ልዩ ዕትም» ላይ «ሃይማኖት በመድበለ ሃይማኖት ማኅብረሰብ» በሚል ርእስ የተዘጋጀውን መጣጥፍ መመልከት ከበቂ በላይ ማረጋገጫ ነው፡፡ ጽሑፉም የሚያጠነጥነው ሀገራችን ኢትዮጵያ የመድበለ ሃይማኖት ማኅበረሰብ ሀገር እንደ መኾኗ መጠን ሁሉም ቤተ እምነት ከእነርሱ ውጪ ካሉ ቤተ እምነቶች ጋራ እንዴትና በምን ኹኔታ ተከባብረው መኖር እንዳለባቸውና በመድበለ ሃይማኖት ማኅበረሰብ ውስጥ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አኳያ የሃይማኖት እኩልነትና ነጻነት ከሕግ አንጻር በምን አግባብ መፈታት እንዳለበት የሚያመለክት ነው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በመርሑ ከማመን በላይ በተግባር ብዙ ርቀት መጓዙን ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡ ጽሑፎቹ «የእኔ ይበልጣል፣ የሌላውያንሣል» በሚል ትምክህት ሌላውን ለመድፈቅ አለመነሣቱንም በሚገባ የሚገልጹ ሐቆች ናቸው፡፡ «ሁሉም እኩል መኾኑ የእኔን ሃይማኖትክብርና ሞገስ ይቀንሳል» በሚል ተግባራዊ እንቅስቃሴ አለማካሔዱን ብቻ ሳይኾን የሃይማኖት እኩልነት መርሕን በአግባቡ ተንትኖ እየተገበረው ያለ ማኅበር መኾኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ከዚሁ መርሕ በመነሣት «ክርስትናና እስልምናን ጨምሮ ማንኛውም ሃይማኖት በመሠረቱ የሚሰብከው በሰላም አብሮ ተቻችሎ መኖር ነው፤» በማለት የሌሎችንም ቤተ እምነታት ሰላም ወዳድነት ዕውቅና የሰጠ የአብሮነትና የመከባበር ትእምርት ነው ማኅበረ ቅዱሳን፡፡ /ሐመር፣ መስከረም/ጥቅምት 1999 ዓ.ም.፣ 22/።

የመጨረሻው የመንግሥት የሃይማኖት አክራሪነት ብያኔ፣ «መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ መርሕ በመጣስ መንግሥታዊ ሃይማኖት ካልኾነ ማለት ወይም ሃይማኖታዊ መንግሥት ከሌለ በሚል ይህንኑ ለማሳካት በተግባር መንቀሳቀስ» የሚል ነው፡፡ ከዚህ የሃይማኖት አክራሪነት ብያኔያዊ መስፈርት አንጻር ማኅበረ ቅዱሳን ሲፈተሽ ፍርጃው ተገቢ አይደለም፡፡

የፍርጃውን አስገራሚ ገጽታ ጉልሕ የሚያደርገው ደግሞ «የሃይማኖት አክራሪነትና የፀረ አክራሪነት ትግላችን» በሚል ርእስ ለአመራር ሥልጠና በተዘጋጀው ሰነድ ላይ የሰፈረው አቋም ነው፡፡ የሥልጠና ሰነዱም ማኅበረ ቅዱሳንን ሲገልጸው፣ «ማኅበረ ቅዱሳን የእምነትነጻነትን፣ የሃይማኖት እኩልነትንና መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ መርሕ ይቃወማል»በማለት ነው፡፡

ዳሩ ግን ማኅበረ ቅዱሳን በሰነዱ ላይ እንደተቀመጠው የእምነት ነጻነትን፣ የሃይማኖት እኩልነትንና መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ መርሕ ሊቃወም ይቅርና እንዲያውም ሐመር መጽሔትና ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አለኝታነቱን አረጋግጠው በርእሰ አንቀጾቻቸው በተደጋጋሚ አስፍረዋል፡፡ ለዚህም የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣን 14ኛ ዓመት ቁጥር 21፣ ቅጽ 14 ቁጥር 121 ኅዳር 1999 ዓ.ም ዕትም ብቻ መመልከት በቂ ነው፡፡ አይደለም ማኅበረ ቅዱሳን ለመኾኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን «ክርስቲያናዊ መንግሥት» ብቻ የሚል አስተሳሰብ ያለው የት ነው? በሀገሪቱ ሕግም ኾነ በሃይማኖታቸው መሪ ተቋም ውስጥ ከማይተዳደሩትና በሌላ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ ዓለም ዓቀፍ የእስልምና አክራሪ ቡድኖች ጋራ ማኅበረ ቅዱሳን ተደምሮ የሚፈረጅበት መስፈርትም ግልጽ አይደለም፡፡

ማኅበረ ቅዱሳንና አባላቱ የተገነቡበት ሥነ ልቡና ለአክራሪነት የተመቸ አይደለም

በርግጥ የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም ከመስከረም 1 – 15 ቀን 2002 ዓ. ም. ለኅትመት በዋለችው ስምዐ ጽድቅጋዜጣ ላይ እንዳመለከቱት፣ «አክራሪ» ማለት የሃይማኖቱን ሕግ አክብሮ የሚኖር፣ ተግቶ የሚጾም፣ የሚጸልይ፣ በሃይማኖቱ ላይ ለሚነሡ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥና ታሪኩንና ቤተ ክርስቲያኑን የሚወድ፣ ለሃይማኖቱ የሚቀና፣ የማይዋሽ ወይም ወደ ከፍተኛ ሥነ ምግባራዊ ሕይወት ራሱንም የሃይማኖት ወገኑን ሁሉ ለማድረስ የሚተጋ ከኾነ የማኅበራችንን አባላት ሊገልጽ ይችላል፡፡ ሰዎች ምናልባት በልማድ በዚህ ብያኔ ለመጥራት ፈልገው ከኾነ ችግር ላይኖረው ይችላል፤ ነገር ግን በዚህ ኹኔታ የሚመላለሱት ክርስቲያኖች «አክራሪ» እያሉ ከማጥላላት ይልቅ አጥባቂ፣ ዐቃቤ ሃይማኖት፣ ቀናዒ ቢባሉ የተሻለ እንደኾነ እሙን ነው፡፡

በሌላ በኩል ግን «አክራሪ» የሚለው ቃል በሰነዱ ላይ እንደተቀመጠው፣ «አብያተ ክርስቲያናትንና ገዳማትን ለፖሊቲካ ዓላማ ጥቅም ላይ ማዋል፣ ከተቃዋሚ የፖሊቲካ ድርጅቶች ጋር በመተሳሰር ፀረ መንግሥት ቅስቀሳና አድማ ማስተባበር፣ በሃይማኖቶች መካከል የከረረ ጥላቻን በመዝራትና በማስተጋባት በሕዝብ ውስጥ የመተማመን፣ የመከባበርና የመቻቻል ዕሴት እንዲሸረሸር ሌት ተቀን መረባረብ» ከኾነ ግን ከማኅበራችን አቋምና ከአባሎቻችን ሥነ ልቡና እጅግ የራቀ አሉባልታ ነው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ፀረ መንግሥት ቅስቀሳና አድማ ሊያደርግ ይቅርና በጅማና ኢሉ አባቦራ አክራሪዎች በክርስቲያኖች ላይ ግድያ በፈጸሙበት ወቅት በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 14ኛ ዓመት ቁጥር 21፣ ቅጽ 14 ቁጥር 121 ኅዳር ዕትም ላይ የወቅቱ መልእክት ያለው ዜናና ርእሰ አንቀጽ ጽፏል፡፡ ርእሰ አንቀጹ የመንግሥትንም ጥረት የሚያሳይና ለወደፊቱ መንግሥት፣ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ማድረግ ያለባቸውን የሚጠቁም ነበር፡፡

በዜናውም የመንግሥትን ጥረት «የሕዝቡን ሰላም በሚያደፈርሱ ኀይሎች ላይ መንግሥትና ኅብረተሰቡ የተጠናከረ ርምጃ እየወሰዱነው፡፡ . . . በጅማና ኢሉ አባቦራ አህጉረ ስብከት አንዳንድ ወረዳዎች በተከሰተው ግጭት ለችግሩ መንሥኤ ናቸው የተባሉትምሕግ ፊት እየቀረቡ ነው» በማለት ነበር የገለጸው፡፡ እንዲህ የዘገበው ማኅበር ነው እንግዲህ ፀረ – ሕገ መንግሥት የተባለው፡፡ እንዲህ አድርጎ ከፈረጀ ማኅበረ ቅዱሳን በኀይል እስላሞችን ወይም ፕሮቴስታንቶችን ኦርቶዶክስ አድርጓል? መስጊድ አቃጥሎ እስላሞችን ወይም የማምለኪያ ቦታዎችን አቃጥሉ ፕሮቴስታንቶችን ገድሏል? ለሚሉ ጥያቄዎችም መልስ መስጠት ይገባ ነበር፡፡ አለበለዚያ የመንግሥት አካሂደዋለኹ የሚለው የፀረ አክራሪነት እንቅስቃሴ በመንግሥት መርሐ ግብር ተጠቅመው ስውር ዓላማቸውንና ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም የተዛባ ፍረጃና የተሳሳተ አቻ ፈጠራ ላይ ለተሰማሩ አካላት መሣርያነት አለመጋለጡን በምን ማረጋገጥ ይቻላል?

ይኹንና ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካል በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቀ ሕግና መተዳደሪያ ደንብ ያለው የቤተ ክርስቲያኒቱ አካል እንጂ ሌላ የእምነት ጽንፍ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ የምታውቃቸው ጋዜጣ፣ መጽሔትና መካናተ ድሮች አሉት፤ ምን እንደሠራም በግልጽ ማየት ይቻላል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን እንደተፈረጀው ሳይኾን መቻቻልን በተመለከተ ከማኅበሩ ሚዲያዎች ቀድሞ የዘገበ ነበር ለማለትም የሚቻል አይመስለንም፡፡

በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ጥቅምት ወር 1999 ዓ.ም ዕትም በጅማና በኢሉ አባቦራ የደረሰውን ጥቃት በዜናው ዘግቦ ነበር፡፡ ማኅበሩ ይህን ያደረገው ጥቃቱ በቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈጸመ በደል ስለኾነ ብቻ አይደለም፡፡ አንድን ነገር እየሰሙ እንዳልሰሙና እንደሌለ ከመቁጠር ይልቅ ችግሩን በትክክል አሳውቆ ለመፍትሔው መሥራት ይገባል ብሎ ስለሚያምን ብቻ ነው፡፡

በተጠቀሰው የጋዜጣው ዕትም ባወጣው ርእሰ አንቀጽም የቆየው የመቻቻል ባህል ዳብሮ እንዲቀጥል የሚጠይቅ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የአካባቢው የመንግሥት አካላት ሊፈጽሙት ይገባል የሚላቸውን ተግባራት በማመልከት የማኅበሩን አቋም አንጸባርቋል፡፡ በቀጣዩ ወር ኅዳር 1999 ዓ.ም ዕትም ግን በመቻቻል እንዴት መኖር እንደሚገባ የሚያሳይ ሰፊ ሽፋን ያለው ሥራ ተሠርቷል፡፡ የመቻቻልን ምንነት፣ በኢትዮጵያ የነበረውን ታሪካዊ ቦታና አስፈላጊነት በመተንተን የሁሉም ቤተ እምነት ተከታዮች በዚሁ ሀገራዊና መንፈሳዊ ባህላችን ጸንተው እንዲኖሩ የሚያግባባ ነበር፡፡ ርእሰ አንቀጹ ደግሞ ከላይ የተገለጹትን አሳቦች በማጽናት ተግባብቶና ተከባብሮ መኖር የሚያስገኘውን ጥቅም ካካተተ በኊላ ለዚህ ባለድርሻ የኾኑ አካላት ሁሉ ድርሻቸውን እንዲወጡ የሚጋብዝ ነበር፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን «በሃይማኖቶች መካከል የከረረ ጥላቻን ሊዘራና ሊያስተጋባ» ይቅርና ሁሉም የእስልምና ተከታዮች አንድ ዓይነትና አክራሪዎች አለመኾናቸውን የሚያሳዩ ሥራዎችን የሠራ ማኅበረ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ በስምዐ ጸድቅ ጋዜጣ ጥር 15 – 30 ቀን 2000 ዓ.ም በአርሲ የእስልምና ተከታዮች ለቤተ ክርስቲያን ግንባታ ያደረጉትን አስተዋፅኦ ከዘገበ በኋላ በርእሰ አንቀጹ ደግሞ የሁለቱን የእምነት ተከታዮች መረዳዳት አብነት በማድረግ ድርጊቱን አወድሷል፡፡

ከየካቲት 15 – 30 ቀን 2000 ዓ.ም ዕትም ደግሞ በወልቂጤ አካባቢ በቤተ ክርስቲያን ምረቃ ላይ ድንጋይ የወረወሩ አክራሪዎች ልጆቻቸውን ለሕግ አካላት አሳልፈው በመስጠት ለመቻቻሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉትን ሙስሊም ሽማግሌዎችን ድርጊት በአዎንታዊ ዘግቧል፤ ሥራቸውም ተወድሷል፡፡ ይህም መቻቻልን በተግባር ያሳየ ዘገባ ብቻ ሳይኾን የማኅበረ ቅዱሳን ትእምርተ መከባበር መኾኑንም ያሳየ ነበር፡፡

የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ቅዠት?

በርግጥ ማኅበሩ ወጣቱን በሃይማኖት አክራሪነት ይቀርጻልን የሚለውን ለመረዳት ሌላውን የማኅበሩን ሥራዎች ማየት የሚገባ ይመስለናል፡፡ ለአብነትም ማኅበረ ቅዱሳን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን የሚያስተምርባቸው ኻያ ያህል የመማርያ መጻሕፍት ታትመው አገልግሎት ላይ ከዋሉ ቆይተዋል፡፡ ትምህርቱ የሚሰጠው በይፋ በቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ሰው የኾነ ፍጡር ሁሉ ሊከታተለው የሚችለው ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ይፋዊ በኾነ መንገድ በሚሰጡበትና መጻሕፍቱን ሁሉ መመርመር በሚቻልበት ኹኔታ ያለምንም ማስረጃ «ወጣቶችን በሃይማኖት አክራሪነት ይቀርጻል» ማለት ስሕተት ነው፡፡

ይህን አገላለጽ የሚያይና የማኅበሩን ሥራ በርግጥ የሚያውቅ የዚህ አሳብ አፍላቂዎች በመንግሥት የፀረ አክራሪነት አጀንዳ አስታከው ማኅበረ ቅዱሳንና ቤተ ክርስቲያንን ለማሳጣት ወይም ለማጋጨት የተነሡና ሃይማኖታዊ መግፍኤ ያላቸው ኀይሎች ሊኾኑ አይችለምን? በርግጥ የማይኾኑበትስ ምክንያት ሊኖር ይችል ይኾን?

ቀደም ብለን እንደገለጽነው ማኅበረ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያን ትውልዱን በትምህርቷ ትዋጅ ዘንድ ሥርዐተ ትምህርት ቀርጾ ንጹሕ ቃለ እግዚአብሔር ብቻ የሚያስተምር ማኅበር ነው፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትን ይጠብቃል ተብሎ ይታማ ካልኾነ በቀር በአክራሪነት ሊወነጀል አይችልም፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን መዋቅራዊ ቁመና ለአክራሪነት ብቻ ሳይኾን ለፖሊቲካም የሚመች አይደለም፡፡ በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ መስከረም 1 – 15 ቀን 2002 ዓ.ም ዕትም ላይ የማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም እንዳመለከቱት፣ ማኅበሩ ሃይማኖታዊ አገልግሎት ለመስጠት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር የተቋቋመ የአገልግሎት ማኅበር ነው፡፡ ማኅበሩም እንደ ተቋም የሚሰጠው አገልግሎት ሃይማኖታዊ ነው፡፡ መቼም ቢኾን ለየትኛውም ዐይነት የፖለቲካ አደረጃጀት ለማገዝ/ለመሥራት ተቋማዊ ፍላጎት የለውም፡፡

በዚህ አጋጣሚ ማኅበሩ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ የገለጸውን አቋሙንም አስታውሶ ማለፍ የሚገባ ይመስላል፡፡ በአንቀጽ 5 ላይ «ማኅበሩበማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት አይኖረውም» በማለት ማኅበሩ ፖለቲካ ላይ ጣልቃ የማይገባ መኾኑን ይገልጻል፡፡ የዚህን አንቀጽ ይዘት ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል በማኅበሩ ያሉ የተወሰኑ አባላት በሓላፊነት ላይ እያሉ የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዳይሆኑ በ1998 ዓ.ም የሥራ አመራር ጉባኤው ወስኗል፡፡

በውሳኔውም መሠረት፡- የሥራ አመራር ጉባኤ አባላት፣ የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ አባላት፣ የኦዲትና ኢንስፔክሽን አገልግሎት ክፍልአባላት፣ የኤዲቶሪያል ቦርድ አባላት፣ መደበኛ መምህራን፣ የማኅበሩ ጋዜጠኞች፣ የማእከላት ሰብሳቢዎች በሓላፊነት እያሉየማንኛውም የፖለቲካ ፓ­ርቲ አባል መኾን አይችሉም፡፡ ስለኾነም ማኅበሩ እንደ ተቋም የትኛውንም የፖለቲካ አስተሳሰብ በመደገፍ ወይም በመቃወም ከ­ርቲዎች ጋር ግንኙነት ስለማይኖረው ለማንም ስጋት ወይም ዕድል ሊሆን የሚችል ተቋማዊ ምቹነት የለውም፡፡

ይህ ባይኾን ኖሮ ከመላዋ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና የተለያዩ ማኅበራዊ ዳራዎች የተሰበሰቡ አባላቱ በየትኛው የፖለቲካ አቋም ሊስማሙና ቤተ ክርስቲያንን ሊያገለግሉ ይችላሉ? የማኅበሩ አቋም ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት እንዳይኖረው የተወሰነው ግን ለዚህ ሲባል ብቻ አይደለም፡፡ በአንድ የፖለቲካ ፓ­ርቲ ውስጥ በርእዮተ ዓለም የተሰባሰቡ የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች ይኖራሉ/ፓ­ርቲው አክራሪ ሃይማኖታዊ ፓ­ርቲ እስካልኾነ ድረስ/፤ እንደዚሁ ሁሉ የተለያየ የፖሊቲካ አመለካከት ያላቸው ሰዎች የአንድ ቤተ እምነት ተከታዮች ይኾናሉ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም ሃይማኖታዊ ዕሴታቸውንና ለቤተ ክርስቲያናችን ማበርከት አለብን የሚሏቸው ዓላማዎች የሚያገናኟቸው ሰዎች የተሰበሰቡበት ማኅበር ነው፡፡ ስለዚህ ዓላማው አንድና አንድ ነው – ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ብቻ፡፡ ስለኾነም እንደ ማኅበር በየትኛውም የፖሊቲካ ርእዮተ ዓለም ላይ ጣልቃ ገብነት የለውም፤ ወደፊትም አይኖረውም፡፡

የብዥታው ምንጭና ምንነት

እውነታው ከላይ የተመለከትነው ከኾነ ማኅበረ ቅዱሳን «አክራሪ» ያሰኘው የብዥታው ምንጭና ምንነት ምን ይመስላል? የሚለው ሌላው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡
የመጀመሪያው፦ የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን የተሳሳተ መረጃ ነው፡፡ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ንጽሕት ርትዕት የኾነችውን እምነትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ህልውና ለማጥፋት በመፈታተን ለዘመናት ሌት ተቀን ሳያቋርጡ እንደሚጥሩት ሁሉ፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጅ የኾነው የማኅበረ ቅዱሳንን ቅን መንፈሳዊ አገልግሎትም እንዲኖር አይፈልጉም፡፡ በተለይም በክርስትና ስም እንቀሳቀሳለን የሚሉ የተለያዩ የእምነት ድርጅቶችና የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ አራማጆች ሁሉ፣ ከውጭም ኾነ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጉያ ውስጥ ኾነው የሚያደርሱትን ጥቃትና ቡርቦራ በመከላከል፣ ለቤተ ክርስቲያን አባቶችና ለምእምናን በማሳወቅ የሚያደርገውን ቀና ጥረት በሚገባ ያውቁታል፡፡

በጌታችንና በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሠረት ላይ ጸንታ በእርሱ ጥበቃ የምትኖረውን ቤተ ክርስቲያን በመፈታተን እኩይ ዓላማቸውን በፈለጉት መጠን እንደልባቸው ለማሳካት አለመቻላቸውን ተረድተውታል፡፡ ለእኵይ ተግባራቸው እንቅፋት የኾነውን ማኅበር ንጹሕ መንፈሳዊ አገልግሎት ለማስቆም ባገኙት አጋጣሚና መድረክ ሁሉ የተሳሳቱና የተፈበረኩ መረጃዎችን ይሰጣሉ፡፡ የፍረጃው ምንጭ ይኸው የተሳሳተና የተፈበረከ መረጃ ነው፡፡
የማኅበረ ቅዱሳንን አገልግሎት ለማስተጓጎል የሚጣደፉት እነዚህ የኑፋቄና የጥፋት ኀይሎች በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅሮች ውስጥ ሓላፊነት ይዘው ቤተ ክርስቲያንን ለሚያጠፉ አካላት የማይታይ ስውር እጅ ኾነው ለመሥራት እየሞከሩ ያሉግለሰቦችና ቡድኖች ማኅበረ ቅዱሳን የተለየ አጀንዳ ያለው ይመስል ስጋት ኾኖ እንዲታይ ያልፈነቀሉት ድንጋይ፣ ያልወጡት ዳገትናያልወረዱት ቁልቁለት የለም፡፡

የራሳቸው ጥቅምና ክብር እንጂ የቤተ ክርስቲያን ንጹሕ ዓላማ የማይታያቸው እነዚህ በእሳት የሚጫወቱ ግለሰቦችና ቡድኖች ሲፈልጉ በጥርጣሬ፣ በመመሪያና ደንብ፣ ሲያሻቸው ደግሞ ስም በማጥፋትና በአባላቱ መካከል መለያየት ለመፍጠር በመሞከር. . . ወዘተ ማኅበረ ቅዱሳንን መቅበር፣ በመቃብሩም ላይ መቆም፤ ከዚያም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አንድነትና ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል ያደረጉት እንቅስቃሴ ሁሉ በእነርሱው ቋንቋ «በማኅበሯ» ሲከሽፍባቸው መንግሥት ታላቅ ሓላፊነት ያለበት አካል እንደ መኾኑ መጠን የሚመች ቦታ ይዘው የራሳቸውን ውስጣዊ ፍላጎት በመንግሥት መርሐ ግብር አሳዝለው ማኅበሩን ያስመታልናል የሚሉትን የሐሰት መረጃ መፈብረክ ተያይዘውታል፡፡

በጥቅሉ የመናፍቃኑንና ቤተ ክርስቲያንን እናድሳለን ብለው የተነሡት የመናፍቃኑ ተላላኪ ቡድኖች ሤራና የአክራሪ እስልምናን እንቅስቃሴ በመረጃ አስደግፎ በማጋለጡ፣ ከክፉ ትምህርታቸው መመለስ ያልፈለጉ የተሐድሶ ኑፋቄ ቡድን አባላት ከቤተ ክርስቲያን ተወግዘው እንዲወጡ ስለተወሰነባቸውና ሌሎችንም የቤተ ክርስቲያን ችግሮች እየተከታተለ ለዕድገቷና ብልጽግናዋ በመሥራቱ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ወዳጆች ማፍራት መቻሉ የእግር እሳት የኾነባቸው አካላት የፍረጃ ውጤት ነው የማኅበሩ «አክራሪ» መባል፡፡

ሁለተኛው፦ የተሳሳተ አቻ ፈጠራ የወለደው ብዥታ ነው፡፡ አንዳንድ የመንግሥት ተቋማትና ሓላፊዎች አንድን ችግር ለመፍታት ሲሉ ሚዛን የጠበቁና የማያደሉ የሚባሉ እየመሰላቸው ማኅበረ ቅዱሳንን ለወሃቢያ የተሳሳተ አቻ ፈጠራ አክራሪ ማለታቸው ሌላው የብዥታው ምንጭ ነው፤ ነገር ግን ይህ ፈጽሞ አግባብ አይደለም፡፡ ከዚህም ውጭ የተሰጣቸውን መንግሥታዊ ሓላፊነት ዘንግተው በራሳቸው የሃይማኖት አመለካከት ምክንያት የማኅበሩን መኖር የማይፈልጉ አካላት የሰጡት መረጃ ሊኾን እንደሚችል መጠርጠር፣ የመረጃውን ፍሰት/አካሔድ/ መመርመርና ተገቢውን እርምት መውሰድ አለመቻልም ለብዥታው መነሻ ነው፡፡

ሦስተኛውና የመጨረሻው፦ የብዥታው ምንጭ፣ ማኅበረ ቅዱሳን «እውነት ነጻ ያወጣችኊል» በሚለው የወንጌል ቃል መሠረት አሉባልታውን ሁሉ እየተከተለ በወቅቱ ምላሽና አጸፋ አለመስጠቱ ነው፡፡ በጊዜ ሒደት ግን የመረጃውን ስሕተት ከማኅበሩ እውነተኛ ማንነት ጋራ አለመግለጻችን ራሳችንን ለከሳሾቻችን የፈጠራና የተሳሳተ መረጃ ረዳት አድርጎ ሊያስቆጥረን ይችል ይኾናል፡፡ የኾነው ኾኖ ማኅበሩ እንደ እምነት የአገልግሎት ተቋምነቱ ላልሠራው ሥራ አይጨነቅም፤ ጊዜ ይወስዳል እንጂ እውነቱን ደግሞ ማንም አይደብቀውም፡፡

ጌታ በወንጌል እንደተናገረው «የማይገለጥ የተከደነ፣ የማይታወቅ የተሰወረ ምንም የለምና» /ማቴ. 10፥26/ የሁሉንም ስውር ተንኮል እግዚአብሔር በጊዜው ጊዜ ይገልጠዋል፡፡ ያን ጊዜ ማኅበሩ ማን እንደኾነም በእውነት ይታያል፡፡ በዚያን ጊዜ ሁሉም የዘራውን ያጭዳል፡፡ ጠብ እየዘራ ያለ አካል ቢኖር እርሱ የጠብ ውጤት የኾነውን መከራ ከዘራው ዘር ማጨዱ አይቀርም፡፡

ከዚህ በኋላስ...

መንግሥት በየትኛውም የእምነት ተቋማት አሉ የሚላቸውን ችግሮች ማንሣቱ ወይም ተቋማቱ ራሳቸው እንዲፈቱ እገዛ መስጠቱ የሚያስመሰግነው ተግባር ነው፤ ነገር ግን የሚያሰራጫቸው መረጃዎች ይህን ተግባሩን ጥያቄ ውስጥ እንዳይከቱት መጠንቀቅ ብቻ ሳይኾን ማስተካከያ ሊሰጥበትም ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ መፍትሔው መፍትሔ መኾኑ ቀርቶ ለችግር ፈጣሪዎቹ ከለላ ሰጭ እንዳይኾን ያሰጋል፡፡

ሃይማኖታዊ ጉዳይ በተፈጥሮው ውስብስብና በእጅጉ ጥንቃቄ የሚፈልግ ነው፡፡ በኻያኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛው አጋማሽ ላይ በሕንድና ቀደም ብሎም በግሪክ የመንግሥትን ኃይል ተጠቅመው በእውነኞቹ አማኞች ላይ ታላቅ ጥፋት ካደረሱት ውስጥ የአንዳንዶቹን አካላት ታሪክ ማየትም ለእኛ ምሳሌ ሊኾነን ይችላል፡፡ የተሰጣቸውን ሓላፊነት በመጠቀምና የተሳሳተ መረጃ በማቀበል የመንግሥትን አግባብነት ያለው የፀረ አክራሪነት እንቅስቃሴ ከትክክለኛው አቅጣጫ ሊያስቱ የሚችሉ አካላት መሣሪያ እንዳያደርጉት ስጋታችን ታላቅ ነው፡፡ ሐሰት ተደጋግሞ በመነገሩ እውነት ቢመስልም በፍጹምና መቼም እውነት ሊኾን አይችልም፡፡

በሌላ በኩል፣ ሚዛን ለመጠበቅ በሚል ስሜት ሁሉንም አንድ ዓይነት ጥፋት እንዳጠፉ አድርጎ መመልከትና መግለጽም መቆምይኖርበታል፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት ለተለያየ ዓላማ ከሚያወጣቸው ይፋዊ ሰነዶች ጥናትን መሠረት ያደረጉ መረጃዎች ብቻ ይጠበቃሉ፡፡ ለምሳሌ፣ በሃይማኖታዊ ጉዳይ ላይ የተጻፉ ጸሑፎችን በሙሉ ሰብስቦ አጥንቶና ገምግሞ ማውጣት ቢቻል ሕዝቡንም በአግባቡለማስረዳት ይጠቅማል፡፡ ማን መጀመሪያ ምን ብሎ በሌላው እምነት ላይ ጻፈ? የትኞቹ ምላሾች ናቸው? የትኞቹስ የትንኮሳ ጽሑፎች ናቸው? ሌላው ቀርቶ ሃይማኖትን ለማሳመን፣ ሌላውን ለማስረዳት አልያም ለማጣጣል ብቻ የተደረጉት ላይ ቢጠና እንደ ዘይትና ውኃ ተለይተው ከሩቅ የሚታዩ ናቸው፡፡ ነገር ግን ሁሉንም በአንድነት በመፈረጅና በሕግ የተቋቋመውን ካልተቋቋመው እየደባለቁ በመናገር የተፈጸመን ድርጊት ሁሉ በአንድ ላይ በመጫንና በመለጠፍ ውጤት ማምጣት እንደማይቻል ይታወቃል፡፡

ስለዚህ በቂ ማስተካከያዎችና እውነተኛ ገጽታን የሚገልጹ ሥራዎች ለዛሬ ባይደርሱ ለነገ ይጠበቃሉ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም የሃይማኖት አክራሪነትን መቃወም ብቻ ሳይኾን በጽኑ ያወግዛል፤ ማኅበረ ቅዱሳን የሃይማኖት አክራሪነት ሳይኾን የሃይማኖት አጥባቂነት ትእምርት ነውና!!

ተያያዥ መጣጥፎች
ክርስትና "አክራሪነት"ን የሚያበቅል ነገረ ሃይማኖታዊ መሠረት የለውም

ማኅበረ ቅዱሳን አክራሪ ሁኖ የገደለው ሰው የለም

ቀጣዩ የኢሕአዴግ ዒላማ ማኅበረ ቅዱሳን ይኾን?




                                             ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Saturday, October 5, 2013

ዘመነ ጽጌ

ከገነት የተሰደደውን አዳምን ወደ ቀደመ ክብሩና መንበሩ ከዚያም ወደ ሚበልጥ ክብር ለመመለስ የተወለደው ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ገና ከህፃንንቱ ጀምሮ ስደትን እና መከራን ተቀብሏል፡፡
ጌታ ሲወለድ ሰብአ ሰገል «የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት አለ? በምሥራቅ ኮከቡን አይተን ልንስግድለት መጥተናል» እያሉ በኮከብ እየተመሩ በመጡ ጊዜ በይሁዳ፣ በገሊላና በሰማርያ የሮማውያን ተወካይ የነበረው ንጉሥ ሄሮድስ የጌታችን ንግሥና ምድራዊ ንግሥና መስሎት መንግስቴን ሊቀማኝ ነው ብሎ ደነገጠ፡፡ ፊሪሳውያን «መሲህ ተወልዶ ከሮማውያን አገዛዝ ነጻ ያወጣናል፡፡» ብለው ያምኑ እንደነበር ስለሚያውቅም ይህ የተፈጸመ መስሎት ጭንቀቱ በረታ፡፡ የተወለደውን ሕፃንም ለመግደል ተነሳ፡፡
ስለዚህም ሰብአ ሰገልን አስጠርቶ «ሂዱ ሕፃኑን ፈልጉ ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔም እንድሰግድለት ወደ እኔ ተመልሳችሁ ያለበትን ንገሩኝ» በማለት በሽንገላ ተናገራቸው፡፡
ጠቢባኑም ከሄሮድስ ከተለዩ በኋላ በኮከቡ እየተመሩ ጉዞአቸውን ቀጥለው ጌታችንን ከእናቱ ጋር አገኙት ፤ ተንበርክከው ሰገዱለት፤ ወርቅ ፣ ዕጣን፣ ከርቤ እጅ መንሻ አቀረቡለት፡፡

የእግዚአብሔር መልአክ ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ፤ ነገር ግን መንገድ ቀይረው ወደ ሀገራቸው እንዲሄዱ በነገራቸው መሠረት በሌላ መንገድ ወደ መጡበት ተደብቀው ተመለሱ፡፡

«እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ «ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነስ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሸ፤ እስክነግርህም በዚያ ተቀመጥ አለው፡፡ » /ማቴ. 2 13 14/

ዮሴፍም ተነሣ፤ በዕድሜዋ በጣም ልጅ የነበረችው እመቤታችን ገና የተወለደውን ሕፃን አቅፋ የምትቀመጥበት አህያም ተዘጋጀ፡፡ ጉዞአቸውን ጀመሩ፡፡ ከእስራኤል ወደ ግብጽ በእግር ለመሔድ የሲናን በረሃ ማለፍ የግድ ነው፡፡ በዚያን ዘመን ከእስራኤል ወደ ግብጽ የሚወስዱ ሦስት የተለያዩ መንገዶች ነበሩ፡፡ በሽፍቶች ላለመጠቃት መንገደኞች በቡድን በቡድን ሆነው በእነዚህ መንገዶች ይሔዱ ነበር፡፡

እነርሱ ግን ንጉሥ ሔሮድስ ተከታትሎ ሊይዛቸው ስለሚችል በእነዚህ መንገዶች መሔድ እንደሌለባቸው ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህም በእግዚአብሔር መልአክ እየተመሩ ባልታወቁ መንገዶች መሔድ ነበረባቸው፡፡ ለበርካታ ቀናትና ሳምንታት ሸለቆዎችን በመውረድና ኮረብታዎችን እየወጡ ጉዛአቸውን ቀጠሉ፡፡ ሽማግሌው አናጢ ዮሴፍ ከፊት ሁኖ አህያዋን ባልተስተካከለውና ማለቂያ የሌለው በሚመስለው የበረሃ መንገድ ላይ ይመራ ነበር። ሰሎሜም ስንቃቸውን ይዛ ከኋላ ትከተል ነበር፡፡ በጣም አስቸጋሪ እና አስጨናቂ ጉዞ ነበር፡፡ ቀን ቀን የሚያቃጥለውን የፀሐይ ሐሩር ሌሊት ሌሊት ደግሞ የበረሀውን ውርጭ /ብርድ/ መታገል ነበረባቸው ምግባቸውንም በተአምራት ያገኙ ነበር፡፡

በመጨረሻም በመጽሐፈ ስንክሳር እንደተመዘገበው ግንቦት 24 ቀን ግብጽ ደረሱ፡፡ በግብጽም ባሉ የተለያዩ ከተሞች ተዘዋወሩ፣ ጌታም በተለያዩ ቦታዎች በርካታ ተአምራትን አደረገ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ተቀብለው ሲያስተናግዷቸው ሌሎች ደግሞ አሳደዋቸዋል፤ መከራንም አጽንተውባቸዋል፡፡ በዚሁ ስድታቸው ወቅት ጌታ እና እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያም መጥው ሀገራችንን ባርከዋል።

ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል በስደት ከቆዩ በኋላ ሄሮድስ ሞተ። ሄሮድስም ከሞተ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ «የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ አለው፡፡ እርሱም ተነስቶ ሕጻኑንና እናቱን ይዞ ወደ እስራኤል ሀገር ገባ» ማቴ 2-19-21/

ቅዱስ ዮሴፍ ይህንን «.. ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ..» የሚለውን የመልአኩን ቃል የሰማው ቁስቋም በምትባል በግብጽ ባለች ቦታ ነው፡፡

በኋላ በዚህች ቦታ ላይ የእመቤታችን ቤተክርስቲያን ተሰርቶ ቅዳሴ ቤቱ ኅዳር 6 ቀን ከብሯል። ሃያ ሦስተኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ቴዎፈሎስ /384-412 ዓ.ም/ ደግሞ በጌታ እና በእመቤታችን ስደት ወቅት የሆነውን ነገር እንዲገለጥለት ለብዙ ጊዜ ጸሎት ካደረገ በኋላ ህዳር 6 ቀን እመቤታችን ተገልጣለት በጉዞው ወቅት የሆነውን ነገር ሁሉ ነግራዋለች፡፡ ስለዚህ ኅዳር 6 ቀን በሁሉም ምሥራቃውያን አብያተ ክርስቲያናት የእመቤታችን ከስደት የመመለሷ ነገር የሚታሰብበት ሁኗል፡፡

በሀገራችን መስከረም 25 ቀን ዘመነ ክረምት አልፎ መስከረም 26 ቀን ዘመነ ጽጌ ይጀምራል፡፡ ጽጌ ማለት አበባ ማለት ሲሆን ዘመነ ጽጌ ማለት የአበባ ዘመን ማለት ነው፡፡ ዘመኑ አበቦች የሚያብቡበትና ሜዳዎችንና ተራሮችን የሚያስጌጡበት ዘመን ነው፡፡ ፍሬ የተባለ ጌታን ያስገኘች እመቤታችን በአበባ ትመሰላለችና ዘመኑ የጌታንና የእመቤታችንን ነገር በአበባና በፍሬ ለመመሰል የተመቸ ነው፡፡

ስለዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከመስከረም 26 ቀን ጀምሮ እስከ ኅዳር 6 ቀን ድረስ የጌታን እና የእመቤታችን ስደት ታስባለች፡፡

በዚህ ዘመን ቅዱስ ያሬድ እና አባ ጽጌ ድንግል ባዘጋጇቸው ድርሰቶች የጌታችን እና የእመቤታችን ስደት በማኅሌት ይታሰባል፤ ምስጋና እና ልመና ይቀርባል። እነዚህን ለየሳምንቱ በሚዘጋጁት ትምህርቶች እናቀርባቸዋለን፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ስደቱን ለማሰብና በረከት ለማገኘት በርካታ ክርስቲያኖች ዘመኑን በጾም ያሳልፉታል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በማቴዎስ ወንጌል ትርጓሜው /Homilies on the Gospel of Saint Mathew/ ይህንን ስደት አስመልክቶ ያስተማረውን ትምህርት ከዚህ ቀጥለን አቅርበናል፡፡

ሰብአ ሰገልም ከሄዱ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በህልም ለዮሴፍ ተገልጾ፡- ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሳና ሕፃኑን ከእናቱ ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ እስክነግርህም ድረስ በዚህ ተቀመጥ አለው እርሱም ተነስቶ ሕፃኑና እናቱን ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው ይፈጸም ዘንድ ወደ ግብፅ ሄደ። ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ።

ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደተሳለቁበት ባወቀ ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ /ጌታን ለማስገደል በማሰብ / ጌታ በተወለደባት ከተማ በቤተልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን ሕጻናትን አስገደለ፡፡ /ማቴ. 1.13-18/

እዚህ ላይ ሕፃኑን በተመለከተና ሰብአ ሰገልን በተመለከተ ልንጠይቃቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡ ለምን ሰብአ ሰገልም፣ ሕፃኑም /ጌታም/ በዚያው አልቆዩም? ለምን እነርሱ እንደ ተሳዳጅ /fugitive/ በድብቅ ወደ ፋርስ፣ እርሱም ከእናቱ ጋር ወደ ግብፅ ሄዱ?

ከዚህ ሌላ ምን መደረግ ነበረበት? ጌታ በሄሮድስ እጅ መውደቅና ከዚያ አለመገደል ነበረበት? እንዲህ ቢያደርግም ኖሮ ሥጋን መዋሃዱ ግልጽ አይሆንም ነበር፡፡ የክርስቶስ የማዳን ሥራም አይታመንም ነበር፡፡

ሥጋን መዋሃዱን የሚያሳዩ ይህን የመሳሰሉ በርካታ ነገሮች ተደርገው፣ ሥጋን ለበሰ /ተዋሃደ/ መባሉ ተረት /ውሸት/ ነው የሚሉ ካሉ ሁሉን ነገር እንደ አምላክነቱ ብቻ ቢያደርገውማ ከእነዚህ የሚበልጡ ብዙዎች በተሳሳቱ ነበር፡፡

ሰብአ ሰገልንም በፍጥነት የላካቸው አንደኛ ለፋርስ ሰዎች መምሀራን እንዲሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጌታን ለማስገደል ላሰበው ሄሮድስ እየሞከረ ያለው የማይቻል ነገርን መሆኑን አስረድቶ የሄሮድስን እብደት ለማቆምና ንዴቱን አስታግሶ ከከንቱ ድካሙ እንዲያርፍ ለማድረግ ነበር፡፡

ምክንያቱም አምላካችን ጠላቶቹን በግልጽ እና በኃይል ማስገዛት ብቻ ሳይሆን በቀላል እና ትንሽ በሚመስሉ ነገሮች ማሳመንም፣ ያውቅበታል፡፡

ለምሳሌ ግብጻውያንን በግልጽ /በኃይል/ ንብረታቸውን ለእስራኤል እንዲያስረክቡ ማድረግ ሲችል እርሱ ግን በጥበብ ያለ ጦርነት ይህንን እንዲያደርጉ አድርጎአቸል፡፡ ይህም አድራጎቱ ከሌሎቹ ተአምራት ባልተናነሰ ሁኔታ በጠላቶቹ ዘንድ የሚፈራ አድርጎታል፡፡

ለምሳሌ ፍልስጤማውያን ታቦተ ጽዮንን ማርከው በመውሰዳቸው በተቀጠቀጡ ጊዜ የሀገራቸውን ጠቢባን ከእግዚአብሔር ጋር ለመዋጋት እንዳይሞክሩ በነገሯቸው ጊዜ ከሌሎች ተአምራት ጋር ይህንን እግዚአብሔር በሥውር የሠራውንም ሥራ አንስተውታል፡፡ በግልጽ ከተደረጉት የተለየ አድርገው አላዩትም፡፡ 1ኛ ሳሙ. 6-6

በዚህ ጊዜም የተደረገው ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ደም የጠማውን ነፍሰ ገዳይ ሊያስደንቅ የሚችል ነገር ነበር፡፡ ሄሮድስ ሊያስብ የሚገባው እንዲህ ነበር፡፡ ሰብአ ሰገል እንደካዱት፣ እንደተናቀና መሳቂያ መሳለቂያ እንደሆነ ባወቀ ጊዜ መደንገጥ ትንፋሹ መቆም ነበረበት፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ካላሻሉት /ካላስተካከሉት/ ግን እርሱን ከጥፋቱ ለመመለስ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ያደረገ እግዚአብሔር በእርሱ ጥፋት ሊጠየቅ አይችልም፡፡ ሄሮድስ ከዚህ በኋላ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ ያደረገው የእብደቱ ብዛት እነዚህ ሁሉ እውነተኛ ግልጽ ነገሮች እንዲያሳምኑት ስላላደረገ ነው፡፡ ስለዚህ ከጥፋቱ መመለስ አልቻለም፡፡ በክፋቱ ስለ ቀጠለበትም ስለ ሞኝነቱ የከፋ ቅጣት ተቀብሏል፡፡

ሕፃኑ ለምን ወደ ግብጽ ሄደ? የመጀመሪያውን ምክንያት ወንጌላዊው ራሱ በግልጽ ይነግረናል፤ «ልጄን ከግብጽ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብጽ ሄደ» /ማቴ. 1-15/

ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ድርጊት ለዓለም መልካም ተስፋ ተሰብኳል፡፡ በዚያን ጊዜ በዓለም ካለው ቦታ ሁሉ በከፋ ሁኔታ ባቢሎን /ፋርስ/ እና ግብጽ በእምነተ ቢስነት /በአምላክ አልባነት/ ነበልባል ተቃጥለው ነበር፡፡ እርሱም ከመጀመሪያው ሁለቱንም እንደሚያስተካክል ምልክት ሰጥቶ ሰዎችን ማዳኑ /ስጦታዎቹ/ ለዓለሙ በሙሉ እንደሆኑ አውቀው በተስፋ እንዲጠብቁ አደረጋቸው፡፡ ለዚህም ወደ አንዱ /ባቢሎን፣ ፋርስ/ ሰብአ ሰገልን ላከ፣ ሌላውን /ግብጽን/ ራሱ ከእናቱ ጋር ጎበኘ፡፡

ከዚህም ሌላ በዚህ የምንማረው ሌላ ትምህርት አለ፤ ከፍ ያለ ጽናት ሊኖረን እንደሚገባ፡፡ ይህ ምን ዓይነት ነው? ክፉ ሃሳብ /ተንኮል/ እና ክፉ ድርጊት ገና በመጠቅለያ ካለበት ጊዜ ጀምሮ በእርሱ ላይ እንደሆነ ተመልከቱ፡፡ በልደቱ ጊዜ መጀመሪያ ክፉ ነፍሰ ገዳይ፣ ተነሳበት ከዚያም ስደት እና ሀገርን ትቶ መሄድ ተከተለ፡፡ ያለ ምንም ጥፋትና በደል ከቤቷ እንኳን ርቃ ተጉዛ የማታውቀው እናቱ ወደ አረመኔዎች /barbarians/ ሃገር ተሰደደች፡፡ አስጨናቂና አስቸጋሪ የሆነ ረጅም ጉዞ እንድታደርግ ታዘዘች፡፡ ይህንን የሰማ ሰው መንፈሳዊ አገልግሎት ሲፈጽም አስጨናቂ ችግሮችና ህመሞች ቢደርሱበትና ህመሞች ቢያጋጥሙት መሸበር የለበትም፡፡

«የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ስለፈጸምኩ መሸለም መከበርና ታዋቂ መሆን ሲገባኝ ለምን ይህ ሆነ?» ማለትም የለበትም፤ ነገር ግን ሁላችንም ይህንን እንደ ምሳሌ ወስደን ሁሉን ነገር በደስታ መቀበል አለብን፡፡ መንፈሳዊ ነገሮች ባሉበት ሁሉ ተቃዋሚ እንደማይጠፋ እና የመንፈሳዊ ነገሮች ሂደትም ይህ መሆኑንም መረዳት አለብን፡፡

ቢያንስ ይህ ነገር የሆነው በሕፃኑና በእናቱ ብቻ ላይ ሳይሆን በሰብአ ሰገልም ላይ መሆኑን እናስተውል፡፡ እነርሱም እንደ ተሳዳጅ /fugitive/ ሆነው በምስጢር እንዲሸሹ ሆነዋል፡፡

ሌላም አስደናቂ ነገር ተመልከቱ፡፡ የእግዚአብሔር ሐገር፣ የተስፋ ምድር የተባለችው ፍልስጤም በጌታ ላይ የተንኮል መረብ /ሤራ/ ስትዘረጋ የኀጢአትና የጣኦት አምልኮ ሀገር የሆነችው ግብጽ ደግሞ ተቀብላ አዳነችው፡፡

ጌታችን በእግረ ሥጋ በተመላለሰባቸው ዘመናት ያደረጋቸው አብዛኞቹ ነገሮች ወደፊት ሊመጡ ላላቸው ነገሮች ትንቢት ናቸው፡፡

ዮሴፍ ጌታንና እናቱን ይዞ ወደ ግብጽ እንዲሄድ በመልአክ ታዘዘ፡፡ ግብጽ በሥፋት ጣኦት የሚመለክባት ሀገር ነበረች፡፡ ይህም በኋላ ክርስትና በአምልኮት ባዕድ ወደ ነበሩ ህዝቦች /አሕዛብ/ ዘንድ ለመውሰዷ ትንቢት /ምልክት/ነው፡፡ እመቤታችን ጌታን ይዛ ወደማታውቀው ሀገር ስትሰደድ ቤተልሄም /ይሁዳ/ ሄሮድስ ባስገደላቸው ሕፃናት በሰማዕታት ደም ተጥለቅልቃለች፤ የሄሮድስ ጭፍጨፋና ሕፃናቱን መግደሉ ወደፊት ክርስቲያኖች በአይሁድ እጅ ለሚቀበሉት ሰማዕትነት ምሳሌ ነው፡፡

መልአኩ ተገልጦ የተነጋገረው ከእመቤታችን ጋር ሳይሆን ከዮሴፍ ጋር ነበር፡፡ ምን አለው? «ተነሳ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ..» የእመቤታችን በግብረ መንፈስ ቅዱስ መጽነስ ሲነግረው ያለው «እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ» ነበር፡፡ አሁን ግን እጮኛህን አላለውም «የሕፃኑን እናት» አለው እንጂ፡፡ ምክንያቱም እመቤታችን ጌታችንን ከወለደች እና በጌታ ልደት ጊዜ የሆኑትን ነገሮች /ኮከቡን፣ ሰብአ ሰገልን/ ካየ በኋላ ሁሉን ነገር ተረድቶ ተረጋግጦ ነበር፡፡ በቂ ነገር ዓይቶ፣ ባየው ነገር ተረጋግቶ ነበር፡፡ ስለዚህ መልአኩ አሁን በግልጽ ይናገራል «ልጅህን» ወይም «እጮኛህን» አላለም፡፡ «ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሂድ አለው» እንጂ፡፡ የስደቱንም ምክንያት አብሮ ይነግረዋል፤ «ሄርድስ የሕፃኑን ነፍስ ይፈልጋልና፡፡»

ዮሴፍ ይህንን ሲሰማ ቅር አልተሰኘም፤ «ይህን ነገር ለመረዳት ይከብዳል፤ ሕዝቦቹን ያድናቸዋል አላለከኝም ነበር? አሁን ደግሞ ራሱን እንኳን ማዳን አይችልምን? እኛም ከቤታችን ወጥተን ርቀን ለብዙ ጊዜ መሰደድ አለብን አሁን ያለት ነገሮች ከተሰጠው ተስፋ /ቃል/ ጋር ተቃራኒ ናቸው፡፡» አላለም ጻድቅ እና እውነተኛ አማኝ ነበርና፡፡

ምንም እንኳን መልአኩ መመለሻውን ግልጽ ሳያደርግ እስከምነግርህ ድረስ በዚያው ተቀመጥ ቢለውም ስለሚመለሱበት ጊዜ አልተጨነቀም፤ አልጠየቀምም፡፡ ዮሴፍ ፍርሃትም እንኳን አላሳየም፡፡ ሁሉንም ነገር በደሰታ ተቀበለ እንጂ፡፡

ሰውን ወዳጅ የሆነው እግዚአብሔር መከራንና ደስታን በሰዎች ሕይወት ላይ ያመጣል፡፡ በችግር ወይም በደስታ ብቻ አያኖርም፡፡ ነገር ግን ሁለቱንም ችግርን /ሀዘንን/ እና ደስታን /ሃሴትን/ እያፈራረቀ ያመጣል፡፡ አሁንም ያደረገው ይህንኑ ነገር ነው፡፡ ዮሴፍ ድንግልን ጸንሳ ባያት ጊዜ ተጨነቀ፤ ተረበሸ፤ ታወከ፡፡ በዚህ መሃል ግን መልአኩ ተገልጦ ፍርሃቱን አስወገደለት፡፡ ሕፃኑን ተወልዶ ባየ ጊዜም ከፍ ያለ ደስታ ተደሰተ፡፡ ደስታው ብዙም ሳይቆይ አደጋ መጣ፤ በሰብአ ሰገል መምጣት ከተማው ተረበሸ ንጉሡም ከእብደቱና ከክፋቱ የተነሳ የተወለደውን ሕፃን ሊገድል ተነሳ፡፡ ይህ ጭንቀት ደግሞ በደስታ ተተካ ኮከቡና የሰብአ ሰገል ለጌታ መስገድ እጅግ አስደሳች ነበሩ፡፡ ከዚህ ደስታ በኋላም ጭንቀትና ፍርሃት መጣ፡፡ መልአኩ «ንጉሥ ሄሮድስ የሕፃኑን ነፍስ ይፈልጋል፡፡» ብሎ ነገረው፡፡

በዚህ ጊዜ ጌታችን በሕዝብ ፊት ተዓምራት ለማድረግ ጊዜው ገና ነውና መሰደድ አስፈለገው፡፡ ምክንያቱም ገና በልጅነቱ ተአምራትን በአደባባይ /በሕዝብ ፊት/ ቢያደረግ፣ ሥጋን እንደተወሃደ አይታመንም ነበር፡፡

በአንድ ጊዜ ሁሉን ማድረግ ሲችል ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅጸን ያደረው፣ እንደ ሕፃናት ጡትን እየጠባ፣ በጥቂት በጥቂቱ ያደገው፣ ሥራውን እስኪጀምርም ሠላውን ዘመን በዝምታ /በስውር ተዓምራት/ ያሳለፈው፡- የተዋህዶን ነገር እንረዳ ዘንድ ነው፡፡

አይሁድ ትንቢቱን በተመለከተ ጥያቄ ቢያነሱ እና ልጄን ከግብጽ ጠራሁት የተባለው ስለ እኛ ነው ቢሉን ይህ የትንቢት አካሄድ /መንገድ/ ነው እንላቸዋለን፡፡ ብዙ ጊዜ ስለተወሰኑ ሰዎች የተናገረው የሚፈጸመው በሌሎች ነው፡፡ ያዕቆብ ሊሞት ሲል ልጆችን ሰብስቦ በኋለኛው ዘመን ምን እንደሚደርስባቸው ሲነገራቸው እንዲህ ብሎ ነበር፡-

ስምኦንና ሌዊ ወንድማማች ናቸው፤

ሰይፎቻቸው የአመጽ መሣሪያ ናቸው፡፡

ከምክራቸው ነፍሴ አትግባ፡፡

ከጉባኤያቸውም ጋር ክብሬ አትተባበር

በቁጣቸው ሰውን ገድለዋልና

በገዛ ፈቃዳቸው በሬን አስነክሰዋልና፡፡

በያዕቆብ እከፍላቸዋለሁ፡፡ በእስራኤልም እበትናቸዋለሁ፡፡ ዘፍ. 49-7

ይህ ግን በእነርሱ አልተደረገም በልጆቻቸው እንጂ፡፡ በዘፍ. 9-25 ላይ ተጽፎ እንደሚገኘውም ኖህ እንዲህ ብሎ ነበር፡- «ከነአን ርጉም ይሁን ለወንድሞቹም የባሪያዎች ባሪያ ይሁን» ይህ የተፈጸመው በከንአን ሳይሆን በእርሱ ዘሮች ነው፡፡

ይህ መቼ እና እንዴት እንደሆነ በመጽሐፈ ኢያሱ እና በመጽሐፈ ዜና መዋዕል፤ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ እንዲህም ሆነ በዮርዳኖስ ማዶ በተራራማው በቆላውም በታላቁ ባሕር ዳርና ሊባኖስ ፊት ለፊት የነበሩ ነገሥታት ሁሉ ኬጢያዊ፣ አሞራዊም፣ ከነአናዊም፣ ኢያቡሳዊም፣ ይህን በሰሙ ጊዜ ኢያሱንና እስራኤልን ሊወጉ ወጡ፡፡

በዚያም ቀን ኢያሱ ለማኅበሩ በመረጠው ሥፍራ እስከ ዛሬ ድረስ፣ ለእግዚአብሔር መሠዊያ እንጨት ቆራጮች ውኃም ቀጂዎች አደረጋቸው፡፡ /ኢያ. 9-1-27/

1ኛ ዜና.8-7 ሰሎሞንም ኬጤያውያንንም፣ አምራውያንንም፣ ፌርዜያውያንንም ኢያቡሳውያንንም የቀሩትን ከእስራኤል ወገን ያልሆኑትን ሕዝብ ሁሉ... ገባሮች አድርጎ መለመላቸው፡፡

ይስሐቅ «ለወንድሞችህ ጌታ ሁን፡፡ የእናትህም ልጆች ይስገዱልህ»፡፡ ብሎ ያዕቆብን የመረቀው ምርቃት የተፈፀመው በእርሱ ሳይሆን በልጆቹ ነው፡፡ ዘፍ. 27-19

ስለዚህ እርሱ ባይወለድ ኖሮ፣ ትንቢቱ ፍጻሜውን አያገኝም ነበር፡፡ ወንጌላዊውም ያለውን አስተውሉ፡- «ይፈፀም ዘንድ፡፡» ይህም እርሱ ባይመጣ አይፈፀምም ነበር ማለት ነው፡፡

በዚህኛውም ጊዜ የተደረገው /የሆነው/ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር ነው፡፡ መጀመሪያ ለእስራኤል የተነገረው ነገር በኋላ በጌታ ተፈጽሟል፡፡ ደግሞስ የእግዚአብሔር እውነተኛ ልጅ ሊባል የሚችለው የትኛው ነው? ጥጃን ያመለከና ለቤልሆር ልጆቹን የሰዋ? ወይስ በባሕሪው ልጅ የሆነና የወለደው አባቱ «የምወደው ልጄ» ብሎ የሚያመሰግነው?

ከዚህም ሌላ /ግብጽ መሄዳቸው/ እመቤታችን ከፍ ያለ ክብር ያላት እንደሆነች እንዲታወቅ ተደርጓል፡፡ ህዝቡ የሚመኩበትን ከእግዚአብሔር ያገኙትን ስጦታ እርሷም ለራሷ አግኝታለችና፡፡ ማለትም፣ እነርሱ ከግብጽ በመውጣታቸው /ከስደት በመመለሳቸው/ ይመኩና ይኮሩ ነበር፡፡ ይህንኑ የሚመኩበትን ነገር ለእመቤታችንም ስጣት፡፡

ያዕቆብና ህዝበ እስራኤል ወደ ግብጽ በመሄዳቸውና ከዚያም በመመለሳቸው የእርሱን ግብጽ ሄዶ መመለስ ምሳሌ እየፈጸሙ ነበር፡፡ እነርሱ ግብጽ የሄዱት በረሃብ /በድርቅ/ የመጣ መሞትን ለማምለጥ ነበር፡፡ እርሱ ደግሞ በተንኮል መሞትን ለማምለጥ ነው፡፡

እነሱ /ህዝበ እስራኤል/ ግብጽ መሄዳቸው ከረሃቡ /ከድርቁ/ ተርፈዋል፡፡ እርሱ ግን እዚያ በመሄዱ በኪዳተ እግሩ /በእግሩ በመርገጥ/ ምድሪቱን ቀድሷታል፡፡

በዚህ ራሱን ዝቅ በማድረጉ መሀልም ግን የአምላክነቱ ማሳያዎች /ምልክቶች/ ተገልጸዋል፡፡ ሰብአ ሰገልና እርሱን ለማምለክ በኮከብ እየተመሩ መጡ፤ አውግስጦስ ቄሳርም የሕዝብ ቆጠራ አዋጅ በማወጅ ልደቱ ቤተልሔም እንዲሆን አገለገለ፤ በግብጽም በርካታ ተዓምራት ተደርገዋል፡፡

አሁን ወደ ግብጽ ብንሄድ በረሃው ከማንኛውም የአትክልት ስፍራ የተሻለ ሥፍራ ያማረ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመላእክት አምሳል ያመሰግኑበታል የሰማእታት ብሔር፣ የደናግል በአት፣ የሰይጣን አገዛዝ ድል የተመታበትና የክርስቶስ መንግስት ደምቆ የሚያበራበት ቦታ ነው፡፡

በትምህርተ ሃይማኖታቸው /doctrine/ ካላቸው ትክክለኛነት በተጨማሪ፣ በህይወታቸውም ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያሉ፡፡ ያላቸውን ሁሉ ትተው ራሳቸውን ከዓለም ካገለሉና ለዓለሙ በሙሉ ከተሰቀሉ በኋላ በድጋሚ የተቸገሩትን ይረዱ ዘንድ የጉልበት ሥራ ይሠራሉ፡፡

ስለሚጾሙና ብዙ ጊዜ በተመስጦ ስለሚያሳልፉ፤ ቀናቱን /ጊዜን/ ሥራ በመፍታት /ቦዝነው/ ማሳለፍ ተገቢ ነው ብለው አያስቡም፡፡ ስለዚህም ቀኑን በጸሎት ሌሊቱንም በዝማሬና በትጋት ያሳልፉታል፡፡ ከዚህም የሐዋርያውን አሰር ይከተላሉ፡፡

«ከማንም ብር ወይም ወርቅ አላስፈለገኝም እነዚህ እጆቼ በሚያስፈልገኝ ነገር ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት እንዳገለገሉ እናንተ ታውቃላችሁ፡፡ እንዲህ እየደከማችሁ ድውያንን ልትረዱና፣ «እርሱ ራሱ ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብጽዕ ነው» የሚለው የጌታን የኢየሱስን ቃል ልታስቡ ይገባችሁ ዘንድ አሳየኋችሁ፤» ሐዋ. 10-34 ይህንን የሐዋርያውን ቃል ሲሰሙ በበረሃ ያሉት የግብጽ መነኮሳት እንዲህ ይላሉ፡- «እርሱ /ሐዋርያው/ በእግዚአብሔር ቃል እንዲመግባቸው ብዙዎች እየጠበቁት የእጅ ሥራ ይሠራ ከነበረ፣ መኖሪያችንን በገዳም፣ በዱር፣ በበረሃ ያደረግን፣ የከተማ ጾር /ፈተና/ የቀረልን እኛማ ከጸሎታችንና ከተመስጦአችን የተረፈንን ጊዜ ለተመሳሳይ ሥራ ልናውለው ምን ያህል ይገባናል)!»

እኛም ራሳችንን እንመርምር ሀብታምም ድሃም የሆንን እነዚህ መነኮሳት ከሰውነት /እጅና፣ እግር/ በስተቀር ምንም የሌላቸው ሲሆኑ የተቸገሩትን ለመርዳት እንዲህ ከወጡና ከወረዱ የተረፈንን እንኳን ለእነዚህ ሰዎች /ችግረኞች፣ ድውያን/ የማንሰጥ እኛ ለዚህ አድራጎታችን ምን ምክንያት፣ ምን ማስተባበያ ማቅረብ እንችላለን፡፡

ታላቁን አባት ቅዱስ እንጦንስን እናስታውስ፡፡ ይህ ሰው የተወለደው ፈርኦን በተወለደበት ሀገር ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ምክንያት እነርሱን አልመሰለም፡፡ የነበረው ሰማያዊ ራእይ ስለጠበቀው እግዚአብሔር በሚወደው መልኩ ህይወቱን አሳልፏል፡፡ ከጽድቁ የተነሳ ከእርሱ በኋላ የሚመጡ መነኮሳት ምን ዓይነት እንደሚሆኑ እግዚአብሔር አሳይቶታል፡፡

ጻድቁ እንጦንስን ታሪክ ማንበብና ማድነቅ ብቻ ሳይሆን በሕይወት መተርጎምም ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን አለመበርታት ቦታን፣ አለመማርን፣ የአባቶችን መርገም... ምክንያት አናድርግ፡፡
ነገሮችን በማስተዋል ስንመለከት እነዚህ ሁሉ ነገሮች ለእኛ መሰናክል መሆን አይችሉም፡፡ አብርሃም ጣኦት አምላኪ አባት ነበረው /ኢያ. 24-2/ ነገር ግን የአባቱን ክፋት አልወረሰም፣ የሕዝቅኤልም አባት አካዝ ኀጢአተኛ ሰው ነበር፡፡ ሕዝቅያስ ግን የእግዚአብሔር ወዳጅ ነበር፡፡

ዮሴፍም በግብጽ ሆኖ ራሱን በትምህርት አስጊጧል፡፡ ሦስቱ ሕፃናትም በባቢሎን ቤተመንግስት ሆነው ታላቅ ራስን መግዛት አሳይተውናል፡፡ ሙሴም በግብጽ ነበር፣ ቅዱስ ጳውሎስም በዓለም ነበር፤ ነገር ግን እነዚህን ሁሉ ያሉበት ቦታና ሁኔታ ከጽድቅ ጉዞአቸው አላደናቀፋቸውም፡፡


ዘመነ ጽጌ በዲ/ን ዳንኤል ክብረት

                                                        

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!

ምንጭ፦ ማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ

Monday, September 30, 2013

400,000 ብር እና አዲስ ፕሬዝዳንት

በአዲስ ዓመት እንደ አገርም እንደ ግለሰብም አዲስ ሥራ ለመሥራት ይታቀዳል። በዚህ አመት ደግሞ ልዩ የሚያደርገው አገራችን ኢትዮጵያ ፕሬዝዳንታዊ "ምርጫ" (ምርጫ የሚለውን ቃል የተጠቀምኩት ሕገ መንግሥቱን ለማክበር እንደ ሆነ ይታወቅልኝ) የምታካሂድበት ጊዜ መሆኑ ነው። መንግሥት (አገራችን ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ ስለሚሆን ነው) በሕገ መንግሥቱ መሰረት በየስድስት ዓመቱ የአዲስ ፕሬዝዳንት ምርጫ ያካሂዳል። በዚህ አመትም ክቡር ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የ12 አመት የፕሬዝዳትነት ስልጣናቸውን የሚለቁበት ጊዜ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ 2 አነጋጋሪ ጉዳዮች ጎልተው ወጥተዋል።

1. ቀጣይ አገሪቱን በፕሬዝዳትነት ማን ይምራት

 ለአገራችን እድገትና ሰላም የሚያስቡና የሚቆረቆሩ ምሁራን በተለያየ መልኩ አገሪቱን ማን ቢመራት የተሻለ ሊሆን ይችላል ብለው ሃሳባቸውን በማካፈል ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል በኖርዎይ ኦስሎ, ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሴር ተክሉ አባተ በጡመራ ድረ ገጻቸው ላይ ሃሳባቸውን አስቀምጠዋል።

በአንድም በሌላም አገራችንን የተሻለ ሰው ቢመራት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ምኞት ነው። ነገር ግን ማነው የተሻለውን ሰው በፕሬዝዳንትነት ቦታ ላይ እንዲቀመጥ ማድረግ የሚችል የሚለው ትልቁ ጥያቄ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ መቀመጥ ቢችልስ አቅሙንና እውቀቱን ተጠቅሞ መስራት የሚችልበት ከባቢያዊ አየር አለ ወይ ነው። በግልጽ ቋንቋ መንግሥት እንዲህ አይነት ሰዎችን ይፈልጋል ወይ የሚለው የሁላችንም ገሃዳዊ ጥያቃችን ነው።

ስለ አዲስ ፕሬዝዳንት ስናነሳ በስፖርቱ አለም ታዋቂነትን ያተረፈውና አገራችን ኢትዮጵያን ለአለም ስሟን ያስተዋወቀው አንበሳው ኃይሌ ገ/ስላሴ በምርጫው እንደሚሳተፍ የተገለጸበት ሌላው ትልቁ ወቅታዊ ጉዳይ ነው።



ኃይሌ ገ/ስላሴ Google pic

ኃይሌ ገ/ስላሴ በህብረተሰቡ በኩል ትልቅ ቦታና ክብር ያለው ሰው እንደ መሆኑ መጠን በዚህ ምርጫ የሚሳተፍ ከሆነ ብዙ ነገሮችን መመልከትና መወሰን ይኖርበታል።

  1. የመንግሥትንና የህብረተሰቡን የአንድነት ሁኔታ
  2. የመንግሥትን ምንነት(እውቀቱንና ስልጣኑን በነጻነት መጠቀም መቻሉን)
  3. በመንግሥትና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ያለውን ልዩነት
  4. በመንግሥትና ውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውን መካከል ያለውን ልዩነት
  5. ለቀጣይ 6 ወይም 12 አመት አገሪቱን በፕሬዝዳትነት ለመምራት የሚያስችል በቂ እውቀት መኖሩን ...ወዘተ
ወደ ምርጫ ከመግባቱ በፊት እነዚህንና መሰል ነገሮችን በሚገባ ማጤን ይኖርበታል። ነገሮችን ሳይመለከት ቢገባ ግን ክብሩንና የወደፊት ጉዞውን በቀላሉ ሊያጣ እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ምክንያቱም የአገራችን መንግሥት በህብረተሰቡ ዘንድ በተለያየ መልኩ ተቀባይነቱ በእጅጉ የቀነሰበት ሁኔታ ላይ በመሆኑ የኃይሌንም የወደፊት ጉዞ አስቸጋሪ እንዳያደርግበት የብዙዎች ሃሳብ ነው።

2. የክቡር ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የወደፊት የኑሮ ሁኔታ




የክቡር ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የወደፊት ሕይወት ነው። ከኃላፊነት የተነሱት የአገርና የመንግሥት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የምክር ቤት አባላትና ዳኞች የሚያገኙዋቸውን መብቶችና ጥቅሞች ለመወሰን መንግሥት ባወጣው አዋጅ መሰረት ለተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ቤት በወር 400,000 ብር መከራየቱን ጠቅሳል፡፡ ይህ ከፍተኛ የቤት ኪራይ ወጪ ግን ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ሲገናዘብ ለማመንና ለመቀበል አስቸጋሪ ነው። እኔ ግን ትልቅ ጥያቄ የፈጠረብኝ መንግሥት ለፕሬዝዳንቱ የተከራየው ቤት መኖርያ ወይስ የንግድ የሚለው ነውና ደሞዛቸውስ ስንት ነበር የሚለው ነው። መኖርያ ቤት እንደሆነ ደግሞ ተገልጾልናል፤ ነገር ግን መኖርያ ቤት ይህን ያክል ወጪ እንዴት ሊያወጣ ቻለ የሚለው የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
ስለዚህ አገሪቱ ለአንድ ከኃላፊነት ለለቀቀ ባለስልጣን ለቤት ኪራይ፣ ለመኪና፣ ለሰራተኛ፣ለህክምና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ጨምሮ ከፍተኛ ገንዘብ በወር ወጪ ታደርጋለች ማለት ነው። ይህን ጉዳይ መንግሥት ለአገራችን በምን ያክል መጠን እንደሚያስብ በጥልቀት ለመረዳት በጎ አጋጣሚ ፈጥሮልናል።
በዚህ ዙርያ የእኔ ሃሳብ ይህን ያክል የአገሪቱን ገንዘብ ወጪ ከማድረግ ይልቅ መንግሥት ከኃላፊነት ለሚለቁ ከፍተኛ ኃላፊዎች የሚሆን ቤት ቢያስገነባ የተሻለ ይሆናል። ምክንያቱም የሚገነባዉ ቤት ለወደፊት የአገሪቱ ቋሚ ንብረት ይሆናል፤ ከዚያም በላይ ለኪራይ በየወሩ የሚወጣውን ከፍተኛ ገንዘብ ይቀንሳል።



Saturday, September 14, 2013

ሰው እና ሕገ ሕሊና/ተፈጥሯዊ ሕግ

ሰው ማነው? ብሎ ለጠየቀ “ሰው ንግግሩን ይመስላል” እንዳትለኝ ንግግሩ እምነቱንና ሃሳቡን ሙሉ በሙሉ የሚያመለክት ዕውቀት አይሆነውምና ነው፡፡ በተለይ ከዘመኑ ድርጊታችን ስንመለከተው ንግግራችን እና ድርጊታችን ፍጹም ተቃራኒ ሁኖ እናገኘዋለን። ለሰው ባሕርያዊ ተፈጥሮና ዕውቀት ምስክሩ ውስጣዊ የአዕምሮ አቋምና የሕሊና ሕግ ነው ብለንም አንደመድምም፡፡ ሰው እንዲያውቅ የተመደበለት የሕግ ተፈጥሮ ዕውቀት መጀመሪያ ክፍል መልካምን ማወቅ፡፡ ሁለተኛ ክፋትን ንቆ መልካምን ገንዘብ ማድረግ፡፡ ሦስተኛ መልካምን በግብር መግለጽ ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቱያን ሊቃውንት ይሁዳን ሲገልጹ “በአፍ አምኖ በልቡ የካደ” ይሉታል፡፡ ባህላችን “አፈ ቅቤ፤ ሆደ ጩቤ” እንዲል፡፡ ይሁዳ በጊዜያዊ ጥቅም ተታሎ ለሕሊናው መገዛት ስላልቻለ አምላክን ያህል ጌታ ለሞትና ለስቅላት አሳልፎ ሸጠ። ከሐዋርያት ማኅበርም በእራሱ ድርጊት ተለየ።
የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር መሠረት ሕገ ልቦና/ሕሊና ስንል ያለ ትምህረት በተፈጥሮ የሚሰጥ ሲሆን ይህም ሕገ ልቦና፤ ሕገ ህሊና፤ ሕገ ተፈጥሮ ወይንም ሕገ ጠብዓያዊ በመባል ይታወቃል፡፡ ሕገ ኦሪትና ሕገ ወንጌል፤ ሕገ ሕሊናን ይተረጉማሉ፡፡ ለአብነት ብንጠቅስ አዳምና ሔዋን ቅዱስ ዳዊትትን፣ ቅዱስ ጴጥሮስንና ይሁዳን፤ ከመጸጸት ክፉዎችን ከማዘን የምታደርሳቸው የሕሊና ኮሽታ ነች፡፡ በኑሮ ሂደት ሀዘን፣ ጸጸት ርትዕ በምናደርግበት ጊዜ ልዩ መንፈሳዊ ጥበብ አልያም ዕውቀት በመታደል ሳይሆን ሰው በመሆናችን በሕሊና ውስጥ የተቀረጸ በህሊና ሚዛን የሚሰጥ ፍርድ በመኖሩ ነው፡፡ ለምሳሌ አብርሃምን ስንመለከት ምንም የተጻፈ ሕግ፣ ሰባኪና መምህር ባልነበረበት ወቅት በሕገ ልቦና/ሕሊና ተመርቶና ተመራምሮ ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር ችሏል። አባቱ ታራ ይከተለው የነበረው መንገድ እጅግ ስህተት መሆኑን ተረዳ። ለከዚህም በተጨማሪ ሕገ ሕሊና በጽሑፍ ከተሰጡን ሕግጋት /ሕገ ኦሪት፣ ሕገ ወንጌል፣ ማሕበራዊ ሕግ/ በላይ ሰማያዊና ምስጢርን ለመጠበቅ ሲያገለግል እናገኘዋለን፡፡ የቤተ ክርስቲያን የሀገር የግል ምስጢር ይጠበቅ ዘንድ መንፈሳዊ ሕግና ማህበረሰባዊ ሕግ ይደነግጋል፡፡ የአምላክ እናት ድንግል ማርያም ያለ ምድራዊ ሕግ አስገዳጅነት በሕገ ልቦና ዳኝነት ለሰማያዊ ምስጢር የታመነች ነበረች “እናቱ ማርያም በልቧ ትጠብቀው ነበር” እንዲል፡፡ /ሉቃ.2÷19/፡፡
“ሰው ራሱ መጽሐፍ ነው” የሚለው የአነጋገር ስልት የሚያስተላልፈው ሰው ይነበባል፤ ይጠናል፤ ይተነተናል፤ ይጸድቃል፤ ይሻራል ለማለት ነው፡፡ ከሌሎች ሥነ ፍጥረታት በላይም አስተማሪና ሚስጢራዊ ነው። እነዚህን ተግባራት ለሌሎችም ሆነ ለራሳችን ለድርጊታችን ብያኔ ፍርድ ለመስጠት ረቂቅ የሕሊና ልጓም እንደ መሠረት ሆኖ ያገለግላል፡፡ ሰው በውስጡ የሚያረጋግጣት እውነት በክበበ አዕምሮ በሚጨበጥ ሕገ ባሕርይ ከመገለፅ እምቢ አትልም፡፡ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት እምነት በቅድሚያ እንዲገኝ ግድ ቢሆንም በተግባር ወይንም በድርጊት ካልተዋሃደ ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ፍሬ ቢስ፤ ረብ የሌለው ከንቱ ድካም ይሆናል፡፡ ለመሆኑ እምነታችን ከድርጊታችን ለምን ተዛነፈ? በጽናት የምናምነውን እምነት አጥቦ የመውሰድ ብቃት ያለው ሃይል ይኖር ይሆን? በዕለት ተዕለት ማኅበራዊ መስተጋብር የምንወስናቸው መጠነ ሰፊ ጥቃቅን ውሳኔዎች ውህደ ሃይማኖት ምግባር የታሹ ወይስ የስሜት ውጤቶች ናቸው? እርግጥ ነው ስሜት አልባ ሰብአዊ ፍጡር ሊሆን አይችልም፡፡ 
ነገር ግን ነፍስን ደስ የሚያሰኝ ሰማያዊ እውነት ከስሜት በላይ ነው፡፡ እውነት ደግሞ በሕገ ሕሊና ያለ አምላካዊ ሕግ ነው። ሕጉን ያለመፈጸም እንጂ መካድ አይቻልም ምክንያቱም ተፈጥሮአዊ ሕግ ነውና። ሰው ድርጊቱን ምክንያታዊ ቢያደርገውም እውነቱን ግን በትክክል ሕሊናው ይነግረዋል። ከሰው ሊሰወር ይችላል ከሕሊናው ግን መሰወር አይችልም። ብዙ ሰዎች ትክክል ያልሆነ ድርጊት ለመፈጸም ከአሰቡበት ጊዜ ጀምሮ ከራሳቸው ጋር ይሟገታሉ፤ ልፈጽመው ወይስ ይቅርብኝ በማለት። እውነቱንና ትክክለኛውን መንገድ ግን ሕሊናቸው በተለያየ መንገድ ያሳውቃቸዋል። ቅዱስ ጳውሎ እንደተናገረው "እነርሱም ሕሊናቸው ሲመሰክርላቸው፥ አሳባቸውም እርስ በርሳቸው ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ።"(ሮሜ 2፥15)
በገሃዱ ዓለም በብዙዎቻችን ሕይወት የሚታየው ውሳኔዎቻችን በድካም ባካበትነው ዕውቀት፤ መንፈሳዊ አስተምህሮ፤ ዓለማዊ ጥበብ፤ የቅዱሳን ሕይወት ሳይሆን ለስሜት ያጋደለ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለሁለት ጌታ መገዛት አይቻልም የሚለውን ኃይለ ቃል ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተማረው ይሁዳ ለ30 ብር ሸጦታል ለምን ትለኝ እንደሆን ሰው ክፉን ነገር እስኪሰራ ሰው ልበ ሙሉ ይሆናልና ነው፡፡ ሁለተኛው የህሊና ዓይን ከነፍስ ባይለይም በኃጢአት ምክንያት ይጨልማል ይደክማልና ነው፡፡ በአጭር አገላለጽ ድርጊታችንን የሚቆጣጠረው በዕለቱ ስሜታችንን ያቀጣጠለው ኃይል እንጂ በጥረት ያካበትነው ትምህርት ወይም ዕውቀት ሆኖ አይታይም፡፡
ሰው በሕገ ሕሊና፣ በሕገ ኦሪት፣ በሕገ ወንጌልና በሕገ ማህበራዊ መገዛቱን ትቶ በጊዜአዊ ስሜት ለጥቅምና ለስልጣን፣ ለክብርና ለእይታ ማደር ከጀመረ ለአገርም፣ ለቤተሰቡም ለራሱም ሳይሆን በቅዠትና በሰላም እጦት ሕይወቱ እንዲሁ ያልፋል። ሰው ሆይ ከምንም በላይ ለተፈጥሮአዊ ሕግ ተገዢ ሁን፤ ሕሊናህ ይዳኝህ፤ ለመልካም ነገር ትጋ፤ እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ!!!  

ምንጭ፦ ማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ (ሚያዝያ 26፣2003ዓ.ም)

Tuesday, September 10, 2013

አዲስ ዓመት፣ አዲስ ዕቅድ

በየአመቱ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ከእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት ቀጥለን በአዲስ ዓመት ዕቅድህ/ሽ ምንድን ነው? የሚለው የተለመደ ጥያቄ ነው። መልሳችንም እንደ ሥራ መስካችንና አመለካከታችን የተለየ መልክና ይዘት ይኖረዋል። በአዲስ ዓመት በት/ት ገበታ ላይ የሚገኙ ሁሉ ጥሩ ውጤት ማስመስገብን፣ አርሶ አደሮች ጥሩ ምርት ማምረትን፣ በንግዱ ዓለም የሚገኙ ትርፋማነትን፣ ማኅበርተኞች የማኅበራቸውን ዓላማና ግብ መሳካትን፣ ፖለቲከኞች መልካም አስተዳደርንና የተቀናቃኛቸውን ክስረት፣ መንግሥት የስልጣን ዘመን ማራዘሚያ መንገዶችን እና ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪን/ትምህርትን  በአጽንኦት ይሻሉ ይመኛሉ።
አሁን  በአለንበት ዘመን  ምኞታችንን  ሁሉ እውን  ለማድረግ በእጅጉ ከባድ ነው። ሆኖም ግን ልናተኩርባቸው  የሚገቡ ነገሮችን ለይቶ  ለስኬት የሚያበቃንን መንገድ መከተል  ብልህነት ነው። በአጭር ከዚህ በታች ልናተኩርባቸው የሚገቡ ነገሮችን ለመነሻ ያክል ጥቂት ልበል።

እንደ  ክርስቲያን በአዲሱ ዓመት ልናተኩርባቸው የሚገቡ፦
  • ከበፊቱ በበለጠ ከጠላታችን ዲያቢሎስ ጋር የምንዋጋበትን እቃ ጦር ለመልበስ ታጥቀን የምንነሳበት፣ 
  • ቤተ ክርስቲያንን ከበፊቱ በበለጠ ልናገለግልና ልንገለገልባት በጽዕኑ ዓላማ ቆርጠን የምንነሳበት፣
  • ቤተ ክርስቲያን የሁከት፣ ፀረ ሰላም፣ ፀረ ልማት እንዳይደለችና የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት ት/ቤት እንደሆነች በኩራት የምንመሰክርበትና የምንገልጽበት፣ 
  • ቤተ ክርስቲያን አክራሪነትን የምትቃወም እንጂ አክራሪነት የሚለው ቃል ፈጽሞ ሊሰጣት እንደማይገባ በድፍረት የምንመሰክርበት፣ 
  • ከሰዎች ጋር መታረቅና ፍቅርን በስጦታ መልክ መለገስ፣
  • ሰውነታችንን በንስሃ ታጥበን በአምላክ ቅዱስ ሥጋና ክብር ደም ታትመን አዲስ ሕይወትና አዲስ መንፈስ የምንይዝበት ዘምን እንዲሆን ይፈለጋል።
እንደ  መንግሥት በአዲስ ዓመት፦
  • መልካም አስተዳደር ለማስፈን መጣር፣
  • ሕግን ከወረቀት ባለፈ በተግባር ማዋል፣
  • የህዝቡን ብሶት ሰምቶ ለችግሩ ደራሽ መሆን፣
  • አገራዊ ስሜትን ለህብረተሰቡ ማስገንዘብ፣
  • ለዲሞክራሲ ግንባታና ለአገራዊ እድገት የሚጥሩ ተቀናቃኝ/ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማበረታታት፣
  • በሃይማኖት ጣልቃ ገብነትን ማቆም፣
  • ለሰባዊ መብት ተቆርቋሪ መሆን፣
  • ከአላግባብ የታሰሩ እስረኞችን መፍታት፣
  • ትክክለኛ መረጃ ሳይኖር ሰዎችን፣ድርጅቶችንና ተቋማትን  ያልሆነ ስም ሰጥቶ ማሸማቀቅን ማቆም፣
  • ስልጣን የህዝብ መሆኑን በተግባር ማሳየት እና መሰል ተግባሮችን የሚተገብርበት ዘምን እንዲሆን ይፈለጋል። 
እንደ ሰራተኛ በአዲስ ዓመት፦
  • ለሌላ ሁለተኛ ወይም ሦስተኛ አካል ሳይሆን ለህሊና መስራት፣
  • በማነኛውም የሥራ መስክ ህዝብን እንደምናገለግል  በሚገባ መገንዘብ፣
  • ለሕገ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ለሕገ አምላክም መገዛት፣
  • ማጭበርበር፣ ሙስና እና ጥቅመኝነትን አምርሮ  መጥላትና ማጋለጥ፣
  • ፍቅርን  በስጦታ መልክ ለሰዎች መለገስ፣
  • በማነኛውም መልኩ ለእውነት ለመስራት እራስን ዝግጁ ማድረግ ይገባል።
እንደ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲ በአዲሱ ዓመት፦
  • ለህዝብና ለሃገር መቆማችሁን በትክክል ሊያስረዳ  በሚችል መልኩ ዓላማችሁን መግለጽ፣
  • የመንግሥት አካላትን በፖሊሲና በዓላማ እንጂ  በማንነታቸው አለመተቸት፣
  • ማንኛውንም ድርጅት ወይም ተቋም ለፖለቲካ ቅስቀሳ አለመጠቀም፣
  • ስድብንና ዛቻን ትቶ ሙህራዊ የአነጋገር ዘይቤ መጠቀም፣
  • ድርጅታችሁ ከብሔር ይልቅ  አገራዊ እንዲሆን  ማድረግ፣
  • የመንግሥትን  መልካም ሥራዎች ካሉ ማበረታታትና መደገፍ፣
  • ለዲሞክራሲ፣ ለሰላምና ለአድነት ቆርጦ መነሳት ከእናተ በአዲስ ዓመት ይጠበቃል
ሁላችንም 2006 ዓምን እነዚህንና ሌሎች አስፈላጊ ተግባራትን ለመተግበር አቅደን አዲሱን ዓመት መቀበል ይገባናል።   

ዘመነ ማርቆስ/2006 ዓም የሰላም፣ የፍቅር፣ የደስታ፣ የአንድነት፣ የሕይወት ብልጽግና   እንዲሆንልን አምላከ ቅዱሳን በቸርነቱ  ይርዳን፡አሜን!።

Sunday, September 8, 2013

የዘመን መለወጫ በዓል፤ ዕንቍጣጣሽ፤ የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።


 +++ እንኳን ለ፳፻፮ ዓም  በሰላም አደረሳችሁ!+++

 ይህ ከዚህ በታች ስለ አዲስ ዓመትና የኢትዮጵያ የዘመን አቀጣጠር በተመለከተ ሰፋ ያለ ጽሁፍ ታላቁ የቤተክርስቲያን አባት አለቃ አያሌው ታምሩ ያስተማሩት ት/ ት ሲሆን በእርሳቸው ስም ከተከፈተው መካነ ድር ላይ በቀጥታ የተወሰደ ነው። መልካም ንባብ....... 





«በመለከት ድምፅ መታሰቢያ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ።» (ዘሌ ፳፫፥፳፫-፳፬።)

መግቢያ
በኢትዮጵያ የእምነት ትምህርት እየሰፋና እየጸና የቆየ በመሆኑ ምክንያት ከትምህርትነት ዐልፎ ወደ ባህልነት ተለውጦአል። እንዲያውም አብዛኛው የእምነት ትምህርት ትምህርት ነው ከሚባል ይልቅ ባህል ነው በሚባለው ስሙ የታወቀ ሆኖ ይገኛል። የባህል ዘርፎች ከሆኑ የእምነት መገለጫዎች አንዱ በዓል ነው። በዓል በሞላው የሰው ዘር ዘንድ የባህል መሠረቶች ከሆኑት አንዱ ክፍል ነው። እምነት ያለው በእምነቱ፥ እምነት የሌለውም በልማዱ የባህል ሥነ ሥርዐት የሌለው የሰው ዘር የለም። ግን በመሠረቱ የባህል መነሻው እምነት ነው። እያደር እየዋለ ወደ ልዩ ልዩ ልማድ እየገባ መሠረቱን ለቆ ይገኝ እንደ ሆነ ነው እንጂ በዓል ሲባል መሠረቱ እምነት ነው። በእምነት ላይ ነው ሁሉም የሚመሠረተው። ከበዓላትም ተቀዳሚ ሆኖ የሚገኘውን የዘመን መለወጫ በዓልን ስንመለከት በልዩ ልዩ ክፍለ ዓለማት፥ በልዩ ልዩ የሰው ዘሮች ባህል ውስጥ የታወቀ፥ ጸንቶ የኖረና የሚኖር ሆኖ እናገኘዋለን። የሰው ልጆች እንደ ጠባያቸው፥ እንደ ባህላቸው፥ እንደ ልማዳቸው እና እንደ እምነታቸው መሠረት ያዳበሩት፤ አንዳንድ ጊዜም ነገሥታት ወይም አምባገነን መሪዎች በሚያመጡት የሥርዐት ጠቀስ ሁኔታ እየተፈጠረ ጸንቶ የኖረ የዘመን መለወጫ ሥርዐት በየአገሩ ይገኛል። በእምነት ክፍል ግን የምንመለከታቸው እጅግ አነስተኞች ናቸው። እነዚህ እምነቶች የሚቀራረቡበትም የሚለያዩበትም ነገር አለ። ለምሳሌ ክርስቲያኖች ከአይሁድ ጋራ መሲሕ ይመጣል የሚሉትን በትንቢት እምነት ሲቀበሉ ከኖሩ በኋላ ጊዜው ሲደርስ፤ ጊዜ ደረሰ፥ ተስፋ ተፈጸመ፥ አምላክ ሥጋ ለበሰ ብለው በማመናቸው፤ እንዲሁም እግዚአብሔር በአካል ሦስት፥ በባሕርይ አንድ ነው፤ አብ ወልድን መንፈስ ቅዱስን አስገኘ፥ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ተገኝተዋል፤ እንዲህ ቢሆን ግን መቅደም መቀዳደም፥ መብለጥ መበላለጥ የለም ብለው በማስተማራቸው ክርስቲያኖች የተለየ ፈለግ የሚከተሉ ናቸው። ይህም ስለ ሆነ እምነታቸው ጠባብ በር፥ ጠባብ መንገድ ይባላል። ጠባብ በር፥ ጠባብ መንገድ ይሁን እንጂ መጨረሻው ደግሞ መዝለቂያው ሕይወት መሆኑን ራሱ መድኃኒታችን ስለ ገለጠ የክርስትና እምነት ዘላቂ ሕይወት ያለውና የሚሰጥ መሆኑ የታመነበት ነው።

የዘመን መለወጫ በዓል

የዘመን መለወጫ በዓልን በተመለከተ የተለያዩ የእምነት ክፍሎች የየራሳቸው መነሻ ምክንያት አላቸው።
በአይሁድ የዘመን መለወጫ ተብሎ የሚከበረው መባቻ ተብሎ ከሚጠራው ቀን የተለየ ነበረ። እነሱ የዘመን መለወጫን የሚያከብሩት በሚያዝያ ነው። ይህንንም ያደረጉበት ምክንያት አባቶቻቸው ወደ ግብጽ ተሰደው ሁለት መቶ ዐሥራ ዐምስት ዓመት በግብጽ ከኖሩ በኋላ እንደገና ከግብጽ ወጥተው ወደ ኢየሩሳሌም ሲገቡ እግዚአብሔር እነሱን ከግብጽ አውጥቶ፥ ባሕር ከፍሎ፥ ደመና ጋርዶ ወደ ምድረ ርስት ለማድረስ ከግብጽ ያወጣበትን ቀን ልክ ነጻነታቸውን እንዳገኙበት ቀን አድርገው በየዓመቱ የዘመን መለወጫ ብለው እንዲያከብሩትና ወሩንም የወሮች መጀመሪያ እንዲያደርጉት ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ስለ ተሰጣቸው በዚህ መሠረት ሚያዝያን ያከብራሉ።
ክርስቲያኖች ግን የዘመን መለወጫ በዓላቸውን በልዩ ልዩ አገር እንደ መሆናቸው መጠን አላስተባበሩም። በተለይም ጎላ ብሎ የሚታየው የጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር ከሌሎች አቆጣጠር የተለየ መልክ ያለው ነው። አውሮፓውያን የጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር የሚባለውን የሚከተሉ ሲሆን ይህ አቈጣጠር የዓመተ ምሕረት መለወጫ እንጂ ጠቅላላ የዘመን መለወጫ አለመሆኑ በግልጽ ይታያል። ያንንም ቢሆን እንደ ጠባዩ፥ እንደ አጠራሩና እንደ ፍላጎታቸው ልክ በመድኃኒታችን ልደት አልጀመሩም። የልደትን በዓል እንደ ቀን አቆጣጠራቸው ካከበሩ በኋላ እንደገና በስምንተኛው ቀን የዘመን መለወጫ ብለው ያከብራሉ። ይህም የጎርጎሮሳውያን የዘመን አቈጣጠር በክርስቶስ ልደት ላይ አለመመሥረቱን፥ ሌላ ጠባይ ወይም ሰው ሠራሽ ሥርዐት የተቀላቀለበት መሆኑን ያሳያል። ክርስትናን ተመርኩዞ ቢነሣ ኖሮ በእርግጥ የመድኃኒታችንን ልደት መነሻ አድርጎ ሊዘምት በተገባው ነበር። ይህ ባለመሆኑ ግን አሁንም ቢሆን የልደቱን በዓል ለብቻ አክብረው እንደገና ከሳምንት በኋላ የዘመን መለወጫ በዓልን ያከብራሉ። ከዚህም በተጨማሪ የወሮችና የቀኖች ስያሜአቸው ከእምነታቸው ጋራ ምንም የሚገናኝ አይደለም። እንዲያውም በአብዛኛው የሮማን አስተዳደር ጠባይ የተከተለ ፍንጭ ይታይበታል። ለምሳሌ ያህል ሰንዴይ የሚሉት ቀን ፀሐይን ያመልኩ ስለ ነበረ ከዚያ ጠባይ ተወርሶ የዚያን ምልክት ይዞ የሚኖር ሆኖ ነው የምናገኘው። ወሮችም በዚሁ ዐይነት አቅጣጫ የተሰየሙ መሆናቸውን እናያለን። ለምሳሌ በነጁልዮስ ቄሣር፥ በነ አውግስጦስ ቄሣር፥ በነ ኦክታብዮስ ቄሣር ስያሜ ጁላይ፥ ኦገስት፥ ኦክቶበር እያሉ የሰየሟቸው ስያሜዎች እዚያ ውስጥ ይገኛሉ። በዚህ ዐይነት ውሥጡ ሲመረመር ሰም ለበስ ሰው ሠራሽ ሥርዐት እንጂ የእምነት መሠረት ያለው ሆኖ አናገኘውም። በጎርጎሮሳውያን የዘመን አቈጣጠር ውሥጥ መሠረቱ ከእምነት ጠባይ ጋር የሚመሳሰል መንሥኤ ያላቸው አንዳንድ መነሻዎች ያሉ መስለው ይታያሉ። በዚያን ጊዜ የነበሩ የሮማ ነገሥታት ሁሉ አውግስጦስ የሚባለውን ስም የወሰዱት አምላክ ነን ለማለት ነበር። እና እያንዳንዳቸው መሥዋዕት ይቀርብላቸው፥ ዕጣን ይታጠንላቸው ስለ ነበረ መነሻው እምነት መሰል ምክንያት ሆኖ ይታያል። ከሮማ ነገሥታት አንዱ ጥጦስ የኢየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ ባቃጠለ ጊዜ አይሁድ ተስፋ እንዲቆርጡ ጭፍሮቹ ቅድስተ ቅዱሳኑ ከመቃጠሉ አስቀድሞ በመሬት ውሥጥ ለውሥጥ ገብተው እቤተ መቅደሱ ላይ የእሱን ምስል አቁመው ለእሱ መሥዋዕት ሠውተው፥ እሱን አመስግነው እግዚአብሔርን እንዲሰድቡ አድርጓል። ይህ ድርጊትም የአይሁድን መንፈስ በከፍተኛ ደረጃ እንደ ሰበረ ይነገራል። እንግዲህ የጎርጎሮሳውያን የዘመን አቈጣጠር በዚህ ዓይነት የተመሠረተ ጠባይ ነው የሚታይበት።

የኢትዮጵያ ዘመን አቈጣጠር

ወደ ራሳችን እንመለስና ስለ ኢትዮጵያ በዓል አከባበር ደግሞ እንመልከት። የኢትዮጵያ እምነታዊ ባህል የሚወረሰው በሦስት ዐይነት ጠባይ ነው። አንዱ ሕገ ልቡና ይባላል። ከመጽሐፍ በፊት የነበረ ነው። ከአበው ቃል በቃል የተወረሰ ነው። ሁለተኛው በሕገ ኦሪት ከኦሪት የተቀዳ ነው። ሦስተኛው በሕገ ወንጌል ከወንጌል የተማርነው ነው። እና በሦስት ዐይነት ጠባይ የሚመራ ነው። በዚህ ዐይነት ከወረስናቸው በዓላት ማለት በሦስቱም ጠባያት ከወረስናቸው በዓላት የየራሳቸው መልክ ያላቸው አሉ። ለምሳሌ ልደት፥ ጥምቀት፥ ዕርገት፥ ደብረ ታቦር እነዚህን የመሳሰሉት ከወንጌል የተማርናቸው ናቸው፤ በብሉይ የሉም። ፋሲካ፥ በዓለ ጰራቅሊጦስ ደግሞ ከኦሪት የተማርናቸው ናቸው። የዘመን መለወጫ በዓል ግን ከሕገ ልቡና ቃል በቃል ተምረን፥ በኦሪት የመጽሐፍ መሠረት አግኝተንለት በወንጌልም አጽንተን ይዘነው የኖርነው ሦስት የሥራ ዘመን ክፍል የተላለፈና እዚህ የደረሰ ነው። ምንም እንኳ ከሳይንቲስቶች አቈጣጠር ባይስማማም እኛ የዘመን መለወጫ ብለን በሀገራችን ባህል የምናከብረው ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር የተገኘበት፥ ብርሃን፥ ጊዜ፥ ዕለት፥ ሰዓት የተፈጠሩበት፤ ለብርሃን፥ ለጊዜ፥ ለዕለት፥ ለወር ለዓመት ጥንት መሠረት የሆነ ቀን ነው። ይህንን ሁሉ በማስገኘት እግዚአብሔር ራሱን የገለጠበት፥ ዓለምን በመፍጠር ከሃሊነቱን ያረጋገጠበት ቀን ነው ብለን ነው የምናከብረው። ስለዚህም ጥንተ ብርሃን፥ ጥንተ ዕለት፥ ጥንተ ጊዜ፥ ጥንተ ፍጥረት ርእሰ ዐውደ ዓመት ብለን ነው የምናከብረው። በዚህ ስያሜ በዓሉ ርእሰ ዐውደ ዓመት፥ ቅዱስ ዮሐንስ፥ የዘመን መለወጫ ብለን እናከብረዋለን።
ርእሰ ዐውደ ዓመት የምንለው፤ ዐውድ ማለት በግእዙ ቋንቋ ዙሪያ፥ ክብ የሆነ ነገር ማለት ነው። የዓመት ጠቅላላ ቀኖች መሠረታውያን ቀኖች የሚባሉት ሦስት መቶ ስድሳ አራት ቀኖች ናቸው። እነዚህም በኀምሳ ሁለት ሱባዔ ተከፍለው ለእያንዳንዱ ቀን በዓመት ውስጥ ለሰባቱ ዕለታት ኀምሳ ሁለት ኀምሳ ሁለት ቀን ይደርሳቸዋል። ከነዚህ ቀኖች የተሳሳበ የሴኮንድ፥ የደቂቃ፥ የሰዓት ዕላፊ ተጠራቅሞ ሦስት መቶ ስድሳ ዐምስተኛዋን የዘመን ማገጣጠሚያ ቀን ያስገኛል። ይህቺ ቀን እንግዲህ ዙሪያ፥ ክብ መግጠሚያ ናት ማለት ነው። በዚህች ቀን አማካይነት ወደ ዐዲሱ ዘመን መጀመሪያ እንተላለፋለን። ይህቺ ቀን ዕለት አዕዋዲት፥ ዕለተ ምርያ የመዘዋወሪያ ቀን ወይም የመጨረሻ ቀን ተብላ ትጠራለች። በአራት ዓመት ደግሞ ከዚህች መሳሳብ የምትገኝ አንዲት ቀን ትመጣለች። ሦስት መቶ ስድሳ ስድስተኛ። ይህቺ ቀን ዕለተ ሰግር ትባላለች። መረማመጃ ማለት ነው። አንድ ቀን ታስተላልፋለች። እንግዲህ እነዚህን ሁለቱን ቀኖች ተከትሎ የሚመጣው ቀን የዘመን መጀመሪያ፥ የዘመን ክብ መነሻና መድረሻ ተብሎ ርእሰ ዐውደ ዓመት ተብሎ በግእዙ ይጠራል። እነዚህ ቀኖች በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ተጠቃለው አንድ ጊዜ የሚገኙ ናቸው።
የኢትዮጵያ ቍጥር መሠረቱ መጽሐፈ ሔኖክ የሚባለው ነው። መጽሐፈ ሔኖክ በ፲፱፥ ፳፥ ፳፩ እና ፳፪ ምዕራፎች የሚሰጠን የፀሐይን፥ የጨረቃን ጉዞ መነሻ አድርጎ የወሮችን፥ የዕለታትን፥ የዓመታትን መነሻ፥ መድረሻ፥ መዘዋወሪያ ብተታቸውን፥ ጥንታቸውን ነው የሚያሳየው። ስለዚህም በሔኖክ ቍጥር የወር ቀኖች ቍጥር ሠላሳ ናቸው። በሦስት በሦስት ወር ግን አንድ ቀን ትከተላቸዋለች። እና ዓመቱ ለአራት ይከፈላል። በዘጠና አንድ በዘጠና አንድ ቀን። ጠቅላላው ይሄ ድምር ሦስት መቶ ስድሳ ስድስት ቀን ይመጣል። ይህ ካለቀ በኋላ አንዲት ቀን ለዘመን ማገጣጠሚያ ዕለተ ምርያ የምትባለው ትመጣለች። እንግዲህ በኢትዮጵያውያን ቍጥር ወሩ ከሠላሳ አያንስም፤ ከሠላሳ አይተርፍም። ለዓመቱም ሦስት መቶ ስድሳ ዐምስት ቀን መደበኛው አቆጣጠር ነው ማለት ነው። ይህ ነገር በአውሮፓውያን ቍጥርም አለ። ግን እነሱ ከዓመት ወሮች ሰባቱን ሠላሳ አንድ ሠላሳ አንድ አድርገው አራቱን ደግሞ ሠላሳ ሠላሳ አድርገው አንዷን ወር ሦስቱን ዓመት ሃያ ስምንት፥ በአራተኛው ዓመት ሃያ ዘጠኝ አድርገው ያጣጧታል። እንግዲህ የአቀማመጡ ለውጥ ካልሆነ በስተቀር በቍጥር አካሄድ ዞሮ ዞሮ የዓመት ቀኖች ሦስት መቶ ስድሳ ዐምስት ወይም ሦስት መቶ ስድሳ ስድስት በመሆን አንድ ሆነዋል ማለት ነው። ልዩነቱ ግን የአቀማመጥ ለውጥ ነው። በኢትዮጵያ አቈጣጠር ግን ጠቅላላውን ፲፪ ወሮች መደባቸው ሠላሳ ብቻ ነው። እነዚያ በሔኖክ መጽሐፍ በጣልቃ ገብነት የነበሩት አራት ቀኖች ተጠቅለው ጳጉሜን በሚባል በዓመቱ መጨረሻ ላይ ተገኝተዋል። ዐምስተኛዪቱ ቀንም ከእነሱ ጋር ተገኝታለች። ይህም ለቍጥር ተራ ቅምር መቅናት የተደረገ እንጂ ቀኑን የሚለውጥ ምንም ነገር የለበትም። እና ከእነዚህ ቀኖች በኋላ የምናገኘው ቀን ርእሰ ዐውደ ዓመት ይባላል። ይህንን በዓል ከአዳም ጀምሮ እስከ ኖኅ ድረስ የነበሩ ዐሥሩም አበው በዐሥሩ ትውልድ እስከ ማየ አይኅ ድረስ ሲያከብሩት እንደ ቆዩና ኋላም የኖኅ ልጆች ከአባታቸው ተቀብለው ሲያከብሩት እንደ ነበረ ኩፋሌ የተባለው መጽሐፍ በምዕራፍ ፯ ያስረዳናል። እንግዲህ ኢትዮጵያ ይህንን ቀን የወረሰችው ከአበው ነው የምንለው በዚህ ምክንያት ነው።
በሰናዖር ሕንጻ ጊዜ የሰው ዘሮች ሁሉ ተበታትነው በየክፍለ ሀገራቸው ሲገቡ ኢትዮጵያውያን አባቶችም ወደ ኢትዮጵያ በገቡ ጊዜ ከኖኅ በቃል ያገኙትን የእምነት መሠረት ይዘው ገብተዋል። ያን ጊዜ ይዘዋቸው ከገቡ ነገሮችም አንዱ የዘመን መለወጫ በዓል ነው። ይህም በክረምቱ መጨረሻ በየዓመቱ የሚከበር ነው። በዚያ ጊዜም ኖኅ ከመርከብ በወጣ ጊዜ በሰኔ ወር መሥዋዕት ሠውቶ ሰውንና እግዚአብሔርን ካስታረቀ በኋላ እግዚአብሔርም በዕርቁ መሠረት፤ «ከእንግዲህ ወዲህ ክረምትና በጋ፥ ብርድና ሙቀት፥ መዝራትና ማጨድ፥ መዓልትና ሌሊት ሰዓታቸውን ጠብቀው ይፈራረቃሉ እንጂ የሰው ዘር ጨርሶ ከምድር የሚጠፋበት ፍጹም ቍጣ የሚደረግበት ጊዜ የለም፤» ብሎ ቃል ኪዳን እንደ ሰጠው ወዲያውኑ ክረምቱ በሰኔ ተጀምሯል። እስከዚያ ድረስ ሰማይ በደመና የሚሸፈንበት ቀን አልታየም ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ምድርን ውሥጥ ለውሥጥ የምታጠጣ የመስኖ ውሃ ነበረች እንጂ በሰማይ ደመና አይታይም ነበር። ኖኅ ከመርከብ ከወጣና መሥዋዕት ሠውቶ ሰውና እግዚአብሔር ከታረቁ በኋላ ግን ሰማይ በደመና ተሸፈነ፤ በዚያ ጊዜም የእግዚአብሔር የቀስቱ ምልክት በደመና ላይ ይታይ ጀመረ። ክረምትም እንደ እግዚአብሔር ቃል ሦስቱን ወሮች ጠብቆ ይመላለስ ጀመረ። እንግዲህ፤ «የዕዳሪ ዕርሻ ምስክር አያሻ፤» እንደሚባለው የኢትዮጵያ ክረምት ትናንትና ነበረ የሚባል ሳይሆን ዛሬም እኛ ደርሰንበት በሰኔ ተጀምሮ በመስከረም የሚፈጸም መሆኑን እንመለከታለን።

ዕንቍጣጣሽና መስከረም


በዚያም ጊዜ የነበሩ ኖኅና ልጆቹ ሰማዩ በደመና በመክበዱ ምክንያት ማየ አይኅ እንደገና ይመጣ ይሆን፥ የጥፋት ውሃ እንደገና ይዘንም ይሆን እያሉ ሲደነግጡ ከርመው በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ሙሉ የፀሓይ ብርሃን ስላዩ፥ ምድር በአበባ አሸብርቃ ስለ ተገለጠችና በዚህም የእግዚአብሔርን ቸርነት፥ የቃል ኪዳኑን መጽናት ስለ ተረዱ ይህንን በዓል ቀድሞ ከአባቶቻቸው እንደ ወረሱት ያው ጥንተ ብርሃን፥ ጥንተ ዓመት፥ ጥንተ ዕለት አድርገው አክብረውታል። ሲያከብሩትም እንግጫ ነቅለው፥ አበባ ጐንጕነው መጀመሪያ መሥዋዕት ይሠዉነት ከነበረው ቦታ ሄደው ለእግዚአብሔር ገጸ በረከት አቅርበው ከዚያ በኋላ ግን እርስ በርሳቸው የአበባ ስጦታ በመለዋወጥ አክብረውታል። ሲያከብሩትም ዕንቍጣጣሽ በሚል ቃል እውነት የመልካም ሞኞታቸውን ይገላለጡበት ነበር። ዕንቍጣጣሽ ማለትንም ብዙ ታሪክ ጸሓፊዎች በልዩ ልዩ መልክ ተርጕመውታል። እንዲያውም ንጉሡ ሰሎሞን ለሳባ ንግሥት የዕንቍ ቀለበት ሰጥቷት ነበርና «ዕንቍ ለጣትሽ» ማለት ነው ብለው የጻፉ ብዙ ሰዎችም አሉ፤ የሚናገሩም አሉ። ነገሩ ግን እንዲህ አይደለም። ዕንቍጣጣሽ ማለት ተንቈጠቈጠ፥ አንቈጠቈጠ ከሚለው ቃል ተወስዶ ምድር በአበባ አጌጠች፥ ሰማይም በከዋክብት አሸበረቀ እንደ ማለት ሰማይን በከዋክብት ያስጌጠ አምላክ ምድርንም በአበቦች አጎናጸፋት ለማለት የተሰጠ ቃል ነው እንጂ ስለ ሳባ ንግሥት የተሰጠ አይደለም። ሁለተኛም አባቶቻችን ኢትዮጵያን በሙሉ ሀብት ተረክበዋት ነበርና፤ «ዕንቍ ዕጣ ወጣሽ፤» ሲሉ ወደ አገራቸው ሲገቡ ለአገራቸው መታሰቢያ አድርገው የተጠቀሙበት ቃል ነው ይባላል። በመሠረቱ ግን ያ የጥፋት ውሃ ቀርቶ ምድር ጸንታ፥ አበባ ቋጥራ፥ ፍሬ ለመስጠት ተዘጋጅታ መገኘቷን የሚያበሥር ቃል ነው።
መስከረም የሚባለው ወርም ኖኅ በመርከብ ውሥጥ በነበረ ጊዜ እንደ ዕብራውያን አቈጣጠር ሰባተኛ በሆነው በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ መርከቢቱ አራራት ከሚባለው ተራራ ላይ ዐርፋ ምድር ጨብጣለች። በግእዝ ቋንቋ መርከብ መስቀር ይባላል። ከዘመን ብዛት በኋላ «ቀ» ወደ «ከ» ተለውጦ መስከረም ተባለ እንጂ መስቀርም ምድር አገኘች፥ መርከብም ምድር ነካች ለማለት የተሰጠ የወሩ ስያሜ ነው።
በዚህ መሠረት አባቶቻችን ፊትም ከአበው እንደ ተቀበሉ፥ ኋላም ከሕገ መጽሐፍ ደግሞ ተቀብለውታል። ይህን ከአዳም እስከ ኖኅ፥ ከኖኅ እስከ አብርሃም ቃል በቃል ሲተላለፍና ሲያከብሩት የቈዩትን የመባቻ በዓል ጌታ ለሙሴ በመጽሐፍ ሰጥቶታል። ይህንንም በኦሪት ዘሌዋውያን ምዕራፍ ፳፫ ከቍጥር ፳፫ ና ፳፬ እናገኘዋለን። ስሙም በዓለ መጥቅዕ ይባል ነበር። «በሰባተኛው ወር በወሩ በመጀመሪያው ቀን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ በዓል ይሁንላችሁ፤» ብሎ እግዚአብሔር ለሙሴ በሰጠው ትእዛዝ ጸንቶ ሲከበር ቈይቷል። በጠቅላላ በዚህ በዓል መነሻነት በመስከረም የምናከብራቸውን በዓላት ሁሉ የሚጠቁመው ምንባብ የሚገኘው በዚሁ ክፍል ነው። በኦሪት ዘሌዋውያን ምዕራፍ ፳፫ ከቍጥር ፳፫ እስከ ፴፯ የተጻፈው እንዲህ ይነበባል። «እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት፥ በመለከት ድምፅ መታሰቢያ፥ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት፤ ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባንን አቅርቡ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፤ በዚህ በሰባተኛው ወር ዐሥረኛው ቀን የማስተስረያ ቀን ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ ሰውነታችሁንም አስጨንቋት፤ ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባንን አቅርቡ። በአምላካችሁም በእግዚአብሔር ፊት ማስተስረያ ይሆንላችሁ ዘንድ የማስተስረያ ቀን ነውና በዚያ ቀን ሥራ ሁሉ አትሥሩ። በዚያም ቀን የማይዋረድ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። በዚያም ቀን ሥራ የሚሠራውን ሰው ሁሉ ከሕዝቡ መካከል አጠፋዋለሁ። ሥራ ሁሉ አታድርጉበት፤ ከምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዐት ነው። የዕረፍት ሰንበት ይሁንላችሁ፤ ሰውነታችሁንም አዋርዱ፤ በወሩ በዘጠነኛው ቀን በማታ ጊዜ፥ ከማታ ጀምራችሁ እስከ ማታ ድረስ ሰንበታችሁን አድርጉ። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ በዚህ በሰባተኛው ወር ከ፲፭ኛው ቀን ጀምሮ ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር የዳስ በዓል ይሆናል። በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁን፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት። ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር የእሳት ቁርባንን አቅርቡ፤ በስምንተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ። ለእግዚአብሔርም የሚቃጠለውን ቍርባን አቅርቡ፤ ዋና ጉባኤ ነው፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት። የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የእኽሉንም ቍርባን፥ መሥዋዕቱንም፥ የመጠጡንም ቍርባን፥ በየቀኑ የእሳት ቁርባን ወደ እግዚአብሔር ታቀርቡባቸው ዘንድ የተቀደሱ ጉባኤዎች እንዲሆኑ የምታውጇቸው የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው።» (ዘሌ፤ ም ፳፫፥ ቍ ፳፫ - ፴፯።) እንግዲህ ከላይ በተጠቀሰው ጥቅስ ላይ ሦስት ቀኖች እናያለን። አንደኛ፤ ከወሩ በመጀመሪያ ቀን በመለከት ድምፅ የሚከበር ለእግዚአብሔር መታሰቢያ የሆነ ቀን፤ ሁለተኛ በሰባተኛው ወር በዐሥረኛው ቀን የሚከበር ሰው ሁሉ የሚዋረድበት፥ ትሕትና የሚያደርግበት፥ ንስሐ የሚገባበት የሥርየት ቀን፤ ሦስተኛው በሰባተኛው ወር ከዐሥራ ዐምስተኛው ቀን ጀምሮ ለስምንት ቀን የሚከበር ዳስ ተተክሎ፥ ድንኳን ተጥሎ የሚከበር በዓል፤ ሦስት በዓሎች ናቸው።እነዚህም በአንድ ወር ውሥጥ የሚከበሩ ናቸው። ይህ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው ትእዛዝ ትኩረት የሚያሻው ነው። ይህንን ትእዛዝ እግዚአብሔር ለሙሴ በመጽሐፍ ሰጠው። ከሙሴ ወዲህ በመጽሐፍ ተቀረጸ እንጂ ከዚያ በፊት የነበሩ አበው ግን በመጽሐፈ ኩፋሌና በመጽሐፈ ሔኖክ እንደሚገለጠው ቃል በቃል በተወረሰው መሠረት ብቻ ያከብሩት ነበረ። የመጀመሪያው ቀን፤ በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን በመለከት ድምፅ የሚከበር በዓል ይደረግ የሚለውን ቃል ስንመለከት በመለከት ድምፅ የሚሉ ቃላት እናገኛለን። መለከት የሚለው ቃል በአማርኛው ቋንቋ ይነጥላል፤ አንድ ክፍልን ብቻ ይመለከታል። በግእዙ ቋንቋ ግን መጥቅዕ ነው የሚለው። በዓለ መጥቅዕ ነው የሚባል። መጥቅዕ ማለት መለከትንም፥ ዕንቢልታንም፥ ነጋሪትንም የሚያጠቃልል ነው። በእንዲህ ዐይነት ሥርዐት የሚከበር የዘውድ በዓል ነው። ሌላም በድሮው ቋንቋ ተናገርኩት እንጂ የአንድ መሪ በዓል ነው ማለት ነው። የአንድ ብሔራዊ የአመራር በዓል ማለት ነው። ዘመን አየሠለጠነ፥ ዓለም እየሠለጠነ ከሄደ ወዲህ ግን በመድፍ ድምፅ ነው ብሥራቱ የሚከፈተው። ይሄ መሪዎች ራሳቸው የጦር ሰዎች ስለ ሆኑ ከእምነታቸው ይልቅ ጦርነትን ወይም ደግሞ ከእምነት እነሱ ኀይልን ስለሚመለከቱና በኀይል ስለሚደገፉ የመድፍ ድምፅ ጨመሩበት እንጂ በዓሉ የእምነት እንደ መሆኑ መጠን የነጋሪት፥ የመለከት፥ የዕንቢልታ ድምፅ እንጂ የመድፍ ድምፅ አይፈልግም ነበር። እና በመለከት፥ በዕንቢልታ፥ በነጋሪት ድምፅ የሚከበር፥ አንድ መሪ ሥልጣን የጨበጠበትን ቀን የሚያስታውስ በዓል ነው። እንግዲህ ይሄ በዓልም ለሰው ሳይሆን ወይም ለሥርየት ሳይሆን ወይም ለሌላ ምክንያት ሳይሆን ለእግዚአብሔር በመለከት ድምፅ የሚከበር በዓል ነው። ምን ማለቱ ነው? እግዚአብሔር ዓለምን ፈጥሮ፤ መላእክት ባደረው ጨለማ ተውጠው ሲጨነቁ በነበረ ጊዜ፤ «እቤ አነ እግዚአብሔር፤ ለይኩን ብርሃን፤» «እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ብርሃን ይሁን፤» ብሎ ድምፁን በማሰማት አምላክነቱን፥ ከሃሊነቱን፥ ጌትነቱን፥ ሥልጣኑን፤ በጠቅላላውም የማያልፍ፥ የማይሻር፥ የማይለወጥ መንግሥቱን ያወጀበት ቀን ስለ ሆነ ለእግዚአብሔር በመለከት ድምፅ የሚከበር በዓል ነው ይባላል። ሰባተኛ ወር የሚለው ግን ዕብራውያን እንዲወጡበት ለታዘዘው፥ እነሱ ሚያዝያ እኛ መጋቢት ለምንለው ወር ነው እንጂ ለጠቅላላው የዓለም ወሮች አይደለም። በእስራኤል ቍጥር ነው ሰባተኛ ያለው። በእኛ ግን የወሮች መጀመሪያ ነው። ለእስራኤላውያንም ቢሆን ያኛውን የወሮች መጀመሪያ ይሁናችሁ ሲል ይህንን ግን የመባቻ በዓል መጀመሪያ አድርጎታል። መባቻ ማለትም መግቢያ፥ ብተት፥ የወር መጀመሪያ ስለ ሆነ የወር መጀመሪያ የዓመት መጀመሪያ እንደ መሆኑ መጠን እንግዲህ የመባቻ በዓል እንዲከበር ያዘዘው እግዚአብሔር በዚሁ ቀን በመሆኑ የኢትዮጵያ በዓል አመሠራረት ጥንታዊና ቀዳማዊ፥ ዘለዓለማዊ፥ በጽኑ መሠረት ላይ የቈመ መሆኑን የሚያመለክተን ቀዋሚ ምልክት ነው። ከሕገ ልቡና እንደ ተቀበልነው በሕገ ኦሪትም አጽንተነዋል ማለት ነው።
ሌላው ከወሩ በዐሥረኛው ቀን የሚለው እነሱ በዚሁ ወር በዐሥረኛው ቀን የጾም ቀን አድርገው ያከብሩት ነበረ። የእስራኤል ዜጋ ወይም የእስራኤልን እምነት የተቀበለ ሁሉ ይህን ቀን የስንሐ ቀን መግቢያ አድርጎ ይጠቀምበት ነበረ። በዘመነ ወንጌል ግን በሱ ፈንታ በዓለ ስቅለት ተተክቶበታል። ይህም ሆኖ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዓሉ አለ። የቈየበትም በሁለት ጠባይ ነው። አንዱ እንደ ዛሬው መገናኛ ሙሉ በሙሉ የተካከለና የተሻሻለ ባለ መሆኑ ምክንያት ሕዝብ ሁሉ ክረምቱን ጨርሰው ወደ ከተማ የሚመጡበት፥ መሪያቸውን የሚያገኙበት፥ ስለ ሀገሪቱ በጠቅላላ በክረምት ተዘግቶ የነበረውን ሁሉ የሚወያዩበት ቀንና መሪውንም እንኳን አደረሰህ የሚሉበት ቀን ስለ ነበረ እስከ ዘመናችንም ተቀጸል ጽጌ እየተባለ ይጠራ ነበረ። በኋላ ግን የጌታችን ግማደ መስቀሉ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ በዐፄ ዳዊት ዘመን ስለ ገባበት በዓለ መስቀል ተተክቶበታል። መስከረም ፲ ቀን ማለት ነው።
ሦስተኛው ከ፲፭ ቀን ጀምሮ ለስምንት ቀን አክብሩ ተብሎ በታዘዘው በበዓለ መጸለት ፈንታ የመስቀል በዓል ተተክቶበት ከደመራው ጀምሮ እስከ መስከረም ፳፬ ቀን ስምንት ቀን ሙሉ በቤተ ክርስቲያን በዓለ መስቀል፥ ዘመነ መስቀል እየተባለ ነው የሚከበረው። እንዲያውም በአንዳንድ ጎሣዎች ይኸውም ጸድቆ ስምንት ቀን ሙሉ በዓል ሆኖ ሲሠራበት የነበረ እንዳለ ይታወቃል። እንግዲህ እነዚህ በዓላት ሦስቱም በፊት በዓለ መጥቅዕ፥ የሥርየት ቀን፥ የቂጣ በዓል ተብለው ይጠሩ የነበሩት በእኛ ቤተ ክርስቲያን ርእሰ ዐውደ ዓመት፥ የዐጤ መስቀል፥ መስቀል ተብለው የሚከበሩት በዓላት ናቸው። በዚህ ዐይነት እነዚህ መሠረታውያን የባህል በዓላት ከሕገ ልቡና ወደ ሕገ ኦሪት፥ ከሕገ ኦሪትም ወደ ሕገ ወንጌል ተላልፈው እዚህ የደረሱ ናቸው። እንግዲህ ርእሰ ዐውደ ዓመት የምንለው የዘመን መለወጫ ከምንለው ጋራ አንድ ነው።

ቅዱስ ዮሐንስ

የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ በዓል ሌላው ስሙ ቅዱስ ዮሐንስ ይባላል። ቅዱስ ዮሐንስ የሚባልበትም ሁለት ጠባይ አለው። አንዱ፤ መጥምቁ ዮሐንስ በሄሮድስ አንቲጳስ ጊዜ ከጳጉሜን ፩ ቀን ጀምሮ ታስሮ ሰንብቶ በመስከረም ፩ ቀን ዐሳብ ስለ ተቆረጠበትና በመስከረም ፪ ቀን እንዲሞት ውሳኔ ስለ ተሰጠበት አንገቱን በሰይፍ ተቆርጦ ስለ ሞተ ሊቃውንት ይህንን በዓል እሱ ራሱ ለኦሪትና ለወንጌል መገናኛ መምህር ስለ ነበረ ይህም በዓል ላለፈው ዘመን መሸኛ፥ ለሚመጣው ዘመን መቀበያ እንዲሆን ብለው በመስከረም ፩ ቀን እንዲከበር ስላደረጉ በሱ ስም ቅዱስ ዮሐንስ እየተባለ ይጠራል። በሁለተኛው ግን ከአራቱ ወንጌላውያን አንዱ ወንጌላዊ ዮሐንስ የተሰየመበት ስለ ሆነ በአቆጣጠርም ተራ ወደ ኋላ ተመልሶ ቢቈጠር ዓለም የተፈጠረበት ዘመን በዘመነ ዮሐንስ እንዳጋጣሚ ሆኖ ስለሚገኝ ቅዱስ ዮሐንስ ተብሎ ይጠራል።

ዓመተ ዓለምና ዓመተ ምሕረት

በዘመናት አቈጣጠር ውሥጥ ሌላው የምንመለከተው የዓመተ ዓለምና የዓመተ ምሕረት ቍጥር ነው። አውሮፓውያን ምንም እንኳ ቀኑን ዕለፍ ተቀደም ቢያደርጉትም ዓመተ ምሕረትን የሚቈጥሩ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነው። ከዚያ በፊት ያለውን ግን እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አራት ሺሕ ዓመት ቢሉም፥ ወይም በሳይንሱ ጠባይ ልዩ ልዩ መልክ ቢሰጡትም ተከታታይ ቍጥር አድርገው አይዘምቱበትም። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ወረሰችው ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረውን ፭ ሺ ፭፻ ዘመን፥ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ያለውን ፳፻፪ ዘመን በማለት አጠቃላ ዓለም ከተፈጠረ ፸፭፻፪ (ሰባት ሺሕ ዐምስት መቶ ሁለት) ዓመት ነው ትላለች። ለዓመተ ምሕረትም፥ ለዓመተ ዓለምም መነሻ የምታደርገው ያንኑ መስከረምን ነው። ለምን? የዘመናት ቍጥር ጥንት የዕለት፥ የሰዓት መሠረት ባደረገችው በዚያው ቀን የተነሣች፥ በዚያው ወር የጀመረች ስለ ሆነ ነው። ዓመተ ምሕረትንም በዚያው ማጽደቋ እመቤታችን ጌታን ፀንሳ ሳለች ወደ ኤልሳቤጥ ቤት በሄደች ጊዜ ኤልሳቤጥን ሰላምታ ስትላት ኤልሳቤጥም የእመቤታችንን ድምፅ ስትሰማ ዮሐንስ በማሕፀኗ ሳለ ለጌታ ሰግዶ ነበርና ይህንኑ መሠረት አድርጋ የዓመተ ምሕረት ለውጡ ከልደት ብቻ ሳይሆን ከፅንስ ጀምሮ ነው በማለት ያንኑ በማጽናት ተቀብላዋለች። የሰባት ዓመት ዕለፍ ተቀደም ቍጥሮች ልዩነት መነሻው አሁንም ቢሆን ከአውሮፓውያን የቊጥር ውሳኔ እንጂ ከኢትዮጵያውያን የቍጥር ውሳኔ አይደለም። ማለትም አውሮፓውያን የቤተ መቅደስን መፍረስ ሲናገሩ ከዕርገት በኋላ በ፵፬ ዓመት፥ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ፸፯ ዓመት ነው ብለዋል። ስለዚህ ውጥን ጨራሽ ቍጥር ተውጦ የሚቀር በመሆኑ ይህ ከእነሱ የፈለቀ እንጂ ከኢትዮጵያውያን አይደለም። ኢትዮጵያ ግን ከመሠረቱ ያንን ይዛ በመጣችው እስካሁንም ድረስ ደርሳበታለች። ይህም የተለወጠው ከውጪው ሥርዐት አያያዝ ነው ማለት ነው። በዚህ ዐይነት ይህንን የዘመን መለወጫ በዓል ስናከብር ቈይተናል።

ዓመታት በአራቱ ወንጌላውያን ስም ስለ መሰየማቸው

ቀደም ሲል ሰዎች በልዩ ልዩ ምልክት ይጠቀሙ ነበረ። በተለይም ሕዝቅኤልና ኢሳይያስ የኪሩቤልን ሥዕል፥ የኪሩቤልን መልክ በትንቢት ራእይ ዐይተው አንዱ አንበሳ፥ አንዱ ላም፥ አንዱ ሰው፥ አንዱ አሞራ ይመስላል ብለው በመናገራቸው ወደ እምነት የተቃረቡ ሰዎች ሁሉ በዚህ መሠረት አድርገው የኪሩቤል ጌታ፥ የእኛ ፈጣሪ፥ በሰማየ ሰማያት ላይ የሚኖር በኪሩቤል የሚመሰገን ነው ለማለት በዚህ ይጠቀሙ ነበረ።
በሐዲስ ኪዳን ደግሞ የቤተ ክርስቲያን መሠረት በአራቱ ማዕዘን በምሥራቅና በምዕራብ፥ በሰሜንና በደቡብ ያለ የሰው ዘር ሁሉ በሚጠቀምበት በወንጌል ትምህርት ላይ የተመሠረተ ስለ ሆነና ዓለም በአጠቃላይ የሚመራበት ቅዱስ ወንጌልም በአራቱ ወንጌላውያን የተጻፈ ስለ ሆነ ቤተ ክርስቲያን ወንጌሉን ስትቀበል ጸሓፊዎችንም ለክርስቲያኖች ቃል በቃል ለማስጠናት እንድትችል ዘመኑ በአራቱ ወንጌላውያን እንዲሰየም ሆኗል። ይህም ስለ ሆነ ማቴዎስ፥ ማርቆስ፥ ሉቃስ፥ ዮሐንስ በዘመናት ላይ መታሰቢያ አግኝተዋል።
ማቴዎስ በገጸ ብእሲ፥ ሰው በሚመስለው ኪሩብ ይመሰላል። ምክንያቱም የአብርሃም ልጅ፥ የዳዊት ልጅ ብሎ አምላክ ሰው መሆኑን የሚያስተምር፥ ትምህርቱንም በዚህ የጀመረ ስለ ሆነ ነው።
ማርቆስ በገጸ አንበሳ ይመሰላል። ምክንያቱም በግብጽ የላምና የበሬ ምስል ይመለክ ነበረና ያንን አጥፍቶ በዚያች አገር ወንጌል እንድትስፋፋ ስላደረገ ማርቆስ በገጸ አንበሳ፥ በአንበሳው ምስል በተመሰለው ኪሩብ ተመስሏል።
ሉቃስ ላም በሚመስለው ኪሩብ ተመስሏል። በተለይ በወንጌሉ በምዕራፍ ፲፭ ስለ በደለኛው ልጅ ሲጽፍ በደለኛው ልጅ ወደ አባቱ በመጣ ጊዜ አባቱ ያን በደለኛ ልጅ ሳይጸየፍ፤ «በሉ ሰውነቱን እጠቡት ልብሱን አልብሱት፥ ፍሪዳ አምጡና እረዱ፤ እንብላ፤ እንጠጣ። ይህ ልጄ ሞተ ስለው ድኗል፤ ጠፋ ስለው ተገኝቷል፤» ብሎ በምሳሌ ባስተማረው ትምህርት መሠረት ጠፍቶ የተገኘው ልጅ አዳም፥ የተቀበለው እግዚአብሔር አብ፥ መሥዋዕት ሆኖ አባቱንና ልጁን ያስታረቀው እግዚአብሔር ወልድ ነው ብሎ ትምህርት ስለ ሰጠ በዚህ አንጻር በላም መልክ በተመሰለው ኪሩብ ተተክቶ ሉቃስ ተጠርቶበታል።
በአሞራ መልክ በተመሰለው ኪሩብ የተጠራው ዮሐንስ ነው። በተለይም ንስር የሚባለው አሞራ ከወፎች ሁሉ በላይ ርቆና መጥቆ ይሄዳል ይባላል። እንዲህም ሆኖ ምንም ዐይነት ነገር ከመሬት ወድቆ ቢያይ አይሠወረውም፤ ወርዶ በፍጥነት ሊያነሣው ይችላል ይባላል። ዮሐንስም ሌሎች ወንጌላውያን ከደረሱበት፥ ከመረመሩት ምስጢር በላይ ረቆ፥ መጥቆ የምስጢረ ሥላሴን ነገር አምልቶ፥ አስፍቶ፥ አጕልቶ ስለ ጻፈና ስላስተማረ፥ ብዙ ራእይም ስለ ገለጠ በንስር በተመሰለው ኪሩብ ተመስሏል።
የእነዚህ ወንጌላውያን ትምህርት ክርስቲያንን ሁሉ፥ የሰውን ልጅ ሁሉ ለእግዚአብሔር ልጅነት የሚያበቃ፥ ሰውና እግዚአብሔርን የሚያዋሕድና የሚያዛምድ ሆኖ ስለ ተገኘ እንግዲህ ራሱ መድኃኒታችን፤ «ራሱን የካደ፥ ቤትን፥ ንብረትን፥ ወገንን ትቶ የተከተለኝ ሁሉ በዚህ ዓለም መቶ ዕጥፍ ዋጋ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘለዓለም ሕይወት ያገኛል፤» ሲል በሰጠው ቃል ኪዳን መሠረት እነዚህ ወንጌላውያንም ለክርስቶስና ለቤተ ክርስቲያን ባቀረቡት አገልግሎት መሠረት በዓለም የተሰጣቸው ልዩ መታሰቢያ ነው። ልዩ መታሰቢያ፥ ሽልማታቸው ነው ማለት ነው። በዚህ መሠረት መምህሮቻችንን ለማስታወስ እንድንጠቀምባቸው የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አዝዘዋል። ይህን ትእዛዝ ኢትዮጵያ አጽንታ ኖራለች። ያዘዙም ጠቅላላው የዓለም ሊቃውንት ናቸው።

መጥቅዕና አበቅቴ

መጥቅዕና አበቅቴ የሚባሉት በዘመናት ቍጥር ውሥጥ በልዩ ልዩ መልክ የመጡ ነገሮች ናቸው። ሁሉም ከዓመታት የሚተርፉ ቀኖች ናቸው። አበቅቴ የሚባለው በጨረቃ ከሚቈጠረው ቍጥር የሚተርፈው ነገር ነው። መጥቅዕ ማለት ግን የዓመቱን በዓላት ለማውጣት የምንጠቀምባቸው መሠረታዊ ቀንና ተጨማሪዎቹ ነገሮች ናቸው። በዚህ ትምህርት መግቢያ ላይ በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን በመለከት ድምፅ ለእግዚአብሔር በዓል አድርጉ የሚል ጥቅስ አይተን ነበረ። ይህንን በዓል እስራኤል በኦሪት ዘመን በሚያከብሩበት ጊዜ ከአሉበት ዓመት ጀምሮ እስከ ሰባት ዓመት በዓላቱ ተዘዋውረው የሚውሉበትን ቀን፥ ይልቁንም በሰባተኛው ዓመት ባሮች የነበሩ ነጻ የሚወጡበት፥ በወለድ አገድ፥ በዋስትና፥ በብድር ወለድ ምክንያት ተይዘው የነበሩ ርስቶች፥ ቤቶች ሁሉ በነጻ ወደ ባለቤቱ እንዲመለሱ እግዚአብሔር ያዘዘው ትእዛዝ የሚፈጸምበት፥ ዐዋጅ ሁሉ የሚታወጅበት ቀን ነበር። ዛሬ ደግሞ ይህ የመስከረም መጀመሪያ ቀን በዓመቱ ውሥጥ ያሉትን አጽዋማትን፥ በዓላትን ቤተ ክርስቲያን በዐዋጅ ለክርስቲያኖች የምታስታውቅበት፥ የምትገልጽበት ስለ ሆነ ያ ቀን መጥቅዕ ተብሎ ተጠርቷል። ስለ ሆነም መጥቅዕ ሲመታ፥ ደወል ሲደወል፥ ነጋሪት ሲመታ፥ ሲጎሸም፥ ዕንቢልታ ሲነፋ የመሰብሰብ ጥሪ ስለ ሆነ ሁሉ በየመልኩ የሰልፍ እንደ ሆነ የሰልፍ፥ የበዓል እንደ ሆነ የበዓል መልኩንና ሥርዐቱን ይዞ ተጠሪው ሊሰበሰብ እንደሚችል በዚህም ምክንያት አጽዋማት፥ በዓላት ተሰብስበው የሚገኙበት ስለ ሆነ መጥቅዕና አበቅቴ ተብለው ይጠራሉ ማለት ነው።

ስለ ቅዱስ ድሜጥሮስ ቀመር

ቀመር ማለት በግእዙ ቋንቋ ቍጥር ማለት ነው። ሒሳብ እንደ ማለት። የቍጥር ዐይነት ማለት ነው። የቍጥር ዐይነቱ የድሜጥሮስ ብቻ አይደለም። ዐሥራ ዘጠኝ ዐይነት የቀመር ዐይነቶች አሉ። ግማሾቹ ከነቢያት፥ ግማሾቹ ከሐዋርያት፥ ግማሾቹ ከሊቃውንት የተገኙ ናቸው። የቍጥር ደረጃም አላቸው። የሔኖክ፥ የሙሴ፥ የኢያሱ፥ የሕዝቅኤል፥ የዳንኤል፥ የዳዊት፥ የኤርምያስ፥ የድሜጥሮስ፥ የዮሐንስ አቡቀለምሲስ ተብለው በልዩ ልዩ መልክ ይጠራሉ። እነዚህ ቍጥሮች እንደ ዐይነታቸው ሥራ ተሠርቶባቸዋል።
ከመጀመሪያዎቹ ሰዎች ሔኖክ አጠቃሎ ከጥፋት ውሃ ጀምሮ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የትውልዱን በትውልድ፥ የዘመኑን በዘመን ተራ ቈጥሮ የሰውን ልጅ ተስፋ አብሥሮበታል። ከሔኖክ በኋላ የተነሡ ነቢያት ደግሞ ሰዎች በተስፋ የመድኅንን መምጣት ይጠባበቁ ነበርና ቍጥር እየሰጡ እንዲጠባበቁ አድርገዋቸዋል። ለምሳሌ በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ ፱ እንደ ተጻፈው ዐይነት የተወሰነ ዘመን እየሰጡ ሲጠባበቁ ቈይተዋል። በዮሐንስ ራእይም ሰባት ማኅተም፥ ሰባት መጥቅዕ፥ ሰባት ጽዋ ብሎ ክፍለ ዘመኑን በሰባት በሰባት መድቦ ይህ ዓለም እስከሚፈጸም ድረስ የሚደርሰውን በውሥጡ ያቀፈ ትምህርት ሰጥቶበታል።
የቅዱስ ድሜጥሮስ ግን ሐዋርያት በትምህርት ሰጥተውት ከሥራ ላይ ለማዋል በስብከት መፋጠን ምክንያት ሳይተካከል ቀርቶ አንድ መቶ ሰማንያ ዓመት ሙሉ ተዘበራርቆ የነበረውን ሥርዐት ያስተካከለበት ቍጥር ነው። ሐዋርያት ዲድስቅልያ በተባለው የሥርዐት መጽሐፋቸው የትንሣኤ ዐቢይ ጾምና ጾመ ሐዋርያት፥ ጾመ ነነዌም መነሻቸው ከሰኞ እንዳይወጣ፤ ደብረ ዘይት፥ ሆሣዕና፥ ትንሣኤ፥ ጰራቅሊጦስ እሑድን እንዳይለቁ፤ ስቅለት ዐርብን፥ ርክበ ካህናት ረቡዕን፥ ዕርገት ኀሙስን እንዳይለቁ ብለው ወስነዋል። ነገር ግን በዚያ ጊዜ በነበረው ስደትና በስብከት መፋጠን ምክንያት ሐዋርያትም በሰይፍ፥ በእሳት፥ በስለት እየተገደሉ፥ ተከታዮቻቸውም እየታደኑ ብዙ ችግር ስለ ነበረ ይህንን ወስኖ ለክርስቲያኖች የሚሰጣቸው አልነበረም። ስለ ሆነም የወሩን ብተት ተከትለው ልደትን እንዳከበሩ ወዲያው ጥምቀትን ያከብሩ ነበር። ጥምቀትን ካከበሩ በኋላ ደግሞ በማግሥቱ ዐቢይ ጾምን ይጾሙና በመኻል ደግሞ ዐርፈው እንደገና ከመጋቢት ፳፪ ቀን ጀምረው ሰሙነ ሕማማትን አክብረው በዓለ ስቅለትን፥ በዓለ ትንሣኤን ያከብሩ ነበረ። ኋላ ቅዱስ ድሜጥሮስ በእስክንድሪያ መንበር በተቀመጠ ጊዜ ስለዚህ ጉዳይ ብዙ ያስብና ይቈረቈር ስለ ነበረ የእግዚአብሔር መልአክ ይህንን በሱባኤ፥ በጸሎት፥ በቀኖና እንዲጠይቅ አዘዘውና በሱባኤ፥ በጸሎት፥ በቀኖና ሆኖ ከእግዚአብሔር ስለ ጠየቀ ተገልጾለት ይህንን ቀመር ሰጥቶአል። እና በእያንዳንዱ በዓል መካከል መዘዋወሪያ ቀኖች አድርጎ እነዚህ ቀኖች ለዚያ መውጪያ መውረጃ እንዲሆኑ፤ ጾመ ነነዌ ወደ ኋላ ቢመጣ ጥር ፲፮ን እንዳይነካ፥ ወደ ፊት ቢሄድ ደግሞ ከየካቲት ፲፱ እንዳያልፍ ፤ ዐቢይ ጾም ምንም ወደ ኋላ ቢመጣ የካቲት ፪ን እንዳይነካ፥ ከመጋቢት ፮ ደግሞ እንዳያልፍ እንደዚህ በሆነ ሥርዐት ስለ ወሰነው ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በዚሁ ዐይነት ይመላለሳል። ይሁን እንጂ ሌሎች የዓለም ክርስቲያኖች ይህን ሳይጠብቁ ሚያዝያ በባተ በመጀመሪያው ቀን የተገኘውን እሑድ ተከትለው በዓለ ትንሣኤን ሲያከብሩ ይኖራሉ። በኢትዮጵያ ግን ይሄ ተጠብቆ ያለ ነው፤ እስከ አሁን ድረስ አልተለወጠም።
እንግዲህ በዓላችን በመሠረቱ ከአበው፥ ከመጽሐፍ የወረስነው ነው እንጂ እንደ እንግዳ ድንገተኛ ደራሽ፥ እንደ ወንዝ ድንገተኛ ፈሳሽ አለመሆኑን በዚህ መረዳት አለብን። ይህም ከሆነ ያለንን ከትውልድ ወደ ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት ደግሞ ከእያንዳንዳችን የሚፈለግ ነው። እንግዲህ እያንዳንዳችን ከአባቶቻችን የተቀበልነውን ይህን አኩሪ እምነትና ሥርዐት ለልጆቻችን የማውረስ ግዴታ አለብን።
የሚያስፈልግ ሆኖ ከተገኘ ከአውሮፓውያንም ሆነ ከሌሎች ሥልጡኖች እንደ ተግባረ እድ ያለውን የሙያ ማዳበሪያ መቀበል ይገባናል። ግን ልንቀበለው የማይገባንን መቀበል፥ ልንተወው የማይገባንን መተው፥ ልናፈርሰው የማይገባንን ማፍረስ ይሄ ከቁም ነገር አይቈጠርም። «የዝንጀሮ ሰነፍ ያባቱን ዋሻ ይጠየፍ፤» ይባላል። እኛ መቼም ቆዳችንን፥ ቀለማችንን እስካለወጥን ድረስ ኢትዮጵያውያን ነን። ይህን ማመን አለብን። ኢትዮጵያዊነት ደግሞ እኛን የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር አይደለም። ስለ ኢትዮጵያ ቀዋሚውን ምስክር፥ ዓለም ያመነም ያላመነም ተስማሞቶ የሚቀበለውን መጽሐፍ ቅዱስን ብንመረምር በቍጥር በርከት ባሉ ቦታዎች ላይ ተጠቅሳ፥ ያውም በቅድስና መልክ ተቈጥራ የምትገኝ ኢትዮጵያ ናት። በተለይም፤ «ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፤» የሚለው ቃል ብዙ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋራ የተገናኘንባቸውን ብዙ ነጥቦች፥ ብዙ ታሪኮች፥ ብዙ ሥራዎች ያቀፈ ስለ ሆነ ይህ ብቻ ራሱ ሊያጓጓን ይገባዋልና እንግዲህ ከባህል የወረስናቸውን ማንኛቸውንም ሥርዐቶች ጠንቅቀን ለልጆቻችን ማውረስ ይጠበቅብናልና እግዚአብሔር ይህን ለመፈጸም ይርዳን። አሜን።

ምንጭ፦ http://www.aleqayalewtamiru.org/new_year_2003.html

Tuesday, September 3, 2013

የሃማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ አስፈላጊ ነበር???

ይህ ጉባኤ በዋናነት የተቋቋመው ለአገር ሰላምና በእምነት ተቋማቸው ለሚያስተዳድሩት ህብረተሰብ(የእምነት ተቋም) ደህንነት እንጂ ለመንግሥት ወይም ለአንድ የፖለቲካ ድርጅት አይደለም። በተለይ ደግሞ ይህ ጉባኤ በእምነት ተቋማት መካከል አለመግባባት እንዳይፈጠር እና ወደ አልተፈለገ ግጭት/እሰጣ ገባ/ ውስጥ እንዳይገባ ሁሉም የየራሱን የሃይማኖት አስተምሮ በመቻቻል እንዲሁም ሰላምና ፍቅር በተሞላበት መንገድ እንዲያካሂዱ ለማድረግ የተቋቋመ ይመስለኛል።
በትናትናው እሁድ ማለትም በ26/12/2005 ዓም የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ግን ከዓላማው በእጅጉ የራቀ እና ሁኔታዎችን ያላገናዘበ መስሎ ይታያል። እርግጥ ነው ይህ ጉባኤ አገራዊ ሰላም ሊያደፈርሱ ይችላሉ ብሎ ያመነባቸውን ጉዳዮች ለህዝብ ይፋ ማድረጉ የሚበረታታና ለወደፊትም ሊቀጠልበት የሚገባ ተግባር ነው። ነገር ግን ይፋ ከማድረጉ በፊት የሃይማኖት ኮሚቴ እንደመሆኑ መጠን በርካታ ቅድመ ስራዎች ሊኖሩት ይገባል። የህብረተሰቡን ነባራዊ ሁኔታ፣ የእምነት ተቋማት አመለካከትና የፖለቲካ አቅጣጫን በሚገባ ማጤን ከዚህ ትልቅ ከሚቴ ቀርቶ ከአንድ ግለሰብ ሊሰወር የማይገባ ነገር ነው።
የህብረተሰቡን ነባራዊ ሁኔታ በትክክል መገንዘብ ያስፈልጋል ሲባል የተፈጠረውን ችግር ህብረተሰቡ በምን መልኩ ነው የተረዳዉ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ሊያስወጣ በሚችል መልኩ ነው? ውይስ የግንዛቤ እጥረት አለበት? ወይስ በሌላ አቅጣጫ ነው የተረዳው? የሰላማዊ ሰልፍ አስፈላጊነት? እና መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት ህብረተሰቡ ያላበትን የግንዛቤ ደረጃ መለካት፣ ማጤንና መመልከት ይገባል። እንዲሁም ህብረተሰቡን ግንዛቤ ከማስጨበጥ አንጻርም ይህ ኮሚቴ ትልቅ ኃላፊነት አለበት። ሰላማዊ ሰልፍ ወይም ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት የችግሩን አሳሳቢነት ማለትም በአገርና በሃይማኖት ተቋማት ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ችግር በሚገባ በተለያየ መልኩ ማስረዳትና ማሳወቅ፣ መግለጽና ማስተላለፍ ይኖርበታል። ምናልባት ኮሚቴው ይህን አድርጊያለሁ ቢልም በቂ ነው ብዬ አላምንም። በዚህ መልኩ ህብረተሰቡን ማንቃትና ወደ አንድ የግንዛቤ መንፈስ እንዲመጣ ሳያደርጉ ውሳኔ መወሰን ይባስ ብሎ አገራዊ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራት ከጥቅሙ ጉዳቱ እጅግ የከፋ ይሆናል።
የእምነት ተቋማት አመለካከት ምን ይመስላል የሚለውንም በሚገባ መረዳት የኮሚቴው ተቀዳሚ ተግባር ነው። የዚህን ኮሚቴ የእያንዳንዱ አባል የወከለው የእምነት ተቋሙ ነው። ስለዚህ ከእምነት ተቋሙ ጋር መነጋገር፣ መወያየት፣ የችግሩን አመጣጥና ሁኔታ፣ በተቋሙ ላይ ሊያስከትለው የሚችለውን ችግር በሚገባ ማየትና ተደጋጋሚ ውይይቶች ያስፈልጋሉ። ችግሩ ተፈጠረ ከተባለበት ተቋም ወይም ቦታ ድረስ በመሄድ ችግሩን በውውይት ለመፍታት መሞከር ይኖርበታል። በእኔ አመለካከት የሃይማኖት ተቋማት ከመንግሥትም በላይ ለሰላምና ለህብረተሰቡ ደህንነት የሚቆሙ ናቸው። ስለዚህ ችግሩን በውይይት፣ በትምህርትና በተግሳጽ ለመፍታት መጣር ያስፈልጋል። ኮሚቴው እንደኮሚቴ ከመወሰኑ በፊት ከወከለው የእምነት ተቋም ጋር ግልጽ ውይይት አድርጎ ችግሩን ሊፈታ በሚችል መልኩ አንድ አቋም መያዝ ይኖርበታል። በእውነት የትናቱ ሰላማዊ ሰልፍ ግን የተፈጠረውን ችግር ሊፈታ ይችል ነበር??? መልሱን ለእናንተ ትቸዋለሁ።
ይህ ኮሚቴ ከፖለቲካ ነጻ እንደመሆኑ መጠን / በወረቀት ደረጃ ማለቴ ነው/ አንድ ውሳኔ በሚወስንበት ጊዜ የፖለቲካ አቅጣጫውን መመልከት ያስፈልገዋል። ምንም እንኳ ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ ናቸው ቢባልም መንግሥት ከሃይማኖት ነጻ ሁኖ ስለማያውቅ አቅጣጫውን እና ሂደቱን ከውሳኔ በፊት መረጃዎችን መሰብሰብና መፈተሽ ያስፈልጋል። የህብረተሰቡ የፖለቲካ አመለካከት ምን ይመስላል? የገዢው ፓርቲ ያለበት ደረጃ? የተቀዋሚ የፖለቲካ እንቅስቃሴና ሌሎችንም ተያያዝ ነገሮችን መፈተሽ ይኖርበታል። እነዚህ ሁኔታወችን ሳይገነዘብ ወደ ውሳኔ ከገባ ግን በአንድ ተጽዕኖ ውስጥ ሊገባ ይችላል፤ ይኸው ገባም። የሃይማኖት ተቋም የሰላም ኮሚቴ ተብሎ በአንድ ተጽዕኖ ውስጥ ዥው ብሎ መግባት ግን ችግሩ እንዲበባስ ያደርገዋል፤ በተጫማሪም ሌላ ችግር ይፈጥራል እንጂ መፍትሔ ሊያመጣ አይችልም።
ጉባኤው መመልከት ያልቻላቸው ግልጽ ነገሮች፦
1. ችግሩን፦ ጉባኤው በአዲስ አበባ በ10 ክፍለ ከተሞችና በ116 ወረዳዎች በተካሄደው ህዝባዊ የሰላም ኮንፈረንስ እንዲሁም ከፍትህ ቢሮ ጋር በመተባበር ከነሐሴ 15-16 በተካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ ላይ የሃይማኖት መሪዎችና ተከታዮቻቸው «ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማችን እየታየ ያለው የአክራሪነትና የፅንፈኝነት እንቅስቃሴ የሀገራችንን ሰላምና ልማት የሚያውክ፣ በሰላም አብሮ የመኖር እሴቶቻችንን የሚያናጋና የሃይማኖት መልክ የሌለው የጥፋት እንቅስቃሴ ከመሆኑም በላይ በህገ መንግሥታችን የተደነገገውን የሃይማኖት እኩልነትና የእምነት ነፃነት የሚፃረር ስለሆነ በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሟችንን ማሰማት እንፈልጋለን» ተብሎ በአቋም መግለጫ የተላለፈውን መሰረት በማድረግ ሰልፉ እንደተዘጋጀ በጋዜጣዊ መግለጫ ስለሰልፉ አስፈላጊነትም በማብራራት ሰላማዊ ሰልፉ በመጪው እሁድ ከንጋቱ 12 ሰዓት በመስቀል አደባባይ የሚካሄድ ሲሆን፤ በከተማው ውስጥ ያሉ የሃይማኖት ተቋማት በሙሉ በጋራ በመሆን ለሰላም፣ ለልማት፣ ለመቻቻልና ለአብሮነት ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚገልጹበት የሰላም መድረክ ነው//፤ በማለት የጉባኤው ኮሚቴ በገለጸልን መልኩ ችግሩን ሙሉ በሙሉ እንውሰደው ብንል እንኳ የሃይማኖት አክራሪነት ከመቼ ወዲህ ነው በሰላማዊ ሰልፍ ሊገታ የሚችለው። ኃያላን አገራት እንኳ በተደራጀና ዘመናዊ ስልትን በመጠቀም አክራሪነትን ማቆም ሳይችሉ እኛ እንዴት ነው በሰላማዊ ሰልፍ ልናቆመው የምንችለው። እንደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሰላማዊ ሰልፍ ለሰላማዊ ትግልም ልንጠቀምበት አልታደልንም። ስለዚህ ጉባኤው የሃይማኖት አክራሪነትን በሰላማዊ ሰልፍ ለመግታት መሞከሩ የችግሩን ምንነት አለመረዳት ነው። ችግሩን በሚገባ ሳይረዱ ደግሞ ውሳኔ መወሰኑ ከመፍትሔው ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ብዙ መናገር የሚያስፈልግ አይመስለኝም። ችግሩም መቶ ፐርሰንት/100%/ አክራሪነት ነው ብሎ ለመፈረጅ ማስረጃ የሚያጥር ይመስለኛል። በግሌ አክራሪነት የለም፣ አይኖርም የሚል አመለካከትና ግንዛቤ የለኝም። ቢሆንም ግን በሰላማዊ ሰልፍ ከችግሩ እንወጣለን የሚል እምነት ፍጽሞ አይኖረኝም።
2. ስዓት፦ ሰላማዊ ሰልፉ እንዲጀመር የተደረገበትን ስዓት እንኳን ስንመለከተው ጉባኤው ከወከለዉ የእምነት ተቋም ጋር ጥብቅ ውይይት አለማድረጉን በቀላሉ መመልከት እንችላለን። በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ያን እና ሌሎችም ማለት ይቻላል በየሳምንቱ እሁድ ጥዋት የአምልኮት ስርዓታቸውን የሚፈጽሙበት ስዓት ነው። ስለዚህ ስዓቱን እንኳ ያገናዘበ ሰላማዊ ሰልፍ አለመጥራት የግደለሽነት ያስመስላል። ወይም በሌላ ተጽዕኖ ውስጥ መሆኑን በግልጽ ለመረዳት አያዳግትም። በተጽዕኖዎችና በግደለሽነት የሚደረጉ ማንኛውም ነገሮች ደግሞ ችግርፈጣሪ እንጂ ችግር ፈቺ መቸውንም አይሆኑም።
3. ቀን፦ በሰላማዊ ሰልፉ አስፈላጊነት ጉባኤው ካመነ በቀላሉ ሊመለከተው የሚገባው ነገር የሚደረግበትን ቀን ነው። በዚያ ቀን ምን ተያያዥ ነገር አለ? ቀኑ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል፣ ለእምነት ተቋማትና ለፖለቲካ ፓርቲዎች ምቹ ነው? የሚለውን ጥያቄ ጉባኤው ከመወሰኑ በፊት መመልከት ይኖርበት ነበር። ጉባኤው ግን በተቃራኒው የተጓዘ ይመስላል። ይህ ቀን ማለትም 26/12/2005 ዓ.ም ግን ሰማያዊ ፓርቲ የአገር ሰላም እንዲሰፍን፣ ሰባአዊ መብት እንዲከበር፣ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ከአላግባብ የታሰሩ ዜጎች እንዲፈቱ፣ እኩልነት እንዲረጋገጥ፣ ሙስናና አገርን ወደ ኋላ ሊጎትቱ የሚችሉ ችግሮችን ለመቅረፍና ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር ከመንግሥት እንኳ ሳይቀር ፍቃድ ጠይቆ ለ2ተኛ ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ የጠራበት ቀን ነበር። ጉባኤው ግን ይህን ሳያገናዝብ በመጥራቱ ለፓርቲው አባላት እስራት፣ እንግልትና ድብደባ ምክንያት ሁኗል። ፓርቲው የጠራው ሰላማዊ ሰልፍም በእስራትና በድብደባ እንዲቀየር አድርጎታል። ሙሉ በሙሉ ጥፋቱ የመንግሥት ቢሆንም የጉባኤው አባላት ለዚህ ተግባር ተባባሪ በመሆናቸው ተጥያቂ አድርጓቸዋል። ሌሎችን እናተ ጨምሩበት.......
በአጠቃላይ የጉባኤው ሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ አስፈላጊ ነበር የሚለውን ሁላችንም በራሳችን አስተያየት እንስጥበት እና እንማርበት። አስፈላጊ አልነበረም ለምንል ሰዎች ወደፊት እንዲህ አይነት ተያያዥ ክስተቶች እንዳይፈጠሩ ምን እናድርግ ለማለት ሃሳብ መለዋወጡ መልካም ስለሚሆን ለመነሻ ያክል የግሌን ሃሳብ አቅርቢያለሁ።