Friday, May 3, 2013

ዕለተ ዓርብ/ስቅለት


ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ «አውቀውስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት» /1ቆሮ.1-18/፡፡ እንዳለ ይህ ዕለት የአይሁድ ካህናት ያለበደል ያለጥፋት ንጹሕና ጻድቅ የሆነውን ጌታ የሰቀሉበት ዕለት ነው፡፡ ዕለቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ሁሉ መድኃኒት ለአዳምና ለልጆቹ ሲል በመልእልተ መስቀል በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ መዋሉን የምናስብበት ታላቅ ቀን ነው፡፡ /ማቴ.27-35-75/፡፡ በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ፡፡ እነርሱ ግን እኛስ ምን አግዶን? አንተው ተጠንቀቅ አሉ፡፡ ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሔደና ታንቆ ሞተ፡፡ የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም አሉ፡፡ ተማክረውም የሸክላ ሠሪ መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት፡፡ ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተባለ፡፡ /ማቴ.27-3-9/
የሰው ልጆች በዘር ኃጢአት /ቁራኝነት/ ይኖሩበት የነበረው የጨለማ ሕይወት ያከተመበት ፍጹም ድኅነት ያገኙባት ታላቅ ዕለት ናት፡፡ ክርስቲያኖች ሁልጊዜም ዕለተ ዓርብ ሲመጣ ሕማሙን ስቅለቱን ሞቱን የሚያስቡበት ጊዜ ነው፡፡ በሮማውያን ሕግና ሥርዓት መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የሕይወት መቅጫ አርማ ሆኖ ሳለ ለእኛ የዲያብሎስ ድል መንሻ ስላደረገው በስቅለቱና በሞቱም ሕይወትን ስለአገኘን በዚህም ምክንያት መልካሙ ዓርብ በመባል እንደሚታወቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያትታሉ፡፡
በመስቀል ላይ ሳለ 7 ነገሮችን ተናገረ/7ቱ "አጽርሐ መስቀል" በመባል ይታወቃሉ። እነሱም፦
" አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ" ማቴ 17፦46
" አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው" ሉቃ 23፦34
" ዛሬ በገነት ከኔ ጋር እንድትኖር በእውነት እነግርሀለሁ" ሉቃ 23፦4
" አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ" ሉቃ 23፦ 46
" እነሆ ልጅሽ እነኋት እናትህ" ዮሐ 19፦26
" ተጠማሁ" ዮሐ 19፦28
" ሁሉ ተፈጸመ " ዮሐ 19፦ 30
ጌታ ሁሉ ተፈጸመ ብሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ስጋው በራሱፈቃድ ከለየ በኋላ አምላክነቱን ለመግለፅ የታዩ ተአምራት የሚከተሉት ናቸው፤

በሰማይ፤ /ማቴ 24፦29 እና 27፦45/
1. ፀሐይ ጨለመች
2. ጨረቃ ደም ሆነች
3. ከዋክብት ረገፉ

በምድር፤/ማቴ 27፦51_53/
1. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይእስከ ታች ተቀደደ
2. ምድር ተናወጠች
3. መቃብሮች ተከፈቱ
4. ሙታን ተነሱ


ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ክንዋኔዎች በሰሙነ ሕማማት
በዐቢይ ጾም ከሠርክ ሆሣዕና ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ዕለታት የሚገኙበት ሳምንታት ሰሙነ ሕማማት ይባላሉ፡፡ ዕለታቱም የዓመተ ፍዳ፣ የዓመተ ኩነኔ መታሰቢያ ናቸው፡፡ በእነዚህ ዕለታት ውስጥ የተለያዩ ትውፊታዊ እና ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች አሉ፡፡ ከነዚህ ክንዋኔዎች ውስጥ አለ መሳሳም፣ አክፍሎት፣ ቄጤማ ማሰር፣ ጥብጣብ፣ ጉልባን እና ሕጽበተ እግር ይገኙበታል፡፡ ስለእነዚህ ክንዋኔዎች በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስላለው ትውፊታዊ አፈጻጸም መዛግብት አገላብጠን እና በኢትዮጵያ ኣርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ አባል የሆኑትን ሊቀ ካህሃት ክንፈ ገብርኤል አልታዬን አነጋግረን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
አለመሳሳም
በሰሙነ ሕማማት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች መስቀል እንደማይሳለሙት ሁሉ መጨባበጥ፣ መሳሳምና የትከሻ ሰላምታ መለዋወጠን አይፈጽሙም፡፡ ሰላምታ የማንለዋወጥበት ምክንያት፣ አይሁድ ጌታን ለመስቀል ሰኞ እና ማክሰኞ መከሩ አልሠመረላቸውም፡፡ ምክራቸው የተፈጸመው ረቡዕ ነው፡፡
ስለዚህ አይሁድ አያንሾካሾኩ “እንስቀለው… አንግደለው” ብለው ይማከሩ ነበር፡፡ ያነን ለማስታወስ ሰላምታ አንለዋወጥም፡፡ መስቀልም አንሳለምም፡፡ ሳምንቱ የክፋት ምክር የተመከረበት እንጂ የፍቅርና የደስታ ሰላምታ የታየበት ባለመሆኑ ይህንን በማሰብ ሰላምታ አንለዋወጥም፡፡
ይሁዳ ጌታን በጠላቶቹ ለማስያዝ “እኔ የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት” ብሎ በሰላምታው ምልክት ሰጣቸው ይህ ሰላምታ አምሐ ቅድሳት አይደለም፤ ተንኮል የተሞላበት እንጂ፡፡ የዲያቢሎስም ሰላምታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሔዋንን “ሰላም ለኪ” ብሎ ነው ያታለላት፣ የዲያቢሎስ እና የይሁዳ ሰላምታ ሰይጣናዊ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ወቅትና ሁኔታ ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ሰላምታ ልውውጥ የለም፡፡ ዛሬ እየተስተዋለ ያለው ይኸው ሰላምታ ያለመለዋወጥ ሁኔታ ሥርወ መሠረቱ ይህ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ እዚህ ትውልድ ላይ ደርሷል ይቀጥላልም፡፡

ሕጽበተ እግር
ጌታ በፍጹም ትሕትና የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበት፣ ከሐዋርያት ጋር ግብር የገባበትና የክርስትና ሕይወት ማሕተም የሆነውን ምሥጢረ ቁርባን ያከናወነበት ዕለት ነው ጸሎተ ሐሙስ፡፡
ሕጽበተ እግር ጌታችን በዚህ ዕለት “አናንተ ለወንድማችሁ አንዲህ አድርጉ” ለማለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ምክንያት የተሰጠ ምሳሌ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው “አኔ ለአናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና፤ እውነት እውነት እላችኋለሁ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም፣ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም፤ ይህን ብታውቁ ብታደርጉትም ብፁዓን ናቸሁ” /ዮሐ.13÷16-17/ በማለት ትሕትናውን አሳይቷል፡፡
ጌታ በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር ሲያጥብ “እኔ መምህራችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኳችሁ አርአያዬን ሰጥቻችኋለሁ፤ እናንተም የወንድማችሁን እግር ታጥቡ ዘንድ ይገባል፡፡ ነገር ግን ከእናንተ አንዱ ለሞት አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም “ማን ይሆን?” አሉ፡፡ ጌታም “ኅብስት ቆርሼ፣ ከወጡ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው” አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ደነገጡ፡፡ ይሁዳን ማመልከቱ ደነገጡ፡፡ ይሁደን ማመልከቱ ነበር፤ ለጊዜው አልገባቸውም፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን የሐዋርያቱን እግር በማጠብ ትሕትናን ካስተማራቸው በኋላ፤ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሰጣቸው፤ የኦሪትን መሥዋዕት የሻረው እና መሥዋዕተ ሐዲስን የሠራው በዚሁ ዕለት ነው፡፡
በዚህ ሃይማኖታዊ መነሻነትም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚከናወኑ ድርጊቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- በወሎና በጎንደር ከጉልባን በተጨማሪ በተለይ በጸሎተ ሐሙስ ዕለት ብቻ የሚጋገር የተለየ ዳቦ አለ፡፡ ይህ ልዩ ዳቦ በወሎ “ትኩሴ” በጎንደር ደግሞ “ሙጌራ” ይባላል፡፡ ይህ ዳቦ ጌታ ለሐዋርያት የሰጣቸው ኅብስት አምሳያ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ከዚህ ቀን ውጪ በሌላ ጊዜ አይጋገርም፡፡ በመሆኑም ሰው ሁሉ ዳቦውን ለመብላት የሚጠባበቀው በታላቅ ጉጉት ነው፡፡ አልፎ አልፎ ግን ሃይማኖታዊ ሥርዓት በሚከበርባቸው እንደ ማኅበርና ሰንበቴ በመሳሰሉት መንፈሳዊና ማኅበራዊ ትውፊቶች የሚቀርብበት ጊዜ አለ፡፡
በትግራይ በዕለተ ስቅለት ከተለመደው የጾምና የስግደት ሥርዓት በተጨማሪ የሚከናወኑ ድርጊቶች አሉ፡፡ በዕለቱ ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት መታሰቢያ ሲባል ወንዶች ልጆች በሙሉ ፀጉራቸውን እንዲላጩ ይደረጋል፡፡ ያን ቀን ያልተላጨ ልጅ “ኃጢአት ይሆንበታል” ስለሚባል ሳይላጭ የሚውል ልጅ የለም። ልጃገረዶች በበኩላቸው በዛፍ ላይ ገመድ በማሰር ዥዋዥዌ ይጫወታሉ፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት የጌታን እንግልትና መስቀል ለማዘከር ነው ይባላል፡፡
እነሆ ይህንን ዕለት በማስታወስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሐዶ ቤተ ክርስቲያን ከሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ እስከ ቀሳውስት ያሉት አባቶች በያሉበት አጥቢያ /ደብር/ በመገኘት በመዓርግ የሚያንሷቸውን የካህናት፣ ዲያቆናት እና የምእመናንን እግር ያጥባሉ፤ የሚያጥቡትም የወይራ እና የወይን ቅጠል በመዘፍዘፍ ነው፡፡

አክፍሎት
በሰሙነ ሕማማት ዕለተ ዓርብ ከስግደት በኋላ ምእመናን በየቤታቸው ጥቂት ነገር ለቁመተ ሥጋ ቀምሰው እስከ እሑድ /የትንሣኤ ሰዓት/ ይሰነብታሉ፡፡ ይህ አክፍሎት ይባላል፡፡ ብዙው ምዕመን ከዓርብ ጀምሮ የሚያከፍል ሲሆን አንዳንዶች ግን ከሐሙስ ጀምረው ያከፍላሉ፡፡ ይህም እመቤታችን፣ ያዕቆብ እና ዮሐንስ የጌታን ትንሣኤ ሳናይ እህል ውኃ አንቀምስም ብለው እስከ ትንሣኤ መቆየታቸውን ተከትሎ የመጣ ትውፊት ነው፡፡
ይህንን ትውፊት አስመልክቶ ሄሬኔዎስ፣ አውሳብዮስ የተባሉ ጸሐፍት፤ ሐዋርያት በሰሙነ ሕማማት ከደረቅ ዳቦ አና ከትንሽ ውኃ በቀር እንደማይመገቡ እና ከሐሙስ ጀምረው እንደሚያከፍሉ ጽፈዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሐዋርያት ሌሎቹንም እንዲያከፍሉ እንዳሳሰቡና ከሐሙስ ጀምሮ ያልተቻለው ቢያንስ ከዓርብ ጀምሮ እንዲያከፍል ማዘዛቸውን ጽፈዋል፡፡ የእኛ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትም ይኸው ነው፡፡ ቅዳሜ ይበላል ማለት ግን ቅዳሴው ሌሊት ስለሆነ በልቶ ማስቀደስ ነውና በልቶ እንደመቁረብ ይቆጠራል፡፡

ጉልባን እና ቄጤማ
ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚባላ ንፍሮ ነው፡፡ የጉልባን ትውፊት እስራኤላውያን ከግብፅ ተሰደው በሚወጡበት ጊዜ በችኮላ ስለነበር፤ አቡክተው ጋግረው መብላት ያለመቻላቸውን ሁኔታ ያመለክታል፡፡ ያን ጊዜ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መብላት፤ ንፍሮም ቀቅለው ስንቅ መያዝ ተግባራቸው ነበር፡፡ ይህን ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ቂጣና ጉልባን በማዘጋጀት በዓሉ ይታሰባል፡፡
በጸሎተ ሐሙስ ይህንን መሠረት በማድረግ የሚዘጋጀው ጉልባን አንዲህም ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ጨው ውኃ የሚያስጠማ በመሆኑ የጌታን መጠማት ያስታውሳል፡፡ ይህ ትውፊታዊ ሥርዓት ከእስራኤላውያን የመጣ ሲሆን በኢትዮጵያም አብዛኛዎቹ የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ሥርዓቱ ዛሬም ይከበራል፡፡
ጥብጣብ
በሰሙነ ሕማማት ዕለተ ዓርብ የስቅለቱ መታሰቢያ ነው፡፡ ምእመናኑ በሰሙነ ሕማማት የሠሩትን ይናዘዛሉ፡፡ ካህናቱም በወይራ ቅጠል ትከሻቸወን እየጠበጠቡ ቀን ከሰገዱት ስግደት በተጨማሪ ሌላ ስግደት ያዟቸዋል፡፡ ጥብጠባው የተግሳፅ ምሳሌ ነው፡፡ ጥብጣብ የሚደረግለት ሰው በሕማማቱ ወቅት የፈጸመው በደል ወይንም ኃጢአት ካለ ይህንኑ በመናገር የስግደቱ ቁጥር ከፍ እንዲል ይደረጋል፡፡
ይህ በስቅለት ቀን የሚፈጸም ሥነ ሥርዓት ሲሆን፤ ጠብጣቤ ማለት ቸብ ቸብ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዕለተ ስቅለት ሲሰግድ ሲጸልይ፣ ሲያነብ ከዋለ በኋላ ሰርሆተ ሕዝብ /የሕዝብ መሰነባበቻ/ ከመሆኑ በፊት፤ በወይራ ቅጠል እያንዳንዱን ምእመን ጀርባ ቸብ ቸብ መደረጉ፣ የጌታን ግርፋት ያስታውሳል፡፡

ቀጤማ
በቀዳም ስዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለ ዓዋዲ/ እየመቱ “ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሃደ” የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር፤ ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደሰጠን እና ትንሣኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር፤ ቀጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመናኑም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ፡፡ ቀጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ የደፉበትን ድርጊት የሚያስታውስ ነው፡፡
በዚህ ዕለት ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲያቆናት ቀጤማ ተሸክመው ቃጭል ሲያቃጭሉ መታየታቸው ዕለተ ትንሣኤውን ለሚናፍቅ ምእመን ትልቅ ብስራት ነው፡፡

                                    ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ እግዚአብሔር በሰላም!
(ምንጭ፦ ስምዐ ጽድቅ ልዩ እትም ዘሰሙነ ሕማማት መጋቢት 2002/ከማኅበረ ቅዱሳን ድኅረ ገጽ )

No comments:

Post a Comment